[the_ad_group id=”107″]

"አእምሯችን ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር በጣም የተቆራኘ ነው።"

  • ሕንጸት፡- አእምሮ፣ አንጎል፣ ጭንቅላት ስንል ምን ማለታችን ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- እንግዲህ አእምሮ በእንግሊዘኛው “mind” የምንለው ነው፤ አንጎል ደግሞ “brain” የምንለው ነገር ነው። ጭንቅላት በአጠቃላይ የሁለቱ ድምር ነው። ጭንቅላት ስንል ስለ አእምሮም እያወራን ሊሆን ይችላል፣ ስለ አንጎልም እያወራን ሊሆን ይችላል። አሁን የምንነጋገርበት ከሕመም ጋር በተያያዘ ያለውን ነው። “አንጎል” ስንል በራስ ቅላችን ውስጥ ያለ፣ ክብደቱ ወደ አንድ ኪሎ ግራም አካባቢ የሚመዝን፣ በጣም ለስላሳ የሆነ ሥጋ ነው። ይህ የሰውነታችን ክፍል ምናልባት ከጥርሳችን ቀጥሎ በጣም ጠንካራ በሆነ አጥንት የተከበበ ነው። ይህ አንጎል የምንለው አንድ አካል ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ አካሎች በአንድነት ተቀናብረው የሚሠሩበት እንደ ሲስተም ያለ የሰውነት ክፍል ነው። አካላችንን፣ ስሜታችንን እንዲሁም ሐሳባችንን ሳይቀር የሚቆጣጠር ነው። በአጭሩ በጣም ሰፊ ሥራ የሚሠራ ነው። ስንሞት ከሌላው ሰውነታችን ጋር አብሮ ይበሰብሳል።

አእምሮ በምንልበት ጊዜ ግን ከዛ የረቀቀ ነው። ‘እዚህ ጋ ነው’ ብለህ ምልክት የማታደርግበት ነው። ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ አንጎል የሰውነታችን ክፍል ሲሆን፣ አእምሮ ግን የነፍሳችን ክፍል ነው። በክርስትና እምነት እንደምናምነው ነፍስ ሟች አይደለችም፤ አንጎል የምንለው ግን እዚሁ የሚቀር ነው። ቀላሉ ማመሳሰያ መንገድ ኮምፒውተር ነው። ኮምፒውተር ሁለት አካላት አሉት፤ አንደኛው ሃርድ ዌር የሚባለው ክፍል ሲሆን፣ ይህም በዐይን የሚታየውና የሚዳሰሰው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሶፍት ዌር የሚባለው ሲሆን፣ ይህም በኮምፒውተር ውስጥ በተለያዩ ፕሮግራሞች በኩል የምናገኘው ነው። እነዚህ በኮሞፒውተሩ የፊት ገጽ (መስኮት) ላይ የምናያቸው እንጂ በእጃችን የምንነካቸው አይደሉም። አእምሮም እንደዚሁ ነው፤ ልክ እንደ ኮምፒውተሩ ከጀርባ ሆኖ ሁሉን የሚሠራው ነው።

  • ሕንጸት፡- የአእምሮ ሕመም ሲባል ምን ማለት ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- የአእምሮ ሕመም ስንል የአንጎል ወይም የአእምሮ ተግባር መታወክ ነው። የአእምሮ ሕመም መገለጫው ብዙ ነው። ለምሳሌ፣ አንደኛው የአእምሯችን ተግባር ስሜታችንን መቆጣጠር ነው። የስሜት መዋዠቅ ወይም የስሜት መውረድ ሲደርስብን (“ድባቴ” የምንለው ዐይነት ማለት ነው) የአእምሮ ተግባር ታውኳል ልንል እንችላለን። ሌላኛው የአእምሯችን ትልቁ ሥራ እውነታን ከውሸት መለየት ነው። እውነታን የማየት ችሎታዬ ሲዛባ ‘አእምሮዬ ታመመ’ ይባላል። በተለምዶ “እብደት” የሚባለው፣ አንድ ሰው እውነታን የማወቅ ችሎታው ሲጠፋበት ወይም የሌለ ድምፅ ሲሰማ፣ የሌለ ነገር ማየት ሲጀምር እና የመሳሰሉትን ሲያደርግ ነው። ይህም የአእምሮ መታመም ምልክት ይሆናል። ሌላው ደግሞ አንድ ሰው በሱስ ሲያዝ፣ የሚወስዳቸው ነገሮች የአንጎልን ኬሚካል ስለሚረብሹት የእንቅልፍ ወይም የስሜት መዛባት ይገጥመዋል። ለዚህ ነው ሱስ የአእምሮ ሕመም ነው የምንለው። ስለዚህ የአእምሮ ሕመም የምንለው የአእምሮን ወይም የአንጎልን ተግባር የሚያዛቡ ነገሮች ተፈጥረው ሲገኙ ነው።

  • ሕንጸት፡- ለአእምሮ ሕመም መንስኤ ናቸው የሚባሉት ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ምሕረት፡- የሚገርምህ ነገር አንጎላችን የሰውነታችን 3 ወይም 4 ከመቶ የሚሆን ክብደት እንኳን አይይዝም፤ ነገር ግን ከምንበላው ምግብ 25 ከመቶ የሚሆነውን ኀይል የሚወስደው እሱ ነው። ይሄ የሚያሳየን ምን ያህል ከባድ ሥራ እንደሚሠራ ነው። ለምሳሌ፣ አእምሯችን ስንተኛ አያርፍም፤ ሕልም ያልማል፤ በእንቅልፍ ጊዜ ቀን የሠራነውን ነገር ሁሉ ወደ ትዝታ ማኅደር ያከማቻል። ለዚህ ነው በቂ እንቅልፍ ስናጣ ነገሮችን መርሳት የምንጀምረው። ለማለት የተፈለገው፣ ከአእምሯችን ጋር የሚገናኙ ነገሮች ሁሉ አእምሯችንን የማበላሸት አቅም አላቸው። ለምሳሌ ሱስ የሚያመጡም ሆኑ ሱስ የማያመጡ ኬሚካሎች አእምሮ ላይ ተጽእኖ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሌላው፣ ሰው ካለው ሞራላዊ ዕሴት ውጪ ሲኖር በአእምሮ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ አለ፤ ይህም አንድ የሕመሙ መንስኤ ይሆናል ማለት ነው። እንደሚታወቀው ሰው አካላዊ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ነው።

ለሁለቱም ዓለማት እንደ አስተርጓሚ ሆኖ የሚሠራው ደግሞ አእምሮ በመሆኑ ምክንያት በመንፈሳዊው ዓለም ተጽእኖ ውስጥ ይኖራል፤ በበጎም ሆነ በመጥፎም ማለት ነው። ሌላው መንስኤ ኀዘን በትክክል ሳይያዝ ሲቀር፣ በጭንቅላት ላይ አካላዊ ጉዳት ሲደርስ፣ የተለያዩ የአእምሮ ቁስለቶች (ኢንፌክሽንስ) ሲከሰቱ (የማጅራት ገትር ሊሆን ይችላል) የአእምሮ ሕመም ሊመጣ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዘር የሚተላለፍም የአእምሮ ሕመም ሊኖር ይችላል። አስተዳደግ በበኩሉ ለአእምሮ ሕመም ሊዳርግ የሚችልበት አጋጣሚ አለ። በልጅነታቸው ከፍተኛ ጥቃት (ጾታዊም ይሁን ሥነ ልቦናዊ ወይም ደግሞ አካላዊ) የሚደረሰባቸው ሰዎች ለአእምሮ ሕመም ሊጋለጡ ይችላሉ። ሌላው ደግሞ የሰብእና ዕድገት አለ፤ ልክ አካላዊ ዕድገት እንዳለ ሁሉ። ሰብእና በተለያየ ምክንያት ስንኩል ሊሆን ይችላል፤ በአደጋ፣ በአስተዳደግ፣ በሌሎችም ምክንያቶች። እነዚህ ነገሮች የሰብእና መዛባት (personality disorder) ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንግዲህ እንደዚህ እያለን ብዙ ነገሮችን ልንዘረዝር እንችላለን።

  • ሕንጸት፡- ለአእምሮ ሕመም ዕርዳታ ሰጪ ሊሆኑ የሚችሉት ምን ዐይነት ሰዎች ናቸው?

ዶ/ር ምሕረት፡- የአእምሮ ሕክምና ወይም ደግሞ የምክር እገዛ በሙያ ደረጃ ባልተስፋፋበት አገር እነማን ናቸው ሕክምና ሊሰጡ የሚችሉት የሚለው ግራ አጋቢ ነው። እንግዲህ በሌላው ዓለም ስም ያላቸው፣ የተለያየ ደረጃና ድንበር ያላቸው ሙያዎች አሉ። በእኛ አገር ከአእምሮ ወይም ከሥነ ልቡና አንጻር ላሉ ችግሮች አጋዥ ተደርገው የሚቆጠሩና እንደ ዐዋቂ ሐኪም የምናያቸው የሃይማኖት ሰዎችን ወይም በዕድሜ የቀደሙ አዛውንቶችን ወይም ደግሞ የባህል ሐኪሞችን ነው። አንድ ሰው ድባቴ ውስጥ ቢገባ ወይም ግጭት ውስጥ ቢሆን ወይም ደግሞ የስሜት መረበሽ ቢገጥመው እነዚህ ሰዎች ናቸው በመጀመሪያ የሚያገኙት። በእኛ አገር ይህ ነገር ከፍተኛ ቦታ እንዳለው መርሳት የለብንም። ‘ልክ ነው፤ ልክ አይደለም፤ ምን ያህል ማድረግ ይችላሉ?’ የሚለው እንዳለ ሆኖ።

ከሙያ አንጻር ካየነው ግን ሕክምናም ይሁን ምክር ወይም የተለያዩ እገዛ ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ በአብዛኛው ከምእራቡ ዓለም ወይም ከዘመናዊ ሕክምና የተወረሱ ናቸው። አንደኛው፤ በሕክምና ሙያ ውስጥ አእምሮ ነክ ጉዳዮችን የሚያዩት ሳይካትሪስቶች ናቸው። ሳይካትሪስት ማለት “የአእምሮ ሐኪም” የሚለውን ነው የሚይዘው። አንዳንድ ሕመሞች መንስኤአቸው የነርቭ ከሆኑ (እንደ ማጅራት ገትር፣ የአንጎል ኢንፌክሽን) ኒውሮሎጂስቶችም ይሳተፋሉ። ሌላው እንግዲህ፣ ሥነ ልቡናዊ የሆኑ ማለትም የሜዲካል ጉዳይ የሌላቸው ከሆኑ ክሊኒካል ሳይኮሎጂ ወይም ደግሞ ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ላይ ያጠኑ ሰዎች በአእምሮ ችግሮች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን እገዛ ሊሰጡ ይችላሉ። ከሳይካትሪስት እና ሳይኮሎጂ ውጪ ሆኖ በተለያየ መንገድ የማማከር ሙያ የሚሠለጥኑ ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፓስቶራል ካውንስሊንግ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በሥነ መለኮት ት/ቤቶች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገና ፓስቶራል የሆነ የማማከር ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ። ሌላ እንግዲህ በቂ ሥልጠና ያልወሰዱ፣ ነገር ግን ሰዎችን ለመምከርና ለመርዳት ዝንባሌው ያላቸው ሌይ ካውንስለርስ ይባላሉ። በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች የሚሄዱት ወደ እነርሱ ጋር ነው፤ ብዙ ሥራም የሚሠሩት እነርሱ ናቸው።

  • ሕንጸት፡- አንድ በአእምሮ ሕመም የተያዘ ሰው የመዳን ዕድሉ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- ብዙ ዐይነት የአእምሮ ሕመሞች አሉ፤ እያንዳንዱ ሕመም ደግሞ የራሱ የሕመም መጠን አለው፤ እንዲሁም የታማሚው የአእምሮ ሕመሙን የመቋቋም አቅም አለ፤ ታማሚው ማግኘት የሚችለው ድጋፍ እና የመሳሰሉት በሕመሙ የመዳን ያለመዳን ዕድል ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ አለ። ሌላው ለችግሩ ትክክለኛውን ዕርዳታ ማግኘትም ወሳኝ ነው። መንፈሳዊ ለሆነው ችግር መንፈሳዊ የሆነ ዕርዳታ፣ አካላዊ ለሆነው ችግር አካላዊ ዕርዳታ፣ በአጠቃላይ ትክክለኛውን ዕርዳታ በትክክለኛው ጊዜ ማግኘት ውጤቱን ይወስናል። ስለዚህም ለሁሉም ዐይነት ሕመም ተመሳሳይ የሆነ ግምት መስጠት ያስቸግራል። እንደየችግሩ ነው ማየት የምንችለው።

  • ሕንጸት፡- በኢትዮጵያ የአእምሮ ሕመም ደረጃው የት ድረስ ነው? ቁጥሮችስ ምን ያሳያሉ? እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ?

ዶ/ር ምሕረት፡- አንዳንድ የአእምሮ ሕመም ዐይነቶች በየትኛውም ዓለም መጠናቸው ሳይጨምር ሳይቀንስ የሚሄድባቸው አጋጣሚ አለ። Schizophrenia የምንለው የአእምሮ መቋወስ (በተለምዶ “እብደት” የሚባለው) በብዙ አገር ተመሳሳይ የሆነ ቁጥር ነውያለው፤ከ0.5-1 ከመቶ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። እንደ ድባቴ፣ ጭንቀት፣ የሰብእና መዛባት፣ ሱስ ወይም ደግሞ ሕፃናት ላይ የሚታዩ የአእምሮ ዝግመት የሚባለው (autism) እና ሌሎችም ቁጥራቸው ይዋዥቃል። ለዚህም የከተሞች መስፋፋት ያመጡት የኑሮ ለውጥ ወይም ውጥረት ያመጣው እንደ ሆነ ይታመናል። ምክንያቱም አእምሮ ላይ ጫና ሲበዛ የአእምሮ መረበሽ ወይም መታወክ ይበዛል። በአጠቃላይ በእኛ አገር እንደ ድባቴ፣ ጭንቀት፣ የሰብእና መዛባት እና ሱስ እንደ ሕመም ስለማይታዩ ሕመሞቹ ያሉ አይመስልም። ይሁን እንጂ፣ የሕዝቡ ንቃት እያደገ ሲመጣና ሚዲያው ማውራት ሲጀምር ከቁጥጥር ውጪ የሆነ እስኪመስል ድረስ የበዛ ሆኖ ይታያል። ችግሩም በዝቶ ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ በአጠቃይ ለነገሩ ያለን ግንዛቤ እያደገ ሲመጣም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ብዙ የአእምሮ ሕመሞች የአማርኛ ስም የላቸውም፤ ይሄ የሚያሳየን እውቅና ያልተሰጣቸው መሆኑን ነው። በአጠቃላይ ግን በአገራችን በቂ ጥናት ስለመሠራቱ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የተወሰኑ ጥናቶች አሉ ነገር ግን ሁሉን ይወክላሉ ወይ የሚለው አስቻጋሪ ነው። ስለዚህ ቁጥሩን ማወቅ ራሱ አስቸጋሪ ነው።

  • ሕንጸት፡- የአእምሮ ሕመምና መንፈሳዊው ዓለም ወይም ልምምዶችን የማያያዝ ዝንባሌ ይታያል፤ በርግጥ ተያያዥነት አላቸው?

ዶ/ር ምሕረት፡- እንግዲህ እንደምትጠይቀው ባለሙያ ንጽረተ ዓለም መልሱም ሊለያይ ይችላል። ʻመንፈሳዊ ዓለም የለም፤ እግዚአብሔር የለም’ የሚል ባለሙያ ብትጠይቅ፣ ʻልማዳዊ እምነት ነው’ ብሎ ነው የሚመልስልህ። ይህንን ከግምት ከተን፣ እኔ እንደ ክርስቲያንነቴ፣ መንፈሳዊ ዓለም አለ ብዬ አምናለሁ። መንፈሳዊ ዓለም ደግሞ አንድ ዐይነት አይደለም፤ ክፉ ዓለም አለ፤ በጎ አለ፤ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት አሉ፤ ደግሞ ከእሱ በታች የሆነ ነገር ግን ከሰው ልጆች በላይ የሆነ ክፉ የመናፍስት ዓለም አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ያንን በግልጽ ያስቀምጣል። እንግዲህ እነዚህ መንፈሳዊ ኀይላት/አካላት ከሰው ጋር የሚጋሩት ነገር ባለ አእምሮ መሆናቸው ነው። እኛም ከሌላው ፍጥረት የምንለየው፣ መንፈሳዊ ስለሆንን ብቻ ሳይሆን ባለ አእምሮ ስለሆንም ጭምር ነው። እግዚአብሔር አእምሮ ስላለው እንደ ባለ አእምሮ ነው የሚያወራን። ከአእምሮ ጋር ደግሞ ፈቃድና ስሜት አብሮ አለ። ክፉውም መንፈሳዊ ዓለም ባለ አእምሮ ነው። ዘፍጥረት ላይ ሄደህ እባቡ ከሔዋን ጋር ሲያወራ በአእምሮ እንደተጠቀመ ታያለህ። ለዚህ ነው ጳውሎስ የሔዋንንም ሐሳብ እንዳበላሸ ሁሉ የእኛንም እንዳያበላሽ የሚመክረው። ለምሳሌ የዳቢሎስን ሽንገላ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሽንገላ አእምሮ ላይ የሚሠራ ነገር ነው። ስለዚህ አእምሯችን ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር በጣም የተቆራኘ ነው። እኛ ፍላጎቱ እንኳ ባይኖረን፣ መንፈሳዊው ዓለም በአእምሯችን ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። በ2ኛ ቆሮንቶስ ላይም አእምሮን እንደሚማርክ ይናገራል። ትልቅ ትግል አእምሮን የማረከ ሰውየውን ወይም ሴቲየዋን ማርኳል ማለት ነው።

እዚህ ላይ ሁለት ችግር ያለባቸው አመለካከቶች አሉ፤ አንደኛው መንፈሳዊውን ነገር ከአእምሮ ጋር ያለ ማዛመድ ችግር ነው። ʻመንፈሳዊው ዓለም አእምሮዬ ላይ ምንም ዐይነት ተጽእኖ የለውም፤ ሰዎች በጣም እያመናፈሱ ነው’ የሚል ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አእምሯዊ የሆነውን ነገር ሁሉ መንፈሳዊ የማድረግ ዝንባሌ አለ። ይህንን ያልኩበት ምክንያት አእምሯችን ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ያን ያህል ዝምድና ቢኖረውም፣ በአካላዊው ዓለም ወይም ተፈጥሯዊ በሆነ ምክንያት የመጠቃት ዕድልም ያለው መሆኑንም ለማስገንዘበ ነው። በመሆኑም አእምሯችን በሁለቱም ዓለማት በእኩል ደረጃ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ስለዚህ የትኛው አካላዊ ነው የትኛው መንፈሳዊ ነው የሚለው መታወቅ አለበት። መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ስትክድ በጣም ብዙ ነገር ነው እንደሌለ የምታስበው። አንተ የለም ስላልክ የለም ማለት አይደለም።

  • ሕንጸት፡- የአአምሮ ሕመምን ከእርኩስ መንፈስ ተጽዕኖ ጋር አያይዞ የማየት አመለካከት አለ፤ ለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ታሪኮች እንደ አስረጅ ይቀርባሉ። ለምሳሌ ሳኦል እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ አጋንንት ያስወጣለት ብቻውን ይኖር የነበረው ሰው።

ዶ/ር ምሕረት፡- ሳኦልን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ክፉ መናፍስት ያሰቃዩት እንደ ነበረ ይናገራል። ይሁን እንጂ ምናልባት ከሳኦል በላይ ኢዮብ ተሰቃይቷል። ኢዮብ በብዙ ስቃይ ውስጥ ነበር፤ ድባቴ ውስጥ እንደ ነበረ ትረዳለህ። ይሁን እንጂ ኢዮብ አጋንንት አልነበረበትም። እንደውም መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጻድቅ ሰው እንደ ነበረ ነው የሚናገረው። ዳንኤል ለተወሰኑ ሳምንታት ያህል በጣም ከፍተኛ በሆነ ሐዘን (ድባቴ) ውስጥ እንደ ነበረ ይነግረናል። እነ ጳውሎስም በጣም ከባድ የሆነ ሐዘን ውስጥ ያልፉ እንደ ነበር እናያለን። እንግዲህ የሳኦልን ስቃይ ብቻ አይተን፣ ስቃይን ሁሉ አጋንንት የሚፈጥሩት ነው እንዳንል የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ማየት ይኖርብናል። የሰዎች የአእምሮና የስሜት ስቃይ ሁልጊዜ አጋንንት ውስጣቸው ስላለ ብቻ አይደለም። መንፈሳዊ በሆነው ዕይታ እንኳን ብዙ መንስኤዎች አሉ። ሆኖም ግን አጋንንት እንደዚህ ዐይነት ሁኔታ አይፈጥሩም ወይ ስትል፣ የሳኦል ታሪክ በጣም ይገልጻል። እንደውም ሲዘመርለት ወይም መንፈሳዊ ነገር ሲሰጠው ሲረጋጋ ያሳይሃል። ይሄ መንፈሳዊ መፍትሔ እንዳለው የሚያሳይ ነው።

  • ሕንጸት፡- አሁን ደግሞ ወደ ሌላ የአእምሮ ሕመም እንለፍና ድባቴ ምንድን ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- እንደሚታወቀው ሁላችንም ስሜት አለን። በማንኛውም ጊዜ የስሜት ከፍታና ዝቅታ ሊከሰት ይችላል። ሁላችንም በአንድ የስሜት ደረጃ አንቆይም፤ ስሜታችን ዝቅ ይላል – ʻአዘንኩ’ ወይም ʻደበረኝ’ እንላለን፤ ስሜታችን ከፍ ይላል – ʻደስ አለኝ’ እንላለን። በጣም ከፍ ብሎ ከታየ ʻወፈፍ አደረገው’ እንላለን፤ ነገሩ ከተለመደው ደስታ በላይ ከሆነ። በሌላ አንጻር ስሜቱ በጣም ዝቅ ብሎ፣ ወርዶ አስተሳሰቡን፣ ኑሮውን፣ ግንኙነቱን፣ ሥራውን፣ የሕይወት ዕይታውን ሁሉ ካጨለመበት ከተለመደው ድብርት በጣም የከፋ ይሆናል። ለምሳሌ ዛሬ ደብሮኝ ከሆነ ነገ ደኅና ነው የምሆነው። ይሁን እንጂ ይህ ዐይነቱ ስሜት ከሁለት ሳምንት በላይ ከሆነ ወይም ጊዜው ከረዘመ፣ ውሳኔዬ ላይ ተጽእኖ ካሳደረ፣ የሕይወት ዕይታዬን፣ ዋጋ የምሰጠውን ነገር ሁሉ ላይ ጉዳት ካስከተለ ያ ሕመም ነው። ስለዚህ ድባቴ ማለት ከቁጥጥር ውጪ የሆነና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የስሜት ዝቅታ ማለት ነው።

  • ሕንጸት፡- አንዳንድ ሰዎች ከተለመደው ውጪ በሆነ መንፈሳዊ ልምምድ ውስጥ ይገቡና እንግዳ ነገር ሲያደርጉ ይታያል፤ ለዚህም የተለያየ ምክንያት ሲሰጡ ይሰማሉ። ለምሳሌ መንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ውስጥ ነኝ የሚል ወይም ደግሞ ባገኙት “ልዩ መገለጥ” እየተመላለሱ እንዳለ ሊናገሩ ይችላሉ። በእንዲህ ዐይነት ልምምድ ውስጥ ባለ እና የአእምሮ ሕመምተኛ በሆነ ሰው መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት ምንድን ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- ይህንን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎቹ የሚሉትና የሚያደርጉት ነገር በእግዚአብሔር ቃል ሲፈተሽ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነገር ነው ቀዳሚው ርምጃ መሆን ያለበት። ቀጥሎ ሕመም ነው ወይስ ስሕተት ነው የሚለውን ነገር ነው የምናየው። ብዙ ጊዜ ግን አንድ ነገር የአእምሮ ሕመም ነው ለማለት፣ ግለ ሰቡ እንደ አንድ አእምሮ እንዳለው ሰው ከሌሎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ ሠርቶ መኖር መቻላቸው፣ የስሜታቸው ሁኔታ፣ ራሳቸውን የመግዛት ሁኔታና ሊገመት (predictable) በሚችል መንገድ የመኖር ሁኔታ እንዲሁም ቀድሞ ከምናውቀው ማንነታቸው በተለየ አኗኗራቸው ተዛብቶ ሌላ ሰው ከእነርሱ ጋር መኖር ሲያቅተው ሕመም ልንለው እንችላልን። አንድ ሰው በሩን ዘግቶ ሥራ ባይሠራ፣ የግል ንጽሕናውን ባይጠብቅ ወይም ደግሞ የሰዎችን መብት (privacy) ባያከብር፣ እየጮኸ ቢረብሽ እና የመሳሰሉትን ቢያደርግ ስም ይኑረውም አይኑረውም ሕመም ማለት እሱ ነው። እንግዲህ ይህንን ሕመም የአእምሮ ሕመም ነው ወይስ መናፍስታዊ ተጽእኖ ነው የሚለው መለየት ያስፈልጋል። ለዚህም ሁለት ነገር ያስፈልጋል። የአንድን ሰው ባሕርይ ብቻ አይቶ ሕመም ነው ማለት ስሕተት ላይ ሊጥል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስም ላይ የምናያቸው አጋንንታዊ የሆኑ ነገሮች በባሕርይ የአእምሮ ሕመም ነው የሚመስሉት። ወይ የሚጥል በሽታ ይመስላሉ፣ ወይ ዕብደት ይመስላሉ፣ ወይ ድባቴ ይመስላሉ። የመጀመሪያው ጥያቄ ʻመንፈሳዊ መሆኑን የምናውቀው እንዴት ነው?’ የሚለው ነው። መንፈሳዊ መሆኑን የምናውቀው፣ በእግዚአብሔር መንፈስና በቃሉ ዕርዳታ ነው የሚታወቀው። የተለየ የመለየት ሥጦታ ያላቸው ሰዎች ደግሞ በዚህ ላይ ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው። ማንም ሰው ተነሥቶ የማይመቸውን ባሕርይ ʻይሄ አጋንንት ነው’ ካለ በሕክምናና በምክር ልንረዳቸው የምንችላቸውን ሰዎች ባልሆነ ምክንያት የባሰ እንዲታመሙና እንደውም ለአጋንንት እንዲጋለጡ ልናደርጋቸው እንችላለን። ምክንያቱም አእምሯቸው በዚያን ሰዓት ሽፋን ይፈልጋል፤ እንደ ፈረሰ አጥር ስለሆነ። አንዳንዴ ደግሞ በመንፈሳዊው ወይም በጸሎት መረዳት ያለባቸውንና ነጻ መውጣት የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች አይተን ʻይህ የአእምሮ በሽታ ነው፤ ወደ ሕክምና ውሰዱት’ ማለት የአእምሮ ሕክምና የሌለውን ዕርዳታ በመድኃኒት የሰዎቹን ሁኔታ ልንቆጣጠር እንችላለን፤ ነገር ግን ውስጥ ያለውን ችግር ልንፈታው አንችልም።

  • ሕንጸት፡- ጥቂት የማይባሉ ክርስቲያኖች፣ የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች (psychiatrist) እና የሥነ ልቡና ባለሙያዎች (psychologist) የሚሰጡት ምክር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆኑት ዕሴቶች (values) ጋር ላይስማሙ ይችላሉ ሲሉ ይደመጣል። በርግጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የማማከር አገልግሎትና የሕክምና ሳይንሱ ስሙም ናቸው ማለት ይቻላል? ካልሆነስ፣ አንድ ሕይወቱን በመጽሐፍ ቅዱሳዊው መርሖዎች ላይ መምራት የሚፈልግ ሰው ከተጠቀሱት ባለሙያዎች የሚያገኘውን ምክር እንዴት አጣጥሞ መሄድ ይችላል?

ዶ/ር ምሕረት፡- ምን ማለት ነው መሰለህ፤ ለምሳሌ አንድ ሴት ባልተፈለገ ሁኔታ ብታረግዝና ክርስቲያን የሆነ የማሕፀን ሐኪም ጋ ብትሄድ፣ ʻልጁ ይወለድ’ ነው የሚላት፤ በክርስትና ዕሴት (value) ውርጃ ልክ ስላልሆነ። ውስጥ ያለው ሰው ነው፤ የመጣበት መንገድ ስሕተት ሊሆን ይችላል፤ የሚወጣበት መንገድ ደግሞ የመጀመሪያውን ስሕተት አያስተካክለውም። በሌላ አንጻር ደግሞ ውርጃ ኀጢአት አይደለም የሚልና ክርስቲያናዊ ዕሴት ውስጥ የማይኖር ሐኪም ደግሞ ʻይውጣ’ ሊል ይችላል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ተመሳሳይ ችሎታ ያላቸው የተለያዩ ሰዎች (ሐኪሞች) ጋ ሲሄድ የተለያየ መልክ ነው የሚያገኘው ማለት ነው። ይሄ ለአእምሮ ሕክምና ብቻ አይደለም ለማለት ነው። በአእምሮ ሕክምና ከዛ የበለጠ ደግሞ የሥነ ልቦና ባለሙያውም ይሁን የአእምሮ ሐኪሙ የግል እምነት፣ መንፈሳዊ ዕይታ ችግሩን የሚያይበትን መንገድ ይወስነዋል። ችግሩን የምናይበት መንገድ ደግሞ መፍትሔውን የምናይበትን መንገድ ይወስነዋል።

ስለዚህ አንድ ሰው ድባቴ ውስጥ ገብቶ ወደ ሒኪም ቢሄድና መንፈሳዊውን ነገር ሁሉ እንደሌለ በሚያስብ ሰው ሲታይ፣ ሌላ የአስተሳሰብ (value) ግጭት ይፈጠራል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ያ ሐኪም ʻይሄ የእንቅልፍ መድኃኒት ይረዳሃልና ውሰድ’ ቢል፣ ያኛው ሰውዬ እግዚሓርን የማያምን ወይም ደግሞ የእኔን እምነት የማይቀበል ነው ብሎ የእንቅልፍ መድኃኒቱን አለመውሰዱ አይጠቅመውም። ሰውየው የሚያይበትን ሙሉ ዕይታ ግን ላልቀበለው እችላለሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ የእኛን እምነት የሚከተሉ በቂ የሆኑ ሐኪሞች በሌሉበት ሁኔታ አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ አልጠቀምም ማለት ሞኝነት ይመስለኛል። አገልግሎቱን መርጦ መጠቀም ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ ያ ሰው የሚሰጠን ምክር/አገልግሎት የተሻለ ሁሉ ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ አንድ ክርስቲያን የሆነ ግን በቂ ዕውቀቱ የሌለው ሐኪም ደግሞ፣ የምናምነውን ሁሉ አምኖ፣ ነገር ግን የሚሰጠን ምክር ጥቅም ላይኖረው ይችላል። እዚህ ላይ ማየት ያለብን መሠረታዊው ነገር፣ የሕይወትና የመንፈሳዊ ዓለም ዕይታህ አንድ ነገር ሲሆን፣ በችግሩ ላይ ያለህ ሥልጠናና እውቀት ሌላ ነገር መሆኑን ነው። ሁለቱም ያለው ሰው ካለ እሰየው ነው።

  • ሕንጸት፡- ስለዚህ የሐኪሙን ወይም የአማካሪውን ምክር/ትእዛዝ እንዳለመፈጸም አይቆጠረም ማለት ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- እንዳልኩህ አንዳንድ ነገሮች ክርስትና ዕሴት ጋር የሚጋጨ ሊሆን ይችላል። ያንን አድርግ ስትባል የአንተ የእምነት አስተሳሰብ (value) ነው የሚመጣው፤ መፍትሔ ብቻ አይደለም። ሐኪሙ ወይም አማካሪው፣ ’አጋንንት ብሎ ነገር የለምʻ ካለ መወሰን አለብህ። መድኃኒቴን ይዤ እሄዳለሁ፤ ሌላውን ነገር ግን አልሰማውም የሚል ዐይነት ብስለት ካለህ ትችላለህ። ምንም ችግር የለውም። ልትከራከረውም እኮ ትችላለህ።

  • ሕንጸት፡- እኛ አገር ብዙ ሰዎች የሐኪምን ቃል ሙሉ ለሙሉ እንደ ወረደ የመቀበል ዝንባሌ ያለ ይመስለኛል። ስለዚህ፣ የታካሚው ነጻነት የት ድረስ ነው የሚለውን ግለጽ ለማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው።

ዶ/ር ምሕረት፡- ልክ ነው። ሐኪሞች ችሎታ አላቸው እምነት አላቸው። የምንሄደው እምነታቸውን ለመካፈል ሳይሆን፣ ችሎታቸውን ለመካፈል ነው። ብዙ ሰዎች ችሎታውንም እምነቱንም የመቀበል ግዴታ ያለበት ይመስለዋል።

  • ሕንጸት፡- በቤተ ክርስቲያን ደረጃም ሆነ በተለያዩ መልኮች መንፈሳዊ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች የአእምሮ ሕመምን በተመለከተ ሊከተሉት የሚገባው አካሄድ ምን መሆን አለበት ትላለህ?

ዶ/ር ምሕረት፡- አንድ ሰው ጥሩ አማካሪ እንዲሆን የሚያስችሉት ሦስት ነገሮች አሉ። አንደኛ ችሎታ ነው። እንደማንኛውም ነገር በችሎታ የሚሠራ ነገር ስለሆነ ችሎታ ያስፈልጋል። ሁለተኛ ደግሞ፣ ሥጦታ አለ፤ መንፈሳዊ ሥጦታ ሊሆን ይችላል ወይም ተፈጥሯዊ ሥጦታ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ያለ ሥጦታችን የቱንም ያህል ብንማር ውጤታማ ላንሆን እንችላለን። ሦስተኛው ነገር ደግሞ ዕውቀት ነው። ለምሳሌ አንድ በድባቴ ችግር ውስጥ ያለን ሰው ለመርዳት ስለ ድባቴ ያለኝ ዕወቀት መሠረታዊ ነው። የቱንም ያህል ሥጣታና ችሎታ ቢኖረኝ፣ ዕወቀቴ በጉዳዩ ላይ ውስን ከሆነ ያንን ሰው መርዳት አልችልም።

ብዙ ሰው ዕወቀቱን አያሳድግም፤ ስለዚህ ዝም ብሎ የግምት ምክር ነው የሚሰጠው። ዕውቀት የሌለው ነገር ሁልጊዜ ስሕተት ነው። ዕውቀት በሌለን ነገር ላይ አላውቅም ማለት መማር አለብን። አላውቅም ብሎ መቆም ሳይሆን ግን የምንችለውን ያህል ለማወቅ መጣር፣ ዕውቀቱ የት እንዳለ መመርመር ያስፈልጋል። በልምድ የሚያማክሩ ሰዎች ትልቁ ማወቅ ያለባቸው ነገር፣ የሚችሉትንና የማይችሉትን ለይተው ማወቅ ነው። ሁሉንም የመሞከር ግዴታ የለባቸውም። ሥጦታ ስላለህ ሁሉንም አትመክርም፤ ሁሉንምም አትፈታም። አንዳንድ ሰዎች ጸልየው ወደ ቤት ይልካሉ። ጸልዮ ወደ ቤተ መላክ ማማከር ማለት አይደለም። መጸለይ ሊያስፈልግ ይችላል። ግን ዋናው ሥራው አንድ ሰው የገባበትን ግራ መጋባት አስተካክለህ፣ ቀኝና ግራውን አሳይተህ፣ የመሰወን አቅም እንዲኖረው አድርገህ (አንተ አትወስንለትም)፣ ምርጫውን ራሱ አድርጎ እንዲሄድ የማድረግ ችሎታ ነው።

ወደ ችሎታም ስንመጣ፣ ችሎታ ማለት ከሰው ጋ ማውራት፣ ሰውን ማዳመጥ፣ ምስጢርን መጠበቅ፣ መጠየቅ፣ ማቆም ሲኖርብህ ማቆምና የመሳሰሉት ናቸው። በዚህ አገልግሎት ላይ ያሉ ሰዎች በዚህ ካላደጉ ከሚሰጡት ጥቅም ጉዳቱ ሊበዛ ይችላል የሚለው ነው ምክሬ።

  • ሕንጸት፡- በጣም አመሰግናለሁ!

የተዘነጋው አሁን

ሁላችን በሐሳብ ባህር ላይ ቀዛፊዎች ነን። ቀዘፋው ደግሞ በትላንት እና በነገ የሐሳብ ማዕበል የሚናጥ ነው። ከትላንት ለመማርም ሆነ ነገን የተሳካ ለማድረግ አሁንን መኖር መጀመር እንዳለብን ይህ የተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) መጣጥፍ መንገድ ይጠቁማል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕሙማን ምቹ ቦታ ናት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም”

እውቁ የሥነ አእምሮ ሐኪምና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም አሳሳቢነቱ ጨምሯል ስለሚባለው የአእምሮ ሕመም ከሕንጸት መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ፣ ችግሩን በተመለከተ በወንጌላውያን አማኞች መካከል ስላለው የአመለካከት ክፍተትና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ርምጃዎች ሚክያስ በላይ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.