[the_ad_group id=”107″]

ኢትዮጵያ የ“አረማዊ ደሴት”?


ከሁሉ አስቀድሜ የእግዚአብሔር ሰላም ይድረሳችሁ እላለሁ።

ለዚህ ሐተታ መነሻው የ”እሬቻ” በዓልን ማክበር መስፋፋቱ ነው። ስለ እሬቻው በጽሑፉ መጨረሻ የምመለስበት ይሆናል። መጀመሪያ ግን አስረጂነት እንዳለው ስላሰብኩ በአራተኛው ምዕተ ዓመት መባቻ ስለ ነበረው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በገባኝ መጠን እተርካለሁ።

በአራተኛው ምዕተ ዓመት መባቻ ላይ፣ አረማዊነት በክርስትና ላይ የሞት የሽረት ፍልሚያ በሮሜ ግዛት (ኢምፓየር) አካሂዷል። ያንን ፍልሚያ የመራው በእልዋሪቆን ክፍለ ጦር የተሾመው ጥንቅቁ ዐፄ (ኢምፐረር) ዲያቅልጢያኖስ ነበር። ይኸው ዐፄ በወታደራዊ ሥርዐት አልበኝነትና ተያይዞ በመጣው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር ምክንያት በመፈራረስ ላይ የነበረውን የሮማን ግዛት እንደገና በሥርዐት አደራጀ፣ ገነባ። ክርስቲያኖቹ የባዕድ አምልኮ ይሉት የነበረውን የሮማውያንን ባሕላዊ አምልኮና አስተሳሰብ ሁሉም ሮማዊ እንዲከተለው ፖሊሲ አድርጎ አወጣ1። ይኸው ሕዝባዊ ሃይማኖት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ገጽታ ነበረው። ማኅበራዊ ገጽታው ሕዝቡ በጠቅላላ ወይም በከፊል አደባባይ ወጥቶ ሰልፍ ማሳየት፣ መሥዋዕት ማቅረብ፣ ጨዋታ መመልከት ሲሆን2፣ ፖለቲካዊ ገጽታው ደግሞ ለመንግሥት ታማኝነትን ለመግለጽ የሚደረግ መሆኑ ነው3

ዐፄው በዚሁ ፖሊሲው መሠረት ሃይማኖቱን የማነቃቃት ሥራ ሠራ4። የውስን አካባቢ አማልክት ለነበሩት እጅግም ትኩረት ያልሰጠ ቢሆንም፣ ለመላው አገር ሰላምን ያደርጋሉ ለተባሉት ግዛት አቀፍ አማልክት መሠዊያዎችን ሠራ፤ ሐውልቶችን አቆመ፤ ቤተ መቅደሶችን ዐደሰ፤ አዳዲሶቹን አነጸ5፤ አረማዊ እምነቱን የሚያራምዱ ፈላስፎችን በአማካሪነት ሰየመ፤ አረማውያንን በአገረ ገዢነት ሾመ። ስለ ሃይማኖቱ ጥልቅ ስሜት ነበረውና ራሱም መሥዋዕት አቀረበ።

ይኸንን ሲያደርግ ክርስቲያኖቹን አልተጋፋም። ምክንያቱ በውል ባይታወቅም በአደባባይ እየተገኙ በአረማዊው ሥርዐት እንዲካፈሉ አላስገደዳቸውም፣ ኋላ ላይ የጭቃ ጅራፉን ማምጣቱ ባይቀርም። እንዳውም ለበርካታ ዓመታት በቤተ መንግሥቱ፣ በሲቪሉ እንዲሁም በወታደራዊው መስክ የማይናቅ ሚና እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል6። በግል ጠባዩም ምስጉን ሲሆን፣ ጥምቀት የቀረው ይመስል ነበር7፤ አገሬውም ሞራል እንዲኖረው የሚገድደው ነበር8። ይህን ሃይማኖታዊ ፖሊሲ ለመምረጡ ገፊው ምክንያት ምን እንደ ነበር የተለያዩ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ፤

  • እርሱና አጋዥ ገዢዎች ወግ አጥባቂ የሃይማኖቱ ተከታዮች ነበሩና በሃይማኖት ተቆርቋሪነት ተገፋፍቶ ያደረገው ነው9
  • ዐፄዎች የጥንቱን አምልኮ ለማስቀጠልም ሆነ አዲስን ለማስተዋወቅ ኀላፊነት ነበረባቸውና ይኸንኑ ኀላፊነት ለመወጣት ነው10። (በጥንቱ አምልኮ “ሕዝቡ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐትን በትትክል ሊፈጽም፣ አማልክቱ በለውጡ ሀብትን፣ ጤንነትንና ወታደራዊ ድልን ሊሰጡ የሰላም ስምምነት” ነበር።)
  • በወቅቱ ለሮማ መመሰቃቀል ምክንያቱ የሮማውያን አምልኮ ማሽቆልቆሉ ነው ብሎ ሕዝቡ ያምን ነበርና11፣ የጥንቱን ገናናነት መላሽ ተብሎ እንዲታይ ነው።12 (መድብለ አምላክ ሃይማኖታቸው ለሮማውያኑ የገናናነታቸው ምንጭ አድርገው የሚወስዱትና በዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚያሳዩት ልምምድ ነበር13)።
  • ይህንን የጥንቱን የገናናነት ስሜት ለተያያዘው የግዛት ግንባታ የሕዝብን ድጋፍ መግዢያ ሊያደርገው አስቦ ይሆናል1415
  • አማልክቱን በጋራ ማምለክ የተባበረ ግዛት ምልክትም ማስረገጫም ነበርና ለሕዝቡ የአንድነት ስሜት ይሰጣል ብሎ አስቦበት ነው16
  • ቀደም ሲል ሲደረግ እንደቆየው ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ እንዳይደረግበትና እንዳይገደል በወታደሩ ዘንድ ቅቡልነቱን ለማረጋገጥ ነው። (በወታደሩ ዘንድ ለፀሓይ አምላክ (ለጁፒተር) መሥዋዕት ማቅረብ ተወዳጅነት ነበረው17።) ዜጎችም ለመንግሥት ያላቸውን ታማኝነት እንዲያሳዩበትና እንዲያረጋግጡበት ነው18 የሚሉ ይገኙበታል።

የሮማ ባሕላዊ ሃይማኖት የሌሎችን አማልክት የሚያገልል አልነበረም። ሮማውያኑ በወረራ የሚይዟቸውን ሕዝቦች አማልክት ሴኔቱ፣ ሲያጸድቀው ከሮማውያኑ አማልክት ጋር ተቀላቅለው እንዲመለኩ ይደረጋል1920። (በነገራችን ላይ ሴኔቱ ውድቅ አድርጎበት እንጂ ንጉሥ ጢባርዮስ (የሉቃስ 3፥1) ኢየሱስን ከሮማውያን አማልክት መካከል ሊቀላቅለው ፈልጎ ነበር ይባላል21)። የሮማውያንን አማልክት ክብር ሳይነካ ማንም በሮማዊ ግዛት የገባ ሕዝብ የየራሱን አምላክ ቢያመልክም የሚከለከል አልነበረም። ይህም ማለት ለሮማውያኑ ዋና ከሚባሉት ‘አማልክት’ ለማናቸውም መሥዋዕትን እያቀረበ የራሱን አምላክ ቢያመልክ አይከለከልም ነበር ማለት ነው። ይኸንን ሲያደርጉ በሥርዐታቸው አሳፋሪ ነገር ከታየባቸው አምላኪዎቹ ይቀጣሉ። ሮማውያኑ ከአስነዋሪው ሥርዐት ሲካፈሉም ፍርድ ይጠብቃቸዋል2223። በጊዜው ይህ የሮማዊነት ማንነት መገለጫ ከሆኑት አንዱ ልማድ ነበርና፣ የሮማውያንን ባሕላዊ ሃይማኖት የማይከተሉቱ በዚህ ማዕቀብ ውስጥ እስካደረጉት ድረስ ሃይማኖታቸውን እንዲያከናውኑ ይፈቀድ ነበር።

ይህ እንደዚህ ሆኖ ሳለ፣ በሮማውያኑ ግዛት ይኖሩ የነበሩቱ አይሁዶች፣ ማኒኪያኖች፣ ግኖስቲኮችና ቀጥተኛዎቹ ክርስቲያኖች ግን አምላካቸውን ለማቀላቀልም ሆነ በሮማውያኑ ቁንጮ አምላክ ሥር ለማድረግ የሚፈቅዱ አልሆኑም። ጥንታዊ መሆን እንደ መልካም ነገር ይቆጠር ነብርና እንዲሁም ሌሎችን ወደ ይሁዲነት አይቀይሩም ነበርና፣ ባለ ጥንታዊ ሃይማኖት አይሁዶቹ መሥዋዕት ከማቅረብ ሥርዐቱ ግዴታ ነጻ ተደረጉ፤ በንግዱና በፍርድ ሥርዐቱ ተካፈሉ፤ ከማኅበረ ሰቡ ተዋሐዱ። ምንም እንኳ በሮማውያኑ አማልክት ባያምኑም መናፍቃኑ፣ ግኖስቲኮቹ ደግሞ በታዘዙ ጊዜ በባዕድ አምልኮው ሥርዐት ለመካፈል እምቢ አላሉምና24 እነርሱ አልተነኩም።

የማኒኪያኖቹና የቀጥተኛ ክርስቲያኖቹ ሁኔታ ግን የተለየ ሆነ። ማኒኪያኖቹ (መሥራቹ ማኒ ፋርሳዊ ነበር) ከፋርስ መንግሥት ጋር ውስጥ ለውስጥ ይገናኛሉ፣ በፋርስና በሮማ ግዛት መካከል በነበረው ጦርነት ለፋርስ ያግዛሉ ተብለው ተጠረጠሩ፤ ሌሎችን ወደ እንግዳ ሃይማኖታቸው ያፈልሳሉም ተባሉ። በእነዚህ ምክንያቶች በገዢዎቹ ስላልተወደዱ የማጥፋት ዘመቻ ተካሄደባቸው። በኋላ በክርስቲያኖቹ ላይ ስለሚነሣው ስደት ማሟሻ ተደረጉ25

ቀጥተኛ ክርስቲያኖቹ ሃይማኖታቸው ጥንታዊ ያልነበረ ከመሆኑም በላይ፣ እምነታቸውን ከይሁዲነት ነጥለው ሲያሳዩት ኖረዋልና በመጀመሪያ ባይነኩም በመጨረሻ ግን ከአይሁዶቹ ጋር ተቆጥረው የሚዘለሉ አልሆኑም። በሌላ በኩል ሮማውያኑ እንደሚጠብቁባቸው የክብረ በዓሎችንና የፌሽታ ቀኖችን አያከብሩም፣ በሰልፍ መታየትና በጨዋታ ሥፍራም ለመገኘት አሻፈረኝ የሚሉ ሆኑ። በቤተ መቅደሶችና በመሠዊያ ሥፍራዎች እየተገኙም መሥዋዕት አያቀርቡም፣ አያመልኩምም26፤ ለመሥዋዕትነት ከታረደው ሥጋም አይበሉም። ለይስሙላ እንኳ በውጭያዊ ሥርዐቱ አይካፈሉም፤ ዕጣኑን እንኳ አይበትኑም። እነዚህን እምቢ ማለታቸው ሳይበቃቸው ለባሕላዊ አማልክቱ መሥዋዕት ማቅረብ ጣዖትን ማምለክ ነውና መሥዋዕት አታቅርቡ በማለት ሌሎቹን የሚያከላክሉና ያቀረቡትንም የሚወቅሱ27 ሆኑ።

በሳንቲሞችና በስጦታዎች ላይ ቄሳሮቹ የአማልክት ልጆች ተደርገው መቀረጻቸውና28 ወታደሩ በሚያደርገው አምልኮና ጥንቆላ ሥራ መካፈሉ የማይመቻቸው ነበርና በውትድርና ለመልመልም እምቢተኝነትን አሳዩ። በኋላ ላይ በርግጥ ገዢዎቹ ራሳቸው ከውትድርናው አሰናብተዋቸዋል።

እንዲህም አስተማሩ፦ ‘አረማውያኑ የምታመልኳቸው አማልክት የማይሰሙና የማይናገሩ ግዑዛን ጣዖቶች ከበስተኋላቸው ያሉት መናፍስት መሰሪ አጋንንት ናቸው29። ይኸኛው ዓለም ለሚመጣው ዓለም የዝግጅት ሥፍራ ነው። እናንተ የምታመልኳቸው አማልክት አሉ ቢባሉና ይረዳሉ ቢባል እንኳ፣ የሚረዱት ለዚህና ለአሁኑ ዓለም ብቻ ነው። የዘላለም ጥፋትን ለማምለጥ ወይም የዘላለም ሽልማት ለማግኘት አይረዱም። በመንግሥተ ሰማያት የዘላለም ደስታ ይገኛል። በገሐነም እሳት ለዘላለም መቃጠል አለ። ከገሐነም ማምለጥም ሆነ መንግሥቱንም መውረስ የሚቻለው ሰማይንና ምድርን፣ ባህርንም በውስጡ ያሉትን ሁሉ የፈጠረውን እውነተኛውን አምላክ በማመን ነው30። ኢየሱስ ተሰውቶልናል ሌላ መሥዋዕት አያስፈልገንም’ እያሉ አስተማሩ። በዚህ ዐይነት መንገድ ሌሎቹን አማልክት ዕውቅና ለመስጠት እምቢ አሉ።

አረማውያኑም ቢሆኑ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ልኂቃኑ ከገዢዎቹ ጋር አብረው ክርስቲያኖቹን ሞገቱ። የተማሩቱን ወደ አረማዊ ሃይማኖት ለመመለስ31 በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩትን ክርስቲያኖችም ለማስከተል በብዙ ተጉ።እነዚያ ሁሉ ቢመለሱ በትምህርታቸው መድብለ አምላክ ሃይማኖቱ አይዳከምም፣ የሮማ ግዛትም ምንኛ በጠነከረ ብለው አሰቡ32። በዚህ ግባቸው መሠረት ፀረ ክርስቲያን ሐተታ ጻፉ፣ ፕሮፖጋንዳም አሠራጩ።

ክርስትናን የማይመስል33 አድርገው ተናገሩበት። የአዲስ ኪዳን መጽሐፍን በልብ ወለድና በቅራኔ የተሞላ አድርገው ለማሳየት ተጣጣሩ። ታምራቱንም የፈጠራ ታሪክ አድርገው ሳሉ። ጴጥሮስንና ጳውሎስን (በአጠቃላይ ሐዋርያቱን) እየዞሩ ውሸት የሚያስፋፉ34 በማለት ስማቸውን አጠፉ። ክርስቶስንም አውርደው ከ“ቲያናው አፖሎኒየስ”35 ጋር በማወዳደር አምላክ እንዳልሆነ36 ለማሳየት ደከሙ፤ የክርስቶስን ትምህርት ተገዳደሩ። እንዲህ በማለት፦ “እንዴት ሀብታሞችን መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ ያገልላል? እንዴትስ አጋንንቱ እሪያዎች ውስጥ እንዲገቡ ይፈቅዳል?”37

ክርስቲያኖቹንም እብሪተኛ፣ ያልተማሩ አጭበርባሪዎች በማለት አበሻቀጧቸው። ‘የፀሓይ አምላክን እያመለኩ ክርስቶስን የእርሱ አንዱ ነጸብራቅ አድርገው ማምልክ ይችሉ38 አይደለምን? ክርስቶስ ራሱ የብርሃን አምላክ ነኝ ይላል አይደለም? የራሳቸውን አምላክ እንዳያመልኩ ማን ከለከላቸው?’ በማለት ከአረማዊው ሃይማኖት ጋር ለማቀናጀት ሞከሩ። እግዚአብሔር ብቻውን አምላክ መሆኑን አላስተዋሉም። አረማውያን ፈላስፎችም ቢሆኑ የተንዛዛውንና ሥርዐት ያልያዘውን የአማልክትን መብዛት39 እንዲሁም የእንስሳትን መሥዋዕት መደረግ በሒስ መጥረባቸው አልቀረም። “እነርሱ ባላጠፉት ጥፋት ስለ ምን እንስሳቱ ይሠዋሉ?” ጥያቄያቸው ነበር። ነገር ግን በባሕላዊ ሥርዐቱ በአዳባባይ እየተገኙ ስለሚካፈሉ የሚናገራቸው አልነበረም40። ለዚህም ይመስላል አማልክቱን ሁሉ በአንድ ዋና አምላክ ሥር ለማዋቀር የተሞከረው41

አረማዊ ሃይማኖት በግልና በልብ ማመንን አይጠይቅም፤ በግል ድነትን የሚሰጥም አይደለም። ውጪያዊና ማኅበራዊ ሥርዐቱን42 ማክበርን ብቻ የሚፈልግ ሃይማኖት ነው። ክርስትና ግን ለዘላለም የግል ድነትን ይሰጣል። ስለዚህ ቀስ በቀስ ትዕግስት በተሞላው የማስተማርና አርአያ የመሆን ሥራ መጀመሪያ በተማሪነት በማቆየት ከዚያ በኋላ ሙሉ የክርስቲያን ማኅበር አባላት በማድረግ የወቅቱ ክርስቲያኖች ብዙዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አፈለሱ43። ክርስትና በገጠሬውም በከተሜውም በሀብታሙም በድኻውም ዘንድ በቁጥር ትልቅ እምርታ አሳየ። ክርስቲያኖቹ እየበዙ መሄዳቸው ግን አምልኮታዊና ፖለቲካዊ44 ገጽታ ያለውን ሥጋት በገዢዎቹ አስከተለ። አምልኮታዊው ሥጋት የሌሎቹን አማልክት አለመቀበላቸውና የአረማዊነት ተከታዩ ቁጥር እየቀነሰ ለመሄዱ ምክንያት መሆናቸው ሲሆን፣ ፖለቲካዊው ሥጋት ደግሞ ዲያቅልጢያኖስ እና ጓደኞቹ የገነቡትን አስተዳደር እድገቱን የሚገታ፣ ቀጣይነቱን የሚያሰናክል መስሎ መታየቱ ነው።

አዎ፤ ክርስቲያኖቹ ለሮማዊነታቸው የማይታመኑ ሆነው ታዩ። ከማኅበረ ሰቡ ያፈነገጡ ተደርገው ተቆጠሩ። እንደ ክርስቲያኖቹ ሐሳብ ግን፣ ለሮማዊነታቸው ምንም የሚያስጠረጥር ነገር የለውም። የሚኖሩት በሮማውያን ምድር ነው፤አለባበሳቸው፣ አመጋገባቸው፣ ቋንቋቸውና ልማዳቸው እንደ አረማውያኑ ጎረቤቶቻቸው ነው። ችግሩን ይጋራሉ፤ ከሮማውያን በምን ይለያሉ?

ታማኝ ተደርገው አለመቆጠራቸውን አልተቀበሉትም። ቀረጥን ይከፍላሉ፣ ስለ ገዢዎቹ ጤንነት እንዲሁም አገዛዛቸው መልካም እንዲሆን ይጸልያሉ፤ ስለ ሰዎች ልጆች ሁሉ ስለ ለማኅበረ ሰባቸውም ይማልዳሉ። የቀደሙ እናቶቻቸውና አባቶቻቸው ያደረጉት ይኸንኑ ነውና። ስለዚህ ስለ ምን እንደማይታመን ወገን ይቆጠራሉ? ክርስቲያኖቹ በአረማውያኑ አምልኮ ጉዳይ ላለመነካካት የተገፋፉት በእምነታቸው የማይቀበሉት ልማድ ስለ ሆነ ብቻ ነው። አረማውያን ባለሥልጣኖቹ ግን የሚታያቸው የማይታዘዙ፣ መንቻኮች፣ ከሃዲዎች፣ ለሕግ የማይገዙ እብሪተኞች45 እንደሆኑ ነው። ስለ ግል ድኅነት ማስተማርን ሕዝባዊ ኀላፊነትን ማምለጫ አድርገው ጠረጠሩት። ክርስቲያኖቹ ከመንግሥታዊ አስተዳደር የተጓደነ መዋቅር ነበራቸውና ይህም ግዛታዊ ቁጥጥሩን ለማረጋገጥ የማይመች ሆኖ ታያቸው46

ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች አሉ መባሉ እንዳለ ሆኖ በነዚህ ሥጋቶች ምክንያት ዲያቅልጢያኖስ ከተባባሪ ገዢዎቹ ጋር በመሆን ድንበሩን ካስከበረ፣ የገዢዎቹን ሥልጣን ካደላደለና የኢኮኖሚውን ችግር ካቃለለ በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ47 ጊዜ ክርስቲያኖቹን ወደ ሕዝባዊው ሃይማኖቱ እንዲመለሱ በአምልኮውም በመካፈል ለዐፄው ታማኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ለማድረግ ወሰነ። እየተካረሩ የሚሄዱ ተከታታይ አዋጆችን በማውጣት ርምጃዎችን ወሰደ።

  • በአስተምህሮ ላይ የነበራቸውን ክርክር መዳኛ እንዳያገኙ፣ መጽናኛም እንዳይኖራቸውና እንዲሰነጣጠቁ ይመስላል ቅዱሳት መጽሐፍትን አቃጠለባቸው፤
  • እንዳይሰበሰቡበት የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎችን አቃጠለ፤ አፈራረሰ፤
  • ኢኮኖሚያቸውን ለማድቀቅ ሀብት ንብረታቸውን ወረሰ፤
  • ዜግነታቸውን ካደ፤
  • ቤተ ክርስቲያንን ያለ መሪ ለማስቀረትና መዋቅሯን ለማፈራረስ ሠራ፤
  • ከዚያ ቀደም ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መከራ እምነታቸውን ያላስታረቁትን አሰቃያቸው፤ በረኻብ፣ በመሞትና ከጣዖት ጋር ንክኪ ያለውን ምግብ በመብላት መካከል እንዲመርጡ አደረጋቸው።

ብዙዎቹ ክርስቲያኖች በመከራው መጽናት ቢያቅታቸውም በርካቶች እምነታቸውን ሳያስታርቁ ጸንተው መሰከሩ። መከራን እንደ እግዚአብሔር ስጦታ ቆጠሩት፤ እንደ በጎ ወታደር ሆነው ተጋደሉ፤ እስከ ሞት ድረስ ታመኑበት፤ ሰማዕት ሆኑ፤ክርስቶስን በመከራው መሰሉበት። ኧረ እንዳውም፣ ክርስቶስ ራሱ በጸጋው በመከራቸው ተካፈለ ማለት ይሻላል48። ሁኔታውንም ኢየሱስ ክርስቶስን በገዢዎች ዘንድ ለመመስከሪያ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቀሙበት። በመከራ መጽናታችውን እምነታቸውን ማሳያ ብቻ ሳይሆን ሴት፣ ወንድ ጨዋ፣ ባርያ፣ አይሁድ ግሪክ ልጅ ሽማግሌ ሳይባል ሁሉም እኩል የሚካፈልበት ቀዳሚ የማንነታቸው መገለጫ አደረጉት። አዎ፤ በመከራ መጽናታቸው ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁበት መለያ ሆነ49

“የእሬቻ ደሴት?”

በመግቢያው እንደተጠቀሰው ይህ ሐተታ የተጻፈው በኢትዮጵያ መከበሩ እየተለመደ ስለመጣው ስለ “እሬቻ” ጉዳይ አስረጂ እንዲሆን ነው። “እሬቻ” በክርስቲያኖች ዘንድ እንደ ሮማውያን ባሕላዊው (ሕዝባዊ) አምልኮ ሆኖ የሚታይ ነው። የባዕድ አምልኮ ነው። አዎ፤ አረማዊነት ነው። ይህ ባሕላዊ ሃይማኖት እንዲስፋፋ በርትተው የሚሠሩ ወገኖች መኖራቸውን ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፤ በአማካሪነት እየሠሩ ያሉ ልኂቃን እንዳሏቸውም መገመት ስሕተት አይሆንም። የፖለቲካ ድጋፍ እንዳላቸውም በአደባባይ የሚታይ ነው። የቀለም ትምህርት ከተማሩት የሚደግፉት ጥቂቶች እንዳልሆኑ ይነገራል። የእነዚህ የእሬቻ አፍቃሪዎች ነገረ ሥራቸው፣ ኢትዮጵያን የእሬቻ ማለትም፣ “የአረማዊ ደሴት” ለማድረግ እየሠሩ ያሉ ያስመስልባቸዋል። ገፊ ምክንያታቸው ምናልባት ዲያቅልጢያኖስ ለሮማውያን ባሕላዊ ሃይማኖት የነበረውን ዐይነት ወይም ተቀራራቢ ዐላማና አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል።

መስፋፋቱ በበዓሉ ላይ በሚገኘው የሰው ቁጥር የሚለካ ከሆነ እጅግ ተስፋፍቷል ማለት ያስደፍራል። ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ የውጭ አገር ሚሲዮናውያንና የአገር ውስጥ ወንጌል አገልጋዮች ለብዙ ዘመናት በጸለዩበት፣ በደከሙበትና መከራ በተቀበሉበት ምድር ላይ ገና ወንጌል ያልደረሳቸው ወይም ከእምነታቸው ወደ ኋላ የተመለሱ ብዙ አሉ ማለት ነው። ይህ የአሁኑንና መጪውን የክርስቲያን ትውልድ ኀላፊነት የሚያገዝፈውና እጅግም የሚያከብደው ይሆናል ማለት ነው።

የቅርቡ የኢትዮጵያ ክርስቲያን ትውልድ ገጥሞት የነበረውን ሌላ ዐይነት ተግዳሮት ተቋቁሞ እንዳለፈው ይታወሳል። ኢትዮጵያን የ“ሶሺያሊዝም ደሴት” በማድረጉ ሥራ የነበረውን ተግዳሮት ተጋፍጦ አሁን በማለፍ ላይ ይገኛል። ለመጋፈጡ ምክንያቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አልነበረም፤ በጊዜው ሲራመድ የነበረው ሶሺያሊዝም እውነተኛ አምላክን የሚያስክድ በመሆኑ ሃይማኖታዊ እንጂ።

  • በአእምሮ አጠባው ምክንያት ላለመሳት፣
  • “አብዮቱ ከሁሉም በላይ” የሚለውን መፈክር ላለማለት፣
  • መንግሥትንም ሆነ ሌሎችን “እግዚአብሔር የለም” በሚለው አቋማቸው የደገፈ መስሎ ላለመታየት፣
  • “አሳምነኝ ወይ ላሳምንህ” በሚለው ጭቅጭቅ ላለመጠምዘዝ ተጠንቅቋል።

እግዚአብሔርን የሚክደውን ትምህርት በስብከት፣ በመዝሙር፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በጸሎት እንዲሁም በክርክር መክቷል፤ በመከራውም ጸንቷል።

የአሁኑና የሚቀጥሉት ክርስቲያን ትውልዶች ደግሞ የሚጠብቃቸው ተግዳሮት ኢትዮጵያን “የአረማዊ ደሴት” ለማድረግ በሚመስለው ሂደት ያለው ይሆናል። መጋደላቸውም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ምክንያት አይሆንም። አረማዊ አምልኮቱ ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምላክ ዞር እንዳይሉ እንዳይከለክላቸው ወይም የዞሩትን ወደ ኋላ እንዳይመልሳቸው ስለ ነፍሳት መጨነቅ እንጂ። ይህን ተግዳሮት ስለ መጋፈጥ “እሬቻና መዘዙ” በሚል ርእስ ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ባቀረቡት የዩ-ትዩብ መልእክት50 አርአያነትን አሳይተዋል።

የእርሳቸው ትጋት እሬቻ ባንሠራራበት ማኅበረ ሰብ ወንጌልን ስለ ማድረስ ፈር ቀዳጅ ሆኖ የሚታይ ነው። የወንጌል ሥራው ብዙዎችን የማረከ ጊዜ ወይም ሊማርክ ነው ተብሎ በታመነ ጊዜ የሮማ አረማውያን ዐፄዎች እንዳደረጉት እሬቻ አፍቃሪዎችም ክርስቲያኖችን ለመሞገት መነሣታቸው አይቀርም። ካለፈው የአረማውያን ታሪኮችና ውድቀቶች በመማር የጠነከረና በዘዴ የተሞላ ተግዳሮት ይዘው እንደሚከሰቱም ይጠበቃል። ክርስትናን መልሰው በመሞገቱ ከወንድሞችና ከእኅቶች መካከል ወደ ኋላ ያፈገፈጉት ዋናዎቹ ሆነው ሊገኙም ይችላሉ። ለሙግት ይበጃቸው ዘንድ በእሬቻው ላይ አንዳንድ የማስማማት ሥራም ይሠሩ ይሆናል፤ መከራም አያደርሱም ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም። በሌላ በኩል ክርስቲያኖቹም ተመጣጣኝ መመከቻ ዘዴ ያሰናዳሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል። ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች የማይደባለቅ ሆኖ ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ማፍለሱን እንዲቀጥል ይተጋሉ። ዐቀብተ እምነት አገልጋዮች ተግተው ይሠራሉ። እሬቻ አፍቃሪዎቹ መከራ የሚያስነሡ ቢሆን ሁሉም ክርስቲያኖች ይደርስባቸዋል ወይም ተቋቁመው ያልፋሉ ባይባልም ብዙዎች ግን በእግዚአብሔር ቸርነትና ጸጋ ይቋቋሙታል።

በማለፍ ላይ ያለው ትውልድ ኢትዮጵያን የ“ሶሻሊዝም ደሴት” በማድረግ ትግል ሳቢያ የደረሰበትን ተግዳሮት በመቋቋም በዓለም ዙሪያ ካሉ ክርስቲያኖች የሞራል ድጋፍ አግኝቷል። የእሬቻ አፍቃሪዎች ኢትዮጵያን የአረማዊ ደሴት ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ክርስቲያኖች የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ሲቋቋሙም ያንኑ ድጋፍ የሚያደርጉ እንደሚኖሩ ተስፋ ይደረጋል። በዚህ አጋጣሚ ለቀደመው ትውልድ ድጋፍ አሳይተው ለነበሩ ሁሉ ምሥጋና ይድረሳቸው።

ያም ሆነ ይህ ሁለንተናዊ ታላቅነት ላይ ደርሰዋል የተባሉ መንግሥታትን ግፊት የቀደሙትን ክርስቲያኖች እንዲቋቁሙ ያስቻለው እግዚአብሔር የነገዎቹንም ያስችላቸዋል። አረማውያኑ የመጥፋት ጫፍ ላይ ካደረሷቸው በኋላ ጣልቃ እየገባ ክርስቲያኖቹን ያበዛቸው እግዚአብሔር ወደ ፊትም እንደዚሁ ያደርጋል።

  • እምነታቸውን ከአረማዊ እምነት ጋር የማያቀላቅሉና በመልካም የሕይወት ምሥክርነት የሚያሳዩ፤
  • የማዳን ወንጌሉን በሚቃወሟቸው መካከል (በቤትና በውጭ) በድፍረት የሚያስታውቁ፤
  • እሬቻ ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚወስድ መንገድ አለመሆኑን በፍቅር የሚያስረዱና ስለ እሬቻ አፍቃሪዎቹ መዳን የሚጸልዩ፤
  • ከዚህ ዐይነት አምልኮ ጋር የሚተባበሩትን ክርስቲያኖች በቅንነት የሚወቅሱ፤
  • መከራ በደረሰባቸው ጊዜ ምስክርነታቸውን የማያጠፉ፤
  • እንዳውም መከራውን ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ለመናገር እንደ መልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙበት፤
  • በክርስቶስ ያገኙትንና ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ኅብረት የማያጠፉ፤
  • ብድራታቸውን ትኩር አድርገው በማየት የሚጽናኑና የሚጸኑ ክርስቲያኖችን እግዚአብሔር ያብዛ።

እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! አሜን!

  1. Frend, “Prelude”, 4 ( in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  2. Grigori Ferri The Last Dance of the Salins: The Pagan Elite of Rome and Christian Emperors in the Fouth Century AD , 132
  3. Hrvoje Gračanin, Religious Policy and Policizing Religion during the Tetrarchy, 145
  4. Frend W. H. C. ,MARTYRDOM AND POLITICALOPPRESSION (in Philip F. Esler The Early Christian World Vol I-II)P831 & Williams, 161-162(in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  5. Williams, 162 in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution
  6. Riccioc, Giuseppe. The Age of Martyrs: Christianity from Diocletian to Constantine: Prologue No.31 http://strobertbellarmine.net/books/Riccioc%20–%20Martyrs.pdf Arthur James Mason MA. The Persecution of Diocletian: A Historical essay , 38-40
  7. Arthur James Mason MA. The Persecution of Diocletian: A Historical essay , 40
  8. Arthur James Mason MA. The Persecution of Diocletian: A Historical essay ,49 & The Early Christain World Vol 1-2, 831
  9. Williams 161-162 (in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  10. Gaddis, Michael. There is No Crime for Those Who Have Christ: Religious Violence in the Christian Roman Empire. & Hrvoje Gračanin, Religious Policy and Policizing Religion during the Tetrarchy, 144
  11. Peti?, Joshua, “The Extension Of Imperial Authority Under Diocletian And The Tetrarchy, 285-305ce” (2012). Electronic Theses and Dissertations, 2004-2019. 2412. , 40 https://stars.library.ucf.edu/cgi/viewcontent.cgi? article=3411&context=etd
  12. Frend WHC. Martyrdom and Persecution in the Early Church , 6. extension of power, 41
  13. Gordon Robertson, How Christianity Survivedin Pagan Rome https://www.cbn.com/special/davincicode/grobertson_christianity_paganrome.aspx and G. E. M. de Ste. Croix WHY WERE THE EARLY CHRISTIANS PERSECUTED, 30
  14. Frend prelude P 3 (in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  15. Fritz Heichelheim, A History of the Roman People . 2nd Ed. Upper Saddle River: Prentice Hall, 2003. ,41
  16. Frend WHC. Martyrdom and Persecution in the Early Church ,9
  17. Peti?, Joshua, “The Extension Of Imperial Authority Under Diocletian And The Tetrarchy, 285-305ce” (2012). Electronic Theses and Dissertations, 2004-2019. 2412. , 41 https://stars.library.ucf.edu/etd/2412
  18. Hrvoje Gračanin, Religious Policy and Policizing Religion during the Tetrarchy ,145
  19. Mark Humphries Christianity and Paganism in the Roman Empire, 250-450 C.E. Chap3, 1
  20. Frend W.H.C The Early Church , 13
  21. https://www.newadvent.org/fathers/250102.htm Eusebius’ Church History 2.2.1-3
  22. Frend W.H. C “The Early Church”, 13
  23. Hrvoje Gračanin, Religious Policy and Policizing Religion during the Tetrarchy , 146
  24. G. E. M. de Ste. Croix WHY WERE THE EARLY CHRISTIANS PERSECUTED , 29
  25. Frend W.H.C ,Martyrdom and Poletical Oppression ( in Philip F. Esler The Early Christian World Vol 1-2 , 831) J.W.C Wand p 124 Simon Corcoran Diocletian P 248
  26. scho?, Making of Religion, 1, (in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  27. Frend W.H.C ,Martyrdom and Poletical Oppression ( in Philip F. Esler The Early Christian World Vol 1-2, 824)
  28. Marija BUZOV THE TOPOGRAPHY OF EARLY CHRISTIAN SISCIA Classica et Christiana, 4/2, 2009,48
  29. G. E. M. de Ste. Croix WHY WERE THE EARLY CHRISTIANS PERSECUTED , 25
  30. BART D. EHRMAN https://www.history.com/news/inside-the-conversion-tactics-of-the-early-christian-church
  31. Marija BUZOV,THE TOPOGRAPHY OF EARLY CHRISTIAN SISCIA Classica et Christiana, 4/2, 2009, 47
  32. Riccioc, Giuseppe. The Age of Martyrs: Christianity from Diocletian to Constantine, No.25
  33. Frend “prelude”,2(in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  34. Frend, “Prelude”, 2(in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  35. “የቲያናው አፖሎኒየስ” ክርስቶስ በምድር በተመላለሰበት ዘመን የነበረ ግሪካዊ ነው። የቲያናው አፖሎኒያስ ፈላስፋ፣ መናኝና አስተማሪ የነበረ ሲሆን፣ ተከራካሪዎቹ ኢየሱስ ካሳያቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ታምራቶችን አሳይቷል ይላሉ።
  36. Arthur James Mason MA. The Persecution of Diocletian: A Historical essay, 58-60
  37. Frend, “Prelude”, 12 (in https://en.wikipedia.org/wiki/Diocletianic_Persecution)
  38. Riccioc, Giuseppe. The Age of Martyrs: Christianity from Diocletian to Constantine Prolouge No. 29
  39. Riccioc, Giuseppe. The Age of Martyrs: Christianity from Diocletian to Constantine Prolouge No. 27
  40. WHY WERE THE EARLY CHRISTIANS PERSECUTED G. E. M. de Ste. Croix P26
  41. Grigori Ferri The Last Dance of the Salins: The Pagan Elite of Rome and Christian Emperors in the Fouth Century AD , 135
  42. G. E. M. de Ste. Croix WHY WERE THE EARLY CHRISTIANS PERSECUTED, 24
  43. Christopher P. Jones, Between Pagan and Christian , 9
  44. G. E. M. de Ste. Croix WHY WERE THE EARLY CHRISTIANS , 27
  45. Gaddis, Michael. There is No Crime for Those Who Have Christ: Religious Violence in the Christian Roman Empire. University of California press: Berkeley, 2005 P 34
  46. Christianity Did Christians Destroy Classical Culture and Create the Dark Ages? © Dr M D Magee P5
  47. Hrvoje Gračanin, Religious Policy and Policizing Religion during the Tetrarchy P146
  48. Jannel N. Abogado, O.P. Persecution and Martyrdom in The Early Church History, Motives and Theology
  49. Stacey Stiles, FAITH AND IDENTITY OF MARTYRS IN THE EARLY CHURCH ,1-2
  50. htps://www.youtube.com/watchttv=FGhinxYuw-k&ab_channel=EECAtlantaTV

Share this article:

መሪነትም እንደ ውበት

ለመሆኑ፣ የየቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች አንድን የአመራር ዘይቤ በሚመሯት ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንዲውል ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳሰቡት የአመራር ዘይቤውን ውጤታማነት ማየት ቢቸግራቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ተጨማሪ ያንብቡ

ዓለም በ2007 እንዴት አለፈች?

የተለያዩ ክስተቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማያያዝ፣ “በዚህ ጊዜ ጌታ ሊመጣ ነው፤ የዓለም መጨረሻ ሊሆን ነው” የሚሉ ግምቶች ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለመኖራቸው ታሪክ እማኝ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት:- የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ

አማረ ታቦር Seeing and Savoring Jesus Christ ከተሰኘው የጆን ፓይፐር መጽሐፍ በተከታታይ ከሚያቀርባቸው ጽሑፎች መካከል፣ ይህ “የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት፦ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ” ሲል ወደ አማርኛ የመለሰው ይገኝበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.