[the_ad_group id=”107″]

ቅዱስ መንፈስም ይለያል!

በደግም ቀን ሆነ በክፉዉም ዘመናት ክርስቶስን እና እውነተኛ ትምህርቱን የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሊሆን ይገባል ስንል በብዙ ምክንያቶች ነው። አንድም ዙሪያችን በብዙ እንቅስቃሴዎች የተሞላ በመሆኑ በተፈጥሮውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ብቻችንን አይደለንምንና ነው። አንድም በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የማይገዛ ሕይወት፣ ትምህርት እና አገልግሎት ለሌሎች ብዙ መንፈሶች ጥቃት ስለሚጋለጥ ነው። አንድም የእግዚአብሔር ቤት የመንፈስ ቅዱስ ብቸኛ ግዛት ሥር እንዲሆን ቀድሞውኑ ድንጋጌ ወጥቷልና ነው። እርሱ መንፈስ ቅዱስ መምራቱን፣ ማስተማሩን፣ መምከሩን፣ ኀይልንና ድንቅን ማድረጉን፣ ወንጌል ማሮጡን በብቸኝነት ይገራና ይመራ ዘንድ የቤቱ ደንብ ነው።

ሠራተኛው የቤቱ አገልጋይ ሆኖ ይገኝ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ቤት ሊያገለግል የሚወድ ቢኖር ዝቅ ብሎ የበላይነቱን ለመንፈስ ቅዱስ ይሰጥ ዘንድ ግድ ብሏል፤ የእምነቱ መሥራች እና ባለ ራእይ ክርስቶስ። በዚህ በሰማይ ንኪት ዕቅድና ዐላማ የተሠራው ቅዱሱ ቤት ለእግዚአብሔር መንፈስ ይገዛል እንጂ ሌላ አማራጭ አይኖረውም። ጌታ ኢየሱስ በትምህርቱ (ከሞት ከተነሣም በኋላ 40 ቀን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲያስተምራቸው) ለደቀ መዛሙርቱ ያ“ሳሰባቸው ነገር ቢኖር የመንፈስ ቅዱስን ሙላትና ኀይል እንዲጠባበቁ እንዲሁም እንዲቀበሉ ነው።

ለእነዚያ ለቀድሞዎቹ ይህ ከሆነ የዛሬ አማኞች ከዚያ ሌላ ወይም በታች መጠበቅ የለባቸውም።

ከተነገረው፣ ከተወሰነው፣ ከተሰጠው “ሌላ ወይም በታች” ግን የለም ማለት አይደለም። ቤተ ክርስቲያን እንዲያ መንፈስ ዐልባ ሆና ኖራ አታውቅም አትበሉ። ለ“ሌላ እና በታች” ለሆነ ተሰጥታ አታውቅም አትበሉ፣ ዝንጉዎች አትሁኑ። ሰዎች (ማለትም የሰው መንፈስ እና ኀይል) አወዛውዟት ያውቃል፤ ደግሞ ደጋግሞ። ሰው ብርቱው፣ ብርቱ ነኝ ባዩ የሰው ዐሳብ እና መንፈስ ከባለቤቱ ከእግዚአብሔርም ቤቱን ቀምቶ ያውቃል፤ ብዙ ጊዜ። እያልኩ ያለሁት አንዱ መንፈስ ቅዱስ ተገፍቶ “ሌላው” ተመሳስሎ እና አመሳስሎ “እኔው ነኝ” ሊል ይችላል። ራሱ ይሠራና “ከመንፈስ ቅዱስ ነው” ይላል። ይህ አንዱ “ሌላ” ነው። የብርሃን መስሎ የጨለማውም መቅረቡ እና ማገልገሉም ሌላው ነው። ስለዚህም ነዉ “መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ” እና እንዳልሆኑ እንመረምር ዘንድ ቃሉ ግድ ያለን።

የመጀመሪያዎቹ አማኞች ቅዱስ መንፈስ ሲቀበሉ፣ በእርሱ ሲጠመቁ፣ ያንን ብርቱ ኀይል ሲቀበሉ ʻምን እንዲሆኑ፣ ምንስ ሊተገብርባቸው ነው?ʼ የሚለው ጥያቄ ሰፊ ምላሽ ውስጥ በዚህ ልዩ ዕትም መጽሔት ከቀረቡት ጽሑፎች መሠረታዊ መልስ ማግኘት ትችላላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዐላማ “የመንፈስ ቅዱስ አብሮነት በቤተ ክርስቲያን ከሌለ፣ የሚገባውን ሥፍራ በቤተ ክርስቲያን ካልያዘ፣ አማኞች በሙላቱ ካልኖሩ ምን ይሆንባቸዋል?” የሚል መንደርደሪያ ላይ ከታሪክ አንጻር ጥቂት ማሳያዎችን ያቀርባል፤ “ከቅዱሱ ጋር መወገን ከሌሎች መንፈሶች ያርቃል” የሚል ማበረታቻም ያክላል።

ቅዱስ መንፈስ ካልተገኘልን . . . ለሌላው መዳረግ እንዳይሆን

ከ13ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ ምክንያቶች ሊደረደሩለት በሚችልበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን በጉልበት ዐልባነት ግን ክንዱን ፈላጊነት፣ የትምህርት እና የሕይወት ንፅሕና ጉድለት ግን መውጫ መንገድ ፍለጋ ብርቱ ጥረት የታየበት ዘመን ውስጥ ነበረች። እንበል፣ “ድውያንና በርኩሳን መናፍስት የተሠቃዩት” ይፈወሱ ነበር ቢለን የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን የሚነግረን ቅዱስ መጽሐፍ�፣ በዚያ አስቸጋሪ ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አጋንንት ያለባቸው ሰዎች አሉ፣ መንፈሱ ግን እንዲሁ በዋዛ አይወጣም፤ ድውያን ይሠቃያሉ ግን ቤተ ክርስቲያን ለፈውሱ ኀይል አልባ ነበረች። ይብሱኑ ከችግሮቹ መውጫ ቀዳዳ ብዙ ብልሃቶች የተበጃጁበት እና ለምእመናን የቀረበበት ዘመን ነበር። ነገሩ፣ “ቅዱሱ ካልረዳ ሌላው ይረዳ ከሆነስ?” ነው።

እናም ቅጠል በጥሰው ፈጭተው ይሁን፣ “የአምላክ ስም” ተደጋግሞ የተጻፈበትን ወረቀት በማንበብ በማነብነብ፣ በማንበልበል ለተቸገረው ወገን መፍትሔ መስጠትን የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የተጋፈጠችው ጉዳይ ነበር። “የትኛው ነው የተፈጥሮ?”፣ “የትኛው ነው ከላይኛው?”፣ “የትኛውስ ነው ከሌላኛው?” የሚለውን ለመለየት የተጣረው ጥረት ልክ ይህ ነው አይባልም። ዋነኛው ተገዳዳሪ የነበረው ግን የላይኛውን ከሌላኛው (ከርኩሱ) መለየት መክበዱ ነበር፤ የዚህኛውን ከዚያኛው መለየት።

የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ሀብቷ
እና ኀይሏ መንፈስ ቅዱስ ነው።
የእርሱ ሥራ ደግሞ የጌታ
ኢየሱስን ማዳን መግለጥ ነው፤
ኢየሱስን መሾም ነው።

ፍራንሲስካዊው ካህን ጂሮላም አዞሊኒ በዚህ “የዚህኛው – የዚያኛው” ውጥረት ፊት ለፊት ከተጋፈጡት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ውስጥ አንዱ ነበር። አጋንንትን በማውጣት ብዙዎችን ይረዳል። አንድ ወቅት ግን ለአንድ ሕፃን “ቢጸልይ” መንፈሱ እምቢ አለ። ፈውስ ራቀ፣ መንፈሱ አልርቅ አለ። የሕፃኑ እናት አሳዘነችውና ካህኑ በአቅራቢያ ላለች አንዲት ጠንቋይ ደብዳቤ አስይዞ ላከ። ደብዳቤው፡- “ፈቅጄልሻለሁ፣ ከዚህ ሕፃን አጋንንት አስወጪ” ይላል። አሁን የምጽፍላችሁ በርግጥ ስለ ሆነ፣ ስለ ተፈጸመ ታሪክ ነው። በዚህ ድርጊቱ ተከሶ በዘመኑ ጠንቋይ አደና (Witch-hunt፣ ደግሞም Roman Inquisi on ይባላል) ላይ በተሰማሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወኪሎች ዘንድ ቀረበ፣ ስለ ጥፋቱ ተጠየቀ። አንድ ወቅት እርሱም ታማሚ እንደ ነበር ነገራቸው፤ ተቸግሮም አንዲት ጠንቋይ ጋር ሄደ። ጠንቋይቷ ግን የጠንቋይ አደናውን ፈርታ ለነፍሷ ብላ መጠንቆሏን ማቆሟን፣ ንስሓ መግባቷን ነገረችው። “ችግሬን ፍችልኝ፣ ከዚያ በኋላ እኔም እንደ ካህንነቴ ኀጢአትሽን እንድትናዘዥ አደርጋለሁ” አላት። የተደበቀው ወጣ ወይንም አወጣችዉ፣ መንፈሱም ሠራባት። ጂሮላምም፣ “ይህቺኑ መሣይ ጠንቋይ ሴት ጸልያልኝ ድኛለሁና ሕፃኑንም በጸሎቴ መርዳት ባልችል እንደማውቀውና እንደተገለጠልኝ ወደ ጠንቋይቷ ዘንድ መላኬ እውነት ነው” አለ። ቅጣቱንም ተቀበለ።� ይህ ስለ አንድ ሰው ጉዳይ ነው።

ትንሽ ሰፋ ላድርገው። በእርግጥ በዘመኑ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ጠንቋይ ሆኖ ያገኘችውን “ቅጣት” ነው በምትለው መንገድ ቀጣች፣ ንስሓ የገቡትን አንበረከከች፣ በጭካኔ ድርጊት ገደለች፣ አስወገደች፤ ወይም በማናዘዝ ለማስወገድ ጣረች። ችግሩ እንደ ጂሮላም ያሉት መብዛታቸው ነው። በጣሊያን አገር በሞዶና ግዛት ብቻ ከ1580 – 1600 ድረስ በጥንቆላ ሥራ እና ጠንቋይ በማማከር ተግባር ተጠርጥረው ጠንቋይ አደና (Witch-hunt) ኮሚቴ ፊት ከቀረቡት ውስጥ 20 ከመቶ የሚሆኑቱ የቤተ ክርስቲያን መሪ ካህናት (“ፓስተሮች”) እና በቤተ ክርስቲያን አጋንንትን በማስወጣት የሚታወቁ አጋንንት አውጪዎች (Exorcists) ነበሩበት።2

እነዚህ እንግዲህ ከዚያኛው ሠፈር ወደ እዚህኛዉ ቤት የተሻገሩ እና መንፈሱን ያሻገሩ ነበሩ። ከዒላማ ወጥተው በቤቱ ውስጥ ሊደላደሉ የሞከሩ፣ ከቅዱሱ ጋር መሆን ሲያቅታቸው ሌላውን የሾሙ ነበሩ።

ጠቢባኑ (The Wise Ones)

ከሌላው ወገን በሆነ መንፈስ የተመሩ፣ ከቅዱሱ ጋር ትውውቅ የሌላቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባታቸውን በዚያው ዘመን የነበረ ታሪክ ይዘግባል። ቤተ ክርስቲያን በጽኑ አልታገለችም አትበሉ፤ የቻለችውን ሞክራለች። ግን “ከዚያኛው” መንፈስ መገላገሉ ቀላል አልነበረም፤ ሰዎቹ የዋዛ አልሆኑም። ከሩቅ ዒላማ ከመሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን ጠጋ አሉ፤ ወይም በቤቱ ውስጥ ያሉት ወደዚያኛው ጠጋ አሉና “ያኛውን” አቀረቡት።

በአንዳንድ አካባቢዎች እነዚያ የቤተ ክርስቲያን አባልም ሆኑ። ዕድሜ ለታጋሽ ቄሶች እና አቅመ ቢስ ማኅበረ ምእመን ይሁን እንጂ እነኛዎቹ ለአገልግሎትም ጎንበስ ቀና አሉ። በሕዝቡም ዘንድ ጠቢባን (The Wise Ones) በመባል የሚታወቁ አጋንንት አውጪዎች እና በሽታ አባራሪዎች ተደርገው የክብር ቦታ ተሰጣቸው። ይህ የሆነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው።� በእንዲህ መሣይ መንገድ ከውጪ የሆነው መንፈስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ በሩ ወለል ተደርጎ ተከፈተ።

በኢትዮጵያም ውስጥ በዚያው ተመሳሳይ ዘመን የሆነው ይህንኑ ይመስላል። ለካህናትና ለነገሥታቱ (በተለይ ለዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ /1433-1468/) ያስቸገረው የምእመናኑ ጥዋት በቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ከተሰዓት ጠንቋይ ቤት ማዘውተር ነበር። እናም ንጉሡ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሆኖ ፀረ ጠንቋይ አዋጅ አስነገረ።� ቅጣቱም አስከፊ ነበር። የጠነቆለውም ሆነ ያስጠነቆለው ሰው አንገት ከላይ ተነሣ፣ በጭካኔ ሆዱ በጦር ተቀደደ።� የጠፋዉ ጠፋ፤ የተረፈው ግን ቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ፣ ወይም ከክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ ጋር የሩቅ ቅርብ ሆነ።

በተለምዶ “ደብተራ” የሚባሉት ድልድይ ሆኑ። መተት ሲመትቱ፣ “በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” ይላሉ። ይህ ለእነርሱ ትልቅ መልእክት ነበረው። ሕዝቡ ቀድሞውኑ በወጨበራ በተሠራለት ትምህርት “ሰይጣን በስመ አብ አይልም!”3 ይል ስለ ነበር “እኛም የእናንተው ነን” ለማለት፣ “ከሰይጣን ወገን አይደለንም” ለማለት፣ “የሰይጣን ብንሆን ʻበስመ አብ እንል ነበር ወይ?ʼ” ለማለት፣ ጨለማውን ብርሃን ለማስመሰል ነው። ከጥንቆላ ጽሑፍ ውስጥ፣ “በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” (በጌታ በኢየሱስ ስም) የሚል ብታነቡም አትደነቁ። ʻእንዴት የጌታን ስም ደፍሮ ጠራ፣ እንዴት ሆነለት?ʼ አትበሉ። ከዋና ባለቤቱ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር አይገናኝ እንጂ ለማነብነብማ ሲለው ሲጠራው የጉድ ነው።

እናም ይህ የድግምትና የምትሓት እውቀታቸውን “የሰሎሞን አምላክ ጥበቡን ሰጠን” ቢሉም ያው “የማቀራረቢያው” ሸፍጥ፣ የአማኙን ልብ ማስከፈቻ ነው። “ጠቢባን”፣ “የሰሎሞንን ጥበብ የወረሱ” ሲባል የሩቅ ሳይሆን፣ የዚያኛው መንፈስ ሳይሆን፣ የዚህኛውን ለማስመሰል ነው። በዚህኛው ቅዱስ መንፈስ ሰው ካልተወረሰ ለዚያኛው መጋለጡም ግሩም ማሳያ ነው። ያ መንፈስ ደግሞ መጫኛ ቀጥ አድርጎ ያቆማል፣ የተሰወረን ይገልጣል፣ ድውይ ፈወስኩ ይላል፣ ከበታቹ ያለውን መንፈስ አስወጣሁ ይላል፣ ሀብት ያበዛል፣ ለመካን ልጅ ይሰጣል፣ የሞተዉን እና የሩቅ ዘመድ ስም በመጥራት ያስደንቃል፣ የጠፋውን ዕቃ ያስገኛል፣ ተኣምራትንና ድንቅን ያደርጋል። በዚህ ትንግርት ፊት ቆሞ “ከዚያኛው ነው” ለማለት አቅም ያሳጣል። “ጠንቋይ ነኝ” አይልም፤ “የሰሎሞን ጥበብ አለብኝ” ይላልና ያደናግራል። “ተቃዋሚያችሁ ነኝ” አይልምና “እቀፉኝ፣ ለእናንተ ከአምላክ ተሰጥቻለሁ” ይላል።

በዚህ ዘመንም “የመለየት መንፈስ!”

ዛሬስ ስንቱ “ሰይጣን ኢየሱስ አይልም” ብሎ ቤቱን ወለል አድርጎ ለክፉው መንፈስ ሰጥቷል?! ከእዉነተኞቹ እየተመሳሰሉ አደባባይ የሞሉ አንዳንድ ሓሳዊያኑ አጋንንት አዉጪ ነን ባዮቹ እና ተንኮለኛ ሠራተኞች ከዚህም ከዚያም በቀዱት መናፍስት ስንቱን የዋህ እያተራመሱት ነዉ?! በርግጥ ግን ከቅዱሱ መንፈስ የራቀ ሕዝብ የዚያኛው መንፈስ መጫወቻ ቢሆን አይገርምም። ያኛው አመሳስሎ፣ ተመሳስሎ ይቀርባል፤ ቀርቦለታል። እውነት መስሎ፣ እውነት ተናጋሪ ሆኖ ይቀርባል። የ97 ብር ኖት ፎርጂድ ሆኖ ለምን እንደማይሠራ ታውቃላችሁ? ያንን የሚመስል እውነተኛ የብር ኖት ስለሌለ ነው። ቀጣፊው ቢሠራ 100 አድርጎ ነው። ታዲያ እንዴት ይለያል? በእውነተኛው ብር ኖት መሥፈርት! እውነተኛውን ጠንቅቆ ማወቅ ሐሰተኛውን ይገልጣል። ይኸው ነው! የጌታ የሆኑቱ ያኛውን አያጡትም።

የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ሀብቷ እና ኀይሏ መንፈስ ቅዱስ ነው። የእርሱ ሥራ ደግሞ የጌታ ኢየሱስን ማዳን መግለጥ ነው፤ ኢየሱስን መሾም ነው። ሰዉ በጌታ ቤት ዉሰጥ ገንኖ ስታዩ ወደ ሌላኛዉ መንደርደሪያዉ አንዱ ምልክት ይሄዉ ነዉ ። ከሽባው መፈወስ በኋላ “እኛን ለምን በመደነቅ ታዩናላችሁ”5 ያሉቱ ሐዋርያት ሊታይ የሚገባው ኢየሱስ ብቻ ስለሆነ ነው። ፈዋሹ እርሱ ስለሆነ! ትልቁ ሊገን የሚገባ፣ ʻተመልከቱትʼ መባል ያለበት፣ እሱ ጌታ ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስ ተኣምር እና ድንቃ ድንቅ ቢያደርግ ዬትኛዉንም “የእግዚአብሔር ሰው” ከፍ ሊያደርግ፣ “ባለ ልዩ ቅባት” ሰው ሊያወጣ ሠርቶ አያውቅም። እንዲያ “ሊሆን ይችላል” ያለዉ ተላላው አሣዛኙ ሕዝብ ነው፤ በሰዉ ጫማ ስር የተንበረከከ፤ ከቅዱሱ አምልጦ ለስዉ መንፈስ የገበረ።

እናም ቤተ ክርስቲያን ዛሬ መለመን ያለባት የመለየት ጸጋን ነው። ይህ ጸጋ በመናፍስቶች መኻል ይለያል፤ የትኛው ከላይኛው፣ የትኛው ከምድሩ፣ የትኛውስ ከጥልቁ እንደ ሆነ ይገልጣል። በዚህ ዘመን ልመናዬ ለቤተ ክርስቲያን ይህ ጸጋ ይበዛ ዘንድ ነው።

ደግሞም ቃሉ እውነተኛ መስፈርት ሲሆንልን ቅዱስ ቃሉን የሰጠ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምን እንደ ሆነ እናውቃለን። በዚህ ቃል ቤተ ክርስቲያንን ምን ሊያደርግ፣ በአማኞች ሕይወት ምን ሊጠራ እንደ ፈለገ ፍንትዉ ባለ ብርሃን እናያለን።

በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በብርቱ የመንፈስ ቅዱስን ጉብኝት መፈለግ ያለባት ለሌላው ተላልፋ እንዳትሰጥም ነው። በወንገርጋራ ትምህርት ተነድተን ሰይጣን “ኢየሱስ አይልም” “የኢየሱስን ስም መጥረት አይችልም” ያልነው ራሱ ሰይጣን ብዙዎችን አስታጥቆ አስርጎአል። እዉነታዉ ይሔዉ ነዉ። የእኛኑ ቋንቋ የሚናገሩ፣ እኛው የምንሰብከውን የሚሰብኩ፣ የእኛው መሰብሰቢያ ውስጥ የሚያድሩ። ያኔም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን እንዲሁ ነበር፤ አሁን ደግሞ እጅግ ረቅቆ ብቅ ብሏል። እዚህም እዚያም፣ በየ“ክርስቲያን” ሳተላይት ቲቪው ጥንቆላ “በኢየሱስ ስም!” ሲደረግ በብዙዎቹ የዋሓን ተላላዎች ልብ ውስጥ ሠርጎ ገብቷል። እውነት ሲያንስ፣ ብርሃን ሲደክም ይህ እንደሆነ ታያላችሁ። ይህን ነውር መገልበጫው እና ጎርበጥባጣ መንገዱን ማስተካከያው፣ የጠፋብንን የደበዘዘብንን መልሰን ማግኘት ብቻ ነው፡- ክርስቶስን የሚሾም፣ የማዳን ሥራውን የሚያጎላ፣ የወንጌልን ውበት የሚያደምቅ መንፈስ ቅዱስ!

ማጣቀሻ

  1. ሐዋ. 5፥16
  2. Mary O’Neil, “Sacredote Overo Strione: Ekclesias cal and Supers ous Remedies in Sixteenth Century Italy,” in Steven L. Kapland (ed.) Understanding Popular Culture: Europe from the Middle Ages to the Nineteenth Century (Berlin: Mouton Pub, 1984) 68-69.
  3. O’Neil, 53-83.
  4. Robin Briggs, Witches, and Neighbors: The Social and Cultural Content of European Witchcraft (New York: Penguin Books, 1998), 172-173.
  5. Taddesse Tamrat, Church and State in Ethiopia, 1270-1527 (Oxford: Clarrendon Press, 1972) ገጽ 239። ዐፄው የጠንቋዮቹን ኀይል ይፈራ፣ ለሕይወቱም ይሠጋ ነበር (ገጽ 247፣ ዋቢ iv) ተመሳሳይ ቅጣቶችን በዚሁ በታደሰ ታምራት መጽሐፍ ላይ ይመልከቱ (ገጽ
  6. 240 እና ገጽ 240)። አንዳንድ ምንጮችም ሚስቱ እና ሁለት ልጆቹ የሞት ቅጣት እንደ ተወሰነባቸው ይጠቁማሉ።
  7. ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለሕዝቡ ያዘዘው “በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ” ሁሉም እንዲሉ እና ሰውነታቸው ላይ እንዲያስጽፉ ነው (ገጽ 239)።
  8. ሐዋ. 3፥11-13

Afework Hailu (Ph.D.)

Afework Hailu serves EGST as lecturer in Church History and Dean of Students. He holds a Ph.D. from the School of Oriental and African Studies at the University of London. His doctoral dissertation was titled The Shaping of Judaic Identity of the Ethiopian Orthodox Täwaḥədo Church: Historical and Literary Evidence, which discussed the origin and development of the so-called Jewish cultural elements such as circumcision, and Sabbath in the Ethiopian Church. The study analysed pertinent historical, archaeological, and literary evidence available from the Aksumite, Zagwe, and ‘Solomonic’ dynasties. The study will be published as ‘Jewish’ Elements in the Ethiopian Church (Gorgias Press, USA). Before his doctoral study at SOAS, Dr. Afework earned Masters degrees from Addis Ababa University in Cultural Studies, the Free University Amsterdam in Church History, and a Master of Theology from EGST. He has taught theological and historical courses in theological colleges in Ethiopia. His general academic interest is in the field of history, but specifically history of Christianity, African and Ethiopian church history, Eastern Christianity, Jewish-Christian relations, Muslim-Christian relations, culture and culture formation, religion and Development/Environment. He has a growing passion for the study of practical aspects of church reform. ዶ/ር አፈወርቅ ኀይሉ በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (ኤገስት) የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህር ሲሆን፣ የት/ቤቱ የተማሪዎች ዲን በመሆን ያገለግላል። ዶ/ር አፈወርቅ የፒኤችዲ ጥናቱን ለንደን በሚገኘው School of Oriental and African Studies (SOAS) ያደረገ ሲሆን፣ የጥናቱ ትኩረትም የአይሁድ ማንነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚመለከተ ነው። አፈወርቅ የፒኤችዲ ጥናቱን ከማድረጉ በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባህል ጥናት፣ አምስተርዳም ከሚገኘው Free University በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት በነገረ መለኮት ጥናት የማስተርስ ዲግሪዎች አሉት። ዶ/ር አፈወርቅ በጠቅላላው በታሪክ መስክ ላይ ምርምር ማድረግ የሚወድድ ሲሆን፣ በክርስትና ታሪክ፣ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ክርስትና ታሪክ፣ የምሥራቅ ክርስትና ታሪክ፣ የአይሁድ ክርስትና ግንኙነት፣ የሙስሊም ክርስቲያን ግንኙነት፣ ባህል እና የባህል ለውጦች እንድሁም ሃይማኖትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረግ ጥናት ያካሂዳል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ተሓድሶና ተግባራዊነቱ ላይ ልዩ ትኩረት አለው። ዶ/ር አፈወርቅ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ነው።

Share this article:

ፖለቲካችን ክርስቲያናዊ ዕሴቶችን ይሻል!

አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ እንዳለች በብዙዎች ዘንድ መግባባት አለ። የተጀመረው ለውጥ የሚፈለገው ቦታ ላይ እንዲደርስ ሁሉንም የኅበረተ ሰብ ክፍል ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አሁንም በብዙዎች ዘንድ እምነት አለ። የወንጌላውያን አማኞች የኅብረተ ሰቡ አካል እንደመሆናችን ለአገራችን ሰላም፣ ፍትሕ እንዲሁም ብልጽግና የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እስከ አሁን በነበረን አገራዊ ተሳትፎ ‘ብዙ ትኩረት አልሰጣችሁም’ ተብለን የምንወቀሰው እኛ ወንጌላውያን፣ ለዚህ ወቀሳ አዎንታዊ ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ ላይ እንዳለን ይሰማናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ቅዱስ መንፈስም ይለያል!

በደግም ቀን ሆነ በክፉዉም ዘመናት ክርስቶስን እና እውነተኛ ትምህርቱን የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሊሆን ይገባል ስንል በብዙ ምክንያቶች ነው። አንድም ዙሪያችን በብዙ እንቅስቃሴዎች የተሞላ በመሆኑ በተፈጥሮውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ብቻችንን አይደለንምንና ነው። አንድም በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የማይገዛ ሕይወት፣ ትምህርት እና አገልግሎት ለሌሎች ብዙ መንፈሶች ጥቃት ስለሚጋለጥ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

“አትብሉ – ብሉ”

በዔድን የነበረው ሕይወት “መልካም” እጅግ ያማረም ነበር። ከምድር ዐፈር የተበጀው ሰው በዚህ ውብ ስፍራ ተቀመጠ፤ እንዲኖር፣ እንዲያለማ፣ እንዲንከባከብም። በዚያ የነበረው ዛፍ ሁሉ “የሚያስደስት ለመብልም መልካም” ነበር (ዘፍ 2፥9)። ሕይወት አካላዊ (ውጪአዊ) ብቻ ስላይደለ ከመኖርና ከመደሰት ያለፈ ደርዝ አለው፤ ነፍሳዊ፣ መንፈሳዊ ገጽታ። ይህም ደግሞ የተሟላ እንዲሆን በሚታየውና በሚበላው መካከል ምጡቅና ረቂቅ የሆነው አምላክ እንዲታሰብ፣ እንዲከበርም ታሰበ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.