[the_ad_group id=”107″]

ግብዝነት – በአንድ ቀን ውሎ

“እናንተ ደግሞ … አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፥ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፥ ወዮላችሁ።”

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ

በቀን ሁለቴ፣ ማለትም ጥዋትና ማታ ዜና መከታተልን ማንም አይከለክለኝም፤ ከድሮም እንዲሁ ነበርኩ። ሚስቴ ደግሞ ፊልም ነፍሷ ነው፤ የምግብ ዝግጅት ጣቢያዎችንም ታዘወትራለች (ባሏ በምግብ ቀልድ ስለማያውቅ ምን ታʼርግ?)። ጥዋት ከቤት ከመውጣታችን በፊት ቢቢሲን ከፍቼ ወዲህ ወዲያ ስል ቈየሁና የዜና ዕወጃ ሰዓት ሲቃረብ ጣቢያው የፊልም ሆኖ አገኘሁት። “እንዴ ዜና ደርሷል እኮ! ደሞʼስ እኔ የከፈትኩትን ጣቢያ ለምን ትቀይሪያለሽ?” በማለት ቀኑን በሐሳብ ልዩነት ጀመርኩ።

እስቲ አብረን እንዋል

ወደ ሥራ ለመሄድ ሦስት ታክሲዎችን እይዛለሁ። ቀደም ብዬ ካልወጣሁ ደግሞ ግፊያው አይቻልም። ታክሲ መያዣው ቦታ ደጋግመን በመተያየትና አብረን በመጓዝ ብዛት ሰላም ከምላቸው ሰዎች ዛሬም አንድ ሁለቱ ጥንዶች አሉ። ከአንድ ታክሲ ትንሽ ዐለፍ የሚሉ ተሳፋሪዎች እጅብ ብለዋል። የመጀመሪያውን ታክሲ ሲመጣ እንደ ምንም ሾልኬ ገባሁና የረዳቱ ብብት ሥር፣ የመኪናው ባትሪው ላይ ተቀመጥኩ።

ከእነኛ ጥንዶች መካከል ወንድዬው ቀድሞ ገባና ውጭ ለቀረችው ጓደኛው ቦታ ያዘ። ተከትሎት የገባው ትልቅ ሰውዬ አጠገቡ ሊቀመጥ ሲሞክር፣ ይህኛው “ሁለት ነን” በማለት ላለመጠጋት ሞከረ። ውጭ የነበረችው ጓደኛው ከሰውዬው ኋላ ትጠብቃለች። ድርጊቱን እኔም ስለማዘወትረው አልገረመኝም። ሰውዬው ዘወር ብሎ ልጅቷን አያትና በጸጥታ ወረደ፤ ጨዋ ሰው።

ረዳቱ ከንፈሩ ደርቆ የተሰነጣጠቀ መሬት መስሏል። ጠጕሩን ግራና ቀኝ ተላጭቶት የመኻሉን ብቻ እንደ አጥር አቁሞታል። ሒሳብ ለመሰብሰብ እጁን ብድግ ከማድረጉ ሽታው አፍንጫዬን ወጋኝ፤ ክንፉ ተቈጥቷል (እንዴት በጥዋት እንዲህ ይሸትለታል?)። ወደ ጎን ሸሸሁት። የሚኒባሱ ኋላ ወንበር ላይ የተቀመጠች ደማቅ ወጣት ፊት ለፊት ትታየኛለች። ቀለም በዝቶባታል፤ ዐይኖቿ፣ ከናፍሯ፣ ጉንጯ…፤ ʻየጓደኛዬ የሥዕል ስቱዲዮ ስሄድ ያየኋት ጅምር ሥዕል ነፍስ ዘራች እንዴ?ʼ ስል አሰብኩ። ረዳቱ ገንዘብ ለመቀበል ወደ አንድ ጎን ዘወር ሲል በደንብ አየኋት። አስለቃሽ ይመስል ደረቷን ገልጣ ጥላለች፤ ስለዚህም የጡቶቿ ግማሽ አካል በመስኮት ለገባችው የማለዳ ጀንበርና ለሰው ዐይን ተሰጥቷል። የለበሰችው የአጭር አጭር ቀሚስ ነው።

ሌላ ሰው ገባ፤ ያለው ክፍት ቦታ ኋላ ነው። ከኋለኛው ወንበር ላይ የተቀመጠችዋ ደማቅ ሴት ልትጠጋለት  አልፈቀደችም፤ ብትጠጋ ወንበሩ ከልብሷ ይልቅ የተሻለ ልብስ ይሆናት ነበር። “ጠጋ ትዪልኝ?” በማለት በወፍራም ድምፅ ጠየቃት፡፡ “አይመቸኝም፤ ቅርብ ወራጅ ነኝ” ድምፅዋ እንደ ሰንጢ ቀጭን ነው። “ምናለ ብትጠጊ?” አዲስ ገቢው ሰውዬ እንዳልገባው ሰው ሆነ፤ “አይመቸኝም አልኩህ እኮ፣ አይሰማህም?” ደገመችለት። ደረማምሷት ዐልፎ ተቀመጠ። ሊቀመጥባት ምንም አልቀረው! ሌላ ሰው ከፊት ወረደ፤ ፈጥኜ ቦታ ለወጥኩ።

ትራፊክ ፖሊሶች አዘውትረው የሚቆሙበትን ቦታ ከማለፋችን ረዳቱ ማሳዘል ሲቀረው ሰው በሰው ላይ ማጨቅ ጀመረ። “ወንድሜ ለእኅትህ ትጠጋላት?” ይላል ወንዱን – ድንቄም ትሕትና!። ከውጭ የምትገባውን ደግሞ፣ “ነዪ፤ ወንድምሽ ጋ ቁጭ በይ” ሲል ሰው ያዛምዳል (በዚህ ተግባብተው ለቁም ነገር የበቁ ይኖሩ ይሆን?)። ሾፌሩ ሳይቀር፣ “እኔም ቅርብ ወራጅ ነኝ” በማለት እየቀለደ አንድ ሰው አስገብቷል፡፡ ውጭ ያለውን ሰው ብዛት ስመለከት እንደማይቀርልኝ ገባኝ። ስለዚህ በር ላይ ያለችውን ወፍራም ሴት አጠገቤ እንዳያስቀምጣት ሠግቼ ከፊት ያለችውን ቀጭን ልጅ፣ “ነዪ ወደዚህ” በማለት እየጋበዝኩ መጠጋት ጀመርኩ። ወፍራሟ ገባች፤ የጎኗ ንብርብር ሥጋ ዝግዛግ ሠርቷል (ጭስ ቅርጽ የሚባለው ይህ ይሆን?)፡፡ ወዲያው ዘወር አልኩና፣ “አሁንስ አይበቃም?” አልኩት ረዳቱን። “ሰው አይጠገብም!” ነበር መልሱ። ሣቅን።

ሾፌሩ ይሮጣል፤ አነዳዱ ኮንትሮባንድ ዕቃ እንጂ ሰው የጫነ አያስመስለውም። ብዙም ሳንርቅ በሌላኛው አቅጣጫ የሚመጣ ታክሲ በመብራት ምልክት ሰጠው። ትራፊክ ፖሊስ በቅርብ ርቀት አለ ማለት ነው። ተሳፋሪዎችን ለማውረድ ጥድፊያ ተጀመረ። አሥቂኝ ነበር። ቅድም “እኅቴ፣ ወንድሜ” በማለት ሲወተውታቸውና ሲያግባባቸው እንዳልነበር እያካለበ አወረዳቸው።

ረዳቱ ወዲያውኑ ገንዘብ መሰብሰብ ከመጀመሩ፣ “ጋቢና ሒሳብ” አለ። ዝም። “ኧረ ጋቢና ሒሳብ”። አሁንም ዝም። ረዳቱ የሰውዬውን ትከሻ ነካ አደረገው፤ ፊቱን ሳይመልስ ዐሥር ብር የያዘ እጁን ወደ ኋላ ላከ። “ዝርዝር የለህም?” አለ ረዳቱ (ኧረ ጉድ፤ ዐሥር ብር ዝርዝር እንደ ሆነ ያልሰማ ሰው አለና!)። ድንገት “ወራጅ” አለች አንዲት ቀጭን ድምፅ። በእውነት ግን “ወላጅ” ያለች ነው የምትመስለው። ታክሲው ቆመ፤ አጭር ቀሚሷ ወረደች። ዝንጥ ብሎ የለበሰ ሰው ረጅም ቁመቱን ይዞ ተተካ (ለመቀመጥ ስንቴ እንደሚተጣጠፍ እንጃ!)፤ ሰውዬው እንደ ጉንዳን ከወደ ጭንቅላቱ ይተልቃል። ልጅቱ ወደ ነበረችበት የኋላ ወንበር ሄደ። ቅድም ከልጅቱ ጋር በ“ጠጋ በዪልኝ” ሲጨቃጨቅ የነበረው ሰው አሁን የእርሷን ቦታ ስለ ያዘ ማለፊያ የለም። “ጠጋ በልልኝ ለመግባት አይመችም” አለ ረጅሙ ሰው፤ ጎብጦ ነው የቆመው። “እኔም አይመቸኝማ! ለምን ራስህ አታልፍም?” አለ መላሹ (የቅድሙ ጠያቂ፣ አሁን ተጠያቂ ሆኗል)። “እንዴት አድርጌ ልለፍ፤ እያየኸው!” ያኛው ግን በጭራሽ ሊጠጋለት ፍላጎት አልነበረውም። ቅድም ልጅቱን ካልተጠጋሽልኝ በማለት ራሱ ወጥሮ ይዟት እንደ ነበር ረሳው ማለት ነው?

አጠገቤ ያለው ሰው ስልክ ጮኸ፤ “ደርሻለሁ! ታክሲ ላይ ነኝ” አለ እየተርበተበተ (“ታክሲ ላይ ነኝ? ውስጥ መስለኸኝ!” አልኩ በሆዴ)። እንዲህና እንዲያ እየሆነ ወደሚቀጥለው ፌርማታ ደረስን። ወርደን እኔ ሁለተኛውን ታክሲ ለመጠበቅ ስቆም እኒያ የሰፈሬ ጥንዶች ተሳስመው ተሰነባበቱ። ሁለተኛው ታክሲ መያዣ ተስፋ ያስቈርጣል። ብዙ ጊዜ የሚሳካልኝ በጕልበት ሳይሆን በብልጠት ነው፤ በመሹለክ። ታክሲው ሕዝቡ ያለበት ሊደርስ ጥቂት ሲቀረው እንደሚቆም ገባኝና ነጠል በማለት ሄጄ የጋቢናውን በር ያዝኩ። ተሳካልኝ።

ዘወር ስል ሕዝቡ ይጋፋል። ሰፈርተኛዬ ዘግየት ብሎ ገብቷል። ሾፌሩ ወደ ኋላ ዘወር አለና፣ “ቄሱ እዚያ ታች እየባረከ ነው፤ ትርፍ እንዳትጭን” አለው ረዳቱን፤ ቄሱ ትራፊክ ፖሊስ መሆኑ ነው። ከታክሲ ሾፌርና ከንሥር የማንኛቸው ዐይን በርቀት ምልከታ እንደሚበልጥ ማወቅ ተመኘሁ። ሾፌሩን ተከትዬ ወደ ኋላ ዘወር ስል፣ አንድ ክፍት ቦታ አለ። ያ ከሰፈሬ ጀምሮ የመጣው ወጣት ግማሽ አካሉ ታክሲው ውስጥ ነው። ተወርውሮ ሊቀመጥ ሲል፣ ክፍት ቦታው አጠገብ የተቀመጠው ግዙፍ ሰውዬ፣ “ሁለት ነን” በማለት ማለፍ ከለከለው። ጓደኛዬ ተናዷል፤ “ይህን ሁሉ ግፊያ እያየህ እንዴት ውጭ ላለ ሰው ቦታ ትይዛለህ?” ሲል ተናገረ። “እንዴት አልይዝም? ሚስቴ እኮ ናት!” መለሰ ያኛው። ጣልቃ ገብቼ ልገላግል አማረኝ፤ ግን ማንን ልደግፍ? ለሚስቱ ቦታ የያዘውን ሰውዬ እንዳልናገረው፣ እኔም የማደርገው ነው። ወጣቱን እንዳልናገረው ሰፈርተኛዬ ነው፤ ግን ቅድም እርሱ ራሱ እንደዚህ አድርጎ አልነበረምን?

ጠቡ በቀላሉ አልበረደም፤ ሾፌሩ ደግሞ “ካልተስማማችሁ አልሄድም” ብሎ ሙጭጭ አለ። ተሳፋሪዎቹ ሁሉ ጮኹበትና ሰፈርተኛዬ እንደ ተናደደ ወረደ። ጕዞአችን ያለ ጭቅጭቅ እንዳይሆን ተብሏል መሰል በክፍያ ሰበብ ጠብ ተጀመረ። አፉ የአቦካዶ መጭመቂያ የሚመስለው ረዳት ለማስረዳት ይጥራል። ሴትዮዋ አንድ ብር ከአምሳ መክፈል ፈልጋለች። ረዳቱ፣ “ተመኑ ሦስት ብር ነው” ይላል። መስማማት አልቻሉም፤ ሁሌም ጣልቃ ገብቶ መገላገል እና ማስረዳት ያምረኛል። እንደ ምንም ታገሥኩ። ረዳቱ መከራከር ሰለቸው መሰል፣ “ከፈለግሽ ተሳፋሪ ጠይቂ” ከማለቱ፣ “አሁን ጠሩኝ” አልኩና ተሳፋሪዋን ማስረዳት ጀመርኩ። እግዚአብሔር ይስጣት፣ አላሳፈረችኝም። ከፈለች፤ “ምናለ በእርጋታ ብታስረዳኝ” በማለት ረዳቱ ላይ እያልጎመጎመች።

ታክሲው ቀጥሏል። ተሳፋሪዎች ይገባሉ፤ ይወርዳሉ። የአንዷ ስልክ ጠራ፡- “የሎ” አለች አንሥታ፤ “እየደረስኩ ነው፤ ኮንትራት ታክሲ ይዣለሁ” አለች በዚያው ድምፅ። አላመናትም መሰለኝ፤ “ኮንትራክት ታክሲ ሥር ነኝ አልኩህ እኮ!” አለች በሞልቃቃ ድምፅ (“ታክሲ ሥር” ደግሞ የት ነው? ሰዉ “ውስጥ” የሚለውን ቃል አያውቀውም እንዴ?)። ረዳቱ ባተሌ ነው፤ “ሳይሻገር ወራጅ አለ? ጫፍ ወራጅ አለ?” በማለት እየጠየቀ ሰው ይጭናል። “ትርፍ ጭነሃል” አልኩት ሾፌሩን፤ “የሰው ትርፍ የለውም!” በማለት መለሰልኝ። ከሾፌሩ ፊት ባለው የፀሓይ መከላከያ ላይ “ፍቅር ካለ ታክሲ ባስ ይሆናል” የሚል ጥቅስ ተለጥፏል። በእኔ በኩል ደግሞ፣ “የዓባይ ቃል ስላለብን ጠጋ ጠጋ በሉ” የሚል ነው የሚነበበው። የሥራ መርሓቸው መሆኑ ገባኝ።

ደግሞ ሌላ ጭቅጭቅ ተጀመረ። ቀጭኑ የታክሲ ረዳት ከወፍራም ተሳፋሪ ጋር ይተጋተጋል። አሁንም አንደ ብር ከአምሳ እና ሦስት ብር ነው ንትርኩ። ዞር አልኩና ረዳቱ አላግባብ ገንዘብ ስለ መጠየቁ አስረዳሁ። ረዳቱ አልተቀበለኝም፤ ይባስ ብሎ “ምን አገባህ?” አለኝ። ኀፍረቴን ውጬ ዝም። ግን ግን ቅድም ዳኝነቴን ሲፈልግ አልነበር? ታዲያ አሁን ተሳፋሪ ስለ ደገፍኩ ነው ያቀለለኝ!? እርሱን ብደግፈው እንዲህ ይለኝ ነበር?

ጠቡ አልበረደም። “ደደብ!” አለ ተሳፋሪው፤ ረዳቱም የመልስ ምት ለመስጠት ሴኮንድ አላባከነም፤ “የአንተ ዐይነቱን ድንጋይ ለማጓጓዝ መማር አያስፈልግም!” አለው (እኔ የምለው፤ ʻእንዲህ ስትሰደብ እንዲህ መልስ ስጥʼ የሚል ሥልጠና የሚሰጣቸው አካል አለ እንዴ? ታዲያ በዚህ ፍጥነት እንዴት ነው መልስ የሚመጣላቸው?)።

ታክሲያችን ወደ ቦሌ እያቀና ነው። ቦሌ በቀለበት መንገዱ ድልድይ በኩል ነው የሚያልፈው። ቅድም የገቡት ሴትዮ ይቁነጠነጣሉ፤ ሳይናደዱ አልቀሩም። “ልጄ፤ የገርጂ ታክሲ የት ነው የማገኘው?” ጥያቄአቸው ለረዳቱ ነው። “እዚያ ድልድይ ይግቡ” መለሰ ወያላው የፊት ለፊቱን የቦሌ ድልድይ እያመለከተ። ድንገት ሴትየዋ ግንፍል አሉ፤ “አንተው ራስህ ድልድይ ግባ! የአባቴ አምላክ ድልድይ ያግባህ!” ደንግጠናል። “ተከትለኸኝ መጣህ? ማን እንደ ላከህ ዐውቃለሁ”፤ ሴትዮዋ ርግማናቸውን ቀጥለዋል። ረዳቱ ቦሌ ድልድይ ሥር ታክሲ እንደሚያገኙ መናገሩን እንደ ስድብ እንደቈጠሩበት ሰዉ ገብቶታል፤ እንባቸው እስኪወርድ የሚሥቁም አሉ። ሴትዮዋ ወደ እኛ ዞሩ፤ “ጥርሳችሁ ይርገፍ! ደሞ ትሥቃላችሁ? ወይ ዘመን! ‘ድልድይ ግቢ’ ይበለኝ? አሮጊት የማይከበርበት አገር! ቱ፣ ቱ! …”፡፡ ታክሲዋ በሣቅ የምትርገፈገፍ መሰለች። ከእሳቸው በቀር ተሳፋሪዎቹ ሁሉም ነው የሚንፈቀፈቀው፤ ረዳቱ እንኳ አረንጓዴ ሣቅ ይሥቃል!

“ያዝላቸው” አለ ረዳቱ፤ ሌላ አሮጊት ውጭ ቆመዋል። ቶሎ መግባት ግን ቸገራቸው። ከፊት የተቀመጠች ወጣት እጇን ሰድዳ ያዘቻቸውና ቀስ ብለው ገቡ። የሚያምሩ ደርባባ ሴትዮ ናቸው፤ ነጩን ጠጕራቸውን በአጭሩ ተቈርጠውታል። “እግዚአብሔር ይደግፍሽ!” አሉ እየተቀመጡ። ወዲያውኑ ለመክፈል ቦርሳቸውን መበርበር ያዙና፣ “ልጄ፣ ዝርዝር ያለኝ አይመስለኝም” አሉት ረዳቱን። “ችግር የለውም እማዬ” አለ ረዳቱ። “ችግር አይንካህ!” አሉት እሳቸውም መልሰው፤ የተባረኩ አሮጊት!

ቀኑ ብዙም የተለየ አልነበረም። ወደማስተምርበት ትምህርት ቤት ደርሼ ቢሮ ስገባ፣ የሥራ ባልደረቦቼ አንዳንዶቹ Facebook ላይ አፍጥጠዋል፤ ሌሎቹ ካርታ ይቀጣቀጣሉ። ገና ከመግባቴ፣ “ኧረ ብርድ፤ እባክህ ዝጋው!” አለኝ አንዱ ጀርባውን በእጁ እየደገፈ፤ ሰንጢ የተሰካበት ነው የሚመስለው። የእርሱ የብርድ ፍርሃትማ አይነሣ! የመስኮት መጋረጃ እንኳ ሲከፈት ይጮኻል፤ ብርሃንም ይበርደዋል እንዴ? እያልኩ አስባለሁ አንዳንዴ።

ሌላኛዋ ባልደረባዬ ማታ ማታ አብራኝ ትማራለች። እግሮቿ ረጃጅም ከመሆናቸው የተነሣ ደረቷ ላይ የተሰኩ ይመስላሉ። ረጅም ቀሚስ አያጣትም፤ ቀለሙ ደግሞ ሁሌም ጥቊር ወይም ቡኒ ነው። ጠጕሯ ረጅምና የሚያምር ቢሆንም በወጉ አትይዘውም፤ “ያለ ቦታው በቅሎ!” ትላታለች የቢሮአችን። ሁሌም ጥዋት ጥዋት ፊቷ እንደ ተቋጠረ ነው። የተቈጣ ወንድ ትመስላለች፤ (በቤተ ሰብ ግፊት ሴትነትን መለማመድ የጀመረ ወንድ ትሆን?) ትምህርት ቤት ጎን ለጎን ነው የምንቀመጠው። አስተማሪዎቻችን ሲገቡ ሳይዘጋጁ መግባታቸውን ቀድማ የምታውቀው እርሷ ናት፤ በዚህም ሁሌ ታማርራለች። እኔ ስገባ ወረቀት ፍለጋ ቢሮአችንን ስታተራምስ ነበር፤ ማስተማሪያ ወረቀቷ እንደ ጠፋት ገባኝ። “ወይ ታሪክ! እርሷ እዚህ ሳትዘጋጅ እየገባች፣ ሰውን ግን ትኰንናለች!” አልኩኝ በሆዴ። የመናገር ድፍረት ግን ከየት ይምጣ? ከዚያ ሰዓቴን መልከት አደረግሁና፣ “ዛሬ ʻክላስʼ የለም እንዴ?” አልኳት፤ “አሁን ገብቼ ነጠላ ዜማ እለቅቃለሁ እባክህ” አለችኝ ለአፍታ ቀና ብላ። ባለ አንድ ʻክሬዲት አወር ክላስ ʼ ሲኖረን እንዲህ ነው የምንባባለው። “ታዲያ ሰዓት አላለፈም?” ከማለቴ፣ “ዐሥር ደቂቃማ የኮ’ቴ ነው” ብላኝ ወጣች። (“የኮ’ቴ”? አውሮፕላን ማረፊያ መሰላት እንዴ?”)። ዝም እንዳልኩ ለማስተማር ገባሁ።

አስተምሬ ስወጣ ምሳ ሰዓት ደርሷል። ሁላችንም 6፡00 ሰዓት ከሞላ አንዲት ደቂቃ እንድታልፍ አንፈቅድም፤በተለይ አስተምረን ስንወጣ። ተማሪዎቹ ሆዳችን ገብተው የሚቦጠቡጡን ይመስል በራብ አረፋ እየደፈቅን ነው የምንወጣው። ምሳ በቡድን መብላት ለምደናል።

የምሳው ማኅበር ዋነኛው አባል በቡድን መብላት የሚመርጠው የሰው ድርሻ ለመብላት ይመስለኛል። በየመኻሉ ውሃ እየጠጣ ከበላማ አንችለውም። አንድ ማታ ቤቱ ሦስት እንጀራ በልቶ እንጀራ በማለቁ መብላት እንዳቆመ አጫውቶናል። መቼም እግዚአብሔር ለኀጢአታችን ቅጣት ነው እርሱን የሰጠን። “በዚህ ሆዱ ሚስት እንዴት ነው የሚያገኘው?” የሚለው ጥያቄ እንዳሳሰበን ይኖራል። ከሰሞኑ ግን ድንገት መጥፋት፣ ስልክ ላይ ከእኛ ነጠል ማለትና ረጅም ሰዓት ማውራት ሲጀምር አይተናል። የሁላችንም ጥያቄ፣ “ሆቴል ይኖራት ይሆን?” የሚል ብቻ ነበር። ቢሮ ሲገባ ቦርጩ ቀድሞት ስለሚገባ አንድ ጊዜ እንደ ምንም ሰብከን ጂም አስገባነው።እግዚኦ! “እንኳን እናቴ ሞታ እንዲሁም አልቅሽ አልቅሽ ይለኛል” ያለችው ሴትዮ ታሪክ ተደገመ። እንኳን ስፖርት ጀምሮ እንዲሁም “ብላ! ብላ!” ነበር የሚለው። አ…ል…ቻ…ል…ነ…ው…ም። ከታናሽ ወንድሜ በኋላ ምግብ በpassion የሚመገብ ሰው ከእርሱ በቀር ገጥሞኝ አያውቅም። እናም ክብደት እንዲቀንስ የጀመረው “ጂም” ለክብደት መጨመር ሰበብ ሆነው (“ቢያጠምቋት ባሰባት” አለ የአገሬ ሰው!)። ስለዚህ “ጂም” እንዲያቆም ለጊዮርጊስ ስለት ለማስገባት ምክክር ሁሉ ተጀምሮ ነበር። ሳምንት ሳይሞላው አቆመልን። እፎይ!

ምሳ ልንበላ የገባንበት ቤት ኢቲቪ ተከፍቷል። የዜናን ትክክለኛ ትርጕም የማያውቅ ጣቢያ የዜና መርሓ ግብር ሲኖረው አሳዛኝ ነው። “ዜናው”፣ መዝናኛው፣ ስፖርቱ፣ … ሁሉም ዝግጅት ፕሮፓጋንዳና ቀሽም ስብከት ነው። ቴሌቭዥኑ Amnesty International እና Human Rights Watch ስለ ኤርትራ ያቀረቡትን ሪፖርት እያራገበ ነው። አቅራቢው በደስታ ነው የሚያወራው (ለዚህ “ግኝቱ” ደሞዝ ይጨመርለት ይሆን?)። ኢቲቪ እነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ ሲያወሩ ያወግዛቸዋል። ስለ ኤርትራ ሲናገሩ ግን እጅ እጅ እስኪል ሲደጋግመው ይኖራል። ወይ ምጭውት!

ቀኑ ከወትሮው የተለየ የነበረው ሰዉ ሁሉ ፊት ላይ ኀዘን በመነበቡ ብቻ ይመስላል፤ ትናንትና ማታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ተሸንፎ ወጥቷልና። ብቻ ይህንና ያንን ስል ዋልኩና ሲመሽ ከሥራ ባልደረባዬ ጋር ወደ ቤት መንገድ ጀመርን። ማታ ትምህርት ቤት ከሌለኝ ብዙ ጊዜ እርሱ ጋር ነው የምሄደው፤ ያኔ በሎንቺን ከመታጨቅ እድናለሁ። ጓደኛዬ በአጠገቡ የሚያልፉትን አዳዲስ መኪናዎች ሁሉ ቢመኝም፣ የያዛት መኪና አዲስ ናት። በዚህ ላይ ብልጣ ብልጥና ደፋር ስለሆነ መንገድ ሲዘጋጋ ከእርሱ ጋር መሄድ መታደል ነው። እንደ ምንም ተሽሎክሎኮ ያሰበበት ይደርሳል (ዘመኑስ የደፋርና የሾላካ አይደል!)።

ሥራ መውጫ ስለሆነ መንገዱ እንደ መዘጋጋት ብሏል። ጓደኛዬ መሥመር ጠብቆ መሄድ አይሆንለትም፤ እየሾለከ ሰው ፊት ይጋረጣል። አሁንም እንደ ልማዱ አደረገ። የተቀደመው አሽከርካሪ ጡሩንባውን አጮኸበት፤ ጓደኛዬ መናደዱን ያወቅሁት “በረሮ” ብሎ ሲሳደብ ነው (ከሞባይል ስልክ ጋር ውሸት፣ ከመኪና ጋር ስድብ የሚያድላቸው ማነው?)። ሐሳቤን ሳልጨርስ እግረኛ ድንገት ገባበት፤ ጓደኛዬ፣ “ገመድ አይሻልህም?” በማለት በመስኮት ተናገረና በመሪው ብርታት አደጋ ሳያደርስ ዐለፈ። አንዲት የተቆነነች ወጣት ስልኳን ጆሮዋ ላይ ለጥፋ በመዝናናት በዜብራ ላይ ስትሻገር ደረሰባት። “ሟች!” በስድብ ጠራት ጓደኛዬ፤ ቅድም ታክሲ ውስጥ የተለጠፈው፣ “ሟች ከመሞቱ በፊት ዜብራ ላይ እየተሳሳመ ነበር” የሚለው ጽሑፍ ትዝ አለኝ።

ጓደኛዬ ስለ ሚስቱ ስሞታ እያወራልኝ ነው። ከተጋቡ ገና አንድ ዓመታቸው ማለፉ ነው። የእርሷ ዘመዶችና ጓደኞች ቤታቸው እየመጡ ያድራሉ፤ እርሷም ጓደኞቿ መጥተው እንዲያድሩ ስትጋብዝ ብዙ ጊዜ ሰምቷታል።ሊጠይቁት ፈልገው ማደር የሚፈልጉ ጓደኞቹም ሆኑ ዘመዶቹ እንዲመጡ ግን አትፈቅድም፤ ሰበብ ትደረድራለች። ይህን ሲያወራልኝ የሚያውቀውን ሰው ፍለጋ ዐንገቱን በመስኮት አሰግጎ ነው፤ ዐይኖቹ ይቃብዛሉ። ድንገት በጫወታ መኻል፣ “እገሌ ያውና!”፣ “የእገሊት መኪና!” ይላል፤ ተንጠራርቶና ተጣርቶ ሰዎችን ሰላም ይላል። ይሄኔ ከኋላው የመጣ ተሽከርካሪ ዐለፈውና ከፊቱ መጓዝ ጀመረ። ጓደኛዬ ተናደደ፤ ወሬው ተቀየረ። “በሰው መሥመር ዘው ይላል እንዴ? ዝተት!” እኔም ተደርቤ እንድናገር እየጠበቀ ነው። እንዴ … እርሱ ራሱ ሁሌ እንዲህ አይደል የሚያደርገው? ቅድምስ ይህንኑ አድርጎ የለምን? ዝም እንዳልል ደግሞ በተመቸው ጊዜ ሁሉ የሚሸኘኝ ወዳጄ ነው? ምን ይሻላል?

ሚስቴ ትዝ አለችኝ። ማታ ማታ ታጥቤ ወይም ቤት ውስጥ ያለ ካልሲ ቈይቼ እግሬ ከቀዘቀዘ ስንተኛ ትሸሸኛለች፤ በጭራሽ እግሬ እንዲነካት አትፈቅድም። እጄም ከቀዘቀዘ መተቃቀፍ የለም (“በብርድም ሆነ በሙቀት ጊዜ” የሚል ሐረግ በጋብቻ ቃል ኪዳናችን ውስጥ አልነበረም እንዴ?)። የእርሷ እግር ሲቀዘቅዝ ግን እግሮቼ መኻል ከትቼ ማሞቅ የባልነት ግዴታዬ ነው። ከበረዳትም ዕንቅልፍ እስኪወስዳት አቅፌ ማሞቅ አይቀርልኝም። እንዲደረግልን የምንወደውን ነገር ለሰው የማናደርገው ለምን ይሆን?

ይህን ሳወጣ ሳወርድ ቤት ደረስኩ። ሚስቴ ቀድማኛለች፤ የገበታ ጠረጴዛው በምግብ ተሞልቷል። የምወደው ሰላጣም አለ (አቤት ሚስቴ ሰላጣ ስትሠራ!)። እኔ ደግሞ ጥሎብኝ የቀረበውን ምግብ ሁሉ ካልጨረስኩ አልነሣም፤ ሰሓኑ ባዶ ሲሆን፣ “አጸዳሁልሽ!” እላለሁ በኵራት፤ ትልቅ ጀብዱ እንደ ፈጸመ ሰው። “አንደኛውኑ እግርህን ታጥበህ መሶቡ ላይ ለምን አትቀመጥም?” ይለኛል ታናሽ ወንድሜ። ሚስቴ የቤት ልብሷን ለብሳ ፊልም እየተመለከተች ነው። ሰዓቱ የቢቢሲ ነው፤ የርቀት መቈጣጠሪያውን በማንሣት ጣቢያውን ቀየርኩና ዜናዬ ላይ ተተከልኩ። “Give the man his remote” አለች እየሣቀች። “ጥዋት ‘ጣቢያውን ቀየርሽብኝ’ እያልክ ስትዘፍን ነበር። አሁን ግን …” አለችኝ ቀና ብላ። ዜናውን እየተመለከትን ራታችንን በላን፤ ከዚያም ወደ መኝታ አቀናን።

ደኅና እደሩ!

Share this article:

ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ፦ ዐጭር ታሪካዊ ቅኝት

ገናዬ እሸቱ “የተላኩ” በተሰኘው ዐምድ፣ ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ተብሎ የሚታመንባቸውን የተለያዩ ዘመናትና የወንጌል እንቅስቃስውን ሂደት በወፍ በረር ታስቃኘናለች። ይህ ጽሑፏ በተከታታይ ከምታስነብባቸው የወንጌል ተልእኮ ተኮር ከሆኑ ሥራዎቿ የመጀመሪያው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.