[the_ad_group id=”107″]

"ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕሙማን ምቹ ቦታ ናት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም"

እውቁ የሥነ አእምሮ ሐኪምና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም አሳሳቢነቱ ጨምሯል ስለሚባለው የአእምሮ ሕመም ከሕንጸት መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ፣ ችግሩን በተመለከተ በወንጌላውያን አማኞች መካከል ስላለው የአመለካከት ክፍተትና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ርምጃዎች ሚክያስ በላይ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል።

  • በአገር አቀፍ ደረጃ የአእምሮ ሕመምተኞች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል? በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ ይኸው ችግር በቁጥር ለመግለጽ በሚያስችል መልኩ የተደረገ ጥናት ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- ʻበአገራችን ያለው የአእመሮ ጤንነት ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ወይ?ʼ ለሚለው ጥያቄ፣ አሳሳቢነቱ አጠያያቂ አይደለም፤ ነገር ግን፣ ʻከየት ተነሥቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሰ?ʼ ለሚለው መነሻው ምን እንደ ሆነ በትክክል ስለማይታወቅ ካለፉት ዘመናት ይልቅ አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ይሆናል። ምክንያቱም በቀደሙት ዘመናት የታወቀ ብዙ ነገር ስለሌለ። ነገር ግን፣ በሌላ መንገድ አሳሳቢ ነው ለማለት የሚያስችለን ከሕዝባችን ቊጥር ዕድገት ጋር ተከትሎ፣ ከአኗኗር ዘይቤአችን መቀየር ጋራ ተያይዞ፣ ከኢኮኖሚያችን፣ ከማኅበራዊ ሕይወታችን በከባድ ለውጥ ላይ፣ በፍጥነት ታላቅ ለውጥ እያስተናገድን ባለንበት ሁኔታ ላይ የአእምሮ ጤንነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቊጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። እናም አሳሳቢ ነው። በተለይ ይህንን ችግር ለመፍታት በአገር ደረጃ ካለው የግብዓት ዕጥረት አኳያ፣ የአገልግሎቱ መጠን አናሳነት፣ የባለሙያዎች ቊጥር ውስንነት ጋራ ተደማምሮ ስናየው የችግሩ መጠን ከፍተኛ ነው ብለን መናገር እንችላለን።

ʻይሄ ጕዳይ በወንጌል አማኝ ማኅበረ ሰቡ አኳያ ሲታይ ምን ይመስላል?ʼ ለሚለው፣ በፕሮቴስታንቱ ማኅበረ ሰብ ላይ በተለየ የተጠና ጥናት የለም። ነገር ግን ችግሩ እዛም ውስጥ አለ። የዚያም ማኅበረ ሰብ አማኝ ቊጥር እየጨመረ በሄደ ቊጥር የሕመምተኛውም ቊጥር በዚያው መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሄ በእኔም ልምድ፣ በየቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ዕይታና ልምድም በግልጽ እየታየ ያለ ችግር ነው። እንግዲህ የአእምሮ ሕመም ዘርን፣ ወገንን፣ ሃይማኖትን፣ ጾታን፣ የኑሮ ደረጃን የማይለይ፣ በማንም ሰው ላይ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል የጤና ችግር ነው። ስለዚህም በፕሮቴስታንቱ ማኅበረ ሰብም ይሁን ወይም በሌላው ልዩነት ያለ አይመስልም።

  • ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕሙማን ምቹ ሥፍራ ነች ማለት እንችላለን? ካልሆነችስ ምክንያቱ ከምን የመጣ ነው?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- የወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን ከሌላው በተለየ ለአእመሮ ሕሙማን ምቹ ናት ብሎ መናገር አይቻልም፤ እንደዚያም ብለ ለመናገር የሚያስደፍር መረጃ የለም። ʻለምንድን ነው?ʼ ካልን፣ አእምሮው የተረበሸ ሰው በአብዛኛው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል። ፈውስን ከእግዚአብሔር ለመለመን፣ ጸሎት እንዲደረግለት ወደዚያ ይሄዳል። የሚያምነውም፣ የማያምነውም ይሄዳል። ይሁን እንጂ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ደግሞ በእንደዚህ ዐይነት ችግር ላሉ ሰዎች የሚሆን አመቺ አቀባበልና ተስማሚ የሆነ አገልግሎት ማቅረብ ስላልተቻለ፣ የዕውቀቱም ሆነ የግንዛቤው ችግር ስላለ ከሌላው ቦታ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ለእንደዚህ ዐይነት ሰዎች ምቹ ናት ለማለት የሚያስደፍር መረጃ የለም። እንዲያውም ሁሉም ነገር ከክፉ መናፍስት ጋር የተገናኘ ነው የሚል ግንዛቤ ከመኖሩ የተነሣ፣ ለሕሙማን ፍቅርን፣ ርኅራኄን፣ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን የማቅረብ፣ መጠለያና አልባሳትን የመስጠትና እንደማንኛውም ሰው እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት አይታይም። በመሆኑም፣ የወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕሙማን በተለየ መንገድ ምቹ ቦታ ናት ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር ነገር የለም።

  • በአእምሮ ሕመምተኛና በክፉ መናፍስት አማካኝነት በሚመጣ የአእምሮ መታወክ መካከል ያለው አንድንነትና ልዩነት ምንድን ነው? በክፉ መንፈስ ለሚመጣ ሕመም የሚደረግ ሕክምና ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ከባድ የሚያደርገው ይህንን ጕዳይ በተመለከተ ሁለት ጽንፎች መኖራቸው ነው። አንደኛው ጽንፍ፣ በሳይንሱ ዓለም በመናፍስት ምክንያት ሰዎች የአእምሮ ሕመም ሊይዛቸው ይችላል ተብሎ አይታመንም። የተለየ የመናፍስት ዓለም እንዳለም ተቀባይነቱም ሆነ እምነቱ የለም። ስለዚህ የአእምሮ ሕመም ሁሉ መነሻው ሥነ ሕይወታዊ ነው፣ ማኅበራዊ ነው፤ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ነው፤ ከእነዚህ በተለየ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሊኖረው ይችላል ብሎ አያምንም፤ አያስተምርም፤ ምርምርም ሆነ ጥናት አያደርግም።

በመንፈሳዊው በኩል ደግሞ፣ በጣም መንፈሳዊ ነን ብለው ስለ አእምሮ ሕመም መንፈሳዊ ግንዛቤው ወይም መረዳቱ አለን የሚሉ ሰዎች ደግሞ ምክንያቱ መንፈሳዊ ብቻ ነው፤ ከክፉ መንፈስ ብቻ ነው የአእምሮ ሕመም ሰዎችን ሊያጠቃ የሚችለው፤ ስለዚህ መፍትሔውም ጸሎት ብቻ ነው፤ ከእግዚአብሔር በሚመጣ ኀይል ብቻ ነው መፍትሔ ያለው እንጂ፣ ሕክምና ወይም ሳይንሱ ስለዚህ ጕዳይ የሚያመጣው መፍትሔ የለም ተብሎ ይታመናል።

እነዚህ ሁለቱ በጣም የተራራቁ ጽንፎች ናቸው፤ የከረሩ፣ ሁለት ጥጎች ናቸው። እንግዲህ እንደዚህ ሁለት የከረሩ ጽንፎች ሲኖሩ ብዙ ጊዜ፣ እውነቱ መኻል ላይ ነው የሚቀረው። እኔ፣ እንደ አእምሮ ሕክምና ባለሙያነቴም ሆነ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አማኝነቴ እውነቱ መኻል ላይ ቀርቷል ብዬ ነው የማምነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱና ሕመም የነበረባቸውን ሰዎች ስናይ “የሌጌዎን መንፈስ” የነበረበትን ሕመምተኛ እናገኛለን። በዚህ ሰው ላይ የታዩና የተገለጡ ባሕርያት በሙሉ፣ የአአምሮ ሕመምተኞች የሚያሳዩአቸው ባሕርያት ናቸው። በርግጥ እነዚህ ባሕርያት ሁሉም በአእምሮ ሕመምተኞች ላይ የሚታዩ ሳይሆን፣ ጠና ያለ ወይም ከበድ ያለ የአእምሮ ሕመም ያላቸው ሰዎች ላይ የሚታዩ ባሕርያት ናቸው። እራሱን ይጎዳ ነበር፣ ራቁቱን ነበር፣ ሰውን ለመጉዳት ይሞክር ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ታስሮ ነበር፤ ለብቻ ተገልሎ በመቃብር ቦታ ይኖር ነበር ይላል። ይህ ገለጻ በእኛ አገር ያለውን የአእምሮ ሕመምተኞችን አያያዝ የሚመስል ነው።

ይህን ዐይነት ሰው ይዘህ እኔ ጋ ለሕክምና ብትመጣ ለሕመሙ የምሰጠው ስምና የሕክምና ዐይነት አለ፤ የማዝዝለት የመድኃኒት ዐይነት አለ። ይህንን ሰው፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉ መንፈስ እንዳለበት ተረድቶ፣ መንፈሱን እንዲወጣ በአዘዘውና መንፈሱ ከሕመምተኛው በተለየው ጊዜ፣ ይህ ሰው ወደ እራሱ እንደ ተመለሰና ጤነኛ መሆን እንደ ቻለ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይናገራል። ከዚህ ተነሥተን ስንመለከት፣ ሰዎች በሌላ መንፈስ ጥቃት ምክንያት የአእምሮ ሕመምተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ መካድ አይቻልም። በሌላ በኩል ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የሕክምና መጽሐፍ ስላይደለ የሕመም ዐይነቶችን ሁሉ ዘርዝሮ መነሻቸውን አልነገረንም። ከዚህ የተነሣ የአእምሮ ሕመም በሌሎች ምክንያቶችም ሊመጣ ይችላል ብለን ብናምን ከክርስትና እምነታችን ጋር የሚጋጭ ነገር አድርገን መውሰድ አንችልም።

በነገራችን ላይ የክፉ መናፍስት አሠራር ለአእምሮ ሕመም ብቻ የተተወ አይደለም። “ጎባጣ” የነበረች ሴት እና ማየትና መናገር የተሳነው ሰው የነበረ ሰው በክፉ መናፍስት ተጽእኖ ሥር እንደ ነበሩና መንፈሱ ሲወጣላቸው፣ ሙሉና ጤነኞች ሰዎች እንደ ሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይናገራል። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያለው እምነት የአእምሮ ሕመም ከክፉ መናፍስት ጋር ብቻ ተያይዞ የሚታይ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህም አመለካከትና እምነት የተነሣ ለአአምሮ ሕመምተኞች የሚደረገው ጥንቃቄና እንክብካቤ በጣም አናሳ ሆኖ ይታያል።

ትልቅ ፈተና ሆኖ የሚመጣው፣ እንዴት መለየት ይቻላል የሚለው ነው። ሕመሙ የመጣው በክፉ መንፈስ ምክንያት ነው ወይስ በሌሎች ምክንያቶች ነው የሚለው ከባድ ፈተና ነው። እግዚአብሔር በተለየ መንገድ መናፍስቱን የመለየት ስጦታ ለሰዎች ሰጥቷቸው ካለወቁት በስተቀር፣ በሕክምናው ዓለም (አማኝም ቢሆን) ʻይሄ እንደዚህ ነው፣ ያ እንደዚያ ነውʼ ብሎ ድምዳሜ መስጠት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን፣ በማንም ምክንያት ይሁን ወይም በምንም ምክንያት ሰዎች በመረበሻቸው፣ እንቅልፍ በማጣታቸው፣ ራሳቸውን ባለመጠበቃቸው የሚመጣባቸውን ችግር መድኃኒት በሚሰወስዱበት ጊዜ፣ በአብዛኛው (ሁሉም ማለት ባይቻልም) የመረጋጋት፣ እንቅልፍ በትክክል የመተኛት፣ ራሳቸውን በትክክል የማወቅ፣ አካባቢያቸውን የማወቅ፣ ከሰዎች ጋራ የተሻለ ግንኙነት የማድረግ፣ ከዚያም አልፎ ታክመው ፈጽመው የመዳንና ወደ ቀደመው ተግባራቸው ሄደው ምርታማ ሆነው፣ ቤት ትዳር መሥርተው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ሕይወታቸውን መርተው የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ በብዛት ስላሉ ይህን መካድ ደግሞ አስቸጋሪ ነገር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ʻበልዩ መንፈስ ምክንያት የአእምሮ መታወክ ካለ ሕክምናው ሊያድነው ይችላል ወይ?ʼ የሚለው ጥያቄ ከባድ ጥያቄ ነው። እስከ አሁን ድረስ ባለው ጥናት መሠረት ለአንዳንድ የአእምሮ ሕመም ዐይነቶች መቶ በመቶ የሚያድን ሕክምና የለም። ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ ታክመው በጥሩ ሁኔታ ሕይወታቸውን መምራት የሚችሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ታክመው ደግሞ (አነስተኛ ቊጥር ያላቸው ቢሆኑም) ወደ ቀደመው ሕይወታቸው መመለስ የማይችሉ፣ ተከታታይ የሆነ ድጋፍና ዕርዳታ፣ የሌሎች ሰዎች እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አሉ። በመሆኑም፣ ሕክምናው አሁን በደረሰበት ደረጃ ሙሉ በሙሉ ወይም ለሁሉም መቶ በመቶ መፍትሔ አምጥቷል ብሎ መናገር አይቻልም። ይህ እስካልተቻለ ድረስ ደግሞ ሰዎች በሌላ መንገድም ዕርዳታ ሊገኝ ይችላል ብለው ቢያምኑና ቢፈልጉ፣ ልክ አይደላችሁምʼ ብሎ መንቀፍ ከትእቢተኝነት አልፎ ሳይንሳዊ አያደርገንም። ምክንያቱም፤ አንደኛ፣ ለብዙዎቹ የአእምሮ ሕመም ዐይነቶች ጥርት ባለ መንገድ ʻመነሻው ይሄ ነውʼ ብሎ ለመናገር የሚያስችል ማስረጃ የለም፤ ብዙ ነገሮች ገና በጥናት ሂደት ላይነውያሉት።ʻእኛጋርብቻነውመፍትሔ ያለው፤ እኛ ጋር ሁሉም ዕውቀት አለ፤ ስለዚህ ሰዉ ሌላኛውን አማራጭ መሞከር የለበትምʼ የሚል ካለ እሱ ሳይንቲስት ነው ብዬ ለማለት ይቸግረኛል።

  • ከአጋንንት እስራት ነጻ ለሚወጡ ሰዎች ልዩ የሆነ የሥነ አእምሮ ክትትል ያስፈልጋቸዋል?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- እንግዲህ በእኛ ሙያ የተለያዩ ዐይነት የሕክምና ዐይነቶች አሉ፤ የመድኃኒት ሕክምና አለ፤ የማማከር ሕክምና አለ (psychotherapy)፤ ሌሎችም ዐይነት ሕክምናዎች አሉ። እነዚህ ሁሉ ሕክምናዎች ብቻቸውን ሰውየውን ወደ ነበረበት ቦታ አያመጡትም። ለምሳሌ፣ ሥራውን አጥቶ፣ የነበረውን ክኅሎት ሁሉ ረስቶ፣ በዚህ ሕመም ተቸግሮ የኖረ ሰው፣ መድኃኒት ሰጥተነው እነዚያ ይታዩ የነበሩት ችግሮቹ ቆመው ሊረጋጋ ይችላል። ነገር ግን ይህ ሰው ማኅበራዊ ክኅሎቶቹን፣ ሙያውንና የመሳሰሉትን ነገሮች ደግሞ አጥቷቸዋል። ስለዚህ ይህ ሰው እንደገና ማገገም (rehabilitation) ያስፈልገዋል። ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመሳሰሉት ዐይነት ድጋፎች እንዲሁም ክትትሎች ያስፈልጉታል። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች የሕክምና ተቋማት አንድ ሰው መድኃኒት ተሰጥቶት ወይም ʻበጸሎት ተፈውሰሃልʼ ተብሎ ብቻ ሊተው አይገባውም፤ እንዲህ ያለውም አካሄድ ትክክል አይመስለኝም። እንዳልኩት ብዙ ክትትል መደረግ አለበት፤ በጸሎትም ሆነ ቁሳቁሳዊ በሆነው ሁሉ ዕርዳታና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ታማሚዎቹ ራሳቸውን ችለው፣ ተቋቁመው ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት እስኪችሉ ድረስ ይህን መሰሉ ክትትል ያስፈልጋቸዋል።

  • ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በእግዚአብሔር ስም የሚነገሯቸው “የተስፋ ቃል” አለመፈጸም ወደ ከፋ ችግር እየወሰዳቸው እንደ ሆነ ይነገራል፤ አንዳንዶችም ፍጹም ለሆነ የአእምሮ መታወክ እንደተዳረጉ ይታወቃል። እርስዎ እንደ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያነትዎ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አማኝነትዎ በዚህ ላይ ያለዎትን አመለካከት ቢነግሩን?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- እንደዚህ ዐይነት ነገሮች፣ በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ በብዛት እየተከሰቱ፣ ʻእግዚአብሔር እንደዚህ ብሏል፤ ይህን ተናግሯል፤ ይህንን አምጡ፤ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ይሆናልና ያላችሁን ንብረት ሽጡ፤ ሥራችሁን ተዉና ይህን አድርጉʼ እየተባሉ፣ ነገር ግን የተባላለቸው ነገር ሳይፈጸም እየቀረ ብዙ ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎች እንዳሉ እኔም በግሌ አውቃለሁ፤ ሰምቻለሁም። ከሙያ አጋሮቼ ጋር ስንወያይም ይህን መሰሉ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች እንደገጠሟቸው ነግረውኛል። አዎ፤ ከዚህም የተነሣ የአእምሮ መረበሽ የገጠማቸው፣ ሕክምና ያስፈለጋቸው፣ ሁሉን ነገር ያጡ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ።

ይሄ በሰው ሥነ ልቦና ላይ ጉዳት ማምጣት ነው፤ ከእምነቱም ወይም ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጋር የማይሄድ ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰው እምነቱን በአግባቡ ካለማወቁና ካለመረዳቱ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ደግሞ በግል ሊኖር የሚገባው ግንኙነትና ኅብረት የላላ በመሆኑ ነው። በሁለቱም ወገኖች በኩል፤ ተጠቂ የሆኑትም ሆነ ይህን ነገር አድርጉ የሚሉትም ሰዎች ጭምር። እኔ መቼም፣ ቤተ ክርስቲያን ጕዳዩን በትክክል ተረድታና አውቃ፣ እነዚህን ሰዎችም ለይታ ምእመናንን ከጥቃት ልትጠብቃቸው፣ እንዲህ ያለው ልምምድም ሆነ አስተምህሮ ትክክል አለመሆኑን በግልጽ ልትናገር፣ ይህን ጕዳይ የፈጸመውን ሰው ልትገሥጽ፣ ልትመክር፣ ልትመልስ ይገባታል ባይ ነኝ። ጉዳት የደረሰባቸውንም ሰዎች በማጽናናት አብራቸው ልትቆም ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ፣ እንዲህ ዐይነት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እምነቱንም ሊተዉት ይችላሉ፤ እንዲያውም ጠላት ሆነው ሊነሡ ይችላሉ። ʻእኔ ተታልያለሁ፤ ስለዚህ እምነቱ በጠቅላላው ሰዎችን ማታለያ ነው እንጂ እውነተኛ አይደለምʼ ሊሉ ሁሉ ይችላሉ። በመሆኑም፣ ይህን ከተሳሳተ መረዳት የመጣን ችግር የማስተካከል ትልቁ ኀላፊነት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነው እላለሁ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአእምሮ ሕመም ለደረሰባቸው ሰዎች የሚደረግ ጸሎትን በተመለከተ ልናገር የምፈልገው ነገር አለ። ይህም ጸሎቱ መልክ መያዝ ያለበት ይመስለኛል። ሁሉም ሰው ክፉ መንፈስ አለበት ተብሎ፣ ክፉ መንፈስ እንዲወጣ ሲገሠጽ፣ ሲጮኽበት፣ ብዙ ነገር ሲባል ይውላል፤ ነገር ግን ርግጠኛ ሳይኮን የመጣው ሰው ሁሉ አጋንንት እንዳለበት ተደርጎ መቆጠሩ ተገቢ አይደለም። ይህ ዐይነቱ ጸሎት በሚጸለይለት ሰው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ በራሱ በጣም ከባድ ነው።

ሌላው፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ዐይነት ሕመም ነው የፈወሰው። አሁን ግን እንደምናየው፣ እሱ መፈወስ የሚችለው ተደርጎ የሚወሰደው በክፉ መንፈስ የተያዙትን ሰዎች ብቻ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ደብዳቤ ይጽፉልኛል። ይህንን የሚያደርጉት የተቸገሩ ሰዎችን ወደ እኔ ሲልኩ ነው፤ “ዶ/ር አታላይ፤ ይህ ሰው እንዲህ ዐይነት ባሕርይ ታየበት፤ እኛም አጋንንት ያለበት መስሎን ጸለይንለት፤ ነገር ግን አሁን ያ አለመሆኑን ተረድተናል፤ ስለዚህ የአእምሮ ችግር ስለ ሆነ ወደ አንተ ልከነዋል” ይላሉ። ይሄ አባባል እኔን ያሳዝነኛል። እውነት ክርስቶስ የሚችለው አጋንንትን ማስወጣት ብቻ ነው እንዴ? እነዚህ ሰዎች እውነተኛ እምነት ያላቸው ከሆኑ፣ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ይዘው ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው። እውነተኛው የእግዚአብሔር መንፈስ ከመጣ የትኛውንም ዐይነት ሕመም ሊፈውስ ይችላል ብሎ ማመን ነው ያለባቸው እንጂ፣ ʻአጋንንት ከሆነ ክርስቶስ፤ አጋንንት ካልሆነ ደግሞ ዶ/ር አታላይʼ ማለት ያለባቸው አይመስለኝም።

ይህን ስል ሰዎች ወደ ሕክምና መምጣታቸው ትክክል አይደለም ለማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ወደ ሕክምና እንዳይሄዱም ሲከለክሉ፣ እንዲያውም አስረው ለብዙ ወራት ያለ ምንም መፍትሔ ሲያቆዩአቸው ይስተዋላል። መድኃኒቱን እየወሰዱ እኮ ሊጸለይላቸው ይችላል፤ ምንም የሚቃረን ነገር የለውም። እንዲያውም መድኃኒቱን ቢወስዱ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብላቸው የመረዳት አቅማቸውም የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ ተረጋግተው ለመስማት ጉልበት ያገኛሉ፤ በጸሎት ለመተባበርና አምኖ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብም ይችላሉ። ስለዚህ መድኃኒቱን እየወሰዱ፣ ዘለቄታ ላለውና እንከን ለሌለው ፈውስ መጸለይ ይገባል። ሕክምናው ከተጀመረ ጸሎቱ አይሠራም የሚባል ነገር የለም። እግዚአብሔር ርኅሩኅ አምላክ ነው።

  • ለሌላው አካላችን ጤንነት ሲባል በተወሰነ ጊዜ የጤንነት ምርመራ እንደሚደረግ ሁሉ፣ አንድ ሰው ለአእምሮ ጤናው ደኅንነት ሲል በየጊዜው ምርመራ ማድረግ ያስፈልገዋል? ወይስ ከቶውኑ አያስፈልገውም?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- የአእምሮ ጤንነትን በተመለከተ አንድ ሰው በተወሰነ የጊዜ እየመጣ ምርምራ ማድረግ አለበት የሚባል ነገር መኖሩን እኔ አላውቅም። ይሁን እንጂ፣ አንድ ሰው ከቀድሞ የተለየ ሆኖ ሲገኝ፤ ለምሳሌ በባሕርዩ የበለጠ ቁጡ እየሆነ ከመጣ፣ እንቅልፍ ካጣ፣ የሥራ ውጤታማነቱ ከቀድሞው በጣም እየቀነሰ ከመጣ፣ ከሰው ጋር ያለው መግባባት ከቀነሰ፣ እራሱን የመጠበቅና የመንከባከብ ዝንባሌው ከተቀየረ ወይም ደግሞ ውጥረት ሲኖርበትና ከሌላው ጊዜ የተለየ ስሜት ከተሰማው ባለሙያ ማማከሩ በጣም አስፈላጊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ከዚያ በተረፈ ግን እያንዳንዱ ሰው በዓመት ወይም በሁለት ዓመት የአእምሮውን ጤንነት እየሄደ ምርመራ በማድረግ ማጣራት አለበት የሚባል ነገር እስከ አሁን አልሰማሁም።

  • እንደ ሥነ አእምሮ ባለሙያነትዎ የወንጌላውያን አማኝ ማኅበረ ሰብ የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ዝንባሌና አካሄድ ምን ትርጕም ይሰጥዎታል?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- እንደ አማኝ ብለህ ብትጠይቀኝ ሳይሻለኝ አይቀርም መሰለኝ።በሁለቱም አቅጣጫ ሊያዩት ይችላሉ?

ፕሮፌሰር አታላይ፡- እሺ እንግዲያው፤ እኔ እንዳየሁት ከሆነ፣ በአማኙ ማኅበረ ሰብ እየተቀየረ ነው የምለው አመለካከት በአብዛኛው በምድራዊ ሥኬት ዙሪያ በጣም የሚያጠነጥን እየሆነ መጥቷል። ትምህርትም፣ ጸሎቱም፣ እምነቱም፣ ብዙው ነገር ከዚህ ጋር የተገናኘ ይመስላል። ጌታችንን በሚያከብር ሳይሆን፣ እራስን በማክበር፣ የእራስን ስም በጣም ከፍ ከፍ የማድረግ የውድድር ዘመን ሆኗል ብዬ አስባለሁ። እራስ ወዳድነትን ትቶና ሌላውን አስቀድሞ፣ ደግሞም ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን እውነትና አስተምህሮ ተረድቶ እራስን ለመግዛትና ለመምራት የሚደረግ ጥረት ብዙ አይታይም። አሁን ያለው ውድድር፣ አንዱ ከሌላው ተለይቶ እራሱን የትኩረት ማእከል የሚያደርግበትን መንገድ መፈለግ ላይ ነው። የእግዚአብሔርን ሐሳብና ፈቃድ አውቆና ለዛ ተገዝቶ፣ እሱን አክብሮ ለመኖር ያለው ትጋትም ሆነ አመለካከት ወይም አስተሳሰብ በጣም እየራቀን መጥቷል። ከዚህም የተነሣ፣ አማኝ ባልሆነው ማኅበረ ሰብ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው ጨውና ብርሃን ሆኖ የመመላለሱ ነገር አሁን እየደበዘዘ መጥቷል። የሚቀናበት ሕይወት ሊኖረን አልቻለም።

በመሆኑም፣ ብዙ ሰዎች ለእኛ ንቀት እና ክብር ያጣ አመለካከትና አስተያየት እንዲኖራቸው ሆኗል። በርግጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ባሕርይ እያነጸባርቅን ብንኖርም መነቀፋችን እንደማይቀር መጽሐፍ ቅዱሳችን ይናገራል። በዚህም መልኩ በአገራችን በእምነታቸው ምክንያት የተገደሉ፣ አካላቸውን ያጡ፣ ለብዙ ዓመታት በእስር ቤት ተጥለው ቆይተው የተፈቱ አሉ። ነገር ግን የአሁኑን ነቀፌታችን አሳሳቢ የሚያደርገው ከክርስቶስ መንገድ በተቃራኒው በመሄዳችን ምክንያት እየመጣብን ያለ መሆኑ ነው። በአንዳንድ ሰዎች ዘንድም አእምሯችንን እንደሳትን ተደረገን የመቆጠር ነገርም አለ። የአምልኳችን ሁኔታ በጣም ተቀይሯል፤ አካባቢን የሚረብሽ፣ የሌላውን ሰው ሰላም የሚነሣ፣ ስሌላው ግድ የሌለን፣ የሌላው ሰው መብት መጠበቅ እንዳለበት እንኳ ግንዛቤው የሌለን ሆነናል። ልክ የጌታችን ባሕርይ እንደ ሆነው ሁሉ፣ ሰዎችን አክብረን፣ ገበናቸውን ይዘን ልናገለግላቸው፣ መልካም ምሳሌ ልንሆናቸው አልቻልንም። ይህንን የሚያደርጉ ፈጽሞ የሉም እያልኩ አይደለም። በምግባራቸውም ሆነ በአጠቃላይ በሕይወት አካሄዳቸው ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ፣ በአብዛኞቻችን የሚታየው ሕይወት ከዚያ የራቀ ይመስላል። ስለዚህ ሰዎች ሌላ ስም ቢሰጡን የሚያስገርም አይሆንም።

ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

Share this article:

መሄድህን ቀጥል

ይህ የቴዎድሮስ ሲሳይ ጽሑፍ፣ “ዘወትር ሳትታክት መሄድህ፣ የምትጠብቀውን ለማግኘትህ ምስክር ላይሆን ይችላል፤ በአንጻሩ፣ የሚበልጠውን ስለ መፈለግህ እና ስለ መናፈቅህ ምኞትህን ያመለክታል። ይህም በሰማይ ዋጋ አለው።” ይላል፤ ወደ ቅዱሳን ኅብረት፣ ወደ እግዚአብሔር ጕባዔ መሄድ ለደከማቸው የምክር ቃል ባካፈለበት መልእክቱ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.