
[the_ad_group id=”107″]
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ በአሁኑ ጊዜ የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ዓለም አቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ (ዳይሬክተር) ሲሆኑ፣ ለረጅም ዓመታት በመንግሥት ሥራ በተለያዩ ኀላፊነት ደረጃዎች ሲሠሩ የቆዩ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ንጉሤ ጋዜጠኞችንና የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎችን በማሠልጠን እንዲሁም በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ከኮሙኒኬሽን እና ከመሪነት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚታወቁ ከመሆኑም በላይ፣ በአሜሪካን አገር የሚገኘው የሃጋይ ዓለም አቀፍ አድቫንስድ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ፋኩልቲ አባል በመሆን ያገልግላሉ። ሚክያስ በላይ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡን በሚመለከት ስለ ኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም፣ አብያተ ክርስቲያናት ከኅብረተ ሰቡ ጋር ስላላቸው መስተጋብር እንዲሁም በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያንን አመራር ጋር ሊያያዙ በሚችሉ ጭብጦች ዙሪያ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- በዚህ አቅጣጫ በተለያዩ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ መስኮች ከኅብረተ ሰቡ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ወይም ለመቀራረብ ሲያከናውኑ የሚታዩ አንዳንድ ጥረቶች መኖራቸው የሚያጠራጥር ባይሆንም፣ አጥጋቢ ሆኖ የሚታይ የጐላ የግንኙነት መርሓ ግብር አለ ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ይመስለኛል። በዚህ አቅጣጫ ብዙ ይቀረናል። እንኳን በኅብረተ ሰቡ መካከል ገብቶ የመንቀሳቀስና ተሳትፎ የማድረግ ጉዳይ ይቅርና፣ እርስ በርስ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል የመቀራረቡ፣ የመተዋወቁ፣ የጠነከረ ኅብረት የመፍጠሩና አብሮ የመሥራቱ ጉዳይ ገና የሚቀረው ሆኖ ይታያል። በአሁኑ ጊዜ በተጨባጭ በተግባር ተገልጦ ከሚታይ ኅብረትና አንድነት ይልቅ በግል የመደራጀት ትኩረትና የውድድር መንፈስ የሚያይል ይመስላል።
ምንጊዜም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ስኬታማነታቸውን ከሚለኩባቸው መንገዶች አንዱና ዋንኛው በኅብረተ ሰቡ ውስጥ ካላቸው የቀረበና የጠለቀ ግንኙነት አኳያ መሆኑ ግንዛቤ ማግኘት አለበት። እኔ እንደምረዳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ʻየዓለም ብርሃን እና ጨውʼ የመሆን ተቀዳሚ ትርጉሙ ይኸው ነው። እያንዳንዱ ቤተ እምነት አጥቢያዎቹ በሚገኙበት ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ ከተማና በአገር አቀፍ ደረጃም ቤተ ክርስቲያን ከኅብረተ ሰቡ ማለትም ከወጣቱ፣ ከሴቱ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙነት፣ በኅብረተ ሰቡ ሕይወት፣ በአካባቢው ዕድገትና ልማት ላይ ሊያደርገው የሚገባው ተሳትፎና ሊያመጣ ስለሚገባው በጐ ተጽእኖ በማሰብና የጉዳዮችን ቅደም ተከተል ለማውጣት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
እንደሚታወቀው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በንጉሡም ጊዜ ሆነ በደርግ ጊዜ ኅልውና አልነበራቸውም፤ ያሳለፉት የስደትና የመከራ ዘመን ነበር። ስለሆነም ከኅብረተ ሰቡ ጋር ተቀራርቦ የመሥራት ባህል ሊያዳብሩ አልቻሉም። ነጻነቱ ውስን እንደ ነበረ ተሳትፎውም ውስን ሆኖ መቆየቱ ግልጽ ነው። ይህ ሁኔታ አሁን በአብዛኛው ተለውጦአል። ዛሬ የነጻነት ነፋስ በመንፈስ ላይ ይገኛል። እምነትን ያለ ፍርሃት መተግበር ተችሎአል። ከዚህ የተነሣ ይመስለኛል ያለፉት ሃያ ዓመታት ቤተ እምነቶች በአብዛኛው ራስን በማደራጀትና ነጻነቱን በማጣጣም ላይ ብቻ ያተኮረ ተግባር እንጂ ኅብረተሰ ቡን ትኩረት ያደረገ አገልግሎት መፈጸም አልተቻለም።
በዚህ በኩል ውጤታማ መሆን የሚቻለው በመጀመሪያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እርስ በርስ የበለጠ በመቀራረብ ኅብረትን በተግባር ማጠናከር ሲችሉ ነው። በተግባር የተገለጸ የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነት ሲኖር ከኅብረተ ሰቡ ጋር የበለጠ መቀራረብ፣ ግንኙነት መፍጠርና ፍሬያማ የሆነ ተሳትፎ ማድረግ የሚቻል ይሆናል። ኅብረተ ሰቡን በመቅረብ አገራዊ አጀንዳም ነድፎ በግልም በጋራም መንቀሳቀስ ይቻላል። ይህ ወደ ኅብረተ ሰቡ ዘልቆ የመግባት ጉዳይ እያንዳንዱ ቤተ እምነትና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አጀንዳ ይዘው ትኩረት ሰጥተው የበለጠ የሚወያዩበት፣ ጉዳዮችን ለይቶ በማውጣት የተግባር መርሓ ግብር አዘጋጅተው ሊንቀሳቀሱበት የሚባ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ ክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ በአገሩ ዕድገትና ልማት፣ በአጠቃላይ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖረው ፋይዳ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ፍትሕን፣ እኩልነትንና ጽድቅን ከሚፃረሩ የኀጢአት ሥራዎች በስተቀር ቤተ ክርስቲያን በአገር ጉዳይ የማትሳተፍበት ምንም ዐይነት ተግባር የለም። ዛሬ በአገራችን የአመራር ሂደት ቁልፍ ቦታ ይዘው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ቁጥር ቀላል ግምት የማይሰጠው ነው። በፖለቲካ ሥርዐቱ ውስጥ ኅሊናቸውን ንፁሕ አድርገው እግዚአብሔርን በመፍራት የድርሻቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙ በከፍተኛ የመንግስሥት ኀላፊነት ሥራ ላይ የተሠማሩ በርካታ ክርስቲያኖችም መኖራቸው እሙን ነው። ይህን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው በድፍረትና በመሰጠት እግዚአብሔርንም አገራቸውንም ለማገልገል ፈቃደኛ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል። እነዚህ ወገኖች ለእውነት፣ ለፍትሕና ለመልካም አስተዳደር ይቆማሉ፣ ሙስናንና አድልዎን በመቃወም ይሠራሉ የሚል እምነት አለኝ። ሌሎችም ተመሳሳይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሊበረታቱና በጸሎት ሊታገዙ ይገባል።
ዛሬ በሁሉም የልማት ዘርፍ በከፍተኛ ባለሙያነት፣ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ መምህርነት የተሰማሩ መሃንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ወዘተ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። በከፍተኛ ችሎታቸው የሚጠቀሱ፣ እግዚአብሔርንም የሚፈሩና አገራቸውን የሚወዱ ቅን ልቦና ያላቸው፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አባል የሆኑ ምሁራን በሁሉም ክልሎችና በበርካታ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በቢዝነሱም ዓለም በተለያዩ የግል ሥራዎች በመሳተፍ ላይ የሚገኙ፣ በኢንቬስትመንት መስክም ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ራሳቸውንም አገራቸውንም በመጥቀም ላይ ያሉ ይገኙባቸዋል።
ይህ የሚደነቅ ቢሆንም፣ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዛሬም በውስጣቸው በተለያዩ የአገር ግንባታ መስክ አስተዋጽኦ ለማድረግ ከሚችሉትና በርካታ ቁጥር ካላቸው ምዕመናን አንጻር እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ እምነትን በተመለከተ ከተገኘው ሰፊ ነጻነት አኳያ ተሳትፏቸውን ማስፋትና ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል። እዚህ ላይ መታወስ የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ወይም ክርስቲያኑ ኅብረተ ሰብ በየጊዜው በነበሩ ሥርዐቶች፣ በተለይም በንጉሡና በደርግ ጊዜ ከደረሰባቸው ስደትና እንግልት አኳያ ስለ አገርና ስለ መንግሥት ይዞት እንዲቆይ የተደረገው አስተሳሰብ የተዛባ ነበር ለማለት ይቻላል። ፖለቲካውን በጭፍን የመጥላትና ስለ አገርም ሊኖር የሚገባ በጐ ስሜት አልፎ አልፎ መቀዝቀዝና ከመንግሥት አስተዳደር ጋርም መሥራት ኀጢአት ነው የሚል አስተምህሮ አስተሳሰቡ ሚዛናዊ እንዳይሆን ተጽእኖ አድርጐበት ቆይቶአል። አሁንም ከነበረው ሁኔታ የተነሣ መንግሥትና ፖለቲካ ጨለማ ሆኖ የሚታየው ሕዝበ ክርስቲያን ቁጥር ቀላል አይደለም። ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ ይህን ለመለወጥ ወይም ለማስተካከል በተቀናጀ መልኩ ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ነው ለማለት ይቻላል። ክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ በዚህ አቅጣጫ ተገቢውን ምክርና ትምህርት እንዲያገኝ የአብያተ ክርስቲያናትን ትኩረት ይሻል።
ክርስቲያኑ ዛሬ በችሎታውና በልምዱ፣ በድፍረትና በቅንነት ከእምነቱና ለእግዚአብሄር ካለው ታማኝነት ሳይላቀቅ ሀገሩን በሠፊው ሊያገለግልና ወገኑንም የበለጠ ሊጠቅም የሚችልባቸው መንገዶች ሰፊ ናቸው። ሌላው ይህን በተመለከተ ያለው ችግር አብዛኛው በአመራር ላይ የሚኙት የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና አስተማሪዎች ራሳቸው በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው ግንዛቤ ወይም አመለካከት የጠበበ ወይም የተዛባ መሆኑ ነው። ስለሆነም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናኖቻቸው ሀገራቸውን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በአመለካከትና በአስተሳሰብም ወደኋላ ሳይቀሩ ጊዜውን በመዋጀት በሀገራቸው ሁለንተናዊ ልማትና ግንባታ የድርሻቸውን የበለጠ ማከናወን እንዲችሉ በሀሳብ መርዳትና ማበረታታት አንዱ አጀንዳ አድርገው መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል የሚል አስተያየት አለኝ።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- ማኅበራዊ ፍትሕና እኩልነት የአንድ አገር ሕዝብ አብሮና ተደጋግፎ የመኖር ዋስትና እንዲሁም የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች ናቸው። በአንድ አገር ሰላምን በዘለቄታው ማስፈን፣ ልማትንም ማጠንከርና ማፋጠን የሚቻለው ፍትሕና እኩልነት በሰፈነበት ሥርዐት ውስጥ ብቻ ነው። ዴሞክራሲ የምንለው ኅብረተ ሰቡ በፍትሕና በእኩልነት መሠረት ላይ ቆሞ ያለ ፍርሃትና ስጋት ምርጫና ተሳትፎ ማድረግ ሲችል ነው። ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አንዱ ተልእኮ ነው። ቤተ ክርስትያን ራስዋ በሰላም መኖርና እምነትዋንም በአግባቡ መለማመድ የምትችለው ፍትሕና እኩልነትን የሚያስቀድም አስተዳደር ሲኖር ነው። ፍትሕና እኩልነት በሌለባቸው ሥርዐቶች ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን ምን ዐይነት ፈተና እንደነበረባቸው ብዙዎቻችን ምስክሮች ነን። ስለሆነም አብያተ ክርስቲያናት ምእመኖቻቸውን የፍትሕንና እኩልነትን ዋጋና ጠቀሜታ ማሳወቅ ማስተማር ይገባቸዋል። ለሰው ልጆች ማኅበራዊ ፍትሕንና እኩልነትን በሚያመጡ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ምእመናኑ አስፈላጊውን ተሳትፎ ማድረግና ራሳቸውንም ወገንንም መርዳትና መጥቀም እንደሚገባቸው ማበረታታት ይገባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን እንዲያውም በማናቸውም ፍትሕና እኩልነትን በሚመለከቱ አገራዊ ጉዳዮች ቀዳሚ ሆና መገኘት አለባት። አገርንና ሕዝብን በሚጠቅም የማኅበራዊ ፍትሕ ሥራም ላይ ምዕመኑ ችሎታውንና ልምዱን አቀናጅቶ ራሱን ሳያገል ተሳትፎ እንዲያደርግም ምክር ሊሰጠው ይገባል። ዛሬም በዚህ አቅጣጫ ተሳትፎ የሚያደርጉ መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ ይህ የበለጠ ግንዛቤ አግኝቶ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይገመታል።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መገናኛ ብዙኀንን በመጠቀም ውጤታማ ናቸው ወይ? የሚለውን ከመመለስ አስቀድሞ ለመሆኑ አብያተ ክርስቲያናት የሚዲያውን ኀይልና ጠቀሜታ ተገንዝበው በአግባቡ መጠቀም ችለዋል ወይ? የሚለውን መመለስ ተገቢ ይመስለኛል። መገናኛ ብዙኀን ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት ለግንዛቤ ማስፋትና የባሕርይ ለውጥ ለማምጣት ከመጠቀም ባሻገር፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋት ጠቃሚነት ያላቸው ዐይነተኛ መሣሪያ መሆናቸው ከታወቀ ወይም ግንዛቤ ካገኘ ውሎ አድሯል። ይህንንም ቀደም ብለው የተረዱ ግለ ሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት ለረዥም ጊዜ ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል። መገናኛ ብዙኀን የምስራቹን ቃል በሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ ለማድረስ የሚያስችሉና እስከ አሁን ምትክ ያልተገኘላቸው መሣሪያ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። መገናኛ ብዙኀን ዛሬ ታላቁን ተልእኮ ለማከናወን፣ በሕዝቦች መካከል ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን ለማጠንከርና መቀራረብንና መግባባትን ለማምጣት የሚያግዙ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ትኩረት ሰጥተው፣ ገንዘብና የሰው ኀይል መድበው በአግባቡ የሚጠቀሙባቸው አብያተ ክርስቲያናት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በአገራችን የሚታየው በአብያተ ክርስቲያናት መገናኛ ብዙኀንን በንቃት የመጠቀም ሁኔታ ዛሬ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት የምናገኝባቸውና የምንባረክባቸው የክርስቲያን ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችና አንዳንድ መጽሔቶች እንዳሉ ሁሉ፣ ትምህርታቸው የተበረዘና አደናጋሪ፣ በአብዛኛው ስሜታዊነት የሚታይባቸውና አወዛጋቢ ሆነው ይታያሉ። አንዳንዶቹ ይልቁንም የዋኾችንና ዝቅተኛ እውቀት ያላቸውን በቀላሉ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚመሩ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ የሚጠቀሙበትን የሚዲያ ባሕርይ አለመረዳትና ጥንቃቄና እውቀት ካልታከለበት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በውል ያለመገንዘብ ችግር አለባቸው። እንደነዚህ ዐይነቱንም ሥነ ምግባርንና የቃሉን እውነት የጠበቀ ሥራ እንዲሠሩና ሕዝቡ የሚያስፈልገውንም እያጠኑ እንዲያቀርቡ፣ በተጨማሪም ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር መሥራት እንዲችሉ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።
እውነቱን ለመናገር በዚህ አቅጣጫ የሚታየው የአብያተ ክርስቲያናት ተሳትፎ እምብዛም ነው ወይም ደካማ ነው ቢባል ስሕተት አይመስለኝም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን አለን (ሦስትና አራት ሚሊዮንና ከዛም በላይ) የሚሉ ቤተ እምነቶች እንኳን ኅብረተ ሰቡን ለማስተማር ቀርቶ የራሳቸውን ምእመናን እንኳን በአግባቡ እርስ በርሱ እንዲቀራረብ ለማስተማር የሚረዳ ሙያዊ አስተዋጽኦ ተደርጐበት የሚዘጋጅ ቀጣይነት ያለው መጽሔት ወይም የሚዲያ ሥራ የላቸውም። ይህ ገጽታ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስትነጻጸር በጣም ኋላ ቀር ያደርጋታል።
ሚዲያው ኅብረተ ሰቡን ለማስተማር፣ በጐ ተጽአእኖ ለማምጣት ክርስቲያኑን ማኅበረ ሰብ ለማቀራረብና በክርስትና ሕይወቱ ዕድገት ለማምጣት የሚረዳ ዐይነተኛ መሣሪያ ነው። መገናኛ ብዙኅን በቤተ ክርስቲያን መሪዎችና በምእመኑ መካከል የሐሳብ መራራቅና ግጭት እንዳይኖር፣ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል፣ ዛሬ በአሳሳቢ ሁኔታ እየሰፋ የመጣውን የአስተምህሮት ግድፈት ችግር ለማጥበብ፣ በክርስቲያኑ መካከል የጋራ አጀንዳ አዘጋጅቶ ለመወያየት፣ ለመስማማትና በተግባር ለመንቀሳቀስ የሚረዳ መሣሪያ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ተገቢውን ግንዛቤ ያገኘ መስሎ አይታይም። በያለበት በርካታ ባለሙያዎች መኖራቸው መታወቅም ዕቅድና ዝግጅት ተደርጐ ከሥራው ጋር እንዲገናኙ አልተደረጉም። በዚህ ረገድ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እያከናወኑ ከሚታዩት ይልቅ አንዳንድ አማኝ ግለ ሰቦች ወይም ድርጅቶች በየግላቸው ለማድረግ የሚሞክሩት ጥረት (ይህ የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም) ጐልቶ የሚታይና ሊበረታታ የሚገባው ይመስለኛል።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- ከላይ እንደገለጽኩት በመጀመሪያ በኅትመትም ሆነ በብሮድካስት ዘርፍ በአብያተ ክርስቲያናት ሲከናወን የሚታይ የጐላ ተሳትፎ የለም። በጥያቄው እንደተጠቀሰው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትም ጥቂቶቹ ሲገመገሙ ʻበአብዛኛው መርሑ የሚጠይቀውን የሙያ ሥነ ምግባር ተከትለው የሚሠሩ፣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት የሚያንፀባርቁ ናቸው ወይ?ʼ የሚለው ጉዳይ በእርግጥም ውይይት የሚያሻው ዐቢይ ነገር ነው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው እነሱም ባደረጉት ጥረት በብሮድካስትም ሆነ በኅትመት ሚዲያ አገልግሎቱን የጀመሩትንና ለመጀመርም ጥረት የሚያደርጉትን ሁሉ ʻእግዚአብሔር ይባርካቸውʼ ማለት ተገቢ ይመስለኛል። ዛሬ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አኳያ፣ በተለይም ደግሞ በትንሹ ወደ ሃያ ሚሊዮን ከሚሆነው የወንጌላውያን አማኞች ቁጥር አኳያ ያሉት የሚዲያ አገልግሎት ጨርሶ በቂ አይደሉም። ዛሬም በርካታ የሚዲያ አገልግሎቶች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነው። ሕዝቡም በሚዲያ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን አብዝቶ እንደሚፈልግ በርካታ ምልክቶች ይጠቁማሉ።
ʻሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባርና የእግዚአብሔርን የቃል እውነት በተመለከተ እንዴት ይታያሉ?ʼ ለተባለው በርካታ ችግሮች መኖራቸው የማይካድ ነው። ምንም እንኳን በቅን መንፈስ የክርስቲያኑን ማኅበረ ሰብ በመልካም ትምህርት ለማገልገል፣ በሚቻል ሁሉ ለሕዝብ የሚጥምና የሚጠቅም መሠረታዊ ጉዳይ ላይ በመጻፍና ፕሮግራም በማዘጋጀት ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ግለ ሰቦችና ተቋማት ቢኖሩም፣ በአጠቃላይ የክርስቲያን ሚዲያዎች ሲታዩና ተግባራቸው ሲገመገምም አብዛኛዎቹ አንባቢውንም ሆነ ተመልካቹን የማይመጥኑ፣ በቂ ጥናት ተደርጐባቸው የማይዘጋጁ፣ እውነትና ተጨባጭነት ሳይኖራቸው አየር ለመሙላት ብቻ የሚቀርቡ፣ ከንቱ ውዳሴ የሚያበዙና በይዞታቸውም የማይስቡ፣ አንዳንድ ጊዜም መረጃዎቻቸው የተዛቡ፣ ለማን እንደተዘጋጁ/እንደተጻፉ፣ ለምን እንደተዘጋጁ/እንደተጻፉ፣ ለመረዳት የሚያዳግቱ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን የአንድነት መንፈስ የሚያደፈርሱ፣ በቅራኔዎች ላይ የሚያተኩሩ፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ሰብእናና ክብር የሚነኩና የሚያሳፍሩ ሆነው ይታያሉ።
በአንዳንድ መንፈሳዊ ቴሌቪዥን የምናያቸውም ሆነ በአንዳንድ መጽሄሔቶችም ላይ ተጽፈው የምናነባቸውን ʻየእኛ ናቸውʼ ብሎ ለማውራት ቀርቶ አንዳንዴ ለማየትም ያሸማቅቃሉ። አንዳንዶቹ ለእግዚአብሔር ክብር የሚዘጋጁ ሳይሆን ለንግድና ለትርፍ ወይም የራስን ዝና በማስተዋወቅ ለመጠቀም ታስበው የተቋቋሙ መሆናቸውን ሥራቸው ይመሰክራል። የሚታይባቸው የሥነ ምግባር ጉድለት ብቻ ሳይሆን የችሎታ ማነስም ጭምር መሆኑ በግልጽ ይታያል። በተለይ አንዳንድ መጽሔቶች የሚጽፉባቸውን አርዕስተ ጉዳዮች በውል ያልተረዱ፣ ማኅበረ ሰቡ የሚያስፈልገው ምን እንደ ሆነ የማይገነዘቡ፣ አሉባልታን ተከትለው የሚዘግቡ ሆነው ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የተወሰኑ ሐሳቦችን ብቻ የሚያራምዱ ጠባብና ስሜታዊነት የሞላቸው ናቸው ቢባል ትክክለኛው መገለጫ ነው። ብዕር ስለያዙ ብቻ መጻፍ፣ ከማይክሮፎን ጀርባ ስለተቀመጡ ብቻ መናገር የሚችሉና ሁሉን የሚያውቁ የሚመስላቸው ጥቂቶች አይደሉም። ለሁሉም ተግባር ሥርዐትና ሕግ እንዲሁም ሥነ ምግባር ያለው መሆኑን ይዘነጋሉ። በተለይ በእግዚአብሔር ስም የሚሠራ ሥራ በረከት ብቻ ሳይሆን ራስንም ሌሎችንም የማሳሳት አደጋም እንዳለውና ጥንቃቄና እውነተኛነት መለያዎቹ መሆናቸውን ይስታሉ። የከበረውን ብርቱ ነገር እንደ ልጅ ጨዋታ መቀለጃ ያደርጋሉ። “ቅዱሳን ተንቀጥቅጠው የሚገቡበትን አዳራሽ ሰነፎች ኳስ ይጫወቱበታል” እንደሚባለው ነው።
ለማንኛውም ተግባር እውቀትና ልምድ መሠረቱ መሆኑንም አይገነዘቡም። ብዙዎቹ አዘጋጆች ከመነሻው ሙያውም ስለሌላቸው ወይም ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ከመነሻው ተምረውና አውቀው ስላልተነሡ፣ ከቅናት በስተቀር ልምዱም ስለሌላቸው አንዳንድ የሚያሳዝኑና የሚያስደነግጡ ሁኔታዎችን እናነባለን፣ በክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም እናያለን። ከእነዚህ ከአንዳንዶቹ ጋር አልፎ አልፎ ውይይቶች ተካሂደዋል። በአንዳንዶቹ ላይ እኔም ተሳትፌአለሁ። ምክርና ትምህርትም ለመስጠት ተሞክሮአል። ይሁን እንጂ ውጤቱ እንደታሰበው አልሆነም። ከሙያው ግድፈት በተጨማሪ የሥነ መለኮት እውቀት እውርነት ሲደመር ሚዲያውን አደናጋሪ፣ ሲያልፍም አሳፋሪና አሳሳች ትምህርቶች የሚስተጋባበት መድረክ አድርጐታል። ሚዲያውን በባለቤትነት ከሚመሩት ወይም ሥራውን የሚያስተባብሩት አንዳንዶቹ ʻገንዘብ መክፈል በሚችሉ አየር ጊዜውን መሙላትʼ በሚለው የተሳሳተ የአሠራር ዘይቤአቸው፣ በኅትመትም የተሰማሩት ʻይህ ምዕመኑን ያንጻል ወይ? ያስተምራል ወይ? ለሕይወት ያለው ጠቃሚነት ምንድነው? የእግዚአብሔርንስ እውነት የተከተለ ነው ወይ?ʼ የሚሉት ጥያቄዎች ሳያሳስባቸው ይልቁንም ʻበገበያ ላይ ሲቀርብ ገንዘብ ያስገኛል ወይ? ነገር ይጭራል ወይ?ʼ በሚል ደካማ አስተሳሰብ እየተመሩ ሕዝቡን በስሕተት ነፋስ ከወዲያ ወዲህ ያዞሩታል።
የእግዚአብሔርን ስም ይዞ የሚነሣ ማንኛውም የሚዲያ አገልግሎት በመጀመሪያ ማክበር የሚገባው እግዚአብሔርንና ቃሉን ነው። የስብከታችንም ሆነ ሚዲያ ላይ የመውጣታችን ዋንኛ ምክንያት ራሳችንን ለማስተዋወቅ ከሆነ የከበረውን የእግዚአብሔር ዓላማ ይስታል። የእግዚአብሔርን ሕዝብ አንድነትና ፍቅር ያደፈርሳል። በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚሠሩት ብዙዎቹ የሚዲያ ተቋማት በአግባቡ የተቀረጸ የኤዲቶሪያል መመሪያም ሆነ ሥራውን በበላይነት የሚከታተልና ተገቢውን ምክር የሚሰጥ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸው አባላት የሚገኙበት አማካሪ ቦርድም የላቸውም። በመካከላቸው የሚገኙት ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ለሚጽፉባቸውም ጉዳይ በቂ ግንዛቤ የላቸውም። ለሕዝብ በሚቀርብ ዐቢይ ጉዳይ ላይ ሲጽፉ አንዳንዶች ጭንቀት አይታይባቸውም። እነዚህ ችግሮች ትኩረት ተሰጥቶአቸው መስተካከልና የሚዲያ ሥራዎቻችን የሙያ ሥነ ምግባር ተከትለው መጓዝ ይኖርባቸዋል የሚል ሐሳብ አለኝ።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- ስላልተጠቀምንባቸው የወንጌል አገልግሎት ዕድሎች ለመግለጽ የሚቻለው በመጀመሪያ የነበሩት ዕድሎች ምን እንደ ነበሩ ለመጠቆም ስንችል ነው። ያለፉት 23 ዓመታት ከእምነት ነጻነት አኳያ ለወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የተለዩ ዓመታት ነበሩ ቢባል የተሳሳተ አይመስለኝም። የእምነት ነጻነቱና ለወንጌል አገልግሎት የተከፈቱት በሮች ወሰን አልነበራቸውም። በአገራችን ሰፊ የወንጌል አገልግሎት ዕድሎችን ተመልክተናል። ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ በተጨማሪ ከቀበሌ አዳራሽ አንሥቶ እስከ ስታዲየም ድረስ፣ የሲኒማና የቲያትር ቤቶችን ጨምሮ ለወንጌል ሥራ የመጠቀም ዕድሉ ሰፊ ነበረ። ለወንጌል ሥርጭት የሚረዱ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችንና የተለያዩ ጽሑፎችን አሳትሞ ለማሰራጨትም ነጻነቱ ገደብ አልነበረውም። ቀድሞ ቤት ተከራይቶ፣ ፈቃድ አግኝቶ ወንጌል ማስተማር በማይቻልበት አገር ዛሬ መንግሥት አልፎ ተርፎ ለሃይማኖት ድርጅቶች ከፍተኛ እውቅና ከመስጠት ባሻገር መሬት እስከማደል የደረሰበት ጊዜ ውስጥ ደርሰናል። ይህን ዕድል በመጠቀም በርካታ የእምነት ድርጅቶች ተቋቁመዋል፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸውን ሕንፃና ቢሮ ለመሥራት ችለዋል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ተመሥርተዋል። ሌሎችም መልካም ጅምሮችና ክንዋኔዎች መኖራቸው ግልጽ ነው። ይህን ዕድል በሚቻል መጠን ለመጠቀም ጥረት ያደረጉ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
የዚያኑ ያህል ያልተጠቀምንባቸው ብዙ ዕድሎች አሉ። ጥያቄውም በዚህ ላይ የሚያተኩር ይመስለኛል። ወንጌላውያን አብያተ ክርቲያናት የተከፈተውን በር የሚመጥን ወይም የተገኘውን ዕድል ያህል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር ለማለት አይቻልም። በተጨማሪም ሊታይ የሚገባውን ያህል ዕድገትና ሊሠራ የሚገባውን ያህል የወንጌል ስርጭት ሥራ ተከናውኗል ማለት ይቸግራል። በአብዛኛው የወንጌል ሥራው በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ወይም ዙሪያ የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ሽብሸባ እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመድረስ የሚያስችል አጥጋቢ የሆነ የወንጌል ስርጭት ስልት ተቀይሶ ሲከናወን የሚታይ እንቅስቃሴ አይደለም። ሕዝቡን በአግባቡ ከመድረስ ባሻገር ምእመኑንም ደቀ መዝሙር የማድረግና በቃሉ እውነት የማሳደግ ተግባርም ደካማ ነው። ዕድሉን በሚቻል መጠን ለመጠቀም ይቻል ዘንድ ወጣቱንና የተማረውን ወገን በቤተ ክርክቲያን አገልግሎትና በመሪነት የማሳተፉም ጉዞ ትኩረት ያልተሰጠው ወይም በጣም አዝጋሚ ሆኖ ቆይቶአል ማለት ይችላል።
ሌላው ከላይም እንደጠቆምኩት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዕድገት ለምእመኑ የአእምሮ መታደስና ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችለውን ሚዲያውን አልተጠቀምንበትም። ምእመኑን በመንፈሳዊ ሕይወቱና ግንዛቤውን ለማስፋት በአያሌው ሊረዱ የሚችሉትን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ያገኘነውን ዕድል ያህል ጨርሶ አልተጠቀምንባቸውም። ዕድሎችን በዕቀድና በፕሮግራም ለመጠቀም ደግሞ በመጀመሪያ ዕድሎችን ማየት መቻል እንዲሁም የዕድሎችን ዋጋና ጠቀሜታ የሚገነዘብ አመራር ይጠይቃል። ዕድሎችን ከመጠቀም አኳያ በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት የሚታየው አንዱ አሳዛኝ ሁኔታ ይህ ሚዲያውን እምብዛም ትኩረት ሰጥተን መጠቀም ያለመቻላችን እንቆቅልሽ ነው። ከይቅርታ ጋር አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከእሑድ ጠዋት ስብከት በስተቀር አገልግሎት ያለ አይመስላቸውም። ዕድሉን በአግባቡ ለመጠቀም ካልተቻሉባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋናው ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ቤተ እምነት ድረስ የሚታየው የአመራር ችሎታና ልምድ ማነስ እንዲሁም ነገሮችን አስፍቶና አርቆ የማየት ችግር መሆኑን ብዙዎች አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ስለሆነም ጠባብነትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ሥራ አስፍቶ ለማየት የአለመቻል ሁኔታ ተግባራችንን አንካሳ አድርጐታል። በተጨማሪም በአብያተ ክርስቲያናት፣ በተለይም በአመራር ላይ በሚገኙ አገልጋዮች መካከል የሚያጋጥሙ የአመለካከትና የግንዛቤ ልዩነትንና ግጭትን አስወግዶ ለመሥራት የሚያስችል ክኅሎትና ልምድ መታጣትም ዕድሉን የሚጠበቅብንን ያህል እንዳንጠቀም እንቅፋት ሆኖአል። በአንዳንድ ቤተ እምነቶችና አጥቢያዎች ጭምር እነዚህን ችግሮችና ያሉትን ሁኔታዎች በግልጽነት፣ በድፍረትና በአእምሮ ብስለት አውጥቶ ለመወያየት አለመቻልና በአንዳንዶች ዘንድ ፈቃደኝነት አለመታየቱም ብዙ ዕድሎች እንዲያልፉን ያደረገ ይመስላል። ዛሬም ቢሆን ልንጠቀምባቸው የምንችል በርካታ ዕድሎች አሉን። አብያተ ክርስቲያናት ነቅተው አመቺ ሁኔታዎችን ማየት፣ ትኩረት ሰጥቶ መወያየት፣ ስልት ቀይሶ መንቀሳቀስ፣ በተለይ ወጣቱንና ጠቃሚ ሐሳብ ሊያመነጭ የሚችለውን የተማረ የሰው ኀይል ሳይፈሩ ማሳተፍ አስፈላጊ ይሆናል። ምንጊዜም የእግዚአብሔር ሕዝብ በአግባቡ ሊሳተፍ ያልቻለበት አገልግሎት ፍሬያማና ዘላቂ ሊሆን አይችልም።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በትክክለኛ መንገድ ላይ ናቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ነገሮችን ማየትና ማገናዘብ ይጠይቃል። በእርግጥ በዚህ ላይ እኔ ያደረኩት ቀጥተኛ የሆነ ጥናት የለም። ይሁን እንጂ ከሁኔታዎች ጋር አብሬ ያለሁ በመሆኑ፣ በተለያዩ መንገዶችም ከብዙዎች ጋር የማደርገው የአገልግሎት ተሳትፎና ግንኙነት ስላለ የምናገረው ከእነዚህ የሚመነጨ የግል አስተያየቴን ነው። ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ከላይም በጠቆምኩአቸው በጐ ጐኖችና ሌሎችም በጐ ተግባራት የተነሣ በትክክለኛው መንገድ ለመሄድ ሰፊ ጥረት ሲያደርጉ ዐያለሁ። ይህ የሚበረታታና ድጋፍ ሊሰጠው የሚገባ አካሄድ ነው። አንዳንዶች ያሉባቸውን የአመራር ችግሮች ለመቅረፍና የምእመኑን መንፈሳዊ ዕድገት ለማፋጠን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችንና ኮሌጆችን በማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በአመራር ስልት ላይም ትምህርት የሚሰጡ አሉ። አንዳንዶች ምዕመኑ በተለይም ወጣቱ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖረው የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማሉ። ቅርንጫፎችን በመክፈት፣ አገልጋዮችን በአመራር ስልት በማሰልጠን ይንቀሳቀሳሉ። የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ኅብረተ ሰቡን በወንጌል አገልግሎት ለመድረስ የምእመኑንም የሕይወት ዕድገት ለማምጣት የሚሠሩም አሉ። ሌሎችም በጐ ገጽታዎች መኖራቸው አያጠያይቅም። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ትክክለኛ አቅጣጫ ነው።
በእርግጥም መስተካከል የሚገባቸው ትክክለኛ ያልሆኑ አካሄዶችም አሉ። የመጀመሪያው ጉዳይ አብያተ ክርስቲያናት በአመራር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለይቶ የማወቅና የመፍታት አቅም ማጣት ነው። አልፎ አልፎ ከሚታዩት ችግሮች አንዱ በአመራር ላይ በሚገኙትና በምእመኑ መካከል የቅርብ ግንኙነትና መተዋወቅ አለመኖር ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ግልጽ የሆነ ተከታታይ ውይይትና የምክክር ተሳትፎ የማይታይ በመሆኑ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች መሪዎች በራሳቸው እምነት ከማጣት፣ ሊነሡ ይችላሉ ብለው ከሚፈሩአቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ስጋትና በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ከሚታዩ አንዳንድ የታወቁ ችግሮችና ግልጽነት ከጐደለው አስተዳደር ጭንቀትና ፍርሃት የተነሣ ምእመኑን ከተሳትፎ ማግለል ወይም ብቃት የሌላቸውንና ገመናቸውን የሚሸፍኑላቸውን ለአመራር መምረጥ የለባቸውም። ምእመኑ የቤተ ክርስትያን አመራር፣ የገንዘብ አጠቃቀም፣ የአገልጋዮች አመራረጥና ስምሪትን፣ የወንጌል አገልግሎት ዕቅድን በተመለከተ ግልጽና እውነተኛ ውይይት እንዲደረግና ተሳትፎ እንዲኖረው ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ሥራውን ያበለጠ ያግዛል። ይሁን እንጂ ይህን የሚያስተናግዱ የቤተ ክርስቲያን መድረኮች እጅግ ጠባብ ናቸው።
ከዚህ በላይ ደግሞ በአንዳንድ ቤተ እምነቶችና መንፈሳዊ ድርጅቶች ሁሉንም የሚወስኑትና አመራሩን የሚቆጣጠሩት የተወሰኑ ወይም ጥቂት መሪዎች ናቸው። ከአንዳንድ ሁኔታዎች መታዘብ የሚቻለው መሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚያስጠጓቸው ወይም ለአመራር እንዲመረጡ የሚያደርጉት የሚፈልጓቸውንና በሐሳባቸው የሚስማሙላቸውን ሰዎች ይመስላል። በአንዳንድ ሥፍራዎች አገልግሎቱን ለማስተባበር የሚመረጡትም የሚቋቋሙት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለይስሙላና የጥቂት ሰዎችን ዓላማ የሚያስፈጽሙና በሁሉም ነገር “አሜን” ሲሉ የሚታዩ ሆነው ይገኛሉ። ይህ ዐይነት አካሄድ እንኳን በመንፈሳዊ አሠራር በምድራዊውም አሠራር ተቀባይነት የሌለው፣ ይልቁንም የተወገዘ ነው። ምእመኑም በብዙ ሥፍራ የተሳትፎው ልክ ማጨብጨብና የቀረበለትን መባረክ ብቻ መሆን የለበትም። ነገሩ የሚያሳስባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደሚናገሩት አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶች የቤተ ሰብ ወይም የግል ንብረቶች ተደርገው የተዋቀሩ ወይም የሚካሄዱ ናቸው። ሌላው ችግር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለማወቅ የበላይ ሲሆን፣ ልምድ ሲታጣ ከዚህም አልፎ አንዳንዶች በጓደኝነትና በዘር መነጽር ነገሮችን ማየት የሚጀምሩ ሲሆን ትልቅ አደጋ አለው። በተጨማሪም በአንዳንድ ሥፍራዎች ብርሃናችንን እንዲከለል ያደረገው ጨለማ ማለትም የእርስ በእርስ ግጭትና መለያየት፣ የአስተምህሮታችን መዘበራረቅና ሲብስም ግራ አጋቢ መሆን ነው። ይህ ደግሞ ከትክክለኛው መንገድና ገጽታ እንዳያርቀን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል። በአጠቃላይ ከበጐ ገጽታችን ጐን የሚታየውን የተሳሳተና አሳሳቢ አካሄድ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- የስብስቡ አባላት በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥር ከሚገኙ የተለያዩ ቤተ እምነቶች፣ የሥነ መለኮት ትምህርት ኮሌጆችና በሌሎችም መንፈሳዊ አገልግሎቶችና ተቋማት በኀላፊነት፣ በአስተባባሪነት፣ በመሪነት፣ በአስተማሪነት፣ በደራሲነት፣ የተሰማሩና እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ በአገልግሎታቸው የሚታወቁ መሪዎች ጭምር ያሉበት ነው። የስብስቡ ዋና ዓላማ ዛሬ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታዩትን አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮችን የበለጠ በማጥናትና ምንጫቸውን በማወቅ እንዲሁም የሚሆነውን መፍትሔ አብሮ በመፈለግና በመጸለይ አብያተ ክርስቲያናትንና መሪዎችን መደገፍ፣ መምከርና መመካከር እንዲቻል ታስቦ የተቋቋመ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ትኩረትን የሚሹ መንፈሳዊ ሕይወት ዕድገትን፣ አስተምህሮንና አመራርን የሚመለከቱ ጉልሕ ችግሮች ይታያሉ። እነዚህ ችግሮች አልፎ አልፎ የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ እያጠፉና የእግዚአብሔርንም ስም እያሰደቡ ነው። የእግዚአብሔር ነገር ግድ የሚለው ሁሉ እነዚህን ሁኔታዎች ዝም ብሎ ሊመለከት አይችልም፡፡ ዛሬ የግል ክርስትና ሕይወት ልዕልና ከደቀ መዝሙርነት ሕይወት እየራቀ፣ ከእውነትና ከቅድስና መንገድ እየወጣ፣ ተአማኒነትንም እያጣ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። የሥነ ምግባር ጉድለት፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሕይወት መታጣት አሳሳቢ እየሆነ መጥቶአል። ክርስቲያኑ ዓለምን በወንጌል ከመለወጥ ይልቅ በዓለም እየተለወጠ የመሄድ ዝንባሌ ጐልቶ እየታየበት መምጣት ብዙዎችን የሚያስጨንቅ ሆኗል። ሌላው ከዚህ ጋር አሳሳቢ ጉዳይ በተለያዩ ሁኔታዎች የአስተምህሮዎችን ከእውነት እየራቀ የመሄዱ ሁኔታ ነው። የእግዚአብሔርን እውነትን በአግባቡ ሳይረዱ ወይም ሳይማሩ የወንጌል አስተማሪዎች፣ መጋቢዎችና ነቢያት አድርገው የሾሙና የቀቡ በወንጌል አገልግሎት ላይ አደጋ እያስከተሉ ነው። እውነቱን ለመረዳት ማይችሉ የዋኾች በርካታ ሰዎች በእነዚህ የሐሰት መገለጥ ትምህርትና ትንቢት እየተጠለፉ ሲወሰዱ ይታያል።
ይህ ሁኔታ እውነቱን ለተረዱና ለሚያውቁ ሁሉ እጅግ አስጨናቂና አሳሳቢ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች እውነትን እየገፋ የሚሄደው ይህ የሐሰት ትምህርት ጨለማ ለብዙዎች ግራ መጋባትን ፈጥሮ ይገኛል። በርካታ አብያተ ክርስቲያናት አደገኛ በሆነ መንታ መንገድ ላይ የሚገኙ ይመስላል። አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን ሄደው ለመስማት የሚናፍቁት የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ተከፍቶ መነበብን ሳይሆን፣ አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት ተነሥታ ትንቢት ሲነገር መስማት ነው። ሰዎች ለሕይወታቸው፣ ለኑሮአቸውና ለሚገጥሙአቸው ችግሮች ሁሉ ምሪት የሚፈልጉት ከቃሉ ሳይሆን ከተወሰኑ ሰዎች መገለጥ ነው። ብዙውን ጊዜ በአንዳንድ ሥፍራ ከፍተኛ ጭብጨባና ምስጋና የሚሰማው በቃሉ ልዕልና ለተገለጠ እውነት ሳይሆን በትንቢት ስም ለሚነገር ያልሆነ መገለጥ ነው። ዛሬ ከምንጊዜውም ይልቅ እውነተኛ አስተማሪዎችና ለቃሉ ታማኝ የሆኑ መሪዎች የሚፈለጉበት ጊዜ ሆኗል። አንዳንድ መሪዎችም እውነትን ቢረዱም ከሰዎች ፍርሃትና ይሉኝታ የተነሣ፣ ሲያልፍም የእንጀራ ጉዳይ ይሆንና በግልጽና በድፍረት ለመናገርና ለማስተማር አይፈልጉም።
ይህ የተጠቀሰው ስብስብ ወይም ኮሚቴ ትኩረት ሰጥቶ የሚያጠናው በዚህ አቅጣጫ ጭምር ነው። ሌላው ሦስተኛው ትኩረት ሰጥተን የምንወያይበት በአመራር ላይ ስለሚታዩ አንዳንድ ግድፈቶች ነው። በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለሚታዩት የሕይወትም ሆነ የአስተምህሮ ጉድለቶች አንዱ ምንጭ የትክክለኛ አመራርና መንፈሳዊነት ዕጦት ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች እንደሚታየው መሪዎች የሚታገሉትና የሚጋደሉት ለእግዚአብሔር ክብርና ሥራ መሆኑ ቀርቶ ለአገልግሎታቸውና ለቦታቸው ሆኖ መታየቱ ብዙዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኖአል። መሪዎች ለኑሮአቸውና ለሥልጣናቸው አብዝተው የሚጨነቁ ከሆነ በአገልግሎታቸውና በስብከታቸው ላይ ተጽእኖ ያደርግባቸዋል፤ ሕይወታቸውን ስጋት ይገዛዋል። ስለሆነም እውነት የሚናገሩትን ስለሚፈሩ እየራቁ ይመጣሉ። ግልጽነትና መልካም አስተዳደር ይጠፋል። ግንኙነትና የአገልግሎት ተሳትፎም በወዳጅነትና ታማኝነትን በማሳየት ስለሚሆን የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ዓላማውን እየሳተ ይመጣል። የቤተ ክርስቲያን ዕድገትም ይቀጭጫል። ስለሆነም በዚህና በመሳሰሉ ችግሮቻችን ላይ የስብስቡ አባላት አብረው እየጸለዩና በመመካከር የተለያዩ ጥናቶችን በማዘጋጀት ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በመሆን ዐውደ ጥናት ለማዘጋጀትና ለመወያየት ዐስበዋል። ለወደፊቱም እግዚአብሔር እንደፈቀደ ተከታታይነት ባለው መንገድ ውይይቱንና ትምህርቱን ለመቀጠልም ዕቅድ አለ።
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፡- ይህ ከሁላችንም ፊት የተደቀነ ኀላፊነትና አደራ ነው። በአገራችን ክርስትና ትርጉም እንዲኖረው፣ ሥነ ምግባርን ጠብቆ እንዲዘልቅ፣ የአብያተ ክርስቲያናትም ተልእኮ ስኬታማ እንዲሆንና በጨለማ ውስጥ እውነተኛ ብርሃን ሆኖ እንዲታይ በአእምሮ መታደስና በክርስቶስ ፍቅር ሸክም መንቀሳቀስ ይገባል። አገልጋዮችና መሪዎች ምዕመኑ ለዕድገቱ የሚያስፈልገውን ቀረብ ብሎ በማወቅ ሊያገለግሉት ይገባል። ክርስትና ትርጉም እንዲኖረው፣ አገልጋዮች ራስን በመካድ የእግዚአብሔር የሆነውን ትኩር ብሎ በማየት ምእመኑን ማገልገልና ምሳሌ ሆኖ መምራት ይጠበቅባቸዋል። መሪዎች በምእመናኖቻቸውም ሆነ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ምሳሌ የሆነ ሕይወት ሊኖሩ አስፈላጊ ይሆናል። ክርስትና ትርጉም እንዲኖረው ለወጣቱ ትኩረት መስጠት፣ በቃሉ ማሳደግና ለአመራር ማዘጋጀትና ማሳተፍ ከምንጊዜውም ይልቅ አጣዳፊ ሆኖ ይታያል። ወጣቱም ሆነ በአጠቃላይ ምእመኑ የወቅቱን ተግዳሮት እየተረዳ፣ በአሸናፊነት የሚያልፍባቸውን የጊዜውን መልእክት ማዘጋጀት ይጠይቃል። በአሁኑ ጊዜ በርካታ ምእመን ከሚታይባቸው እውቀት ከተለየው ቅናት ተለይተው፣ ከባዶ ስሜታዊነት ርቀው በመንፈስና በአእምሮ ብስለት እንዲመላለሱ ማስተማርና መደገፍ ይገባል። በተጨማሪም፣ በየደረጃው ከአጥቢያ እስከ ቤተ እምነት፣ ከቤተ እምነት እስከ ኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ድረስ የመንፈስ አንድነትን በመፍጠርና ኅብረትን በማጠንከር በጥናት ላይ የተመሠረተ የወንጌል ሥርጭት ስልት መቀየስና መንቀሳቀስ አስፈላጊ ይሆናል። ከእነዚህ በተጨማሪም ክርስትና ትርጉም እንዲኖረው የቤተ ክርስቲያንም ብርሃን ጐልቶ እንዲታይ አብያተ ክርስቲያናት መልካም አስተዳደርን ማሳየት፣ በግልጽነትና በእውነት ምእመናኖቻቸውን መምራት፣ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑንም አምኖ መቀበል ይጠበቃል።
Share this article:
እውቁ የሥነ አእምሮ ሐኪምና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም አሳሳቢነቱ ጨምሯል ስለሚባለው የአእምሮ ሕመም ከሕንጸት መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ፣ ችግሩን በተመለከተ በወንጌላውያን አማኞች መካከል ስላለው የአመለካከት ክፍተትና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ርምጃዎች ሚክያስ በላይ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል።
ʻመሪዎች ለሁሉም ዐይነት ተቋማዊ ችግር ፍቱን መድኃኒቶች ናቸውን?ʼ በርግጥ በአመራር ላይ ጥናት ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን መሪዎችን እንዲህ ባለ መልክ አያቀርቧቸውም። እጅግ የተደነቁቱ የአመራር ዘይቤዎችም ሳይቀሩ (ለምሳሌ፡- ሎሌያዊ አመራር – “Servant Leadership” እና ተሃድሷዊ አመራር – “Transformational Leadership”) ላለንበት ተቋማዊም ሆነ አገራዊ ችግር ብቸኛ መፍትሔ እንዳይደሉ እነዚሁ ምሁራን ይስማማሉ። ይህን አቋማቸውን “Leadership is not a panacea to all our problems” በማለት ነው የሚገልጡት – መሪነት ለችግሮቻችን ሁሉ ፍቱን መድኃኒት አይደለም እንደማለት ነው። ይህ ሲባል ግን የመሪዎች ሚና እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ ሊታሰብበት ይገባል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment