[the_ad_group id=”107″]

ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ

ዐጭር ታሪካዊ ቅኝት

የታሪክ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያውያን ሕገ ኦሪትን ተቀብለው እግዚአብሔርን እስኪያመልኩ ድረስ በፀሓይ፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት፣ በእንስሳት፣ በአራዊት፣ በዛፍ እና በክፉ መናፍስት ያመለኩ ነበር። ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኢትዮጵያ ንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ የሆነ ሰው፣ በፊሊጶስ አማካኝነት ወንጌልን ከተረዳና ከተጠመቀ በኋላ፣ የተረዳውን እውነት ወደ ኢትዮጵያ ይዞ እንደ ተመለሰ ይታመናል።

አሁን ወደሚታወቀው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌል የገባበትን ጊዜ በርግጠኝነት ለመናገር አዳጋች ቢሆንም፣ እንደ ግለ ሰብ በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (የሐዋርያት ሥራ 8፥26-40)፣ እንደ መንግሥት ደግሞ በንጉሥ ኢዛና ዘመን እንደ ሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ወንጌላዊው ፊሊጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የወንጌልን የምስራች ቃል ከነገረው በኋላ፣ ጃንደረባው ይህን ወንጌል ይዞ በ34 ዓ.ም. ገደማ ወደ ኢትዮጵያ እንደ ገባ ይታመናል። በሌላ የታሪክ ዘገባ መሠረት ቅዱስ ማቴዎስ፣ ወንጌልን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ እንደ ገባ፣ በአክሱምም ጥቂት ሰዎችን እንዳጠመቀ፣ ሕይወቱም በዚያው መሥዋዕት ሆኗል።

 

በአራተኛው ክፍለ ዘመን ፍሬምናጦስ እና ኤዴስየስ በተባሉ ሁለት ሶሪያዊ ወንድማማቾች አማካኝነት ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ እንደ ገባ ሩፊኖስ በተባለ የቤተ ክርስትያን ታሪክ ጸሐፊ ተዘግቦ ይገኛል። እነዚህ ወንድማማቾች ምፅዋ ላይ ተማርከውና ወደ አክሱም ተወስደው የቤተ መንግሥቱ ባለሟል መደረጋቸውን ለወንጌል ምስክርነት ጥሩ አጋጣሚ አድርገው ተጠቅመውበታል። “አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን” ተብሎ የተሰየመው ፍሬምናጦስ፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ጳጳስ ሆኖ አገልሏል።

ክርስትና በኢትዮጵያ የበለጠ የተስፋፋው፣ ከ451 እስከ 480 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በገቡት ዘጠኝ መነኮሳት አማካኝነት ነው። እነዚህ መነኮሳት መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ከግሪክና አርማይክ ወደ ግዕዝ በመተርጐም ትልቅ አስተዋፆ አበርክተዋል።

እምነት ለድነት ያለው ስፍራ ማዕከላዊ የሆነበት ስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የተካሄደው በ15ተኛው ክፍለ ዘመን፣ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት (1434 – 1468) ሲሆን፣ የዚህ ታልቅ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ጀማሪ በምንኩስና ስሙ እስጢፋኖስ ተብሎ የሚታወቀው የትግራይ ተወላጅ ነው። ይህ ወጣት ብዙ ተከታዮችን ያፈራ ሲሆን፣ በትምህርቶቹና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ያሉ ሥነ መለኮታዊ ቀኖናም ሆነ ሃይማኖታዊ ልምዶች ላይ ጥያቄዎች በማንሣቱ፣ የሕይወት መሥዋዕትነት ያስከፈለውን ብዙ መከራ እና ስደት ተቀብሏል።

ድነት እንዲሁ በጸጋ፣ በክርስቶስ በተደረገ ቤዛነትን በማመን እንደ ሆነ እንዲሁም ስለ ሥላሴ፣ ስለ ሰንበት፣ የጌታ ራት ያለ አስተምህሮን፤ ስግደት ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ለወላዲተ አምላክ፣ ለሥዕል፣ ለመስቀል፣ ለንጉሥ እንደማይገባ እስጢፋኖስ ያስተምር ነበር። ይህም ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር ከመነሳቱ ከሠላሳ ዓመታት በፊት የተደረገ የተሓድሶ እንቅስቃሴ ነበር ማለት እንችላለን።

 

 

በንጉሥ ኢዛና ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስትና፣ ከአክሱም ሥርወ መንግሥት እስከ ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ድረስ ብሔራዊ ሃይማኖት (state religion) ሆኖ ቆይቷዋል። ሆኖም ዮዲት ጉዲት በ10ኛው ክፍለ ዘመን በቤተ ክርስትያን ላይ ያደረሰችው ጉዳት፣ ኋላም የአህመድ ግራኝ ወረራ (1528-1632 እ.ኤ.አ.) እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ የቤተ ክርስትያንን አቅም አዳክሞታል። ቤተ ክርስትያናትና ቅዱሳት መጻሕፍት ተቃጥለዋል፣ ምዕመናን ታርደዋል፣ እጅግም ብዙ ጥፋት ደርሷል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ አህመድ ግራኝን ለመዋጋት የፖርቹጋልን ድጋፍ የጠየቀች ሲሆን፣ ከጦርነቱም በኋላ ፖርቹጋል የካቶሊክ እምነትን ለማስፋፋት ሚስዮናውያንን ልካ ነበር።

በ15ተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በሮችዋን ለሚስዮናውያን ክፍት ያደረገችው ከአህመድ ግራኝ ወረራ እና ከኦሮሞ እንቅስቃሴ ከደረሰባት መከፋፈል ለማገገም ነበር። ታዲያ በዚያን አጋጣሚ የገቡት የኢየሱሳውያን (Jesuits) ሚስዮናውያን የበለጠ ጉዳት አስከትለው፣ በሚስዮናውያን ላይ የነበረው ተኣማኒነት ላይ ውሃ ቸልሰው፣ ከአገሪቱም በግድ ተገፍትው ነበር የወጡት። ከዚያ ሁሉ በኋላ ግን በኢየሱሳውያን የተጻፉ ጽሑፎች ለበርካታ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ ደጋግሞ መምጣት ምክንያት ሆኑ። በ16ተኛው ክፍለ ዘመን በኢየሱሳውያኑ የተጻፉ ጽሑፎች በደቡብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ስለሚኖሩ የኦሮሞ ሕዝቦች ያትታሉ። ይህንንም ተከትሎ የኦሮሞ ሕዝቦችን ለመድረስ ብዙ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።

የአውሮፓ ተሐድሶ መቶ ዓመታትን ካስቆጠረ በኋላ፣ በቀዳሚነት ለሚስዮን ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሚስዮናውያን ጀርመናውያን ነበሩ። ከእነዚህ ሚስዮናውያን መካከል፣ በንጉሥ ፋሲል ዘመነ መንግሥት (1625-1660) ጊዜ ወደ ጎንደር የዘለቀው ፒተር ሄሊንግ (1607-1652 እ.ኤ.አ.) በፋና ወጊነት ተጠቃሽ ነው። ሄሊንግ በኢትዮጵያ ከነበረችው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሌላ የክርስትና ሃይማኖት መመሥረት ሳይሆን፣ የቤተ ክርስትያኒቱን አትኩሮት ወደ እግዚአብሔር ቃል በመመለስ (ሪፎርም በማድረግ)፣ በተለይም በድነት ላይ ባላት ሥነ መለኮታዊ አስተምሮ ላይ አጽንዖት በመስጠት መሠራት እንዳለበት ያምን ነበር። ሆኖም አገልግሎቱ በዐጭር የተቀጨ ሲሆን፣ በ1652 ወደ ግብፅ በሚሄደበት ጊዜ ሃይማኖቱን እንዲክድ ግድ ባሉት ቱርኮች እጅ ሕይወቱ ዐልፎል። ፒተር ሄሊንግ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ አማርኛ ከመተርጐሙ ባሻገር፣ ጥሎ ስላለፈው አሻራ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም።

ከፒተር ሄሊንግ ህልፈት መቶ ዓመታት በኋላ፣ በ1782 ዓ.ም. የስኮትላንዱ ተጓዥና ተመራማሪ ጅምስ ብሩስ፣ የዓባይን መነሻ ለማግኘት ስላደረገው አሰሳ እና የጎንደርን ታሪክ በጽሑፍ መዘገቡ እንዲሁም ፈረንሳዊው ሐኪም ሻርል ፖንሴን ያየውን ለዓለም ማሳወቁ አውሮፓውያን ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሩ መነሣሣትን ፈጥሯል። ኢትዮጵያ ከ16ተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እስከ 18ተኛው ክፍለ ዘመን (ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል) ሚስዮናውያንም ሆኑ ማናቸውም አውሮፓውያን ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የከለከለች ቢሆንም፣ በ18ተኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ብዙ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ይህም አውሮፓውያን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ አህጉር ኢኮኖሚን መሠረት ያደረገ ሰርጎ ገብነት አካል እና የክርስትናን እምነት የማስፋፋት ተልዕኮ ነበር።

 

በዚህ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ቀደምት ሚስዮናውያን መካከል ከእንግሊዝ ፕሮቴስታንት ድርጅት፣ “የቤተ ክህነት ሚስዮናዊ ጉባዬ” (Church Missionary Society) የተላኩት በቤጌምድር እና ትግራይ የተንቀሳቀሰው ሳሙኤል ጎባት (1799- 1879) እና ትግራይ በ1829 የደረሰውን ክርስትያን ኩግለር መጥቀስ ይቻላል። እንደ ሄሊንግ እነርሱም በኢትዮጵያ ከነበረችው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ጋር ዐብሮ በመሥራት መጽሐፍ ቅዱስ የማሰራጨት እና ሕዝቡን በቅዱስ ቃሉ መሠረት እንዲመራ በማገዝ ተሐድሶ የማምጣት ትልም ነበራቸው። ወንጌላትን እና የጳውሎስን መልእክቶች በአማርኛ ትርጕም በማሰራጨቱ ላይ ስኬታማ ቢሆኑም፣ የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ ግን አልቻሉም። ኩግለር ከአንድ ዓመት በኋላ ሕይወቱ በአደጋ ያለፈ ሲሆን፣ ሳሙኤል ጎባት ለሦስት ዓመታት ስኬታማ አገልግሎት በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ በ1826 ዓ.ም. ከጀርመናዊው ሚስዮናዊ ኢዘንበርግ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። ሆኖም ሳሙኤል ጎባት በሕመም ምክንያት ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ አገሩ የተመለሰ ሲሆን፣ ኢዘንበርግም ኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከተወዳጀው ጆሀን ክራፍ ጋር በሸዋ ላይ ለወንጌል ሥራ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም፣ የእጅ ሙያ ያልነበራቸው በመሆኑ በጊዜው በነበሩት የሸዋ አስተዳደሪ ሳህለ ሥላሴ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀሩ።

ክራፍ በሽዋ በነበረው የአራት ዓመት ቆይታ የኦሮሞን ሕዝብ በወንጌል ለመድረስ የሕዝቡን ቋንቋ በመማር አሳልፏል። የኦሮሞን ሕዝብ በወንጌል የመድረስ ፍላጎት ያሳደረበት ከዓመታት በፊት ፖርቹጋላዊው ባልተዛር ቴሌዝ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ የጻፈውን መጽሐፍ በማጥናቱ ነበር። እሱም ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ በመጻፍ ለአውሮፓውያን ያስተዋወቀ ሚስዮናዊ ነው። “ሰሜን ኢትዮጵያ ክርስትያኖች ናቸው፤ ለእነርሱ ወንጌል በመስበክ አንደክምም። ይልቅስ ከሸዋ ጀምሮ የሰፈረ ሌላ ሕዝብ (የኦሮሞ ሕዝብ) አለ። ይህ ሕዝብ ክርስትያን አይደለም። ለዚህ ሕዝብ ወንጌል እንስብክ” ሲል በጻፈው መልእክት ላይ ገልጿል። 


ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ከማጥናት ባለፈ፣ ጀርመን ለአውሮፓ የሆነችውን ያህል የኦሮሞ ሕዝብም ለአፍሪካ መሆን ይችላል ብሎ የተናገረው ንግግር ትልቅ ተጽእኖ ከማምጣቱ የተነሣ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ‘የአፍሪካ ጀርመን’ ብሎ መጥራት ሳይቀር ተለምዶ ነበር። በዚህም ምክንያት ከ18ተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ የአውሮፓ ሚስዮናውያን እንቅስቃሴ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያተኮረ ሆነ። ክራፍ የተወሰኑ የወንጌል ክፍሎችን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጐምና በአባ አብርሃም በ1840 የተተረጐመውን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከሚካሔል አረጋዊ ከተባለ የጎንደር አማኝ ጋር በመሆን የተሻሻለ ትርጕም በማሳተም ትልቅ አስተዋፆኦ አደርጓል።

 

 

በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት (1855-1868)፣ ንጉሡ አገሪቷን ወደ ሥልጣኔ ለማምጣት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሣ የዕደ ጥበብ ሙያ ለነበራቸውን የአውሮፓ ሚስዮናውያን ይቀበሉ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ከስዊዘርላንድ “Pilgrim mission” የተባለና ስድስት ሰዎችን ያቀፈ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በ1848 መጥቶ ነበር። እነርሱም በእጅ ሙያ ንጉሡን በታማኝነት ከማገልገል ባለፈ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ያደረጉት ጥረት ንጉሡም ሆነ አቡኑ ባለመፍቀዳቸው ጥረታቸው የተሳካ አልነበረም። ሆኖም ግን ከእነርሱ መካከል፣ ማርቲን ፍላድ የተባለ ሚስዮናዊ የንጉሡም ሆነ የአቡኑን ፈቃድ አግኝቶ በጎንደር አካባቢ ላሉት ቤተ እስራኤላውያን ወንጌል ይሰብክ ጀመር። ይህም አገልግሎቱ ውጤታማ ሆኖ ብሩ እና ሚካሔል አረጋዊ በተባሉ ኢትዮጵያውያን አማኞች ሊቀጥል ችሏል።

የዐፄ ቴዮዎድሮስ መንግሥት እየተዳከመ በነበረበት ወቅት፣ የስዊድን ሚስዮን አገልግሎት ቡድን የኦሮሞን ሕዝብ በወንጌል የመድረስ ራእይ በመሰነቅ በ1860 ዓ.ም. ምፅዋ ላይ ደርሷል። ሆኖም ግን በጊዜው የነበረው አለመረጋጋት በሸዋ ዐልፈው እንዳይሄዱ አግዷቸዋል። ዐፄ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት በሆኑበት ጊዜ የከረረ የሃይማኖት ፖሊሲ ማራመዳቸው ሚስዮናውያኑ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ለመግባት የነበራቸውን እቅድ አወሳስቦታል። ኢትዮጵያም ከ1878-1914 ዓ.ም. ለወንጌል ሥራ አስቸጋሪ አገር ሆና ቆይታለች።

የኦሮሞን ሕዝብ ለመድረስ የመጣው የስዊድን ሚስዮን (Swedish Evangelical Mission) ወደ አገሪቱ ለመግባት ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ፣ በሐማሴን በሚገኙ የኩናማ ሕዝቦች ዘንድ የወንጌል አገልግሎት ጀመረ። በዚያም በነበራቸው አገልግሎት በሐማሴን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በእምነት በሆነ የመዳን ወንጌል ካመኑ ቄሶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው። በኩናማ ለአራት ዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ በጊዜው የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ኩናማን ለቅቀው ወደ ምፅዋ እንዲሄዱ አስገደዳቸው። ሚስዮናውያኑ የወንጌል አገልግሎቱን ሊቀጥሉበት የሚችሉበትን አዲስ መንገድ በማሰብ ሉንዳን በተባለው መሪያቸው አማካኝነት በምፅዋ በ1872 እ.ኤ.አ. አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍተው ይንቀሰቀሱ ጀመር። በስዊድን የእምነት ተልእኮ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሚሲዮናውያን ያከናወኑት ትልቅ ተግባር ዘመናዊ ትምህርት ቤት መክፈታቸው ነበር።

በጊዜው በነበረው የባሪያ ንግድ፣ ከትውልድ መንደራቸው በባሪያ ፈንጋዮች አማካኝነት ለባርነት በቀይ ባሕር አካባቢ ተወስደው ወደ አረብ አገራት ለመሸጥ የሚጠባበቁ ልጆች ነበሩ። እነርሱም በአውሮፓውያን፣ ማለትም በጣልያኖች እና በአካባቢው ይኖር በነበረ የእንግሊዝ ቻንስለር ይዋጁ (ነጻ ይወጡ) ነበርና፣ ሚስዮናውያኑ እነዚህን ተማሪዎች በመቀበል ማስተማር እና የወንጌልን ምስራች መንገር ጀመሩ። እነዚህ በባርነት ተሸጠው፣ ከዛም ነጻ የወጡ የወንጌል መልእክተኞች ለውጪ አገር ሚሲዮናውያን ዝግ ወደ ነበሩ የኢትዮጵያ ክፍለ አገሮች ወንጌልን ይዘው መግባት ችለው ነበር። ይህ መንገድ ወደ መኻል ኢትዮጵያ ለመዝለቅ ተሰልቶ የተጀመረ አልነበረም፤ ነገር ግን የውጭ ተወላጅ ሚስዮናውያን ያልሆነላቸውን በአገር ተወላጆች ውጤት ያስገኘ መንገድ ነበር። ይህም ከአገር በቀል ሚስዮናውያን መፈጠር ባለፈም፣ ለወንጌላውያን ቤተ ክርስትያን መመሥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በዚህ ትምህርት ቤት ከተማሩት የመጀመሪያ ተማሪዎች ከምፅዋ ተነሥተው ለወንጌል ሥራ ወደ ኦሮሞ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተንቀሳቀሱ ቀደምት ወንጌላውያን መካከል፣ የአማራው ነጋዴ ንጉሤ እንዲሁም በቦጂ ወለጋ ወንጌል ያደረሰው የሐማሴኑ ቄስ አባ ገብሬ እዮስታቲዮስ እና ከባርነት ተዋጅቶ የኦሮሞን ሕዝብ በወንጌል የደረሱት እና መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ የተረጐሙት አናሲሞስ ነሲብ እና አስቴር ጋኖ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን በውጪ አገር ሚሲዮናውያን ወንጌል ወደ አገሪቱ ይዘው ከመምጥታቸው በፊት እነዚህ አገር በቀል ሚሲዮናውያን ወንጌልን ወደ ጅማ እና ወለጋ አካባቢዎች ለመውሰድ ችለዋል።

የዐፄ ምኒልክ ዘመን መንግሥት ለውጪ ሚስዮናውያን ለተወሰነ ጊዜ አመቺ የነበረ ቢሆንም፣ ንጉሡ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ጋር ሊፈጥር የሚችለውን ቅራኔ ለማስቀረት በሚል ከነበራቸው ነጻ (liberal) አቋም አፈግፍገዋል። ሆኖም የስዊድን ሚስዮን በሐማሴን የነበራቸውን አገልግሎት በኢምኩሉ በሚገኘው የሥልጠና ጣቢያቸው ጋር በማዋቀር አገር በቀል ሚስዮናዊያንን ወደ ኦሮሞ ሕዝብ መላክ ችለው ነበር። በጣሊያን ወረራ ወቅት የውጪ ሚስዮናውያን አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ሲገደዱ፣ አገር በቀል ወንጌላውያን የወንጌሉን ዐደራ ይዘው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰዋል።

ዐፄ ኀይለ ሥላሴም፣ “አገር የጋራ ነው፤ ሃይማኖት የግል ነው” በሚል መርሖአቸው እያንዳንዱ ሰው የእምነት ነጻነቱ እንዲከበርለት ሚስዮናውያኑም ከእምነታቸው ጎን ለጎን የትምህርት እና የሕክምና አገልግሎት እንዲያስፋፉ ድጋፍ አድርገዋል። 


የወንጌል ስርጭት ዕድገት በኢትዮጵያ አዝጋሚ ሂደት የነበረው ነው ማለት እንችላለን። በአክሱም መንግሥት ሥር የነበሩ ሕዝቦች፣ ወንጌልን ለመስማት ሁለት መቶ ዓመታት ያህል ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። የወንጌሉ መልእክት፣ የሰሜን ሸዋው ዛጕዌ መንግሥት ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ሮሃ ላስታ የደረሰው በ13ተኛው ክፍለ ዘመን ነበር። በ15ተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ጎጃም እና ጎንደር ደረሰ፤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ጀባት፣ ሀዲያ እና ሰሜን ባሌ ሲደርስ፣ በ19ተኛው ክፍለ ዘመን የምኒልክን መንገሥ ተከትሎ ወንጌል ወለጋ፣ ከፋ፣ ኢሊባቡር፣ ጋሞ ጎፋ፣ ሲዳሞ እና ባሌ አካባቢዎች ደርሶ ነበር።


ዋቤ መጻሕፍት

ወንድዬ ዓሊ። እኩለ ሌሊት ወገግታ፦ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስትያን ታሪክ (1934 1966 ዓ.ም.) ቅጽ አንድ። የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስትያን የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት፤ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ፤ 1992 (ገጽ 1-10)።

ጌታቸው በለጠ። ኤሎሄ እና ሃሌሉያ፦ እኩለ ሌሊት ወገግታ (1934 1966 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስትያን ታሪክ 1966 1992 ዓ.ም. ቅጽ አንድ። የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስትያን የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት፤ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ፤ 1992 (ገጽ 58)።

ባሕሩ ዘውዴ። የኢትዮጲያ ታሪክ ከ1847 1983። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፤ 2000 ዓ.ም.፤ (ገጽ 23-24)።

Fekadu Girma. Evangelical Faith Movement in Ethiopia፡ Origins and Establishment of the Ethiopian Evangelical Church, Mekane Yesus. (p.43).

Tibebe Eshete. Evangelical Movement in Ethiopia Resistance and Resilience. 2009 (p.66-72).

ጆናታን ሃልደብራንት (ትርጕም ጌቱ ግዛው)። የቤተ ክርስትያን ታሪክ በአፍሪካ። Lapsley, Brooks Foundation, Addis Ababa (1993). Dallas, Texas, USA (2001).

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ።የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥት ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል በ1920ዎቹ ዓመታት። ሴንትራል አታሚዎች፤ አዲስ አበባ።

Share this article:

የምዕራባውያንን የአስተምህሮ ዓሣ መብላት በብልሃት

“ያለ በቂ ጥንቃቄ የተቀበልነው ምዕራባዊ ክርስትና ምን ዐይነት እርምት ይሰጠው? የተሓድሶ ትምህርት በተገኘባቸው አህጉራት ማኅበራዊውን እውነታ እንዴት አበጀው ወይም ቀረጸው?” እያሉ የሚጠይቁት ምትኩ አዲስ፣ የምዕራባውያንን የተሓድሶ አስተምህሮዎች ስንቀዳ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ

መልካም ጅምሩ እንዳይደናቀፍ

የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

በዓለ ጰራቅሊጦስ

በኢትዮጵያ ከ1555-1585 ዓ.ም. የነገሠው የዐፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል ጸሐፍት ዜና መዋዕሉን መጻፍ የጀመሩት የሚከተለውን ጸሎት በማቅረብ ነበር። “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተብቍዖ ወሰአሎ ለእግዚአብሔር አቡከ ከመ ይፈኑ ላዕሌነ ጰራቅሊጦስሃ መንፈሰ ጽድቅ ዘኢይክል ዓለም ነሢኦቶ። ወመጺኦ ውእቱ ይመርሐነ ኀበ ኵሉ ጽድቀ ነገር። እስመ አይነግር እም ኀቤሁ ፈጠራ ወሐሰት አምሳለ ካልኣን መናፍስት እለ አልቦ ጽድቀ[ቅ] ውስተ አፉሆሙ። – ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ዓለም ሊቀበለው የማይችለውን የእውነት መንፈስ የኾነውን ጰራቅሊጦስን ይልክን ዘንድ የባሕርይ አባትኽን እግዚአብሔርን ማልደው፤ ለምነውም። መጥቶም ወደ እውነት ነገር ኹሉ ይመራናልና፤ በአፋቸው ውስጥ እውነት እንደሌላቸው እንደ ሌሎች መናፍስት የሐሰትን ነገር ከራሱ አንቅቶ አይናገርምና” (የዐፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል 1999፣ 3)።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.