[the_ad_group id=”107″]

ቃለ መጠይቅ ከአገኘሁ ይደግ ጋር

“‘የግድ አንድ ሰው ጥራ’ ከተባልኩ … እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዘምረውን … እርሱን አደንቃለሁ”

አገኘሁ ይደግ በኢትዮጵያ የወንጌላውያን አማኞች የዝማሬ አገልግሎት ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚነሡ ዘማሪያን መካከል የሚጠቀስ ነው። ዘመን ዘለቅ በሆኑት ዝማሬዎቹም ብዙዎች ተጽናንተዋል፣ ታንጸዋልም። የሕይወትን አስቸጋሪ ፈተናዎች በመቋቋም እግዚአብሔርን በጽናት ማገልገሉ ለአርኣያነት የሚያበቃው እንደ ሆነ የሚያውቁት ይናገራሉ። የዚህን ዘማሪ 25ኛ የአገልግሎትና 20ኛ የትዳር ዘመን በዓል ምክንያት በማድረግ ሕንጸት የቆይታ ዐምድ እንግዳ አድርጎታል። ጳውሎስ ፈቃዱ ከዘማሪ አገኘሁ ይደግ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።


  • 25ኛ ዓመት የአገልግሎት እና 20ኛ ዓመት የጋብቻ ክብረ በዓልህ ሊከበር እንደ ሆነ ሰምተናል፤ ለመሆኑ ይህን መርሓ ግብር ያዘጋጀው ማነው? ዓላማው ምንድን ነው? ይዘቱስ?

በቅድሚያ በሕንጸት መጽሔት ላይ ስለ ተሰጠኝ ዕድል ጌታን በጣም አመሰግናለሁ፤ እናንተንም ማመስገን እፈልጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ የዚህን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የአገልግሎት በዓል ሐሳቡን ያመጡት ጓደኞቼ ናቸው። እኔ እንደውም ማገልገል ከጀመርኩ አንድ ሁለት ዓመት ዘለል ይላል፤ 27 ዓመት ገደማ ይሆነኛል። ለተለያዩ ሰዎች “የአድናቆት ቀን” ማዘጋጀት ተጀምሮ እንደ ነበር ይታወቃል፤ ጓደኞቼ ግን፣ “ይሄ ዐይነቱ ነገር እንኳ አይሆንም፤ ነገር ግን ምን አ’ርገን ይህን ወንድማችንን እናበረታታው?” በማለት አስበው ነው ያዘጋጁት። እናም “አይዞህ በርታ፤ እስካሁን ካገለገልከው የቀረው ይበልጣል” በማለት ለማበረታታት እነ ማሙሻ ፈንታ፣ አውታሩ ከበደ እና ገነት በርሄ ተነጋግረው እንደ ኮሚቴ ነገር አበጅተው የጀመሩት ነው። ብዙ ነገሮችን አይተው ይሆናል እንግዲህ። ዓላማውም እግዚአብሔርን ማመስገን እና በዚያ ምስጋና ደግሞ ለእኔ የመንፈስ ስንቅ፣ የሞራል ስንቅ ለማዘጋጀት ይመስለኛል።

  • የምታበረታታው ዳዴ የሚልን፣ “ወፌ ቆመች” የሚባልለትን ጀማሪ አይደለም እንዴ? አንተ እኮ ለ27 ዓመታት ስትሮጥ ኖረሃል።

ይኸውልህ በዚህ ዘመን እንኳን ለእንደ እኔ ዐይነቱ ሰው አይደለም፣ ለዐይናማዎቹም ቢሆን ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አለ። ይሄን ያህል ዓመት ማገልገል በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ትልቅ ትግል እንደ ሆነ የቅርብ ምስክር እናንተ ናችሁ። እንግዲህ እንደምታውቀው ኑሮ እንኳን ፈተና ነው ኢትዮጵያ ውስጥ። ኑሮ ፈተና መሆን የለበትም ነበር ለአገልጋይ። ይህን ያህል ዓመታት ሁሉ 6 ቤተ ሰብ እያስተዳደርኩኝ፣ በቤት ኪራይ እየተንከራተትን ነው ያለሁት። በዚህም ላይ የጋበዘን ቤተ ክርስቲያን ካሰበን አሰበን፣ ካላሰበንም ሦስት ጊዜ “ጌታ ይባርካችሁ” ብሎ የሚሸኝበት አገር ኑሮም ራሱ ተግዳሮት ነበር። ከኑሮ ሌላ ደግሞ ተፈጥሮዬ ራሱ ይታገለኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ ጠላት አንድ ሚሊዮን ሰውን ከሚዋጋ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን የሚያገለግለውን ሰው ተስፋ ቢያስቆርጠው አንድ ሚሊዮኖቹን በአቋራጭ ያገኛቸዋል። እነዚህ ጓደኞቼ ደግሞ በአንድም በሌላም መንገድ ከእኔ ጋር ልዩ ልዩ ታሪክ አላቸው። ማሙሻ እና እኔ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ አንድ ላይ ነበርን፤ አብረንም ኖረናል። በአገልግሎቴም ገጠርም ሆነ ብዙ ቦታ ስሄድ ይዞኝ ይሄድ ነበር። እናም ከየት እንደ መጣሁና አካሄዴንም ሁሉ ያውቃል። ስለዚህ አሁንም “ይሄንን ወንድማችንን አይዞህ እንበለው” በማለት አስበው፣ “ከጎንህ ነን” ለማለት ነው ያዘጋጁት። ግን ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ለማመስገን ይመስለኛል።

  • ታዲያ እነዚህን ውጣ ውረዶችና እነዚህን ትግሎች እንዴት አለፍካቸው? ዓመታቱ ረጅም ናቸው፤ በዚያውም ዕድሜህን እያስታወስኩህ መሆኑ ነው።

አዎን፤ አዎን፤ እኔ አሁን አርባ አምስት ዓመቴ ነው። ማገልገል ስጀምር የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እንደ ነበርኩ አስታውሳለሁ፤ ግን አሁን እንግዲህ “እንዴት አለፍካቸው?”የሚለውን ለመመለስ አንዳንዶቹን ነገሮች ላሳይህ። ክፍለ አገር አንዳንድ ቦታ አገልግሎት ሲጠሩኝ በአውቶብስ ነው የምሄደው። የምወርድበት ቦታ ሰዎች እንደሚጠብቁኝ ዐውቃለሁ። ነገር ግን ያኔ ሞባይል ባልነበረበት ጊዜ ይቅርና ዛሬ በሞባይል ዘመን እንኳን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሳይገናኙ ይቀራሉ። እናም እኔም ከብዙ ሰዎች ጋር እተጣጣለሁ። አንድ ጊዜ እንደውም አንድ ክፍለ አገር አንድን ሰው ለአራት ሰዓት የጠበቅኩበት ጊዜ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሰዉ ለምሳ ሲወርድ እኔ ብቻዬን የምቀመጥበት ጊዜ አለ።

  • አውቶብስ ውስጥ?

አዎን። ሰዉ ደግሞ ፈልጌ ይመስለዋል እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ይረዳል። እናም በእነዚህ ሁሉ ውስጥ የእግዚአብሔር ዕርዳታ አልተለየኝም፤ እጄን ይዞ መርቶኛል። ክፍለ አገር ስሄድም ልክ እንደ ሌላው ሰው በፈረስ፣ በበቅሎ፣ አንዳንዴም ሩቅ የእግር መንገድ ይዘውኝ ነው የሚሄዱት።

  • ክፍለ አገር ብዙ ትወጣለህ?

አዎን። አሁን እኮ ብዙ ዘማሪ ውጭ አገር ነው ያለው፤ እኛ አሁን ባለፈው ስንቆጥር ወደ 15 በላይ ዘማሪ የለም። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙ ሰው ወደ ገጠር ለመሄድ አይደፍርም። ለምሳሌ በቅርብ ቀን ወደ ባሌ ጊኒር ሄጄ ነበር። “ብዙ የሚያዩ ሰዎች እምቢ ብለውን ነበር። አገኘሁ ግን መጣ” ብለው ተደሰቱ፤ ትልቅ ምስጋና ነው ያደረጉት። ታዲያ እነዚህ ነገሮች ተግዳሮት ሳይሆኑ ቀርተው ይመስልሃል? በጣም ከባድ ናቸው። ለእኔ ግን ከዚህ በባሰም ሁኔታ ውስጥ ብሄድ የጌታን ውለታ አይከፍልልኝም። በዚህም ላይ ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ነው በቤቱ የሾመኝ። ስለዚህ፣ “ከዚህ በባሰም ሁኔታ አገለግልሃለሁ” ያልኩበት አንድ ታሪክ አለኝ። እርሱን ልንገርህ?

  • እባክህ …

በ82 ዓ.ም. አንድ ቦታ ተጋብዤ ስሄድ ነው ነገሩ የሆነው። በበትር ነበር ከሰበታ እየመጣሁ የማገለግለው። በነገራችን ላይ እኔ ያለ በትር መሄድና በመሪ መሄድ የጀመርኩት በ83 ዓመት ነው። ዝነኛ እየሆንሁ ስመጣ ሰዉ መንገድ ላይ ሰላም እያለኝ፣ “አንተ መኪና ቢገጭህስ? ነውር አይደለም እንዴ?” ሲሉኝ ነው በትር ያቆምኩት። እንጂማ መርካቶም ሆነ ኮልፌ ስሄድ ብቻዬን ነበር። እንዲያውም አንድ ቀን ያጋጠመኝን አስገራሚ ነገር ልንገርህ። አንድ ምሽት 3 ሰዓት ከምናምን ሆኗል፤ ከ26 ቁጥር አውቶብስ ወርጄ ሌላ አውቶብስ ይዤ ነበር የምጓዘው – ወደ ኮልፌ። ታምራት ኀይሌ ጋ ለማደር በበትር ነው የምሄደው። እና የሆነ ቦታ ላይ አንድ ሰው መጣ። ማን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ድምፁንም አልሰማሁም። መጣና እጄን ያዘኝ። “ማነህ? ወዴት ነህ? ለምንድን? እንዴት?” ምንም አላወራንም። ነገሩ ትንሽ እንደ መፍራትም፣ እንደ መገረምም አድርጎኛል። ያ ሰው ግን ታምራት ኀይሌ በር ላይ አድርሶኝ ሄደ። አንተ የፈለግከውን በለው፤ እኔ ግን የእግዚአብሔር መልአክ ነው ብዬ አምናለሁ። እንዲህ እግዚአብሔር እጄን ይዞ መርቶኛል፤ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም። በአገልግሎት ቦታም እግዚአብሔር አምላክ በአንተ ይናገራል ብለው ሰዎች አይጠብቁም። በእግዚአብሔር ቤት ብዙ ንቀት ጠግቤአለሁ።

አንድ ቀን የሆነ ቦታ እየሄድኩኝ ነበር – በበትር። ይሄ ነው እንግዲህ የታሪኬ መጀመሪያ፤ ነገርን ነገር አንሥቶት አርዝሜብህ ነው። እና ወደዚያ ጉባኤ ደረስኩኝና ምንም መፈታት አቃተኝ። ምክንያቱም እንዳልኩህ በኑሮና በአንዳንድ ነገሮች ልቤ አዝኖ ስለ ነበር ነው። እኔ ደግሞ የድኻ ልጅ ነኝ፤ የምጠጋው ዘመድም የለም። የቤተ ክርስቲያንንም ታሪክ ታውቀዋለህ። አሁን ለምሳሌ አንድ ሀብታም ሰው የሆነ ነገር ቢጠይቅ የሚሰጠው ሰው ያገኝ ይሆናል። እንደ እኛ ዐይነት ሰዎችን ግን የሚያስብ አይኖርም ነበር። ይሄ እኮ የሩቅ ዘመን ታሪክ አይደለም፤ የ20 የ25 ዓመት ታሪክ እኮ ነው የማወራህ። ያን ጊዜ ወደ ጉባኤው ሄጄ በሐዘን ተቀምጬ እያለሁ፣ “እስቲ አገኘሁ ጉባኤውን በጸሎት ይከፍትልናል” ተባለ። “ጭራሽ!” አልኩና፣ ያው እንግዲህ ምግብ ላይም አንዳንዴ የሚባለውን እንደምንለው የሚባለውን ብዬ ተቀመጥኩ። ከዚያ በኋላ “አዝማች ቢዘመር ውስጤ እየተፈታ ይሄዳል” ብዬ አሰብኩ። ያኔ አዝማች ምርጫ ነበር፤ ታውቃለህ። መሪው የተመረጠውን አዝማች ሦስት አራቴ አዘመረና “አሁን ወንድማችን አገኘሁ ይዘምርልናል” ሲል ምን ልበል? ቆምኩኝና ዝም ብዬ ክራሬን መቃኘት ጀመርኩ። እኔ ብታምንም ባታምንም ውስጤን ነበር የምቃኘው። ክራሩማ ከመጀመሪያውም ተቃኝቷል። እና በዚያ ሁኔታ ሳለሁ ከጉባዔው ኋላ አካባቢ ድንገት አንድ ርኩስ መንፈስ ጮኸ። በቃ ይገርምሃል ወዲያው እኔም የሆነ ነገር ለቀቀኝ፤ ደስ አለኝ። ኋላማ ማመን አትችልም፤ የፈውስ ፕሮግራም ይመስል ነበር። ከግራ ከቀኝ አጋንንት ይጮኽ ነበር። ከዚያ ዘመርኩ፤ መድረክ ለቅቄ ልወርድ ነው? ስዘምር፣ ስዘምር፣ ስዘምር … ከዚያ ምን አልኩ መሰለህ? “ጌታ ሆይ፤ ከአሁን በኋላ ከዚህ የከፋ ነገር እንኳ ቢያጋጥመኝ ዕድሜ ልኬን፣ እስከምሞት እዘምርልሃለሁ” ብዬ ቃል ገባሁ። ከዚያ የከፋ ሁኔታም ገጥሞኝ ያውቃል፤ ግን ደስተኛ ነኝ። እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ያሳለፈኝ ጌታ ከሁሉ በላይ ስሙ የተባረከ ይሁን።

  • መዝሙሮችህ ብዙ ጊዜ የጻድቅ ሰው ጉዞን፣ የሕይወት ውጣ ውረድን፣ በእግዚአብሔር እጁ የተያዘን ሰው ይሥላሉ። መዝሙሮችህ ትውልድ እየተሻገሩም አይተናል። እንዴት ነው እንደዚህ የሆነው?

ሌላ ሰው ቢያወራው ነው የሚሻለው። እኔʼኮ ምሕረት ተደርጎልኝ ስዘምር እንጂ ድምፃዊም አይደለሁም። መልእክተኛ እሆን ይሆናል። ምሕረት ስለተደረገልኝ ዝም ብዬ ስዘምር ነው እንዲያ የሆነው። አንድ ታሪክ ታውቅ ይሆናል። “‘እግዚአብሔር እረኛዬ ነው’ የሚለውን መዝሙር የምታውቁ” ሲባል አንደኛው ወጣት በቃሉ ምዕራፉን አለው። ከዚያ ጉባኤው አጨበጨበለት። ከዚያ ደግሞ አንድ ሽማግሌው ወጡ። በእርግጥ ይሳሳቱ ነበር፤ ግን ጉባኤው ያለቅስ ነበር። ጉባኤው ካለቀ በኋላ ያ ወጣት፣ “አባቴ ነገሩ ምንድን ነው? ሰዉ ለእርስዎ ጊዜ ያለቅሳል፤ ለእኔ ያጨበጭባል” ሲላቸው፣ “አይ ልጄ አንተ የምታውቀው መዝሙሩን ነው፤ እኔ እረኛውን ራሱን ዐውቀዋለሁ” ብለዋል የሚል ነገር ሰምቻለሁ። ይህ ስለ እግዚአብሔር የማወቅን እና እግዚአብሔርን ራሱን የማወቅን ልዩነት ይነግረናል።

መቼም እኔ ራሴን ከፍ እያደረግሁ እንዳይመስልብኝ እፈራለሁ እንጂ፣ አንዳንዴ በዓመትም አንድ መዝሙር አልቀበልም። በሁለት ዓመት አንድም ያልተቀበልኩበት ጊዜ አለ። አንዳንዴ ደግሞ በዓመት ዐሥር መዝሙር እቀበላለህ። ጥሶኝ ሲመጣ፣ ዐልፎ ሲመጣ ነው የምዘምረው፤ ዝም ብዬ አይደለም። ምናልባት ሕይወቴን ስለምዘምር ይሆናል። ይህን ከእኔ የበለጠ የተረዳ ሰው ማን አለ ብለህ ነው? የሆነን ነገር ለማሳፈር እኮ ነው እግዚአብሔር ያልሆነን ነገር የመረጠው። ውሃውን እኮ ነው ወይን ጠጅ ያደረገው። አይደለምን? ምናምንቴና ትርጉም የለሽ ለነበረው ሕይወቴ ትርጉም የሰጠው ጌታ ኢየሱስ ነው። እኔ ካልዘመርኩ ማን ይዘምራል?

  • ለመሆኑ ከእኛ ትውልድ ዘማሪዎች ነው አገኘሁ የሚመደበው? ወይስ ከየትኛው ትውልድ ነው?

አንተ የትኛው ነህ? እኔ አንተን ሳውቅህ የትና የት ዓመት! ራስህን ልጅ ልታደርግ ካልሆነ በቀር። እኔ እንግዲህ አገልግሎት ስጀምር ታምራት ኀይሌም አንዳንድ ቦታ አገልግሎት ተክቶኝ ነው የጀመርኩት። እነ ታደሰ እሸቴ ሲዘምሩ ነበርኩ። ከዚያ ደግሞ የእነ ተስፋዬ ጫላ ትውልድ መጣ። እነ ሊሊ፣ እነ ዳንኤልም መጡ። የእነ መስፍን ጉቱ፣ የእነ አውታሩም ደሞ መጣ። ብዙ ጊዜ ጥሩ መዝሙሩን ስሰማ ደስ የሚለኝ እንዳልካቸው ሐዋዝም አለ። እነ ተከስተም አሉ።

አሁን ደግሞ የእነ ኤፍሬም ዓለሙ፣ የእነ ቴዎድሮስ አለ። እኅቶች ደግሞ እንዳይቀየሙ … እነ አዜብ። እነዚህም ሁሉ ልጆች የእኔ ጓደኞች ናቸው። ዛሬም 25 ዓመቴን ላከብር አይደለ? የ23 ዓመት ዕድሜ ካለው ዘማሪ ጋር አብረን እየተላፋን እንደ እኩያ ነው የምጫወተው። እኔ እንዲያውም 45 ዓመት የሞላኝም አልመስልም፤ ስለዚህ እኔ ከየትኛው ነኝ? ምናልባት የየትውልዱ አገናኝ ነኝ።

  • የትውልድ አገናኝ?

ምክንያቱም እነ ገዛኸኝ ሙሴም ሲዘምሩ አብሬ ነበርኩ፤ እነ ወንደሰን ደሳለኝም። ታደሰ እሸቴ የእኔ ሚዜ እንደ ነበር ታውቃለህ። ለኢትዮጵያ መዝሙር ብዙ አስተዋጽኦ ያበረከተው ጌታ ያውቃል ግርማይም ጓደኞዬ ነው። ስለዚህ ከየትኛው ትውልድ ትመድበኛለህ? ከሁሉም ቢሆን አይሻልም? ስለዚህ የትውልድ አገናኝ የሚለው ተስማምቶኛል።

  • በዚህ ዘመን አንዳንድ ሰዎች በዝማሬ አገልግሎት እንደ ተሰላቹ ይናገራሉ። ሰዎቹ ቢሰላቹ እውነትነት አላቸው ትላለህ?

መቼም ውሸትም አይደለም፤ ግን መዝሙር ብቻ እኮ አይደለም፤ ብዙ ነገር እኮ ፈር ለቀቀ። መዝሙሩም አብሮ የዚያ ሰለባ ሆኗል። የቤተ ክርስቲያን መንሸራተት፣ በቤተ ክርስቲያን የብዙ ነገሮች ፍሬ መታጣት መዝሙሩም ላይ ባይታይ ነው የሚገርመው እንጂ። መዝሙራችን ላይ ብዙ ችግር አለ። ለምሳሌ፣ ታስታውስ እንደ ሆነ ሙሴ እግዚአብሔር የሚለውን ነበር የሚሰማው፤ አሮን ደግሞ ሕዝቡ የሚለውን። ሙሴ እንዲያውም ሊወገር ነበር። እናም እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ሕዝቡ የሚለንን ነው የምንሰማው። “ይሄኛውን ዐይነት መዝሙር አዘጋጁልን፤ ይሄኛውን አርጉልን” ስለሚሉን፣ በኋላ እግዚአብሔር ደግሞ ይክበርበት አይክበርበት ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሆኖም ብልሽቱ ሁሉም መዝሙር ላይ ነው ደግሞ አልልም። እግዚአብሔር እንኳንስ ከወጣቶች ቀርቶ፣ ከሚጠቡ አፍ እንኳ ምስጋና ያዘጋጃል። የአንዳንዶቹም መዝሙር የአምልኮ መንፈስ እኮ አለው። ይገርምሃል። ታዲያ ያንን የሚያጠራ መንፈሳዊ አባት ያስፈልጋል።

በእኔ ጊዜ መንፈሳዊ አባቶች ነበሩን፤ ሄደን እናማክራቸዋለን። የተንጋደደውን መዝሙራችንን ያስተካክሉልናል፤ ምክንያቱም 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 ቁጥር 26፣ “በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው … ለአንዱ በልሳን መናገር አለው” ስለሚል መዝሙር የጸጋ ስጦታ ነው ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱም ʻአዲስ ዝማሬን ለአምላካችን በከንፈሬ ጨመረʼ ነው የሚለው። የሚጨመር ነው አፍህ ውስጥ፤ ʻመዝሙር በሌሊት ትሰጣለህʼ ነው የሚለው። ለሙሴም መዝሙር አጽፎታል። ይሄ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚፈስ ነው። ግን ሳሙኤልን ዔሊ እንደ መከረው የሚመክር እና “እንዲህ ነው እኮ አዘማመር፣ ስትዘምር እንዲህ አቃናው” የሚል ሰው በጣም በእውነት ያስፈልጋል። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ስሕተት አጋጣሚዎች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል። ቢሆንም መታገሡ ጥሩ ነው፤ ባይሰላቹ።

  • እንደ ቀዳሚ ዘማሪነትህ አንተስ ሌሎችን ትመክራለህ? ምከንያቱም ከወጣቶቹ ጋር ታዘወትራለህና!

እኔን ብዙ ሰው ይመክረኝ ነበር፤ ግን “ምከረኝ” ብሎ ወደ እኔ የመጣ የለም። ቢኖርማ፣ እንኳን አብረን ለአንድ መድረክ፣ ለአንድ አገልግሎት የተጠራን ወንድሞችን ቀርቶ በሌሎች ነገሮችም ቢሆን ሳያገባን እንኳ ምክር የምንሰጥበት ጊዜ ብዙ ነው። ስለ ጋብቻም እንኳ ምክር የምንሰጥበት ጊዜ ብዙ ነው። ስለዚህ እኔ በጣም ዝግጁ ነኝ፤ ሰው ከመጣ።

  • ድሮ ሰበታ መርሓ ዕውራን እያለህ “ውሰደኝ” ብለህ ትጸልይ ነበር ይባላል – እንደ ኢዮብ፣ እንደ ኤልያስ።

ውይ ያልጸለየ አለ እንዴ!?

  • እና ጌታ ሳይወስድህ ቀርቶ ጥዋት ራስህን ስታገኝ ምን ነበር የምትለው?

እርግጥ ኑሮ በሚመርህና አንዳንድ ነገር አልመች ሲልህ ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ሕልውና ውስጥም ስትገባ “ውሰደኝ” ትላለህ። ብዙ ጊዜ እንደዚያ ብያለሁ። ከዚያ በኋላ ጥዋት ሲነጋ ምን እንዳልኩ ግን አሁን አላስታውስም። ምን ብለውህ ይሆን? በእኔ ስም ደግሞ ብዙ ቀልድ እንደሚነገር ታውቃለህ።

  • ይልቁኑ አንተ ቀልድ እንደምትወድ ዐውቃለሁ።

በእኔ ላይ ከተነገሩት አንዱን ላጫውትህ?

  • እሺ።

እንግዲህ አንድ ሰው ስብከት ላይ ሲናገረው የሰሙ ሰዎች የነገሩኝ ነው፤ ለነገሩማ ሁለት ሦስት ሰባኪ ሰብኮበታል። አንድ ጊዜ ማሙሻ ለአገልግሎት የሆነ ቦታ ይዞኝ ሄዶ ነው አሉ። ምንድን ነው የሆነው? እኔ ልዘምር ስቆም እልልታም የለም፤ ሰዉም “እምጵጽ” አይልም፤ ከንፈሩንም አይመጥም። ከዚያ እየዘመርኩ ከነበርኩበት አቆምኩና፣ “ማሙሻ ባዶ ቤት ነው እንዴ የምታስጮኸኝ!” እንዳልኩ ነው የሚነገረው። ይሄ እንግዲህ በእኔ ስም የተፈጠረ ነው፤ ይህንን የሚመስል ብዙ ቀልድ አለ። በርግጥ ደስ ይለኛል፤ ሰዉ ስለሚወደኝ ነው እንደዚህ የሚጫወተው።

  • አንተም በራስህ ትቀልዳለህ፤ ሰምቼህ ዐውቃለሁ።

በጣም። ያው እንግዲህ እነ ደሉ ጸጋዬ፣ “እያየህ ለምን አትሄድም?” ሲሉኝ፣ “እኔ በማየት አይደለም እንደ እናንተ የምሄደው፤ በእምነት ነው” እላለሁ።

  • ወደ ትዳርህ ልውሰድህ። 20 ዓመት?

አዎ።

  • እንግዲህ ለ7 ዓመት ገደማ ካገለገልክ እና ዝነኛ ከሆንክ በኋላ ነው ያገባኸው ማለት ነው?

የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነበርኩ ሳገባ።

  • በስንት ዓመትህ?

ስንት ዓመቴ ይሆናል? 25 ዓመቴ። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነበርኩ፤ ሰበታ መካነ ኢየሱስ። እንዲያውም ሽማግሌዎች ወደ እርሷ ቤተ ሰብ ሲሄዱ፣ “እርሱ እኮ ከኮተቤ ኮሌጅ ተመርቋል፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌም ነው” ተብሎ እንደ መስፈርት ተወስዶ ነበር፤ ይገርምሃል። አሁን ካገባሁ ሃያ ዓመት ሆነኝ፤ ትልቁ ልጄ ጥር ላይ 19 ዓመት ይሆነዋል።

  • እነዚህን 20 ዓመታት መለስ ብለህ ስታይ ስለ ትዳር ምንድን ነው የተማርከው?

ትዳር በጣም ከባድ ነው፤ እንኳን እንደ እኔ ላለው ሰው ቀርቶ፣ ለሌላውም ቢሆን። ትዳር እኔን የመቅረጫ አንድ መንገድ ሆኖ ነው ያገኘሁት። በጣም ከባድ ነበረ። እንግዲህ እሷም ከሌላ ቤተ ሰብና አስተዳደግ ነው የመጣችው፤ በተመሳሳይ እኔም ከሌላ ቤተ ሰብና አስተዳደግ ነው የመጣሁት። ከዚያ ለእርሷ መኖር አለ፤ ለልጆች መኖር አለ፤ እሷ ለእኔ ለመኖር የምትታገለው አለ። ብቻ እግዚአብሔር እኔን ለመሥሪያም የተጠቀመበት ነው ብዬ ነው የማስበው። በርግጥ ትዳር ጥሩ ነው፤ ከአንድ ሁለት ይሻላል። ሰው ሁለት ሲሆን ይጠነክራል፤ በቀላሉ አይሰበርም። ግን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ታዳጊ አገር፣ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለ፣ የምክር እና የብዙ ነገሮች ጉድለት ባለበት ቦታ ትዳር በጣም መንፈሳዊ ሰው መሆንን ይጠይቃል። ብዙ ኀላፊነቶችን ለመሸከም የተዘጋጀህ መሆን አለብህ። እነዚያን ደግሞ በእግዚአብሔር ርዳታ ተወጥቻቸዋለሁ። ግን በጣም ከባድ ነበሩ።

  • እግዚአብሔር ይመስገን። ሰርግህን ስታስብ ምን ትዝ ይልሃል የመጀመሪያ ነገር?

አንተ የምታስታውሰው ምንድን ነው?

  • እኔ ቀበቶህን ነው። ቀበቶ ተረስቶ ከሰው ነበር ቀበቶ የወሰድከው።

አዎ፤ የታምራት ኀይሌ ቀበቶ ቀዳዳ ተበስቶለት ነበር ያደረግሁት። ቀበቶ ጠፍቶ …

  • በጣም ቀጭን ነበርክ ያኔ።

አዎ በጣም ቀጭን፤ ዝግጅቱ ላይ ቪዲዮውን ታየዋለህ። ታምራት ኀይሌ ደግሞ ወፍራም ነው። ብንለው ብንለው ቀበቶው ወገቤ ላይ ሁለት ዙር ሊሞላ ነበር፤ ብቻ የእርሱ ቀበቶ ተበስቶ እንዳደረግሁት ታስታውሳለህ። ሌላ ግን ሰዉ፣ “ዐይኑ ይበራል፤ ዐይኑ ይከፈታል” ብሎ ስላሰበ ቤቴል መካነ ኢየሱስ ጠጠር መጣያም አልነበረም። በዚያ ዘመን እንኳን 100 ምናምን መኪና እንደ መጣ አስታውሳለሁ። የዛሬ 20 ዓመት። የሽብሸባ መዘምራንም ነበሩ።

ሰዉ ያኔ ምን መሰለህ ስጦታ ይዞ የመጣው? የሸክላ ጥቅስና መጽሐፍ ቅዱስ። የሸክላ ጥቅሱ ግማሹ እየተሰነጠቀ አለቀ። “እኔና ቤቴ” የሚለው ግማሹን ሲይዝ፣ “እግዚአብሔርን እናመልካለን” የሚለው ሌላኛው ግማሽ ላይ እየቀረ። ከጌታያውቃል ጋር ስንጫወት “እባክህን እንደው የሚረከበኝ መዝሙር ቤት ፈልግልኝ” እያልኩት እንሥቅ ነበር። አሁን እኮ ሰው ሲያገባ መኪና ነው የሚበረከትለት፤ ታውቃለህ አይደል? ወይም ቤት። ለመሣቅ ያክል ነው … (ረጅም ሣቅ)

  • የልጆችህ ስም ብዙ ጊዜ ይነሣል።

አዎን። የመጀመሪያው ልጄ መዳን አገኘሁ ነው። እጮኛ ሳይኖረኝ በፊት ነው ያሰብኩት፤ “ወደፊት ሳገባና ስወልድ፣ ልጄ ሴትም ትሁን ወንድ፣ መዳን እለዋለሁ” ብዬ ነበር። እናም ልጄ ወንድ ሆነ፤ መዳን አገኘሁ አልኩት። ከዚያ ከአርያም አገኘሁ፤ ከዚያ ደግሞ ወዳጅ አገኘሁ። የመጀመሪያው ልጄን ስወልድ ወላይታ ነበርኩ፤ ሚስቴ አጠገብ አልነበርኩም። እነ ጌታያውቃል ለካ ሆስፒታል አብረዋት ነበሩ። ሁለተኛዪቱን ልጄን ስወልድ ደግሞ ኮምቦልቻ ነበርኩ፤ የዛሬ 17 ዓመት። ከዚያ ጌታ ያውቃል ምናለ? “አንተ ብርድ አልበረደህ፤ ሆስፒታል ለሆስፒታል አልተንከራተትክ፤ መዳን አገኘሁ ለምን ትላለህ? ከመሬት አገኘሁ ለምን አትልም?” አለኝ። እና ሁለተኛዋን ልጄን “ከአርያም” ስላት፣ “ከመሬት እንዳልልህ ብለህ ነው ወይ ከአርያም ያልከው?” እያለኝ እንሥቅ ነበር አብረን። እኔም እርሱ ልጅ ሲወልድ “ለአንቺም” በላት አልኩት፤ ለአንቺም ጌታ ያውቃል። ሦስተኛው ልጄ ወዳጅ አገኘሁ ይባላል። ሦስት ናቸው። ሙሉ መዳን …

  • ሙሉ የባለቤትህ ስም ነው።

አዎን ሙሉ የባለቤቴ ነው። ሙሉ መዳን ከአርያም ወዳጅ አገኘሁ ብዬ እንደዚህ ገጣጠምኩት።

  • ሁሉንም አንተ ነው ያወጣኸው ማለት ነው? ለእርሷ ዕድል አልሰጠሃትም?

አዎ አልሰጠኋትም። ስነግራት ትስማማለቻ! እግዚአብሔር ይስጣት።

  • አሜን!

እኔ በእርሷ አንዳንድ ነገር እንደምስማማው፣ እርሷም ይሄኛውን ነገር ለእኔ ትተውልኛለች። እኔ ብዙ አወራለሁ፤ እርሷ ዝም ትላለች። ይሄ ነው።

  • አሁን የምታከብረው የጋብቻ በዓልህንና የአገልግሎትህን የብር ኢዩቤልዩ ስለሆነ ሰዎች በአገልግሎትም በትዳርም ጸንተው ይቆሙ ዘንድ ምን ትመክራለህ?

መቼም የእግዚአብሔር ክብር እና የእግዚአብሔር ሞገስ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ፣ እንደ እኔ ያለው ሰው ክብር አግኝቶ ለዚህ አይበቃም ነበር። አንተም ለቃለ ምልልሱ እኔ ጋ አትመጣም ነበር። ስለዚህ ከሰው ካስተዋወቀኝ ከመዝሙሩ አገልግሎት ልጀምር። መዝሙር ትልቅ ክብር ነው። እኔ ለማይዘምር ሰው አዝናለሁ። ለምን መሰለህ? እንዴት አድርጎ ፍቅሩን ለጌታ ይገልጣል? ሙዚቃ እኮ ኪነ ጥበብ ነው። ሰማይ ምድሩን፣ ሸንተረሩን፣ ወንዙን ስታይ እንደምትረዳው እግዚአብሔር ራሱ የኪነ ጥበብ ምንጭ ነው። ለዚህ ጌታ ስዘምር ትንሽ እፎይ እላለሁ። “አሁን መዘመር የማይችል ሰው ምን ይል ይሆን?” እላለሁ አንዳንዴ። ስለዚህ ለሚዘምሩ ሰዎች መምከር የምፈልገው ሁልጊዜ ከነፍሳቸው እንዲዘምሩ ነው።

በ1982 ዓ.ም. “ከዘማሪዎች ማንን ታደንቃለህ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር። “የተለያየ ሰው የተለያየ ቀለም ስላለው እኔ ማንንም ለማድነቅ እቸገራለሁ። ‘የግድ አንድ ሰው ጥራ’ ከተባልኩ ግን፣ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዘምረውን ሰው እርሱን አደንቃለሁ” ብያለሁ። አሁንም እርሱን ነው የምደግምልህ፤ እስከ መጨረሻው ሰዎች እንዲዘምሩ። ቢወልዱም እንዲዘምሩ፣ ባይመቻቸውም እንዲዘምሩ፣ ቢመቻቸው፣ ቢሳካላቸውም እንዲዘምሩ። እኔ አሁን በዚህ መቅረጸ ድምፅ እንኳ የማልሰጥህ፣ ብዙ ትግል ታሳልፋለህ። በዚያ ሁሉ ግን የሚረዳህም የሚረ’ዳህም እግዚአብሔር ብቻ ነው። ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር እንኳ ቢገጥም ወጣቶች መዘምር እንዲቀጥሉ እሱን አበረታታለሁ።

ሁለተኛው ጋብቻ ነው። ስለ ጋብቻ እንኳን ብዙ መካሪ ላልሆን እችላለሁ። ባለቤቴን ሰዎች መጥተው፣ “ከአገኘሁ ምን ተማርሽ?” ሲሏት፣ “እርሱ ፍቅር ነው” ብላ እኔን ከፍ አደረገችኝ። ባለቤቴን ጌታ ይባርካት፤ እኔን ስለ ተሸከመች። በብዙ መልኩ ተሸክማኛለች፤ ብዙ የማይመቹ ሁኔታዎችን አብረን አሳልፈናል። ሩቅ ነበር ቤታችን፤ ብዙ ሰው አላገኝም። በዚያ ሁሉ ውስጥ ግን እርሷ ነበረች ጓደኛዬ። አሁን በዚህ ጊዜ ሰበብ ፈጥሮ ትዳሩን የሚፈታ ሰው አለ፤ ምክንያት እያለው የማይፈታም አለ። በሰበብ እና በምክንያት መካከል ያለው ልዩነት ይሄ ነው። እኔ መቻቻልን አይደለም ለትዳር የምመክረው፤ መቀባበል እንዲኖር፣ እስከ መጨረሻው ድረስ መዋሐድ እንዲኖር እንጂ። እኔ በእውነት፣ “እገሌ እኮ እንደዚህ ሆነ፤ እገሌ እኮ እንደዚያ ሆነ” ሲሉኝ አልፈርድም፤ አንዳንዶቹ ከእኔ የተሻሉ ሰዎች ስለሆኑ። የሚያዋጣው፣ “እገሌ ፈትቶ ምን ሆነ?” የሚለው ሳይሆን፣ ውጤቱ ምንድን ነው? ወጣቶቹ ልጆች ከእኛ ምን ይማራሉ? የሚለው ነው። እና ብዙ ነገሮችን ታግሠው እንዲያሳልፉ እመክራለሁ። እናም ሰዎች በዚህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲፈጽሙ … መምከር ሳይሆን ጥሪ አቀርባለሁ። ደሞ ምን አላት? 70 ዓመት ናት! (ረጅም ሳቅ)

በተረፈ ስለ ተሰጠኝ ዕድል ሕንጸትን አመሰግናለሁ። ተባረኩ።

  • እኛም እናመሰግናለን፤ ክብረት ይስጥልን።

Share this article:

ዴክሳሜታሶን እና ኮቪድ-19

“ዴክሳሜታሶን” ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሣ መድኃኒት ከሆነ ሰንብቷል። ይህንኑ በሚመለከት ፋርማሲስት ባንቱ ገብረ ማርያም ስለ መድኃኒቱ ምንነትና ታማሚዎችን በማከም ረገድ ያለውን ድርሻ እንዲሁም ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ የሚከተለውን ጽሑፍ ያስነብባሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.