[the_ad_group id=”107″]

መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ

በዘመናችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምስባኮች ላይ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስም መጥራት የተለመደ ቢሆንም፣ ሕዝበ ክርስትያኑ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ጠንቅቆ ያውቃል ለማለት አስቸጋሪ ይመስላል። መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ ግልጽ አስተምህሮ ያለም አይመስልም። ለአንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ ተአምራት ማድረጊያ ኀይል፣ እንዲሁም በጨርቅ ተደርጎ እና በጠርሙስ ታሽጎ የሚወሰድ ትንግርት መፍጠሪያ ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ ማነቃቂያ እና ተሃድሶ የሚያመጣ እሳት ወዘተ. ነው።

የክርስትና እምነት መሠረት የአሓዱ ሥሉስ አምላክ አምልኮ መሆኑ እሙን ነው። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የዚህ አሓዱ ሥሉስ አምላክ አንዱ አካል ነው። ይሁን እንጂ የማንነቱን ያህል በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተገቢውን ስፍራ አልተሰጠውም፣ አሊያም ብዙዎች በመንፈስ ቅዱስ ስም ብዙ አስደንጋጭ እና አስነዋሪ ነገሮችን ፈጽመዋል። በዚህች አጭር መጣጥፍ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የነበረውን ሚና፣ በተለያዩ ዘመናት በመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ እና ልምምድ ላይ የተነሡ የተለያዩ ኑፋቄዎችን በወፍ በረር ተመልክተን፣ በዘመናችን ያሉትን በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በእግዚአብሔር ቃል እንገመግማለን።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በእግዚአብሔር አብ እና በእግዚአብሔር ወልድ አስተምህሮዎች ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠ እና ብዙ ውይይቶች የተካሄዱባቸው መሆኑ ግልጽ ነው። በደፈናው ለተመለከተው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ በቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች እና ታሪክ የተዘነጋ ይመስላል። ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ስለ እግዚአብሔር ወልድ የተለያዩ ጉባኤዎችን ሲያካሄዱ፣ አጽንዖት ሰጥተውትም ባይሆን በእግረ መንገዳቸው የመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮን ነካክተው ዐልፈዋል።

ቅድመ ኒቂያ ዘመን

በቅድመ ኒቂያ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከሆኑት ከአሌክሳንድሪያው ቀሌመንጦስ እና ከአንጾኪያው ቴዎፍሎስ ጽሑፎች መረዳት እንደሚቻለው የእግዚአብሔር አብን፣ የእግዚአብሔር ወልድን እና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መለኮትነት የተረዱ መሆናቸውን መመልከት ይቻላል። እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በአካል ሦስትነታቸው፣ እንዲህ በባሕርይ አንድነታቸውን ለማሳየት “ሥላሴ” የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው በቅድመ ኒቂያ ዘመን የኖረው ጠርጠሉስ (ተርቱልያን) የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት ነው። ጠርጠሉስ በዚህ ቃል አማካይነት የክርስትና እምነት የአሓዱ አምላክ አምልኮት እንጂ የብዝኀ አምላክ አምልኮ አለመሆኑን አሳይቷል።

የጉባኤ ኒቂያ ዘመን

የኒቂያ ጉባኤ መነሻ ምክንያት የሆነው አርዮስ የተባለ የኑፋቄ መምህር ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በባሕርይ አንድ ያልሆኑ እና ፍጡራን ናቸው ብሎ በማስተማሩ ምክንያት ነው። በመጨረሻም ለአሪዮስ መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሔር ወልድ የተፈጠረ፣ በተፈጠረ አካል የተፈጠረ ፍጡር (የፍጡር ፍጡር) ነው። የአሪዮስ ኑፋቄያዊ አስተምህሮ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ተወግዟል።

ድኅረ ጉባኤ ኒቂያ ዘመን

ከኒቂያ ጉባኤ በኋላም መቅዶንዮስ (Macedonius) “መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ብቻ ነው” የሚለውን የአርዮስን አስተምህሮ እርሱም ማስተማሩን ቀጥሏል። ለዚህም ድርጊቱ ምክንያት ተደርጎ ብዙ ጊዜ የሚነሣው በኒቂያ ጉባኤ ላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ አካልነት በግልጽ ባለመቀመጡ ምክንያት ነው። ስለዚህም በ385 ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ በተደረገው ጉባኤ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ከፍተኛ ክርክር ነበር። በዚህኛው ጉባኤ ሦስቱም የሥላሴ አካላት በባሕርይ አንድ መሆናቸው በግልጽ ተቀምጧል።

የመካከለኛው ዘመን

በመካከለኛው ዘመን በመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ ላይ የነበረው ውዝግብ፣ ʻመንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ ወይስ ከአብ እና ከወልድ የሚሰርጽ ነው?ʼ የሚል ነበር። ይህም ቤተ ክርስቲያንን በሁለት ጎራ ከፍሏት ነበር። የምሥራቋ ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ ይሰርጻል የሚለውን የጉባኤ ኒቅያ አቋም ስታጸና፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ ይሰርጻል የሚለውን የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በኑፋቄነት ስትፈርጀው ኖራለች። የምዕራቧ ቤተ ክርስቲያንም የምሥራቋን በዚህ አስተምህሮ ትኮንናለች። ይህ በምሥራቅ እና በምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የልዩነት ጅማሬ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ቅድመ ተሓድሶ ዘመን

በቅድመ ተሓድሶ ዘመን መንፈስ ቅዱስ የሚሰርጸው ከማን ነው? የሚለው ውዝግብ ሰፍቶ እና ጎልብቶ፣ የምሥራቋን እና የምዕራቧን ቤተ ክርስቲያን በ1054 ለሁለት ወደ መክፈል አመራ። ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መከሰቱ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጉዳት እስከ አሁን ድረስ ይሰማል።

የፕሮቴስታን ተሓድሶ ዘመን

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቅድመ ተሓድሶ ዘመን ከቅዱስ አውግስጢኖስ ሐሳብ ዞር በማለት የቶማስ አኳይናስን የሥነ መለኮት አስተምህሮ የቤተ ክርስቲያንቷ የእምነት አቋም ምሰሶ አድርጋ ይዛ ነበር። ይሁን እንጂ በፕሮቴስታንት ተሓድሶ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በቅድመ ተሓድሶ ዘመን ተዘንግቶ ወደ ነበረው ወደ የቅዱስ አውግስጢኖስ ሐሳብ የተመለሰችበት ዘመን ነው። ሆኖም በፕሮቴስታንት የተሓድሶ ዘመን ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቦ መረዳት ላይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠበት ዘመን ከመሆኑ የተነሣ፣ እንደ ማርቲን ሉተር ያሉት የፕሮቴስታንት የተሓድሶ አራማጆች፣ “አንድ ሰው በክርስቶስ የሚያምነው ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቦ መረዳት ሲችል ብቻ ነው” ብለው ያስተምሩና ለዚህ አስተምህሮ ከፍተኛ አጽንዖት ይሰጡ ስለ ነበር ሰዎችን በማዳን ሂደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ያለው ሚና ምን እንደ ሆነ የተዘነጋ ይመስላል። ይሁን እንጂ ከተሓድሶ አራማጆች መካከል የሆነው ጆን ካልቪን በሮም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅድመ ተሓድሶ ዘመን ተዘንግቶ የነበረውን የቅዱስ አውግስጢኖስ አስተምህሮ፣ ማለትም መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ድነት ውስጥ ያለውን ሚና እንደገና አነቃቅቷል።

የድኅረ ተሓድሶ ዘመን

በድኅረ ተሓድሶ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ኀይል ሰዎችን በማዳን ረገድ የሚያከናውናቸው ሁለት ነገሮች ጎልተው ወጥተዋል፤ እነዚህም የውሸት ብህትውና (False Mys cism) እና የውሸት አመክኑያዊነት (False Ra onalism) ናቸው። ጆን ዊስሊ ከተሓድሶ ዘመን በኋላ በመንፈስ ቅዱስን አስተምህሮ ላይ ትልቅ ብርሃን የፈነጠቀው በዚህ ወቅት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ ይበልጥ መረዳት ጀመረች። ምንም እንኳ የጆን ዊስሊ ሥነ መለኮት ፍጹም ባይሆንም ቤተ ክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ በደንብ መረዳት የጀመረችው ግን በእርሱ ዘመን መሆኑን መካድ አይቻልም።

መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን

ከዚህ በላይ በተመለከትነው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ኑፋቄዎች አብዛኞቹ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት የሚያጠነጥኑ የአስተምህሮዊ ኑፋቄዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለአስተምህሮ ሳይሆን ለክንዋኔ ሆኗል። በአተገባበርም ወቅት የሚፈጠሩ ስሕተቶች በብዛት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይስተዋላሉ። እነዚህን ስሕተቶች እንደ ኑፋቄ መመልከት አለብን ወይስ የለብንም? እነዚህ በአስተምህሮ ሊገሩ የሚችሉ ቀላል ስሕተቶች በመሆናቸው በኑፋቄ ጎራ ሊፈረጁ አይገባም የሚል ሙግት ሊነሣ ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ልምምዶች ታሳቢ የሚያደርጉት ምንጫቸውን (አስተምህሯቸውን) በመሆኑ ልምምዶቹም የነፈቁ ናቸው ለማለት ያስደፍራል።

እኔነት የሚፈታተነው የክርስቶስ ማኅበር አንድነት

“ደሞዛችን አልደረሰም እንዴ?” ስትል ጠየቀችኝ። ጠያቂዋ ሚስቴ ስትሆን፣ ትዳር ከመሠረትን ሁለት ሳምንት ገደማ የሆነን ይመስለኛል። ለካንስ ላቤን አንጠፍጥፌ የማገኘው ደሞዝ፣ ከትዳር በኋላ ደሞዛችን ሆኗል! ላቤም የግሌ አይደለም ማለት ነው። ይሄን ማሰቡ ድንጋጤ ለቀቀብኝ። ባልና ሚስት አንድ አካል፣ አንድ አምሳል እንደሆኑ አልጠፋኝም፤ ክርስቲያናዊው ትዳር፣ “ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” በሚል…

ተጨማሪ ያንብቡ

ርብቃ – የእስራኤል እናት

በዚህች አጭር መጣጥፍ እስራኤልን እስራኤል ስላደረገች እናት ለማየት እንሞክራለን። እስራኤላውያን ጠንካራ ሕዝቦች ናቸው። በየቀኑ በዜና ስለ እነሱ ሳንሰማ ማደር አንችልም። አባታቸው ያዕቆብ እግዚአብሔር በሚገርም መልኩ መርጦ የታላቅ ወንድሙ የዔሳው የበላይ ያደረው የእግዚአብሔር ሰው ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.