[the_ad_group id=”107″]

የመጽሐፍ ቅኝት

"መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ"

ርእስ:- መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ:- ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት ይነበቡ? እንዴት ይተርጐሙ? እንዴት ይተግበሩ?
ጸሐፊ:- ምኒልክ አስፋው
የታተመበት ቀን:- 2009 ዓ.ም.
የታተመበት አገር:- ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ
የገጽ ብዛት:- 457


መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያኖች ዘንድ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተደርጎ የሚወሰድ ጥንታዊ ሰነድ ነው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ይኸው መጽሐፍ እየተነበበና እየተተረጐመ እስከ አሁን ዘልቋል። ታዲያ፣ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ሰነድ ስለ ሆነ እንዴት እናንብበው? እንዴትስ ከሕይወታችን ጋር እናዛምደው?’ የሚሉ ጥያቄዎች ሁል ጊዜ የሚነሡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን እና አሁን እኛ ባለንበት ዘመን መካከል ያሉ የባህል፣ የታሪክ፣ የማኅበራዊ ሕይወትና ሌሎችም ልዩነቶች መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብብ በጥንቃቄ እንጂ በዘፈቀደ መሆን እንዴለለበት የሚጠቁሙን ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ሰነድ ስለ ሆነ በተጻፈበትና በእኛ ዘመን መካከል የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ሰፊ ልዩነት አለ። ከዚህም የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስን ተገቢ በሆነ መልኩ ለመረዳት እነዚህን ክፍተቶች ማጥበብ ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ ሥነ አፈታትን አስፈላጊነት የግድ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ሕይወት ጋር ከማዛመዳችን በፊት፣ በተጻፈበት ዐውድ ውስጥ መረዳት አለብን፤ ይህም ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ለቀዳማይ ተደራሲያኑ ያልተናገረውን ለእኛ አይናገርም እንደ ማለት ነው። ለዚህ ነው የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚዎችና አንባቢያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊና ሥነ ጽሑፋዊ ዐውድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት።

ምኒልክ በዚህ ሥራው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ኀላፊነት ባለው መንገድ እንዴት ማንበብና ከዕለት ተ’ለት ሕይወታችን ጋር ማዛመድ እንዳለብ ያስረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡ/የሚያጠኑ ሰዎች የተለያዩ የአፈታት ዘዴዎችን እንደሚከተሉ ይታወቃል። ምኒልክ መጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ጽሑፋዊ እንዲሁም ታሪካዊ ዐውዱን ባገናዘበ መልኩ እንዴት ማንበብ እንዳለብን ከማሳየቱም በላይ፣ “ክርስቶስን ያማከለ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜ (Christocentric hermeneutics) ወደ ትክክለኛው አምላካዊ ሐሳብ ለመድረስ ያጋዛል የሚል ብርቱ ሙግት ያቀርባል (ገጽ 14-15)።

የመጽሐፉ አወቃቀር

መግቢያና መደምደሚያን ሳይጨምር መጽሐፉ በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ትርጓሜ አስፈላጊነት የሚያብራራ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይም ሆነ የተጻፈበት ዘመን የትርጓሜን አስፈላጊነት ያሳያሉ። መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት ያሉት መጽሐፍ ነው። መለኮታዊናቱ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት መጻፉ ሲሆን፣ ሰብአዊ ባሕርይው ደግሞ በሰው ልጆች ቋንቋ እና በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ መጻፉ ነው። ይህ በመሆኑም ምክንያት የቋንቋ ሕግጋትን ባገናዘበ መልኩ መፍታት እንደሚያስፈልግ በዚህ ምዕራፍ ተብራርቷል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና መገለጥ ትንተና የቀረበበት ነው። እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ራሱን የገለጠ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ከገለጠባቸው መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። በዚሁ ክፍል ውስጥ ከመገለጥ በተጨማሪ ቀኖና (canon) ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ‘መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ስንት መጻሕፍትን ይዟል?’ የሚለው ጉዳይ የተለያዩ ቤተ እምነቶች የሚለያዩበት ነው። ልዩነቱን መገንዘብ እንችል ዘንድ በኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ስላሉ የቀኖና ልዩነቶች ሰፋ ያለን ትንታኔ አቅርቧል።

ሦስተኛው ምዕራፍ የትርጓሜ ሥልቶች የተዳሰሱበት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከትውፊት ጋር ያለው ተዛምዶ፣ የአይሁድ የትርጓሜ ስልት፣ የቤተ ክርስቲያን አበው ትርጓሜ ስልቶች ሰፊ ትንታኔ አግኝተዋል። ከቤተ ክርስቲያን አበው መካከል እንደ ፖሊካርጶስ፣ ቀሌምንጦስ፣ አግናጤዎስ፣ አርጌንስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ አውግስጢኖስ ያሉት የትርጓሜ ሥልቶች ለማሳያነት ቀርበዋል። በዚሁ ክፍል ሌላው ትልቅ የሆነ ትኩረት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜ ሥልት/ባህል (የአንድምታ ትርጓሜ) ነው። የአንድምታ ታሪካዊ አመጣጥና የሥነ አፈታት መንገድ በስፋት የተብራራ ሲሆን፣ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመውሰድ አንደምታው እነዚህን ክፍሎች እንዴት እንደሚፈታቸው በምሳሌነት ቀርበዋል። በታሪክ ውስጥ የነበሩና አሁንም ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን ሁል ጊዜ አንድ ዐይነት የአነባበብ መንገድ አይከተሉም፤ ስለዚህም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደተረዱት መገንዘብ የእኛን አነባበብ በመቅረጽ ገረድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ምዕራፍ አራትና አምስት የመጽሐፉ ወሳኝ ክፍሎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ምዕራፎ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽን (literary genres) ባገናዘበ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መፍታች እንደሚቻል የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽ ወይም ዘውግን የያዙ መጻሕፍት ስብስብ ነው። “ልክ ሰዎች የየራሳቸው መልክና ገጽ እንዳላቸው ሁሉ፣ ጽሑፍም የራሱ መልክና ገጽ ወይም ጾታ አለው።” (ገጽ 151)። በዚህም መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕግ፣ የታሪክ፣ የትንቢት፣ የግጥም፣ የቅኔ፣ የደብዳቤ፣ የአቡቀለምሲስ (ራእይ) የመሳሰሉ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጾችን እናገኛለን።   

በምዕራፍ አራት ውስጥ ለኦሪት መጻሕፍት፣ ለታሪክ/ትረካ መጻሕፍት፣ የጥበብ/ቅኔ እንዲሁም የትንቢት መጻሕፍት የተለየ ትኩረት ተሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን እያንዳንዱን የሥነ ጽሑፍ ቅርጾች ባሕርይ በማብራራት ተገቢ የሆኑ የአነባበብ መንገዶችን (ትርጓሜያዊ ሥልቶችን) ይጠቁማል። ክፍሉ ንድፈ ሐሳብን ወይም መርሖዎችን ብቻ የሚዘረዝር ሳይሆን፣ ተግባራዊ የሆኑ ምሳሌዎችንም ያካተተ ነው። 

ምዕራፍ አምስት ትኩረቱ የአዲስ ኪዳን መጻሓፍት ላይ ነው። በአዲስ ኪዳን የሚገኙ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ቅርጾች እንዴት መፈታት አለባቸው የሚለውን ከማሳየቱ በፊት፣ መጽሐፉ አዲስ ኪዳንን ለመረዳት ወሳኝ የሆኑ ታሪካዊ ዳራዎችን ያሳያል። በዚህም ክፍል ይሁዲነት፣ የይሁድ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድኖች ተዳስሰዋል። በመቀጠል ወንጌል፣ መልእክቶችና የራእይ መጻሕፍት የሥነ ጽሑፍ ዐይነታቸውን ባገናዘበ መልኩ እንዴት ሊፈቱ እንደሚገባቸው ትንተና ቀርቦባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ ኪዳን ታሪካዊና ማኅበራዊ መቼት አብሮ ተካትቷል። በእነዚህ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ተመሳሳይ የሥነ ጽሑፍ ቅርጽ ያላቸው መጻሕፍት በአንድ ላይ በማድረግና የሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽ ባሕርያትን በማጉላት ትንታኔ የቀረበበት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ክፍል በምሳሌዎች የተሞላ ነው።

የመጨረሻው ምዕራፍ ስድስት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በመፍታት ሂደት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሚና ምን እንደ ሆነ ውይይት የተደረገበት ነው። ይህንንም ለማሳየት “መገለጥ”፣ “አብርሆት” እና “ትርጓሜ” የሚሉ ቃላት ተብራርተዋል። መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ሂደት ውስጥ ጥናትን እንደማይተካ ወይም እንደማይከለክል ተመላክቷል።

ብይን ስለ መጽሐፉ

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ መጽሐፉ የወንጌላውያን አማኞችን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ትርጓሜን የተከተለ ቢሆንም፣ የኦርቶዶክሳውያንና የካቶሊካውያን ትርጓሜ ስልቶች በቂ ስፍራን አግኝተዋል። ይህ የመጽሐፍን አድማስና ተደራሽነት ከማስፋቱ በተጨማሪ፣ አንባቢያን ሥነ አፈታትን ሰፋ አድርገው እንዲመለከቱት ያስችላቸዋል። መጽሐፍ ቅደስ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት በተለያዩ ቤተ እምነቶች በመነበብ ላይ ያለ መጽሐፍ ነው፤ ስለዚህም ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ለዚህ የበለጸገ የትርጉም ባህል ዕውቅና መስጠት አለበት።

ሌላው የመጽሐፉ ብርቱ ጎን ዐውዳዊ መሆኑ ነው። ጸሐፊው መልእክቱን ተደራሽ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሥነ አፈታት መንገድ አቅርቦልናል። ይህም ሥነ አፈታትን ከምዕራባውያን የወረስነው ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ሲተገበር የነበረ እንደ ሆነ የሚያስገነዝበን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽ በሚተነትንበት ክፍል ሥር፣ ለተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ቅርጽ ማሳያ ይሆኑን ዘንድ ብዙዎቻችን ከምናውቃቸውና አገር በቀል ጸሐፍት ከሆኑት ሥራዎች መካከል በመጥቀስ ሊያስረዳን ሞክሯል። እነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ዳኛቸው ወርቁና የመሳሰሉት እንደ ማሳያነት የቀረቡ ሥራዎች ናቸው።

መጽሐፉ በምርምር ላይ የተመሠረተና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ምሁራን ሥራዎች በስፋት ያጣቀሰ ነው። ይህ ደግሞ ጸሐፊው ለተለያዩ ዕይታዎች ክፍት እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ የራሱን አቋም ከሌሎች ዕይታዎች ባንጻሩ በግልጽ እንዲያስቀምጥ አድርጎታል።

መጽሐፉ የቃላት መፍቻ እና የቃላት ማውጫ (Index) ተዘጋጅቶለት ቢሆን ኖሮ ለአንባቢያን የበለጠ ዕገዛ ያደርግ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ የፊደል ግድፈቶች ተስተውለዋል። በቀጣይ ዕትም እነዚህ እንከኖች ተስተካክለው እንደሚቀርቡ እምነቴ ነው። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ዕትም በአሜርካን አገር የታተመና በአገር ቤት ገበያ ላይ የሌለ መሆኑ፣ ለሁሉም አንባቢያን እንዳይደርስ አድርጎታል። ስለሆነም ለአገር ቤት አንባቢያን በቶሎ የሚደርስበት መንገድ እንዲመቻች ዐደራን አስቀድሜ እጠይቃለሁ።

መጽሐፉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሥነ አፈታት ትምህርት መግቢያ መማሪያነት እንዲያገለግል ሆኖ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጀ ነው። ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄና በኀላፊነት ማንበብ የሚፈልጉ ሁሉ ቢያነብቡት በእጅጉ ይጠቀማሉ።

ወንድማችን ምኒልክ አስፋው እንዲህ ዐይነት ሥራ ለንባብ በማቅረቡ በእጅጉ እያመሰገንሁ፣ ‘እንኳን ደስ አለህ!’ ልለው እወድዳለሁ። ሌሎቻችንም የእርሱን ፈለግ በመከተል በምርምር ላይ የተመሠረተ፣ ዐውዳዊ ገጽታ ያለው እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ መጽሐፍ እንድንጽፍ እግዚአብሔር ይርዳን። 

Share this article:

Humanity

“Our own being is torn apart between reason and emotion. Our identity is stranded in a furious battle between spiritualism and carnalism. Our personality is stretched between holism and reductionism. Is this some sort of a spectrum or a continuum?”

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.