
ከሰውዬው ጀርባ የቆመችው ታላቋ ሴት – ካትሪን ቫን ቦራ
የማርቲን ሉተር ባለቤት ስለነበረችው ካትሪን ቫን ቦራ የሚያወሳው ይህ ጽሑፍ፣ የሉተር የተሓድሶ እንቅስቃሴ ዳር እንዲደርስ ስላበረከተችው ጉልሕ አስተዋጽኦ ታምራት ያዕቆብ እንዲህ ያስነብበናል።
[the_ad_group id=”107″]
እንደ ሁልጊዜውም በዚህም ዘመን ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩ ወይም እግዚአብሔርን “ወክለው” የሚያወሩ በርካቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በእውነት እግዚአብሔርን የሚያውቁ ስለ መሆን አለመሆናቸው ንግግራቸው እና ተግባራቸው የሚያስተላልፍልን መልእክት ቢኖርም፣ ጥቂት የማይባሉቱ ስለ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ሁልጊዜ የሚያውቁ አድርገው ራሳቸውን ለገበያ ያቀርባሉ። ዐውቀውት በመጨረሳቸውም ይመስላል ስለ እርሱ የማወቅ ጕጕት አይታይባቸውም። እግዚአብሔርን ለሚመለከት የትኛውም ጥያቄ መልስ እንዳላቸው አድርገውም ይተውናሉ፤ ይህንን የሚያምኑላቸው ሰዎችም አሉ። የእግዚአብሔርን እርምጃ ቀድመው የሚገነዘቡ፣ ሐሳቡን ከሩቅ የሚያውቁ፣ ማንን መሾም እና ማንን መሻር እንዳለበት የማማከር ቀረቤታ ያላቸው እና ሰዎችን ለቅባት እስከ ማሳጨት ድረስ የሥላሴ ምክር ቤት ቤተኛ የሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚሥሉ ደ“ፋሮችንም ታዘበናል። እንዲህ ዐይነቶቹ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን ዕውቀት ለማሳየት የሚያነሧቸው ጥያቄዎች እና የሚሰጧቸው መልሶች ግን ያስገርማሉ።
ገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ፣ “በቀላሉ መልስ የሚገኝለትን ጥያቄ የሚጠይቅ ወይ እብድ ነው፤ አለዚያም ሰባኪ” ያለው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።1 መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን ዐይነቱን የሰባኪዎች አካሄድ አይከተልም፤ በእግዚአብሔር ላይም ሆነ ስለ እግዚአብሔር ብርቱ ጥያቄዎችን ይሰነዝራል። ከዚህም የተነሣ፣ ከትላንቶቹ ቮልቴር እና በርትራንድ ሩሴል እስከ ዛሬዎቹ ዴቪድ ሂዩም፣ ክርስቶፈር ሂችንስ፣ ሳም ሀሪስ እና ሪቻርድ ዳውኪንስ ድረስ እግዚአብሔር መኖሩን ክደው ሌሎችንም ለማስካድ የሚጽፉ፣ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ እና በአማኞች የሚሳለቁ ሰዎች እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ከሚያቀርበው ሙግት የተለየ ሲያቀርቡ አልታየም።2 አዎን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኀጥአን እና ግፈኞች መበልጸግ፣ እንዲሁም ስለ ጻድቃን እና ደጋግ ሰዎች መጎሳቆል፣ ስለ እግዚአብሔር ለፍርድ መዘግየት እና ስለ ሕይወት ከንቱነት እግዚአብሔርን ይሞግታል (ለምሳሌ፡- መሳ. 6፥13፤ ዕን. 1÷14፤ ኤር. 14፥9፤ መዝ. 44፥22፤ 69፥3፤ መዝ. 22፥1፤ ማቴ. 27፥46)። ነቢዩ ኢሳይያስ፣ “የእስራኤል አምላክ መድኀኒት ሆይ፤ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ” በማለት በግልጽ እንዳስቀመጠው እግዚአብሔር ራሱን የሚሰውር አምላክ ነው (ኢሳ. 45÷15)፤ ነገሮችንም ይሰውራል።
በዐጽሙ ሬሳ እስከ ማስነሣት የደረሰው ኤልሳዕ ለዚህ ምስከር ይሆነናል። ይህን የእግዚአብሔር ሰው ከመቀለብ ባሻገር ከባሏ ጋር ተመካክራ ማረፊያ ያዘጋጀችለት አንዲት ሱነማዊት ሴት ነበረች። ይህ ትልቅ ነቢይ ውለታዋን ለመክፈል ዐስቦ ምን እንዲያደርግላት እንደምትፈልግ ሲጠይቃት ግን ጕድለት እንደሌለባት ነገረችው። እናም ኤልሳዕ ሎሌው ግያዝ እስኪነግረው ድረስ ልጅ እንደሌላት እንኳ እግዚአብሔር አልገለጠለትም ነበር (2ነገ. 4፥13)። ይህች ሴት ነቢዩ ኤልሳዕ በነገራት ትንቢት መሠረት ወንድ ልጅ ብትታቀፍም፣ ይህ ልጅ በአንድ ቀን ሕመም ብቻ ሞተባት። ታሪከኛዋ ሴት የልጇን አስከሬን በቤቷ አስተኝታ የእግዚአብሔርን ሰው ፍለጋ ሄደችና ስታገኘው በእግሩ ሥራ ወደቀች። ኤልሳዕ ይህን ሲያይ አንድ ነገር ተናገረ። ይህች ሴት ማዘኗ ግልጽ ቢሆንም፣ ያዘነችበትን ምክንያትና የገጠማትን ነገር “እግዚአብሔር … ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝም” ሲል አመነ (ቊ. 27)። በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ በተወሰደው ኤልያስ ላይ የነበረው መንፈስ በዕጥፍ የወረደበት ኤልሳዕ እግዚአብሔር ነገርን ሲሰውርበት ነገር የሚሰወርበት ነቢይ ነበር ለካ! እግዚአብሔር የሚገልጥለትን ብቻ ነው የሚያውቀው። እንደ ኤልሳዕ ሁሉ የትኛውም ነቢይ ሁልጊዜም ሁሉ ነገር አይገለጥለትም።
እግዚአብሔር ራሱን ብቻ ሳይሆን መንገዱንም ይሰውራልና ሁልጊዜም በገመትነው፣ በጠበቅነውና በተመኘነው መንገድ አይንቀሳቀስም። መጽሐፉ እንደሚል፣ “እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እኛም አናውቀውም” (ኢዮብ 36፥26)። መንገዱ እና ሥራው የሚያስደንቅ ብቻ ሳይሆን ግራ አጋቢ የመሆኑ አጋጣሚም የላቀ ነው። እግዚአብሔር በፍቅሩ እና በምሕረቱ የሚተካከለው ባይኖርም፣ በቍጣው እና በጭከናውም ቍንጮ ነው (ሮሜ 11፥22)። የሰዎችን ሥራ በእውነት መዝኖ የሚከፍል የመሆኑን ያህል፣ ገና ሳይወለዱና ሥራቸው ሳይታይ ሰዎችን ለሽልማት ወይም ለቅጣት መምረጡን ይናገራል (ሮሜ 9፥11-13)። ለሰዎች ሁሉ ነጻ ፈቃድ ሰጥቷል። ግና የፈለገውን ይምራል፣ የፈለገውን ደግሞ እልከኛ ያደርጋል እንጂ ምሕረቱ በሩጫና በማንጋጠጥ አይገኝም (ሮሜ 9፥16-18)። የገዛ ወታደሩን ሚስት ማማገጡን አድበስብሶ ለማስቀረት ሲል ባሏን እስከ ማስገደል በሥልጣን የባለገውን ዳዊት እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከሞት ታድጎታል (ዘሌ. 20፥10፤ 2ሳሙ. 12፥13)፤ ለእግዚአብሔር ክብር ቀንቶ ስሙ ከሕይወት መጽሐፍ እንዲፋቅ እስከ መጠየቅ የደረሰው ሙሴ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመግባት ይቅርታ ሲለምነው ደግሞ፣ “ይህን ነገር ደግመህ አታንሣብኝ” ብሎታል (ዘፀ. 32፤ ዘዳ. 3፥26)። ሕዝቡን ለማገልገል በስሙ ከተጠሩት መካከል አንዳንዶቹ በጥሪአቸው እና በስጦታቸው ሕዝቡን እያታለሉ በስሙ ሲነግዱ፣ ለስሙ ቀንቶ እርምጃ የማይወስድበት ጊዜም ብዙ ነው።
ለመሆኑስ መኖርን ክፉኛ የሚናፍቁ፣ በመኖራቸውም ለሌሎች ሕይወትን መስጠት የሚችሉ ሰዎች በሚሞቱባት ዓለም፣ ሞትን በጕጕት የሚጠብቁና ወደ መቃብር ሲቃረቡ ደስ እያላቸው ሐሤት ለሚያደርጉ ሰዎች ሕይወት የተሰጠው ለምንድን ነው (ኢዮብ 3፥20-23)? ግፈኞችና አምባገነኖች ዕድሜና ጤና ሲጠግቡ፣ ጨቅላዎች ከአካል ጉድለት እና ከበሽታ ጋር ለምን ይወለዳሉ? ችግረኞችን የሚበዘብዙ በብልጽግና ሲሰክሩ፣ እርሱን በእውነት የሚፈልጉቱና ረብ ያለው ነገር ለትውልድ ለማበጀት የሚባትሉቱ እጅ ሲያጥራቸው እግዚአብሔር ምን ይሰማዋል? ጥጋበኞች ለሚለኩሱት የጦርነት እሳት ንጹሓን ሴቶችና ሕፃናት በማገዶነት ሲቀርቡ፣ እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል? ብዙዎች ልጅ ፍለጋ ቀን ከሌት ሲያለቅሱ፣ የወለዱትን ልጅ ሽንት ቤት ጕድጓድ ውስጥ ለመጣል የሚጨክኑቱ ያለ ፍላጎታቸው የመውለዳቸው አግባብነት እንዴት ይታያል? በዚህ ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔር ምን እንደሚያስብ አናውቅም።
እግዚአብሔር ጥያቄነቱ ለሁሉም ነው። የእግዚአብሔርን ድምፅ ከሚሰሙትና ፈቃዱን ለሕዝቡ ከሚገልጡት ትልልቅ ነቢያት መካከል እንኳ በእግዚአብሔር እንደ ተታለሉ የሚቈጥሩ ነበሩበት (ኤር. 20፥7)። አዎን፤ ነቢያት እንኳ እግዚአብሔርን ሳያውቁት ይቀሩ ነበር፤ የእግዚአብሔርን አእምሮ ማንበብ የሚችል የለምና! ስለዚህም እግዚአብሔር እርሱን በሙላት ይተርክ ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ምድር መላክ ነበረበት (ዮሐ. 1፥18፤ ዕብ. 1፥1-3)።
ግና የማይታየውን አምላክ የተረከልን የሚታየው አምላክ የኢየሱስ ማንነት የውዝግብ እና የልዩነት መንሥዔ ሆኗል። ንጉሡ ኢየሱስ የት እንደሚወለድ ቅዱሳት መጻሕፍትን አጥንው ከማንም በፊት ያወቁት ጸሓፍትና ካህናት (ማቴ. 2፥4-6) እንዲሁም ስለ ትንሣዔው የመጀመሪያ ደረጃ ማስረጃ የደረሳቸው የካህነት አለቆች (ማቴ. 28፥11-15) ሲቃወሙ እንጂ ዕውቀታቸው ወደ እምነት ሲያደርሳቸው አልታየም። ኢየሱስ ከምድር ዘመኑ ጀምሮ እስከ አሁንም ለብዙዎች የመንገድገድ ዋንጫ ነው። ያኔ በሥጋ ዐይናቸው ያዩቱ፣ ሥራውን የተመለከቱቱ በማንነቱ ግራ ተጋብተዋል። ዛሬ የእርሱን ታሪክ እያብጠረጠሩ ለማጥናት የሚሞክሩ ልሂቃን ይሰናከሉታል። ሃይማኖተኞቹም በስሙ ብዙ ጎራዎችን አበጅተውበታል። ኢየሱስ ሲታይ መልስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄም ይታያል፤ ስለዚህም ኢየሱስ የተረከው አምላክም መልስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄም ነው ማለት ነው። ኢየሱስ የማይታየው አምላክ ምሳሌ ነውና (ቆላ. 1፥15)!
እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚያሳዩን እግዚአብሔርን እንደማናውቀው ነው። ሉዐላዊ አምላክ ነውና እንደ ፈቃዱ ያደርጋል። ቅዱስ አውግስጢኖስ እንደሚለን፣ “ዐውቀነዋል፣ ተረድተነዋል፣ ተገንዝበነዋል የምንል ከሆነ እርሱ እግዚአብሔር አይደለም።” (If you understand Him, He is not God.)3 እርሱን ማንቀሳቀስ የሚቻልበትን ምስጢራዊ ቀመር ያገኘም የለም። ምክንያቱም በቤተ ሙከራ ውስጥ፣ በምርመራ ጠረጴዛ ላይ አድርገን እንደምናጠናቸው የትኞቹም ነገሮች እግዚአብሔርን ልናጠናው አይቻለንም። የጥናቱ ባለቤት እርሱ ራሱ ነው። እርሱን ማወቅ የምንችለው ራሱን ሊገልጥልን በወደደው መጠን ብቻ ነው። ሆኖም እርሱ ከመታወቅ በላይ ነውና ማንነቱ ከአእምሮአችን ዐቅም ይልቃል። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር እና እግዚአብሔርን ለማገልገል ትሕትና የግድ ይሆናል። ሰውን ሙሉ በሙሉ ማወቅ የማይቻል መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ለብዙ ዓመታት አብረን የኖርናቸው የትዳር ጓደኞቻችን ላይ እንኳ አዳዲስ ጠባያትን በማየት ልንደነቅም ሆነ ልናዝን እንችላለን። ሙሉ በሙሉ አናውቃቸውም ማለት ግን አናምናቸውም ማለት አይደለም። የትዳር ጓደኛዬን ሙሉ በሙሉ ባላውቃትም፣ ይህ ግን እንዳላምናት አያደርገኝም። ለዚህ መሠረቱ ደግሞ አብሬአት መኖሬ ነው። ከሰው ጋር ጥሩ እና መጥፎ ጊዜአትን አብረን ስናሳልፍ፣ በጋራ ስንሥቅ እና ስናዝን (ስናለቅስ)፣ ተስማምተን ስንጓዝ እና ስንጋጭ እንዲሁም የሆድ የሆዳችንን ስንገላለጥ ይበልጥ እየተዋወቅን እንመጣለን። እርስ በርስ መተማመናችንም በዚያው ልክ ያድጋል። ከእግዚአብሔር ጋር ስንኖርም እንደዚያው ነው።
ሰውን ሙሉ በሙሉ ማወቅ ካልተቻለ እግዚአብሔርንማ ጠንቅቆ ማወቅ በጭራሽ አይታሰብም። ስለዚህም የማንጠብቀውን ነገር እያደረገ የደስታችን ብቻ ሳይሆን የሐዘናችንም ምክንያት ሊሆን ይችላል። የምንሻውን ባለማድረጉም ልናዝንና ልንቀየም እንችላለን። ነገር ግን ይበልጥ አብረነው በኖርን መጠን፣ በጸሎት እና ቃሉን በማንበብ ከእርሱ ጋር ጊዜ ባሳለፍን ቍጥር ይበልጥ እያመንነው እንመጣለን። እርሱን ለማመን እና እርሱን ተደግፎ ለመኖር እርሱን አብጠርጥረን ማወቅ አይጠበቅብንም። ጥያቄዎች ቢኖሩንም (ቢኖሩብንም) እምነታችንን በእርሱ ላይ ከመጣል እና መልካምነቱን ከመቀበል አያቅቡንም። ጥያቄአችን ሳይመለስ በእግዚአብሔር ማመንም ሆነ እግዚአብሔርን ማመን እንችላለን። ለዚህ ኢዮብ ምስክራችን ነው፤ እግዚአብሔር ምን እየሠራ እንደ ነበር ባያውቅም፣ መፈናፈኛ የሚያሳጡ ዕልፍ ጥያቄዎች ቢወጥሩትም፣ እግዚአብሔርን መታመን እንደሚችል ያውቅ ነበርና “እነሆ ቢገድለኝ እንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ” ሲል ተናግሯል (ኢዮብ 13፥15)።
ከእግዚአብሔር ጋር በአግባቡ ለመኖር እና እምነታችንን በእርሱ ላይ ለማድረግ ስለ እርሱ ሙሉውን እውነት ማወቅ የግድ አይደለም። እንዲያማ ቢሆን እስከ ዛሬ ማንም እግዚአብሔርን ባላመነ! ከዚህም የተነሣ አንድሬ ሬስነት እንደሚያስረዳው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ትግል አለብን፤ ይህ ትግል ግን እምነት የማጣት አይደለም። እንዲያውም እምነት ማለት ይህ ነው።4 ከዚህም የተነሣ ከሕያው አምላክ ጋር ያለ አንዳች ጥያቄ እና ትግል በእምነት እንደ ኖረ የሚነግረን ሰው ቢገኝ ከእውነተኛ አይቈጠርም። እንኳን ፍጹም ያልሆነ ሰው ፍጹም ከሆነ አምላክ ጋር ያለ ጥያቄ ሊኖር ይቅርና ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች እንኳ በዚህ መልኩ አብረው መኖራቸውን ቢነግሩን አናምናቸውም። እና ታዲያ የትኛው አማኝ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲህ ሊኖር ይቻለዋል?
ለነገሩማ በእግዚአብሔር ላይ ጥያቄም ሆነ ግራ መጋባት ቢኖረን የምናፍርበት ምክንያት የለም፤ እንዲያውም በዚህ ማፈር ነው የሚያሳፍረው።5 እግዚአብሔር ከመታወቅ በላይ ነዋ! ስለዚህም በልባቸው ምንም ዐይነት ጥያቄ እና የአእምሮ ውጥረት፣ አንዳንዴም ጭንቀት ሳይኖር ያለ አንዳች ግራ መጋባት እና ጥርጥር ሁልጊዜም እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ እንደሚያምኑ የሚናገሩ ሰዎች ቢኖሩ፣ የሚያምኑት እግዚአብሔር የሚባልን ሐሳብ እንጂ ራሱ እግዚአብሔርን አይደለም።6 ለጥያቄና ለሙግት በጭራሽ ቦታ ከሌለ ለጤናማ እምነትም ቦታ አይኖርምና!7
እግዚአብሔር ሕያው አምላክ እንጂ ሐሳብ ወይም አንዳች ቀመር አይደለምና እርሱ ባለበት ሁልጊዜም ጥያቄ አለ! ለአንዳንዱ ጥያቄ መልስ የምናገኘውን ያህል፣ መቼም የማንመልሳቸው ጥያቄዎችም በውስጣችን ተጣብቀው ይኖራሉ። ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዳለው ማመን ዋነኛው የማወቂያ መንገድ በመሆኑ እያመንን እንጓዛለን እንጂ፣ እግዚአብሔርን የምናምነው እና የምንከተለው ጥያቄዎቻችን ሁሉ ተመልሰውልን ወይም ጥያቄዎች ሳይኖሩን ቀርተው አይደለም። እግዚአብሔር ከጥያቄዎቻችን በላይ መሆኑን እያወቅን እናመልከዋለን፤ ወይም እርሱን ትተን ብንሄድም እንኳ ጥያቄዎቹ እንደማይለቅቁን ስናውቅ ከእርሱ ጋር መሆንን እንመርጣለን፤ ወይም ለጥያቄዎቹ መልስ ፍለጋ እየታገልን (ወይም እየታገልነው) እንከተለዋለን፤ ወይም ያለ እርሱ እንዲሁ ከመኖር ከእርሱ ጋር በጥያቄ ተከብቦ መኖር በልጦብን አብረነው እንኖራለን፤ ወይም በቀራንዮ መስቀል ላይ የተገለጠው ፍቅር አሸንፎን እንንበረከካለን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ኖሮ ያለ ጥያቄ መቅረት የሚቻል አይደለም። ምክንያቱም ቶማስ አኳይናስ እንዳለው፣ እግዚአብሔር ራሱ ጥያቄ ነው!
Share this article:
የማርቲን ሉተር ባለቤት ስለነበረችው ካትሪን ቫን ቦራ የሚያወሳው ይህ ጽሑፍ፣ የሉተር የተሓድሶ እንቅስቃሴ ዳር እንዲደርስ ስላበረከተችው ጉልሕ አስተዋጽኦ ታምራት ያዕቆብ እንዲህ ያስነብበናል።
አማረ ታቦር፣ “Seeing and Savoring Jesus Christ” ከተሰኘው የጆን ፓይፐር (መጋቢ) መጽሐፍ እየቀነጨበ ከሚያቀርበው ተከታታይ ጽሑፍ መካከል፣ “በግ’አንበሳው” ሲል ወደ አማርኛ የመለሰውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ውሕድ ማንነት የተብራራበትን ግሩም መልእክት ያንብቡ።
Observers take wait-and-see approach to televangelist “correcting” his prosperity gospel theology.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment