[the_ad_group id=”107″]

እኛ ከእግዚአብሔር ጋር የንግድ ስምምነት የለንም

መጋቢ ጻድቁ አብዶ፣ በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ከሚባሉት አገልጋዮች መካከል የሚጠቀሱና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ለስምንት ዓመታትም የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በትምህርት ዝግጅታቸውም፣ ከኢስት አፍሪካ ስኩል ኦፍ ቲዮሎጂ (East Africa School of Theology) በነገረ መለኮት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በድኅረ ምረቃ መርሓ ግብር በሥልታዊ ነገረ መለኮት ጥናት (MTh in Systmatic Theology) በኢትዮጵያ የሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት (EGST) ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ሥነ መለኮት ሴሚናሪየም ፕሪንሲፓል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሚክያስ በላይ ከጴንጤቆስጤ አስተምህሮና ልምምድ ጋር በተያያዘ ከሚነሡ የስሕተት ትምህርቶች አኳያ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለብዙዎች መነጋገሪያ ስለሆኑት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽሪ  አነጋግሯቸዋል፡፡


  • ሕንጸት፡- የጴንጤቆስጤ እምነትና ለምምድ ለስሕተት ትምህርት ተጋላጭ የሚሆንባቸው አጋጣሚ የሰፋ እንደ ሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ለምን የሆነ ይመስልዎታል?

መጋቢ ጻድቁ፡- በመሠረቱ የትኛውም እምነት ለስሕተት ትምህርት የተጋለጠ ነው፡፡ የጴንጤቆስጤ አስተምህሮ ያላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ መጽሐፉ እንደሚነግረን ከብሉይ ጀምሮ እስከ አዲስ ኪዳን ያለ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ ምእራፍ 2፥1 ላይ፡- “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤” ይላል፡፡ በብሉይ ኪዳንም፣ ኦሪት ዘዳግም ውስጥ ይመስለኛል፣ ሙሴ ʻእንደ እኔ ያለ ነቢይ እግዚአብሔር ያስነሣላችኋልʼ ብሎ በተናገረበት ዐውድ ውስጥ፣ ʻአንድ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ነኝ የሚል በመካከልህ ቢነሣና የተናገረው ካልሆነ የሐሰት ነቢይ ነውʼ ይላል፡፡ የተናገረው እውነት ሆኖ እንኳ ʻሌሎች አማልክትን እናምልክʼ ካለ አሳሳች ነው፤ ወይም ʻእግዚአብሔር ሊፈትንህ ነውና እንዳትከተለውʼ ይላል፡፡ ይሄ የሚያሳየን የተናገረው እውነት አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን እውነት ሆኖ ቢገኝ፣ ነገር ግን ከትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል አስተምህሮ የሚያፈነግጥ ከሆነም ስሕተት መሆኑን ነው፡፡

በርግጥ ጥያቄው በከፊል እውነትነት አለው፡፡ የቆዩት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም፣ ካቶሊካውያንና ኦርቶዶክሳውያን ለረጅም ዘመን የደረጀ አስተምህሮ ያላቸው መሆናቸውና ካህናቱ ወይም አገልጋዮች በአስተምህሮው በደንብ ስለሚቀረጹ፣ ሕዝቡም እነሱኑ ብቻ ስለሚሰማ ራሳቸውን ከስሕተት ትምህርት ለመጠበቅ የተሻለ ዕድል አላቸው፡፡ ወደ ወንጌላውያን ስትመጣ ግን፣ ʻአማኞች ሁሉ ካህናት ናቸውʼ የሚለው ከአግባብ በላይ ሲተረጎም፣ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲመሩ የሾማቸውን አገልጋዮች አለመስማት ወደዚህ ችግር ይወስዳል፡፡ በወንጌላውያኑ፣ ይልቁን ደግሞ በጴንጤቆስጤያውያኑ ʻሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ጸጋ አለው፤ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ስላለ፤ እኔም ገብቶኛል፤ አንተ ብቻ አይደለህም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለብህ፤ እኔም አለብኝ…ʼ ከሚል ሐሳብ ይነሣና አንዳንድ ጉዳዮችን በጥልቅ ሳይረዳ ʻእኔ እንደዚህ ነው የተረዳሁትʼ ብሎ እምቢ የማለት ነገር ይኖራል፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ላለመታዘዝም ሆነ ለስሕተት ይጋለጣል፡፡

አንዳንድ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ልምምድ ወይም በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን በሚፈልጉበት ጊዜ ʻለስሕተት የተጋለጥን እንሆናለንʼ ብለው ይፈራሉ፡፡ እንደሱ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አይደለም ለዚህ የሚያጋልጠን፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ እንጂ፣ ወደ ስሕተት የሚመራ መንፈስ አይደለም፡፡ እንደውም ሐሰትን ለመለየት የሚያስችል ዐቅም ያለው የጴንጤቆስጤ ልምምድ ባላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ የእግዚአብሔርን መንፈስና ስሜታቸውን፣ የእግዚአብሔርን መንፈስና የስሕተት የሆነውን መለየት አለባቸው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ʻመንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ግን ትንቢትን አትናቁʼ ብሎ ለተሰሎንቄ ሰዎች ይመክራል፡፡ ይህ የሚያሳየን ትክክለኛውን መርምረን እንድናውቅ ነው፡፡

እኛ የጥንት ጴንጤቆስጤያውያን (Classical Pentecostal) አስትምህሮን እንደሚያምኑ ሰዎች አንድ ሰው የሐሰት ትንቢት ከተናገረ ለሰውየው ምክር ይሰጠዋል፤ ʻአንተ ዝም ብለህ ነው፤ ትክክል አይደለህምʼ ይባላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያ ትንቢት ጉባኤውን የሚያበላሽ ከሆነ፣ ʻይሄ ትክክል ነው ብለን አንቀበልም፤ አናምንምʼ ተብሎ እዛው እርማት ይሰጣል፡፡ አሁን ግን ይህ ዐይነቱ የመሪነት ሚና ነው የቀረው፡፡ ʻእኔ መንፈሳዊ ወይም ነቢይ ስለሆንኩ እርማት ሊሰጠኝ አይችልምʼ የሚል ካለ፣ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 14፥37 ላይ፣ “ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍኩላችሁ ትእዛዝ የጌታ እንደ ሆነች ይወቅ” ይላል፡፡ ይህም ትእዛዝ፣ ሁሉም ነገር በሥርዐት ይሁን የሚለው ነው፡፡ ይህን አልቀበል የሚል ካለ ʻእናንተም አትወቁትʼ ይላል፡፡ በመሆኑም እረኞች ወይም አስተማሪዎች ይህንን በአጥቢያ ደረጃ ማረቅ አለባቸው፡፡ ይህንን በሚያደርጉ ጊዜ ጤናማ ምእመን ማደግ ይችላል ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን የጥንታውያን ጴንጤቆስጤ (Classical Pentecostal) አስተምህሮን ነው የምትቀበለው፡፡ “ቶፕ ኦፍ ካንሳስን”፣ “አሱዛ ስትሪትን” እና “የኬስዊክ”ን እንቅስቃሴ ያጣጣመ ዐይነት የእምነት አቋም ያላት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ በአብዛኛው ከ“አሴምብልስ ኦፍ ጎድ”ም ሆነ፣ ከ“ቸርች ኦፍ ጎድ” ጋር ሊሄድ የሚችል የእምነት አቋም ነው ያለን፡፡ በአደረጃጀትና በግንኙነት ወይም አገር በቀል መሆናችን የተለየ ቢያደርገንም፣ አስተምህሮታችን በአብዛኛው ከእነዚህ ትልልቆቹ የጴንጤቆስጤ ቤተ እምነቶች ጋር የሚጣጣምና የሚሄድ ነው፡፡

  • ሕንጸት፡- የጴንጤቆስጤ እምነትና ልምምድ በኢትዮጵያ ምድር እንዲስፋፋ የእርሶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዛው መጠን ደግሞ የስሕተት ትምህርቶችና ልምምዶች በተደጋጋሚ ያጠቋታል፡፡ አንዳንድ አገልጋዮችም “የእምነት እንቅስቃሴን” ሲለማመዱ ይስተዋላል፡፡

መጋቢ ጻድቁ፡- ሙሉ ወንጌል የጥንቱን የጴንጤቆስጤ አስትምህሮ የምትከተል ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ገልጫለሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን “የእምነት እንቅስቃሴ” ወይም “የበልጽግና ወንጌል” ተብሎ ከሚጠራው እንቅስቃሴ ፈጽሞ የተለየ ነች፡፡ በእኛ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት የተማሩ ወይም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች የሆኑት ይህንን ቢቀበሉም፣ ወደ ተለመደው አስተሳሰብ (popular view) ከሄድን ግን የካሪዝማቲክና የሦስተኛው ሞገድ (Third Wave) ተጽእኖ ከባድ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሙሉ ወንጌል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቤተ እምነቶች ላይ ተጽእኖውን ያሳረፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስንም ቢሆን፣ ቃለ ሕይወትንም ቢሆን የሚነካ ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች በእምነት እንቅስቃሴና በብልጽግና ወንጌል እንቅስቃሴ ተጽእኖ ውስጥ የወደቀ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያት አለው፡፡ በአብዛኛው ከነጻነት ወዲህ፣ ማለትም በደርግ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በድብቅ ትንቀሳቀስበት ከነበረው የመከራ ዘመን በኋላ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ነጻነት ከተረጋገጠ በኋላ ያደገ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ጉዳዮች ለብዙ ነገሮች እንደተጋለጠች ሁሉ፣ በእምነትም ከቀድሞው በተለየ ለብዙ አስተሳሰቦች መጋለጡ ተፈጥሯል፡፡

ከሥርዐት ለውጡ በኋላ እንደ እነ ጆን ሄካርትና የእነሱን አስተሳሰብ የሚቀበሉ ኢትዮጵያውያንም ከውጪ መጥተዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያኑ ሲመጡ፣ የነባር አብያተ ክርስቲያናትንና የመሪዎቹን ስም ማጥፋትና ማጣጣል ነው የጀመሩት፡፡ መሪን አጥላላህ ማለት ምእመኑን ለማግኘት ትችላለህ ማለት ነው፡፡ ቀላል ነው፡፡ የገላቲያን ሰዎች ከጳውሎስ ለመነጠልና አስተምህሮውን እንዳይቀበሉ ለማድረግ፣ የጳውሎስ ሐዋርያነት ላይ ብቻ ጥያቄ ማንሣት በቂ ነበር፡፡ ደርሶ አንበሳ መሆን ማለት ነው፡፡ በችግሩ ጊዜ ሸሽተው ከቀን በኋላ የተመለሱ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደውም ʻየኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት የለውም ያሉʼ፣ አሁን ግን አባት ለመሆን ሞክረው ብዙ ችግር ውስጥ ያሉ ሰው አሉ፡፡

በነገራችን ላይ ከነጻነቱ በፊት በሙሉ ወንጌል አንድ ዐውደ ጥናት ተካሄዶ ነበር፡፡ እኔ እና ፓስተር መርዕድ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች የተሳተፍንበት ነበር፡፡ ያ ሥራ አሁንም ያለ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለሁለታችን የተሰጠን “መንፈስ ቅዱስ፣ የጸጋ ስጦታዎችና አጠቃቀማቸው” የሚል ነበር፡፡ በተለይ ለእኔ የተሰጠኝ በአጠቃቀሙ ላይ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ያልኩትም ይህንኑ ነው፤ “ነጻነት በሚመጣበት ጊዜ ሰዎች በገፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ፡፡ ታዲያ ያን ጊዜ ጤነኛ የሆነ አስተምህሮ ካልቀደመ ስሜታዊነት ያይላል፤ አረፋ ይበዛል፤ ሰዎችም ለብዙ ነገር በቀላሉ የሚጋለጡ ይሆናሉ” ተብሎ ነበር፡፡ ልክ እንደሱ ነው የሆነው፡፡

ስለዚህ ሐዋርያ ካልተሾመ በስተቀር ቤተ ክርስቲያን ʻቤተ ክርስቲያንʼ ልትባል አትችልም (Apostolic reformation) የሚል ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆነ አስተምህሮ መጣ፡፡ (በመሠረቱ ቤተ ክርስቲያን ʻቤተ ክርስቲያንʼ የምትሆነው በክርስቶስ እንጂ በሰዎች አይደለም፤ መሠረቷም ክርስቶስ ነው፡፡) እንደገናም “ሬማ” የሚባለው ወይም name and claim የተሰኘው የእምነት እንቅስቃሴ ውስጥ አንዳንድ የሙሉ ወንጌል ወጣቶች ገቡ፡፡ አንዳንዶቹም “ተዉ” ቢባሉም አንሰማም አሉ፡፡ በርግጥ እንቅስቃሴው ሁሉም ላይ ተጽእኖ ቢያሳድርም፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ግን በብዛት የሙሉ ወንጌል ሰዎች ናቸው፡፡

ለዚህ ብዙ ምክንያት ይኖራል፡፡ አንደኛው፤ ሙሉ ወንጌል ከፍተኛ የሆነ የአገልጋይ ክምችት ያለባት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ምእመኑ ሁሉ አገልጋይ ነው፡፡ ሁሉም እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገባ ነው፤ ታጋይ (militant) የሆነ ነው ለማለት እችላለሁ፤ ላመነበት ጽኑ አቋም ያለው ነው፡፡ በፊት ምእመኑ ሁሉ ነው የሚሰብከው፣ የሚመሰክረው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ ʻሁላችን ካህናት ነን፤ እኔም ውስጥ ጸጋ አለʼ የሚል አስተሳሰበ ደግሞ አለ፡፡ ከዚህ ተነሥተን ካየነው፣ አንዳንድ ሰዎች ሙሉ ወንጌል ውስጥ ከቆዩ ለመታወቅ የሚኖራቸው ዕድል ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ በተለይ የመታወቅ ፍላጎት ካለ መለየት አለብህ ማለት ነው፡፡ በርግጥ የወጡት ሁሉ ለመታወቅ ባላቸው ፍላጎት ነው ማለት ጅምላ ፍርድ ይሆንብኛል፡፡

ሌላው ሰው መንገድ (outlet) ሲያጣ ዝም ማለት አይችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዚህ ምክንያት ʻሚኒስትሪ ምናምʼ ይሉና ይወጣሉ፤ ወጥተውም አብዛኞቹ የነበሩበትን ቤተ ክርስቲያን ልምምድ ነው የሚደግሙት፤ ነገር ግን እነዚህን ተቀጽላዎቹንም ጨምረው ይወስዳሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያት ሰዉን በቀላሉ ለማግኘት ነው፡፡ እውነተኛ ነቢይ ከሆንክ ብዙ ሰው አታገኝም፡፡ ዓላማህ ብዙ ሰው ማግኘት ከሆነ ግን፣ ሰዉ መስማት የሚፈልገውን ትነግረዋለህ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አዲስ ጎጆ ወጪ በሚሆኑበት ጊዜ ሕዝብ ይፈልጋሉ ማለት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቷን በመጀመሪያ ያጠቃት የስሕተት ትምህርት የ“ኢየሱስ ብቻ” (Only Jesus) ትምህርት ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሥላሴ ትምህርት ላይ በጣም የጠራና የጠነከረ አቋም አላት፡፡ ይህ እኔ ለድኅረ ምረቃ ማሟያ በሠራሁት ጥናት ላይም የተረጋገጠ ነው፡፡

ሌላው ቀጥሎ ያጋጠማት “የአርነት” የሚባለው ትምህርት ነበር፡፡ አርነት የወጡትን ሰዎች አርነት እናወጣለን የሚለው ጭብጥ ያለው ትምህርት ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ክርስቶስ በልባችን ቢኖርም አጋንንቶች በሌላው ማንነታችን ውስጥ ሊኖር ይችላል የሚል አስተምህሮ የነበረው ነበር፡፡ ይህም ትምህርት ሙሉ ወንጌልን ጎድቷታል፡፡ ያንን ለመቃወም በተደረገው ሂደት በሙሉ ወንጌል የነበረው የጸጋ ስጦታ ልምምድ ሁሉ እስከ መቀነስ የደረሰበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ እንግዲህ የ“ሬማ” እንቅስቃሴ ተነሥቶ ነበር፤ ይሄኛው ብዙም ጉዳት አላደረሰም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሐሰት ትምህርት የሙሉ ወንጌል ፈተናዋ አይደለም፡፡ አመራሩ ግን እየበሰለና ለእነዚህ ዐይነት ክስተቶች ተገቢ ምላሽ እየሰጠ ሊሄድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ፣ አንድ ሴሚናሪያምና በሥሩ ወደ ዐሥራ ሁለት የሚደርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች የተከፈቱት፡፡ አሁን አገልጋዮቻችን ሁሉ ገብተው እንዲማሩ እናደርጋለን፡፡ ለነባር አገልጋዮችም የተለየ ሥርዐተ ትምህርት ተዘጋጅቶላቸው ገብተው እንዲማሩ አድርገናል፡፡ ስለዚህ በብዙ ዐይነት መንገድ፣ ማለትም በሥልጠና፣ በመደበኛ ትምህርት እና በሌሎች መንገዶች በመጠቀም አገልጋዮች ግልጽ የሆነ አስተምህሯዊ አቋም እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው፡፡

  • ሕንጸት፡- “የብልጽግና ወንጌል” ስሕተት ነው ብለው ያምናሉ?

መጋቢ ጻድቁ፡- ይህንን እምነት “የስግብግብነት ወንጌል” እንጂ “የብልጽግና ወንጌል” አልለውም፡፡ ትክክለኛውን ብልጽግናማ እኔም አምናለሁ፡፡ ከጥቁር ውሽት ይልቅ፣ ግራጫ የሆነው ውሸት በጣም አደገኛ ነው፡፡ ሰይጣን ሔዋንን ሊያስታት የቻለው እውነትንና ውሸትን አቀላቅሎ ስለቀረባት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ይባርካል፤ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ቁሳዊውን በረከት ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ጥያቄው ግን ʻምን ማለት ነው?ʼ የሚለው ነው፡፡

ይህን ነገር የጀመሩ አንዳንድ ሰዎች፣ እግዚአብሔር ጀምሩ ያላላቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ጀምረው ገቢ ለማሰባሰብ አልሆን ሲላቸው፣ Seed faith (የእምነት ዘር) የሚል ሐሳብ አመጡ፡፡ ይህንንም ለእግዚአብሔር ሥራ ሳይሆን ለግል ስግብግብነት ማሟያ አድርገዋል፡፡

እግዚአብሔር እንደሚያበለጽግ ከሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ የዛሬዋ የሙሉ ወንጌል አማኖች ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ ከ 50 እና 40 ዓመት በፊት የነበሩ ሰዎች ማን ነበሩ? ዛሬስ ማን ናቸው? የሚለው የእግዚአብሔርን ባርኮት የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ ግን፣ ያን ጊዜ ጌታን ያመለክነው እግዚአብሔር በምድራዊው ኑሮ እንዲባርከን አልነበረም፤ ይህን ያህል ዘመንም እንኖራለን ብለንም አላሰብንም፡፡ ለተገለጠልን እውነት በታማኝነት ስንኖር፣ አንዳንዶቻችንን እዚሁ እግዚአብሔር በቁሳዊው ነገር ባርኮናል፤ አንዳንዶቻችን ደግሞ ብንሰቃይም እግዚአብሔር በልጆቻችን በኩል ባርኮናል፤ የእነርሱን አእምሮ ብሩኅ በማድረግ፣ በዕውቀታቸው፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ በልምምዳቸው የላቁ አድርጎ ባርኳቸዋል፡፡ ስለዚህ በየት በኩል ነው እግዚአብሔር የሚክሰው የሚለው የእርሱ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ነገር ግን፣ ʻመቶ ስጥና ዐሥር ሺህ ይሰጥሃልʼ የሚል ከሆነ፣ ይሄ ንግድ ነው ማለት ነው፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር የንግድ ስምምነት የለንም፡፡ እኛ በታማኝነት አምላካችንን የማገልገል ኀላፊነት ብቻ ነው ያለብን፡፡

በአጭሩ የብልጽግና ወንጌል ግማሽ እውነት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚያስተምሩት ግማሽ እውነትን፣ ያውም በጣም አጣመው፣ አዛብተው እንደሚያስተምሩ ነው እኔ የማውቀው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ ስያሜ ስጥ ብባል “የስግብግብነት ወንጌል” ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም የሚበለጽጉት የሚሰጡቱ ሕዝቦች ሳይሆኑ ስጡ እያሉ የሚያታልሉት ሰዎች ናቸው፡፡ በጣም በሚያስገርም መልኩ ደግሞ እነሱ አይሰጡም፡፡ አንድ ሰው እንዳለው ነገሩ እንደ ሱስ ነው፡፡ ሰዉ ባይበለጽግም ያንን ዳጋግሞ መስማት ይፈልጋል፤ እነሱ ይበለጽጋሉ፤ ሕዝቡ ይደኸያል፡፡ እውነተኛው ወንጌል ግን መላ ማኅበረ ሰቡንና አገሩን ይለውጣል፡፡ የወንጌላውያን ክርስትና አውሮፓን ለውጧል፤ ምንም እንኳ ዛሬ አውሮፓ ወደ ድኅረ ዘመናይነትና ወደ ድቀት እየሄደች ብትሆንም ወንጌል ለውጧታል፡፡ በእኛም አገር ቢሆን፣ ወንጌል ቀድሞ የገባባቸው አገሮች የተለየ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ወንጌል ያበለጽጋል፤ ነገር ግን ግለ ሰቦችን ሳይሆን ማኅበረ ሰብን ነው የሚለውጠው፡፡

በተጨማሪም፣ መበልጸግ የሚባለው እግዚአብሔር ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እንዳለው፣ ʻማር እና ወተት ወደምታፈስ ምድር ያገባችኋልʼ ብሎ ʻከምድሯ በታች ማዕድናት አሉ፤ ወንዞች አሉ፤ ሸሎቆዎች አሉ፤ ፏፏቴዎች አሉ፤ እግዚአብሔር ደግሞ ከላይ በዝናብ ይጎበኛታል፡፡ ያን ጊዜ እናንተ ታርሷታላችሁ፤ ቆፍራችሁ ማዕድን ታተገኛላችሁʼ ነው ያላቸው፡፡ ʻእግዚአብሔር ይባርካችኋልʼ ማለት በምኞት ወይም የሰዎችን መኪና እያዩ በማወጅ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የእጆቻችንን ሥራ፣ የሆዳችንን ፍሬ ይባርካል ማለት ነው፡፡ እኛ በተሰጠን ነገር ታማኝ ሆነን መገኘት ነው፤ መባረኩ ደግሞ የእርሱ ድርሻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ያለው፣ ʻመጀመሪያ የእግዚአብሔን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ ከዛ ሌላው ይጨመርላችኋልʼ ነው፡፡ ዛሬ ግን አትኩሮቱ ያለው በሚጨመረው ነገር ላይ እንጂ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ጽድቁ አይደለም፡፡

  • ሕንጸት፡- ከየካቲት 28 – 30 2006 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽሪ የተባሉ ግለ ሰብ አደረጉት ስለተባለው ኮንፈረንስ የእርስዎም ሆነ የቤተ ክርስቲያኖ አቋም ምንድን ነው?

መጋቢ ጻድቁ፡- እኔ በቦታው አልተገኘሁም፤ ይሁን እንጂ በስፍራው ከተገኘ ሰው ግን ስለተደረገው ነገር ሰምቻለሁ፡፡ የአንገት ሻሽ በ200 ብር የገዙ አንዳንድ ወጣቶችንም አግኝቼ ነበር፡፡ በርግጥ ከሰሙት ነገር ተነሥቶ መናገር ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ተደረገው የተባለው ነገር በምንም መንገድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ከግለ ሰቡ ስም ብንጀምር፣ “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” የሚባል ነገር መጀመሪያ አይኖረም፡፡ “ሜጀር ፕሮፌት” እና “ማይነር ፕሮፌት” የተባለው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚዎች በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነቢያት የጻፏቸውን መጻሕፍት መነሻ አድርገው መጠኑ ብዙ የሆነ መጽሐፍ የጻፉትን “ሜጀር ፕሮፌት” ሲሏቸው መጠኑ አነስተኛ የሆኑትን ደግሞ “ማይነር ፕሮፌት” ብለው ሰይመዋቸዋል፡፡ ይህ በሰው የተሰየመ ስያሜ እንጂ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለ ሐሳብ አይደለም፡፡ “ሜጀር ሼፐርድ”ም አላውቅም፤ ትልቁ እረኛ ክርስቶስ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ካየኸው ደግሞ አይቅርብኝ ዐይነት ይመስላል፡፡ እረኝነትም አይቅርብኝ፤ ነቢይነትም አይቅርብኝ ያለ ይመስላል፡፡ ይሄ በራሱ በጣም አደገኛ የሆነ የማንነት ችግር ወይም ቀውስ ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

በአጭሩ፣ 2ኛ ጴጥሮስ 2 ላይ “ገንዘብን በመመኘት ይረቡባቸዋል” ይላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሐሰት ትምህርቶች ከገንዘብ ጋር፣ ከንዋይ ጋር፣ በአጭሩ ከመበልጸግ ምኞትና ፍላጎት ጋር ይያያዛል፤ “በለዓም የዐመፃን ደሞዝ ወደደ” እንደሚለው ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ገንዘብን በዚህ መንገድ ታገኛለህ ሲባል ያንን የሚያገኝ እየመሰለው ሊሳሳት ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ሰውየው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ዘርፎ ነው የሄደው፤ አልሰጣቸውም፡፡ መጠኑ የተለያየ እንደ ሆነ ነው የሰማሁት፤ በጣም አዝናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብር ወደ ውጭ ምንዛሬ ተለውጦ ነው የወጣው ይባላል፡፡ ይሄ በሕግ የሚያስጠይቅም ይመስለኛል፡፡ ጨርቅና ወሃ መሸጥስ ምን ማለት ነው? ʻየጳውሎስ ጨርቁ ፈውሷልʼ ይባላል፤ ነገር ግን ጳውሎስ ጨርቁን ቆራርጦ ሸጧል ወይ ነው ጥያቄው፡፡ ʻብር ኪስ ውስጥ ተጨመረʼ ይባላል፤ ʻአካውንት ውስጥ ብር ገባʼ ይባላል፤ የማን ብር ነው እኔ አካውንት ውስጥ የሚገባው? እኛ አገር ድሮ እንደዚህ ዐይነቱ “ሰላቢ” ይባል ነበር፡፡ የሰላቢነት መንፈስ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚደግፍ አይመስለኝም፡፡ ሰው ያልዘራበትን፣ ያልደከመበትን፣ የራሱ ያልሆነውን ነገር እንዴት ሊወስድ ይችላል፡፡ ʻጌታ ኢየሱስ ከዓሣ ውስጥ ዲናር አውጥቷልʼ ይባላል፡፡ እርሱ አምላክ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንድ አጋጣሚ ወይም ሁኔታ እግዚአብሔር ሉዓላዊ በሆነው ሥልጣኑ ያደረገውን ነገር መድገም አይቻልም፡፡ ጥቅስ ስላለ ብቻ አስተምህሮ አይሆንም፡፡

እንግዲህ በአጠቅላይ ማለት የሚቻለው፣ ይሄ በፍጹም ከአዲስ ኪዳን አስተምህሮት ያፈነገጠ ልምምድ ነው፡፡ በዚህ ላይ ግን የሆኑትን ነገሮች መረጃ ሰብስቦ ማጥናትና አቋም መያዝ የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ በዚህ በኩል መረጃ የሚሰጠን ካለ በደስታ እንቀበላለን፡፡ ቤተ እምነቱ የተለያ አቋም መውሰዱን ርግጠኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን ጉዳዩን እንደማይደግፍ ወይም እንደማይቀበል አውቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ዝም ብሎ ʻአንቀበልምʼ ብቻም ሳይሆን፣ እንደ ቤተ እምነት እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ችላ የምንልበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡ እውነተኛ እረኞች ከሆንን ስለ ምእመናኑ ግድ ሊለንና ርምጃ ልንወሰድ ይገባል፡፡ ለብዙ ዘመን ረድተህ፣ አብረህ አልቅሰህ፣ አብረህ ታመህ፣ አገልግለህ በእግዚአብሔር ጸጋ የቆሙትን ምእመናን አንድ ዘራፊ መጥቶ ዘርፏቸው ሲሄድ እውነተኛ እረኛ ከሆንክ ዝም አትልም፤ ዝም ማለትም አይገባም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያንም ትሁን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ ከኅብረቱም ውጪ ያሉ ቢሆኑ ለሕዝባቸው ሲሉ፣ ለወንጌልም እውነት ሲሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የጸና አቋም መውሰድ አለባቸው ብዬ ነው የማምነው፤ ጉዳዩም የአንድ ቤተ እምነት ጉዳይ አይደለም፡፡ በርግጥ ከሌላው በላይ ኀላፊነቱ እኛ ላይ ይወድቃል፤ ምክንያቱም ከካሪዝማቲክ ስጦታ ጋር ተገናኝቶ የሚቀርብ ነገር ስለሆነ፡፡

  • ሕንጸት፡- አመሰግናለሁ፡፡

Humanity

“Our own being is torn apart between reason and emotion. Our identity is stranded in a furious battle between spiritualism and carnalism. Our personality is stretched between holism and reductionism. Is this some sort of a spectrum or a continuum?”

ተጨማሪ ያንብቡ

የአምልኮ ጥያቄ

ጥቂት የማይባሉ አማኞች “አምልኮ” የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ የሚረዱት በዝማሬ ውስጥ ነው። ይህ ጠባብ ትርጓሜ ደግሞ በአማኞች ሕይወት ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ ማሳደሩ አልቀረም። ለመሆኑ አምልኮና ግብር ያላቸው ዝምድና ምንድን ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ

ለዋጭ ለውጦች!

አድማጭ የሚሹ ብዙ ጩኸቶች እዚህም እዚያም አሉ። የሰው ልጅ የስኬት ብቻ ሕይወት የለውም፤ ውድቀትም አንዱ የኑሮ ገጽታ ነው። በውድቀት ውስጥ ብዙ ሕመሞች በሰዎች ልብ ውስጥ ተቀርቅረው ይገኛሉ። እነዚህ ሕመሞች እንዲታከሙ የሚያስችሉ አድማጭ ጆሮ ያላቸው መካሪዎች በእጅጉ ያስፈልጉናል ይላል ይህ የተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) ጽሑፍ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.