[the_ad_group id=”107″]

እንዴት እንሙት? እንዴት እንኑር?

በምድር ላይ ረጅም ዕድሜ አልኖረም፤ የኖረበት ጥቂት ዕድሜ ግን እስከ ዛሬ ያላባራ የለውጥ፣ የተሐድሶ፣ የፍስሓ፣ የጸጋ ሞገድ አስነሥቷል። ‘ከኖርኩ አይቀር እንደ እርሱ ልኑር’ የሚያሰኝ ትርጉም ያለው ሕይወት ኖረ። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደሚኖር ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚሞትም አሳየን። ከኑሮው ለመቅዳት የምንሻማ ሁሉ ከሞቱም ለመማር ብንዘጋጅ እጅግ እንጠቀማለን።

እውነቱን ለመናገር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሞት የመጣ ነዋሪ ነበር። “በሥጋና በደም የተካፈለው” (ሰው ሆኖ የተወለደው) በሞቱ አማካይነት በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን ለመሻር ነው። እና በመሞት አሸነፈው፤ በንጹሕ ሞት ድል ነሣው፤ ታይቶ በማይታወቅ ዐይነት መሥዋዕታዊ ሞት ሞትንና አለቃውን ቀጣቸው። ቅርንጫፉን በመቁረጥ ሳይሆን፣ የሞትን ሥሩን በጥሶ አመከነው። የሞት መነሻ ሥሩ ኀጢአት ነበረና የኀጢአትን ሰንኮፍ ሲነቅል ሞት ተልፈሰፈሰ። የእግዚአብሔር ስም ይመስገን። ይህ ሟች ልዩ ሟች ነው። ማንም ይሞታል በኀጢአቱ፣ በአዳምነቱ፤ ይህኛው ግን ያለ ኀጢአት ሞቶ ኀጢአተኛኞች ሟቾችን አጸደቀ። አቤት ጥበቡ!

ይህስ ይሁን፣ ታዲያ ትምህርቱ ምንድን ነው? ከአሟሟቱ ምን እንማራለን?

የወንጌላቱ ትራኬ በሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ደንብ ሲቃኝ አድልዎ ያሳያል። ስለ ሕይወቱ፣ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ ትምህርቱ፣ ከጻፉት ጋር በማይመጣጠን መንገድ ስለ ሞቱ የጻፉት ይበልጣል። ምናልባት የመጽሐፋቸውን እርቦ ያህል የጻፉት ስለዚህ ሰው የመጨረሻ ሳምንት ሳይሆን አይቀርም። በከንቱ አላደረጉትም፤ ሞቱ ግዙፍ ሞት ነበርና።

የመጀመሪያው ትምህርት

ኢየሱስ ክርስቶስ ኑሮው የተለካ ዐጭር ጊዜ እንደ ነበረ ዐውቆ፣ ይህንኑ እየተናገረ፣ በዚሁ ዕይታ ይኖር የነበረ ሰው ነበር። በታላቅ መረጋጋት ውስጥ ሆኖ እያለ አንዳች የተልእኮ ጥድፊያ ደግሞ ይጎተጉተው እንደ ነበር ያስታውቃል። “…ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ፤ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም…” ዮሐ 7፥33-34፤ “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል” (ዮሐ 9፥4)፤ ለመሞት ተዘጋጅቶ በተልእኮ ልቡና ውስጥ ይኖር ነበር።

የእኛስ እድሜ ልክ የለሽ ነው እንዴ? ‘ሌሎች ሊሞቱ ይችላሉ፤ እኔ እንኳ ሳልቆይ አልቀርም’ ማለት ከፍተኛ ሽንገላ አይደለምን? የሞትን እውነታ ገፋ ገፋ ማድረግ ሰብአዊ ጨዋታ ሳይሆን አይቀርም። የምር ስንነጋገር ግን ይህን ዐረፍተ ነገር እንኳ አንብበን ሳንጨርስ ሕይወት ልትቋረጥ እንደምትችል አንዘነጋውም። እንግዲያው አንዱ የጌታ ትምህርት ሕይወት ጥቂት ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት መሆኑን ተገንዝቦ በተልእኮ ልቡና እንዲሁም በሥራ ትጋት መኖር ነው። ሕይወት ከቸሩ ጌታ የተሰጠችን ጥሪት ናት። ሙዐለ ሕይወት ትርፋማ እንዲሆን ሳንጨነቅ፣ በብርቱ ትጋት እንድንሠራ ያሻል።

ሁለተኛው ትምህርት

ጌታችን ሞትን እንደ ክብር መሸጋገሪያ መንገድ አድርጎ የቆጠረበት አተያይ ነው። የሞቱ ጊዜ ደረሰ ማለት ለጌታችን የክብሩ ጊዜ ደረሰ የማለት ያህል ነበር። አሟሟቱ ላይ ላዩን ሲያዩት የታላቅ ውርደት ይመስል ነበር። በሐሰተኛ ምስክሮች ተከስሶ፣ በቅርብ ጓደኞቹ ተከድቶ፣ አጠገቡ በነበረ ተማሪው በገንዘብ ተሸጦ፣ በወታደሮች ጥፊና ድብደባ፣ በጅራፍ ግርፊያና በስላቅ እየተነዳ፣ እርቃኑን በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ዐላፊ አግዳሚ እያላገጠበት የሞተውን ሞት እንዴት ነው የክብር መንገድ የሚለው?

ነገሩ እንዲህ ነው፤ መሬት ሲሳለቅበት ሰማይ ያጨበጭብለት ነበር፤ ጲላጦስ እንዲሰቀል ሲፈርድበት አባቱ ትንሣኤውን ያዘጋጅለት ነበር፤ ብቻውን ቀርቶ እየጮኸ ሲሞት ለአእላፍ አማኞቹ የሰማይ በር ያስከፍት ነበር። ሞቱ ታላቅ ዐላማ ስለ ነበረው ጻድቅ አምላክ ያከበረው ሞት ነበረ። አባቱን እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ታዝዞ፣ የሰውን ልጅ እስከ መጨረሻው ድረስ ወድዶ ስለ ሞተ ታላቅ ክብር ተጎናጸፈ። “… በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው” ብሎ ይለናል ሐዋርያው ጳውሎስ (ፊል 2፥9)። እንግዲያው ለእኛ ለምናምነው ሁሉ የመታዘዝና የፍቅር አርኣያ ሆነልን፤ የክብርን መንገድ አሳየን። እና እኛ ከመሞታችን በፊት በዚህ በጠረገልን መንገድ ስንጓዝ፣ በሕመም ብንሞት፣ በአደጋ፣ በእርጅና በሌላ በማናቸውም “አሰቃቂ” ይሁን “ለስላሳ” አሟሟት ብንሞት ግሥገሳችን ወደ ክብር እንደ ሆነ እንድናስብ ያሻል። ‘ጎሽ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ እንኳን ደኅና መጣህ!’ ወደሚለን ቸር አባት እየቀረብን መሆናችንን እናስብ።

ሦስተኛ ትምህርት

ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱን እውነት አስቀድሞ ቢረዳም እጅ አጣጥፎ፣ ጉልበቱን ኮርትሞ በሰቀቀንና በድንጋጤ ሞትን አልተጠባበቀም። እስከ መጨረሻ ትንፋሹ ሕቅታ ድረስ በጎ እየሠራ፣ የያዙትን ወታደሮች እየፈወሰ፣ ለሰቀሉት ምሕረት እየለመነ፣ ከአባቱ ጋር በጸሎት እየተነጋገረ “ተፈጸመ” ብሎ ነፍሱን ሰጠ።

እስክንሞት ድረስ ቦዝዘን እንዳንቀመጥ፣ ከበጎ ሥራ እንዳንታክት፣ ከጸሎት እንዳናፈገፍግ፣ ‘ወይኔ ጉዴ’ እያልን በሰቀቀን እንዳናልቅ አስተማረን። እያንዳንዷን ሰዓት በዘላለም መዝገብ ውስጥ የሚገባ የሰላምና የፍቅር ዘር እየዘራን እንሙት (ያው መሞታችን አይቀርም ብዬ ነው)። የምንወድዳቸውን በጣም እንውደዳቸው፤ ለሚጠሉን እንጸልይላቸው፤ ለአገርና ለሕዝብ መልካሙን ሁሉ እንመኝ፤ እንናገር፤ እንባርክ። እንደዚያ ሀኬተኛ ባሪያ መክሊታችንን ቀብረን የቁጥጥሩን ቀን በድንጋጤ አንጠብቅ። በተሰጠን ትንሽ ትንፋሽ እንኳ በመክሊታችን እየነገድን እንሙት።

አራተኛ ትምህርት

ለሞቱ ቀን ተማሪዎችን እያዘጋጃቸው ሳለ፣ ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መዝሙር ዘመረ (ማቴ 26፥30)። ምን እንደ ዘመሩ ባይጻፍልንም፣ የእኔ ግምት የፋሲካ ሰሞን ስለ ነበረ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ነጻ የወጣበትን፣ የእግዚአብሔርን ትድግናና ግርማ የሚናገር የነጻነትና የምስጋና መዝሙር ሳይሆን አይቀርም። በሞት ሰሞን መዝሙር አልተከለከለም። የሚሠራውን የሚያውቀውና የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነውን፣ የነፍስ ሁሉ ባለቤት የሆነውን ጌታ እያመሰገንነው እንሙት። ሮበርት ፍሮስት ስመጥር አሜሪካዊ ባለ ቅኔ ነበረ። እንጨት አጥር ላይ ቆማ በጧት የምትዘምር ወፍ፣ ሥራ በፈታ አንድ ልጅ በተወረወረ ድንጋይ ተመትታ ጸጥ ስትል አዝኖ እንዲህ አለ፦

There must be some wrong;
in silencing any song!
መዝሙር የሚያዳፍን ዜማ የሚከለክል፣
ጤና ሰው አይደለም ሠርቷል ትልቅ በደል!

ሌላም ብዙ ትምህርት አለው። ለምሳሌ፣ በመስቀል ላይ እየሞተ ሳለ ስለ ወላጅ እናቱ አስቦ ለዮሐንስ ዐደራ መስጠቱ ትልቅ የኀላፊነት አብነት ነው።

የመጨረሻው እራት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲበላ፣ ህብስቱንና ወይኑን ሲሰጣቸው “በእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲሷን ወይን እስክንጠጣ ከዚህ በኋላ አልጠጣውም” ማለቱ የትንሣኤንና የዳግም ምፅዐቱን ተስፋ የሚያለመልም የተረጋጋ ንግግር ነው። ከዚህ ሕይወት በኋላ ሌላ የከበረ ሕይወት አለ፤ ይህንን እየተናገረ የሞተ ሰው ነበረ።

ሁሉን ትምህርት ዘርዝረን አንጨርስም …

ነገር ግን ይህ አስገራሚ ሞት የሞተው ትሑቱ ኢየሱስ የገሃነም ኀይሎች ሊቋቋሙት በማይችሉት ታላቅ ኀይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። በእርሱ የምናምን የሁላችንን ዕንባ የሚያብስ፣ ነፍሳችንን የሚመልስ፣ የመጽናናት ብሥራት ሰጠን። እና ወዳጆቼ እንደ ጳውሎስ፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነው” የማለት ጸጋ ያድለን።

Nigussie Bulcha

መከራው እስካለ

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ እንደ ሆነች እየታየኝ ነው። መከራው ግን ስውር ነው። . . . ስደትን የወንጌላውያን ብቻ አድርጌ ሳስብ መኖሬና ቀድሞ ዘመን ‘ባደረገችው ነገር እግዚአብሔር እያስተማራት ይሆን እንዴ?’ የሚለው መልስ የማይፈልግ ጥያቄዬ ነበር። ይሁን እንጂ፣ እየሆነባት ያለው ከስደት ጋር አንድ መሆኑን በጭላንጭልም ቢሆን . . . እየተረዳሁት ነው።” ባንቱ ገብረ ማርያም

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.