[the_ad_group id=”107″]

የእምነትን ሩጫ እንዴት እንሩጥ?

24 በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። 25 የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። 26 ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ 27 ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። (1ቆሮ. 9፥24-27)

24 በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። 25 የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። 26 ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ 27 ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። (1ቆሮ. 9፥24-27)

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመዲናችን አዲስ አበባ “ታላቁ ሩጫ” የሚል ስያሜ የተሰጠው በቁጥር በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበት ሩጫ በየዓመቱ ይካሄዳል። የውድድሩ ዐይነተኛ መገለጫም በሩጫው ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በዕድሜ፣ በቀለም ወይም በጾታ አለመገደባቸው ነው። ሌላው ይሄንን ሩጫ ልዩ የሚያደርገው ነገር በውድድሩ ውስጥ የሚሳተፈው ሰው በየትኛውም ሰዓት ሮጦ ሩጫውን እስከ ጨረሰ ድረስ የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑ ነው። በዚህ ሩጫ ላይ ተሸላሚ ለመሆን ወይም ዋጋን ለማግኘት ዋነኛው ነገር ሩጫውን ሮጦ መጨረስ ብቻ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ጌታን አዳኛችን አድርገን በማመንና ሕይወታችንን ለእርሱ በመስጠት የጀመርነው የእምነትን ጉዞ በሩጫ ይመሰላል። በቅዱሱ መጽሐፍ አንድ ሰው ጌታን አዳኙ አድርጎ ካመነበትና ከተቀበለበት ጊዜ አንሥቶ በሕይወቱ ውስጥ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ እያለፈ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀው የሕይወት ልክ እስከሚደርስ ድረስ የሚያደርገው ግስጋሴ የእምነት ሩጫ ተብሎ ተጠርቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ አማኞች የእምነትን ሩጫ እንዴት አድርገው መሮጥ እንደሚኖርባቸው የሚያሳይ ታላቅ መንፈሳዊ የሕይወት መመሪያን ሰጥቷቸዋል። ዛሬም ልክ እንደ እነርሱ የሕይወትን ሩጫ ለጀመርን ለእኛ እንዴት አድርገን መሮጥ እንዳለብን የሚያመለክተንን መልእክት እንካፈላለን። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ቆሮ. 9፥25-27 ባለው ክፍል ላይ ለቆሮንቶስ ምእመናን ከሰጣቸው ትምህርት ውስጥ ሁለት ነገሮችን እንመለከታለን።

1. በመጨሻው ቀን ብድራትን እንደምናገኝ በማሰብ መሮጥ ይኖርብናል (24-25)

አማኝ በጀመረው ግስጋሴ ላይ ምንም እንኳን በሕይወቱ ይህ ነው የማይባል ተግዳሮት የሚገጥመው ቢሆንም፣ ማሰብ የሚኖርበት አንድ እውነት በመጨረሻው ቀን ላይ ከጠራው ጌታ ዘንድ የከበረ ብድራትን እንደሚያገኝ ነው። የቆሮንቶስ ከተማ በጊዜው በነበረው የግሪክ ባህልና ፍልስፍና ጫና የበዛባት ከተማ ስለ ነበረች የግሪኮች የስፖርታዊ ጨዋታዎችና ውድድሮች ይካሄዱባት ነበር። ከእነዚህም ጨዋታዎች መካከል አንደኛው ሩጫ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስም በዚያን ጊዜ የነበረውን ሩጫ እንደ ምሳሌ በመውሰድ ለመንፈሳዊ ሕይወት ሩጫ እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል።

በስፖርቱ ዓለም በሩጫ ላይ ምንም እንኳን በርካታ ሰዎች በውድድሩ ውስጥ ተሳታፊዎች ቢሆኑም ሽልማትን በተመለከተ ግን የሚያገኘው አንደኛ የወጣው ሰው ብቻ ነበር። ሁሉም ሰው ሊሮጥ ይችላል፤ ሆኖም ግን የሮጠበትን ዋጋ የሚቀበለው ግለ ሰብ ቀዳሚ ሆኖ የገባው ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን “ታገኙ ዘንድ ሩጡ”

በማለት በክርስትና ሕይወት ሩጫውን ሮጦ ከፍጻሜው የደረሰ ሁሉ የሕይወትን አክሊል የሚያገኝ መሆኑን ይናገራል። ሐዋርያው በዚህ ስፍራ ላይ የሚያመለክተው አማኝ በሕይወቱ በጀመረው ሩጫ ላይ ማሰብ የሚኖርበት የሩጫውን አድካሚነት ሳይሆን፣ በፍጻሜው ላይ የሚያገኘውን መለኮታዊ ብድራቱን ነው። በሌላ አባባል ሮጦ ያልጨረሰ ወይም በመንገድ ላይ የቀረ ሰው ብድራትን አገኛለሁ ብሎ ማሰብ የለበትም ማለቱ ነው። በሩጫው ማብቂያ ላይ የሚገኝ አንድ የከበረ ዋጋ አለ፤ እርሱም የማይጠፋ የሕይወት አክሊል ነው። ያንን ለማግኘት በማሰብ ሩጡ ነው የሚላቸው። በመቀጠልም፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የሽልማቱን ክብር በንጽጽር ያስቀምጣል። በምድር ላይ የሚሮጡት ሰዎች ሮጠው የሚያገኙት ሽልማት የሚጠፋ አክሊል እንደሆነ፣ በአንጻሩ ግን አማኞች በያዙት የእምነት ሩጫ መጨረሻ ላይ የሚያገኙት የማይጠፋውን አክሊል መሆኑን አጽንኦት ይሰጣል። በእምነት ሩጫ ላይ ሙሉ ትኩረትን ማድረግ የሚገባው በፍጻሜው ላይ በምናገኘው ብድራታችን ላይ ነው በማለት የቆሮንቶስ አማኞች ብድራታቸውን ትኩር ብለው በመመልት በዓላማ እንዲሮጡ ያበረታታቸዋል።

ስንቶች ነን በያዝነው የሕይወት ጉዞ ላይ ብድራታችንን ብቻ እያሰብን የምንሮጥ? በያዝነው የእምነት ሩጫ ላይ ሙሉ ትኩረታችን ከጌታ ዘንድ የምናገኘው መለኮታዊ ብድራት ላይ ይሁን እንጂ ግራና ቀኝ እየተገላመጥን እርባና ቢስ በሆነው በዚህ ዓለም ነገር አንጠመድ። ከእኛ ጋር አብሮን የእምነትን ሩጫ የሚሮጠውንም ሌላውን ወንድማችንን ጠልፈን ለመጣል አንሞክር። አንዳንዴ ብድራታችን ከጌታ ዘንድ ሳይሆን እዚሁ ከምድር የሆነ ይመስል ረብ የሌለው ትርፍን ከሰዎች ለማግኘት ሽር ጉድ ስንል እንታያለን። በርግጥ የክርስትና ሕይወት መንገዱ ቀጥ ያለና ምንም ትግል የሌለበት አይደለም። ሆኖም ግን በዚያ ውስጥ የሚረዳንን ጸጋ የሚሰጠን ሕያው ጌታ ከእኛ ጋር ስለሆነ ልባችንን አበርትተን አሁን ያጣነውን ሳይሆን በመጨረሻው ቀን ልናገኝ ያለውን ብድራት እያሰብን እንሩጥ።

2. ሁልጊዜ ስንሮጥ ሕይወታችንን በመመዘን መሆን ይኖርበታል (26-27)

አማኝ በያዘው የሕይወት ሩጫ ላይ ሌላው ማሰብ የሚኖርበት ቁም ነገር ራሱን በሚገባ ማየት ነው። ይኸውም አገልግሎቱንና ሕይወቱን በተመለከተ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መገንዘብ ይኖርበታል። በዚህ ስፍራ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲናገር “ዝም ብዬ ያለ ዋጋ አልሮጥም፤ ነፋስንም እንደሚጎስም ሰው በከንቱ አልሮጥም” በማለት እየሮጠበት ባለው ሕይወት ሩጫ ላይ በምን ዐይነት ብቃት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል። “እኔ ያለ ሐሳብ አልሮጥም” በእውነትም ይሄ አባባሉ በሩጫው ላይ ምን ያህል በማስተዋልና በትኩረት እየገሰገሰ እንደ ሆነ ያሳየናል። በዚህ መልኩ የማይሮጥ ቢሆን ምን ዐይነት አደጋ ሊገጥመው እንዳለም ይናገራል። ይህንንም ሲገልጽ፣ “ለሌሎች ወንጌልን ከሰበክሁ በኋላ እኔ ግን የተጣልሁ ሆኜ እንዳልቀር ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” በማለት ከአገልግሎቱ በላይ ለሕይወቱ ከፍተኛ ጥንቃቄን ሲያደርግ እንመለከታለን።

እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የገባው ነገር በአገልግለቱ ውጤታማና ትርፋማ ሊሆን የሚችለው በግሉ ከጌታ ጋር ባለው ጤናማና የተስተካከለ ግንኙነት ብቻ እንደ ሆነ ነው። ከዚህም የተነሣ ሕይወቱንና አገልግሎቱን ሳይመዝን ዝም ብሎ የሚሮጥ ሰው ልክ ከነፋስ ጋር እንደመታገል ዐይነት የማይጨበጥና የማይያዝ ከንቱ መሆኑን ይናገራል። ሕይወቱን ሳይመዝን በተገኘው መንገድ ብቻ ዝም ብሎ የሚሮጥ ሰው ግብ የሌለውና መድረሻውን የማያውቅ ሯጭ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ለሌሎች ከሰበኩ በኋላም መጣል እንዳለ ስለገባው ብዙ ለፍቶ በመጨረሻው ሰዓት እንዳይጣልና ከውድድሩ ውጭ ሆኖ እንዳይገኝ ራሱን በመግዛትና የሕይወቱን አቋም በመመዘን እንደሚሮጥ ይመሰክራል። “የሚታገል በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል” እያለ በምሳሌ የሚናገረው አማኝም በነገር ሁሉ ራሱን በመቆጣጠርና ሁልጊዜ ፍቃዱን ለጌታው በማስገዛት መኖር የሚገባው መሆኑን ነው።

ዛሬ እኛ የእምነትን ሩጫ የምንሮጥ ሰዎች የምንሮጠው ምን ያህል ሕይወታችንንና አገልግሎታችንን እየመዘንን ነው? ማሰብ የሚኖርብን ዝም ብለን መሮጣችንን ብቻ ሳይሆን፣ በምን ዐይነት የሕይወት አቋም ላይ ያለን መሆናችንን ነው። አንዳንዶቻችን የምናገለግለው በፊት በነበረን መልካም ስምና ዝና ብቻ ሲሆን፣ እርሱኑ እንደ ነጋሪት እየጎሰምን እንጂ አሁን በተጨባጭ ባለን ትክክለኛ የሕይወት አቋም ላይ ቆምን አይደለም። ሌሎችን አገልግሎና ወደ ትክክለኛው የሕይወት መንገድ መርቶ መጣልም እንዳለ እናስብ። እግዚአብሔር የሚልከን ትላንትና በነበረን ስምና ማንነት ሳይሆን ዛሬ በምንገኝበት የሕይወት አካሄዳችን ጭምር ነው። ዛሬ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ዝም ብለን መሮጣችንን ወይም በተለያዩ ፕሮግራሞች መወጠራችንን ሳይሆን በሩጫችን ላይ ምን እየሠራን ነው የሚለውን ነው። እስቲ ለአፍታ ቆም ብለን እናስብ፤ አሁን እየሮጥን ያለነው በዓላማ ነው? ይህን ወሳኝ ጥያቄ ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል። ይህንን የሕይወት መመሪያ ገንዘባችን አድርገን ብንይዘው በሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በጌታም ፊት በድፍረት ሊያስቆመን የሚችል የሕይወት ንጽሕና ይዘን ለመገኝት እንበቃለን።

Hiruy Admasu

አቶ ኅሩይ አድማሱ፣ የመጀመሪያ ዲግሪውን በሥነ መለኮት ጥናት ከኢቫንጃሊካል ቴዎሎጂካል ኮሌጅ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በኢንተር ካልቸራል ስተዲስ (MPhil) ከኒው ኮቨናንት ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ (NCIU)፣ በተጨማሪም ሁለተኛ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ አግኝቷል። ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በስብከትና በማስተማር እንዲሁም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ሲያገለግል የቆየው አቶ ኅሩይ፣ በተለይ ላለፉት 14 ዓመታት በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች ውስጥ በማስተማር አገልግሎት ላይ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ፣ በሙሉ ወንጌል ሥነ መለኮት ሴሚናሪየም የሪሰርችና ፐብሊኬሽን ፋኩሊቲ ኀላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። የተሰቀለውን ክርስቶስን መስበክ፣ ጊታርና ኪቦርድ መጫወትና መዘመር፣ መጽሐፍ ማንበብ እንዲሁም “ናሽናል ጂኦግራፊ” ማየት የሚደሰትባቸው ተግባራት ናቸው።

Share this article:

የካታኮምብ ዋሻዎች

“የጥንት ሮማዊያን እንደ እነዚህ ያሉ ቦታዎችን የሠሯቸው ሞትን ከመጥላትና ከመፍራት የተነሣ፣ ስለ ሞት ላለማሰብ በሚል ነበር። እነዚህን ስፍራዎች ግን ክርስቲያኖች በአንጻራዊ ነጻነት የማምለኪያ ስፍራ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር።”

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢየሱስ? ወይስ ሞት?

“በኢየሱስ የሆንን እኛ በሕይወት ነን፤ ማንም እርሱን በሕይወትነቱ ቢያውቀው በሕይወት ይኖራል። ሊያውቀው ባይወድድ ግን በሞት ይቀራል፤ መጨረሻውም ለዘላለም ከእግዚአብሔር የመለየት ቅጣት ይሆናል።” ዘሪቱ ከበደ

ተጨማሪ ያንብቡ

ጥልቅ ዐሳቢው ጳጳስ

ስመ ጥር ካደረጉትና ዝናን ካጎናጸፉት መጻሕፍቱ መካከል፣ “ኑዛዜ” የተሰኘውን ጥራዝ ሳይጠቅስ የሚያልፍ ጸሐፊ አለ ለማለት ያስቸግራል፤ “ጌታ ሆይ፤ ለራስህ ስትል ስለ ፈጠርከን ልባችን በአንተ ላይ እስኪያርፍ ድረስ የትም ይባክናል” የተሰኘውና ተደጋግሞ የሚነሣው ኀይለ ቃልም ከዚሁ መጽሐፍ ነው ተመዞ የወጣው።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • Iam so satisfied with your sermon or preach .keep it up
    በጠም ቆንጆ ት/ት ናዉ ጌታ ይበሪክህ.

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.