
[the_ad_group id=”107″]
“ሰፊው ሕዝብ ታሪክ ሠሪ ነው!” ይል ነበር ደርግ። የማርቲን ሉተር የተሓድሶ እርምጃ ግን ተቃራኒውን ይነግረናል፤ ታሪክን የሚሠሩት ግለ ሰቦች ናቸው።
የኮምዩኒዝም ችግሩ ግለ ሰቡን ማጥፋቱ፣ ግላዊውን ፍጡር ከቁብ ያለ መቍጠሩ ነው። ኮምዩኒዝም የግል ፍላጎት፣ የግል ምርጫ፣ የግል አቋም … የሚባል ነገር የለውም። “ሰፊው ሕዝብ” ግለ ሰቡን ውጦታልና የግላዊው ሰው አቋምና ሕልውና ሚዛን አያነሣም። በአገራችንም ሕገ መንግሥት ይኸው ነው፤ በ“ብሔር፣ ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች” ተውጦ ግለ ሰቡ ሟምቷል። ግለ ሰቦች ቡድንን እንደሚያበጁ፣ ስለዚህም ግለ ሰብ ከሌለ ብዙኀኑን የሚያቅፈው ቡድን እንደማይኖር ሆን ተብሎ ተዘንግቷል።
የምዕራቡ ዓለም ደግሞ ለግለ ሰቡ አለቅጥ ትኵረት በመስጠት እና ግለኛነትን በማስፋፋት ለኅብረት እንቅፋትን ይፈጥራል። ከዚህ የተነሣ ግለኛነት ሙሉ በሙሉ ነግሧል። ኅብረት ጨርሶውኑ ለሕልፈት ባይዳረግም፣ ሚዛኑ ወደ ግለኛነት ክፉኛ እንዳዘመመ መካድ አይቻልም። ይህም በሕዝቡ አእምሮአዊ ጤና እና ሌሎች ተጓዳኝ ጕዳዮች ላይ ያስከተላቸው ዳፋዎች የብዙ ጥናቶች ርእስ ከሆነ ከራርሟል።
ስለዚህም ከግለኛነት ለራቀ፣ ሆኖም በብዙኻን ላልተዋጠ ግላዊ ፍጡር (ግለ ሰብ) ተገቢውን አትኵሮት መስጠት ሚዛናዊ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ስለ መሆኑ ይህ ጽሑፍ ይሞግታል። ይህንም ለማድረግ በግለኛነት (individualism) እና በግላዊነት (individuality) መካከል ያለውን ልዩነት አስቀድመን ማስቀመጥ ይኖርብናል።
ግለኛነት (individualism)፣ የራስን ነጻነት ከየትኛውም ውጫዊ ሥልጣን፣ የራስን እንቅስቃሴ ከብዙኻን እንቅስቃሴ ሁሉ የበላይ አድርጎ መውሰድ ነው።[1] ግለኛነት ለራስ ብቻ ማድላት ነው፤[2] ራስ ገነንነት ወይም እኔነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራስ ወዳድነት የሚለው ይህንኑ በመሆኑ የግለኛነት ትርጓሜ አሉታዊ ነው።
ግላዊነት ግን ተፈጥሯችን ነው። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር እንደ ፋብሪካ ምርቶች አንድ ዐይነት አድርጎ አይደለም። እያንዳንዳችን የየራሳችን ቀለም፣ የየራሳችን መልክ አለን። እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን በየግላችን ነው የሚያውቀን። ይህኛው ሰው ከዚያኛው ሰው ልዩነት አለው። ይህ ግላዊነት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን ከዚህ ጋር ጠብ የለውም፤ እንዲያውም ግላዊነታችንን የምናጣቅሰው እግዚአብሔር ከሰጠን ማንነት፣ በእርሱ ከተቸረን የመንፈስ ነጻነት ጋር ነው። ግላዊነት፣ ሰው ከሌሎቹ ፍጥረታት ተለይቶ የሚቀመጥበት መስፈርት በመሆኑ አዎንታዊ ነው።
ለፍቅረኛው የሚያበረክትላትን አበባ ለመግዛት ወደ አንድ የአበባ መሸጫ ሱቅ የገባ ወጣት፣ ሱቁ ውስጥ ያገኛቸው አበቦች በሙሉ የሚያማምሩ እስከ ሆኑ ድረስ በዚያ ካሉት አበቦች መካከል የትኛውንም ቢሸጡለት ችግር የለበትም። ለዓውደ ዓመት ወደ በግ ተራ ያመራ አባወራም፣ ተመሳሳይ የሥጋ መጠን (ምናልባትም ተመሳሳይ ቀለም) እስካላቸው ድረስ ባቀረበው ዋጋ የትኛውንም በግ ቢያገኝ ጕዳዩ አይደለም። “ከልጆቻችሁ መካከል አንዷን ለጋብቻ እፈልጋለሁ፤ የትኛዋም ብትሆን ግን ግድ የለኝም። ዝም ብላችሁ አንዷን ፍቀዱልኝ” በማለት ለወላጆች ጥያቄ ማቅረብ ግን በምንም መልኩ አግባብነት አይኖረውም፤ ከንቀትና ከስድብ ይቈጠራል።[3] እያንዳንዱ ሰው የራሱ ግላዊነት አለውና አንዱን በሌላው ሊተኩ ማሰብ ሰብአዊነትን መግፈፍ ነው።
አንድ ደራሲ ያሳተመው መጽሐፍ ቅጂዎች በሙሉ ተመሳሳይ ጥራት እስካላቸው ድረስ፣ ከመካከላቸው የትኛውም መጽሐፍ ላይ ፈርሞ ቢሰጠኝ ለእርሱም ለእኔም ለውጥ የለውም፤ ከመጻሕፍቱ ጋር በተናጠል የተለየ ፍቅርና ስሜት ሊኖረን አይችልም። ደራሲው፣ “ይቺኛዋን ጥራዝ በተለየ ስለምወዳት ለእገሌ ነው የምሰጣት” አይልም። አንዱ መጽሐፍ በሌላኛው ሊተካ ይችላል። ሰው ግን የፋብሪካ ምርት አይደለም። አምራቹ ከእያንዳንዱ ምርቱ ጋር የግል ቍርኝት የለውም፤ ፈጣሪ ግን ከሰው ጋር ግላዊ ቍርኝት አለው። ይሄ በግ ከዚያ በግ፣ ይሄ አበባ ከዚያ አበባ ልዩነት ባይኖረው፣ ይሄ ሰው ከዚያ ሰው ልዩነት አለው። እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ተለይቶ የተፈጠረ ነው። ግላዊ ፍጡራን በመሆናችን ማንኛችንንም ማንም አይተካንም።[4]
የመንፈስ ነጻነት የሰው ሕላዌ መሠረት ነው። ከነጻነት የተነሣ እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ ሰብእና ያለው መሆን ይጀምራል።
የእንስሳት ልዩልዩነት በባዮሎጂካዊ ዝርያቸው ቀድሞውኑ የተወሰነ ነው። የሰዎች ልዩልዩነት ግን ከባዮሎጂ ድንበር ያልፋል። የመንፈስ ነጻነት የሰው ሕላዌ መሠረት ነው። ከነጻነት የተነሣ እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ ሰብእና ያለው መሆን ይጀምራል። የመንትያዎች ሰብእና እንኳ አንድ አይደለም። የመንፈስ ነጻነት በሰዎች ላይ ብቻ የሚገኝና ሰዎችን ከሌሎች ፍጥረታት የሚለይ ክስተት ነው። ተናጠላዊ ማንነታችን ከተፈጥሮ ብናገኘውም፣ የእውነተኛ ግለ ሰብነታችን መንሥኤ የመንፈስ ነጻነት ነው። ይህ ሰውን ከእንስሳ ይለየዋል።[5]
ግላዊነት የተፈጥሮ መልካችን ነው። አንዳችን ከሌላኛችን የተለየን ነን። አንዱ በተሰጥዖው፣ በችሎታው ከሌሎቹ ተለይቶ ይወጣል። ሊዮናርዶ ዳቬንቺ፣ ማንዴላ፣ ማህሌታይ ያሬድ፣ ኀይሌ ገ/ሥላሴ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተከሰቱት። ከእነርሱ ጋር የተቀራረበ ተሰጥዖ ያላቸው ሌሎች ሰዎች ቢኖሩ እንኳ እነርሱን የሚሆን የለም። “የልዩ ክኂሎት (የጂኒየስነት) ዋጋ የግላዊነት ዋጋ ነው።”[6] እያንዳንዱ ሰው በተሰጥዖው፣ በችሎታው፣ በኀላፊነቱ፣ በዘመኑ የተለየ ነውና።
ይህ ጕዳይ ከሰዎች ግንኙነት ጋርም ይተሳሰራል። ግንኙነቶች ሁሉ ሲያደጉ በጣም ግላዊ እየሆኑና አይተኬነታቸው እየጨመረ ይሄዳል።[7] የሩቅ ግንኙነቶች ግላዊ (personal) ስላይደሉ፣ አንዱን በሌላኛው መተካት አስቸጋሪ አይሆንም። አንድ ሠራተኛ ቢሄድ ሌላ ይመጣል፤ ከዚያ ሠራተኛ ጋር ያለው ግንኙነት ሥር እየሰደደ በመጣና ግላዊ በሆነ መጠን ግን አይተኬነትም ዐብሮ ይፈጠራል። አይተኬነት የግላዊ ግንኙነቶች መልክ ነው።
ግላዊነት የተፈጥሮ መልካችን ነው። አንዳችን ከሌላኛችን የተለየን ነን።
ጥልቅ ግንኙነቶች ግን ግላዊ ናቸውና በዚህ ዐይነቱ ግንኙነት የተሳሰርነውን ሰው በቀላሉ አንተካውም። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ወይም በፍች ያጡ ሰዎች ሌላ የትዳር ጓደኛ ያገኙ ይሆናል። አንዱን ባል በሌላ መተካት ይቻላል፤ ባል የነበረው ያ ግለ ሰብ ግን አይተኬ ነው። አንዷን ሚስት ሌላኛዋ ልትተካት ትችላለች፤ የመጀመሪያ ሚስት የነበረችዋን ያችን ግለ ሰብ ግን የሚተካት የለም። ግለ ሰቦቹ አይተኬ ናቸው። ግለ ሰብ አይደገምም። የጣት አሻራችን፣ የዐይናችን ቀለም፣ ዲ ኤን ኤአችን አይደገምም። መንታዎቻችን እንኳ አይተኩንም። ማንኛችንም አንደገምም።
ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ልባዊና የቅርብ ግንኙነት በመሆኑ ግላዊ ነው። እኔ ለእግዚአብሔር አንድ ሰው ነኝ፤ በምንም በማንም አልቀየርም። እግዚአብሔር እኔኑ ለይቶ ፈጥሮኛልና (መዝ. 139፥13-18)፣ ከሌሎች ለይቶ በስሜ ያውቀኛል (ኢሳ. 49፥1፤ 45፥4)። ሲወድደኝም፣ ለሰው ወዳድነቱ ምሳሌ አድርጎ ሳይሆን፣ እኔኑ ራሴን ነው የወደደኝ። ለምኖርበት ዐላማ እና ፍጻሜም ለይቶ አበጅቶኛል። ከራሱ ጋር ኅብረት እንዲኖረኝ ዋጋ ሰጥቶኛልና በማንም በምንም አይለውጠኝም። ከሌላ ሰው ጋር አያምታታኝም። በጸጋው ለይቶ ለሥራው ስለ ጠራኝ (ገላ. 1፥15)፣ በሌላ ሰው ዋጋ አይመዝነኝም።[8] ይህ ምርጫው የማንነቴ መሠረት፣ የምንነቴ ትርጓሜ ነው።
ክርስትና ኅብረት ላይ የሚያተኵር እምነት ነው።[9] ኅብረት ላይ ያተኵራል ሲባል ግን ግለኛነትን ይቃረናል ማለት እንጂ ከግላዊነት (ከግለ ሰብነት) ጋር ተቃርኖ እንደሌለው መታወቅ አለበት።[10] እግዚአብሔር የሁላችን አምላክ መሆኑ ርግጥ ነው። ግና የሁላችን አምላክ የእኔ፣ የልቤ፣ የግሌ አምላክ እንዳይሆን ምን ይከለክለዋል? “እኛ” “እኔ”ን ያስቀራልን? “እኛ” የተሠራው ከ“እኔ” አይደለምን?
እግዚአብሔር የወደደን በየራሳችን ነው። ማንም ማንንም አይሆንምና እያንዳንዳችን በፊቱ ዋጋ አለን። ከመቶ በጎቹ መካከል አንዱ ሲባዝንበት፣ ዘጠኛ ዘጠኙን ትቶ የባዘነውን አንዱን በግ ፍለጋ የተሰማራው እረኛ (ማቴ. 18፥12-14)፣ እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ምን ያህል ግድ እንዳለው የሚያሳይ ነው። “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” የሚለውም ጥቅስ (ማቴ. 16፥26) የአንድ ሰው ነፍስ ከመላው ዓለም በላይ ዋጋ እንዳለው ያመላክተናል።[11]
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” (ማቴ. 20፥28) “ስለ ሁሉ ሞተ” (2ቆሮ. 5፥15) የሚለው ቃል እውነት ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ለእኔ መምጣቱን፣ ለእኔ መሞቱን ማመንም የዚያኑ ያህል እውነት ነው። ከዚህ የተነሣ፣ እያንዳንዳችን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ” በማለት መፎከር ይቻለናል (ገላ. 6፥14)። “በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” (ገላ. 2፥20) እንድንል የሚያስችለንም ጌታ የወደደን በጅምላ ሳይሆን በየግላችን መሆኑን ስናምን ነው።
ክርስትና ኅብረት ላይ የሚያተኵር እምነት ነው። ኅብረት ላይ ያተኵራል ሲባል ግን ግለኛነትን ይቃረናል ማለት እንጂ ከግላዊነት (ከግለ ሰብነት) ጋር ተቃርኖ እንደሌለው መታወቅ አለበት።
እግዚአብሔር በጅምላ አልወደደንም። የእግዚአብሔር ፍቅር የጀማ ፍቅር አይደለምና በየግላችን ተወድደናል። ሲ ኤስ ሌዊስ እንደሚለው፣ እግዚአብሔር ለየግለ ሰቡ የሚሰጠው ጽንፍ የለሽ ትኵረት አለው። እያንዳንዱ ግለ ሰብ በእግዚአብሔር የተወደደው ከሌሎች ጋር ተደምሮ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በምድር ላይ የፈጠረው ያንን አንዱን ግለ ሰብ ብቻ የሆነ ያህል ነው። ክርስቶስ የሞተልንም በዚያው መጠን ነው፤ በየግላችን![12]
ጌታን ለመከተል ያደረግነው ውሳኔ የግል ውሳኔ ነው፤ የብዙኀን አይደለም። በመሠረቱ፣ ለምንም ነገር ኀላፊነት ወስዶ ሊወስን የሚችለው ግለ ሰብ ብቻ ነው። ለምንም ነገር ተጠያቂ መሆን የሚችለውም ግለ ሰብ እንጂ ቡድን አይደለም።[13] ልማትም ሆነ ጥፋት ግላዊ ውሳኔዎች ናቸው። ጌታን ለመከተል ስንወስን የምንቀላቀለው ወደ ቃል ኪዳኑ ማኅበረ ሰብ ቢሆንም፣ ውሳኔው ግላዊ ነው። “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” የሚለው ውሳኔ የየራሳችን፣ የየቤታችን ነው። ክርስቲያናዊውን የቃል ኪዳን ማኅበረ ሰብ ያስገኘው አቋም፣ አስቀድሞ በእያንዳንዱ ግለ ሰብ በግል የተደረገ ውሳኔ ነው።
ክርስትና ጅምላዊ ባለመሆኑ ለጌታ ደቀ መዝሙርነት የምንበቃው የየራሳችንን መስቀል የምንሸከም ከሆነ ብቻ ነው። እያንዳንዱ አማኝም የየራሱ መስቀል አለው (ሉቃ. 14፥27)። ከዚህም የተነሣ፣ በቃል ኪዳን ማኅበረ ሰቡ ውስጥ ስንኖርም የግል ቍርጠኝነት ሊኖረን ይገባል። በሕይወት ጎዳና ላይ ብዙኀን ሲስቱ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ለእውነት ግድ ሲያጣ፣ መንጋው ዓለምን መስሎ ሊኖር ሲጓጓ በየግላችን ልንቆም ያስፈልጋል። ደቀ መዝሙርነት ከመንጋው ተለይተው፣ “እኔ እና ቤቴ ለእውነት እንኖራለን” የሚሉ ግለ ሰዎችን ይጠይቃል!
የእግዚአብሔር ጥሪ ግላዊ ነው። ዘላለማዊ ጥሪው ለእኔ የተላከ በመሆኑ፣ ለዘላለምም በዚህ ጥሪ ሌላውን ሰው አይጠራም። ጸጋውም ጥሪዬን የሚደግፍበት ነውና ለሌላ ሰው አይውልም። ፍጥረትን እና ምርጫን የሚመለከቱ ክርስቲያዊ አስተምህሮዎች በሙሉ ከዚህ ጋር የተሳሰሩ ናቸው፤ ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎች በተዳከሙበት ስፍራ ሁሉ ግላዊነት በግለኛነት ወይም በቡድናዊነት ተውጦ መገኘቱ የአጋጣሚ ጕዳይ አይደለም። በዓለም ላይ በችሎታቸው እኔን ሊተኩ ብቃት ያላቸው ሰዎች በርካቶች ቢሆኑም፣ ማንም እኔን ሊሆን አይቻለውም። ስለዚህም እግዚአብሔር ባስቀመጠኝ ስፍራ በመጽናት እርሱ በእኔ ሊፈጽም የወደደውን ሥራ መሥራት ይጠበቅብኛል። ማንም እኔን ሆኖ በእኔ ተሰጥዖ፣ በእኔ ጊዜ፣ በእኔ መንገድ ሥራውን አይሠራውም። የእግዚአብሔር ጥሪ ከሰዎች ነጥሎ የሚያወጣውና ለብቻ እንዲቆሙ የሚጠይቀው ለዚህ ነው። ጥሪን የሚያከብደውም ይሄ ነው።[14] አሊያማ እግዚአብሔር “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልኛል?” እንዴት ይላል (ኢሳ. 6፥8)? ይህ ሁሉ ሰው እየተተራመሰ እንዴት እግዚአብሔር ሰው ያጣል!?
ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎች በተዳከሙበት ስፍራ ሁሉ ግላዊነት በግለኛነት ወይም በቡድናዊነት ተውጦ መገኘቱ የአጋጣሚ ጕዳይ አይደለም።
ምክንያቱም፣ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሁሉ ከመንጋው ተነጥሎ ለእግዚአብሔር እውነት የሚቆምን ሰው ነው እግዚአብሔርም የሚፈልገው። ብዙኀን አድርባይ ሲሆኑ፣ ብዙኀን ሆዳቸው አምላካቸው ሲሆን፣ ብዙኀን በመንጋ ሲያስቡ፣ እግዚአብሔር ለእውነት የሚቆምና ብቻውንም ቢሆን መንጋውን የሚቃወምን ሰው በብርቱ ይፈልጋል። እግዚአብሔር ለኅብረት በምናደርገው አስተዋጽኦ ቢመዝነንም፣ ለኅብረት ስንል እውነትን ብንሠዋ ግን በፊቱ በደለኞች ነን። ከቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ቅዱስ አትናቴዎስ በራሱ ዘመን ለእግዚአብሔር እውነት ብቻውን ለመቆም የደፈረ ስለ ነበረ “አትናቴዎስ ዓለምን ተገዳድሮ ቆመ” (“Athanasius against the world.”) በሚል ፈሊጣዊ ንግግር እስካሁን ይታወሳል።
እውነት መሠረታዊ ጕዳይዋ ብዙኀን አይደሉም። እውነትን የተረዱ ሰዎች ሲሰባሰቡ ብዙኀንን ቢያስገኙም፣ እያንዳንዱ ግለ ሰብ ራሱን ችሎ ለእውነትና ለሕይወት ወደ መቆም ካላደገ፣ ኅብረቱ ለእውነት የሚቆሙ ቈራጥ ሰዎች ስብስብነቱ እየላላ የፈሪዎች ዋሻ ይሆናል። ኅብረቱ ሚዛን እየደፋ፣ እዚያ ውስጥ ሊጠለል የሚመጣ ግለ ሰብ ሁሉ፣ ውሳኔውን ለብዙኀኑ እየተወ ራሱን ችሎ መቆምን መፍራት ይጀምራል። ከዚህም የተነሣ ሰዎች በግላቸው ለጥሪአቸውና ለሕይወታቸው መቆምን እየዘነጉ ብዙኀኑን ተከልለው ይኖራሉ። ይህም የፍርሃት መዋጮ የቡድኑን ድምር ፍርሀት ያበጃል።
በዚህ መልኩ እያንዳንዱ ፈሪ ግለ ሰብ የየራሱን የፍርሀት መዋጮ እንደ ያዘ በብዙኀኑ ውስጥ ተደብቋልና የኋላ ኋላ ኅብረቱ የፈሪዎች እና የአድርባዮች መደበቂያ መሆኑ አይቀርም። ብዙኀን የተባለው ቡድን የራሱ እጅ ባይኖረውም፣ ሰዎች በግላቸው ማድረግ የፈሩትን ነገር፣ ብዙኀን ደፍረው ሲያደርጉት የመስተዋሉ ምክንያት ከዚህ የራቀ አይደለም። ከዚህም የተነሣ ብዙኀኑ ግለ ሰቡን ይውጡትና መጀመሪያ በግሉ ለእውነት ጨክኖ የወሰነው ያ ብርቱ ሰው ይጠፋል። ሶረን ኪርክጋርድ፣ “ብዙኀን እውነት አይደሉም” (crowd is untruth) የሚለው ለዚህ ነው።[15] አሁን በምድራችን ያለው ክርስትና እዚህ ጋ እንደ ደረሰ ወይም እየደረሰ እንደ ሆነ የምር ዐስባለሁ።
የግላዊነታችን ማጣቀሻ፣ የግላዊ ማንነታችንን መጎናጸፊያ እግዚአብሔር የቸረን የመንፈስ ነጻነት ነውና እኛም ነፍሳችንን መልሰን ለእርሱ ማፍሰስ አለብን። የምንኖርለትም የምንሞትለት ዐላማ እግዚአብሔር ሲሆን፣ የማንነት ክበቡ ይሟላል። የነፍሳችን መገኛም ነፍሳችንን መሥዋዕት ልናደርግለት የተገባው ነው!
በየግላችን ልንቆምለት የተፈጠርንለት መለኮታዊ እውነት ረቂቅ አይደለም፤ እግዚአብሔር በልጁ የገለጠው ግዙፍ ፍቅር እንጂ። ውሃ ልኩም ፍቅሩን በተረዳንበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ዘንድ ይገኛል። ልከኛነቱ በዚህ መልክ ከተጠበቀ፣ ግላዊነት በተናጠላዊነት አይደመደምም። “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” የሚለው ሐዋርያዊ ምክር (1ጢሞ. 4፥16) ከዚህ ይመዘዛል። “ጌታ ለእኔ ሞቶልኛል” ብለው የሚያምኑ ሁሉ፣ “አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ” መሆኑን ያምናሉ። እውነትን የሚፈልጉና በዚህም እግዚአብሔርን አባታቸው ያደረጉ ሁሉ አንዱን እግዚአብሔርን ያመልካሉ። ስለዚህም በአንድነት “አባታችን ሆይ” ማለታቸው አይቀሬ ነው።
የእግዚአብሔር ዕድል ፈንታ ሕዝቡ በመሆኑ (ዘዳ. 32፥9) በእግዚአብሔር የተወደደ ሰው በሕዝቡ ጕዳይ ከዳር አይቆምም። ጌታ ያለቀሰው ጥፋት ለቀረበባት ኢየሩሳሌም፣ ይኸውም ለነዋሪዎቿ አይደለምን (ሉቃ. 19፥41)? ለእውነት መቆም፣ ወንጌልን ከብርዘት መከላከልን ያቅፋል። ዘረኛነትን ለማፈራረስ መንቃትን ያስገድዳል። ባልንጀራ በሰላም እንዲኖር መጣርን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ባልንጀራ ማለት፣ የትኛውም ሌላ ሰው መሆኑን ከመቀበል ይጀምራል። ለእውነት መቆም፣ “እንደ ወንጌል እውነት” ያልሆኑ የሕይወት አካሄዶችን ፊት ለፊት መቃወምን ይጠይቃል (ገላ. 2፥14)። የማንኛችንም ጥሪ በየግል ቢሆንም፣ በከንቱ እንዳንሮጥ ሩጫችንን በቀዳሚዎቹ ሐዋርያት አስተምህሮ ማስፈተሻችን ግድ ነው (ገላ. 2፥2)። ሁሉ የየራሱን ደጅ ማጽዳቱ በፍጻሜው ከተማዪቱን ያጸዳታልና! አሊያ በየደጃችን የምናቀነቅነው “እውነት”፣ ሙሉውን እውነት ሲቀናቀን ይገኛል።
በዚህ ውስጥ በጭራሽ ልንዘነጋው የማይገባ አንድ ድምዳሜም አለ። ይኸውም፣ በነገር ሁሉ ፍጻሜ በእግዚአብሔር ፊት የምንቆመው ለብቻ መሆኑ ነው። ተጠያቂነታችን በየራሳችን ነው። እያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ ኀላፊነት ያለበት ፍጡር ነውና በፍርድ ቀን በግሉ ከተጠያቂነት አያመልጥም። ኀላፊቱን በአግባቡ ባይከውን፣ ጥፋቱን ወደ ሌላኛው ሰው ጫንቃ ማሻገር አይችልም። እንደየአቅማቸው የተለያዩ መክሊቶች የተሰጣቸው ባሮች ምሳሌ ይህን ነው የሚያሳየን (ማቴ. 25፥14-30)። ሰው ግላዊ ፍጥረት ነውና በየግሉ ይፈረዳል።
ሰው ከመንጋ ተለይቶ ለእውነት እንዲቆም፣ ለጥሪው ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠየቀው ለዚህ ነው።
በዚያን ጊዜ፣ የጋራ ሕይወት ያከትምና ግለ ሰቡ በግሉ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል። እናም እኔ፣ ግለ ሰቡ፣ በእግዚአብሔር ፊት ለፊት እቆማለሁ። ብቻዬን። ጌታን ማመን፣ እውነትን መከተል፣ የእግዚአብሔርን ምርጫና ጥሪ መስማትና መቀበል ያለብኝ በግሌ እንደ ሆነ ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊትም ብቻዬን እቆማለሁ። ማንም ማንንም ሊያግዝና ሊረዳ አይችልም። የትኛዋም ቤተ ክርስቲያን፣ የትኛውም ሐዋርያ፣ የትኛውም ነቢይ፣ የትኛውም መጋቢ፣ የትኛውም የእግዚአብሔር ሰው ለእኔ አይቆምልኝም። በሁሉ ዳኛ ፊት የምቆመው እኔው ራሴ ነኝ። ከመሓሪው እና ጠበቃ ከሚያቆምልኝ (1ዮሐ. 2፥1) ከራሱ ከአንድዬ በቀር ማንም በቦታዬ ሊታይልኝ አይችልም። ከዚህ ኀላፊነቴ የሚያላቅቀኝ ምንም ዐይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የለም። ሰው ከመንጋ ተለይቶ ለእውነት እንዲቆም፣ ለጥሪው ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠየቀው ለዚህ ነው።[16]
ለመሆኑ ዛሬ በፈቃዱ ለእግዚአብሔር እውነት የሚቆም ሰው ማነው!?
(ይህ ጽሑፍ ከዚህ ቀደም በ semayawithought.org ላይ ለንባብ የቀረበ ነው።)
[1] J. A. Ryan, “Individualism,”The Catholic Encyclopedia (New York: Robert Appleton Company, 1910).
[2] አማርኛ መዝገበ ቃላት (አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ 1993 ዓ.ም)።
[3] Emil Brunner, Man in Revolt: A Christian Anthropology, tr. Olive Wyon (Cambridge: Lutterworth Press, 1957), 282.
[4] ዝኒ ከማሁ።
[5] Paul S. Chun, Principles of Christian faith (Morrisville: Lulu Press, 2008), 45; Reinhold Niebuhr, The Nature and Destiny of Man: A Christian Interpretation, vol. 1 (Louisville: Westminster John Knox Press, 1996), 55.
[6] Brunner, Man in Revolt, 281.
[7] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 282።
[8] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 283።
[9] በዚሁ ጸሓፊ የተዘጋጀውን “እኔነት የሚፈታተነው የክርስቶስ ማኅበር አንድነት” የሚል ርእስ የያዘ ጽሑፍ፣ ከሕንጸት መጽሔት ቁጥር 8 ዕትም ይመለከቷል።
[10] ክርስትና አያዎ (paradox) ይበዛዋልና ለጤናማ መንፈሳዊነት ሚዛናዊነት ያስፈልጋል። ድነናል ሲል የነገረን ያው መጽሐፍ መዳናችን ከትናንት ይልቅ ዛሬ እየቀረበ መሆኑን በመናገር መዳናችንን ለነገ ያቈየዋል (ኤፌ. 2፥8፤ ሮሜ 13፥11)። የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችን መሆኗን ያበሰረን ያው መጽሐፍ፣ መንግሥቱ ገና እንደምትመጣም ያሳስበናል (ሉቃ. 17፥21፤ 19፥11-12)። የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችንን ከነገረን በኋላ፣ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና እንዳልተገለጠም የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ ነው (ዮሐ. 1፥12፤ 1ዮሐ. 3፥2)። ሰይጣን እንደ ተሸነፈ ያስተማረን መጽሐፍ፣ ሰይጣንን እንድንዋጋም ያሳስበናል (ቈላ. 2፥15፤ 1ጴጥ. 5፥8)። ልክ እንደዚሁም እግዚአብሔር አንድ ሲሆን፣ ግን ሦስት አካላት አሉት። ጌታ ኢየሱስ አምላክ ነው፤ አምላክነቱን ሳይተው ግን ሰው ሆኗል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉት አስተምህሮዎች ሚዛናዊነትንና ጥንቃቄን ይጠይቃሉ።
[11] Chun, Christian Faith (Morrisville: Lulu Press, 2008), 46.
[12] C. S. Lewis, Mere Christianity (New York: HarperCollins, 2009), 168.
[13] Brunner, Man in Revolt, 278.
[14] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 284።
[15] Soren Kierkegaard, The Point of View for My Work as an Author: A Report to History, and Related Writings, tr. Walter Lowrie (New York: Harper & Row, 1962), 113.
[16] Brunner, Man in Revolt, 285.
Share this article:
የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ ጤናማ ትምህርት፣ ጤናማ ኑሮ (ክፍል ሦስት)
የምወድህ (የጽሑፍ ልማድ ኾኖ እንጂ አንቺም አለሽበት) አንባቢዬ ሆይ፣ “ምን ላንብብ? ለማንስ ላስተላልፋት?” እንደምትለኝ እገምታለሁ። ይህችን መጣጥፍ ለመጫር ምክንያት የኾነኝን ነገር መጨረሻ ላይ ነው የምነግርህ። በቅድሚያ ስለ ንባብ/ ማንበብ ጥቂት እንድጫጭር እያነበብህ ፍቀድልኝ።
“I must say, however, that if the government behaves in a cavalier, careless, cunning, off-handed or unilateral manner in terms of the ways in which it tries to resolve the Southern conundrum, I fear that the future of Ethiopia as a nation-state would be in mortal danger”, warns Desta Heliso (PhD) on the current regional statehood request in SNNPR. The article was published first on the weekly Reporter.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
1 comment
Beautifully written! Thank you, Paul!
“…ክርስትና ጅምላዊ ባለመሆኑ ለጌታ ደቀ መዝሙርነት የምንበቃው የየራሳችንን መስቀል የምንሸከም ከሆነ ብቻ ነው። እያንዳንዱ አማኝም የየራሱ መስቀል አለው (ሉቃ. 14፥27)። ከዚህም የተነሣ፣ በቃል ኪዳን ማኅበረ ሰቡ ውስጥ ስንኖርም የግል ቍርጠኝነት ሊኖረን ይገባል። በሕይወት ጎዳና ላይ ብዙኀን ሲስቱ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ለእውነት ግድ ሲያጣ፣ መንጋው ዓለምን መስሎ ሊኖር ሲጓጓ በየግላችን ልንቆም ያስፈልጋል። ደቀ መዝሙርነት ከመንጋው ተለይተው፣ “እኔ እና ቤቴ ለእውነት እንኖራለን” የሚሉ ግለ ሰዎችን ይጠይቃል!…”