[the_ad_group id=”107″]

ማንነት እና ስንክሳሩ

በሰሎሞን ጥላሁን ቨርጂኒያ፣ ዩ.ኤስ.ኤ

ከልጅነት እስከ እውቀት ያለው ማንነታችን ፣ በንኡስ ማንነቶች ተደራርቦ የሚዳብርና በአብዛኛው በማሕበራዊ ስምምነቶች ላይ ተመስርቶ የተገነባ (Socially Constructed) ውስብስብ የእኛነታችን መገለጫ ነው። በመሆኑም ለተለያዩ ተራዛሚና አልላቀቅ ብለው ለሚጣቡ ማሕበራዊ ግጭቶች (Intractable Conflict) ያጋልጠናል። በአገር ዜግነት ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰብነት በዐመታት ውስጥ የመለዋወጥ ጠባይ ያላቸው ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ማንነቶች እንደ ጾታና የቆዳ ቀለም ቋሚና የማይለወጡ አይደሉም፣ ስለዚህ በሚበልጠው የዜግነት ጥላ ላይ የሕልውና አደጋ የሚያስከትሉ ግጭቶች ሲፈጥሩ፣ በድርድር የሚገኝ ማንነትን ማዳበር፣ ለአገር ሰላም ግንባታ የተሻለና ቋሚ አስተዋጽኦ ይሰጣል፣ በውጤቱም ብሔር ብሔረሰቦችን የበለጠ ያዳብራል።

ማንነት ምንድን ነው?

ማንነት “ራስ ጠቀስ ነው” (Reflexive self) ፣ ይህም ማለት የራሳችንን የማንነት ገጽታ ግንዛቤን ከቤተሰብ፣ ከጾታ፣ ከባሕል፣ ጋር በግላችን በምናደርገው ሒደት አዛምደን የምንረዳው እኛነታችን ነው። ማንነት ሲጀምር ግለ ግንዛቤ ነው፣ ስለዚህ ከስብስብ ማንነት በፊት ግላዊ ማንነት ለብቻው ይቆማል። “እኛ ነን” ከማለታችን በፊት “እኔ ነኝ” ይቀድማል። ይህ ግላዊ ማንነት፤ እኛ በግል ከሌሎች ጋር በራሳችን አንጽረንና አገናኝተን ያለን ማንነታችን ነው። እንግዲህ ከዚህ ሌላ ማሕበራዊ፣ ጾታዊ፣ መደባዊ፣ እድሜአዊ፣ እምነታዊ፣ ሙያዊ… ማንነቶች አሉን፣ በሁለት ብንከፍላቸው ተፈጥሯዊ የሆኑና የማሕበራዊ ግንባታ ውጤቶች የሆኑ ናቸው፣ (Natural and Socially Constructed) ወይም የሚለዋወጡና የማይለዋወጡ ናቸው። ግለ ማንነትን ሁለት አድርገን ብናስበው፣ “እኔ” እና “ራሴ” (the “I” and the “Me”), “ራሴ” የተፈጠረው ማንነቴ የማይለወጠው ማንነቴ ሲሆን “እኔ” የተገነባው ማንነቴ በብዙ ሊለወጥ የሚችለው ማንነቴ ነው፤ ስለዚህ አንድ ሰው በእድሜው ውስጥ እጅግ ብዙ የሚለዋወጡ ማንነቶች አሉት።

ማንነትም ሆነ የማንነት ግለ ግንዛቤ በጊዜ ሒደት ውስጥ የሚዳብር ነው

ሰው በሕጻንነቱ የዓለሙ ሁሉ ትኩረት እርሱ እንደሆነ ያስባል፤ ይሁን እንጂ በጉልምስናው ወቅት ግን ዓለም ሌላ አመለካከትም ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት የጋራ እንደሆነች በመገንዘብ፣ እንደ ልጅነቱ በየምክንያቱ ለትኩረት የማያላዝንና ለሌሎችም የተከፈተ ይሆናል። አንዳንዶች እዚያው ጋ ሲቀሩ አስቸጋሪ ይሆናሉ፣ የማንነት ግለ ግንዛቤአቸው ሳይዳብር ሲቀር፣ ትልቁ ትንሽ ይሆናል ማለት ነው፣ እንዲህ ዓይነት ሰብእናም ለግጭት ተጋላጭ (Conflict Prone) ይሆናል።

የማኅበረሰባዊነት ግንዛቤን ማዳበር ከግለሰባዊ ማንነት ጋር የተገናኘ ነው፣ የግለሰብነት ማንነት በማህበረሰብ ማንነት ላይ ተጽእኖ አለው።

በተረጋጋ የማኅበረሰብ ኑሮ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ማንነታቸውን የሚያዳብሩባቸው ሁኔታዎችና በግጭት በተለይም በተራዘሙና ለኅልውና ሥጋት ባለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የሚዳብሩ ማንነቶች የሒደት ልዩነት ስላላቸው የውጤትም ልዩነት አላቸው። በግለሰቦች ውስጥ የሚታዩት ማሕበራዊ ስምምነቶችም ሆነ ትብብሮች ወይም በተቃራኒው ማሕበራዊ አለመተማመኞች ሆነ አለመተባበሮች፣ ግለሰቦች ማንነታቸውን ሲያዳብሩ ያገኙአቸው የሰብእና ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ ሰላማዊ የሕዝቦች ግንኙነት አለመኖሩ ውጤቱ ያልተረጋጋ ማንነት ያለውን ሕዝብ ማስገኘት ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ የሰላማዊ ግንኙነት መኖር፣ ውጤቱ የተረጋጋ ማንነት ያለው ግለሰብ ማስገኘቱ ነው።

ግለ ግንዛቤ እንዴት ይዳብራል

የግለሰባዊነትና የአብሮነት ኃይል

ግለሰባዊነትና አብሮነት (Individuality and togetherness) የሚባሉት “ተቃራኒ” የሚመስሉ ማንነቶች የየራሳቸው ሳቢና ገፍታሪ ኃይል አላቸው። የግለሰባዊነት ኃይል አንድን ግለሰብ ከሌሎች የተለየ እንዲሆን ወደ ራሱ/ሷ የሚስብ ኃይል ነው። በዚህ ውስጥ ልዩ ልዩ ምንጮችን በመጠቀም የራስ ማንነት ግንባታ ይካሔዳል። የአብሮነት ኃይል ደግሞ ወደ ሌላ ለትብብር፣ ለተዛምዶ፣ ለእውቅና የሚስበን ኃይል ነው። ለግለሰቡ ግን በሁለቱ ኃይላት እንቅስቃሴ ወቅት እኩል የምቾት ቀጠና የለውም፣ ግለሰቡ ወደ ሌሎች ለአብሮነት ሲቀላቀል ያለው የስሜት መጨናነቅ ከራሱ ጋር ከሚሆነው ይልቅ ይበልጣል። ስለዚህ ግንኙነቶች ሁሉ ስሜታዊ ናቸው።

የሰብአውያንን የእርስ በርስ ግንኙነት አስመልክቶ ትልቁ የሚዛን ጥበቃ ውጥረት የሚገኘው ወደ ራስ በሚስበው የግለሰባዊነት ኃይልና ወደ ሌሎች የሚጎትተው የአብሮነት ኃይል መካከል ሚዛን መጠበቁ ላይ ነው። – ሉአላዊ ወይም ራስ ገዝ ማንነትን የሚፈልገው እኛነታችንና ከሌሎች ጋር አብሮነትን የሚፈልገው ማንነታችን – እኛ ራሳችን ውስጥ ሳንሰምጥና በሌሎችም ሳንሟሟ ምጥን ማንነት የሚሰጠን ምን አማዛኝ (equilibrant) እናገኛለን? ከሌሎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ለድርድር የማይቀርበው በራስ ገዝ የግለሰባዊነት ግንዛቤአችን ውስጥ ተገንብቶ የኖረው፣ እምነት፣ ግብ፣ ገደብ፣ እሴት.. የትኛው ነው? – ለእኛ የሚመቸንን ቀጠናችንን ባሰፋን መጠን ግጭት የምንፈጥር፣ ወይም የተፈጠረውን ቅጭት የምናሻቃብና ለድርድርም የምናስቸግር እንሆናለን። (የምቾት ቀጠና ቻርት)

የምቾት ቀጠናችን ሲጠብ ግጭቶቻችን ያሽቆለቁላሉ፤ የምቾት ቀጠናችን ሲሰፋ ግጭቶቻችን ያሻቅባሉ ..

አብሮነት ራሱን የቻለ ድብለቃ (ፊውዥን) ነው፤ ራስ በራስ ሳይሆን እርስ በርስ፣ ነው፣ ስለዚህ የስሜት ብስለት ይጠይቃል፣ ግለሰቦች በስሜት በሳል ሲሆኑ የራስም ሆነ ከሌላው ጋር የሚኖራቸው ትምምን ከፍ ይላል፣ ግለ ማንነታቸው ምሉእ የሆነ ሰዎች ያልተጨናነቁ (Non-anxious) በመሆናቸው ለአብሮነትም ያላቸው ዝግጁነትም ይጨምራል። ከእነርሱ ውጪ በሌሎች ዘንድ ያሉት ሁኔታዎች ስሜትን የሚፈትኑ ሆነው ሲገኙም የተረጋጉ በመሆናቸው ራሳቸውን በሚገባ መግለጥ ይችላሉ፣ የስሜት ክልላቸውና የአስተውሎት ክልላቸው አይደባለቅባቸውም። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ታላላቅ መሪዎች ሲሆኑ ስኬታማ ይሆናሉ። ከአገር መሪዎች የፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ፣ የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማና፣ የኢትዮጵያዊውን ክቡር ዶክተር ለማ መገርሳን ማንነት ባልተጨናነቀ የስሜት ምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ ስንኖር በማሕበራዊ ግንባታ ያገኘናቸው ማንነቶች

መለወጣቸው ግድ ነው!

የዐለምና የአህጉራችን ሕዝቦች፣ በግድና በውድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱበት ዘመን ቢኖር፣ ይህ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ነው። እንኳን ከስፍራ ስፍራ ተንቀሳቅሰው ሰዎች ባሉበት ቦታ እንኳ ሆነው ሉል አቀፋዊው ግንዛቤ፣ በእጆቻቸው መዳፍ ባሉ ስልኮች ከተፍ እያለ ነው፤ (በ2020 ዓ.ም 4.68 ቢሊዮን ሕዝብ የሽቦ አልባ ስልክ ተጠቃሚ ይሆናል) በውጤቱም ሌላ ዓለም፣ ሌላ ሕዝብ፣ ሌላ ባሕል፣ ሌላ… እንዳለ እያስገነዘቧቸውና ከጠባቡ መንደሮቻቸው ወጣ ብለው እንዲያስቡ እያስገደዷቸው ነው። ከተሞች እየተስፋፉ፣ ዓይነተ ብዙ ሕዝቦችን አባላት እያደረጉ፣ ገጠሮች በከፊል እየከተሙና እየዘመኑ፣ ሩቁ ቅርብ እየሆነ፣ “እነርሱ” በብዙ “እኛን” እየመሰሉ፣ “እኛም” “እነርሱን” በብዙ እየመሰልን ነው። በ 2050 ዓ.ም. 1.49 ቢሊዮን አፍሪካውያን የከተማ ነዋሪዎች ይሆናሉ! …. ለእነዚህ ለውጦች አሻፈረኝ ባይነት፣ በለውጡ ለሚገኙ እድገቶችም አሻፈረኝ ባይነት ነው።

አቀፋው ጠባብ የሆነ ማሕበረሰብ ይቀⶽጫል፣ በተቃራኒው ደግሞ ከልክ ያለፈ አቃፊ ማሕበረሰብም ራሱን ያጠፋል፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ለውጦችን በማገናዘብ እየቀደመ የሚሔድ ማሕበረሰብ ግን ከለውጦች አትርፎ ራሱን ያተርፋል። ሌላው ቀርቶ የስነ መሬት ዜናዎች እንኳን እንደሚጠቁሙት፤ የአፍሪካ ግኡዙ መልክአ ምድር ምስራቃዊው ክፍል በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ትክክል ቁልቁል እየተገመሰ ነው፤ ስለዚህ ሰብአውያን ብቻ ሳይሆኑ መሬት ራሷ እየተንቀሳቀሰች ነው ማለት ነው፤ ከአንድ ሰው እድሜ በኋላም አንድ ሕዝብ ተገምሶ በውቂያኖስ ማዶና ማዶ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ባጭሩ ያው አይደለንም፤ እየተለወጥን ነው!! ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፤ “ተለዋዋጩ ማንነታችንና የማንነት ግንዛቤአችን የታረቁ ናቸው ወይ?” የሚለውን ነው። ማታ ወደ መኝታችን እየሔደ ያለው ማንነት፣ ጠዋት ከመኝታው ተነስቶ ከቤቱ የወጣው ማንነት ነው ወይ? – ማንነት እንኳን በዘመን ሒደት በአንድ ቀን እንኳ ይለወጣል። በማሕበራዊ ኑሯችን ውስጥ ችግሩ የማንነታችን መለወጥ ሳይሆን የምናስበው እንዳልተለወጥን መሆኑ ነው፣ እንዲህ ዐይነቱ “የአይለወጤነት” አስተሳሰብ “የተቸካይነት ተፋልሶ” (Fixed Identity Fallacy) ይባላል።

በማንነት ነቆራ፣ የተቸካይነት አዙሪት ትውልዳዊ ጥፋት አለው

ቡድኖች ካለፈው ትውልድ ታሪክ አንዱን የስብራት ታሪክ፣ የቁጭት ትርክት አድርገው ቢመርጡ (Collective Memory) ወይም ወደፊት እንዲህ ሊሆን ይችላል የሚል የስብራት ስጋት ትርክት አድርገው ቢመርጡ፣ ሁለቱም ከስሜት ንዝረት አቅጣጫ ያለፈ ቁጭት/በቀልና የወደፊት ስጋት በመሆን፣ ከአሁን ግጭት ጋር እያቀናጁት ስለሆነ አንድ ናቸው። እንዲህ ባለው ስሜት ውስጥ አንድ ብሔር ካለፈው ሁለት መቶ ዓመት ሁኔታዎች ውስጥ በመረጠው የቁጭት ትርክት ወይም ደግሞ ወደፊት ከመቶ ዓመት በኋላ ሊከሰት ይችላል በሚል የስጋት ትርክት ወደ ሙሉ ጦርነት ሊሔድ ይችላል። በዚህ ውስጥ ግን አስደናቂው ነገር አሁን የዚህ ትርክት ስሜት ተሸካሚ የሆነው ትውልድ፣ ያለፈውም “በደል” ሆነ የወደፊቱ ያልተከሰተ “ጥቃት” ቀጥተኛ ንክኪ የሌለው መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ለዚህኛው ለአሁኑ ትውልድ፣ ይህ ያለፈና የአሁን የቁጭትና የሥጋት ትራኬ ስሜታቸውን ለሙሉ ጦር መነሳሻ ሲያዘጋጃቸው እንመለከታለን። ከአዙሪት አለመውጣት የሚያስከትለው ሳንካ በርካታ ነው። ካለፈ ጉዳት ጋር አለመጣበቅና በወደፊት ስጋት ተግባርን አለመምራት የእዚህንና የአሁኑን (Here and Now) በግልም በቡድንም በሚገባ ለመኖር ይጠቅማል።

ይህንን አለማስተዋል ማንነትን መሰረት ሊያደርግ የማይገባ “የማንነት ግጭት” አዙሪት (Vertigo) ውስጥ ይከተናል። የድርድር ሳይንስ ምሁራን ከዚህ አዙሪት መውጣት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ይናገራሉ:: በማንነት ድር በመጠላለፍ ስላለፈው በማውራት የአሁኑና የወደፊቱ እንዳያመልጥ መጠንቀቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። እንደግለሰብም ሆነ እንደቡድን “በገጠመን ግጭት ተዘፍቀናል ወይ? የተጋጩንን ጠላት አድርገን አሉታው ላይ ብቻ ተቸክለናል ወይ? እንግዲያው ቆም ብለን ችግሩን ከሰው ላይ አንስተን የነገረ ግጭት ስም እንስጠው። ያን ጊዜ ችግሩ “እገሌ” ወይም “እነ እገሌ መሆኑ ይቆማል።

በሁለተኛ ደረጃ የመኖርን ዓላማ ዳግም ቃኝቶ፣ ግጭቱን ድንገት አቋርጦ፣ ወደ ከበራ (Celebration) መቀየር። በዚህ ጉዳይ በዓለም ዘመናት ያስቆጠረ የማንነት ውዝግብ ምሕዳር በሆነው መካከለኛው ቅርብ ምስራቅ የግብጽና የእስራኤል ግጭት ላይ በድርድር ባለሙያዎች ታሪካዊ ተብሎ ለዘመናት የሚጠቀሰው የ1977ቱ ድንገታዊው የወቅቱ የግብጽ ፕሬዚዳንት የአንዋር ሳዳት የእስራኤል ጉብኝት ነው። ከዚያ በፊት ዐራት ትልልቅ ጦርነቶችን አድርገዋል፣ ባጭሩ ግን የሰላም ንግግር ጀማሪ ይጠይቃል፣ ይህ እንዳይሆን ፍራቻው ወደፊት አለመግባባት ሲፈጠር አሁንም ያ ወገን ቀዳሚ ተነሳሽነት ይጠበቅበታል የሚል ስጋት ነው፣ በዚህ ምሳሌና በውጤቱ ግን ይህ ሁልጊዜ እውነት አይደለም። በአገራችን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን የግጭት መቀራቅር መንጭቆ ያወጣ፣ የሳዳትን መሳዩ ድንገታዊው የዶክተር ዐቢይ የኤርትራ ጉብኝት ነው። ርግጥ ነው ከዚያ በፊት ለሕዝብ ይፋ ያልሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደተደረጉ በኋላ ላይ ተሰምቷል። ይሁን እንጂ ጉብኝቱም ሆነ የተራዘመው ግጭት መቋረጥ ድንገት ነው። ይህ በሁለቱ አገሮች ማንነት ላይ ያስከተለው የተሐድሶና የተስፋ ብርሃን፣ ማንነትን መሰረት ካደረጉ የግጭት አዙሪቶች መንጭቆ መውጣት ምን ያህል አዋጭ እንደሆነ ይመሰክራል። በጠባቡ ማንነት ለመኖር መወሰን ራስን መግደል ነው!

Originally posted at Addis Admass

Hintset's Pick

Hintset's Pick is a collection of hand-picked articles from different websites.

Share this article:

በሚድን በሽታ ተይዛ በሽታው እየገደላት ያለች አገር፦ኢትዮጵያ

“የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን ዐሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፣ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው። እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈጽሞ አንችልም። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፣ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን ወደ ሞት ይወስደናል። ታዲያ ምን ይሻላል?” ዘላለም እሸቴ (ዶ/ር)

ተጨማሪ ያንብቡ

ሊላሽቅ የሚገባው የኢትዮጵያውያን ልቅ ጀብዱ

የታሪክ አጥኚው አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፉ፣ ኢትዮጵያዊነት “ጨዋነት” ብቻ አለመሆኑን፤ ይልቁን ጸያፍ የሆነ “የጀብደኝነት” አመለካከት ከማንነታችን ጋር የተጋባ መሆኑን ከታሪካችንና ከአሁኑ ሁናቴ ጋር ያዛምደዋል። “ልቅ” የተባለው ይህ “ጀብደኝነት” በቶሎ ካልላሸቀ ያጠፋናል ይላል ዶ/ር አፈወርቅ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.