[the_ad_group id=”107″]

" 'መንፈስ ቅዱስ ካልተናገረ እኔ የምነግራችሁ አንዳች የለም’ ብሎ ጉባኤውን ማሰናበት ጤናማነት ነው"

መጋቢ መስፍን ሙሉጌታ በኮልፌ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በመጋቢነት ያገለግላሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ዘወትር ዓርብ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታዘጋጀው “የፈውስና ነጻ የማውጣት” መርሓ ግብር ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህ ዘመን በፈውስ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ያገልግላሉ ከሚባሉት አገልጋዮች መካከል የመጋቢ መስፍን ስም ቀድሞ ይነሣል። ሕንጸት ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ስጦታዎቹ እና አጠቃቀሙ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው ስለሚነሡ ጉዳዮች ከመጋቢ መስፍን ሙሉጌታ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል። 


  • ሕንጸት፡- የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በተለይም ደግሞ ፈውስ ድንቅና ታምራትን በመሰሉት ላይ ብዙዎች ግራ የሚጋቡበት ጊዜ ላይ እንደደረስን ይታያል። ብዙ ምእመናን እውነተኛውን ከሐሰተኛው የሚለዩበት ተግባራዊ መንገድ ያላቸው ስለ መሆኑ ርግጠኛ መሆን አንችልም። አንተ በዚህ አገልግሎት ውስጥ እንዳለ ሰው አሁን የሚታየው ውዥንብር መንስኤው ምንድን ነው ትላለህ?

መጋቢ መስፍን:- በእኔ አተያይ አሁን ያለው መደናበርና ግራ መጋባት ዝም ብሎ የመጣ አይመስለኝም። በምድራችን ታላቅ ስደት በነበረበትና ቅዱሳን በኅቡዕ በመደራጀት ጌታን በሚያመልኩበት በዚያ የኮምኒዝም ዘመን መንፈስ ቅዱስ ብዙ ድንቅና ታምራት ሲሠራ አይተናል። በዚህ አገልግሎት ብዙዎች ሲጽናኑና ሲፈወሱ፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩ የወንጌል ብርሃን በርቶላቸው ለሌሎች መዳን ምክንያት ሲሆኑ የማየት ዕድል አጋጥሞናል። የሚገርምህ በዚያ ዘመን የአማኙ ትኩረት የተሰቀለው፣ የሞተው፣ ከሞት የተነሣው፣ በአብ ቀኝ ባለውና ዳግመኛ ተመልሶ በሚመጣው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር። ማንም ሆን ብሎ ድንቅና ታምራትን በዚህ ዘመን እንደሚደረገው ሲያሳድድ አትመለከትም። ʻታድያ አሁን ያለው ውዥንብርና ግራ መጋባት በጸጋ ስጦታዎቹ ላይ እንዴት ሊታይ ቻለ?ʼ ላልከኝ የአብዛኛው ቅዱሳን ዐይን ከመስቀሉ ላይ ተነሥቶ ድንቅና ታምራት ላይ በማተኮሩ፣ አገልጋዮቹም የተሰጣቸውን የጸጋ ስጦታ ለወንጌል ማስፋፊያና ለቅዱሳን መታነጽ ከማድረግ ይልቅ የራሳቸውን ስም ማስጠሪያና ኑሯቸውን መደጎምያ ስላደረጉት፣ ዐይን ያወጣ ስሕተት ሲሠሩ ታስተውላለህ። ከዚህም የተነሣ እውነተኛው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በሐሰተኞች እየተሸፈነ በመምጣቱ መደናበሩ የመጣ ይመስለኛል። እንደዛም ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሌም ቅሬታዎች እንዳልጠፉ ሁሉ በእውነትና በተለወጠ ማንነት ጌታን የሚያመልኩ ምእመናንና አገልጋዮች ዛሬም አሉ ብዬ አጽንዖት መስጠት እፈልጋለሁ.።

  • ሕንጸት፡- ሰዎች ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባልሆነ መንፈስ ሆነው ‘በጌታ በኢየሱስ ስም’ እያሉ ድንቅና ታምራትን ማድረግ ይችላሉ ብለህ ታምናለህ? ከሆነስ ምእመናን እንደነዚህ ያሉትን ሐሳውያን በምን መንገድ ይለዩአቸው?

መጋቢ መስፍን፡- እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች እንደሚነሡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ስለተናገረ ዛሬ መኖራቸው እምብዛም አይደንቀኝም። ጌታ ኢየሱስ በተለምዶ የተራራው ስብከት በምንለው በማቴዎስ ምዕ 7 ከቁጥር 20-23 ላይ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ʻጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይʼ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች ʻጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?ʼ ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፣ ʻከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዐመፀኞች ከእኔ ራቁ’ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” በማለት አስተምሯል። እነዚህ ሰዎች እኮ የኢየሱስን ስም ጠርተው ነው ትንቢት የተናገሩት፣ አጋንንትን ያወጡት፣ ብዙ ታምራትን ያደረጉት። በጣም የሚያስደነግጠኝ ጌታ ኢየሱስ በመጨረሻው የፍርድ ወንበር ላይ ሲሆን እነዚህን ሰዎች ʻከቶ አላውቃችሁም እናንተ ዐመፀኞች ከእኔ ራቁʼ አይደለም የሚላቸው፤ ይልቁንም “ከቶ አላወቅኋችሁም” ነው የሚላቸው። ስለዚህ ትንቢት መናገር፣ አጋንንትን ማስወጣትና ታምራትን ማድረግ እውነተኛ አገልጋይ ለመባል ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ለመታወቅ ዋስትና አይደለም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ምን ያህል አስደንጋጭ ነው።

ታዲያ በኢየሱስ ሳይታወቁ “በአገልግሎታቸው” የታወቁትን ሐሳውያን ምእመናን ሊለዩዋቸው የሚገባው ከፍሬያቸው ነው፤ ዛፍ ከፍሬው እንደሚታወቀው ማለት ነው። ከላይ ባነሣሁት ክፍል ላይ ጌታ ኢየሱስ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ” የሚያደርግ ብሏል። ቀዳሚ የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ሰዎች በአንድ ልጁ አምነው የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ ነው። አማኞች ኢየሱስ ክርስቶስን እየታዘዙና እያመለኩ እንዲኖሩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ʻየእነዚህ ሐሳውያን ፈቃድ ታድያ ምንድን ነው?ʼ ብለን መጠየቅ ከቻልን ለንዋይና ለዚህ ዓለም ተድላ መኖር፣ የክርስቶስን ስም ማላቅ ሳይሆን የእነሱ ስም እንደ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲወጣ መለከት ማስነፋት የሚወዱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች መለያቸው የሚጠፋ ዝና፣ ክብር፣ ገንዘብን መውደድና የሥነ ምግባር ውድቀት ነው። የመንፈስ ፍሬ ሳይሆን የሥጋ ፍሬ ጎልቶ ይታይባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው እንዳለው ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች፣ በአንደበታቸው ግን ማር የሚያንጠባጥቡ የሚመስሉ ናቸው። ሆኖም ትምህርታቸው በመርዝ የተለወሰ ገዳይ ነው። ክርስቶስ ተኮር ባለመሆናቸው ምእመናን በቃሉ ብርሃን አንጥረው በመመርመር ሊለዩአቸው ይገባል እላለሁ።

  • ሕንጸት፡- በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በቀጣይነት ሲዘልቁ አይታዩም ማለት ይቻላል። እዚህ ቦታ እንዲህ ሆነ፤ ሌላ ቦታ እንዲህ ሆነ ወይም ‘እገሌ የሚባል አገልጋይ ተነሣ’ ሲባል ነው የሚደመጠው። እንደ አንተ እምነት ብልጭ ድርግም የሚለው አገልግሎት ምክንያቱ ምንድን ነው?

መጋቢ መስፍን፡- መቼም ይህ ሁኔታ በራሱ ጤናማነት አለው ብዩ አላምንም። የኢትዮጵያ የኤሌክቲሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን አንድ ወቅት መብራትን በፈረቃ ያከፋፍል እንደ ነበር ብዙዎቻችን እናስታውሳለን ብዬ ዐስባለሁ። ʻባለ ሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለምን ይሄንን ሊያደርግ ቻለ?ʼ ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ የኀይል እጥረት ስላጋጠመው ነው የሚል ይሆናል። ይሄ የዚህኛው ዓለም አሠራር ሊሆን ይችላል። ወደ መንፈሳዊው ዓለም ስንመጣ ግን መንፈስ ቅዱስ ሁሉን በሁሉ መግዛት የሚችል አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ የጸጋ ስጦታዎችን ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ አይደክምም፤ የኀይል እጥረትም አያገኘውም፤ እርሱ ሁሉን ቻይ ነውና። 

ደግሞም መንፈስ ቅዱስ እንደሚገባ ለመሥራት የሰዎችን ፈቃድ ይፈልጋል። ሰይጣን ነው የሰዎችን ፈቃድ ሳይጠብቅ በማስገደድ ማድረግ የሚፈልገውን የሚያደርግ። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን የጸጋ ስጦታዎች ጠብቃ በዘላቂነት እንድትቀጥል ካስፈለገ እንደ ኤሌክትሪክ ኀይል ባለ ሥልጣን የኀይል እጥረት ሊያጋጥማት አይገባም። ይሄ ማለት በዚህ አገልግሎት ውስጥ የሚያገለግሉ ሰዎች ዕለት ዕለት የመንፈስ ቅዱስን ኀይል መሞላት ይጠብቅባቸዋል ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ፈቃዱን እንዲገልጥላቸው ዘወትር ፊቱን መፈለግ፣ መንፈስ ቅዱስን ከሚያሳዘን አስጸያፊ ልምምድ በመለየት በቅድስና ሕይወት መመላለስ ይገባል። እንደዚህ ማለት ግን ከኀጢአት የጸዳና እንከን የሌለበት ፍጹም ሕይወት መኖር ማለት ሳይሆን፣ ፈሪሓ እግዚአብሔር ያለውን ኑሮ በመኖር በንሰሓ መመላለስ ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ወስጥ መለያየት፣ ቡድንተኛነትና ዘረኝነት መንገሥ ከጀመረ መንፈስ ቅዱስ ለመሥራት ይቸገራል። በርግጥ ይህ የሚሆነው ባሕርይው ስለማይፈቅድለት እንጂ መሥራት ስለሚያቅተው አይደለም። ስለዚህ እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን እንዲቀጥሉ ካስፈለገ ከመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ጋር መስማማትና የቅድስና ሕይወት ጉልሕ ሚና ይጫወታሉ ብዬ አምናለሁ። 

ሌላው እግዚአብሔር ተጠቀመብኝ የሚል ሰው ክብሩን መሻማት ሲጀምር፣ ቤተ ክርስቲያንም ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር መውሰድ ስትጀምር የጸጋ ስጦታውን የሰጠ እግዚአብሔር መልሶ ሊወስደው ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ብዬ ዐስባለሁ። ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለአገልጋይ የተሠመረ አንድ መሥመር አለ፤ ክብሩን አለመንካት። ይሄንን ባደረግን ጊዜ ውርደታችን እየፈጠነ ይሄዳል። የጥንት መዝሙሮችን በምናዳምጥበት ጊዜ የትኩረት አቅጣቻቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር። መንፈስ ቅዱስም እኮ የሚያከብረው ክርስቶስን ነው። አሁን አሁን ግን እያከበርን ያለው ክርስቶስን ሳይሆን ራሳችንን ነው። ይሄ ደግሞ ትልቅ በደል ነው። እኛ የክብሩ ተጠቃሚዎች እንጂ የክብሩ ተጋሪዎች አይደለንም፤ እግዚአብሔር አንዳች ስለ ጎደለው በእኛ አይገለገልምና። 

  • ሕንጸት፡- አንድ በፈውስ፣ በታምራት አገልገሎት የሚያገለግል ሰው በሚያስተላልፈው መልእክት ወይም በአገልግሎቱ ስሕተት ፈጽሞ ሲገኝ ምን ያድርግ? የቤተ ክርሰቲያን መሪዎችስ ስሕተት የሚፈጽሙ አገልጋዮችን እንዴት ባለ መንገድ መያዝ አለባቸው ትላለህ? 

መጋቢ መስፍን፡- መቼም በሐሰተኛና ስሕተት በሚሠራ መካከል ልዩነት አለ ብዬ ዐስባለሁ። ሆን ብለው ሐሰትን ኑሯቸው ያደረጉ አገልጋዮች የመኖራቸውን ያህል፣ የስሜትና የሥጋ ሐሳብ ተቀላቅሎባቸው የሚሳሳቱም አሉ። ይሄ አገልግሎት በራሱ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ አገልግሎት ነው። አንዳንዴ እውነተኛ ነገር ሊገለጥልህ ይችላል፤ እውነተኛውን ትርጉም ካልተረዳህ እስክትረዳው ድረስ ዝም ማለት ሲኖርብህ፣ ስሜትህ እንደነዳህ ለመተረጎም ብትሞክር መንፈስ ቅዱስ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ሐሳብ አትረዳምና ልትስት ትችላለህ። እንደዛም ሆኖ ስሕተት የሚሠሩ ሰዎች ኀጢአት ሠርተዋልና ንሰሓ ሊገቡ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን ኀላፊነትን ስትሰጥ ከተጠያቂነት ጋር ልትሰጥ ይገባል ብዬ አምናለሁ። ሐሰትን ግን ኑሯቸው ባደረጉ ሰዎች ላይ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዐት እርምጃ ልትወስድባቸው ይገባል። እንደዚህ የሚደረግበት ዐላማ ደግሞ ስሑት የሆነውን ለማረምና ሌሎችን ለማስተማር፣ የተሳሳተውም ከስሕተቱ ተምሮ የተሻለ ሰው እንዲሆን ለመርዳት ነው። 

  • ሕንጸት፡- ትክክለኛ የጸጋ ስጦታ አጠቃቀምን በተመለከተ እርምት እንዲወሰድ የሚናገሩ ሰዎች እንደ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ተቃዋሚዎች ተደርገው ሲወሰዱ ይስተዋላል። በዚህ አገልግሎት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊወቀሱ፣ ሊታረሙ አይችሉም እንዴ?

መጋቢ መስፍን፡- አንተ እንዳልከው እንደዚህ ዐይነቱ መረዳት ያላቸው ሰዎች ጥቂት የሚባሉ አይደለም፤ ነገር ግን ሚዛኑን የጠበቀ ዕሳቤ ነው ለማለት እቸገራለሁ። ስሕተትን ማረም እኮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። በአዲስ ኪዳን ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲስት ሐዋርያው ጳውሎስ ፊት ለፊት ተቃውሞታል፤ ምክንያቱም የሐዋርያው ጴጥሮስ አካሄድ ሰዎች ድነትን ከሚያገኙበት ጤናማው የወንጌል አስተምህሮ ጋር የሚጣረስና ማመቻመች የተስተዋለበት ስለ ነበረ ነው። ልብ በል፤ ሐዋርያው ሲስት ዝም ተብሎ አልታለፈም፤ ፊት ለፊት ተገሰጸ እንጂ። ከዚህ የምንረዳው ልዩ የሆነ አምላክ አለን እንጂ ልዩ የሆነ የማይሳሳት ሰው የለንም። ስለሆነም እርምት የሚያደርጉ ሰዎችን በጭፍኑ በመፈረጅ የመንፈስ ቅዱስ ተቃዋሚዎች አድርጎ ማቅረብ አንድም ከእውቀት ማነስ፣ አንድም በጭፍን ለመፍረድ ካለን ልምድ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ሌላው እርምት የሚሰጡ ሰዎችም ተቀዳሚ ዐላማቸው ሊሆን የሚገባው አገልጋዮቹን ከመቅረጽና ከማቅናት አንጻር እንጂ፣ የበለጠ ተጎድተው ከአገልግሎትና ከቅዱሳን ኅብረት እንዲጠፉ የሚያደርግ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብዬ በጽኑ አምናለሁ።

  • ሕንጸት፡- በመሠረቱ “የፈውስ ፕሮግራም” ወይም “ትንቢታዊ የጉብኝት ዕለት” ብሎ ቀን መቅጠር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይሆናል? ከሆነስ ቤተ ክርስቲያን “የፈውስ ፕሮግራም” ወይም “ትንቢታዊ አገልግሎት” ብላ ሕዝብ ጠርታ በሚጸለይበት መርሓ ግብር ላይ የሚጠበቀው ፈውስ ወይም ትንቢት ሳይመጣ ቢቀር ʻዛሬ እግዚአብሔር ዝም ብሏልʼ የማለት ድፍረት አያስፈልግም ትላለህ?

መጋቢ መስፍን፡- እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲነሣ እሰማለሁ፤ አግባብነት ያለው ጥያቄም ነው እላለሁ። ቀኖች ሁሉ የእግዚአብሔር ናቸው። መንፈስ ቅዱስን በጊዜና በቀን ልንገድበው አይገባም፤ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ መቼና እንዴት ፈቃዱን በሰዎች ሕይወት ላይ መፈጸም እንዳለበት ያውቃልና። በሌላው ጎኑ መጽሐፍ ቅዱሳችን በግልጽ እንደሚያስተምረው የጸጋ ስጦታዎች ልዩ ልዩ ናቸው። ሁሉ ትንቢት የመናገር፣ ሁሉ የፈውስ፣ ሁሉ ታምራት የማድረግ ስጦታ አልተሰጣቸውም፤ ይልቁንም ለእያንዳንዱ የተለያየ የጸጋ ስጦታ ተሰጥቷል እንጂ። ታድያ እዚህ ላይ ልንገነዘብ የሚገባው ነገር ቢኖር፣ ሁሉ የመፈወስ ስጦታ ከሌላቸው፣ ሁሉ ታምራት የማድረግ ስጦታ ካልተሰጣቸው በዚህ ስጦታ የሚያገለግሉ ሰዎች ሊወስዷቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች አሉ። 

አገልጋዮቹ ራሳቸው ሰው እንደ መሆናቸው ውስኖች ናቸው። እያንዳንዱ የታመመ በሽተኛ እንዲፈወስ፣ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ሄዶ መጸለይ የሚወስደውን ጊዜ ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባቸዋል። ይሄ ማለት ግን ሰው ቤት ሄዶ መጸለዩ አግባብነት የለውም እያልኩ አይደለም። ሌላው በየቀኑ የፈውስ ፕሮግራም አለ ብለው አገልግሎቱን ቢጀምሩ ምን ያህል ማዝለቅ ይችላሉ። አገልግሎቱ በራሱ ጊዜ እንድንወስድ፣ እንድንጾም ቃሉን እንድናጠና መንፈስ ቅዱስን እንድንሰማ የሚያስገድደን አይሆንም ወይ? በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ቀንን የምትቀጥረው መንፈስ ቅዱስ በዚህ ቀን ብቻ ነው የሚሠራው ለማለት ፈልጋ ሳይሆን፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አንጻርና አገልጋዮቹም ተገቢውን የዝግጅት ጊዜ እንዲኖራቸው ከማድረግም አንጻር ጭምር ነው። አገልጋዮቹም የሥጋ ድካም ሊያጋጥማቸው እንደሚገባ ማሰብ ተገቢ ነው እላለሁ። 

ሌላው አገልጋዮች ልንወስደው የሚገባ ነገር ቢኖር እኛ የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ አስፈጻሚዎች እንጂ አመንጪዎች አይደለንም። እኛ ሕዝብ በተሰበሰበበት መንፈስ ቅዱስ ዝም ካለ እኛም ዝም ልንል ይገባናል። እሱ ያልተናገረውን መናገር ለእኛ በደል ነው የሚሆነው፤ ሕዝቡንም አይጠቅመውም። ስለሆነም መንፈስ ቅዱስ ካልተናገረ ʻእኔ የምነግራችሁ አንዳች የለምʼ ብሎ ጉባኤውን ማሰናበት ጤናማነት ነው ብዬ አምናለሁ። እንደዚህም ስልህ ወደዚህ መረዳት መጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ሥጋዊ የሆነ አስተሳሰብን መጨቆን ስለሚጠይቅ ቀላል ነገር ነው እያልኩህ አይደለም። መሆን ያለበት ግን ይሄና ይሄ ብቻ ነውና የግድ ልናደርገው ይገባል።

  • ሕንጸት፡- በፈውስ፣ በትንቢትና በታምራት አገልግሎት ላይ የሚታዩት ችግሮች መፍትሔ ካልተፈለገላቸው በአገልግሎቱ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ምን ሊሆን ይችላል?

መጋቢ መስፍን፡- አማኞች የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸው ይቀርና ሰዎችን የሚከተሉ ከርታቶች ይሆናሉ፤ አማኞች በእውነተኛው የጸጋ ስጦታዎች ላይ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው፣ ብሎም ‘በዚህ ዘመን ስጦታዎቹ መሥራት አቁመዋል’ ወደሚል የተሳሳተ መረዳት ውስጥ እንዲገቡ ይሆናሉ። አገልጋዮቹ የጸጋ ስጦታዎቹን ወንጌልን ለመስበክና ቅዱሳንን ለማነጽ ከማዋል ይልቅ፣ ምድራዊ ኑሯቸውን ለመለወጫነት፣ በሥነ ምግባር ውድቀት ውስጥ በመዘፈቅ ለክርስቶስ ስም መሰደቢያና ቤተ ክርስቲያን በተቃዋሚዎችዋ ፊት አንገቷን ደፍታ እንድትሄድ ሊያደርጋት ይችላል። በአጠቃላይ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ጎን ዘርዝረህ የምትጨርሰው አይደለም፤ ይሄ ደግሞ እጅግ ልብን የሚሰብር ነው። 

  • ሕንጸት፡- በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጡ የእንግዳ ትምህርትና ልምምድ አስፋፊዎች በተመለከተ በአማኞች መካከል መከፋፈሎች ታይቷል። ቤተ ክርስቲያን ከውጭ የሚመጡ አገልጋዮችን በተመለከተ ልትወስደው የሚገባው ጥንቃቄ ምን ዐይነት መሆን አለበት ትላለህ?

መጋቢ መስፍን፡- የመጀመርያው መወሰድ የሚገባው ጥንቃቄ ቢኖር ቤተ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥታ መሥራት ይጠበቅባታል የሚለው ነው። እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ያላት ቤተ ክርስቲያን ስንዴውን ከእንክርዳዱና ከገለባው መለየት የሚችሉ ጠንካራና ሥር የሰደዱ የክርስቶስ ተከታዮችን ማፍራት ትችላለች። ለዚህ ደግሞ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ጤናማ የሆነውን የነገረ መለኮትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን ትምህርት በማስተማር ምእመናን ክርስቶስን መስለው እንዲያድጉ ማድረግ ቤተ ክርስቲያን የግድ ልትከተለው የሚገባ መርሕ ነው። ከዚህም የተነሣ ልዩ የሆነ የትምህርት ንፋስና ልዩ ልምምድ በተከሰተ ጊዜ ምእመናን ያለምንም መናወጥ ባሉበት ፀንተው እንዲቆሙ አቅምን ያገኛሉ። ሌላው ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን አስተምህሮና ልምምድ አስቀድሞ በማጥናት ለምእመናን በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመጠበቅ አንጻር የሚጫወተው ሚና ታላቅ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ጠንካራ ሥራ ሊሠሩ ይገባል እላለሁ።

  • ሕንጸት፡- ምእመናንን በሐሰት ትንቢት፣ እውነተኛ ባልሆነ ፈውስ እና ሌሎችም ማደናገርያዎች እያታለሉ ሕዝብ ስለሚያስጨንቁ ሰዎች የኮልፌና አካባቢው የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ይታያል፤ ከአንድም ሁለት ጊዜ አቋማችሁን ለአብያተ ክርስቲያናት ማሳወቃችሁም ይታወሳል። የዚህ ኅብረት ሰብሳቢ እንደ መሆንህ መጠን ኅብረቱ ምን እያደረገ እንደ ሆነ ብትነግረን?

መጋቢ መስፍን፡- የኮልፌና የአካባቢው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በሥሩ ዐሥራ ሦስት ቤተ እምነቶችን የያዘ ኅብረት ነው። ከየቤተ እምነቱ የተወከልን አንዳንድ መሪዎች በሳምንት አንድ ቀን ጠዋት ጠዋት እየተገናኘን የመጸለይ፣ የመመካከር፣ ልምድ የመለዋወጥና አብሮ የመሥራትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አካሄድን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን። አንተ እንዳልከው የተለያዩ የስሕተት አስተምህሮዎችና ልምምዶች ብቅ በሚሉበት ጊዜ በኅብረቱ ውስጥ አባል በሆኑ የሥነ መለኮት አጥኚዎች ጥልቅ የሆነ ዐውደ ጥናት በርእሰ ጉዳዩ ላይ ከሥር መሠረቱ እንዲዘጋጅ ካደረግን በኋላ ምእመናን ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡና ለስሕትት አስተምህሮ እንዳይጋለጡ መረጃዎችን በጋራ እንሰጣለን፤ እናስተምራለን። 

በኅብረቱ ሥር ላሉ የተለያዩ አገልጋዮች ትምህርቶችን፣ ሥልጠናዎችን የምናዘጋጅ ሲሆን፣ በየዓመቱ ለሃያ አንድ ቀናት በጾምና በጸሎት ለምድራችንና ለአፍሪካ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ጉብኝት ትኩረት ሰጥተን እንጸልያለን። ለአርባ ቀን በጾምና በጸሎት የአምላካችንን ፊት የፈለግንበት ጊዜ እንደነበረም አስታውሳለሁ። ኅብረቱ በዚህ ዓመት አንድ የጀማ ስብከተ ወንጌል ከአንድ መንፈሳዊ አገልግሎት ጋር በጋራ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጨመሩበት፣ ከተለያዩ እስራትና ደዌ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነጻ የወጡበትና ምእመናን የተጽናኑበት ጊዜ ነበረን። በተሠራው ሥራ ሁሉ ክብር ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁን! በዚህ አጋጣሚ በኮልፌና አካባቢው ያሉ አገልጋዮችንና ምእመናን ለኅብረቱ ጥንካሬና ለእግዚአብሔር መንግሥት በትጋት እየሠሩ በመሆናቸው እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ ማለት እፈልጋለሁ።

  • ሕንጸት:- እናመሰግናለን!

Mikyas Belay

ሚክያስ በላይ የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር መሥራችና ዳይሬክተር ሲሆን፣ የሕንጸት ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ነው። በኢቫንጄሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ በሥነ መለከት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ጥናት የማስተርስ ዲግሪ ሠርቷል።

Share this article:

የአምልኮ ጥያቄ

ጥቂት የማይባሉ አማኞች “አምልኮ” የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ የሚረዱት በዝማሬ ውስጥ ነው። ይህ ጠባብ ትርጓሜ ደግሞ በአማኞች ሕይወት ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ ማሳደሩ አልቀረም። ለመሆኑ አምልኮና ግብር ያላቸው ዝምድና ምንድን ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ

ፍቅርን የመግለጫ መንገዶች

በፍቅር የተጋመዱ ጥንዶች ትሥሥራቸውን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ማንሣታቸው አይቀርም። አንዳንዱ ጥያቄ የሚሰነዘረው ለአፍቃሪው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ መልስ ከተፈቃሪው ይሻል። ከሚነሡት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው “የፍቅር ጥያቄ” ነው። ራሳችንን፣ “በርግጥ አፈቅራታለሁኝ?”፣ “እሷስ ከልቧ ታፈቅረኛለች?” እንላለን። መነሾው ቢለያይም፣ በደስታ መኻል ስንቅር የሚል ጥያቄ እንደ መሆኑ ያስጠላል፤ ያስፈራልም። ሲ. ኤስ. ሊዊስም፣ “ፍቅር በሕይወታችን ካለ ጽኑና ቀጣይ ደስታ ከዐሥሩ የዘጠኙን እጅ ድርሻ ይወስዳል” እንደ ማለቱ ጥያቄው አይናቅም።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.