[the_ad_group id=”107″]

የማንነት ስምምነት ካልቀደመ እየሠሩ ማፍረስ ይቀጥላል

በአጭሩ ግጭት ማለት “ቡድኖች የግብ ልዩነት ሲኖራቸው” ማለት ነው። ከዚህ አንጻር ከጥቂት ወራት በፊት የኢህአዴግ “ውስጥ ወለድ” ለውጥ፣ “ከውስጥ ወለድ ግጭት” በቀር በሁሉም ዘንድ ተቀባይ በማግኘቱ፣ ጎልቶ የወጣ የግብ ልዩነት ስላልነበረ የ“መደመር” ሂደቱን በአንጻራዊ ቀላል አድርጎት ነበር። ስለዚህ ኢህአዴግ ሲለወጥ (ቢያንስ ዋና ዋና ለውጦች አድርጓልና) ለውጡን የሚፈልጉ ሁሉ ‘ዐላማችን ግቡን መትቷል’ ማለት መቻል ይኖርባቸዋል።

አሁን የማንነት ጥያቄ የሚመለስበት፣ ተከድነው ይበስሉ የነበሩ ድስቶች እፊያቸው የሚነሣበት ወቅት በመሆኑ፣ ሁሉም የወጠወጠውን ገርበብ አርጎ ሲከፍት ጠረኑ እያወደ ነው። ማላከኮችና ማሳበቦች የሚነጻጸሩት “የማምለጫውን ፍየል” (scapegoating) በመፈለግ ሳይሆን፣ አሁን የታዩና እየታዩ ያሉ ክስተቶችን እንዲሁም ክስተቶቹን የወለዷቸውን ቀዳሚ ትርክቶች ተመሳሳይነት ከቡድኖች የቀድሞ ባሕርያት ጋር በማነጻጸር እና በማገናዘብ ነው። አንዳንዶች ያው ናቸው፤ ለአዲስ ተግባር የሚያስፈልግ አዲስ ባሕርይ እያሳዩ አይደለም። የባሕርይ ለውጦች በሌሉባቸው፣ የተግባር ለውጦች አይኖሩም! ባሕርያቸው ያልተለወጠ ቡድኖች፣ በሰላም የሚጎለብተውን አዲሱን ለውጥ “ያገሙታል”።

እንግዲህ አሁን የምናያቸው “ግጭቶች” መሠረታዊ የሆኑና በግልጽ ቋንቋ ወደ አደባባይ መምጣት ያለባቸው “የማንነት ትርጓሜ” ላይ ያሉ ልዩነቶች ናቸው። አልቸኮልኩም፤ አልፈረድኩም፤ ያስተዋልኩትን ነው የምናገረው።

ከኢትዮጵያዊ ማንነት አንጻር ቢያንስ ሦስት ቡድኖች አለ፦

  1. ኢትዮጵያዊነትን እንደ ማንነት ርእዮተ ዓለምም ሆነ፣ እንደ መፈክርም የሚቀበል። ይህ ቡድን ኢትዮጵያዊነትን በዐደራ እንደተቀበለው፣ መጠበቅ እንዳለበትና ለመጪውም ትውልድ ይህንኑ ማስተላለፍ እንዳለበት አምኖ ለዚህ ማንነት ይኖራል፤ ይሞታል።
  2. ኢትዮጵያዊነትን እንደ መፈክር የሚቀበል፣ እንደ ማንነት የሚያንገራግር፣ ግዴለሽ፣ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” ባይ አለ።
  3. ኢትዮጵያዊነትን እንደ ማንነት ርእዮተ ዓለምም ሆነ፣ እንደ መፈክር የማይቀበል ቡድን ደግሞ አለ። ይህ ቡድን ኢትዮጵያዊነትን የተጫነበት እንደ ሆነ የሚያስብ፣ እንደ ታሪካዊ ጠላት የሚያየው ስም፣ ከዚህ ጋር ንክኪ ያለውን ነገር ሁሉ ለማጥፋት የሚኖርና የሚሞት ነው። ለምን ኖረ አልልም፤ የታሪክ ሒደት ፈጥሮታልና። ይሁን እንጂ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረት ይሁን አይሁን፣ በሚገባ መጣራት እንዲሁም ሰይፍ የሌለበት መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል።

እንደ አገር ግን እነዚህ ልዩነቶች ካልታረቁ መቀራቅሩ መልኩን ይቀይራል እንጂ የግጭቱ ዑደት ይቀጥላል (ይህ አይቀሬና አሳዛኝ እውነት ነው)። በማንነታችን ላይ እስካልተስማማን ድረስ እንደ ጅል እየሠራን ማፍረስ እና እየሞትን መኖር ይቀጥላል። እኛ ማነን? በዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ፣ በአንድ ባንዲራ እየታወቅን በምድራችን በባንዲራ ብዛት ከተላለቅን የማንነት ቀውስ ይሏችኋል ይህ ነው። እኛ ማን ነን?

Solomon Tilahun

እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በምናስብበት በዚህ ሰሞን፣ “እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ” ሊኖረን ስለሚችልና ስለሚገባ ምላሽ የሚከተለውን ጽሑፍ ሰሎሞን ጥላሁን ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሕዝብ ከሥልጣን ይውረድ!

ታክሲ ውስጥ ነን። እኔ፣ ምናሴና የምናሴ ባለቤት፣ ዶይ። ታክሲዋ ተጠቅጥቃና ተነቅንቃ ከመሙላቷ የተነሣ፣ እንደ ሰው አፍኗት ብታስነጥስ እንደ እኔ ቀለል ያልን ሰዎች በአፍንጫ እንደሚወጣ የእንጥሻ ፍንጣሪ፣ በር ሳይከፈት እንወጣ ነበር። ወደ መዳረሻችን፣ ̋ተሻግሮ ወራጅ አለ” አንዱ ከኋላ። በረዶና ነጎድጓድ አዘል የስድብ መዓት ስታዘንብ የመጣችው ሴት ደግሞ፣ ̋ሳይሻገር ወራጅ አለ ̋ አለችና ደጋግማ ጮሄች። ሾፌሩ በኀይል መናግሯ ̋ደብሮት ̋ ነው መሰለኝ፣

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.