[the_ad_group id=”107″]

“የውጭ ወራሪና የውስጥ ቦርቧሪ ያልናቸውን ትምህርቶች መግረዝ ይችላሉ ባይ ነኝ”

ተስፋዬ ሮበሌ ይባላል፡፡ ባለ ትዳርና የአራት ወንዶች ልጆች አባት ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው በመኻል አዲስ አበባ፣ አብነት ሆቴል በሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡ ገሚሱን ዕድሜውን የኖረው ግን ኮሌፌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር፡፡ ተስፋዬ አዲስ አበባ ከሚገኘው ኢቫንጄሊካል ቲዮሎጂካል ኮሌጅ በነገረ መለኮት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በማስከተል አሜሪካን አገር በሚገኘው የካልቪን ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ፍልስፍናዊና ምግባራዊ ነገረ መለኮት (Master of Theological Studies (MTS) in Philosophical and Moral Theology) የድኅረ ምረቃ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በዚያው አሜሪካ በሚሽገን በሚገኘው፣ በኮርነር ስቶን ዩኒቨርስቲ በደርዛዌ ነገረ መለኮት (Systematic Theology) ሁለተኛውን የድኅረ ምረቃ ጥናቱን አክሎበታል፡፡ አሁን ሻርሌት ኖርዝ ካሮላይና በሚገኘው በሳውዘርን የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት፣ በዐቅብተ እምነት የዶክተሬት ድግሪውን በማገባደድ ላይ ይገኛል፡፡

ተስፋዬ ሮበሌ ለትምህርት ከኢትዮጵያ እስኪወጣ ድረስ የተስፋ ዐቃቢያነ ክርስትና ማኅበርን በዳይሬክተርነት አገልግሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕቅበተ እምነት ርእሰ ጒዳዮች ላይ የተለያዩ መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡ ከእነዚህም መካከል “የይሖዋ ምስክሮችና አስተምህሮአቸው በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን”፣ “ውሃና ስሙ፡- ʻየሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንʼ የድነት ትምህርት በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን”፣ “ዐበይት መናፍቃን” እንዲሁም “የዳቬንቺ ኮድ፡- ድርሳነ ጠቢብ ወይስ ድርሳነ ባልቴት?” ይጠቀሳሉ፡፡ ተካልኝ ዱጉማ በዕቅበተ እምነት ጕዳዮች ዙሪያ ከተስፋዬ ሮበሌ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርበቧል፡፡


  • ሕንጸት፡- አንድ ትምህርት ወይም ልምምድ ʻኑፋቄ ነውʼ ተብሎ የሚፈረጀው መቼ ነው? ብያኔውን የሚሰጠውስ ማን ነው?

ተስፋዬ ሮበሌ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በነገረ መለኮቱ ዓለም ክርስቲያናዊ ትምህርቶች በሁለት ወገኖች ይከፈላሉ፤ ይኸውም ዐበይት አስተምህሮዎች እና ንዑሳን (ደቂቃን) ትምህርቶች ይባላሉ፡፡ ዐበይት አስተምህሮዎች፣ “ዐበይት” የተባሉበት ቀዳማይ ምክንያት፣ እነዚህን አስተምህሮዎች መቀበልም ሆነ አለመቀበል የአንድን ሰው ዕድል ፈንታ (የዘላለም ሕይወት) ስለሚወስኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ተልኮ የመጣ መሲሕ (አዳኝ) መሆኑን ያለማመን፣ ዘላለማዊ ኲነኔ እንደሚያስከትል ኢየሱስ ራሱ በግልጽ ተናግሯል፣ “በኀጢአታችሁ እንደምትሞቱ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደ ሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና” (ዮሐንስ 8፥24)፡፡

ሌላ ምሳሌ ልጨምር፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ የመነሣቱ ትምህርት ዐቢይ ክርስቲያናዊ ትምህርት ነው፡፡ ይህን አስተምህሮ ያለማመን ዘላለማዊ ኵነኔ ያስከትላል፣ “ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ … እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው … ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም፡፡ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው” (1ቆሮንቶስ 15፥3:4:11:15-17)፡፡ ይህንኑ ጒዳይ አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ እንዲህ ይላል፣ “እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ” (ሮሜ 10፥9)፡፡ ልክ እንደነዚህ አስተምህሮዎች ሁሉ፣ ዕድል ፈንታችንን የሚወስኑ በርካታ ወሳኝ ትምህርቶች አሉ፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ክርስቲያናች በደቂቃን ትምህርቶች ላይ ቢለያዩ (መለያየት ጥሩ ባይሆንም) ልዩነታቸው እንደ ትልቅ ችግር መታየት እንደሌለበት ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ በሮሜ 14፥1-8 ባለው ክፍል ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ቀናትንና ምግብን አስመልክቶ በፍጹም መለያየት እንደማይገባቸው፣ ተቃራኒ አስተሳሰብ ኖሯቸው እንኳ፣ “የጌታ ወገን” እንደ ሆኑ ይገልጻል፡፡

ምናልባት አንዳንድ ሰዎች፣ ታዲያ “የአንድ ሰው ድነት የሚወሰነው በደርዛዌ ነገረ መለኮት (Systematic theology) ባለው ዕውቀት ልክ ነው ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ሊያነሡ ይችላሉ፡፡ እውነታው ይህ ከሆነም፣ በደርዛዌ ነገረ መለኮት ፈተና የወደቀ ሰው ድነቱ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል ማለት ነው? ነገሩ በፍጹም እንደዚያ አይደለም፡፡ ክርስትና የተወሰኑ አንቀጸ ሃይማኖቶችን ማወቅ (ፈላስፎቹ propositional knowledge የሚሉት) ሳይሆን፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በግል ማወቅና ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ ግንኙነት ማበጀት ነው (በመጽሐፍ ቅዱሱ አነጋገር ዳግም መወለድ ነው)፡፡ ስለዚህ ክርስትና የፈተና ጒዳይ ሳይሆን የግል የትውውቅ ጒዳይ ነው፡፡

ነገር ግን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ያለው ሰው የተሳሳተ ዕውቀት ሊኖረው አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ትምህርተ ሥላሴን መተንተን ዐቅም ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ ሙስሊሞች ኢየሱስ “መሲሕ ብቻ” ነው፤ እንደ አርዮሳውያን (የይሖዋ ምስክሮች)፣ “ኢየሱስ ፍጡር ነው” ወይም እንደ ሰባልዮሳውያን (“የኦንሊ ጂሰስ” ድርጅት አባላት) “ኢየሱስ አብ ነው ወይም አብ ያደረበት ሥጋ ነው” የሚል እምነት ሊኖረው አይችልም፡፡ አንድ ሰው በደርዛዌ ነገረ መለኮት ፈተና አንድ ከዐሥር አምጥቶ፣ በሙሉ ትርጒሙ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ በአንጻሩ አንድ ሰው፣ በነገረ መለኮት ፈተና ዐሥር ከዐሥር አምጥቶ፣ ስለ ጌታ እንጂ ጌታን በጭራሽ ላያውቅ ይችላል፡፡ በስመ ጥር ዮኒቨርስቲ ነገረ መለኮትን የሚያስተምሩ አንዳንድ ሰዎች (ለዘብተኛ አቋም ያላቸውን የነገረ መለኮት ሊቃውንት) ከፍተኛ የሆነ የነገረ መለኮት ዕወቅት አላቸው፡፡ እንዲያውም ዕውቀታቸው ከአጥባቂያኑ ምሁራን እጅግ ሊበልጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አምላክ መኖሩን እንኳ እርግጠኞች አይደሉም፡፡

አንድ ሰው በደርዛዌ ነገረ መለኮት ፈተና አንድ ከዐሥር አምጥቶ፣ በሙሉ ትርጒሙ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ በአንጻሩ አንድ ሰው፣ በነገረ መለኮት ፈተና ዐሥር ከዐሥር አምጥቶ፣ ስለጌታ እንጂ ጌታን በጭራሽ ላያውቅ ይችላል፡፡

ስለዚህ አንድ ሰው መናፈቅ ነው የሚባለው፣ ከእነዚህ መሠረታውያን አስተምህሮዎች አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ትምህርቶችን ሳይቀበል ሲቀር ነው፡፡ ይህን ብያኔ የሚሰጠውም ግለ ሰብ ወይም የሃይማኖት ድርጅት ወይም ደግሞ ጒባኤ ሳይሆን የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳ መጻሕፍት ናቸው፤ ምክንያቱም የትምህርቱ ንጽጽር የተካሄደው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንጂ ከግለ ሰቦች ወግና አቋም አንጻር አይደለምና፡፡

  • ሕንጸት፡- የዕቀበተ እምነት አገልግሎት በታሪክም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ዋነኛው ሆኖ እንደ ቆየ እንረዳለን፤ አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ይህ አገልግሎት እንደ ከዚህ ቀደሙ፣ በቤተ ክርስቲያን ዐቢይ አገልግሎት ሆኖ ይታያል ማለት እንችላለን?

ተስፋዬ ሮበሌ፡- የቤተ ክርስቲያን ቀዳማይ ተልእኮዋ የምሥራቹን ወንጌል መሰበክና ወንጌሉንም ከጥቃት መከላከል (commending and defending) ነው፡፡ ከዚህ ጣምራ ዐላማ የተለየ ተልእኮም ሆነ ዕቅድ ሊኖራት አይችልም፡፡ ነገር ግን ዛሬ ስብከተ ወንጌል ማካሄድ እንጂ፣ ስብከተ ወንጌሉን ከሚበርዙ መናፍቃን የትምህርቱን ንጽሕና መከላከል ፍጹም የተረሣ ጒዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህም የተነሣ ከየትኛውም የታሪክ ጊዜ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን በብዙ እንግዳ ደራሽ ትምህርቶች በመናጥ ላይ ትገኛለች፡፡ አንዳንዶቹ ነውጦች አገር በቀል ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌላው የዓለም ክፍል የሚመጡ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድኅረ ዘመናዊ የሚባለው አስተሳሰብ ትልልቅ የትምህርት ተቋማትን ክፉኛ ተጣብቶ (እንደ ውስጥ ደዌ ተውሳክ) ይገኛል፡፡ ብዙ ሥራ አለብን፡፡ ብዙ አምላካዊ ዐደራ አለብን፤ ይኸውም ወንጌልን ከብረዛ በመከላከል እውነተኛውንና ንጽሑን ወንጌል ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ፣ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል ለትውልዱ በሚመጥን መንገድ በማስተማር፣ “በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን፡፡” እንዲል መጽሐፍ (2ቆሮንቶስ 10፥5)፡፡

  • ሕንጸት፡- በአንተ እምነት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያንን ሲፈታተኗት የቆዩ የኑፋቄ ትምህርቶች/እንቅስቃሴዎች እነማን ናቸው? በአሁኑ ጊዜስ?

ተስፋዬ ሮበሌ፡- ወንድም አማረ መስፍን አዘወትሮ እንደሚለው፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት “በውጭ ወራሪና በውስጥ ቦርቧሪ” ችግሮች ክፉኛ እየተጠቁ ነው፡፡ የውጭ ወራሪ የምንላቸው ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውጭ ሆነው፣ ቤተ ክርስቲያንን ክፉኛ በመፈታተን ላይ ያሉትን ትምህርቶች ነው፡፡ ለምሳሌ የይሖዋ ምስክሮች፣ ኦንሊ ጂሰሶች፣ ሞርሞኖች፣ ወዘተ.፡፡ የውስጥ ቦርቧሪ የሚባሉት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ተከታዮችን ያፈሩ፣ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችና ልምምዶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በውስጥ ቦርቧሪነት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል ብዬ የማስበው “የእምነት እንቅስቃሴ” ወይም “የብልጥግና ወንጌል” በመባል የሚታወቀው ትምህርት ነው፡፡ ይህ ትምህርት በአንድ ወቅት በስፋት ተነሥቶ ኋላ ከስሞ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ፣ እንደ እባብ ዐፈር ልሶ ተነሥቶአል፡፡ ይህ ትምህርት ዳግም እንዴት ሊያነሠራራ እንደ ቻለ እኔ በውል አልገባኝም፤ አገር ውስጥ የለሁምና፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በሥራ ላይ ባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አማካኝነት የሚተላለፉ አብዛኞቹ ትምህርቶች፣ በዚህ የተሳሳተ ትምህርት የተጠመቁ እንደ ሆኑ እሰማለሁ፡፡ ይህ ደግሞ መሠረተ እምነታችንን ብቻ ሳይሆን፣ ሥነ ምግባራችንንም ክፉኛ እያበላሸ ያለ ችግር ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ትምህርት መሠረት ሰው መንፈስ ስለሆነ፣ አካሉ ደግሞ መኖሪያው እንጂ እርሱነቱ ስላልሆነ፣ ሰው በአካሉ ወይም በሥጋው በሚሠራው ኀጢአት ተወቃሽ መሆን የለበትም የሚል ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ስለ ገንዘብ ወይም ንዋይ፣ ስለ በሽታ፣ ስለ ሰው ተፈጥሮ፣ ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ ሥራ፣ ወዘተ. የሚያስተምረው ትምህርት ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ ይህን ትምህርት የውስጥ ቦርቧሪ ያልሁበት ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዚህ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰብ ሎሌ ስላደሩ ነው፡፡

“በአሁኑ ወቅት በውስጥ ቦርቧሪነት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል ብዬ
የማስበው “የእምነት እንቅስቃሴ” ወይም “የብልጥግና ወንጌል” በመባል የሚታወቀው ትምህርት ነው፡፡ “

  • ሕንጸት፡- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሚፈታተኗት የስሕተት ትምህርቶች ዝግጁነቱና ዐቅሙ አላት ትላለህ?

ተስፋዬ ሮበሌ፡- ዛሬ ደረጃውን በጠበቀ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የተከታተሉ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አሉ፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ተቀናጅተው በቊርጠኝነት፣ “የውጭ ወራሪና የውስጥ ቦርቧሪ” ያልናቸውን ትምህርቶች እንዲሁም አግድም ዐደግ ልምምዶችን መግረዝ ይችላሉ ባይ ነኝ፡፡ በቤተ ክርስቲያን አመራር አካባቢ ግን ችግሩን በውል የመረዳትም ሆነ ለችግሩ ሁነኛ እልባት ለማበጀት ቊርጠኝነቱ መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ ቢያንስ ችግሩን በውል የተረዳን ሰዎች እጅ ለእጅ ተያይዘን ብንሠራ፣ ትልቅ ውጤት እንደሚገኝ አልጠራጠርም፡፡

  • ሕንጸት፡- በኢትዮጵያ ያለችው ወንጌላዊቷ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ቤተ እምነቶች ታሪካዊ አሻራ ያሳረፉባት መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከዚህ የተነሣ የዕቅበተ እምነት ሥራውን ፍጹም ከባድ አያደርገውም ትላለህ? ምክንያቱም ሰዎች ʻይህ ስሕተት ነውʼ ሲባሉ የቤተ እምነት ጒዳይ አድርጎ የማየት ዝንባሌ እያደረባቸው የመጣ ስለሚመስል፡፡

ተስፋዬ ሮበሌ፡- እያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያን የራሱ የሆነ ታሪክና ትውፊት አለው፡፡ ታሪክና ትውፊትንም ማክበር ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን ታሪካችንና ትውፊታችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ እንዲሠለጥን ልንፈቅድ አይገባም፡፡ ለምሳሌ፣ አንዳንድ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በሚል ሰበብ፣ ክርስትናን የሚያስነቅፍ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተደገፈ ልምምድ አላቸው፡፡ ተው ሲባሉ፣ ʻእኔ እኮ የዚህች ቤተ ክርስቲያን አባል ነኝ፤ አንተ ይህን ልምምድ የምትነቅፈው ከዚህ ቤተ ክርስቲያን ስለሆንህ ነውʼ ይላሉ፡፡ ይህ መቼም ያሳዝናል፡፡ እኛ ለትምህርታችንም ሆነ ለልምምዳችን መሠረት ሊሆነን የሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ የሰዎችን ልምምድና ተሞክሮ ልንከተል የሚገባው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተጣጥሞ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡

አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በአንዳንድ ርእሰ ጒዳዮች ላይ ያላቸው ትምህርት ስሕተት እንደ ሆነ እያወቁ፣ ʻምን ይደረግ እኔ ከዚህ ቤተ ክርስቲያን ነኝʼ የሚሉም ሰዎች አሉ፡፡ ልክ ነው በታሪካቸው ውስጥ ያ አስተምህሮ እንደ ትክክል ሲወሰድ ኖሯል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ትክክል እንዳልሆነ ከተረጋገጠ፣ ቀደምት ልምምዶችንና ትምህርቶችን ወግድ በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጅ መሆናችንን ለናረጋግጥ ይገባል፡፡ ተሐድሶ በአንድ የታሪክ ወቅት ተከሥቶ የሚያልቅ ጒዳይ ሳይሆን፣ ሁል ጊዜ የመታደስ ሕይወትን የሚፈልግ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ለረጅም ጊዜ የዳላስ የመጽሐፍ ቅዱስ ሴሚነሪ ፕሮፌሰሮች ዲስፐንሴሽናሊዝም የሚባለው የነገረ መለኮት አካሄድ ትክክል ነው ብለው ያስቡ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ የእነርሱ ስመ ጥር ፕሮፌሰሮች ʻተሳስተናልʼ በማለት በይፋ እየጻፉ ነው፡፡ አንዳንድ የሉትራን ቤተ ክርስቲያን ምሁራን፣ ቀድሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውሃ ጥምቀት ላይ ያላትን ትምህርት በመተቸት እየጻፉ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእውነት መሸነፍ ለእግዚአብሔር መሸነፍ ነውና፡፡ ይህን በናሙናነት አነሣሁ እንጂ ተሐድሶ የሚፈልጉ በርካታ ትምህርቶች በእኛም የአስተምህሮ ትውፊት ውስጥ አሉ፡፡

  • ሕንጸት፡- እስኪ አሁን ደግሞ ስለ “ተስፋ ዐቃቢያነ እምነት” እናውራ፡፡ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ አባላቱ፣ ስለ ሠራቸው ሥራዎች፣ አሁን እየሠራቸው ስላሉ ሥራዎችና ወደ ፊት ሊሠራቸው ስለሚያስባቸው ሥራዎች ጭምር ብትነግረን?

ተስፋዬ ሮበሌ፡- እንደ ስሙ ሁሉ፣ ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበር፣ ዕቅበተ እምነታዊ የሆነ ሥራ ለመሥራት የተቋቋመ መንፈሳዊ ድርጅት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለውን ሥራ በመሪነት እያከናወነ ያለው ወንድማችን ቄስ ሙሉጌታ ታደሰ ነው፡፡ የማኅበራችን ፕሬዝደንት ደግሞ ወንድም አማረ መስፍን ነው፡፡ በመናፍቃን እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ ትክክለኛው መሠረተ እምነት ማምጣት እንዲሁም ክርስቲያኖች በመናፍቃን እንቅስቃሴ እንዳይወሰዱ መከላከል የድርጅቱ ዋነኛ ዐላማ ነው፡፡

ድርጅቱ ከመንግሥት ዕውቅና ካገኘ 1993 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በመናፍቃን አስተምህሮ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ከትክክለኛው ወንጌል ጋር ሲተዋወቁ አይተናል፡፡ ዛሬም ያንን ሥራ ዐቅም በፈቀደ ሁሉ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ የተወሰኑ ሚስያናውያንንም እየረዳን ነው፡፡ ድርጅቱ በቅርቡ ከአሜሪካን መንግሥት ሙሉ ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ የድርጅቱን ዐላማ በሌሎችም አገሮች ለማስፋፋት ትልቅ ዕድል የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡ ወደ ፊት እግዚአብሔር ቢረዳን በተለያዩ አገሮች ሚስዮናውያንን መላክና ቢሮ የመክፈት ዕቅድ አለን፡፡ ባለፈው ጊዜ አንድ ወንድምን ለአንድ ዓመት ያህል ወደ ዩጋንዳ ልከን ትልቅ ሥራ ሠርቶ ተመልሷል፡፡ ጌታ ገንዘብ ከሰጠን ሌሎች የወንጌል ጀግኖችን ወደ ተለያዩ አገሮች የመላክ ዕቅድ አለን፡፡ አገር ውስጥ በሚገኙ ትልልቅ የትምህርት ተቋማት አካባቢ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የሚያገለግሉ ሰዎችን ማሰማራት፣ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የዕቅብተ እምነት ክበብ መመሥረት እንፈልጋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ የዚህ መጽሔት ተደራስያን ለዚህ ሥራ እንዲጸልዩልን እንዲሁም ዐቅም በፈቀደ ሁሉ እንዲረዱን በማክበር እጠይቀለሁ፡፡ ለመርዳት ዐላማ ያላቸው ሰዎች ቄስ ሙሉጌታ ታደሰን ወይም ወንድም አማረ መስፍን ማነጋገር ይችላሉ፡፡    

  • ሕንጸት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ዕቅበተ እምነት ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት የተቋቋመ ብቸኛ አገልግሎት “ተስፋ ዐቃቢያነ እምነት” እንደ ሆነ ነው የምናውቀው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ አንድ ተቋም ብቻ ይበቃል ብለህ ታምናለህ? ካልሆነስ ምን መደረግ ይኖርበታል?

ተስፋዬ ሮበሌ፡- ጒዳዩ የብዛት ጒዳይ ሳይሆን የጥራት ጒዳይ ነው፡፡ ብዙ መሰል ድርጅቶች መቋቋማቸው ክፋት የለውም፤ ቊም ነገሩ ግን የድርጅት ብዛት ሳይሆን፣ መሥራት ያለብንን ነገር በብቃት ማከናወናወን መቻል ነው፡፡ በርካታ ዐቅመ ቢስ ድርጅቶችን ከምናቋቁም ያለንን ገንዘብና ዕውቀት በአንድ አስተባብረን በጥምረት ብንሠራ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በአገር ላይ ትልቅ ለውጥ እናመጣለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዕቅብተ እምነት አገልግሎት ጌታ ጠርቶኛል የሚሉ ወገኖች ከላይ በስም የጠቀስኋቸውን ወንድሞች ማነጋገር ይችላሉ፡፡ 

  • ሕንጸት፡- በመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ ዕድል እንስጥህ፡፡

ተስፋዬ ሮበሌ፡- በሕንጸት መጽሔት ዝግጅት ክፍል የሚያገለግሉ ወንድሞችንና እኅቶችን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ ጤናማው የክርስቶስ ወንጌል እንዳይሸቃቀጥ የሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም ለወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ያላቸው ተቈርቋሪነት በጣም ያስደንቀኛል፡፡ እግዚአብሔር እንደ እናንተ ያሉ የወንጌል ባለ ዐደራዎችን ስለ ሰጠን ጌታን ከልብ እናመሰግናለን፡፡ አይዟችሁ ብርቱ፤ የማታ ማታ እውነት ማሸነፉ አይቀርም፡፡ ለእውነትም ዋጋ የሚከፍሉ ሰዎች፣ የእውነት ሁሉ አምላክ ብድራት እንደሚያኖርላቸው እናምናለን፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የማንም ባለ ዕዳ አይደለምና፡፡ በርቱ ዐቅም በፈቀደው ሁሉ አብረናችሁ እንቈማለን፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡    

  • ሕንጸት፡- እናመሰግናለን!

Tekalign Duguma

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.