[the_ad_group id=”107″]

“የሁላችን ድርሻ ተጠራቅሞ ነው ውጤት ያመጣነው”

ዘላላም አበበ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስትያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ) ውስጥ ለረጅም ዓመታት አገልግሏል፡፡ ለአራት ዓመታት በደቡብ አካባቢ የኢቫሱ ቢሮ በሙሉ ጊዜ አገልጋይነትና የአካባቢው ቢሮ አስተባባሪ በመሆንና ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ለዘጠኝ ዓመታት ደግሞ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግሎ በቅርቡ በራሱ ፈቃድ የዋና ጸሐፊነት ሥራውን አስረክቧል። ወንድም ዘላለም በትምህርት ዝግጅቱ ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ እርሻ ኮሌጅ በእርሻ ሥራ እንዲሁም ከኢቫንጄሊካል ቲዮሎጅካል ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪውን በነገረ መለኮት ያግኝቷል። ዘላለም በአሁኑ ሰዓት አሜርካን አገር በሚገኘው Gorden Conwell Theological Seminary በሥነ አመራር የድኅረ ምረቃ ትምህርት በመመላለስ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በኢቫሱ ውስጥ በነበረው አገልግሎቱና በተያያዙ ጉዳዮች አስናቀ እንድርያስ ከዘላለም አበበ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 • ሕንጸት፦ በኢቫሱ ውስጥ የነበርህ አገልግሎት እንዴት ተጀመረ?

ዘላለም፦ በኢቫሱ ውስጥ የነበረኝ አገልግሎት የተጀመረው በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ እርሻ ኮሌጅ ስማር የተማሪዎች ኅብረት አሰተባባሪ በነበርኩበት ወቅት ነው። ያን ጊዜ የደቡብ አካባቢ (ክልል) ዓመታዊ የአብሮነት ጊዜ ማዘጋጀት ተፈልጎ እኔ እዚያ ላይ አስተባበርኩ። በወቅቱ አገልጋዮች ይዞ የመጣው የኢቫሱ ዋና ጻሐፊ የነበረ ሰው አገልግሎቱን ጨርሶ ሲመለስ አነጋገረኝ። እርሻ እማር ስለ ነበር “ስትመረቅ ገበሬ መሆን ነው እንዴ የምትፈልገው? ለምን የእግዚአብሔር እርሻ ላይ ገበሬ አትኾንም?” የሚል ነገር አንሥቶልኝ ሄደ። ከዚያ በኋላ ያን ዓመት ማሰብ ጀመርኩኝ። እግዚአብሔርም ለእኔ በሚገባኝ መንገድ ከምርቃት በኋላ ወደ አገልግሎት እንደምገባ ይናገረኝ ነበር። በመጨረሻም ወስኜ የኢቫሱን አገልግሎት ተቀላቀልኩኝ።

 • ሕንጸት ፦ ምን ያህል ዓመት አገለገልህ?

ዘላለም፦ ስጀምር ለአንድ ዓመት ነበር የአገልግሎት ውል የነበረኝ፤ ነገር ግን አንዱ ዓመት ብዙም ሥራ የሚሠራበት አልነበረም። ከዚያ ሳየው ሁለት ዓመት ላድርግ እያልኩ፣ ዐሥራ አምስት ዓመት ያህል አገልግዬ ነው የወጣሁት። በመጀመሪያ በደቡብ አካባቢ ባለው ቢሮ (Regional office) ለአራት ዓመታት ያህል አገለገልኩ። የመጀመሪያው የቢሮው አስተባባሪም እኔ ነበርኩ። ለአራት ዓመት በደቡብ አገልግዬ የወደ ፊት ሥራዬ ከአገልግሎት ጋር የተያያዘ እንደ ሆነ ሳውቅ ደግሞ ሥነ መለኮት ለመማር ወደ ኢቫንጄሊካል ቲዮሎጂካል ኮሌጅ (ETC) ነበር የሄድኩት። ከዚያም የኢቫሱ ቢሮ በዋና ጸሐፊነት እንዳገለግል ያደረሰኝን ጥሪ ከተቀበልኩበት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ነው በኀላፊነት ያገለገልኩት። ስለዚህ በድምሩ ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያህል ነው በተቋሙ ሥር የቆየሁት።

 • ሕንጸት፦ የተማሪዎች አገልግሎትን ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ለየት የሚያደርጉ ባሕርያት ምንድን ናቸው?

ዘላለም፦ የተማሪዎች አገልግሎት ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፣ የቤተ ክርስቲያን ደጋፊ አገልግሎት ነው። የወንጌል ዐደራ በዋናነት የተሠጠው ለቤተ ክርስቲያን ነው። ክርስቶስም መሥርቶ የሄደው ቤተ ክርስቲያንን ነው። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስፈጸም በተለያየ አቅጣጫ የሚረዱና የሚደግፉ ብዙ አጋር ድርጅቶች አሉ። ኢቫሱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንግዲህ በተናጠል ይህንን የተማሪ አገልግሎት ይዞ የሚሄድ ነው። ቤተ ክርስቲያን በጣም ሰፊ አገልግሎት አላት፤ ይህ ግን ትኩረት ያደረገው በተማሪ ላይ ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን እዚህ ውስጥ ገብታ ላገልግል ብትል የተበታተነ አገልግሎት ነው የሚሆነው። አጋር ቤተ ክርስቲያናት ጠቀሜታቸው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማይመቹ ቦዎታች ላይ ይበልጥ እንደ ተዘረጋ የቤተ ክርስቲያን እጅ ሆነው ዘልቀው የሚያገለግሉ ናቸው። በዚህ አቅጣጫ በዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆች ያሉ ተማሪዎችን ማገልገል ነው የተማሪ አገልግሎቱ ሥራ።

እኛ ለኢቫሱ አገልግሎት ብያኔ (Definition) ስንሰጥ “ድልድይ ነው” የምንለው። ተማሪዎቹ ከቤተ ክርስቲያን ነው የሚመጡት፤ ተመልሰው የሚሄዱትም ወደ ቤተ ክርስቲያን ነው። አንድ ሰው እንዳለው ድልድይ ላይ ቤት አይሠራም። ቤተ ክርስቲያን የምንኖርባት ሲሆን፣ የተማሪ አገልግሎት ግን እንደ ድልድይ ሆኖ ነው የሚያገለግለው። ይህ እንግዲህ ልዩ የሚያደርገው ባሕርዩ ነው። ይህ እንዳለ ሆነ፣ አገልግሎቱ ደግሞ የራሱ የሆኑ አራት ዋና ዋና ዐላማዎች አሉት። የመጀመሪያው የወንጌል ሥርጭት ሲሆን፣ ይህ በትምህርት ተቋማቱ ቅጥር ግቢዎች የሚካሄድ ነው፤ ሁለተኛው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ነው፤ ሦስተኛው የሚሲዮን አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህ ተግባራዊ የሚደረገው ተማሪዎች በእረፍት ጊዜያቸው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ ወንጌልን የማብሰር ሥራ የሚሠሩበት ነው። አራተኛው ደግሞ መሪነት ሲሆን፣ ተማሪዎች ከዚያ ሲውጡ በተለያዩ ደረጃዎች በመሪነት ሊያገለግሉ ስለሚችሉ ያንን አቅማቸውን እንዲያሳድጉ መርዳት ነው።

 • ሕንጸት፦ በአገልግሎቱ በነበርህ የቆይታ ጊዜ ኢቫሱ እንደ ድርጅት የተሻለ ኾኗል? ከኾነስ አንደ ግለ ሰብ ያንተ ድርሻ ምን ነበር?

ዘላለም፦ በአገልግሎቱና በድርጅታዊ መዋቅሩ ደረጃ ታሳቢ መደረግ ያለበት ነገር፣ እንደ መሪ የእኔ ድርሻ ቢኖርበትም፣ ስኬቱ ግን የእኔ ብቻ አይደለም። ተማሪዎች ዋናውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ ከተማሪዎች አጠገብ በመሆን ቀንና ሌት የሚደክሙ አገልጋዮችም ደግሞ አሉ፤ ቦርዱና የአስተዳድርት አካላትም እንዲሁ። በሌላ በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ ስዎች ወደ ጌታ እንዲመጡ ምክንያት የሆኑ የወንጌል ሥርጭትና የሚስዮን አገልግሎት ክፍል እና ሌሎችም ክፍሎች (departments) ከፍተኛ ሚና አላቸው። ሰለዚህ የሁላችን ድረሻ ተጠራቅሞ ነው ውጤት ያመጣነው።

እንደ ዋና ጸሐፊ ኢቫሱን ስረከብ ከሰባት የማይበልጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነበሩ፤ ከሦስትና አራት የማይበልጡ የአካባቢ ቢሮዎች ነበሩ፤ የተማሪው ቁጥርም ወደ ዐሥር ሺህ የሚገመት ነበር። ስወጣ ግን የአገልጋዮች ቁጥር ከዐርባ የሚበልጥ፣ የተማሪው ቁጥርም ወደ ዐርባ አንድ ሺህ ገደማ የሚገመት ሆኗል፤ የአካባቢ ቢሮዎችም ዐሥራ ዘጠኝ ደርሰው ነበር። ነገሮች አመቺ ሆነው አይደልም ይህ ሁሉ ለውጥ የመጣው። ማደራጀቱ፣ ገቢ ማሰባሰቡ፣ ሌሎችም ሥራዎች ከባድ ነበሩ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ወደ 154 አገሮች በተሳተፉበትና በካናዳ በተደረገ ስብሰባ የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈጣን ዕድገት ካሳዩ የተማሪ እንቅስቃሴዎች አንዱ የኢትዮጽያው እንደ ሆነ ነው የቀረበው። ለዚህ ምክንያት የሆኑ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ፦ የመጀመሪያው ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች በተጨማሪ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መጨመራቸው፣ በየቦታው ዩኒቨርሲቲዎች መከፈታቸውና በተማሪዎች የሚሠራው የወንጌል ሥርጭት ነው። አሁንም ቢሆን ከአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ትልቁ የተማሪ እንቅስቃሴ ነው። ሌላው የኢቫሱ የምሩቃን ኅብረት በአውሮፓውና በሰሜን አሜሪካው ተቋቁሟል። እነሱ ብዙ ሥራ ሠርተዋል። ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርም ጋር ረዘም ላለ ጊዜ አብረን ሠርተናል። በአንዳንድ ቦታዎችም ዩኒቨርሲቲዎች ከከተማው ራቅ ብለው ስለሚገኙ ወደ ዐሥራ አራት በሚሆኑ ቦታዎች ተማሪዎች አነስተኛ ስብሰባዎችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያካሄዱባቸው የራሳቸው የሆኑ ቦታዎች ተገዝተዋል፤ አንዳንዶቹም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሠርተዋል።

 • ሕንጸት፦ ስለዚህ በኢቫሱ በነበረህ አገልግሎት ተሳክቶልኛል ትላለህ ?

ዘላለም፦ በእኔ ዕይታ በእነዚህ ባነሣኋቸው መንገዶች የተሳካልኝ ይመስለኛል። ሰው እንደ መሆነ የራሴ የሆኑ ውስንነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁሉን ነገር ግን መሥራት አልችልም። በአንድም በሌላም በግሌ በእግዚአብሔር ላይ በመታመን እንደ መሪ ውሳኔ በማስተላለፍ፣ በማስተባበርና በተለያዩ መንገዶች በመንቀሳቀስ የራሴን ድርሻ የተወጣሁ ይመስለኛል።

 • ሕንጸት፦ ተግዳሮቶቹስ ምንድን ነበሩ?

ዘላለም፦ ብዙ ውስንነቶች ነበሩ። ለምሳሌ ሰባት ሰው ብቻ ይዞ የነበረው ድርጅት ከዐርባ በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችልበትን የውስጥ መዋቅር አስቀድመን አልሠራንም። አንዳንዶቻችን ብንመኝም ልንሠራቸው አልቻልንም። የእኔም የግል ባሕርይ ተጽእኖ ይኖረዋል ብዬ ዐስባለሁ። የእኔ ዋናው ትኩረት የነበረው “ትልቁ ሥዕል” ላይ ነበር፤ ራእዩን ይዞ የመሄድ፣ ተቋማዊ የሆኑ የተግባቦት (communication) ሥራዎችን ማከናወን እና የመሳሰሉት ላይ እንጂ፣ አስተዳደራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውስንነቶች እንደ ነበሩኝ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ ለዚህም ቢሆን መፍትሔ ለመስጠት ተሞክሯል። አገልግሎቱን ላስረክብ በነበረባቸው የመጨረሻዎቹ ጊዜያት፣ በቦርዱ አማካኝነት ሰዎችን መርጠን ክፍተቶችን ለመሙላት ሞክረናል።

 • ሕንጸት፦ ከአስተምህሮ አንጻር ብዙ እንግዳ ትምህርቶች በተማሪዎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሎ ይነገራልና በዚህ በኩል የገጠማችሁ ችግሮች ምንድን ናቸው?

ዘላለም፦ ይሄ ዋናው ተግዳሮታችን ነው። ይህ ችግር በአንድ ወቅት በጣም ከፍ ይላል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ይረግባል። አሁን ደግሞ እንደገና ያገረሸበት ጊዜ ነው። እንግዲህ እነዚህ አስተምህሮቶች ብዙዎቹ ከእምነት እንቅስቃሴ ጋር የተገናኙ ሲሆኑ፣ ወጣቱ ላይ ነው ትኩረት የሚያደርጉት። ወጣቱ ያለው ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነው። አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎች በእነዚህ ዐይነት ትምህርቶች ውስጥ ከገቡ በኋላ ወደ መሪነት ይመጣሉ። እሱን ለማስተካከል ጥረት ስናደርግ ከተማሪ መሪዎች፣ አንዳንዴም ከአገልጋዮች ጋር የምንጋጭበት ጊዜም አለ። አንዳንዴ ደግሞ ቡድን ፈጥረው እናገኛቸዋለን። አሁን አሁን ግን የአካባቢ ቢሮዎች ስላሉን በእነሱ አማካኝነት በመካከር ነው ኮንፈረሶች የሚደረጉት፣ አገልጋዮችም የሚጋበዙት። በአገር አቀፍ ደረጃም በዓመት አንድ ጊዜ በሚኖረን አጠቃለይ የአብሮነት ጊዜም ላይ በዚሁ ጕዳይ ላይ ውይይቶች እናካሂዳለን።

 • ሕንጸት፦ በኢቫሱ ውስጥ የነበርህን አገልግሎት ያቆምክበት ሁኔታና ጊዜው ትክክለኛ ነው ብለህ ታምናለህ?

ዘላለም፦ እንግዲህ የዋና ጸሐፊነቱን ሥራ ስጀምር ለአራት ዓመት በሚል ነበር። ከዚያ በኋላ ነበር እንደገና የቀጠልኩት። ቦርዱን ለመልቀቅ በተገቢው መንገድ ከጠየቅሁ ሁለት ዓመት አልፎኛል። የመጀመሪያው ምክንያት መማር እፈልግ ስለ ነበረ ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት የሚል ነበር። ሁለተኛው በእኔ ሊሠራ የሚችል የተወሰነ የአገልግሎት ጊዜ አለ፤ በሌላ ሰው ደግሞ የሚቀጥል አለ። ከእኔ በፊት ብዙ ነበሩ፤ እነሱ ለፍተው እኔ ያጨድኳቸው አሉ። ከእኔ በኋላ ደግሞ የሚመጣ ሌላ ይኖራል። ድርጅቱን በራሱ መንገድ ይዞ የሚሄድ ሰውም ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ለመልቀቅ ጊዜው እንደ ሆነ ነው የማምነው።

 • ሕንጸት፦ አንዳንድ ሰዎች የአንተን ከአገልግሎት ኀላፊነት መልቀቅ ተከትሎ በተካሄደው የመተካካት ሂደት ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ ይደመጣል። ይህ ቅሬታ ተገቢ ነው ትላለል?

ዘላለም፦ ʻተገቢ ናቸው፤ አይደሉምʼ የሚለው የሚወስነው በምናይበት መንገድ ነው። አሁን እኔ ምክንያቶችን ላቀርብ እችላለሁ፤ ሌላውም እንደዚሁ ምክንያቶችን ሊያቀርብና ቅሬታዎችን ሊያነሣ ይችላል። ይሁን እንጂ ኢቫሱ እንደ ድርጅት የራሱ አካሄድ አለው። በመጀመሪያው እንደ ድርጅት ለውጭ ማስታውቂያ ወጥቶ ነበር፤ ማለትም ለኢቫሱ ባለ ድርሻ አካላት ከምሩቃን መካከል ሰው ቢገኝ ተብሎ። ነገር ግን የወጣውን መሥፈርት የሚያሟላ ሰው ሲታጣ፣ ቦርዱ ተማክሮ የውስጥ ማስታወቂያ በማውጣት ሂደቱን ተከትሎ አሁን ላለው ሰው ነው ያስረከበው። ሽግግሮች በተፈጥሯቸው በተለያዩ መንገጫገጮች ያልፋሉ። ግን ምንም እንኳን መንገጫገጮች ቢኖሩም ቦርዱ፣ እኔንም ጨምሮ፣ ያመነበትን ነው ያደረግነው። በእኛ በኩል ደግሞ አመራሩ ያሳለፈው ውሳኔ በጣም ንጹሕና በብዙ ጸሎትና ውይይት የተካሄደ ነው።

 • ሕንጸት፦ በኢቫሱ ውስጥ ልምድ አላቸው የተባሉ አገልጋዮች መልቀቃቸው ይነገራል። በርግጥም እንደሚባለው ከሆነ፣ በአገልግሎቱ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ እንዴት ትገልጸዋለህ?

ዘላለም፦ የተወሰኑ አጋልጋዮች እንደለቀቁ እኔም ሰምችያለሁ። ነገሩን ግን በሁለት መንገድ ነው የማየው፤ አንዱ ልምድ ያላቸው አገልጋዮች ሲለቁ ልምድና ሙያቸውን ይዘው ነው የሚሄዱት። ይህን መሰሉ ነገር ሲከሰት ማንኛውም ድርጅት የሚያጣው ነገር እንዳለ ሁሉ፣ ኢቫሱም የሚያጣው ነገር አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜያችንን ጨርሰን ከኾነ የለቀቅነው፣ አገልግሎቱ የእግዚአብሔር ነው፤ አዳዲስ ሰዎች ሲመጡ በእነሱ መሥራት ከፈለገና ካሰበ በተሻለ መንገድ አገልገሎቱን ይዘውት ሊሄዱ ይችላሉ።

 • ሕንጸት፦ በተያያዘም አገልጋዮች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ እንደ ሆነ ይነገራል። በአንተ የአመራር ጊዜ ተቋሙ አለበት የሚባለውን ይህን ክፈተት ለመድፈን ያደረከው ጥረት ምን ይመስላል?

ዘላለም፦ አንድ አገልጋይ ኢቫሱን ሲቀላቀል የራሱን ደመወዝ የማሰባሰብ ኀላፊነት የእሱ እንደ ሆነ ይነገረዋል። ሲገባ የተወሰነ መጠን፣ ከዚያ እየቆየ ሲመጣ ሙሉ ደመወዙን የማሰባሰብ ኀላፊነት አለበት። ሁላችንም ይህን አውቀን ነው የገባነው። አገልግሎቱ በትግል የተሞላ ነው፤ አንድም ቋሚ የገቢ ምንጭ የለውም። በሌላ በኩል ለእያንዳንዱ ሥራ ገቢ አሰባስበን ነው የምንሠራው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመስፋፋታቸው የተነሣ፣ በሁሉም ቦታ የአገልጋይ ፍላጎት አለ። ያንን ለሟሟላት ስንል በውስጥ ያሉትን ማጠናከር አልቻልንም። ገንዘቡን አሁንም የማሰባሰብ ኀላፊነት የአጋልጋዮች ቢሆንም፣ ቢሮው በተወሰነ መልኩ ድጋፍ ያደርጋል። አገልጋዮች ቀለባቸውን ወይም ደመወዛቸውን እንዲሰበስቡ ይበረታታሉ እንጂ ቢስበስቡም ባይሰበስቡም ደመወዛቸው መከፈሉ ግን አይቀርም። ጥቂቶች ግን ከራሳቸው ያለፈም ያደርጋሉ። በዚህ አጋጣሚ አገልጋዮችን በሙሉ ላመሰግን እወዳለሁ። የእነሱን መነሣሣት፣ መሰጠት፣ የሚከፍሉትን ዋጋና መሥዋዕትነት ስመለከት በእግዚአብሔር ፊት የማለቅስባቸው ጊዜያት ሁሉ አሉ።

 • ሕንጸት፦ በቤተ እምነት ጥላ ሥር ያሉ የተማሪ አገልግሎቶች በኢቫሱ አገልግሎት ላይ ያላቸው አሉታዊ ተጽእኖ ምን ይመስል ነበር ?

ዘላለም፦ ኢቫሱ ምንም እንኳን የራሱ ተልእኮና ራእይ ቢኖረውም፣ ራእዩና ተልእኮው ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ነው። ይህ ካልሆነ የኢቫሱ መኖር ምንም ፋይዳ የለውም። እኔ በአጥቢያዬ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነኝ፤ ከተለያዩ የመሪነት ቦታ ላይ ካሉ ሰዎችም ጋር የቅርብ ግኑኝነት አለኝ። ʻኢቫሱ ከተማሪዎች አካባቢ ቢወጣና በተደራጀ መልክ አገልግሎት መስጠቱ ቢቀር ምን ይፈጠራል?ʼ ብዬም አስባለሁ። ብዙውን ጊዜ ነገሮች ሲበላሹ ነው ጥቅማቸውን የምናው። የተማሪ አገልግሎት በዚያ ያለው ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ ነው። ከዚህ አኳያ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን መከታተልና መደገፍ አለባት። የኢቫሱ አገልግሎት ከተጀመረ አሁን ኀምሳ ዓመት አልፎታል፤ በእነዚህ ዓመታት ውሰጥ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የወጡት ከኢቫሱ ነው።

 • ሕንጸት፦ ከቤተ እምነት የተማሪዎች አገልግሎቶች አካባቢ በኢቫሱ ላይ የሚነሣ ክስ አለ። ይኸውም፣ በኢቫሱ አገልግሎት ሥር ያለፉ ተማሪዎች ወደ ቤተ እምነቶቻቸው አይመለሱም የሚል ነው። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

ዘላለም፦ ʻኢቫሱ በሚሰጠው አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያን አካባቢ አንዳንድ ቅሬታዎች ይቀርባሉ ወይ?ʼ እውነት ነው። እኔ ግን መልሼ ጥያቄ ብጠይቅ ማንን ነው የምንወቅሰው? ኢቫሱ የቤተ ክርስቲያን ነው። እኔ እንግዲህ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ነው በኢቫሱ በኀላፊነት ያገለገልኩት። በጣት ከሚቆጠሩ ቤተ እምነቶች ውጪ ቀርቦ ቅሬታውን ያቀረብልን አልነበረም። አንዳንዶችን እንደውም እኛው ራሳችን ሄደን ነው ያነጋገርናቸው። አብሮ መሥራት ነው መፍትሔ የሚያመጣው። የሚበላሹ ነገሮች ካሉ ቤተ ክርስቲያን የማረም፣ የማስተካከል መብትም ኀላፊነትም አለባት።

ኢቫሱ ከሚወቀስባቸው ጉዳዮች አንዱ ተማሪዎች ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው አይመለሱም የሚል ነው። እኛ ይህ እንዳይሆን ነው የምንሠራው። ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት፣ “ሕይወት ከምርቃት በኋላ” በሚል ሐሳብ ትምህርት እናዘጋጃለን። የቤተ እምነት ኅብረት (Family Fellowship) የሚባል ፕሮግራም አለን። በዚህ ሁሉም ቤተ እምነቶች የራሳቸውን ልጆች የማግኘት ጊዜውም ሆነ ዕድሉም በእኛ በኩል ክፍት ነው። ይህን ለማስተካክል ሲሉ አሁን አንዳንድ ቤተ እምነቶች የራሳቸውን ኅብረቶች ለማደራጀት ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ ሌላ አደጋ አለው። ሁሉም ቤተ እምነቶች በዚህ መልክ ማደራጀት ከቀጠሉ ምን ዐይነት ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል በዚያ ውስጥ ያለፈ ሰው ነው የሚያውቀው። ነገር ግን እነዚህን ሁሉ በማሰባሰብ በተደራጀ ሁኔታ የሚጠብቅ አካል ካለ እሱን እንዴት ነው የምንረዳው ነው መባል ያለበት።

ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤቶች ልከው እስኪመጡ ቁጭ ብሎ መጠበቅም ሆነ፣ አሁን እየሆነ እንዳለው ሙሉ በሙሉ ተስታፎ ማድረግ ሁለቱም ጉዳት አለው። ቤተ ክርስቲያን የራሷን የተማሪዎች አገልግሎት ስትጀምር ልጆቹ ናቸው የሚጎዱት፤ ወደ ኢቫሱም ወደ ቤተ እምነታቸውም ኅብረት መሄድ ይፈልጋሉ። እዚህም እዚያም ብዙ አገልግሎቶች አሉ፤ ይሄ ደግሞ በትምህርታቸው ላይ ተጽእኖ አለው። ሌላው የምጠይቀው ነገር በቤተ ክርስቲያናት ምን ያህል የተደራጀ የወጣቶች ፕሮገራም አለ? ልጆቹ ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ ከሄዱ በኋላ በመከታተል፣ ክረምት ሲመጡም ለእነሱ የሚሆን ፕሮግራም በማዘጋጀት ወጣቶችን የሚይዙ ጥቂት በስም የማውቃቸው ቤተ ክርስቲያናት በእርግጥ አሉ። ይህ ካለተደረገ ልጆቹን እንኳን እኛ ወላጆችም ሊቆጣጠርዋቸው አይችሉም፤ ልጆቹም በዚያ ዕድሜያቸው ብዙ ነገር ሊሞክሩ ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያን የራሷን ኀላፊነት መወጣት አለባት።

 • ሕንጸት፦ አሁን በኢቫሱ ውስጥ ያለህ ተሳትፎ ምን ይመስላል? የወደ ፊት የአገልግሎት አቅጣጫህስ ወዴት ያመራል?

ዘላለም፦ ኢቫሱን በተመለከተ አመራሩን አስረክብያለሁ፤ ነገር ግን በማንኛውም አቅጣጫ ለተማሪዎች ቢሆን ለአገልጋዮች እንዲሁም ለአመራሩም ሁሉ ያለኝን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ ነኝ። አሁን ገና ሽግግር ላይ ስለሆንን በሌላ ደረጃ ለማገልገል ጊዜው ገና ነው። ግን እንደ አንድ ምሩቅ ባለ ድርሻ ነኝ፤ እንደ አገልጋይ ደግሞ የበለጠ ነገሩ ይገባኛል። አንድ የምንለው ነገር አለ “አንዴ ኢቫሱ ከሆንክ ዕድሜ ልክህን ኢቫሱ ትሆናለህ።” አገልግሎቱ ደምህ ውስጥ ነው የሚገባው። በአሁኑ ጊዜ ብዙም ሳልርቅ፣ ብዙም ሳልቀርብ መኻል ላይ ሆኜ አስተዋጽኦ እያበረከትኩ ነው። አዲሱ አመራር የራሱ አካሄድ ስለሚኖረው የእኔ ጥላ ማጥላት የለበትም። ነገሮች በተረጋጋ ሁኔታ ሲቀጥሉ የበለጠ የምሳተፍ ይሆናል። ራሴን በተመለከተ ደግሞ ትምህርት ላይ ነኝ። አሜሪካን አገር በሚገኘው Gorden Conrwel Theological Seminary በሥነ አመራር የሁለተኛ ዲግሪዬን እየሠራሁ ነው።

 • ሕንጸት፡- በቅርቡ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ ምርጫ ጋር ስምህ ተያይዞ ተነሥቶ ነበር። ለመወዳደር ዐስበህ ነበር እንዴ?

ዘላለም፡- እሱ እንግዲህ የሰዎች አመለካከት ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥ እውነቱን ለመናገር እግዚአብሔር እዚህች ምድር ላይ በእኔ የሚሠራው ነገር እንዳለ፣ እኔም ልሠራው የሚፈልገው ነገሮች አንዳሉ ነው የማስበው፡፡ ትምህርቴን በተመላላሽ መማር የፈለግሁት ከዚሁ የተነሣ ነው፡፡ በረጅም ጊዜ ርቀት በአገር አቀፍ ደረጃ ልሠራቸው የማስባቸው ነገሮች አሉ፤ አሁን ግን የአብያተ ክርስቲያናት ዋና ጸሐፊነትን በተመለከተ ጊዜው አይመስለኝም፡፡ ከዕድሜም ሆነ ከልምድ አኳያ ሊሆን ይችላል ገና ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ የእግዚአብሔር ሐሳብ ከሆነ ወደ ፊት ሊሆን ይችላል፡፡

 • ሕንጸት ፦ በመጨረሻ የምትለው ካለህ?

ዘላለም፦ እኛ ዐርባ አንድ ሺህ ተማሪዎች እዚህ መናገር ስለማይችሉ ወክለን እንናገራን እንጂ፣ ተግባራዊ የሆነውን ሥራ የሚሠሩት እነሱ ናቸው። ደግሞ ከእነሱ ጋር በቅርበት ሆነው ትልቅ ሥራ የሠሩትን አገልጋዮችንና እዚህ ያሉ የሥራ ክፍሎችን፣ በተለይም የሚስዮንና የወንጌል ሥርጭት ክፍልን፣ በዚያ ያሉ አገልጋዮችን በጣም ላመሰግን እፈልጋለሁ። ቦርዱ ትልቅ ሚና አለው። በአገልግሎቴ ወቅት ከጎኔ የቆሙ ምሩቃን፣ ቤተ ክርስቲያናት እና ግለ ሰቦች (አገር ውስጥም ሆነ ውጪ ያሉ) ማመስገን እፈልጋለሁ። ከሁሉ በላይ ውድ ባለቤቴን እንዲሁ ማመስገን እፈልጋለሁ። የሚገርምህ እኔ የዛሬ ሰባት ዓመት ሳገባ ብዙዎች አላገቡም ነበርና በሚስት እንደ እኔ ይባርካችሁ ነው የምለው። ሜሪን አመሰግናታለሁ።

 • ሕንጸት ፦ ሜሮን ከኢቫሱ ማሳ ነው የታጨደች ናት?

ዘላለም፦ ልክ ነህ (ሳቅ…) የሚገርምህ ምርቃቴ ሠርቷል፤ ብዙዎች በጥሩ ሚስት ተባርከዋል። በመጨረሻም፣ ሕንጸትንም ማመስገን እፈልጋለሁ።

 • ሕንጸት ፦ እናመሰግናለን!

Asnake Endrias

እግዚአብሔርን የመፍራት በረከት

የምንኖርበትን ዓለም በትዝብት መነፅር ብንመለከት የሰው ልጅ ሕይወት ውጣ ውረድና ትግል የበዛበት በመሆኑ ፍቅርና ጥላቻን እንዲሁም በእምነትና በክህደት መካከል ያለው የነፍስ ፍትጊያ እንዴት እንደ ሆነ ለመረዳት አንቸገርም። ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ራሱን ከሌላው የተሻለ አድርጎ ለሌሎች ለማሳየት ወይም ከሌላው ሰው በልጦ ለመታየት የማይምሰው ጉድጓድና የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የተፈጥሮ ሕግን ተከትሎ ጊዜው ሲመሽና ሲነጋ የሰውም ሕይወት አንዴ ሲጨልም፣ አንዳንዴ ደግሞ ፍንትው ብሎ ፀሓይ እንደወጣችለት ቀን ሲበራ ይታያል።

ተጨማሪ ያንብቡ

አስታራቂ መሪዎች ይፈለጋሉ!

በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኀን የምንሰማው የጦርነት እና የግጭት ወሬ የምንኖርባትን ዓለም በሰቆቃ የተሞላች አድርጓታል፡፡ ጥላቻውና በቀለኝነቱም ከቀን ወደ ቀን እያየለ የሚመጣ እንጂ የሚበርድ አይመስልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.