[the_ad_group id=”107″]

ክርስትና ወደ ኢትዮያ መቼ ገባ?

ጃንደረባው እና ፊልጶስ

ኢትዮጵያ ክርስትናን ከተቀበሉ ጥንታዊ አገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም፣ ክርስትና ወደ አገሪቱ መቼ እንደ ገባ በርግጠኝነት አይታወቅም። ብዙዎች በሐዋርያት ሥራ 8፥26 ላይ የተጠቀሰውን የፊልጶስ እና ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ታሪክ መሠረት በማድረግ በ1ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ሆነ ይስማማሉ። ሌሎች ደግሞ በሐዋርያው ማቴዎስ ስብከተ ወንጌል አማካኝነት ነው ሲሉ፣ ሦስተኛው ወገን በፍሬምናጦስ አማካኝነት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ገብቷል ይላል። እነዚህን ሦስት አመለካከቶች በተወሰነ ቅርበት እንያቸው።

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1ኛው ክፍለ ዘመን ነው ሲባል፣ ሁለት ምክንያቶች ይነሣሉ። አንደኛው፣ ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት የአይሁድ እምነት ከመቀበሏ ጋር የተያያዘ ነው። በሐዋርያት ዘመን ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ በተጨማሪ፣ ጆን ቸርሶስቶም በመጽሐፉ ላይ፣ (St John Chrysostom, In Homily on Pentecost) በጴንጤቆስጤ ቀን ኢትዮጵያውያኖች በኢየሩሳሌም እንደ ነበሩ ይናገራል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ከኢየሩሳሌም ጋር ከነበራት ግንኙነት አንጻር በበዓለ አምሳ ጊዜ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በብዙ ቋንቋ ሲናገሩ ለበዓሉ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ወንጌልንም በግዕዝ እንደተሰበኩ ይነገራል። 

ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጕ በፊት፣ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በእየሩሳሌም በይሁዳም ሁሉ በሰማሪያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” (የሐሥ 1፥8) ብሎ ነበር። ይህንንም የክርስቶስ ትዕዛዝ ተከትሎ፣ ደቀ መዛምርቱ ከበዓለ አምሳ በኋላ ወንጌሉን ወደ ይሁዳና ሰማሪያ እንዳደረሱ ቀጥሎም፣ በፊልጶስ በኵል ለአፍሪካው ጃንደረባ ወንጌል እንደተመሰከረለት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

ኢትዮጵያውያን እንደ እስራኤላውያን በየዓመቱ ለበዓል የመስገድ እና አምልኮተ እግዚሐብሔርን የመፈጸም ልማድ ነበራቸው። የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ እንደ ራሴና ገንዘብ ያዥ የነበረው ጃንደረባ ለእስራኤል አምላክ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር። ጃንደረባውም ሰግዶ ሲመለስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ እርሱ የመጣውን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር በሆነው በፊልጶስ አማካኝነት ክርስትናን ተቀብሎ ተጠምቆ ተምልሷል።

“የጌታም መልአክ ፊልጶስን ‘ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ’ አለው። እነሆም፣ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ፣ በገንዘቧም ሁሉ የሠለጠነ አንድ ኢትዮጵያዊ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መቶ ነበር። ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን፣ ‘ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ’ አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብብ ሰማና፣ ‘በእውኑ የምታነብበውን ታውቀዋለህን?’ ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ ‘የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ያቻላል?’ አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነብበው የነበረ የመጽሐፍ ክፍል ይህ ነበር፦ ‘እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሽላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደት ፍርዱ ተወገደ። ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?’ ጃንደረባውም ለፊሊጶስ መልሶ፣ ‘እባክህ፤ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን? ወይስ ስለ ሌላ?’ አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ውሃ ወዳለበት ቦታ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ ‘እነሆ፤ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?’ አለው። ፊሊጶስም፣ ‘በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዷል’ አለው። መልሶም፣ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ’ አለ፤ ሠረገላውም እንዲቈም አዘዘ። ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውሃው ወረዱ፤ አጠመቀውም። (የሐሥ 8፥26-38)

ይህ ጃንደረባ በ34 ዓ.ም. ገደማ ክርስትናን ተቀብሎ ከተመለሰ በኋላ፣ ታዋቂ የመንግሥት ባለሥልጣን እንደ መሆኑ ለብዙዎች የሰማውን ወንጌል እንዳስተላለፈ፣ በዚህም መልካም ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደ ቻለ ይታመናል። የኢትዮጵያም የታሪክ መዛግብትም ጃንደረባው ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ወንጌልን እንደ ሰበከ ያሳያሉ።

ለታሪክ አዎቂዎች አስቸጋሪ የሚሆነው፣ አሁን በዚህ ዘመን ያለችውን ኢትዮጵያ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተጻፈችውን ኢትዮጵያ መካከል ያለው ንፅፅር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሰው ኢትዮጵያዊ ቢለውም፣ የህንደኬ ንግሥት መናገሻዋን ኑቢያ በማድረጓ፣ ጃንደረባው የኑቢያ መንግሥት ባለሥልጣን እንደ ሆነ ስምምነት አለ። በጥንቱም መልክዓ ምድር ኢትዮጵያ፣ ከግብፅ በስተ ደቡብ ያለውን ኑቢያንና አክሱምን እንዲሁም በጥቅሉ የኩሽ ምድርን የሚያካትት ስያሜ ነበር። የህንደኬ ንግሥት የገዛችው ተብሎ የሚታመነው የኑቢያን እና ሜሮይ ግዛት በ350AD በንጉሥ ኢዛና ጦር እንደ ተያዘችና ዋና ከተማዋም ሜሮይ እንደ ተደመሰሰች ይታመናል።

ማቴዎስ

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያው ማቴዎስ አማካኝነት እንደ ሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ይህም የክርስቶስ ሐዋርያት በዓለም ዙርያ ተበትነው ወንጌልን ሲሰብኩ፣ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለወንጌል መሥዕዋት እንደ ሆነ ይነገራል። ይህም ታሪክ በጥንታዊው የታሪክ ጽሐፊ ሩፊኖስ እና ሶቅራጥስ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ስንክሳር (Synaxarium) ግን ይሄንን ታሪክ አይጠቅስም። በአንጻሩ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው የሐዋርያት ደም ሳይፈስስ ነው ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ይህ ታሪክ በሌሎች መዛግብት ላይም የሚገኝ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ መዛግብትም ማቴዎስ በትግራይ አድዋ አውራጃ እንዳስተማረ ጭምር ይገልጻሉ።

አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ)

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ በዐጭር ጊዜ ውስጥ ይነገራል። የክርስትና ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ ታሪክ አስመልክቶ ግን ብዙ ተቀባይነት ያለው ከ345-410 ዓ.ም. በኖረው የሮማ ጸሐፊ እና የታሪክ ተመራማሪ ሩፊኖስ (Rufinus) የተጻፈው የቤተ ክርስትያን ታሪክ ነው። ሆኖም ግን ከአራተኛ እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተገኙ የግዕዝ መዛግብት ከአራተኛውም ክፍለ ዘመን በፊት ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንደ ነበር ያሳያሉ።

ሩፊኖስ እንዳመለከተው በ300 ዓ.ም. አካባቢ መሮፔዎስ የተባለ መኖሪያው በጢሮስ የሆነ ግሪካዊ፣ በአፍሪካ ዳር በአልጄርያና በቱኒዚያ፣ በትሪፖሊና በእስክንድሪያ እየዞረ ይነገድ ነበር። ይህም ነጋዴ ሁለት ልጆቹን ፍሬምናጦስን እና አድስዮስ (ሲድራኮስን) አስከትሎ በቀይ ባህር በኩል፣ ጥንት የኢትዮጵያ ወደብ በነበረው በአዱሊስ ወይም አለመንደብ በተባለው ወደብ አካባቢ ሲጠጉ፣ ከሮማ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቍመው የነበሩት የአገሪቱ ነዋሪዎች አደጋ ጣሉባቸው። መሮፔዎስን እና መርከቡ ውስጥ የነበሩትን ሌሎች ሰዎች ገድለው የነጋዴውን ልጆች ፍሬምናጦስን እና አድስዮስ ብቻ በማትረፍ ወደ ቤተ መንግሥት በማምጣት ለሐማሴኑ ገዢ ሰጧቸው። የሐማሴኑ ገዢም ወደ አክሱም ወስዶ ለንግሥት የሕየዋ (ሶፊያ) ሰጣት። ንጉሡም ኤልኤማዳ በማስተዋላቸውና ብልሀታቸው ተገርሞ፣ ፍሬምናጦስ ለልጆቹ የሥነ ምግባር እና የሃይማኖት አስተማሪ፣ አድስዮስን ደግሞ ጠጅ አሳላፊ አድርጎ ሾማቸው።

ንጉሡ ለሚስቱ እና ለልጁ ዙፋኑን አውርሶ በጐልማሳነቱ ሕይወቱ ዐለፈ። ሆኖም ከመሞቱ በፊት ፍሬምናጦስ እና አድስዮስ ወደ አገራቸው መሄድ ከፈለጉ እንዲሄዱ ፈቃዱን ሰጥቶ፣ ፈቃዳቸው ቢሆን ግን ንግሥቲቱን ልጆቻቸው ዐድገው ለሥልጣን እስኪ በቁ በማስተዳደር እንዲያግዟት ጠይቆ ነበር፤ እነርሱም ተስማምተው በኢትዮጵያ ቈዮ።

ፍሬምናጦስም ከሕፃንነቱ ወንጌልን እየተማረ ያደገ ክርስትያን ስለ ነበር፣ ለንግሥቲቱ፣ ለልጆችዋ፣ ለመኳንንቱም የክርስቶስን መንግሥት ወንጌል ማስተማሩን ቀጠለ። ታዳጊው ንጉሥም የክርስትና እምነት ተከታይ ሆነ። ኢዛና በራሱ አገር ማስተዳደር የሚችልበት ዕድሜ ላይ ሲድርስ፣ አድስዮስን ወደ አገሩ ለመመለስ ሲወስን፣ ፍሬምናጦስ ወደ እስክንድሪያ በመሄድ በዚያ የነበሩትን ፓትርያልክ አትናቴዎስ ዘንድ በመቅረብ በአክሱም እያደጉ ላሉት የክርስትን ማኅበረ ሰቦች የሚያገለግል የሃይማኖት አባት እንዲልኩ ጠየቀ። ፓትርያልኩም ጳጳሳቱን ሰበሰቡና በዚህ ጕዳይ ላይ ከተመካከሩ በኋላ፣ አትናቴዎስ የሕዝቡን ባህል፣ ልማድ፣ ቋንቋ የለመደ እና የሚያውቅ ካንተ የተሻለ ሰው አናገኝም በማለት ራሱን ፍሬምናጦስን አስተምረው የመጀመሪያው ጳጳስ አድርገው ሾመውና መጽሐፍ ቅዱስ አስይዘው ወደ አክሱም ላኩት።

ፍሬምናጦስ በ341 ዓ.ም. ወደ አክሱም ተመልሶ ወንጌል መስብኩን ቀጠለ። የአክሱም ሰዎች ፍሬምናጦስ ብርሃን የሆነውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው እንዲሁም በጣም ያከብሩትና ይወድዱት ስለ ነበር ስሙን ከሳቴ ብርሃን (ብርሃሃ ገላጭ) ብልው ይጠሩት ነበር። ከሳቴ ብርሃን መባሉ በጨለማ በኀጢአት ለሚኖሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የወንጌል ብርሃን ስላሳያቸው ነው። ከዚህም ጋር አያይዘው ሰላማ (የሰላም ሰው) ብለው ጠርተውታል። ሰላማም ያሉት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተው ለሚኖር ሕዝብ ወንጌሉን በመስበክ ስላስታረቆቸው ነው። ቅዱስ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በሏላ በእጁ ያለውን የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግዕዝ ተርጕሟል።

ኢዛና ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ክርስትና የአገሪቱ እምነት ሆኖ በንጉሣዊው መንግሥት ተቀባይነትን አገኘ። ይህ ማለት ግን ክርስትና ለኢትዮጵያ የተዋወቀው በኢዛና የንግሥና ዘመን ነው ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከግሪክ እና ሮማ ጋር ከነበራት የንግድ እና የባህል ግንኙነት የተነሣ በቀይ ባሕር በኩል ለንግድ ወደ አገሪቱ በመጡ ክርስትያን ነጋዴዎች ከማኅበረ ሰቡ ጋር በነበራቸው ግንኙነት እንደ አክሱም እና አዱሊስ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ላይ አማኞች ነበሩ።

እንዲሁም ክርስትና በንጉሣዊው መንግሥት ተቀባይነት ማግኘቱ ክርስትና የሕዝቡ ሃይማኖት ሆኖ ነበር ማለት አይደለም። አብዛኛው ሕዝብ የባዕድ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። ሆኖም ግን ክርስትና ቀስ በቀስ የተስፋፋ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ክፍል የምናያቸው ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለዚህ ትልቅ አስተዋፆ አድርጓል።

ዋቢ መጻሕፍት

 • St,Jhon Chrysostom, Homily on the Acts of the Apostles, NPNF Philip Scaff, 1886
 • Ephrem Yisak, The Ethiopian Orthodox church, the Red Sea Press, Institute of Semetic Studies, Princeton P. 17
 • Sergew Habte Selassie, Anchient and Medivial Ethiopian History to 1270, P. 97
 • Rufinus, Historica Ecclesiastica, vol. xxi, col 479: Socrates Scolasticus,-Historia ecclesiastica p.57
 • በጆናታን ሃልደብራንት (ትርጕም ጌቱ ግዛው)፤ የቤተ ክርስትያን ታሪክ በአፍሪካ ‘Lapsley/ Brooks Foundaton, Addis Ababa (1993)/ Dallas, Texas, USA (2001)’ editor ገበየሁ አየለ ገጽ 13-14
 • ወንድዬ ዓሊ፤ እኩለ ሌሊት ወገግታ ቅስ አንድ (1934 1966) የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስትያን ታሪክ 1992 ዓ.ም.። ኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስትያን የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት፤ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ።
 • Fekadu Girma, Evangelical Faith Movement in Ethiopia; Origions and Establisment of the Ethiopian Evangelical Church, Mekane Yesus, Lutheran University Press, 2009
 • Kiros Habte Silassie and Mazengia Dina Ethiopia, A short Illustrated history, Addis Ababa, Ministry of Education and Fine Arts 1969
 • Fekadu Girma, Evangelical Faith Movement in Ethiopia; Origions and Establisment of the Ethiopian evalgelical Church, Mekane Yesus, Lutheran University Press, 2009p. 16-`17
 • Siegbert Uhlig in cooperation with Alessandro Bausi, et al. (eds.) (2010). Encyclopaedia Aethiopica, Vol. 4: O-X. Wiesbaden: Harrassowitz Verlag
 • በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግኅት ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፤ ሴንትራል ፕሪንተርስ፤ አዲስ አበባ፣ ገጽ 15
 • Richard Pankhurst The Ethiopians, The People of Africa Series, Oxford Blackwell pub, 1998

 1. ፍረምናጦስ አትናቴዎስን ለማግኘት በተጓዘበት ወቅት አትናቴዎስን በአርዮሳውያን ስደት ደርሶበት ከመንበሩም ተባሮ ስለ ነበር፣ በቀላሉ ሊያገኘው አልቻለም ነበር። ለሦስት ዓመታትም ያህል ከጠበቀ በኋላ አትናቴዎስ ወደ ቦታው ሲመለስ ሊያገኘው ችሏል። አትናቴዎስንም በተሰደደበት ወቅት አርዮስ ብዙ መጽሓፍት እያባዛ ሲያሰራጭ እና የሕዝቡንም እምነት ሲበርዝ አትናቴዎስም የአርዮስን የስሕተት ትምህርት ለመቅደም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከያሉበት እንዲሰበሰቡ በማድረግ 27ቱን ቅዱሳን መጻሕፍት በአንድ ላይ እንዲጠረዙ አድርጓል። በወቅቱም ቢፅ ሐሳውያን በሐዋርያት ስም ብዙ መልእክቶችን ጽፈው ስለ ነበር ሥራው ከባድ ነበር። ለአትናቴዎስ ወደ 600 መጻሕፍት የቀረቡለት ሲሆን፣ ከብዙ ማጣራት ሥራ በኋላ በእግዚአብሔር ዕርዳታ 39 የብሉይ እና 27 የአዲስ ኪዳን በጥቅሉ 6 መጻሕፍትን በማዘጋጀት 50 ኮፒም አባዝቶ አብያተ ክርስትያናት እንዲመረምሩት ሰጥቷል። እነእርሱም ከስሕተት ንፁሕ እንደ ሆነ ተስማምተው፣ የቤተ ክርስትያን መመሪያ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፈዋል።
 2. ፍሬምናጦስ የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግዕዝ ከመተርጐሙ በፊት፣ የኢትዮጵያ ምሁራንን አሰባስቦ የግዕዙን ፊደል መልክ ማስያዝ አስፈልጎት ነበር። ይኸውም የግዕዝ ፊደል፣ ‘ሀለሐመ ሠሸቀበ…’  የነበረ በመሆኑ ለስሕተት ትርጕም ስለሚያጋልጥ እስከ ሰባት እንዲበተን በማድረግ (ለምሳሌ፣  ሀ ሁ ሂ ሃ ሄ ህ ሆ) ተደርጎ ዛሬ የምንጠቀምባቸው ፊደላት ተሠርቷል። 

Genaye Eshetu

Genaye Eshetu is a Creative Communicator. She did her BA in Language and Literature and her Masters in Journalism and Communication. She aspires to combine and use various communications means, especially media, which is the global language of this generation, for creative evangelism.

Share this article:

የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት:- የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ

አማረ ታቦር Seeing and Savoring Jesus Christ ከተሰኘው የጆን ፓይፐር መጽሐፍ በተከታታይ ከሚያቀርባቸው ጽሑፎች መካከል፣ ይህ “የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት፦ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ” ሲል ወደ አማርኛ የመለሰው ይገኝበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“የውጭ ወራሪና የውስጥ ቦርቧሪ ያልናቸውን ትምህርቶች መግረዝ ይችላሉ ባይ ነኝ”

ተስፋዬ ሮበሌ ለትምህርት ከኢትዮጵያ እስኪወጣ ድረስ የተስፋ ዐቃቢያነ ክርስትና ማኅበርን በዳይሬክተርነት አገልግሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕቅበተ እምነት ርእሰ ጒዳዮች ላይ የተለያዩ መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡ ከእነዚህም መካከል “የይሖዋ ምስክሮችና አስተምህሮአቸው በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን”፣ “ውሃና ስሙ፡- ʻየሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንʼ የድነት ትምህርት በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን”፣ “ዐበይት መናፍቃን” እንዲሁም “የዳቬንቺ ኮድ፡- ድርሳነ ጠቢብ ወይስ ድርሳነ ባልቴት?” ይጠቀሳሉ፡፡ ተካልኝ ዱጉማ በዕቅበተ እምነት ጕዳዮች ዙሪያ ከተስፋዬ ሮበሌ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

3 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • በጣም ጡሩ ስራ ነው ከልቤ ላመሰግን እወዳለሁ ።በዚህ አጀማመር መቀጠልን እዳይረሱ “እግዚአብሔር ከናተ ጋር ይሁን አሜን

 • God bless you
  የእግዚአብሔር ፀጋ ከእናንተ ጋር እንድሆን እመኛለሁ በርቱ ወንጌል ለፍጥረታት በዚህ መልክ እንደሚደርስ አልጠራጥርም ።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.