[the_ad_group id=”107″]

“ጥበቡን ከእግዚአብሔር እና ከመንፈሳዊነቱ ውጪ ልተርከው አልችልም።”

“ጥበቡ፡- የምድረ በዳው እረኛ” በሚል ለንባብ የበቃው መጽሐፍ በብዙ ቅጂዎች ተባዝቶ መነበብ ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። ባለፉት ዐሥራ አንድ ወራትም በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በመጽሐፉ ይዘትና ቅርጽ ላይ የተለያዩ ውይይቶች ተካሄደዋል። በዋናነት በአንድ ቤተ ሰብ ሕይወት ላይ የሚያጠነጥነው ይህ መጽሐፍ የብዙዎችን ስሜት መግዛት እንደቻለም ይነገራል። ሰላማዊት አድማሱ ከጸሐፊዋ ወ/ሮ ሊሻን አጎናፍር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።


 • “ጥበቡ፡- የምድረ በዳው እረኛ” የተሰኘው መጽሐፍ ለኅትመት ከበቃ ወራቶች ተቆጥረዋል፤ የአንባቢያን ምላሽ እና የስርጭቱ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ነሐሴ 25፣ 2005 ዓ.ም. በኢትዮጰያ ውስጥ ተመርቆ ለስርጭት የዋለው ይህ መጽሐፍ ምንም እንኳን ገና ዓመት ያልሞላው ቢሆንም ከጠበቅነው በላይ ከሰው እጅ እየደረሰ ይገኛል። እስካሁን በዐሥር ወራት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ብቻ ወደ 25 ሺህ ኮፒዎች ተሰራጭተዋል። የአንባቢያን ምላሽን በተመለከተ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና ከውጪ አገራት በድረ ገጻችን፣ በኢሜል እና በስልኮች በጣም ልብ የሚነኩ በርካታ አስተያየቶች እየደረሱን ነው። በቀን ቢያንስ ሁለትና ሦስት የስልክ ጥሪዎችን አስተናግዳለሁ። ከእነዚህም መካከል፣ ʻበዕንባ አንበብነውʼ፣ ʻበጣም አስተማሪ ነውʼ፣ ʻየጸሎት ሕይወታችን እና እምነታችን ታደሰበትʼ የሚሉት ከአስተያየቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ʻእግዚአብሔር በሰው ሕይወት ውስጥ እንዲህ ከሠራ፣ በእኛም ሕይወት ውስጥ ይሠራል ማለት ነውʼ የሚል ተስፋን አምጥቷል። በዚህ ደግሞ በጣም ደስ ብሎኛል።

 • መጽሐፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ ከደረሱ አስተያየቶች በመነሣት ʻይሄ በዚህ መልክ ባይጻፍ ጥሩ ነበርʼ የምትይው ነገር ይኖር ይሆን?

ʻመጽሐፉን ያገኘው ሰው ሁሉ ቢያነበው ጥሩ እንዲሆን መንፈሳዊነቱ ቢቀነስ ጥሩ ነበርʼ ያሉኝ ሰዎች አሉ።

ከዚህ አስተያየት ተነሥተሽ ʻበዚህ መንገድ ባላቀረብኩትʼ ብለሽ ነበር?

በፍጹም አላልኩም። ምክንያቱም ታሪኩ ከመንፈሳዊነት ውጪ ሊታይ አይችልም። በዚህ መጽሐፍም ማስተላለፍ የፈለኩት ነገር መንፈሳዊነቱን ነው። ከዚያ ሌላ አድርጌ ብጽፈው ለኅሊናዬ ትክክል አይሆንም።

 • ከዚህ ውጪ ግን የተሰጡ ሌሎች አስተያየቶች አሉ?

በርግጥ አንዳንዶች ʻይሄ ባይሆንʼ ያሉት አለ። ለምሳሌ፣ በእምነታችን ምክንያት የተሰደድንበት ጊዜ ነበር። ቀብሪደሃር እያለን የኮሚኒዝም ፍልስፍና ወይም የኢህአፓ ተካታይ የነበሩ ወጣቶች “ሞት ለዶ/ር ጥበቡ፤ ሞት ለኢምፔሪያሊዝም” እያሉ ቤታችን ላይ ድንጋይ ይወረውሩ ነበር። በተመሳሳይም በአባቴ የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ የነበረውን የተቃውሞ ሁኔታ በመጽሐፉ ገልጫለሁ። እናም አንዳንድ ሰዎች ʻይሄ ያለፈ ነገር ነው፤ ባትገልጪው ጥሩ ነበር፤ ለምን አስፈለገ?ʼ ብለውኛል። ለእኔ ግን ይህ አንዱ የሕይወታችን ወይም የታሪካችን ክፍል እንደመሆኑ መተው ነበረብኝ ብዬ አላምንም።

 • መጽሐፉን ለመጻፍ መነሻ የሆነው ዋናው ምክንያት ምን ነበር?

የመጸሐፉ ዋና ዓላማ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለመናገር ነው። እግዚአብሔር ሕያው ነው፤ እግዚአብሔር ኀያል ነው፤ እግዚአብሔር የታሪክ ባለቤት ነው። ʻእግዚአብሔር በአንድ ግለ ሰብ ሕይወት፣ ብሎም በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ ዕድል ወይም ስፍራ ከተሰጠው በሰው ደረጃ የማይታመን ነገር ሊሠራ ይችላልʼ የሚለውን ነው ማስገንዘብ የፈለኩት። ለእግዚአብሔር ክብር ነው የጻፍኩት።

 • ዓላማው ግቡን መቷል?

ከጠበኩት በላይ ዓላማዬ ግቡን መቷል። ይህም ታላቅ ደስታን ፈጥሮልኛል። ʻእግዚአብሔር ሆይ፤ ዓላማው ሰዎች አንተን እንዲያዩ ነው፤ ከፈቀድንልህና እሺ ካልንህ በሰው ሕይወት ውስጥ የምትሠራው ይህን ነው፤ ሰው ደግሞ ይህንን እንዲያይልኝ እፈልጋለሁʼ ብዬ ብዙ ጸልያለሁ። ያነበቡት ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ነው ያዩት። በመጽሐፉ ውስጥ ስለ ጸሎት የተጠቀሰ ታሪክ በመኖሩ ʻየጸሎት ኀይላችን ታድሷልʼ ያሉኝ ሰዎች አሉ፤ በዚያን ዘመን የነበረውን ኅብረት በማየትም ሰዎች ልባቸው እንደተነሣሣ ገልጸውልኛል። ከዚያ በተረፈ ግን ብዙ ወጣቶች ልብን በሚነካ መልኩ የሚናገሩት ነገር አለ። በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሄጄ የሰማሁት፣ ʻእግዚአብሔር ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ለትውልዱ የሰጠው መመሪያ መጽሐፍ ነውʼ የሚል ነበር። ከዚህም አልፎ መጽሐፉን አንብበው ጌታን እስከመቀበል የደረሱ ሰዎች እንዳሉም ለመረዳት ችያለሁ። እንግዲህ እግዚአብሔር ጸሎቴን በዚህ መልኩ ስለ መለሰለኝ አመሰግነዋለሁ።

 • ይህን መጽሐፍ ልትጽፊው ካሰብሽና ከጀመርሽው በኋላ ብዙ ጊዜ መቀጠሉ እየቸገረሽ እንዳቋረጥሽው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ገልጻሻል፤ ችግሩ ምን ነበር?

ለእኔ ይሄ ታሪክ የእግዚአብሔርን ሕልውና በጉልሕ ያየሁበት ታሪክ ነው። ስለዚህ እንዴት አድርጌ ብተርከው ያየሁትን እግዚአብሔር ለሰው ማሳየት እችላለሁ የሚል ከባድ ጭንቀት ነበረኝ። ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ ጸጥ ያለ እና የተረጋጋ ሁኔታ እፈልግ ነበር። ከባለቤቴ የሥራ ሁኔታ ጋር ተደምሮ እርፍ ብዬ በሰከነ አእምሮ እና ልብ ለመጻፍ የሚያስችለኝ ሁኔታ አልነበረኝም። ስለሆነም ለተደጋጋሚ ጊዜ እየጀመርኩ አቋርጬዋለሁ።

 • አንዳንድ አንባቢያን የመጽሐፉ መንፈሳዊ ድምፀት ከማየሉ የተነሣ ታሪካዊ ፋይዳውን ለማየት እንደተቸገሩ ይናገራሉ።

መቼም ጥበቡን ብሔራዊ ጀግና ያሰኘው በሕይወቱ ያለው እግዚአብሔር ነው። ጥበቡን ከእግዚአብሔር እና ከመንፈሳዊነቱ ውጪ ልተርከው አልችልም። ጥበቡ ኃይለሥላሴ መንፈሳዊ ሰው ነው። የእሱም ሆነ የቤተ ሰቡ ሕይወት ከዚህ ተነጥሎ መታየት አይችልም። እውነት አልዋጥ ካለን በጣም ይደንቀኛል፤ ምክንያቱም አንድ መንፈሳዊ ሰው ለአገሩ ታሪክ ሠሪ መሆን እንደሚችል እንዴት ሊታየን እንዳልቻለ አስገርሞኛል። ይህን መረዳት ላልቻሉ ብዙ ነገር ቀርቶባቸዋል እላለሁ።

 • ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመጽሐፉ ውስጥ ያለው የዶ/ር ጥበቡም ሆነ የአንቺ ታሪክ ʻሰው ሰው አይሸትምʼ የሚሉ ሰዎች አሉ።

መቼም ሁላችን ክርስቶስን እንድንመስል ተጠርተናልና ይህ ሕይወት ልንኖረው የማንችለው የሕይወት ደረጃ ነው ልንል አንችልም። በቃ፤ እኛ ኖርነውም አልኖርነውም የሕይወታችን ጥጉ ክርስቶስን መምሰል ነው። ሰው ሰው እንዲሸት ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፤ ይሁን እንጂ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ሰው ሰው የሚሸቱ ታሪኮች አሉ። እንደ ሰው ስናዝን ልባችን ሲሰበር፣ እንደ ሰው ስንቸገር፣ እንደ ሰው ተስፋ ስንቆርጥ፣ በአጠቃላይ የነፍስ ጩኸት በመጽሐፉ ውስጥ ተንጸባርቀዋል። ከዚህ ውጪ ግን ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆነ የሕይወት መርሖ የለንም፤ እርሱን ልንመስል ተጠራን፤ ነገር ግን እርሱን ለመምሰል እየሄድን ነው፤ ስለዚህ በዚያ ዐይነት ሕይወት ውስጥ እንዳለ ማንም የእግዚአብሔር ሰው ጠረኑ ክርስቶስ ኢየሱስን ነው ሊመስል የሚገባው ብዬ እላለሁ። ከዚህ ውጪ መልስ የለኝም።

 • በትዳርችሁ ተጋጭታችሁ አታውቁም?

እግዚአብሔር ይመስገን ወደ ጠነከረ ጠብ፣ ወደ አለመስማማት ብሎም ወደ ፍቺ የሚያደርስ ግጭት በመካከላችን ተፈጥሮ አያውቅም። አንዳንድ የሐሳብ ልዩነቶች በመካከላችን ቢፈጠሩ እንኳን በዛ ሁኔታ ውስጥ አንቆይም ወይም አንከርምም። ግጭት ቢፈጠር ቶሎ መሥመር ማስያዝ የቤታችን አንዱ መመሪያ ነበር። በጠባችን ላይ ጀንበር ጠልቃ አታውቅም።

 • ምንም እንኳን ስያሜው “ጥበቡ” ቢልም የመጽሐፉ በርካታ ገጾች ስለእሱ አያወሩም፤ እንደውም ስለራስሽ የጻፍሽው የሚመስላቸው ሰዎች አሉ።

እንግዲህ ይሄ መጽሐፍ አውቶግራፊ እንዳንለው ጥበቡ ስለራሱ አልጻፈውም፤ ባዮግራፊም እንዳንለው ሙሉ በሙሉ ስለእርሱ ብቻ የሚያወራ መጽሐፍ አይደለም። ʻይሄ መጽሐፍ ምን ዐይነት ነው?ʼ ብለው ለሚጠይቁኝ ወገኖች፣ ከሁለቱም የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች የተዳቀለ (hybrid) ነው። አዲስ ዐይነት አጻጻፍ እንደሆነም አላውቅም። በአንድ ካታጎሪ ውስጥ ልከተው አልቻልኩም። ምክንያቱም ጥበቡ ማለት እኔ ነኝ፤ እኔ ማለት ጥበቡ ነው። የእርሱን ታሪክ ከእኔ ነጥዬ አላየውም፤ የእኔን ታሪክ ከእርሱ ነጥዬ አላየውም። ስለዚህ ታሪካችንን ሙሉ የሚያደርገው የሁለታችንም፣ የልጆቻችንም፣ አብረውን ደግሞ በዚህ ታሪክ ውስጥ የተጓዙትን ሰዎች ጭምር መተረክ ነው።

 • በመጽሐፉ ያሉ ታሪኮች ምንም እንኳን ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ቢሆንም፣ ኹነቶቹ የአሁን ጊዜ እንዲመስሉ ተደርገው ቀርበዋል። ምናልባት በሥነ ጽሑፍ ወይም በጋዜጠኛነት ሙያ መሥራትሽ ለዚህ ጠቅሞሽ ይሆን?

ሊሆን ይችላል። ለነገሩ የጋዜጠኝነት ኮርስ የወሰድኩት ለአንድ ዓመት ነው፤ የብዙ ዓመት የጋዜጠኝነት ልምድም የለኝም። የሠራሁት ለጥቂት ጊዜ ነው፤ እሱም በመጀመሪያ የፕሮግራም አዘጋጅነት ቀጥሎም የዜና አዘጋጅነት ነው እንጂ በሪፖርተርነት አልሠራሁም። ነገር ግን የሥነ ጽሑፉ ነገር ከልጅነቴም እግዚአብሔር በውስጤ ያስቀመጠው ነገር ነው።

 • “የምድረ በዳው እረኛ” የሚለው ርእስ ለምን ተመረጠ?

ይህን ርእስ እኔ አልነበርኩም የመረጥኩት፤ አብረውት በምርኮ ዐሥራ አንድ ዓመት ከቆዩት ሰዎች መካከል የተሰጠ ርእስ ነው። በተለይ፣ “የእኛ ሰው በሶማሊያ እስር ቤት” የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፈው አቶ ጥላሁን አትሬሶ በመጽሐፉ ላይ ገልጾታል። ʻዶ/ር ጥበቡ፣ ሙሴ ለእስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ ከእግዚአብሔር እንደተሰጣቸው ሁሉ፣ ለእኛም በሕይወት ወደ ምድራችን እንድንገባ እግዚአብሔር የሰጠን እረኛ ነበረʼ ብሏል። እናም ʻየምድረ በዳው እረኛʼ የሚለው ሐሳብ የመጣው ከምርኮ ተመላሽ ወገኖች ሲሆን፣ ሐሳቡም ተገቢ ስለሆነ አድርጌዋለሁ። “ጥበቡ” የሚለውን የሰጠሁት ግን የባለቤቴ ስም ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ጥበብ በታሪኩ ውስጥ ስለሚታይ ጭምር ነው፤ ሰም እና ወርቅ ዐይነት ስለሆነ ያንን መርጫለሁ።

 • ዶ/ር ጥበቡ ከተደራራቢ የሥራ ኀላፊነቶች ባሻገር ለመንፈሳዊ ሕይወቱ በቂ ጊዜ በመሰጠት ሚዛናዊ ሕይወት ይኖር እንደ ነበር በመጽሐፉ ተገልጿል። የጊዜ አጠቃቀሙ ምን ይመስል ነበር?

በእስር አብረውት ያሳለፉ ወገኖች የእንቅልፍ ሰዓቱ በጣም ጥቂት እንደ ነበር ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ የእንቅልፉ ሰዓቱ ቢበዛ አራት ወይም ሦስት ነበር። ይህንንም እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋ አዘውትሮ ያደርግ ስለ ነበር ሚዛናዊ በሆነ ሕይወት ሙያዊ ግዴታውን ከእግዚአብሔር ፊት ሳይርቅ ይከውን ነበር። ይህ ከወጣትነቱ ጀምሮ የተለማመደው ነበር። ለጸሎት እና ለቃሉ ሁልጊዜም ቅድሚያ ይሰጣል። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ካለው እሱን ያስቀድማል። ይህንን ካስቀደመ ሌሎቹ ሁሉ ቦታ ቦታ እንሚይዙለት የሚያምን ሰው ነው፤ ይህ ሲሆን ደግሞ አይቻለሁ።

 • ወደፊት ከመጽሐፉ ባሻገር የዶ/ር ጥበቡን የሕይወት አሻራ በምን መልኩ ለትውልድ ለማስላለፍ ዐስበሻል?

እንግዲህ ጥበቡ ቀድሞን ሄደ እንጂ ከድሮም ጀምሮ አንድ ቀን ወደ ሀገራችን ገብተን ሁለንተናዊ አገልግሎት የምንሰጠበት ነገር እናደርጋለን እያለን እናስብ፣ እንጸልይም ነበር። ጥበቡ ጡረታ ሲወጣ ወደ አገራችን ከመመለስ ውጪ ሌላ ምንም ዓላማ አልነበረንም። ለሕዝባችን አቅማችን የፈቀደውን ለማድረግ እናስብ ነበር። እግዚአብሔር ገና ተማሪ እያለ ያለማምደው የነበረውና ቤተ ሰቡንም የወረሰው ይሄ ሁለንተናዊ አገልግሎት የመስጠቱ ነገር ላይ ነበር ትኩረታችን የነበረው። ምንም እንኳን ጥበቡ ዛሬ አብሮን ባይኖርም ራእዩ አብሮን አለና ያንን ለመፈጸም እንፈልጋለን። ይህም መጽሐፍ ወደዚህ አገልግሎት ለመግባት እንዲያግዘን ነው የምናስበው።

ከዚህ ሌላ ብዙ ሰዎች መጽሐፉ በዶክመንተሪ ወይም በፊልም መልክ ቢሠራ ብለው ጠይቀውናል፤ እኛም ስናስበውና ስንጸልይበትም የቆየ ነገር ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህንንም ለማድረግ እንፈልጋለን። ታሪኩ የአንድ መንፈሳዊ ሰው ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአገርም ታሪክ ነውና በዚህም መልክ ለሕዝብ እንዲቀርብ እናስባለን። እንግዲህ እግዚአብሔር ሁሉን በጊዜው ያሳካል።

Selamawit Admasu

ሊላሽቅ የሚገባው የኢትዮጵያውያን ልቅ ጀብዱ

የታሪክ አጥኚው አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፉ፣ ኢትዮጵያዊነት “ጨዋነት” ብቻ አለመሆኑን፤ ይልቁን ጸያፍ የሆነ “የጀብደኝነት” አመለካከት ከማንነታችን ጋር የተጋባ መሆኑን ከታሪካችንና ከአሁኑ ሁናቴ ጋር ያዛምደዋል። “ልቅ” የተባለው ይህ “ጀብደኝነት” በቶሎ ካልላሸቀ ያጠፋናል ይላል ዶ/ር አፈወርቅ።

ተጨማሪ ያንብቡ

የማንነት ስምምነት ካልቀደመ እየሠሩ ማፍረስ ይቀጥላል

አገራችንን በዚህ ጊዜ እየተፈታተናት ያለው ጉልሕ ችግር፣ በማንነት ላይ ያሉ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ስላላገኙ ነው፤ ይህንንም በተገቢው መንገድ እስካልፈታን ድረስ ውጥረቶች መቀጠላቸው አይቀርም ይላል በሰላም ግንባትና በእርቅ ላይ ተመራማሪ የሆነው ሰሎሞን ጥላሁን።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች:- (The 70 Resolutions of Jonathan Edwards)

በዐሥራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን፣ በምድረ አሜሪካ ለተነሣው መንፈሳዊ መነቃቃት ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ እንዳደረገ የሚነገርለት ጆናታን ኤድዋርድስ፣ በግል ሕይወቱ ለመተግበር የቆረጠባቸውን ውሳኔዎቹን አማረ ታቦር፣ “ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች” በሚል ወደ አማርኛ የመለሰው እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.