
After More Than Two Decades of Work, a New Hebrew Bible to Rival the King James
The pre-eminent scholar Robert Alter has finally finished his own translation.
[the_ad_group id=”107″]
“እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፤
ከቍጣ የራቀ፣ ምሕረቱም ብዙ ነው።”
(መዝሙር 105፥8)
በአማረ ታቦር
እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ እንደ ሆነ ብዙዎቻችን እናውቃለን። ይህም ሆኖ፣ የምሕረቱን ስፋትና ርዝመት፣ ከፍታውንና ጥልቀቱን ምን ያህል ተረድተነው ይሆን? በዚህ ጽሑፍ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማውሳት፣ የእግዚአብሔር የምሕረቱ መጠን ገደብ የለሽ መሆኑን እና የማዳን እጁን ኀይል ለማየት እንሞክራለን።
የሰው ልጆች ሁሉ ኀጢአተኞች ነን፤ “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤” (ሮሜ 3፥10)። ሁላችን ኀጢአት ሠርተናል፤ “የእግዚአብሔርም ክብር” ጎድሎናል (ቊ. 23)። ይህም ሆኖ፣ “አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፤ እርሱም፣ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና” (ቊ. 11-12) በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ቅዱሳን የድነት ምሥራችን ያበሥራቸዋል።
እግዚአብሔር ለሙሴ፣ “ለሚወድዱኝ፣ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” እንዳለው እናስታውሳለን (ዘፀ. 20፥6፤ ሉቃ. 1፥50፡ 54 በተጨማሪ ይመልከቱ)። ንጉሥ ዳዊት፣ “የእግዚአብሔር ምሕረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ፣ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው” እያለ ያውጃል (መዝ. 13፥17)።
ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱም ስለ የጌታ ምሕረት ጽፏል። ሁለተኛው ምእራፍ ላይ፣ “በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤” ብሎ በመጀመር፤ “የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን” ይላል። ይህም ሆኖ፣ “ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፣ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤ በጸጋ ድናችኋልና” በማለት የጌታ አምላካችንን ገደብ የለሽ ምሕረት ይገልጣል (ቊ. 1-5)።
አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሳቸውን ማዳን የማይችሉ ኀጢአተኞችን አዲስ ፍጥረት የሚያደርግ የምሕረት አምላክ መሆኑን በብዙ ቦታዎች እየደጋገመ ይናገራል። “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፣ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፣ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” (ቲቶ 3፥4-5፤ 1 ጴጥ. 1፥3 በተጨማሪ ይመልከቱ)።
የእግዚአብሔርን የምሕረቱን ጥልቀት፣ የማዳን እጁ ኀይልን ለማየት እንድንችል፣ ከብሉይ ኪዳን የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን ምናሴን ታሪክ ቀጥለን እንመልከት። ማጠናከሪያ እንዲሆኑ ከአዲስ ኪዳን ሁለት ተጨማሪ ዐሳቦችን በዐጭሩ መቋጫ እንዲሆኑ ተጨምረዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ትርጕም መፍቻ (ኮንኮርዳንስ) “ምናሴ” የሚለውን ስም፣ “እንዲረሳ የሚያደርግ”[1] ሲል ይተረጕመዋል። “ዮሴፍም የበኵር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፤ እንዲህ ሲል፦ እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ” (ዘፍ. 41፥51) የሚለውን የስሙን መሠረት ያስታውሷል። ምናሴ ዮሴፍ በግብፅ ምድር የወለደው የመጀመሪያ ልጁ ነው። ያዕቆብ አንቀላፍቶ ወደ አባቶቹ ከመከማቸቱ በፊት፣ ለሚወድደው ልጁ ዮሴፍ ሁለት ድርሻን በመስጠት፣ ኤፍሬምና ምናሴን ከሌሎቹ ልጆች እኩል አድርጓቸዋል (ዘፍ. 48፥5-6)። በዚህም ምናሴና ኤፍሬም ከእስራኤል ዐሥራ ሁለት ነገዶች ውስጥ ሁለት ድርሻ ኖራቸው።
ከዚያ በመቀጠል ደግሞ፣ “ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ” የነበረው የምናሴ ነገድ ተወላጁ ጌዴዎንን እናገኛለን (መሳፍንት 6 ይመልከቱ)። በመጨረሻም፣ ዛሬ ትንሽ ልልለት የፈለግሁት የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን ምናሴ ሁለተኛው የነገሥት መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን። በዚህ ሰው ሕይወት የተገለጠውን የእግዚአብሔር ገደብ የለሽ ምሕረት ለማሳየት እሞክራለሁ።
መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ፣ “ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ” በማለት ይህን ሰው ያስተዋውቀናል (20፥21)። ከዚያም ቀጣዩ ምእራፍ፣ “ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱ ስም ሐፍሴባ ነበረ” በማለት ታሪኩን ይጀምራል (21፥1)። በጣም የሚገርመው ግን፣ ምናሴ የአባቱ ሕዝቅያዝን ዙፋን እንጂ፣ መልካምነቱን አልወረሰም ነበር። “እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ” (2 ነገ. 21፥2)። አባቱ ሕዝቅያስ፣ “በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም። ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፥ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ።” ተብሎ የተመሰከረለት ነበር (2 ነገ. 18፥5-6)። በሚያሳዝን ሁኔታ ምናሴ የአባቱን እጅግ መልካም መንገድ አለመከተል ብቻ ሳይሆን፤ ጭራሽ እጅግ የከፉ ኀጢአቶችን ሠራ።
ምን አደረገ?
1 ነገሥት 21፥3-7 የምናሴን ኀጢአት እንደሚከተለው ዘርዝሮ አስቀምጦታል፦
ከእነዚህ በተጨማሪ (ቊ. 8)፣ “እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ ‘በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፣ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም’ ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቈመ።” በዚህም፣ “እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።” (ቊ. 12) ይላል።
ይህም ሳይበቃው፣ “ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።” (ቍ. 16)
ከላይ እንዳየነው በይሁዳ ለአምሳ ዐምስት ዓመታት ከነገሠ በኋላ፣ “ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።” (ቊ. 16) እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን ልጨምር። ምናሴ መንገሥ የጀመረው በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ከነበር፣ የሞተው በ67 ዓመቱ ነበር ማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ የሠራው ኀጢአት ዙፋኑን የተረከበው ልጁ አሞጽም በሚያሳዝን ሁኔታ እንደደገመው ቀጣይ ቊጥሮቹ ይናገራሉ። አሞጽ የነገሠው ሁለት ዓመት ብቻ ሆኖ፣ “… ባሪያዎች አሴሩበት፤ ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት” (ቊ. 23)፤ “በዖዛም አትክልት ባለው በመቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ” (ቊ. 23) ብሎ ያበቃል።
አሁን በዚህ ጽሑፍ ማሳየት ወደፈለግሁት ቍም ነገር ልለፍ። ከላይ የተቀመጡት በሙሉ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ምእራፍ 33 ላይ ተደግመዋል። ሆኖም፣ ዜና መዋዕል ውስጥ ያለው ታሪክ አንድ ተጨማሪ መረጃ አለው። እርሱም፣ የምናሴን መጨረሻ (ወይም አጨራረስ) በተመለከተ ነው። እንዲህ አስቀምጦታል፦ “እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም” (ቊ. 10) ብሎ ይጀምራል። ይህ አለመስማት ቅጣትን አመጣ። ቀጣዩ ቊጥር የሆነውን ይነግረናል፣ “ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር[2] ያዙት፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት” (ቊ. 11)። ንጉሥ ምናሴ ተዋረደ። የንግሥና በትረ መንግሥት የሚይዝበት እጁ በካቴና እና በሰንሰለት ታሰረ። ወደ ባዕድ ምድርም ተጋዘ።
ይህን ጊዜ ምናሴ ምን አደረገ?
“በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ፤ ወደ እርሱም ጸለየ” (ቊ. 12-13)። በሌላ አባባል ወደ ልቡ ተመልሶ (እንደ ጠፋው ልጅ ሉቃስ 15) ራሱን ዝቅ በማድረግ ንስሓ ገባ። እግዚአብሔር በጣም የረዳው ሰው! ለመሆኑ እግዚአብሔር ሰማውን? ሁለተኛ ዕድልን ሰጥቶ ተቀበለውን? አዎን ሰማው። ተቀበለውም! “እርሱም [አምላኩ እግዚአብሔር] ተለመነው፤ ጸሎቱንም ሰማው፤ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ አወቀ።” (ቊ. 12-13)።
ምናሴም መቀየሩን በተግባር አሳየ
“ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተ ውጭው ከግዮን ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሳ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። በዖፌልም አዞረበት፤ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፤ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው። የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፤ የደኅንነትና የምስጋናም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ።” (ቊ. 14-17)።
አንባቢ፣ በምናሴ ታሪክ የእግዚአብሔር አምላካችንን ገደብ የለሽ ምሕረት እንደሚያይ ተስፋ አደርጋለሁ።
ወንጌል ውስጥ “ወንበዴ” የሚል መጠሪያ ከተሰጣቸው ውስጥ “በርባን” አንዱ ነው፤ ኢየሱስ ምትክ ሆኖለት ከእስር የተፈታው በርባን። “ሁሉም ደግመው፦ በርባንን እንጂ ይህን [‘የአይሁድ ንጉሥን’] አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።” (ዮሐ. 18፥40) ከዚህ ሰው ሌላ ግን፣ በመጨረሻው መጨረሻ ሰዓት ላይ ጌታ ገደብ የለሽ ምሕረት ያደረገለት ዐመፀኛ አለ። እርሱም፣ ከጌታ ጎን ተሰቅሎ የነበረው ወንጀለኛ!
ሐኪሙ ሉቃስ በወንጌሉ ምእራፍ 23፥39-43 ላይ እንዲህ አስቀምጦታል፦ “ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፦ ‘አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን’ ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ፦ ‘አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም’ ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም፦ ‘ጌታ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ አለው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ በሕይወቱ እግዚአብሔር ገደብ የለሽ ምሕረት የታየበት ሰው ነው። ስለ ኢየሱስ ምስክር የነበሩትን የጌታ ደቀ መዛሙርት ያሳድድ የነበረው ሳውል፣ ጌታ በደማስቆ መንገድ ላይ ተገናኝቶት የወንጌሉን ብርሃን አበራለት (የሐሥ. ሥራ 9)። ከዚያን በኋላ ብዙ መከራን ተቀብሏል። ይህም ሆኖ ግን፣ እግዚአብሔር ያደረገለትን ምሕረት ደጋግሞ መስክሯል። ለምሳሌ ያህል፣ “ቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፣ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” (1 ጢሞ. 1፥13) ይላል። ከሦስት ቊጥር በኋላም “ስለዚህ ግን፣ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።” (ቊ. 16) በማለት ይህንኑ ያጸናል።
የአምላካችን የእግዚአብሔር ምሕረት ገደብ የለውም። ምሕረቱ እጅግ የበዛ ነው። የመዝሙር መጽሐፍ ብዙ ቦታ ላይ “እግዚአብሔር ቸር ምሕረቱም ለዘላለም ነው” ይላል (መዝ. 100፥5፤ 107፥1፤ 118፥1-4፤ 136)። የእግዚአብሔር አምላክ ምሕረት የተገለጠው ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ከሆነው ዔድን ገነት ጀምሮ ነው። የጌታን ትእዛዝ በዐመፅ የተላለፉት የመጀመሪያ ወላጆቻችን በፍርድ ቅጣት የዘላለም ሞት ይገባቸው ነው። እግዚአብሔር አምላክ አዳምና ሔዋንን ከዔደን ገነት ያስወጣቸው ግን፣ የድነት ተስፋን ሰጥቶና የቁርበት ልብስን አልብሷቸው ነበር (ዘፍ. 3)።
ጌታ ምሕረቱን በእምነት አባቶቻችን በኖህ፣ በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ እንዲሁም በእስራኤላውያን ሕይወትና ኑሮ ውስጥ አሳይቷል። ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይጠይቅ እስራኤልን በማስቈጥሩ ምክንያት፣ አምላካቸው ተቆጥቶ ቅጣትና መቅሠፍት በሕዝቡ ላይ አመጣ (1 ዜና መዋ. 21)። ዳዊት ጥፋቱን አውቆ፣ “እግዚአብሔርን፣ ‘ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኃጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ’ አለው።”
ለልመናው መልስ ተሰጠው። “እግዚአብሔርም ለዳዊት ባለ ራእይ ለጋድ፣ ‘ሂድ፤ ለዳዊት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው’ ብሎ ተናገረው።” (ቊ. 8-10) የአምላኩን የምሕረት እጅ በተደጋጋሚ የተመከተው ዳዊት፤ “ጋድን፣ እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ’ አለው።” (ቊ. 13)
እኛም የእግዚአብሔር አምላካችንን ገደብ የለሽ ምሕረት እንዳንረሳ። በየጊዜውም ወደ ምሕረቱ ዙፋን በንስሓ እንቅረብ። ለዚሁም ጌታ ይርዳን። አሜን።
[1] H4519: Menashsheh፡ causing to forget
[2] የአቢሲኒካ መዝገበ ቃላት ድረ ገጽ፤ የዛንጅር ትርጕም፦ ክፉ ወንጀልን የሠራ ሰውን ማሰሪያ ወፍራም ሰንሰለት ዛንጅር ይባላል (ዛንጅር ([ዐረቢኛ])።
Share this article:
The pre-eminent scholar Robert Alter has finally finished his own translation.
“የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን ዐሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፣ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው። እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈጽሞ አንችልም። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፣ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን ወደ ሞት ይወስደናል። ታዲያ ምን ይሻላል?” ዘላለም እሸቴ (ዶ/ር)
ምኒልክ አስፋው ወረርሽኙ “መቅሰፍት ወይስ መገሥጽ” ለሚለው ጥያቄው በሰጠው ምላሽ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ አሰሳ በማድረግ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ተሻጋሪ መርሖዎችን እንካችሁ ይላል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
2 comments
እሜክሰ በርታ ፀጋ ይብዛልህ
አሜን ይሹ። አመሰግናለሁ!