[the_ad_group id=”107″]

እባካችሁ ስሙኝ! ጩኸቴንም ቀሙኝ!

እኔ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ነኝ፤ ደግሞም ክርስቲያን ኢትዮጵያዊም ነኝ። አገሬ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ፣ እንደ አንድ ባለ ዐደራ ክርስቲያንና እንደ ኢትዮጵያዊ ጩኸቴን መጮኽ፣ ከተሳካልኝም ጩኸቴን ለሌላው ማጋባት እፈልጋለሁ። የጩኸቴ ትኩረትም፣ “አገር አቀፍ የሰላም ግንባታ ተድበስብሶ የሚታለፍ ባለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ዜጎችም አስተሳሰባቸውን ከዚህ በታች በተገለጹት የሰላም ግንባታ መርሖች1 ሊፈትሹ እንደሚያስፈልግ” የሚጠቁም ነው።


የማኅበራዊ ግጭት ገጽታ

ማኅበራዊ ግጭት (social conflict) ከ1960ዎቹ (እ.አ.አ.) ገደማ አንሥቶ እንደ ሙያ ራሱን ችሎ መጠናት ይጀምር እንጂ፣ ክስተቱ የሰው ልጅ ጥንታዊነትን ያህል ዕድሜ ያስቈጠረ ነው።2 የማኅበራዊ ግጭቶች መነሻ እንደየቦታው የተለያየ ገጽታ ቢኖረውም፣ መሠረታዊ የሆኑ ሰብአዊ ምክንያቶቹ ተመሳሳይ ወይም አንድ ዐይነት ናቸው። የማኅበራዊ ግጭት መንሥኤዎች ናቸው የሚባሉትን በአጭሩ በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን። እነዚህም፡-

  • የመሠረታዊ ፍላጎት (Need) አለመሟላት
  • የርእዮት ዓለም (Creed) ልዩነት
  • ሥሥት (Greed) ናቸው

እነዚህን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች በጥንታዊውም ሆነ በዘመናዊ ዓለም ስናስተናግድ ኖረናል፤ ወደ ፊትም ማስተናገዳችን አይቀርም።

ማኅበረ ሰባዊ የግጭት ሰንሰለትን ወይም የማያቋርጥ የግጭት ዑደትን እንዴት ማራራቅ፣ ማዘግየት፣ ማቋረጥ ከተቻለም ማስቀረት ይቻላል? የሚለውን እንደሚከተለው ለመጠቆም እሞክራለሁ።

ማኅበራዊ ግጭት በባሕርይው ኸይዋች (organic) ነው። ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያከትማል፤ እንደ ሁኔታውም ዳግም ያንሠራራል ወይም በሌላ ጊዜ፣ በሌላ ዐይነት መልኩ ይገለጻል። ከተከሰተ በኋላ የሚኖረው ጥፋት ወይም ልማት በነገረ ግጭቱ ዐይነት፣ በባለድርሻዎቹ ዐይነት፣ ከሁሉም በሚበልጥ ደግሞ በአያያዙና በቅድመ መፍትሔ ስሌቱ መጠን እና ልዕቀት (the quality of conflict analysis) ይወሰናል።3

ይህ ጽሑፍ ሊያቆማቸው የሚፈልጋቸው ሁለት የሐሳብ ዐምዶች አሉት። የመጀመሪያው፤ በፍላጎት ወይም በግብ ልዩነት መንሥኤነት ግጭት ከተከሰተ በኋላ ልናመልጣቸው የማንችላቸው አራት ለውጦችን የምናስተናግድ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እነዚህም ለውጦች በግለ ሰብ፣ በግንኙነት፣ በመዋቅርና በባሕል ደረጃ የሚከሰቱ ናቸው። ለእነዚህ ለውጦች የሚኖረን ምላሽ፣ የድኅረ ግጭት ማኅበራዊ ኑሯችንን መልክ በጉልሕ ይወስነዋል። ሁለተኛው፤ እነዚህ ግጭት ያስከተሏቸው ለውጦች ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሔ የሚያገኙት ምሕረት፣ እውነት፣ ፍትሕ/ጽድቅ እና ሰላም ስፍራቸውን ሲይዙ ነው ይላል። እነዚህን በሁለት የተከፈሉ የሰላም ግንባታ ቅድመ ሁኔታዎች በመጠነኛ ዝርዝር እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።


አራቱ አይቀሬ ለውጦች

  1. በግለ ሰብ ደረጃ፦ ግጭት የሰዎችን ግላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ማንነት ይቀይራል፤ ከዚህም የተነሣ አመለካከት ይለወጣል፤ ተግባር ይቀየራል። በአጭሩ ከግጭት በፊት የነበርነው ሰዎችና ከግጭት በኋላ የምንኖረው ሰዎች የተለያየን እንሆናለን። ይህ ግንዛቤ ያላቸውና የሌላቸው ሰዎች ለግጭቱ ሂደት የሚያበረክቱት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ መለያየቱ አይቀርም። በሌላ አገላለጽ፣ የተከሰተው ግጭት ʻበእኔ ላይ ወይም በእኛ ላይ ለውጥ አስከትሏልʼ የሚል ዐመኔታ ያለው ግለ ሰብም ሆነ ቡድን ገና ከመጀመሪያው ግጭቱን የመፍታት ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል።
  2. በግንኙነት ደረጃ፦ ግጭት በፍጥነትም ሆነ በአዝጋሚ በሚያሻቅብበት ጊዜ ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው ግለ ሰቦች መካከል ነባር የተግባቦት መሥመሮች መልካቸውን ይቀይራሉ፤ አቋሞች የከረሩ ይሆናሉ። “እኔና እርሱ/እርሷ” ወይም “እኛ” እና “እነርሱ” የሚሉ ጎራዎች ይፈጠራሉ፤ መተማመንም ይቀንሳል። ከዚህም የተነሣ የተግባቦት መንገዶች ይለወጣሉ፤ የትብብር መንገዶች ይቀየራሉ፤ የውሳኔ አሰጣጥ መንገዶች በሌላ ይተካሉ። ይህንን ሁለተኛ አይቀሬ ለውጥ መቀበል ለመፍትሔ በሚደረገው ጥረት የተባባሪነትን መንፈስ ይሰጣል።
  3. በመዋቅር ደረጃ፦ ግጭት መዋቅሮችና ልዩ ልዩ ሥርዐቶች ላይ ተጽእኖ ያመጣል። ከቤተ ሰብ አንሥቶ እስከ ድርጅት፣ የማኅበረ ሰብ ወይም የኅብረተ ሰብ ግንኙነቶች የሚደራጁበት የኀይል አሰላለፎች ሁሉ ይቀያየራሉ። ከዚህም የተነሣ ማኅበራዊ ሁኔታዎች መልካቸውን ይለውጣሉ፤ ቅደም ተከተሎች ይቀያየራሉ፤ ተቋማዊ መዋቅሮች በሌላ ይተካሉ። እንዲህ ዐይነት ለውጦች ታምቀው በቆዩ ቅራኔዎች ድንገተኛ ፍንዳታ ወይም አዝጋሚ በሆነ ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ናቸው። በመዋቅር ደረጃ የሚከሰቱ ለውጦች በተለይ ብሔራዊ ገጽታ ካላቸውና የተከሰቱትም በድንገት ከሆነ፣ አጠቃላይ ማኅበራዊ ተቻችሎትን (social homeostasis) ያናጋሉ። ለምሳሌ፣ በቅርብ ዓመታት በአረብ አገራት የተከሰቱ ድንገተኛ ለውጦች አካባቢው ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዳይመለስ አድርጎታል።
  4. በባሕል ደረጃ፦ ባሕልን አስመልክቶ ዐመፅ/ኀይል ያለበት ግጭት ሲከሰት በዘመናት የዳበረ የባሕል ገጽታ አብሮ ይቀየራል። በሽማግሎችና ወጣቶች መካከል ያለ ግንኙነት፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል የሚኖር ግንኙነት፣ ወዘተ. መልኩን ይለውጣል። ከዚህም የተነሣ ባሕሉ የሚዋቀርባቸው አመለካከቶች ሁሉ መቀያየር ይጀምራሉ፤ መከባበርና መቀባበል/መቻቻል ስፍራቸውን ላለመከባበርና ላለመቀባበል ይለቅቃሉ። በመሆኑም፣ እነዚህን ለውጦች ማመንና መቀበል ወደ መፍትሔው ለመድረስ ግማሽ መንገድ የመጓዝን ያህል ይጠቅማል። የዚህ መሠረታዊ ሐሳብ የሚመነጨውም፣ “እያንዳንዱ ግጭት የሚያስከትለው ውጤት አለው” ከሚለው መርሕ ነው። ስለዚህ “ቀጣዩና አልቀጣዩ” (continuity and discontinuity) የትኛው ነው ብሎ መለየት የግድ ያስፈልጋል።

በአገራችን በየአጋጣሚው ጫፍ እየደረሱ የከሰሙት አገር አቀፍ
የእልቂት እምቅ ኀይላት የሚያመለክቱን አንድ ነገር፣ የሕዝብን ጨዋነትን ወይም የመንግሥትን ኀያልነት ሳይሆን፣ የመለኮትን ጣልቃ ገብ አትርፎት ነው ብዬ አምናለሁ። የሕዝብ ጨዋነት ያቆማል፤ የመንግሥትም ኀይል ይደክማል፤ ልክ መሆን ግን ይጠቅማል።


ባለንበት የማኅበረ ሰብ ክፍል (ቤተ ሰብ፣ መንደር፣ ትምህርት ቤት፣ የሃይምኖት ተቋም፣ መንግሥት) ግጭት ሲያጋጥመ፣ ግጭቶቹን ተከትለው ለሚመጡ ለውጦች ዕውቅና መስጠት የሁላችንም ኀላፊነት ሊሆን እንደሚገባ መስማማት ያስፈልጋል። የግጭቱን ደረጃ አጥንተን፣ ያስከተለውን ጕዳትና ጥቅም አገናዝበን የምናደርገው ርምጃ (interventions) ወይም የምንሰጠው የመፍትሔ መንገድ (resolution proposals) የግጭትን ዑደት/ሽክርክሪት ለመግታት በእጅጉ ያግዛል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ግጭቱ ባስከተለው ለውጥ የተነሣ የተፈጠሩትን ጕዳቶች በሚገባ ሳናገናዝብ ወይም በመሸፋፈን የምንሰጣቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ከመፍትሔነታቸው ይልቅ የዳግም ግጭት መፈልፈያነታቸው ያይላል። የብዙ አገሮች ያልተቋረጠ ግጭት ምክንያቱ ይኸው ነው። አገራችንም ከሌሎቹ አገራት የተለየች ልትሆን አትችልም።

በአገራችን ኢትዮጵያ የመንግሥታት ለውጥ በተደጋጋሚ ተደርጓል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በግለ ሰብ፣ በግንኙነት፣ በመዋቅር እና በባሕል ደረጃ ያሉ ለውጦች በላይ በላዩ፣ በፈጣን መልኩ እና ሥር በነቀለ ሁኔታ ተከስተዋል። እንደ ጋራ ውጤትም ከፍተኛ የማንነት ቀውስ አስከትለውብናል። ከዚህም የተነሣ በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ግጭታችን ባሕርይ ነባሩን ትውልድ ምን ዐይነት አገር ሲፈጥር እንደ ኖረ ባለማወቅ ግራ ተጋብቶ በኀዘን ወደ መቃብር እንዲሄድ እያስገደደው ነው። መጪውም ትውልድ ቢሆን፣ ተሠርተው ባላለቁና በተዘባራረቁ የታሪክ ወለለቶች (echoes of conflicting histories)፣ “ማነኝ? የማን ነኝ?” በሚል የማንነት ቀውስ ውስጥ ተይዞ አለ።

በአጭሩ ከላይ የተጠቀሱት አራት የግጨት ድኅረ ለውጦች በአግባቡ ካለመያዛቸው የተነሣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሽከረከር፣ አሰልቺ የግጭት ዑደት ውስጥ ገብተናል። አያያዛችን እንዲሁ ከቀጠለም በከረሩና በተወሳሰቡ አጥቢያዊ፣ ክልላዊና ብሔራዊ የግጭት ዑደቶች ውስጥ መዝለቃችን አይቀርምለን። ይህ ክፉ ትንቢት አይደለም፤ የክስተቶችን ሳቢያና ውጤት (cause and effect) ስናይ የምናገኘው ተጨባጭ እውነታ ነው።

በዚህ ዘመን በአፍሪካና በእስያ የነባር ግጭቶችን ግርሻዎች አይቶ ያልተማረ፣ የእነዚህን አገሮች አስከፊ ተግባር የማይደግምበት ምንም ምክንያት የለም። በአገራችን በየአጋጣሚው ጫፍ እየደረሱ የከሰሙት አገር አቀፍ የእልቂት እምቅ ኀይላት የሚያመለክቱን አንድ ነገር፣ የሕዝብን ጨዋነትን ወይም የመንግሥትን ኀያልነት ሳይሆን፣ የመለኮትን ጣልቃ ገብ አትርፎት ነው ብዬ አምናለሁ። የሕዝብ ጨዋነት ያቆማል፤ የመንግሥትም ኀይል ይደክማል፤ ልክ መሆን ግን ይጠቅማል።

በአገር ደረጃ የተከሰቱና ሊታጠፉ የማይችሉ እንዲሁም መልሰው እንደ ነበሩ ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮች አሉ። ብዙዎቻችን እነዚህን ነገሮች የተረዳን ለመሆናችን ጥርጥር ውስጥ የሚከትቱን የታሪክ ተቸካይነት (Nostalgia) ይታይብናል።

ታዲያ ምን እናድርግ? የአገራችንን ነባርና አሰልቺ የሰላም ማጣት ችግር በሚከተሉት ባለ አራት ምሰሶ እና ባለ አንድ ድምድማት መፍትሔ መስጠት ቢረፍድም መቅረት የሌለበት ነው እላለሁ። እነዚህ መፍትሔዎች እዚህ በአጭር ይቅረቡ እንጂ ዝርዝራቸው ሰፊ እንደ ሆነና ወደ ተግባርም ለማምጣት እልህ አስጨራሽ እንደሆኑ እገነዘባለሁ። ይሁን እንጂ ዘመኑን ሁሉ ለጦርነት የተደራጀና የተጋ ሕዝብ ለሰላም ግንባታ ቢረባረብባቸው በጊዜ፣ በኀይል እና በአገር ጥሪት ሳንባክን ታሪክ መሥራት እንችላለን። አንድ አገር ዘመናትን ያስቆጠረ ግጭት ወለድ ቀውስ ውስጥ ስትገባ የሚጠብቋት አማራጮች አራት ናቸው ይላሉ የዓለም የሰላም ሎሬት ተሸላሚው ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ። በቀል፣ በክስ/በሕግ ተጠያቂ ማድረግ፣ ምንም አለማድረግ እና እውነትን መሠረት ያደረገ ብሔራዊ እርቅ፤ የእኚህ ሰው ምርጫ በአራተኛ ደረጃ የተጠቀሰው ምርጫ ነው።4


ባለ አራት ምሰሶ እና ባለ አንድ ድምድማት መፍትሔ

በርካታ አዎንታዊ የለውጥ ሐሳቦች ከተለያዩ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ የታመነ ነው፤ ይሁን እንጂ በብሔራዊ ደረጃ የሚያስፈልጉ ለውጦች የሚከተሉት አራት ወሳኝ ዐምዶች ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባል። እነዚህ አእማድ መፍትሔዎች በሰላም ግንባታ ምሁርነታቸው ታዋቂ የሆኑትና ዓለም አቀፍ የላእላይ መዋቅር ግጭቶች ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ/አንጋሪ (macro level conflict mediator)፣ ጆን ፓል ሌደራክ የሚጠቁሟቸው የሰላም ግንባታ መርሖች ናቸው። እነዚህ አራቱ መርሖዎች፡- እውነት፣ ፍትሕ ወይም ጽድቅ፣ ምሕረት እና ሰላም ናቸው። የእነዚህ አራት መርሖዎች መሠረት መዝሙረ ዳዊት 85፥10 ነው። “ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው፤ ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።”


ምሕረት

ምሕረት ርኅራኄ፣ አዲስ ጅማሬ፣ ዳግም መቀበል ነው፤ የጸጋ ሐሳብ ነው። ምሕረት ባይኖር ጤናማ ግንኙነት አይታሰብም፤ ርኅራኄ ከሌለ ግንኙነታችን አይፈወስም። ምሕረት ሲታሰብ ሦስት ነገሮች ይኖራሉ፡- የተበደለ፣ በዳይ እና በደል። በሌላ አገላለጽ ጎጂ፣ ተጎጂና ጕዳት ይኖራሉ። ምሕረት ያለፈውን መርሳት ማለት ሳይሆን፣ ተበዳይ ጕዳቱን መነሻ አድርጎ ለበቀል አይነሣሣም ማለት ነው። ይህንን ጽንሰ ሐሳብ በሰፊው ለመረዳት የሕዳሴ ፍትሕ (restorative justice) መሠረታዊ ግንዛቤን ማግኘትን ይጠይቃል። ምሕረት ብቻውን ከሆነ ደረቅ ጡጦ ነው፤ ማባበያ ሽፋን ነው። ወዲያው ፈጥኖ ብን ይላል። ለብቻው አይቆምም፤ ሌላ ምሰሶ ይፈልጋል። በምሕረት ሰጪውም ሆነ በምሕረት ተቀባዩ ዘንድ ከዳግም በደል ነጻ የሆነ ግንኙነት የሚፈጠርበትን መንገድ እንዲሁም ካለፈ በደል ካሳ ጋር የተገናኙ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል።

ምሕረት ብቻውን ከሆነ ደረቅ ጡጦ ነው፤ 


እውነት 

እውነት፣ “ነው” ማለት “ነው” ሲሆን፣ “አይደለም” ማለት “አይደለም” ማለት ሲሆን፣ ታማኝነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፤ ደግሞም ታማኝነት ከወለደው መተማመን የተነሣ ለመጠቃት እስከሚያደርስ ግልጽ (ተጋላጭ – vulnerable) መሆን ማለት ነው። እርስ በርስ ያለ ለበጣ እንደወረድን መገናኘት ስንችል እውነት አለ ይባላል። እውነት በሌለበት የእርስ በርስ ግጭቶች ሊፈቱ አይችሉም። ዴዝሞንድ ቱቱ (Truth and Reconciliation Commission) በሚል ኮሚሽን ያቋቋሙት፣ እውነቱ ያልተገለጠበት የፍትሕ ሥርዐት ሕዝቦችን እንደማያቀራርብ በማወቃቸው ነው። በሰላም ግንባታ ሒደት ውስጥ እውነት እንዲገለጥ መፈለግ ክስ ማቅረብ አይደልም፤ እውነት ተናጋሪውም ከለላ (amnesty) ሊደረግለት ይገባል። የሒደቱ ግብ የወደፊት የጋራ ኑሮ ነውና። ይሁን እንጂ እውነት ብቻውን ሲሆን ደግሞ እርቃን ያስቀረናል፤ ያስጠቃናል። እውነት ጕዳት፣ በደል ወይም ስሕተት እንደደረሰብኝ ሲታወቅልኝና ሕመምና ኪሣራዬን ሰው ሲያውቅልኝ እውነቱ ተገለጠ እላለሁ። መጽሐፉ ግን “ምሕረትና እውነት ተገናኙ” ስለሚል እውነት ያለ ምሕረት አዲስ ጅማሬ አይሰጠንም። ላለፈው በደል ሃውልት ሊቆምለት ቢችልም፣ አሁን አብሬ ለምኖረው ግን እንቅፋት መሆኑ የለበትም። እንዲህ እንዲሆን ደግሞ ተጨማሪ ምሰሶ ያስፈልጋል፤ ይህም ፍትሕ ወይም ጽድቅ ነው። አንዳንዶች “ፍትርት” ይሉታል (ፍትሕና ርቱዕ) አንድ ላይ እንዲሆኑ በማሰብ።


ፍሕት ወይም ጽድቅ

ትርጓሜው እኩላዊ ዕድል፣ ነገሮችንም በትክክል ማየት፣ ስሕተትን ማረም፣ ጉዳት መፈወስ፣ ሚዛንን ማስተካከል ነው። ያለ ፍትሕ ሰባሮች ነን። ፍትሕ የግለ ሰቡንም ሆነ የቡድኑን መብት ፈላጊ ነው። ይህም በማኅበረ ሰብ መዋቅር፣ ከቤተ ሰብ እስከ ኅብረተ ሰብ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽ ነው። ከፍትሕ ፍላጎት የተነሣ ማኅበራዊ መዋቅር ደጋግሞ ይቀያየራል። የተጎዳ ብዙ መልክ ያለው ካሣ ይከፈለዋል። በማኅበራዊ በደል የተጠቁ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች መልሰው አጥቂ ከሚሆኑበት ምክንያቶች አንዱ በደረሰባቸው የስሜት ስብራት (trauma) ከፍትሕ የሚመነጭ ፈውስ ባለማግኘታቸውም ጭምር ነው። የመጣው ሁሉ ነባሩን ማፍረሱን እንጂ፣ መልሶ የሚገነባው በዛው ፍርስራሽ መሆኑን አላስተዋለም። ስለዚህ ቤቱ ዳግም ተሠርቶ ግማሽ ሲደርስ የድሮው ችግር ብቅ ማለት ይጀምራል፤ ሌላ አፍራሽ ደግሞ ይከሰታል። ባፈረሰው ሸክላ መልሶ አዲስ ልሥራ የሚል። ስለዚህ ከአሰልቺው አፍርሶ ግንባታ ዑደት ይኸው አልወጣንም።

ፍትሕ ለብቻው ሕይወት የለውም፤ ደረቅ ነው፤ ማለሳለሻ ፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጽድቅ/ፍትሕና ሰላም ተስማሙ ወይም ተሳሳሙ ስለሚል፣ ፍትሕ ያለ ሰላም ጓደኛ ዐልባ ነው። ሰላም የሌለበት ፍትሕ የፍራቻ፣ የሥጋት ድባብ አያጣውም፤ እውነተኛ ሰላም ትሥሥራዊ ነው፤ የደኅንነትና የጤና ስሜትን ያስከትላል።


ፍትሕ ለብቻው ሕይወት የለውም፤ ሰላም የሌለበት ፍትሕ የፍራቻ፣ የሥጋት ድባብ አያጣውም፤


ሰላም

ትርጕሙ ብዙ ነው። በጥቅሉ የሕዝቦችና የዓለም ጦርነት ዐልባ ኑሮ፣ እንዲሁም በሰዎች መካከል በግልና በቡድን የተረጋጋ ግንኙነት መኖር፣ ሕዝባዊ ሥርዐትና ሲቪላዊ መረጋጋት መስፈን ነው። ኅሊና ከብስጭት፣ ከጭንቀት ነጻ ሲሆን፣ ሰላም አለ ይባላል። የሰላም ጽንሰ ሐሳብ ፍትሕንና ሁሉን አቀፍ ማኅበረ ሰብን የሚያካትት ብዙ ትርጕምን የያዘ ሲሆን፣ የትርጉሙም ወሰነ ስፋት ቊሳዊና ምግባራዊ ስምሙነትን የያዘ ነው። ስምሙ፣ አንድነት ነው፤ ጤና ነው፤ መከባበርና መጠባበቅ ነው። ሰላም ግን የሌሎች ነገሮች ውጤት ነው፤ ብቻውን አይገኝም። ሰላም ልጁ ቢሆን፣ አንቀልባው ፍትሕ ነው፤ ጡጦው ምሕረት ነው፤ ወተቱ እውነት ነው።

እንግዲህ የእነዚህ ሁሉ እናት ማን ናት ቢባል እርቅ ናት። እነዚህን አራት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስብርባሪ አድርጎ አይደለም የሚያቀርብልን፤ ተገናኙ፣ ተስማሙ፣ ተሳሳሙ ነው የሚለን። በስብርባሪ ለሚፈልጓቸው ውጤታቸውን አያገኙአቸውም። ሁላችን ከማጀት እስከ አደባባይ እነዚህን ነገሮች ለየብቻ ነው የምንፈልጋቸው፤ ስለዚህ አናገኛቸውም!!! ሁሉ ይጮኻል፤ እውነት፣ ስላም፣ ፍትሕ፣ ወዘተ. ይላል፤ ግን በብጥስጣሽ አይገኙም። በባሕርያቸው ወጥ (monolithic) ናቸው። እውነተኛ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ያለ ምንም ምክንያት አይደለም እነዚህን አራቱን አንድ ላይ አስሮ “ተስማሙ”፣ “ተገናኙ” ወይም “ተሳሳሙ” የሚለን።


እርቅ

ለእነዚህ አራት ነገሮች ማኅበራዊ ሥፍራ ወይም መገናኘት ምክንያት እርቅ ነው። ʻታዲያ የት ልናገኛቸው ነው? የት ልናስማማቸው ነው? የት ልናሳስማቸው ነው?ʼ ቢባል፣ ʻአዲስ ኪዳናዊ መገኛቸውስ ምንድን? ወይም የት ነው?ʼ ብንል የምናገኘው እርቅን ነው። ይህ ቃል ሦስት ፊደል ይኑረው እንጂ፣ እንኳን ለአገር አቀፍ ጕዳይ ይቅርና በግለ ሰቦች ደረጃ ለሚደረጉ ግጭቶች እንዴት እልህ አስጨራሽ እንደ ሆነ ጸሐፊው ይገነዘባል። እንደ ሕዝብ ለመቆም ግን ይህ የግድ አስፈላጊ ነው። አገር በጦር ሰራዊት ተደራጅቶ፣ ብዙ መእዋለ ነዋይና የሰው ኀይል አሰልፎ ለጦርነት እንደሚወጣ እንዲሁ፣ ታላቅ ዝግጅት ዘመናዊና ባሕላዊ ዕሴቶች የተደባለቁበት ርብርቦሽ ይጠይቃል። ይህ ዐይነቱ ዘመቻ በሰላም ግንባታ ባለሙያዎች ዘንድ “ስልታዊ የሰላም ግንባታ” (Strategic Peace-building) በመባል ይታወቃል። ሰላም ግንባታ በአጠቃላይ ስለ ሕዝቦችና ስለ ግንኙነታቸው ነው፤ ይህም እርስ በርሳቸውና ከመንግሥት ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ይመለከታል። የሰላም ግንባታ ሥራ ይህንን ግንኙነት ማደስ እና ውጤቱ አስተማማኝነት ያለው እንዲሆን ማድረግ ነው። የዓለም መንግሥታትም የወቅቱ ጩኸት ይኸው ቃል ነው፤ አንዳንድ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት በ2014 የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ሁለት መቶ ጊዜ የተጠቀሰ ቃል “እርቅ” የሚለው ነው።

ይህንን መስማት ለምን ያስፈለገናል? አጭሩ መልስ፣ ወደ ፊት መሄድ የሚቻለው አራቱ በአንድነት በእርቅ ሲገናኙ ብቻ ስለ ሆነ ነው። እርቅ ውስጠ ብዙ ነው፤ ስለ እርቅ ሲነሣ ስለ ይቅርታ፣ ካሳ፣ የኀይል አሰላለፍ፣ የራሱ የእርቁ ሂደት እና የመሳሰሉትን ቅደም ተከተሎች መጠበቅ ይጠይቃል። በረጅም ዓመት ጊዜ ውስጥ ማኅበራዊ ትሥሥሩ ሲፈርስ የኖረን አገር፣ በመሠረተ ልማት (በመንገድ፣ በድልድይ፣ በሕንጻ፣ ወዘተ.) ግንባታ ብቻ መልሶ ማቆም ይቻል ይሆን? እንጃ! መሠረተ ልማቱ ለአገር እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ትሥሥር እንዲኖር ከተፈለገ ግን ማኅበራዊ ጥያቄዎችን መመለስ መቅደም አለበት። ያኔ ፀሓይ ትወጣለች። እኛ የገነባውን መጪው አያፈርሰውም!

ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው፤ ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።
መዝሙረ ዳዊት 85፥10


[1] የጽሑፌይዘቱናአወቃቀሩየተመሠረተው፣“Lederach, J.P. (1997).Building peace: Sustainable reconciliation in divided societies. Washington, D.C.: United States, Institute of Peace Press.” በተሰኘው ሥራ ላይ ነው።

[2] Ramsbotham, Woodhouse, and Miall, Contemporary Conflict Resolution,

[3] Ho-Won Jeong, Understanding Conflict and Conflict Analysis, SAGE Publications, 2008 

[4] Video: (At the Nobel Peace Laureates Conference, University of Virginia, 5-6 November 1998

[5] Andrew Tomlinson Director, Reconciliation – transforming relationships in divided societies, Quaker UN Office, New York

Share this article:


My Father’s Confession: Jesus and the OLF

The Oromo Liberation Front (OLF) has returned to Ethiopia saying it will continue its struggle peacefully after years of armed fighting from outside. The long-time leaders and icons of the movement have been welcomed by many on September 15, 2018 after many years of exile. Sadly, my father didn’t live long enough to see this day.

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.