[the_ad_group id=”107″]

ጴንጤቆስጣዊ - ካሪዝማቲካዊ

ሰሙ ይፍሩ ይባላል። በክርስቶስ ዳግም ልደት አግኝቶ ሕይወቱን ለጌታ ከሰጠ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ሰሙ “ጴንጤቆስጤ” የሚለው ስያሜ ትርጕም ብዙም አይገባውም። በርግጥ በኢትዮጵያ የፕሮቴስታንት/ወንጌላውያን ክርስትና የሚከተሉ ሰዎች የሚሰጣቸው ስያሜ “ጴንጤ” መሆኑን ያውቃል፤ ይሁን እንጂ የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ወይም ክርስትና ስለሚባለው ግልጽ የሆነ መረዳት እንደሌለው ይናገራል። “እኔ ጴንጤ ለእኛ የተሰጠ ሃይማኖታዊ ስያሜ እንጂ እንቅስቃሴ መሆኑን በእውነቱ አላውቅም። እኛ አገር በጌታ የሆኑትን ሁሉ ʻጴንጤʼ ይሏቸዋል። በቃ፤ በጌታ ለሚያምኑ ወይም በኦርቶዶክስ ክርስትና ውስጥ ለሌሉ የተሰጠ ስም ነው የሚመስለኝ።”

በርግጥ የጴንጤቆስጤንም ሆነ የካሪዝማቲክ ክርስትናን ምንነት ጠንቅቆ የማያውቀው ሰሙ ብቻ አይደለም። ብዙ ምእመናን “ፕሮቴስታንት”፣ “ወንጌላውያን”፣ “ጴንጤቆስጣውያን”፣ “ካሪዝማቲካውያን”፣ “የእምነት እንቅስቃሴ/ብልፅግና ወንጌል” የተሰኙ ስያሜዎች አንድነት እና/ወይም ልዩነት በተገቢው መንገድ ስለ መረዳታቸው ርግጠኛ መሆን ይቸግራል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ እነዚህ ስያሜዎች በአንድ ላይ ተጨፍለቀው “ጴንጤ” የተሰኘና በሕግ ያልጸደቀ ስም የተሰጠው ማኅብረ ሰብ አለ።

ሰሙ ይፍሩ ግን ስለ ልዩነቱ ገልጽ የሆነ መረዳት እንደሌለው ከተናገረ በኋላ በዚያው መሄድ የፈለገ አይመስልም፤ “ግን ʻየጴንጤቆስጤ ወይም ካሪዝማቲክ ክርስትና ያልከው ምንድን ነው?ʼ ” ሲል መልሶ ጠይቋል።

የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ

የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በምድረ አሜሪካ እንደ ተጀመረ የሚነገርለት የ“ፕሮቴስታንት” ክርስትና አካል ነው። በአሜሪካን አገር የካንሳስ ግዛት፣ ቶፔካ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ቤተል መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ተማሪ የነበረችው አግነስ ኦዝማን እ.አ.አ ጃንዋሪ 1 ቀን 1901 “በማይደመጥ ልሳን” መጸለይ የጀመረችበት ቀን በዘመናዊው ዓለም የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ጅማሬ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ በዚያው አሜሪካ፣ ሎስ አንጄለስ ከተማ፣ አሱዛ ጎዳና የሆነው ክስተት ለእንቅስቃሴው መስፋፋት ጉልሕ ድርሻ እንዳለው ይነገራል። ክስተቱ ዊሊያም ሰይሞር የተሰኘው መጋቢ ይመራት የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ “በማይደመጡ ልሳኖች” በሚናገሩ ምእመናን መሞላቷ ነበር። ይኸው ልምምድ እየተስፋፋ ሄዶ ለፕሮቴስታንት ክርስትና አንድ ቤተ እምነት እንዲጨመር ምክንያት ሆነ፤ አዲስ ነገረ መለኮታዊ ውይይትንም አስነሣ።

በጴንጤቆስጤ አስተምህሮ መሠረት፣ አንድ አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ከሚያገኘው ዳግም ልደት በተጨማሪ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ያስፈልገዋል። አማኙ በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቁ ምልክትም በልሳን መናገሩ ነውና ይህንንም በክርስትና ሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይለማመዳል። በተጨማሪም፣ የጴንጤቆስጤ ክርስትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዛሬም በአማኞች ሕይወት ውስጥ በሥራ ላይ እንደሚውሉ ያምናል፣ ይለማመዳል።

የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ በመነሻው ላይ ከቀዳማውያኑ (mainline) ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። በተለይም፣ ከድነት ቀጥሎ ይመጣል የተባለው ሁለተኛ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ይህም በልሳን በመጸለይ ይገለጣል መባሉ፣ በተጨማሪም ሌሎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በዚህም ዘመን እንደሚሠሩ ማመኑ ነበር ለገጠመው ተቃውሞ መነሻ።

በቀደምት አብያተ ክርስቲያናቱ የተነሣው ተቃውሞ ግን እንቅስቃሴውን ሊያዳፍነው አልቻለም። በአንጻሩ፣ የጴንጤቆስጤ ንቅናቄ ያስነሣው ሞገድ ነባሮቹ ቤተ እምነቶች በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች (ካሪዝማ) ላይ የነበራቸውን አስተሳሰብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል። በጊዜ ሂደትም የመንፈስ ቅዱስን ሥጦታዎች የሚቀበሉና የሚለማመዱ ነባር አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ይጨምር ጀመር። በኋላም “ሁለተኛው ሞገድ” የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው የካሪዝማቲክ ንቅናቄ ወንጌላውያን የተባሉትን አብያተ ክርስቲያናትን ሲንጥ ከርሞ ወደ ካቶሊካውያኑ መንደር መድረስ ቻለ።

ይህ የካሪዝማቲክ ክርስትና ከጴንጤቆስጤ የሚለይበት መሠረታዊ የአስተምህሮ አቋም፣ ከድነት በኋላ ይመጣል በተባለው የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እና እሱን ተከትሎ የሚገለጠው በልሣን የመጸለይ/የመናገር ልምምድ ብቸኛ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው ብሎ አያምንም። ይሁን እንጂ፣ ካሪዝማቲክ ክርስትና በልሣን መናገርን ጨምሮ በ1ቆሮ. 12፥8-10 ያሉ የጸጋ ሥጦታዎች ዛሬም እንደሚሠሩ ያምናል፤ ይለማመዳል። ካሪዝማቲክ ክርስትናን የሚከተሉ ወገኖች እንደ ጴንጤቆስጣውያኑ ከነበሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ወጥተው አዲስ ቤተ እምነት መጀመር አላስፈለጋቸውም፤ እዛው ባሉበት ቤተ እምነት የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎችን የሚለማመዱ ነበሩ።

በኢትዮጵያ ያለችው ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን (የፕሮቴስታንቱ ክርስትና) በአመዛኙ የካሪዝማቲክ ወይም የጴንጤቆስጤ ክርስትናን የምትከተል መሆኗን ማስተባበል ይቻል ይሆን?

ጕዞ ወደ ደቡባዊው ክፍለ ዓለም

ምንም እንኳን የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ ክርስትና መነሻውን ያደረገው ሰሜን አሜሪካ ይሁን እንጂ፣ ይበልጡኑ ተስፋፍቶና ተጽእኖውን አሳርፎ የሚታየው በማደግ ላይ ነው በሚባለው የዓለም ክፍል ነው። ጆናታን ሩትቨን “The Future of Evangelicalism: Issues and Prospects” በተሰኘ መደብል፣ “Back to the Future for Pentecostal/Charismatic Evangelicals in North America and World Wide: Radicalizing Evangelical Theology and Practice” ብሎ በሰየመው ጽሑፉ የክርስትና ዕድገት፣ በተለይም ጴንጤቆስጣዊው/ካሪዝማቲካዊው ክርስትና ከአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ይልቅ “ደቡባዊ ክፍለ ዓለም” እየተባለ በሚጠራው “ሦስተኛው ዓለም” በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ ያደረጉ ምክንያቶች ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ያስታውሳል።

ሩትቨን እንደሚለው ከሆነ የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ ክርስትና ከምእራባውያኑ ይልቅ ሦስተኛው ዓለም እየተባለ በሚጠራው የዓለም ክፍል እጅጉን የተስፋፋው፣ “የሦስተኛው ዓለም ሰዎች ለችግሮቻቸው ብርቱ የጸሎት ኀይል እንዲሁም የእግዚአብሔር ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አጥብቀው የሚያምኑ በመሆናቸው ነው። በአንጻሩ፣ እግዚአብሔር ለምእራባውያን ዕለታዊ ኑሮ ዋና ነገር አይደለም፤ ለደኻው ግን የሕልውና ጉዳይ ሆኖ ይታዋል። ምእራባዊው ላሉበት ችግሮች (መንፈሳዊንም ጨምሮ) መፍትሔ ፍለጋ የሚሄደው ወደ ባለሙያ ነው። የሦስተኛው ዓለም አማኝ ግን ኀያሉን እግዚአብሔር የሙጥኝ ይላል፤ መሄጃ የለውምና።”

ሌላኛው ሰበብ፣ የሦስተኛው ዓለም ሰዎች የኑሮ ዘይቤ በአመዛኙ የጋርዮሽ (communal) መሆኑ፣ የሚከሰቱ ሁነቶች በቀላሉ በማኅበረ ሰቡ አባላት ላይ ተጽእኗቸውን ያሳርፋሉ። በተመሳሳይ የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ በመሰል ማኅበረ ሰብ ውስጥ በቶሎ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል። በአንጻሩ ምእራባውያን ግላዊ የሆነ የኑሮ ዘይቤን መከተላቸው ለእንቅስቃሴው ዘገምተኛ ጉዞ የራሱን አሻራ ማሳረፉ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኗል።

በሦስተኛው ዓለም ያሉ የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ ቤተ ክርስቲያናት አገልጋዮች እንደ አሜሪካውያኑ/አውሮፓውያኑ ውስብስብ በሆነ የትምህርት ሥልጠና አልፈው የሚመጡ “ባለሙያ አገልጋዮች” አይደሉም የሚለው ሩትቨን፣ እያንዳንዱ አገልጋይም ሆነ ምእመን አለኝ የሚለውን የጸጋ ሥጦታ ለመጠቅም አካዳሚያዊ ፍተሻ ውስጥ አይገባም። በሌላ አንጻር ለዚህ ዐይነቱ ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዳለው ደግሞ በጽኑ ይታመናል። የመጀመሪያው የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ዐሥራ ሁለተኛ ምእራፍ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ አማኝ ሥጦታን እንደሚሰጥ ተገልጿል። በመሆኑም፣ የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ አብያተ ክርስቲያናት አብዛኛው ምእመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥጦታውን እንዲጠቀም ያበረታታሉ። የወንጌል ሥርጭቱም የዚሁ አካል በመሆኑ አገልግሎቱ በተወሰኑ “ቅቡዓን” ጫንቃ ላይ ብቻ እንዳይወድቅ አድርጎታል። በሌላ አባባል አማኞች በሙሉ የወንጌሉ መስካሪዎች በመሆናቸው የክርስትናው ቁጥር በብዙ ቁጥር እንዲያሻቅብ ሆኗል።

የጴንጤቆስጤ ክርስትና በኢትዮጵያ

በቀለ ወልደ ኪዳን (መጋቢ) “ሪቫይቫል ኢትዮጵያና የመለከት በዓል” በተሰኘውና ተሻሽሎ ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው የጴንጤቆስጤ ልምምድ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ እንደፈጀበት ይገልጻሉ። “ጴንጤቆስጣዊው ሪቫይቫል ከካሊፎርኒያው አዙሳ ተነሥቶ እስከ ኢትዮጵያው አዋሳ (አሁን ሀዋሳ) ለመድረስ አምሳ ሰባት ዓመታት ያህል ወስዶበታል።” የሚሉት መጋቢው፣ ይኸው ጉዞ “ወደ ብዙ የእስያና የአፍሪቃ አገሮች ከደረሰ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የደረሰው ማለት ነው።” ሲሉ ታሪካዊ ሂደቱን ያስቃኛሉ።

መጋቢ በቀለ ከጴንጤቆስጤ ጋር የሚያያይዙት ሪቫይቫል ወደ ኢትዮጵያ ለመድረስ የዚያን ያህል ረዥም ጊዜ ለምን እንደወሰደበት ዐበይት ያሏቸውን ሁለት ምክንያቶች ይሰጣሉ። “… የመጀመሪያው የአዙሳው ሪቫይቫል የፈነዳበት ጊዜ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ገና በር እየቆረቆረ የነበረበት ጊዜ መሆኑ ነው። … በመሆኑም፣ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ከበር ውጭ ቆሞ ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ጴንጤቆስጤያዊ ሪቫይቫል ሊከሠት የሚችል አይመስለኝም።” ይላሉ።

በሁለተኛነት የጠቀሱት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ከድንበራቸው ባሻገር ስላለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ በቂ መረጃ ስላልነበራቸው እንደ ሆነ ይገልጹና፣ “… የኦርቶዶክስ ክርስትና ብቻ ቀጥተኛ፣ ሌላው ሁሉ የተጣመመ ስለሚመስላቸው ነበር።” ሲሉ በአገሪቱ ውስጥ ያየለው የኦርቶዶክስ ክርስትና በሩን በመዝጋቱ መሆኑን ያብራራሉ። በርግጥ የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት የነበሩ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እና ሚሲዮናውያን በአገሪቱ ውስጥ በሥራ ላይ እንደ ነበሩ የሚያስታውሱት መጋቢው፣ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት እና ሚሲዮናውያን የነበራቸው ተቀባይነትና ተጽእኖ ውሱን መሆኑ የወንጌላውያን አስተምህሮ ሥር እንዳይሰድድ አድርጎታል ባይ ናቸው።

ወጣቶቹ – አቀጣጣዮቹ

ታምሩ ዘለቀ ለድኅረ ምረቃ ትምህርቱ ማሟያ በጻፈውና “The Origin and Expansion of the Mulu Wongel Church in Ethiopia with Particular Reference to its Missionary Perspective” በተሰኛው ሥራው እንዳተተው፣ እ.አ.አ. በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሃይማኖታዊ ቡድኖች/እቅስቃሴዎች እንደ ነበሩና አብዛኞቹም አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች ውስጥ በስፋት ይንቀሳቀሱ እንደ ነበሩ ይጠቅሳል። እነዚህ በሌሎች ቤተ እምነቶች/ተቋማት የማይመሩ “አገር በቀል የሃይማኖት ቡድኖች” (independent religious groups) ይዘወሩ የነበሩት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ በሚማሩ ተማሪዎች ነበር። ከእነዚህ ቡድኖች መካከል “የሃሌሉያ ቡድን”፣ “የሰማይ ብርሃን ቡድን”፣ “የሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ቡድን” እና “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቡድን” ይገኙበታል።

ይህን መሰሎቹ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ከጴንጤቆስጤ ልምምድ ጋር በተለያየ መንገድ ሊታዋወቁ እንደሚችሉ ሐሳብ መሰንዘር ቢቻልም፣ የፊላንድ፣ የኖርዲክ እና የስዊድሽ ሚሲዮናውያን አስተዋጽኦ ግን ጉልሕ እንደ ነበረ ይታመናል። በተለይ፣ በፊላንዳዊው የሚሲዮን አገልግሎት በኩል በሐዋሳ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውና በኋላም አዲስ አበባ፣ መርካቶ አካባቢ በነበርው የ“ሃሌሉያ ቡድን” አባላት ጥያቄ መሠረት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ለሁለት ሳምንት በ“አዲስ ፊኒሽ ሚሽን ቻፕል” ከቡድኑ አባላት ጋር ያሳለፈው ኦማሄ ቻቻ ግንባር ቀደሙን ሚና ሳይዝ አይቀርም ይላል የታምሩ ጥናት። ቻቻ ከቡድኑ ጋር በቆየባቸው ሁለት ሳምንታት ስለ መንፈስ እና ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አስተምሯቸዋል። በጊዜው ከነበሩ ተማሪዎች መካከል መንግሥቱ ጀምበሬ እንደ ተናገሩት፡- “በመጀመሪያው ቀን በመንፈስ የተሞሉት ሰዎች ሁለት ብቻ ነበሩ፤ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ግን አርባ የሚጠጉ ተማሪዎች በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ” ሲሉ ምስክርነታቸው በዚሁ የጥናት ወረቀት ላይ ሰፍሮ ይገኛል። በኋላ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የጴንጤቆስጤ ልምምድን በከፍተኛ ደረጃ አስፋፍታለች ተብላ የሚታመንባትን “የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያንን” እንድትመሠረት ምክንያት የሆኑትም እነዚሁ ተማሪዎች እና ቡድኖቻቸው ነበሩ።

አቶ ታምሩ ወጣቶቹ ከነበሩበት ቤተ እምነት ወጥተው ጴንጤቆስጣዊ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርቱ ያደረጓቸው ሦስት ሰበቦች መሆናቸውን ያመለክታል፤ እነዚህም ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ ናቸው። ማኅበራዊ ሲባል፣ ወጣቶች በአጠቃላይ በኅብረተ ሰቡ ውስጥ የነበራቸው ሥፍራ ውሱን የነበረ መሆኑን የሚያወሳ ነው። በተለይም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ቀድመው በተመሠረቱት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ወጣቶች የነበራቸው ሚና የተገደበ ነበር። በትምህርት ቤት የሚያገኙት ዕውቀት የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ያሉበትን ማኅበረ ሰብ ችግር በተለየ ምልከታ እንዲያዩትና ከተለመደው ውጪ የመፍትሔ ሐሳብ ይዘው እንዲመጡ አድርጓቸው ነበር። ይሁን እንጂ በአመራር ደረጃም ይሁን በወሳኝ የአገልግሎት ክፍሎች የነበራቸው ኀላፊነት እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ የመገፋት ስሜት ሳያሳድርባቸው አልቀረም። ይህም ʻዐይናቸውን ወደ ሌላ እንዲያማትሩ አድርጓቸዋል ነውʼ ትንተናው።

“መንፈሳዊ” የተባለው ሁለተኛው ምክንያት፣ ከገጠር ወደ ከተማ ለትምህርት ይመጡ የነበሩ ልጆች አይተውት ከማያውቁት ዐይነት የአሰባበክና የአምልኮ ዘዬ ጋር መተዋወቃቸው ልባቸው እንዲሰረቅ አድርጎታል። በዚህም፣ ከነበሩባቸው እናት ቤተ ክርስቲያናት ይልቅ ወደ አዲሱ እንቅስቃሴ ይበልጡኑ ይሳቡ ጀመር። የገቡበትም አዲስ ሃይማኖታዊ ልምምድ (movement) ደግሞ የተቀባይነትና የባለቤትነት ስሜት ፈጠረላቸው። ጆናታን ሩትቨን እንዳለውም፣ በክርስቶስ አካል ውስጥ ያላቸውን መንፈሳዊ ሥጦታ እንዲለማመዱ ይኸው የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ዕድሉን ፈጠረላቸው። እንደ ፈውስ፣ ትንቢት እና በልሳን መጸለይ ያሉ ልምምዶች “አዲሱ ክርስትና” ለሕይወታቸው ቅርብና ተጨባጭ ሆኖ እንዲታያቸው አደረገ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ምናልባትም በዋናነት ከትምህርት ቤት ያገኙት የማንበብ ትሩፋት አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ባህል ሰጥቷቸዋል። ይኸው የንባብ ክኅሎትም መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ሦስተኛ አካል ተርጓሚነት እንዲረዱት አስቻላቸው። በአንዳንድ ሚሲዮናውያን ተቋማት ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች የተተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጆች ተማሪዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በራሳቸው ዐውድ ይበልጥ እንዲረዱት አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በአሜሪካንና በአውሮፓ ይታተሙ የነበሩና ጴንጤቆስጤያዊ ይዘት የነበራቸው የኅትመት ውጤቶች፣ በተለያየ መንገድ ወደ ወጣቶቹ መድረሱ ስለ ዓለም አቀፋዊው የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴና ልምምድ ግንዛቤ እንዲያገኙ አስቻላቸው።

ይህ የተማሪዎቹ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ጊዜ ኢትዮጵያ የክርስቲያን አገር ትባል የነበረች ሲሆን፣ የዚህ ምክንያቱ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት መሆኑ ነበር። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ እንደታየው ከመንግሥት ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበራት መሆኑ ነው። ይህ ለቤተ መንግሥት የነበራት ቀረቤታ ደግሞ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ውጪ በፖለቲካው ውስጥ የነበራትን ሥፍራ ከፍ አድርጎታል። ይሁን እንጂ በ1960ዎቹ በተማሪዎች ይዘወር የነበረው አገር አቀፍ የፖለቲካ ለውጥ ንቅናቄ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፊውዳል ሥርዐቱ ተለይታ እንድትታይ አላደረጋትም። በተለይም ተማሪው የነበረው የፖለቲካ ንባብ ወደ ሶሻሊዝም ያደላ መሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ʻአርጅቷል፣ ጃጅቷልʼ ለተባለው ሥርዐት ምሶሶ ሆናለች ብሎ እንዲከስሳት አደረገው ይላል ታምሩ።

እንግዲህ ይህ የፖለቲካ ንፋስ ወደ ጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ሊገቡ ያሉትንም ሆነ የገቡትን ተማሪዎች አልነካቸውም ነበር ማለት አይቻልም። ይህ ከሆነ ደግሞ፣ ለእኩልነት እና ለፍትሕ ካለቆመ ሥርዐት ጋር በሚያበር የሃይማኖት ተቋም ውስጥ የሚቆዩበትን ዕድሜ የሚያሳጥር ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል። ከዚህ ባለፈ፣ መንግሥት ለወንጌላውያኑ፣ በተለይም ደግሞ የጴንጤቆስጤ ክርስትናን ይለማመዱ ለነበሩት የአምልኮ ፈቃድ መከልከሉ ብቻ ሳይሆን፣ በ1963 ዓ.ም. “መጤ ሃይማኖት” ብሎ የጸሎት ቤቶቹን ሁሉ ከማሸጉ ጀርባ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እጅ እንዳለበት በሰፊው ይታመን ነበር። በአንጻሩ ደግሞ እየመጣ ያለው አዲስ መንፈሳዊው ንፋስ፣ ዐልቦ መደብ ከመሆኑ የተነሣ ሁሉን አካታችና እኩልነትን አብሣሪ ሆኖ መገኙቱ ተማሪዎቹ የነበሩበትን ትተው ወደ አዲሱ እንዲሄዱ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ ክርስትና በአፍሪካ (ኢትዮጵያንም ጨምሮ) እንዲስፋፋ መሠረታዊ ከሚባሉት ተጨማሪ ምክንያቶች አንዱ ዘመናትን ያስቆጠሩት የባህላዊ እምነቶች (traditional religion) ንጽረተ ዓለም ነው። እነዚህ ባህላዊ እምነቶች “አምላክ” በላይ በሰማይ የሚኖር ፈጠሪ ብቻ ሳይሆን፣ በታች በምድር ለሕዝቡ የሕይወት ውጣ ውረድ መላ ሰጪ፣ መፍትሔ አምጪ እንደ ሆነ የሚያምኑ ናቸው። በሚሲዮናውያኑ በኩል የተሰበከው ክርስትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እና ስለ ዘላለሙ ሕይወት ቢያበሥራቸውም፣ ምድራዊ ችግሮቻቸውን (በሽታ፣ መከራ፣ የክፉ መናፍስት ተጽእኖ፣ ወዘተ.) እንዴት አድርገው እንደሚያሸንፉ መንገድ አላሳያቸውም። ለዚህም ነው በአንዳንድ አካባቢዎች እሑድ ጠዋት ቤተ ክርስቲያን ሄደው፣ ማምሻው ላይ “የአዋቂ ቤት” ደጅ ይጠኑ የነበረው።

የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ ክርስትና ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያለው በመሆኑና ቀድሞ የተሰበከው ክርስትና የነበሩበትን ክፍተቶች መሙላቱ አማኞች በሙሉ ልባቸው እንዲቀበሉት አድርጓቸዋል። በሚደረግላቸው ጸሎት የሚያገኙት ፈውስ፣ ምስጢርና እንቆቅልሽ ለሆኑባቸው የሕይወት ጥያቄዎች በእውቀት ቃል በኩል የሚመጣው መልስ፣ በትንቢት አገልግሎቱ በኩል የሚቀበሉት መልእክት፣ ከክፉ መናፍስት እስራትና ተጽእኖ ነጻ መውጣታቸው፣ ወዘተ. እግዚአብሔር በሰማይ ብቻ የሚኖር ሳይሆን፣ አብሯቸው የሚኖር የቅርብ አምላክ መሆኑን እንዲያምኑና ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያዞሩ አድርጓቸውላ።

የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ ምን ይዞ መጣልን?

በርግጥ ይህ እንቅሰቃሴ ወደ ኢትዮጵያ ጊዜ ፈጅቶም እንኳ ከመጣ በኋላ ‘ያበረከተው አዎንታዊ ተጽእኖ አለ ወይ?’ የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ይመስላል። ብዙዎች የሚስማሙበት የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ ለወንጌል ሥርጭት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው። በዚህም እንቅስቃሴው ቁጥራቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ጉልሕ ድርሻ ነበረው።

ጥበበ እሸቴ (ዶ/ር) “The Evangelical Movement in Ethiopia: Resistance and Resilience” በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ከአምሣ ዓመታት በፊት የነበራቸውን ብዛት እንዲሁም ከዚያ በኋላ በተደረጉ የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች እያደገ የመጣውን ቁጥራቸውን አስፍረዋል። እንደ ጥበበ ከሆነ፣ በ1950ዎቹ ወንጌላውያን አማኞች ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሕዝብ ከአንድ በመቶ ያንስ ቁጥር ነበራቸው፤ በ1976 በተደረገው የሕዝብና ቤቶ ቆጠራ ይኸው አማኝ ማኅበረ ሰብ ከነበረበት ከአንድ በመቶ ያነሰ ቁጥር ወደ 5.5 ከመቶ አደገ። ከዐሥር ዓመት በኋላ በተደረገው የ1986ቱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ቁጥሩ ዕጥፍ በሚባል ደረጃ አድጎ ወደ 10.2 ከመቶ ተመነደገ። ከዐሥራ አንድ ዓመት በፊት በተደረገው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት፣ የፕሮቴስታንቱ/ወንጌላውያን ቁጥር ከዐሥራ አራት ሚሊዮን በላይ ደረሰ፤ በመቶኛ ሲቀመጥ 18.6 የሚሆነው ሕዝብ የፕሮቴስታንት ክርስትና ተከታይ እንደ ሆነ ቆጠራውን ያካሄደው የማእከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ ይፋ አድርጎ ነበር። ይኸው የሕዝብና ቤተ ቆጠራ ይፋ ሲደረግ፣ የኤጀንሲው ኀላፊዎች የዚህ አማኝ ማኅበረ ሰብ ቁጥር በመጪዎቹ ዐሥር ዓመታት እንደሚጨምር ሙያዊ ትንበያ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኢማኑኤል ፋንቲኒ “Go Pente! The Charismatic renewal of the Evangelical movement in Ethiopia” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፉ ይህ የአማኞች ቁጥር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከፍተኛ የወንጌላውያን አማኞች ቁጥር ካሏቸው አገሮች አንዷ እንደሚያደርጋት ጽፏል። “ኢትዮጵያ ከዐሥር ሚሊዮን በላይ የሆኑ ወንጌላውያን አማኞች የሚኖሩባት አገር በመሆኗ በአፍሪካ ስማቸው ከፍተኛ ከሆነ የወንጌላውያን አማኞች ቁጥር ጋር ከሚነሣው ናይጄሪያ፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ያሉ አገሮች ጋር ያሰልፋታል።” ብሎ ነበር።

የነገረ መለኮት መምህሩ አቶ ዘለለው አርጋው፣ የጴንጤቆስጤ/ካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ያበረከተው ዕገዛ እንዳለ በሚል ከሕንጸት ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፣ “እኔ ከመጣሁበት የአገልግሎት መሥመር አንጻር ሳየው ከፍተኛ ዕገዛ አድርጓል።” ይላል። “እንደምናውቀው የእኛ አገር ገጠሩም ከተማው ከባዕድ አምልኮ ጋር፣ ከመናፍስት አሠራር ጋር የተገናኙ ብዙ ነገሮች አሉት። ወደ እንደዚህ ዐይነት ማኅበረ ሰብ ስንገባ፣ በተለይ ለሰዎች ነጻ መውጣት ስንጸልይ፣ አጋንንቶችን ስናወጣ … ነበር። ከዚህ አንጻር የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። ብዙዎቹ የውጭ አገር ፈንድ ሳይኖራቸው፣ የተደራጀም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና አመራር ሳይኖራቸው፣ የአምልኮ ቦታ ሳይኖራቸው እንደ ጉድ ሲያድጉና ሲሰፉ አይተናል። በሙሉ ወንጌል ውስጥ ያየሁት እንቅስቃሴ እንደዚህ ዐይነት እንቅስቃሴ ነው።” ሲል የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት የበኩሉን ሚና መጫወቱን ያስረዳል።

ይህ ሲባል ግን የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ እንከን ዐልባ ነበር ማለት አይደለም። ባለፉት ሃያ ዓመታት ከፍተኛ የስሕተትና የኑፋቄ አስተምህሮ እንዲሁም ልምምድ መፍለቂያና መፈልፈያ የሆኑት ጴንጤቆስጣውያኑ መሆናቸው የሚታበል አይደለም። እንዳለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ ያሉት የጴንጤቆስጤ ቤተ እምነቶች ከአስተምህሮ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነው ፍታቴ ይልቅ ወደ ግላዊ ልምምድ እጅጉን ማዘንበላቸው ለስሕተት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል። ግለ ሰቦች ተረዳነው ለሚሉት ማናቸውም ዐይነት መገለጥ ወይም ልምምድ የነበራቸው ያልተገራ ሥሡነት (sensitivity)፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ተጨባጭ (objective) በሆነው እምነትና ሥርዐት ውስጥ እንዳይከለሉ አድርጓቸዋል። በተለያዩ ጊዜያት ለሚነሡባቸው አስደንጋጨ የስሕተት ትምህርቶችና ልምምዶች እሳት የማጥፋት ሥራ ሲሠሩ የቆዩትም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ጉዳት ግን በቤተ እምነቶቹ ዙሪያ ተገድቦ ያበቃ ብቻ አልነበረም፤ የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ከነበረው ከፍተኛ ተጽእኖ የተነሣ ሌሎች በእንቅስቃሴው ጥላ ሥር ያልነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ የአሉታዊው ተጽእኖ ሰለባ መሆናቸው የማይታበል ሃቅ ነው።

ቆይ ግን፤ ማነው ጴንጤቆስጤ?

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ“ነጻነት” ማግስት ከተጋፈጠቻቸው ውስጣዊ ችግሮች አንዱ የስሕተት ትምህርትና ልምምድ መሆኑ ደጋግሞ በመነገር ላይ ያለ ጉዳይ ነው። ይህ የስሕተት ትምህርትና ልምምድ በአመዛኙ “በእምነት እቀንስቃሴ/ብልፅግና ወንጌል” እና እነዚህን አጣማሮ በያዘው “ቅይጥ ክርስትና” ፊት አውራሪነት የሚመራ ነው። እንቅስቃሴው ወጥነት የሌለው ከመሆኑ የተነሣ በአንድ ጎራ ውስጥ ብቻ ሊያስቀምጡት የሚከብድ ተለዋዋጭ ባሕርይ አለው። አሁን አሁን በአገራችን ያሉ የእንቅስቃሴው አራማጆች ራሳቸውን “የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ” ተሟጋች አድርገው ሲያቀርቡ ይታያል። ካሪዝማቲካዊ ቀውሶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የእርምት አስተያየቶችን የሚሰጡ ግለ ሰቦችም ሆኑ፣ ምእመናን ከክፉ ትምህርት እንዲጠበቁ ተገቢውን ርምጃ የሚወስዱ አብያተ ክርስቲያናት (የአገልግሎት ተቋማትን ጨምሮ) በእምነት እንቅስቃሴ/ብልፅግና ወንጌል ሰባኪያንና አራጋቢዎች የጥላቻ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለሆኑ ጥያቄዎች የሚሰጡት ምላሽም በተቃውሞ መፈክር የታጀበ “የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ተቃዋሚ!” የሚል ሆኗል። በርግጥ የጴንጤቆስጤ ክርስትና “በእምነት እንቅስቃሴ/ብልፅግና ወንጌል” አራማጆች ይወካላል እንዴ?

አቶ ዘለለው አርጋው እንደሚለው ከሆነ ይህ እንቅስቃሴ የጴንጤቆስጤ ክርስትናን ሊወክል አይችልም። “ይህንን እንቅስቃሴ ከእግዚአብሔር ነው ብለን እንዳንቀበል የሚያደርጉን ነገሮች አሉ። ይኸውም እንቅስቃሴው በግለ ሰቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፤ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍታቴ (expositions) ብዙም አይጨነቅም፤ የቤተ ክርስቲያን አመራርና የአስተዳደር ዘይቤው በጣም እንግዳ ነው፤ እስከ አሁን ከተለመደውና በአዲስ ኪዳን ቀኖና እንደ መርሕ ብለን የያዝናቸውን የሚጥሱ ነገሮች አሉት፤ ተጠያቂነት የሌለው የፋይናንስ ሲስተም ነው ያለው።” ሲል ምክንያቶቹን ይደረድራል።

አሁን በእኛ አገር ያሉ የእንቅስቃሴው አራማጆች እንደመሟገቻ እያቀረቧቸው ካሉ ነገሮች መካከል የመንፈሳዊ ሥጦታዎች ተፈጻሚነት አንዱ ነው። ተደረጉ የሚባሉ “ፈውሶች”፣ “ድንቆች”፣ “ተኣምራት”፣ ወዘተ. የጴንጤቆስጤ ልምምድ ውጤት መሆኑን ይናገራሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አብሯቸው እንዳለ የሚያምኑት “መንፈስ” በምንም ዐይነት መንገድ የሚፈተሽ ወይም የሚመረመር አይደለም። አስተምህሮም ሆነ የአማኞች ሕይወት፣ አገልግሎትም ሆነ ክርስቲያናዊ ኀላፊነት ለልምምድ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለሚባለው ተጨባጭ መርሕ አይገዛም። የጸጋ ሥጦታዎች እስካሉ ሁሉም አለ፤ “የኀይል አገልግሎት” እስካለ ማንስ ጠያቂ አለ?! ʻከሁሉ በፊት የጸጋ ሥጦታ ይቅደም!ʼ የሚል ጩኸት እዚህም እዚያም እየተደመጠ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ሥልጣናዊነት የተሰኘውን የፕሮቴስታንት የተሐድሶ አቋም ምን ያህሉ አገልጋይም ሆነ ምእመን ከልቡ ያምንበት ይሆን?

የአዲስ ኪዳኑ የጸጋ ሥጦታ ዛሬም ይሠራል ካልን፣ ሰዎችን ወደ ቃሉ እውነት የመመለስ ጉልበት ያላቸው መሆናቸው ላይ መስማማት የግድ ይላል። ሥጦታዎቹ በግለ ሰብ ሕይወትም ይሁን በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ለማነጽ የተሰጡ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያለ አሻሚ ትርጕም ያስተምራል። የጸጋ ሥጦታዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሖዎችን አልፈው ለሕይወትም ሆነ ለአገልግሎት መመሪያ መሆን አይችሉም። ʻየተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል፣ ቀዳሚ የክርስትና ሕይወት መመሪያ ነውʼ የሚለው የወንጌላውያን፣ የጴንጤቆስጤውያን እና የካሪዝማቲካውያን አእማዳዊ አስተምህሮ መሆን ይኖሩበታል። 

የነገረ መለኮት መምህሩ አቶ ዘለለው አርጋው አማኞችም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ተገለጠ በሚባሉ “የጸጋ ሥታዎች” ብቻ ተወስደው እንዳይታለሉ ያሳስባል። “አንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት ስናይ አንዳንድ ጸሐፊዎች ʻpseudo-revivalsʼ የሚሏቸው ሪቫይቫል መሰል ግን ችግሮች ያሉባቸው እንቅስቃሴዎች አሉ። እነዚህ በጣም ዐደገኞች ናቸው። የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን ለመንፈሳዊ ነገር immunized እንድትሆን እንዳያደርጋት እሰጋለሁ።” ሲል እውነተኛ ያልሆኑት ልምምዶች ጥለውት የሚሄዱት ጠባሳ ቤተ ክርሰቲያን ትክክለኛው የሆነው መንፈሳዊ ጉብኝት ሲመጣ እንድትዘናጋ የማድረግ ጉልበት እንዳለው ያሳስባል።

የጴንጤቆስጤ ጭምብል አጥልቆ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊንሰራፋ የሚፈልገው “የእምነት እንቅስቃሴ/የብልፅግና ወንጌል” ከሚታወቅባቸው ባሕርያቱ አንዱ ለእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ያለው የተዛባ አቋሙ ሲሆን፣ መሠረታውያን የሚባሉትን ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችን መናድ “ታላቁ ተልእኮው” ነው። የክርስቲያናዊ ሕይወት ንጽሕናም ሆነ የነፍሳት መዳን “የአገልግሎቱ” ትኩረት አይደሉም፤ የሰውን ልጅ ከተሰጠውና ከሚገባው በላይ በትዕቢት አሳብጦ እዚሁ ምድር ላይ “ማንሳፈፍ” ሌት ተቀን የሚደክምለት ግቡ ነው።

ጴንጤቆስጤውያን ለእምነታችሁ ተጠንቀቁለት!

እንደ ሰሙ ይፍሩ ያሉ ኅልቁ መሣፍርት ምእመናን በስመ “ጴንጤ”፣ በስመ “ጴንጤቆስጤ” ከሕይወት መንገድ እንዳይወጡና የማይጨበጥ ተስፋ ፈላጊ፣ ተንከራታች እንዳይሆኑ የማድረግ ኀላፊነት የሁሉም የወንጌል ባለ ዐደሮች ቢሆንም፣ የአንበሳው ድርሻ ግን የጴንጤቆስጣውያን እና የካሪዝማቲካውያን ሆኗል! ከሁሉም በላይ ራስን ከማጥራት መጀመር ቀዳሚ ተግባራችሁ ሊሆን ይገባል። ‘በርግጥ የምናምነው ይህንን ነው ወይ?’ ብሎ መጠየቅ ለክርስቶስ ወንጌል ንጽሕና ያላችሁን ተቆርቋሪነት በጉልሕ ያሳይላችኋል። ከዚያ ውጭ ያለው ግን ቅይጣዊነት ነው። 

 

Share this article:

ቃል፤ ምጡቅ፣ ፈጣሪ ኵሉ፣ ሥግው

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ዘፍ. 1፥1

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ዮሐ 1፥1-2

በመጀመሪያ ነበርና ከሁሉ በፊት ቃል ኖሯል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

What Would Onesimus Nesib (Abba Gamachis) Plead Ethiopians about Eritrea?

In this article Naol Befekadu asks: “In light of today’s religious freedom in Ethiopia, which was obviously unthinkable during the time of Onesimos, and in light of present-day Eritrea’s persecution of Christianity and other minorities, and the migration of Eritreans to Ethiopia and neighborhood countries, I would love to imagine how would Onesimos Nesib, Abba Gamachis would respond?”

ተጨማሪ ያንብቡ

ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ፦ ዐጭር ታሪካዊ ቅኝት

ገናዬ እሸቱ “የተላኩ” በተሰኘው ዐምድ፣ ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ተብሎ የሚታመንባቸውን የተለያዩ ዘመናትና የወንጌል እንቅስቃስውን ሂደት በወፍ በረር ታስቃኘናለች። ይህ ጽሑፏ በተከታታይ ከምታስነብባቸው የወንጌል ተልእኮ ተኮር ከሆኑ ሥራዎቿ የመጀመሪያው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • የPentecost = በአለ አምሳ ጴንጤ ቆስጤ ጴንጤ
    መቼ ይከበራል?

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.