
የመተማመን ድልድዩን እንጠግን
ይቅርታ መጠየቅ ምን ማለት ነው? ሰዎች ይቅርታ ለመጠየቅ ለምን ይቸገራሉ? የተሠራው በደል በተበዳዩ ላይ ካሳድረው ጉዳት አንጻር፣ የበዳዩ ይቅርታ ጥየቃ የሚያጎናጸፈው ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ ምንድን ነው?
[the_ad_group id=”107″]
ፎርት ዎርዝ፣ ቴክሳስ 2020 እ.አ.አ.
ሰዎች ሁሉ ነገሮችን የሚመለከቱበት የራሳቸው ንጽረተ ዓለም አላቸው። ንጽረተ ዓለም ማለት ሰዎች ያካበባቸውን ዓለም የሚረዱበትና የሚተረጒሙበት አንጻር ማለት ነው። በአብዛኛው ማለት ይቻላል የሰዎች ንጽረተ ዓለም የተገራው በሃይማኖት ነው – አማንያን ከሆንን፤ ወይም በፍልስፍና ነው – ኢአማንያን ከሆንን፤ ወይም በባህል ነው – አረማውያን ከሆንን። እናም ንጽረተ ዓለም የሌለው ሰው አለ ለማለት ያስቸግራል። መከራ፣ ጭንቀትና ሥቃይ ሲነግሥ ምክንያቱን ለመረዳት የምንሞክረው ከሃይማኖት አንጻር ነው። ነገሩን ወስደን የምናዛምደው ከፈጣሪ ወይም ከአምላክ ጋር ነው። በዚህ ጽሑፍ “ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ መቅሠፍት ወይስ መገሥጽ?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሙከራ አደርጋለሁ። ቀጥሎም እንደ ክርስቲያን ወረርሽኙን እንዴት እንመልከተው? የሚለውን ከመጀመሪያው ጥያቄ ጋር አዛምደን እንመለከታለን።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በመላው ዓለም በተከሰተው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ያልተጨነቀ፣ ያልተጠበበና ምናልባትም ያልተመረረ ሰው ያለ አይመስለኝም።2 ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ሃይማኖታዊ ተቋማትም ለወረርሽኙ የየራሳቸውን ትንተና በመስጠት ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶች ወረርሽኙ የተከሰተው በሰው ስንፍናና ስሕተት ነው ይላሉ። ሌሎች ወረርሽኙ የሤራና የተንኰል (conspiracy theory) ውጤት ነው ይላሉ። ሌሎች የኀያላን መንግሥታትን የኀይል አሰላለፍ ለመፐወዝ ነው ይላሉ። ወረርሽኙ መቅሠፍት ነው፤ የአምላክ ቊጣ ነው፤ የፈጣሪ ቅጣት ነው የሚሉም አሉ። ምንም ተባለ ምን አሁን መላው ዓለም በምጥ ላይ ነው፤ በጭንቀትና በሥቃይ ላይ ነው። ወረርሽኙ ማንንም አይምርም። በሀብት መተገንም ሆነ በሥልጣን መጠለል አይቻልም። ቦታና ስፍራ በመቀየር እንኳ ከችግሩ መትረፍ አይቻልም። ቫይረሱ ድንበር አያውቅም፤ ዘርና አገር አይመርጥም። በወረርሽኙ ያልተፈተነ አገር፣ ያልተፈተነ ሥርዐትና ያልተፈተነ ተቋም የለም። ሁሉም ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ደኀራይ ውጥንቅጥ ማለትም ትርምስምስና ፍርክስክስ በሥጋት ከመጠባበቅ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻሉም። የሁሉም አቅም ችግሩን መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል። በርካታ የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚያሳስቡት ለወረርሽኙ መፍትሔ ማግኘት ብንችል እንኳ (ለቫይረሱ ክትባት ቢገኝ እንኳ) ወረርሺኙ ከሚያስከትለው ቀውስ ለመውጣትና ቅድመ ኮቪድ ደረጃ ላይ ለመመለስ ቢያንስ ከ2-3 ዓመት ሊፈጅ ይችላል። አንዳንድ ምሁራን ግን ወደ4 ዓመት ሊወስድ ይችላል ይላሉ። ነገሩ እንዲህ ከሆነ የችግራችን ዑደት ገና አላለቀም ማለት ነው። እናም ቀውሱ ገና ይቀጥላል፤ ቀውሱ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ “domino effect” (chain reaction/ቅጥልጣይ መዘዝ) ሊኖረው እንደሚችል ምንም አጠያያቂ አይሆንም። ከዚህም የተነሣ መጪው ዘመን ብሩኅ አይመስልም። ጨለማው እየበረታ የሚመጣ ይመስላል። ታዲያ ሁኔታውን ምን ብለን እንውሰደው? ምን ትርጒም እንስጠው? አንዳንድ የሃይማኖት ተቋሞች ለምሳሌ አይሁዶች የመሲሑ መምጫ ቀርቧልና ተዘጋጁ እያሉ ናቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ የዓለም መጨረሻ ተዳርሷልና ንስሐ ግቡ እያሉ ናቸው።
ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ነገር አይደለም። ሪቻርድ ፓንክረስት ከ1435–1436 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደ ነበርና ምድሪቱን ባዶዋን ለማስቀረት ተዳርሶ እንደ ነበር ገልጸዋል። ዐፄ ሱስንዮስ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊ በ1606 ዓ.ም. በትግራይ አካባቢ ወረርሽኝ በመከሰቱ ብዙ ሰዎች ለስደት ተዳርገው እን ደ ነበርጠቅሰዋል። በዐፄ ፋሲለደስ ዘመነ መንግሥት (1632–1667) ደግሞ ሁለት ዐበይት ወረርሽኞች – ማለትም ፈንግልና ካባብ – ተከስተው ነበር።3 በተለይ በ1911 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው ወረርሽኝ ለብዙ ሰዎች አስደንጋጭ ነበር። ወረርሺኙ “የኅዳር በሽታ” የሚል ስም እን ደ ተሰጠው መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል።4 “ኅዳር ሲታጠን” ከዚህ ጋር ዝምድና አለው።5 ወረርሽኙ አዲስ አበባን ክፉኛ አጥቅቶ ነበር፤ በቀን እስከ 300 ሰው ይሞት ነበር። ራስ (በኋላ ንጉሥ) ተፈሪ መኮንን እንኳን ሳይቀሩ በወረርሽኙ መጠቃታቸው ሁኔታውን የከፋ አድርጎት ነበር።6 በወቅቱ የዐይን ምስክር ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አለቃ ክንፈ አዲሱ ሁኔታውን ሲገልጹ “በጦር ሜዳ የወደቀ ወንድሙን ተራምዶ እን ደሚሄድ ሰው ሁሉ ማንም በመንገድ ዳር የወደቁትን አንሥቶ የሚቀብር አልነበረም። ሁሉም ተራምዷቸው ይሄድ ነበር። በቤተ ክርስቲያን መቀበሪያ ቦታ አልነበረም፤ አንዳንዶች ይቀበሩ የነበረው በኋላ ቤተ ክርስቲያን ይታነጽባቸዋል በሚል በሜዳ ነበር፤ ስለ ፍታት ማንም ግድ የሚለው አልነበረም” ብለዋል። በአንድ መቃብር ብዙ ሰዎች ተነባብረው ይቀበሩ እን ደ ነበር ተወስቷል። ከበሽታው መክፋት የተነሣ አቡነ ማቴዎስ (በግብጽ ለኢትዮጵያ የተሾሙ አቡን፤ እን ደ ታትሪያርክ የሚቈጠሩ) አዲስ አበባን ጥለው ወደ መናገሻ ለመሸሽ ተገደው ነበር፤ አቡኑ ከሸሹ እኛስ ለምን አንሸሽም በሚል እነ ከንቲባ ወሰን ዘአማኑኤልም አቡኑ በከፈቱት መንገድ ሄደዋል። ራስ ተፈሪ በወረርሽኙ ሕይወታቸው አልፏል የሚለው ወሬም የተናፈሰው በዚሁ ጊዜ ነበር። ራስ ተፈሪ ሕዝቡን ለማረጋጋት ራሳቸውን መግለጥ ነበረባቸው። አለቃ ክንፈ የወረርሽኙን አስከፊነት ሲናገሩ “ልክ እንደ ሰደድ እሳት ነበር” ብለዋል።7
ቀደም ሲል ላነሣኋቸው ጥያቄዎች መልስ ከመስጠቴ በፊት ወረርሽኙን ከሳይንስና ከታሪክ አንጻር በመጠኑ ለመዳሰስ እን ሞክር። የሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት እንዲህ ዐይነቱ ወረርሽኝ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል። በሽታና ወረርሽኝ ድሮም አሉ፤ አሁንም ይኖራሉ። ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ እስካሉ ድረስ በሽታና ወረርሽኝ መኖራቸው አይቀሬ ነው። ባጭሩ መታመም፣ አልፎ ተርፎም መሞት ያለ ነገር ነው። እን ግዳ የሆነብን መላውን ዓለም የሚያስጨንቅ ወረርሽኝ መከሰቱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከቤተ ሙከራ የሚያመልጡ ቫይረሶች አሉ። ስንፍና እንዲሁም ስሕተትባለበት ስፍራ ሁሉ ለአደጋ መጋለጥ አለ። ሤራና ተንኰል ካለ ደግሞ ለጥፋት መዳረግ አለ። እናም በሽታ ይከሰታል፤ ወረርሽኝ ይከሰታል። ቁም ነገሩ የሰው ልጆች ለአደጋ ሳይጋለጡ ጥናትና ምርምር የምናደርገው እንዴት ነው? ክትባትና መድኃኒት የምናገኘው እንዴት ነው? የሚለው ነው። እንዲህ ዐይነቱ ችግር ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ብዙ ወረርሽኞች ተከስተዋል። ለእኛ ነው እንጂ አዲስ የሆነው በሽታና ወረርሽኝ ለዓለም አዲስ አይደሉም።
የሰው ልጆችን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከተ በእርግጥም ወረርሽኝ አዲስ ነገር አይደለም። በታሪክ መዝገብ ከተጻፉት መካከል ጥቂቶቹን ብንመለከት፣ ማኅበረሰብን ያስጨነቁ ወረርሽኞች ቊጥር ቀላል አይደለም። ስለ ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ተነግሮ የምናገኘው በግሪክ ጸሐፊዎች መዝገብ ውስጥ ነው። ወረርሽኝ ከ430 ዓ.ዓ. ጀምሮ ይታወቃል። በ541 ዓ.ም. ከተከሰተው ወረርሽኝ ብንጀምር እንኳ የማኅበረሰብን እንቅስቃሴ ቀጥ ለጥ ያደረጉ ወረርሽኞች ብዙ ናቸው።8 ከ1346-1353 በአውሮፓ የተከሰተውና “ጥቁሩ ሞት” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ ከ75-200 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ጨርሷል። በ1918 የተከሰተውና “ስፓኒሽ ፍሉ” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ ከ50-100 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ቀጥፏል። የፈንጣጣ በሽታ በ1980 ዓ.ም. ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረ ገጽ እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ የብዙ ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ረግፏል። ከ1800-1900 ድረስ ባሉት ዓመታት ብቻ ከ100 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በፈንጣጣ በሽታ ሞተዋል። በ1976 የተከሰተውና “HIV/AIDS” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ ከ36 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ገድሏል። እስከ አሁን ድረስ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቊጥር እጅግ ብዙ ነው፤ ቊጥራቸው ወደ 35 ሚሊዮን ይጠጋል።9 ወረርሽኝም ባይሆን “ታላቁ ረሀብ” በመባልና ከ30%-60% የሚሆኑ የአየር ላንድ ሰዎችን የጨረሰውን መቅሠፍት እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ ለ4 ዓመት የቆየው ረሀብ (ከ1845-1849) መንሥኤው ተክሎችን የሚበላ በሽታ ነው።
እንግዲህ ሳይንስም ሆነ ታሪክ የሚያረጋግጡልን በሽታና ወረርሽኝ አዲስ ነገሮች አለመሆናቸውን ነው። በክርስትና እንዲያውም “ውድቀትና ጥንተ አብሶ” (fall and original sin) የሚባል አስተምህሮ አለ። በዓለም ውስጥ የምናያቸው ችግሮች በሙሉ ሄደው ሄደው የሚዛመዱት ከውድቀትና ከጥንተ አብሶ ጋር ነው። በሽታና ሞት የኀጢአት ውጤቶች ናቸው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የጀመረውን ሥራ ከፍጻሜ እስከሚያደርስና ሁሉንም ነገር አዲስ እስከሚያደርግ ድረስ የውድቀት መዘዝ ይቀጥላል። በመሆኑም ሰዎች ይቸገራሉ፤ ሰዎች ይታመማሉ፤ ሰዎች ይሞታሉ። በውድቀትና በኀጢአት ቅጣት ምክንያት ሰዎች በልዩ ልዩ ፈተና ውስጥ ያልፋሉ። እርግጥ በሰዎች ሥሥት፣ ስንፍናና ተንኰል ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች አሉ። ከሰዎች ክፋት የሚመነጩ መዐቶች አሉ። እናም በሽታ አዲስ አይደለም፤ ሞትም አዲስ አይደለም። ሆኖም አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሲሆን ያስደነግጣል። ሁሉም ነገር እንኩትኩት ሲል ያስበረግጋል። አሁን ሰዎች ሁሉ በፍርሃት መዋጥና ለነገሮች ሃይማኖታዊ መልስ መፈለግ ይጀምራሉ። የበሽታና የወረርሽኝ መንሥኤያቸው ምንድን ነው? መፍትሔያቸው ምንድን ነው? ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት ምላሻቸው ምንድን ነው? ጥንቱንስ ቢሆን ይህ ለምን ሆነ? ለምን ተከሰተ? እነዚህ ጥያቄዎች ሰፊ ትንተና ይሻሉ። በዚህ አጭር ጊዜ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመልስ ሙከራ አላደርግም። ሆኖም እንዲህ ዐይነት እጅግ አስጨናቂ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ሰዓት ክርስቶሳውያን ነገሩን መመልከት ያለባቸው እንዴት ነው? ይህ አሁን የገጠመን ችግር “መቅሠፍት” ነው ወይስ “መገሥጽ”? የአምላክ ቊጣ ነው ወይስ የአምላክ ቊንጥጫ? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ አተኩራለሁ።
ብዙ ሳልሄድ አንድ ቆፍጠን ያለ መልስ ልስጥ። ኮቪድ19 መቅሠፍት ሳይሆን መገሥጽ ነው፤ ቊጣ ሳይሆን ቊንጥጫ ነው።10 ሰዎች ነንና እንደ ሰው ይህ አስከፊ ወረርሽኝ በዓለም ላይ የተከሰተው ለምንድን ነው? በማለት መጠየቃችን አይቀርም። የሳይንስ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡትን ትንተና ለመስማት እንጣደፋለን።ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሱ ይሆናል፤ ምናልባት እንደ እኔ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ – ሁሉንም ምክንያቶች ከእግዚአብሔር አንጻር ካየናቸው ማለቴ ነው። አንደኛው እግዚአብሔር የሰዎችን ልክ ማሳየት ፈልጓል። የባቢሎንን ግንብ ታሪክ ያስታውሷል። ሰዎች አለልክ ተንጠራርተዋል። በሕክምና ጥበባቸውና በዕውቀታቸው ተመክተዋል፤ በጦር ኀይላቸውና በብልጽግናቸው ተደግፈዋል። እግዚአብሔርን መናቅና እርሱን ገሸሽ ማድረግ ናኝቷል። እግዚአብሔር ማእከላዊውን ስፍራ መያዝ ሲገባው ወደ ዳር ተገፍቷል። የእግዚአብሔር ወሳኝነትና አስፈላጊነት ጥርጣሬ ላይ ወድቋል። ይህ ዓለም በራሱ እንደሚኖር ተደርጎ ተቆጥሯል። እናም ሰዎች በዚህ ዓለም ያሻቸውን ለማድረግ መብትና ሥልጣን ያላቸው እስኪመስል ድረስ እግዚአብሔር ባይተዋር እንዲሆን ተደርጓል (የታላላቅ መንግሥታት መሪዎችን ሁኔታ ልብ ይሏል)።
እንግዲህ እግዚአብሔር ልካችንን እያሳየን ነው። አቅማችንን እየነገረን ነው።ይህ ዓለም የማንም ሳይሆን የእርሱ የራሱ እንደ ሆነ እየመሰከረነው። እግዚአብሔር ህልውናውን እያረጋገጠ ነው። ሰዎች ቆም ብለው ዙሪያ ገባቸውን እንዲመለከቱ እያደረገ ነው። የዚህ ዓለም ሠሪና ፈጣሪ እንዳለ እያሳሰበነው። ባለቤቱም እርሱ ብቻ እንደ ሆነ እያመለከተ ነው። በታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ልዩ በሆነ መንገድ ሀልዎቱን የገለጠበት ጊዜ አለ። የዘፀአቱ ታሪክ ይህን ያስታውሰናል። ፈርዖንና ሠራዊቱ ያለ እኛ ማን አለ? በማለት ራሳቸውን ያጌተዩበትና ያመለኮቱበትጊዜ ነበር። እግዚአብሔር ጌታና አምላክ እርሱ ብቻ እንደ ሆነ አሳየ። በእግዚአብሔር ዓለም ሰዎች ራሳቸውን ሲያጌተዩና ሲያመለኩቱ ድርጊቱ ትልቅ እብሪት ይሆናል። የራስ ባልሆነ ነገር መመካትና መታበይ ትልቅ ውድቀት ነው። ይህ ፍጥረተ ዓለም የማንም ሳይሆን የልዑል እግዚአብሔር ነው።
በኮቪድ 19 እንዳየነው ዋስትና ይሰጡናል ብለን የታመንባቸው ነገሮች በሙሉ ተንኮታኩተዋል። የተመካንባቸውና የተደገፍንባቸው ግኝቶች በክፉ ቀን ከድተውናል። በዚህም ክው ያላለና ያልደነገጠ ሰው አለ ለማለት ያስቸግራል። እናም እግዚአብሔር ልካችንን ሊያሳየን ወደደ። እግዚአብሔር ይህ እንዲሆን የፈቀደው ወደ ልባችንና ወደ ልቡናችን ተመልሰን መታመኛችንን እን ድንመርጥ ነው፤ መደገፊያችንን እን ድናውቅ ነው። ያለ እግዚአብሔር የሆነ ወይም እግዚአብሔርን ባይተዋር ያደረገ ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ጉልበትና ችሎታ የትም አያደርሱም። እናም እግዚአብሔር በራሳችሁ አትመኩ፤ አትታበዩ እያለን ነው። ወረርሽኝን ማስቆምም ሆነ ሞትን ማስቀረት ከቶ አንችልም። ወረድ ብዬ በምጠቅሰው ደብዳቤ ላይ ማርቲን ሉተር እንዳመለከተው እግዚአብሔር ከሁለንተናችን ሲወጣ፣ ሰይጣን ወደ ሁለንተናችን ይገባል። ለእግዚአብሔር ስፍራ በነፈግን ቊጥር ለሰይጣን ስፍራ እንሰጣለን። እግዚአብሔርን ማራቅ ሰይጣንን ማቅረብ ነውና። እንግዲህ እግዚአብሔር ወደ ራሱ ሊያቀርበን ሲፈልግ ይገሥጸናል፤ ወደ ራሱ ሊያስጠጋን ሲሻ ይቆነጥጠናል። የመረጥነው ጎዳና ወደ ጥፋት የሚወስድ ሲሆን ቆም እንድንልና እርምጃችንን እንድናስተካክል ይነግረናል። እግዚአብሔር ብዙ ዐይነት መገሠጫዎችና መቆንጠጫዎች አሉት። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ እንደታየው እምቢተኞችንና አንገተ ደንዳኖችን የሚገሥጸው ባስደንጋጭ መንገድ ነው። ኮቪድ 19 አስደንጋጭ ነው፤ ቆም የሚያደርግና ቀና የሚደርግ ነው – ወደ ላይ ወደ ሰማይ።
ሁለተኛው እግዚአብሔር የሰዎችን ክፋት ሃይ ማለት ፈልጓል። ክፋት ከምንጊዜውም በላይ በዝቷል። ሥሥት ከምንጊዜውም በላይ ናኝቷል። ራስ ወዳድነትና ራስ ጠቀምነት ከምንጊዜውም በላይ ነግሧል። ጭቆና፣ ብዝበዛና መድልዎ ምድርን ቀውጧል። በሀብትና በሥልጣን መተገንና ምስኪኖችን መበደል የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። ምድርን ማጐሳቈልና ተፈጥሮ ሀብቷን ምጥጥ ምጥምጥ ማድረግ እን ደ ጀብዱ ተቈጥሯል። አንዳንዶች እን ዲያውም በሸራቸውና በሤራቸው ታብየዋል፤ ሤራና ሸር መከታና ምስኪኖችን መደፍጠጫ ሲሆን መመልከት እንግዳም ነገር አይደለም። በሰዎች ችግርና በሰዎች አበሳ ለመክበር የሚፈልጉ ሰዎች በዝተዋል። ለዚህ አባባል አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። የሰዎችን አገርና የእርሻ መሬት በጉልበት በጠራራ ፀሐይ በመንጠቅ ረገድ ቻይናን የሚስተካከላት አገር የለም። ዛሬ ቻይና በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ አገሮች የምትሠራው ግፍ ከዓመታት በፊት አውሮፓውያን ይሠሩት የነበረው ግፍ ነው። እንደ አውሮፓውያን ሁሉ ቻይናም አፍሪካን በመቀራመት ላይ ትገኛለች። ድሆች ናችሁና ልርዳችሁ ነው ምክንያቱ፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር “ውስጡን ለቄስ ነው”። ቻይና የአውሮፓውያንን መዳከም እንደ ትልቅ ዕድል በመጠቀም ያለ ከልካይ በአፍሪካ ላይ ዘምታለች – እርሷም በተራዋ አፍሪካን ለመቀራመት። ለቻይናውያን ምግባራዊ ፋይዳዎች ቦታ የላቸውም፤ ሐቅና እውነት ስፍራ የላቸውም። በገንዘብና በጥቅም የሚያባብሉትና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው የአገር መሪ እስካገኙ ድረስ ለፍትሕ ስፍራ የላቸውም። መሪዎችን በማሞሰን ረገድ ቻይናን የሚያህላትአገር የለም። የቻይና አካሄድ በጣም ሲበዛ ጭከና የተሞላበት ነው፤ በጣም ሲበዛ ጭቆና የተሞላበት ነው። የቻይና ፖለቲካዊ አካሄድ የሚፍገመገሙ አገሮችን አይቶ አይምርም። በዚያም በዚህም ብሎ፣ከሆነ ለቁርስ፣ ካልሆነ ለምሳ፣ ካልሆነም ለራት ያደርጋቸዋል። አፍሪካ እንደ ቻይና ያሉ ሰልቃጮች እስካሉ ድረስ መቼም መች ከችግሯ አትወጣም። በአሁኑ ጊዜ ለአፍሪካ ትልቋ አበዳሪና መሣሪያ ሻጭ ቻይና ናት። ይህ የቻይና ድርጊት “አዲሱ ቅርምቻ” (the new scramble for Africa) የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።11 ከግለሰቦች ተበድሮ ከብድሩ ነጻ የወጣና ራሱን የቻለ ግለሰብ ይኖር ይሆናል። ከመንግሥታት ተበድሮ ከብድሩ ነጻ የወጣና ራሱን የቻለ አገር ለመኖሩ ግን ያጠራጥራል። የበለጸጉ አገሮችም ሆነ የIMFእና የWorld Bank ትልቁ ሥራ ደሀ አገሮች ከድህነታቸው እንዳይወጡ ሌላ የድህነት ዑደት መፍጠር ነው። እነዚህ ተቋሞች ለድሀ አገሮች ገንዘብ የሚያበድሩት፣ ከድህነታቸው እንዲወጡ ሳይሆን በድህነታቸው ለመክበርና ለመበልጸግ ነው፤ ገንዘብ የሚያበድሯቸው አገራቸውን አልምተው ብድሩን እንዲከፍሉ ሳይሆን መክፈል ከማይችሉት የብድር ዕዳ ውስጥ እን ዲዘፈቁና ሌላ የብድር ዑደት ውስጥ እን ዲነከሩ ለማድረግ ነው።12 ይህ በእውነተኛው በእግ ዚአብሔር ዘንድ እጅግ ጥዩፍ ተግባር ነው። ድሆችን ይበልጥ ማደኽየት እግዚአብሔርን በእጅጉ ያሳዝናል።
ከዚሁ ጋር የሚዛመድ አንድ ሌላ ምሳሌ ልጨምር። የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚያሳስቡት የOil Crisis ዘመን አክትሞ የFood Crisis ዘመን ከጀመረ ሰንብቷል።13 በ20ኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ጥያቄ የነዳጅ ዘይት ነው፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ትልቁ ጥያቄ የሚበላ ምግብ ነው። እንደ ቻይና፣ ሕንድና ሳዑዲ አረቢያ የመሳሰሉ አገሮች አሁን ጥልቁ ችግራቸው የነዳጅ ዘይት ሳይሆን የሚበላ ምግብ ነው። በተለይ ቻይናና ሕንድ የሕዝብ ቊጥራቸውና የምግብ አቅርቦታቸው ከቶ አልተመጣጠነም፤የቻይና ሕዝብ ቍጥር ወደ 1.4 ቢሊዮን ደርሷል፤ የሕንድ ደግሞ ወደ 1.3 ቢሊዮን ደርሷል። የሁለቱ በድምሩ 2.7 ቢሊዮን መሆኑ ነው። ይህም 7.5 ቢሊዮን ከሚሆነው ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ቊጥር 37% በመቶ የሚሆነውን ይይዛሉ፤ 1/3ኛውን ማለት ነው። እናም ሁኔታው ዜጎቻቸውን ለመመገብ ከሚችሉበት አቅም በላይ በመሆኑ ያላቸው አማራጭ ማረሻ ያልነካው መሬት (በትራክተር ያልታረሰ መሬት) እየፈለጉ ከቻሉ መግዛት ካልቻሉ በፖለቲካ ተጸዕኖ መንጠቅ ነው። ቻይናና ሕንድ የሚታረስ መሬታቸውን ከጨረሱ ሰንብተዋል፤ አሁን እያረሱ እህል የሚዘሩበት ምድር እን ኳ ብዙ ዘመን ከመታረሱና በማዳበሪያ ከመኮላሸቱ የተነሣ እንደ ድሮው ብዙ ምርት ሊሰጣቸው አልቻለም። ባጭሩ ዜጎቻቸውን መመገብ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በመሆኑም አሁን ያላቸው አማራጭ ፊታቸውን ወደ ምስኪን ድሀ አገሮች ማዞር ነው – ለመበዝበዝና ለመቦጥቦጥ። ቻይና፣ ሕንድና ሳዑዱ አረቢያ ባለ በሌለ ኀይላቸው ወደ አፍሪካና ወደ ላቲን አሜሪካ ዘምተዋል። ከእነዚህ በቻይና፣ በሕንድና በሳዑዲ አረቢያ ለመበላት ተራቸውን ከሚጠብቁት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፤ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያና ማዳካስካር ሌሎቹ ናቸው። እነዚህ ሦስት አገሮች ማለትም ቻይና፣ ሕንድና ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የእርሻ መሬቶችን ገዝተዋል።ከገዟቸው መሬቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ጨርሶ የሰው እግር ያልረገጣቸውና ማረሻ ያልነካቸው ድንግል መሬቶች ናቸው። በእነዚህ መሬቶች ላይ የሚዘራው ደግሞ ሩዝ ነው፤ እርሻውን ለማካሄድ ትራክተሮችና ገበሬዎች የሚመጡት ከቻይና ነው። መሬቱና ውሃው ነው እንጂ የኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ከቻይና ነው የሚመጣው። ብዙ የኢትዮጵያ ምስኪን ልጆች መሬታቸውን አጥተው ሲቸገሩ፣ የቻይና ዜጎች በኢትዮጵያውያን ሡዐት ይመገባሉ። ማለት እኛ እየተራብን ሌሎች ይጠግባሉ።መሬትን በፖለቲካዊ ኀይል መንጠቅ ይሏል ይህ ነው። አንዳንድ ምሁራን ሁኔታውን “መሬት ዝርፊያ” (Land Grab) የሚል ስም ሰጥተውታል። ሥልጣንን፣ ኀይልንና ሀብትን መከታ አድርጎ ምስኪኖችን መበደል እግ ዚአብሔርን በጣም ያሳዝናል። እግ ዚአብሔር ታጋሽ በመሆኑ ወዲያው እርምጃ ስለማይወስድ ምስኪኖችን መበደል በእግዚአብሔር ዘንድ የማይቈጠር ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የአቤል ደም ወደ እግዚአብሔር እንደጮኸ ሁሉ የምስኪኖችም እምባ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል። እግዚአብሔር ድሆችን አታስጨንቋቸው፤ ፍርዳቸውንም አታጣሙባቸው በማለት አስጠንቅቋል (ዘጸ 22፥22፤ 23፥6)። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች መበደል ይቅርና ፍጥረትን መበደል እንኳ እግዚአብሔርን ያስቈጣል (ዘጸ 23፥11)። በእግዚአብሔር ዓለም ምስኪኖችና ፍጥረት ተመልካች አላቸው። ግዑዟ ምድር እንኳ ዕረፍት እንዲሰጣት ታዟል።
ሦስተኛው የመጽሐፍ ቅዱሱን አምላክ የሚያመልኩትን ብቻ ይመለከታል፤ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሔር እንዴት መጮህና ከአምላካቸው ጋር እንዴት መታገል/መፋለም እንዳለባቸው ለማሳሰብና ለማስተማር ወድዷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር መታገል ምን እንደሚመስል በሚገባ ካሳዩን ሰዎች አንዱ ያዕቆብ ነው። ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ታገለ፤ በትግሉም በእግዚአብሔር ሀልዎት ተጐበኘ። ዳዊትም በመዝሙሩ ወደ እግዚአብሔር መጮህና ከእርሱ ጋር መታገል ምን እንደሚመስል አሳይቶናል። ከእነዚህ ሁለት ሰዎች እንደምንረዳው ከልባቸው ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉና ወደ እርሱም የሚጮሁ ምስኪኖች፣ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳ በተወሰነ ደረጃ የእግዚአብሔርን ማንነት ለመረዳት ዕድል ያገኛሉ። ለምን ብለን ስንጮህና ከእግዚአብሔር ጋር ስንከራከር ጭላንጭል ማየት እንጀምራለን። በተለይ የዳዊት መዝሙሮች ጸሎቶችና ሙግቶች ናቸው ማለት ይቻላል። አንድ ሰው ራሱን በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ማቅረብና ነፍሱን በአምላኩ ዐውደ ምሕረት እንዴት ማፍሰስ እንዳለበት ያስተምራሉ። እግዚአብሔር ከልባቸው ሙጥኝ የሚሉትን ሰዎችን አይገፋም። ይልቁንም ያሉበትን ሁኔታ ከእርሱ አንጻር እን ዲመለከቱ ዕድል ይሰጣቸዋል። እግ ዚአብሔር “ኑና እን ዋቀስ” በማለት ሕዝቡን ጋብዟል (ኢሳ 1፥18)። ይህን ሐሳብ በቅጡ ለመመልከት በመጽሐፈ መዝሙር ላይ ብቻ እናተኩራለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ለመነበብ ዕድል የሚገጥመው መጽሐፍ መዝሙረ ዳዊት ነው ቢባል ትክክል ነው – በተለይ በመከራና በጭንቀት ጊዜ።14 ቅዱሳን ከስብራታቸው ለመጠገን ብዙ ጊዜ የሚሄዱት ወደ መጽሐፈ መዝሙር ነው። በእርግጥም ወደዚህ መጽሐፍ የሚመጡ ሰዎች ይጽናናሉ፤ ይጠገናሉ፤ ነገራቸውንም ከተለየ አንጻር ለመመልከት ዕድል ያገኛሉ። ለምሳሌ መዝ 23 መጥቀስ ይቻላል። ይህን መዝሙር ቢያንስ በሕይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ያላነበበው ሰው አይኖርም። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የቅዱሳን ሐዘን፣ ደስታ፣ ጭንቀት፣ ምሬት፣ ድካም፣ ግራ መጋባትና ተስፋ ለመቊረጥ መዳዳት ምንም ሳይድበሰብስ ተገልጿል። መዝሙረኛው ምዕራፉን የጨረሰው አሳማኝ መልስ እስከሚገኝ ድረስ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ሁልጊዜ የሚብሰለሰለውን ጥያቄ በማንሣት ነው፤ “በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን” (89፥47)? ይህ ጥያቄ ሁልጊዜ በሰዎች ልብ ውስጥ ይብሰለሰላል። በማንኛውም ጊዜና ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች ይህን ጥያቄ በአንድም ሆነ በሌላ ወቅት ይጠይቃሉ። መዝሙረኛው ይህን ጥያቄ ያነሣው በምዕራፍ 89 ላይ ቢሆንም በምዕራፍ 88 ላይ ምርር ብሎ ሲጮህ እናያለን። ወዲያው ደግሞ በምዕራፍ 89 ላይ የእግዚአብሔርን ጽድቅና ታላቅነት አንሥቶ ውዳሴ ሲያቀርብ እናነባለን። መዝሙረኛው በእግዚአብሔር ተስፋ አልቈረጠም፤ ለምን? እንዴት? በመዝሙር 88 እና 89 መካከል ያለውን ንጽጽር ቀረብ ብለን ብንመለከት ሁለቱ መዝሙሮች በአገር በዘመድ የሚገናኙ አይመስልም። መዝሙር 88 የዘመረ ሰው እን ዴት መዝሙር 89 ሊዘምር ይችላል? እግዚአብሔርን እየሞገቱ መወደስ ይቻላል? ከእግዚአብሔር ጋር እየተከራከሩ መዘመር ይቻላል? በዳዊት ሕይወት የምናየው ሁለቱንም ነው። ዳዊት እየሞገተ ይወድሳል፤ እየተከራከረ ይዘምራል።
ነፍሴ መከራን ጠግባለችና ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ ለዘላለም እንደማታስባቸው እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ። | እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል? በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፤ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው አቤቱ የሠራዊት አምላክ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ አንተ ብርቱ ነህ፤ እውነትህም ይከብብሃል። |
ዓይኖቼ በመከራ ፈዘዙ አቤቱ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ በውኑ ለሙታን ተኣምራት ታደርጋለህን? የሞቱስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? | እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው አቤቱ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ የኃይላቸው ትምክህት አንተ ነህና። |
እነዚህ ሁለት መዝሙሮች አንድ ነገር አበክረው ያሳስቡናል። ይኸውም እምነትና ተስፋ ሁልጊዜ እንደ ተፋጠጡ ናቸው፤ ማለት የእምነት ጉዞ ሁልጊዜ ከመፈተን አያርፍም። ቅዱሳን በሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸው አይቀርም (ዳዊት “በሞት ጥላ መካከል” እን ደሚለው፤ 23፥4)። የእግ ዚአብሔር ሕዝብ መሆንም ሆነ በእግዚአብሔር መታመን ከመናወጥ ነጻ አያደርግም፤ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሊናወጡና ግራ ሊጋቡ ይችላሉ። በመጽሐፈ መዝሙር ውስጥ የአማኙ ኅብረተሰብ ሕይወት ከመናወጥና ግራ ከመጋባት ወይም ከፈተና፣ ከመከራና ከሐዘን ነጻ ሆኖ አልቀረበም። እነዚህ ነገሮች እንዲያውም የአማኙን ኅብረተሰብ እምነት መድከም ወይም እንከንነት ሳይሆን የእምነት ጉዞው አንድ አካል መሆናቸውን ያሳያሉ።15 እርግጥ አማኙ ኅብረተሰብ አምላኩን በትዕግሥት መጠበቅ አለበት፤ የእምነቱም ጥንካሬ የሚለካው በጽናት አምላኩን መጠበቅ በመቻሉ ነው። ይሁንና አምላካቸው “መሸሸጊያቸው” (91፥2) በመሆኑ በተናወጡና ግራ በተጋቡ ጊዜ እጃቸውን ይዞ ያሻግራቸዋል (91፥3-16)። ስለዚህ አማኙ ኅብረተሰብ መታወክ የለበትም፤ መሸበር የለበትም፤ መደንገጥ የለበትም። ምክንያቱም እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው (102፥18-19፤ 103፥19፤ 100-106)።እግዚአብሔር ልዑል ጌታ ነው (መዝ 90-91)። እርሱን መጠጊያቸው ያደረጉ ከቶ አያፍሩም። ራሳቸውን በእግዚአብሔር ላይ የሚጥሉ በእግዚአብሔር ይደገፋሉ።
እንደሚታወቀው መጽሐፈ መዝሙር ከቅኔ መጻሕፍት አንዱ ነው። የቅኔ መጻሕፍቱ የሚያጎለብቱበት የየራሳቸው ልዩ ጭብጥ አላቸው። ለምሳሌ መጽሐፈ ኢዮብ “በእግዚአብሔር ዓለም ሥቃይ የነገሠው ለምንድን ነው? በመከራና በሥቃይ ውስጥ የእግዚአብሔር ሚናው ምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ሲመልስ መጽሐፈ መክብብ ደግሞ “የሕይወት ግብ ምንድን ነው? የሕይወት ትርጒም ምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። ኢዮብ በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት (ከሃሌ ኲሉነት) ግራ ተጋብቷል። የመክብብ ጸሐፊ በሕይወት ትርጒም ግራ ተጋብቷል። የቅኔ መጻሕፍቱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በዚህ ዓለመ ሕይወት የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች አንሥተው ተከራክረዋል። የኢዮብ ታሪክ በአማኙ ማኅበረሰብ ዘንድ በእጅጉ የሚታወቀው የእኩይ ጣጣን (the problem of evil) ብቻ ሳይሆን የሙግት ጣጣንም (the problem of argument) የሚያወሳ መጽሐፍ በመሆኑ ነው።16 በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ የእኩይ ጣጣ ተወስቷል፤ የሙግት ጣጣም ተጠቅሷል። ኢዮብ ሁለቱንም አስተናግዷል፤ በአንድ በኩል መከራ ወርዶበታል (የእኩይ ጣጣ የተባለውን)፤ በሌላ በኩል መከራውን ለመረዳትና ቢቻል መከራውን በቃላት ኀይል ለመግለጽ በእጅጉ ጥሯል (የሙግት ጣጣ የተባለውን)። በኢዮብ መጽሐፍም ሆነ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎችን ፣ ዓለምን ፣ እግዚአብሔርንና መከራን ወይም ሥቃይን በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎች የመጨረሻ ነገረ መለኮታዊም ሆነ ፍልስፍናዊ መልሳቸውን አላገኙም። ይሁንና መከራ፣ ሥቃይና ሞት በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የመጨረሻ መልስና መፍትሔ ተሰጥቷቸዋል። ለጥያቄዎቹ የመጨረሻውን መልስ ለመስጠት መከጀል ምናልባት አይጠቅምም ይሆናል። የሚሻለው መጽሐፎቹ እንደሚያሳስቡን ለእግዚአብሔር ልዕልና መገዛትና በእርሱም መታመን ነው። ለእግዚአብሔር ልዕልና የሚገዙና በእርሱም የሚታመኑ ሰዎች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የትንታኔ አቅማቸውን ውሱንነት ይገነዘባሉ። ዕውቀት፣ ጥበብና የትንተና ኀይል መግለጽ የማይችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር በቂ ነው፤ እርሱ ሁሉንም ነገር ያውቃል ማለት ስንጀምር ጥያቄአችን ቢያንስ በከፊል መልስ ማግኘት ይጀምራ ል።17 ያልተመለሱ ጥያቄዎች ቢኖሩን እን ኳ ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር በመምጣት ነገሮችን ከእርሱ አንጻር እንድናጤን ዕድል ይሰጡናል። ነገሮችን ከእግዚአብሔር አንጻርና ከእኛ አንጻር መመልከት ትልቅ ልዩነት አለው። ከእርሱ አንጻር ስንመለከት ተስፋ ይኖረናል፤ ከእኛ አንጻር ስንመለከት ሁሉም ነገር ጭልምልም ይልና ግራ መጋባታችን ዑደቱ ይቀጥላል።
እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ ቅዱሳን የሚያልፉበትን ፈታኝ ወቅት እንዴት መመልከት አለባቸው? አሁን ራሱ እጅግ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እያለፍን ነው። በኮሮና ቫይረስ እየታወክን ነው። ወረርሽኙ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ሥራ እያጣን ነው። በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎች በበሽታው እየተሠቃዩ ነው። አንዳንዶቹም ሕይወታቸው እያለፈ ነው። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ መሥሪያ ቤቶች ወይ ለጊዜው ተዘግተዋል፤ አለዚያም ከሥረው እስከ ወዲያኛው ተዘግተዋል። በርካታ ተቋሞችም እንዲሁ ተዘግተዋል። ቤተ እምነቶችና ቤተ መቅደሶችም ደጆቻቸው ተቆልፏል። እንቅስቃሴ ቀጥ ብሏል፤ ሁሉም ነገር ዝግትግት ብሏል። እንኳን በእኛ ዕድሜ ይቅርና ባለፉት ኀምሳና መቶ ዓመታትም እንዲህ ያለ ነገር ታይቶም ተሰምቶ አያውቅም። ነገሩ ለማንም አስፈሪና አሳሳቢ ነው። ለምን ይህ ሆነ? ለምን እንዲህ ሆነ? ሄድ ሲልም ለምን እግዚአብሔር እንዲህ እንዲሆን ፈቀደ? ከፍ ሲል ያወሳኋቸው መልሶች እነዚህን ጥያቄዎች በተወሰ ደረጃ መልሰዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ለወረርሽኙ መልስ መስጠት አንድ ነገር ነው። ወረርሽኙን እንዴት እንመልከተው የሚለው ግን ሌላ ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው። የመጀመሪያው “ለምን?” የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ሲያደርግ፣ ሁለተኛው “እንዴት?” የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ያደርጋል። ለመጀመሪያው ጥያቄ ቊርጥ ያለ መልስ ለመስጠት ያስቸግር ይሆናል። ሁለተኛው ጥያቄ የመጀመሪያውን ያህል አወዛጋቢ አይሆንም የሚል እምነት አለኝ። ሁለተኛውን ጥያቄ ለመመለስ ፊታችንን ወደ ጥንት ክርስቲያኖች መመለስ ይኖርብናል። የጥንት ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ አስፈሪና አሳሳቢ በሽታ ወይም ወረርሽኝ ባጋጠማቸው ጊዜ ነገሩን የተመለከቱት እንዴት ነበር? በጣም የሚገርመው ክርስትና ያደገውና ከጓዳ ወጥቶ ያበበው በእንዲህ ዐይነቱ አስከፊ ጊዜ ነበር። ክርስትና ከሐዋርያቱ ዘመን በኃላ እስከ 300 ዓ.ም. ድረስ ዕድገቱ ዕድገቱ ያን ያህል ፈጣን አልነበረም። ሆኖም ከ250 ዓ.ም. በኋላ በጣም የሚያስደንቅ ዕድገት ማሳየት ጀመረ። ምን ሆነ? ምን ተከሰተ? ክርስትና እንዴት በቅጽበት ዓለም አቀፍ እምነት ሊሆን ቻለ? ሰበቡ ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ ከ150-300 የተከሰተውና አውሮፓን ሲያስጨንቅ የነበረው ወረርሽኝ እንደ ትልቅ ምክንያት ይጠቀሳል። በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች አስፈሪውን ዘመን የተመለከቱት እንደ ትልቅ ዕድል ነበር። እርግጥ ሌሎች ሲጨነቁ ክርስቲያኖቹን ምን ነካቸው? የሰዎችን ችግር ያቃልላሉ እንዴ? በሰዎች ችግር ይደሰታሉ እንዴ? ይኼ “ገፊነት ወይም ችግር ጠሪነት” አይደለም እንዴ? ሊባል ይችላል። ሮድኒ ስታርክ “The Rise of Christianity”በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ክርስትና በዚያ እጅግ አስፈሪ ዘመን ለማደግና ከጓዳ ወደ አደባባይ ወጥቶ ለማበብ የቻለበትን ሦስት ምክንያቶች ይጠቅሳል።18 እነዚህን ሦስት ምክንያቶች በተለየ መንገድ በማጎልበትናሌሎች ሁለት ምክንያቶችን በማከል አምስት ምክንያቶች እጠቅሳለሁ። በቅድሚያ በ350 ዓመታት ውስጥ ክርስትና በሮም ግዛተ ዐፄ ውስጥ ዕድገቱ ምን ይመስል እንደ ነበር በሚከተለው መንገድ እናጢን፤
ዓመተ ምሕረት | የክርስቲያኖች ቊጥር | ከሕዝቡ አጠቃላይ ቊጥር አንጻር |
40 | 1000 | 0.0017 |
50 | 1,400 | 0.0023 |
100 | 7,530 | 0.0126 |
150 | 40,496 | 0.07 |
200 | 217,795 | 0.36 |
250 | 1,171,356 | 1.9 |
300 | 6,299,832 | 10.5 |
350 | 33,882,008 | 56.5 |
እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በሮም ግዛተ ዐፄ የሚኖሩ ሰዎች ቊጥር ወደ 60 ሚሊዮን ይጠጋል19 |
የክርስቲያኖች ቊጥር በሮም ግዛተ ዐፄ ውስጥ እንዴት በፍጥነት እንዲህ ሊያድግ ቻለ? ከዳር የነበረው እንዴት ወደ መሀል ሊመጣ ቻለ? በ350 ዓመታት ውስጥ ቊጥራቸው ከ120 እንዴት ወደ 33 ሚሊዮን ሊያድግ ቻለ? አንደኛው ምክንያት የክርስትና አስተምህሮ ነው። ክርስትና ምጡቅ በሆነ አምላክ ቢያምንም ቅርብ በሆነ አምላክም ያምናል። ማለት በክርስትና አስተምህሮ የቃል ሥጋ መሆን፣ የአምላክ ከእኛ እንደ አንዳችን መሆን ትልቅ አስተምህሮ ነው (ዮሐ 1፥14)። እንዲህ ዐይነቱ አስተምህሮ ለብዙዎች አዲስ ከመሆኑም በላይ ትንተናውም አስገራሚ ነበር። ከሰዎች እንደ አንዳቸው የሆነና የሰዎችን መከራ የተካፈለ ጌታ እንዳ የሰሙ ሁሉ በትምህርቱ ጥልቀትና መሳጭነት ተገረሙ። ልክ እንደ ሰዎች ያዘነና ያለቀሰ ጌታ እንዳለ ሲሰሙ ልባቸው ተከፈተ። ሰዎች ብቻቸውን መከራ እየተቀበሉ አይደለም፤ ብቻቸውን እየተሠቃዩ አይደለም፤ ብቻቸውንም እየሞቱ አይደለም። ይህን ሁሉ የተካፈለ ጌታ አለ። ይህ ጌታ መከራችን ይገባዋል፤ ሥቃያችን ይገባዋል፤ ሞታችን እንኳ ይገባዋል። ብንሞትም ዳግመኛ ትንሣኤ እናገኛለን። በጥንቱ ዓለም አማልክት ለሰው ጒዳይ ደንታ የላቸውም። እንኳን ለሞት መፍትሔ መስጠት ይቅርና ለሰው ልጆች ህልውና ቁብ የላቸውም።20 በበሽታውና በወረርሽኙ መካከል ክርስቲያኖቹ ያወጁት እውነት ከዚህ በፊት ማንም ያልሰማው አዲስ አስተምህሮ ነበር።መከራና ሥቃይ ለሰው ልጆች ጭንቅ ቢሆኑም፣ ሞት ግን የመጨረሻው አስጨናቂ ነገር ነው። ክርስትና የጥንቱን ዓለም አመለካከት ሙሉ በሙሉ ገለበጠው፤ የግሪኮቹንም ሆነ የአረማውያኑን ፍልስፍና አንኮታኮተው። መከራ፣ ሥቃይናሞት የመጨረሻው አይደሉም፤ ከሞት በኋላ እንዲያውም ሕይወት አለ። ለመላው ፍጥረት ሁሉ የሞተና ከሙታን የተነሣ ጌታ እንዳለ ሲረዱ ብዙዎች ፊታቸውን ወደ ክርስትና መለሱ። እንደሚታወቀው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ሲቃወስ ሃይማኖታዊ ሕይወትም ይቃወሳል። አሁን ሁሉም አካላት የየራሳቸውን መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ከሁሉ በላይ ግን የሃይማኖት ተቋሞች የሚሰጡት መልስ በትልቅ ጉጉት ይጠበቃል። በወቅቱ የነበሩ የሃይማኖት ተቋማት ከሰጡት መልስ ይቅል ክርስትና የሰጠው መልስ እጅግ ልቆና ተሽሎ ተገኘ። የክርስትና መልስ የተጨነቁትን፣ ግራ የተጋቡትንና በሕይወት የተመረሩትን የሚያጽናና ነበር።
ሁለተኛው ምክንያት ቸርነት ነው፤ ማለት ተራድኦ፤ ማካፈል፣ ማከምና ማገልገል ትልቁ ሥራቸው ነበር። በዚያን ክፉ ዘመን ሁሉም ቤቱን ዘግቶ ሲቀመጥ ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ በሽታና ሞት ሳያግዳቸው በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎችን ይንከባከቡ የነበሩት። በርካታ የታሪክ ምሁራን እንዳመለከቱት ከሌላው ማኅበረሰብ ይልቅ ለወረርሽኙ ተግዳሮት ዝግጁዎች የነበሩት ክርስቲያኖቹ ነበሩ።21 በዚያ ክፉ ቀን የክርስቲያኖቹን ያህል እርስ በእርሱ የሚደጋገፍ ማኅበረሰብ አልነበረም። በጣም የሚገርመው በጥንቱ ዓለም መረዳዳትና መደጋገፍ ነውር ነው። ለሰዎች የምሕረት እጅን መዘርጋት ያለፉበትን እንደ መስጠት ነው፤ እናም ሰጪውና ተቀባዩ ይዋረዳሉ፤ ይነወራሉ። ሌሎችን መርዳት ሽንፈታቸውን/ስንፈታቸውን መርዳት ነው፤ ማለት ይበልጥ ሽኑፋን እንዲሆኑ መግፋት ነው። የግሪክ ልጆች አይረዱም፤ አይደገፉም፤ ራሳቸውን ይችላሉ እንጂ።22 እምነታቸው ይህ ይሁን እንጂ ወረርሽኙን ማሸነፍ አልቻሉም። ስታርክ በመጽሐፉ ላይ ክስተቱን ሲገልጽ፣ በወረርሽኙ ምክንያት “1/3 የሚሆነው የሮም ግዛተ ዐፄ ሕዝብ አለቀ። ሐኪሞች ሕሙማንን ጥለው ሸሹ፤ ካህናት ቤተ መቅደሶችን ዘግተው ከአገር ኮበለሉ” ይልና “ክርስቲያኖች ግን ለሁሉም ነገር መልስ ነበራቸው፤ ከሁሉ በላይ ግን ተገቢ እርምጃ ወሰዱ” ይላል።23 ተገቢው እርምጃ ሕሙማንን መንከባከብና በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ መርዳት ነበር። እርግጥ በወረርሺኙ ሳቢያ የሚሞቱት ሰዎች ቊጥር በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ እጅግ አነስተኛ ነበር። ለዚህ እንደ ትልቅ ምክንያት የሚጠቀሰው ለሕሙማኖቻቸው ያደርጉት የነበረው ልዩ ክብካቤ ነው። ይህን ትጋታቸውን የሮሙ ንጉሠ ነገሥት ሳይቀር በምሬት መልክ ገልጾታል (ለምን ተረዳዱ፤ ለምን ለሌሎች ምሕረት አደረጉ፤ ለምን ከእኛ ተሽለው ተገኙ፤ በሚል ቅናት)።24 እርስ በእርስ መተሳሰብ የጥንት ክርስቲያኖች ባህላቸው ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ “እርስ በርሳችሁ” (ἀλλήλων/አሌሎን) የሚለው ቃል 100 ጊዜ ተጠቅሷል። ቃሉ ከአንድነት፣ ከፍቅርና ከትሕትና ጋር ተዛምዷል። ለጥንት ክርስቲያኖች እነዚህ ከታች የተወሱት ምክሮች ዝም ብሎ ቃሎች ብቻ አልነበሩም። ቃሎቹን በእርግጥ በሕይወታቸው ኖረውታል። ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት፤
አንድነትን በተመለከተ | ፍቅርን በተመለከተ | ትሕትናን በተመለከተ |
“እርስ በርሳችሁ ተስማሙ” (ማር 9፥50) | “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ” (ዮሐ 13፥34) | “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” (ሮሜ 12፥10) |
“እርስ በርሳችሁ አታንጐራጒሩ” (ዮሐ 6፥43) | “እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ” (ገላ 5፥13) | “እያንዳንዱ/እርስ በርሳችሁ… ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር” (ፊል 2፥3) |
“እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ” (ሮሜ 12፥16፤ 15፥5) | “እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ” (ኤፌ 4፥2) | “ለእያንዳንዳችሁ/እርስ በርሳችሁ በክርስቶስ ፍርሀት የተገዛችሁ ሁኑ” (ኤፌ 5፥21) |
“እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” (ሮሜ 15፥7) | “እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ” (1ጴጥ 5፥14) | “እርስ በርሳችሁ… የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ” (ሮሜ 12፥16) |
“እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ” (1ቆሮ 11፥33) | “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ሮሜ 12፥10) | “እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ” (1ጴጥ 5፥5) |
አውሳቢየስና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘጋቢዎች እንዳመለከቱት መላው የሮም ግዛተ ዐፄ ነዋሪዎች በወረርሽኙ ምክንያት መፈጠራቸውን ሲጠሉ ክርስቲያኖች ግን በአምላካቸው ደስ እየተሰኙ ማኅበረሰባቸውን ያገለግሉ ነበር። ሌሎች ሁኔታውን እንደ መቅሠፍት ሲመለከቱት እነርሱ ግን የምሥራቹን ወንጌል ለመስበክ እንደ ትልቅ ዕድል ወሰዱት። አንድ የታሪክ ጸሐፊ ብዙ ምንጮችን አመሳክሮ ሁኔታውን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ “ወደፊት የሚተመው የሮም ዐፄአዊ አገዛዝ ኀይል በተደጋጋሚ ይገታ ነበር፤ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ሥልቶች መሥራት አልቻሉም። ወረርሽኙ ልክ አውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ ሁሉንም ጠራርጎ እንደሚወስድ ዐይነት ነበር፤ ሁሉም ነገር ቀጥ አለ፤ ሰዎች ሁሉ በትልቅ በድንጋጤ ተዋጡ”።25 ክርስቲያኖች ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው የተሰጣቸውን ተልእኮ በትጋት መፈጸም ቀጠሉ። አንድ ነገር በሚገባ ተረድተው ነበር። ጳውሎስ እንዲህ እንዳለው፤ “እግዚአብሔር ለቊጣ አልመረጠንምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ፤ የምንነቃም ብንሆን የምናቀላፋም ብንሆን ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ” (1 ተሰ 5፥9-10)። በሕይወት መኖርም ሆነ መሞት ሁለቱም አንድ ናቸው ለማለት የደፈሩት ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ። ምክንያቱም ወሳኙ በክርስቶስ መሆናቸውና እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መሆኑ ነው። ጌታም ያስተማራቸው “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” በማለት ነው (ዮሐ 11፥25)። በጥንቱ ዓለም እነዚህን ቃሎች በጽናት በእርግጠኛነት የሰበካቸው ማንም የለም – ከክርስቲያኖች በስተቀር።
ጥቁሩ ሞት (1347-1350) በመባል የሚታወቀውና 1⁄4 የሚሆነውን የአውሮፓን ሕዝብ የጨረሰው ወረርሽኝ ከዚያ በፊት ከነበሩት ሁሉ በሚገባ ታሪኩ የተዘገበ ወረርሽኝ ነው። ይህ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ሌሎች አራት ወረርሽኞች የአውሮፓን ሕዝብ አናውጠው ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዱ “ቡቦኒክ ወረርሽኝ” የሚባለው ነው።26 ታላቁ የተሐድሶ መሪ ማርቲን ሉተር የኖረው ይህ ወረርሽኝ አውሮፓን ባስጨነቀበት ሰዓት ነበር። ኦገስት 2 ቀን 1527 ዓ.ም. ሉተር የሚኖርባት ከተማ ዌትንበርግ በወረርሽኙ ተጠቃች። ሉተርና እርሱ የሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ መምህራን ከተማዋን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ። ሉተርና ጥቂት ሰዎች ትእዛዙን ወደ ጎን ብለው እዚያው ያሉበት ከተማ ቀሩ። ምክንያታቸው አንድ ብቻ ነበር – የታመሙብንን ጥለን አንሄድም የሚል። ሉተር ሰዎች ከአጠገቡ እየረገፉ እን ኳ ከተማዋን ለቆ ለመውጣት አልፈለገም። በዚህ መካከል አንድ ደብዳቤ ዮሐን ሔስ27 ከሚባል የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ደረሰው። ደብዳቤው አንድ ሁነኛ ጥያቄ ይዟል፤ “ገዳይ ወረርሽኝ ሲከሰት ምን እናድርግ? ጥለን እንሽሽ ወይስ በዚያው ባለንበት ሕሙማንን እየረዳን እንቀመጥ?” የሉተር እጥር ምጥን ያለው መልስ “ወረርሽኝ ሲከሰት እዚያው ባላችሁበት ሁኑና ተረዳዱ” የሚል ነበር። እንደ ሉተር አባባል ተጣጥሎ መሄድም ሆነ መቷቷው ተገቢ አይደለም። በምሳሌ ነገሩን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፤ “የታመመው ወይም መንገድ ላይ የወደቀው ክርስቶስ ቢሆን ወይም እናቱ ብትሆን ሰው ሁሉ እቅፍ ድግፍ ሊያደርጋቸውና ረዳታቸው ለመሆን ይጣደፋል። ሰው ሁሉ ደፋርና ቆፍጣና ይሆናል፤ ማንም ትቷቸው አይሄድም፤ ይልቁንም ሁሉም ለእርዳታ ደፋ ቀና ይላል። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ክርስቶስ የተናገረውን ያላስተዋሉ ናቸው። ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት’ (ማቴ 25፥40)። ስለ ታላቂቱ ትእዛዝ ሲናገር ደግሞ ‘ሁለተኛይቱ ይህችን ትመስላለች፤ እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት’ (ማቴ 22፥39)። እዚህ ላይ እንደምታዩት እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራን መውደድ አልተነጣጠሉም፤ ይልቁንም ተካከሉ። የታመሙብንን ስናገለግልና ስንረዳ ክርስቶስን እያገለገልንንና እየረዳን ነው”።28
ሦስተኛው ምክንያት ፍቅር ነው፤ ማለት የፍቅር እጅን ዘርግቶ ምስኪኖችን መቀበል፤ መጠጊያና መጠለያ መስጠት። ወረርሽኙ ከከተማ እስከ ገጠር መዝለቁና የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱ ብዙዎችን ያለመጠጊያ አስቀርቷል። አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የሮም ግዛተ ዐፄ ነዋሪ በወረርሽኙ ሕይወቱ ረግፏል። በተለይ በ250 ዓ.ም. የተከሰተው ወረርሽኝ አያድርስ ነበር፤ በሮም ከተማ ብቻ በየቀኑ 5,000 ሰዎች ይሞቱ ነበር፤ በገጠሩ ክፍል የሟቾቹ ቊጥር ከዚህም ይከፋል።29 ብዙዎች ቤታቸውን ለመክፈትና መድረሻ ያጡትን ለመቀበል አቅም አጡ። በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖቹ ቤታቸውን በወረርሽኙ ለተጠቁት ክፍት አደረጉ። መድረሻ ያጡትን እየተቀበሉ ማስተናገድና በሚያስፈጋቸው ነገር ሁሉ መርዳት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆነ። ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ እንደ ተቀበለ እነርሱም ሰዎችን ሁሉ ተቀበሉ። በዚህም ከራስ አልፎ ሌሎችን መርዳት ወይም ለሌሎች ራስን መሠዋት ትልቅ ሥነ ምግባራዊ እሴት መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም አስተዋወቁ። የአንድ እምነት ትክክለኛነቱ የሚረጋገጠው ለሰዎች በሚያደርጋቸው መልካም ነገሮች ነው ባይባልም፣ ከፍቅር የሆነ እጅን መዘርጋት ግን ከሃይማኖት ቤተሰቦች ሁሉ ይጠበቃል። ኢየሱስ እንዳስተማረው ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ተገቢ ነው። ይህ ነበር ክርስቲያናዊ መርሗቸው። ከሕመማቸው ያገገሙትና ከሞት የተረፉት ሰዎች በክርስቲያኖቹ ድርጊት እጅግ ተገረሙ። ሌሎች ለማድረግ ያልፈለጉትን ነገር ክርስቲያኖች ብቻ አድርገው መገኘታቸው ልዩነቱ እምን ላይ እንደሆነ ማሰላሰል ጀመሩ። እኛና የእኛ ሰዎች ልናደርግ ያልቻልነውን እነርሱ እንዴት አደረጉት? የስቶይክና የሌሎች ፍልስፍና ተከታዮች ለወረርሺኙ ምንም ዐይነት ምላሽ አልነበራቸውም። ወረርሽኙ መቅሠፍት ነው፤ የአማልክት ቊጣ ነው ከማለት ወዲያ ምክንያቱንና መፍትሔውን መስጠት አልቻሉም።30 ክርስቲያኖቹ ግን እጃቸውን ዘረጉ፤ አጋጣሚውን እንደ ዕድል ወሰዱት። በዚህ ዓለም የሚሆነው ነገር በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሚሆነው የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች በሁኔታዎች መክፋት አይበረግጉም። ይልቁንም እግዚአብሔርን ይታመናሉ፤ ለክብሩም ይተጋሉ።
አራተኛው ምክንያት ወንጌል ሰባኪነትና ተአምራት አድራጊነት ናቸው። የጥንት ክርስቲያኖች ሲበዛ ወንጌላውያን ነበሩ ማለት ይቻላል። በእጃቸውም እውነተኛ ድንቅና ተአምራት ይደረጉ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው አውሳቢየስ ይህን ሁኔታ በሚገባ ዘግቧል።31 ምንም እንኳ አንዳንዶች በወቅቱ የታየውን ፈጣን ዕድገት ከንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ግለ ገጠመኝ ጋር ቢያዛምዱትም፣ ወንጌል ሰባኪነታቸውን መጠራጠር የሚቻል አይመስለኝም።32 በአፈ ታሪኩ መሠረት ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ አንድ ሕልም ያያል፤ ሕልሙ “በዚህ [በመስቀል] ታሸንፋለህ” የሚል አምላካዊ መገለጥ ነበር። በሕልሙ በሰማይ ላይየክርስቶስን መስቀል ተመለከተ።33 እውነትም ቈስጠንጢኖስ የሮም ንጉሦችን ጦርነት ገጥሞ አሸነፈ። ቈስጠንጢኖስ በጦርነቱ ያሸነፈው ሁኔታዎች ተመቻችተው ይሁን ወይም በለስ ቀንቶት ወይም በአምላክ እርዳታ ራሱን የቻለ ክርክር አለው። ታሪክ ጸሐፊው አውሳቢየስ እንደሚለው ቈስጠንጢኖስ የሮም አምባገነኖችን ለማሸነፍ መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተረድቶ ነበር። በወቅቱ ቈስጠንጢኖስ ያየውን ሕልም ትርጒም ባይረዳም ነገሩ አብከነከነው። ስለዚህ አማካሪዎቹን ጠርቶ ነገሩን እንዲያብራሩለት አደረገ። አማካሪዎቹም ክርስቶስ ማን እንደ ሆነ ነገሩት፤ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደ ሆነ ተረኩለት። በሕልሙ ያየውም መስቀል የክርስቶስን ተሠግዎት እንደሚገልጽ አስረዱት። ቈስጠንጢኖስ በሰማው ነገር ተነክቶ የክርስቲያኖችን አምላክ ለማምለክ ወሰነ፤ ጥምቀቱን ግን እንዲዘገይ አደረገ። እዚህ ላይ ትልቁ ነገር በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን በደል ማስቀረቱ ነው። አንዳንዶች ይህን በመንተራስ የክርስቲያኖች ቊጥር ያደገው በቈስጠንጢኖስ ምክንያት ነው ይላሉ። ልክ ነው የቈስጠንጢኖስ ክርስትናን መቀበል እን ደ አንድ አዎንታዊ እርምጃ ይቈጠር ይሆናል።34 ነገር ግን ክርስትና ያደገው ወንጌል በመታወጁና የእግዚአብሔር ብርቱ ክንድ በመዘርጋቱ ነው። ወንጌላዊነት ለጥንት ክርስቲያኖች አዲስ ነገር አይደለም። የጳውሎስ ሦስት ሚሲዮናዊ ጉዞዎች ይህን ይመሰክራሉ። ወደ ዓለም ሁሉ መሄድና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ መስበክ የክርስትና አንዱ ተእልኮ ነው። በአንድ በኩል ወንጌል መሰበኩ፣ በሌላ በኩል ተአምራት መደረጉ ሰዎች ወደ ክርስቶስ እንዲመለከቱ ዕድል ሰጠ። ይህም ልክ በሐዋርያቱ ዘመን እንደተደረገው ነበር፤ “እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” (ማር 16፥20)። በክርስትና ትምህርት መሠረት እግዚአብሔር ልዑል አምላክ ነው። እርሱ በወደደና በፈቀደ ጊዜ ራሱንና ምሕረቱን ይገልጣል፤ ሕሙማንን ይፈውሳል። ሰዎችን መታደግና መቤዥት በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆነ ሁሉ መፈወስና መጠገንም በእርሱ እጅ ነው።
እንግዲህ ክርስትና በዚያን ዘመን ያደገው ወንጌሉ በመሰበኩና በተአምራት በመጽናቱ ነው።35 እዚህ ላይ በርካታ የታሪክ ምስክርነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ሁሉም የሚመሰክሩት የክርስትና ዕድገት ከተአምራ ት ጋር የተዛመደ መሆኑን ነው።36 እን ደ ጠርጡሊያኖስ (155–240) የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆነ ሌላም ምክንያት ይጠቅሳሉ። በራሱ በጠርጡሊያኖስ አገላለጽ “የክርስቲያኖች ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው”። ፕሌኒ የተባለ የሮም ተወላጅና የሕግ ባለሙያ (61–113 ዓ.ም.) ለንጉሥ ትራጃን ባቀረበው ጥናት ላይ እንዳመለከተው ቤተ ጣዖቶች ወናቸውን እየቀሩና ገቢያቸውም እየቀነሰ ነው፤ ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ መዘጊያቸው ቅርብ ነው። ፕሌኒ ንጉሡን ሲያስጠነቅቅ የክርስቲያኖቹ አካሄድ በጊዜ መቀጨት አለበት ይላል።37 ተመሳሳይ ሁኔታም በእነ ጳውሎስ ዘመን ተፈጽሞ ነበር። ለአርጤምስ ቤተ መቅደስ ምስሎችን እየሠራ ብዙ ትርፍ ያገኝ የነበረው ድሜጥሮስ፣ በእነ ጳውሎስ ላይ ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ገቢያቸው እንደሚቀንስና አርጤምስም ባዶዋን እንደምትቀር በብርቱ ማሳሰብ ነበረበት። ጳውሎስ “በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብ እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል” ይላል (ሐሥ 19፥26)። ወንጌል ሲሰበክና ተአምራት ሲደረጉ እንደ አርጤምስ ያሉ ቤተ ጣዖቶች ወናቸውን ይቀራሉ። ምናምን ይሆናሉ፤ ታላቅነታቸውም ይሻራል። ምክንያቱም አሁን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጧል። “የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (1ዮሐ 3፥9)። የጥንት ክርስቲያኖች ወረርሽኙን እያሰቡ ከመጨነቅ ይልቅ ነገሩን እንደ ዕድል ተመለከቱት። እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ ፋንታ አጋጣሚውን ተጠቀሙበት፤ የኢየሱስን ጌትነትና አዳኝነት አወጁበት።
አምስተኛው ምክንያት ሥነ ጽሑፍ ነው። ከሌሎች የእምነት ክፍሎች ይልቅ ክርስትና ለሥነ ጽሑፍ ትልቅ ስፍራ አለው። የጥንት ክርስቲያኖች “የመጽሐፉ ሕዝብ” ነበሩ። የመጽሐፉ ሕዝብ ሲባል ንባብ፣ ጽሑፍ፣ ቅጂና ስርጭት ማለት ነው።38 ምንም እንኳ ኢየሱስ በጽሑፍ ያኖረልን ምንም ዐይነት ነገር ባይኖርም ትምህርቱ ግን ቋሚ በሆነ መንገድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተጠብቋል። የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ በሥነ ጽሑፍ ያምናል። ሙሴና ነቢያቱ የእግዚአብሔርን ቃል በጽሑፍ እንዲያኖሩ ታዘዋል። የአዲስ ኪዳንም ጸሐፊዎች እንዲሁ ታዘዋል። ለምሳሌ ዮሐንስ ያየውን ራእይ እንዲጽፍ ተነግሮት ነበር። “እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ” (ራእ 1፥19)። ምንባብና ንባብ ማለትም ጽሑፍና ማንበብ በክርስትና ተመክሮ ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳላቸው ቅዱሳት መጻሐፍት መስክረዋል። ለምሳሌ ጳውሎስ የድኅነት ምስጢር በምንባቡ ላይ እንደ ተጠበቀ አመልክቷል (2ጢሞ 3፥ 16)። ጢሞቴዎስን “እስክመጣ ድረስ . . . ለማንበብ . . . ተጠንቀቅ” ይለዋል (1ጢሞ 4፥13)። ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብና ማስተንተን የክርስቲያኖች ባህል ነበር። መጋብያኑም ሆነ መምህራኑ ትምህርት ዘለቆች ነበሩ። አምልኳቸው በንባብና በማስተንተን ላይ ያተኰረ ነበር።39 በንባብና በማስተንተን ላይ ያተኰረ አምልኮት ደግሞ መጻሕፍቱን በቅጂ መልክ ማባዛትና ማሰራጨት ይኖርበታል። አሁንም በዚህ ረገድ የጥንት ክርስቲያኖችን የሚወዳደራቸው አልነበረም። “ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ” (ቈላ 4፥16)። ይህ ባህል ከሐዋርያቱ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ላሪ ሑርታዶ እንደሚለው ማንበብ፣ ማስተንተንና ማሰራጨት በክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ የሚታይ ተግባር ነበር። በጥንቱ ሮም ግዛተ ዐፄ በዚህ ረገድ የሚታወቁት ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ፤ ማለት ማንበብና ማስተንተን የክርስቲያኖች ብቻ ልዩ መታወቂያቸው ነበር። ሌሎች የሃይማኖት ክፍሎች የራሳቸው ቅዱሳን ጽሑፎች ቢኖሯቸውም፣ የሚነበቡና የሚጠኑ አልነበሩም።40 በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በማኅበር ማለትም በአምልኮት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በግልም ይነበቡና ይጠኑ ነበር (ሉቃ 1፥4፤ ሐሥ 15፥21)።
ሰማዕቱ ዮስጦስ (100– 165) እንዳመለከተው በእርሱ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ቃሉን በማንበብና በማስተንተን ይተጉ ነበር። በጥንቱ ዓለም የክርስቲያኖችን ያህል በጽሑፍ ባህሉ የሚታወቅ ሕዝብ የለም።41 ከሁለተኛው እስከ አራተኛው ምእተ ዓመት ብቻ በክርስቲያኖች የተጻፉ መጻሕፍት ስፍር ቊጥር የላቸውም። ሊቃውንት እንደሚሉት አዲስ ኪዳን ደብዛው ቢጠፋ እንኳ ከእነዚህ መጻሕፍት ላይ ተለቅሞ ተመልሶ መተካት ይችላል። ማንበብ፣ ማስተንተንና ማሰራጨት ትልቅ ትጋት ይጠይቃል። ትጋት የሚመመጣው ደግሞ ከጽኑ እምነት ነው። ሰዎች ላላመኑበት ነገር ሕይወታቸውን አይሰጡም። በተለይ ነፍስን ለሚጠይቅ ነገር ማንም ራሱን አይሠዋም። የጥንት ክርስቲያኖች በዚያ አስጨናቂ ዘመን በፍርሃት ተውጠው አልተቀመጡም። ይልቁንም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና በማስተንተን ይተጉ ነበር። የክርስትናን አስተምህሮ ይመክቱ ነበር። መምህሬ ክሬግ ኪነር ወደ ክርስትና በመጣ ሰሙን መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም አዲስ ኪዳንን በዓመት አንድ ጊዜ ያነብ ነበር። ከዓመታት በኋላ ይህን ልማዱን አሻሽሎ አዲስ ኪዳንን በወር አንድ ጊዜ ያነብ ነበር። አሁን ግን (እንዲህ ማድረግ ከጀመረ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል) አዲስ ኪዳንን በሳምንት አንድ ጊዜ ያነባል። ሲያስተምር ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በቃሉ ይወጣቸዋል። ለእኛም እንዲህ ይሁንልን። ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት መግቢያ በሮች ናቸው። ቃሉን በማንበብና በማስተንተን ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት መቅረብ ይቻላል። ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ስንቀርብ ሁኔታችንን ከእርሱ አንጻር መመልከት ይሆንልናል።
ለመጨረሻዎቹ ሁለት ምክንያቶች አጽንኦት የሰጠሁት አንድ እውነታ ለመግለጽ ነው። ይኸውም አንዳንድ ለዘብተኞች እንደሚሉት ክርስትና የተስፋፋው በመሃይማን ዘንድ እንጂ በምሁራንና በባለጠጎች ዘንድ አይደለም፤ እናም ዕድገቱ እንደ ትክክለኛ ዕድገት መቈጠር የለበትም ይላሉ። እንደ ካርል ማርክስና ፍሬድሪክ ኤንግልስ የመሳሰሉ ማርክሳውያንም ተመሳሳይ ሙግት ሰንዝረዋል። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ክርስትና የተስፋፋው በዝቅተኛ መደብ በሚገኙ ግለሰቦች ዘንድ ብቻ ነው።42 እምነቱ ባለጠጎች፣ ምሁራንና ነገሥታት ሰፈር አልደረሰም ይላሉ። እንዲያውም ሃይማኖት ላልተማሩ እንጂ ለተማሩ አይሆንም፤ እምነቱ ባልነቁና ባልበቁ ሰዎች ዘንድ ቢስፋፋ ምንም አያስደንቅም። እንደ እነዚህ ዐይነት ሰዎች ችግሮቻቸውን የሚያክሙት ችግሩን በመጋፈጥ ሳይሆን ከችግሩ በመሸሽ ነው። ሃይማኖት ደግሞ ጥሩ መሸሺያና መደበቂያ ነው። የእምነቱ ዋነኛ አቀንቃኝ የነበረው ጳውሎስ እንኳ እቅጩን ተናግሯል። ራሱ ጳውሎስ “ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናል፤ . . . እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ ሆነናል” (1ቆር 4፥9፣13) ብሏል ይላሉ። በእውነተኛው እነዚህ ክሦች ተጨባጭ ማስረጃ የላቸውም፤ ከእውነት የራቁ ብቻ ሳይሆኑ ጭፍን ክሦች ናቸው። በጥንቱ ዓለም ክርስትና ያልደረሰበት የሕይወት ክፍል የለም። የመንግሥት ባለሥልጣኖች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሕክምና አዋቂዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ ታላላቅ ነጋዴዎችና ባለጠጎች ክርስትናን ተቀብለዋል። እንኳን በሁለተኛው፣ በሦስተኛውና በአራተኛው ምእተ ዓመት ይቅርና ሐዋርያቱ በሕይወት በነበሩበት ዘመንም የከፍተኛው መደብ አባላት ክርስቲያኖች ነበሩ። ለምሳሌ ኤርስጦስን መጥቀስ ይቻላል፤ “የከተማው መጋቢ [ከንቲባ] ኤርስጦስ … ሰላምታ ያቀርብላችኋል” (ሮሜ 16፥23፤ 2ጢሞ 4፥20)። ልድያ የምትባል ባለጠጋም ነበረች (ሐሥ 16፥14-15)። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከከፍተኛው መደብ ክፍል በርካታ ሰዎች ተጠቅሰዋል (ሐሥ 9፥36፤ 10፥1)። በሁለተኛውና በሦስተኛው ምእተ ዓመት ላይ የነበሩ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ሳይቀሩ ክርስትናን ተቀብለዋል።43 በመጀመሪያዎቹ አራት ምእተ ዓመታት የነበሩ ክርስቲያን ጸሐፊዎችን ሥራ በቅጡ ያጠና አንድ ሊቅ እንዳሳሰበው ጽሑፎቻቸው ለትምህርት ዘለቆች የሚመጥኑ ጥልቅ ሥራዎች ነበሩ።44 ክርስትና እንዲያውም ከሁሉ አስቀድሞ የተስፋፋው ባልተማሩት ሳይሆን በተማሩት መካከል ነው፤ በቤት አጋልጋዮች መካከል ሳይሆን በዐፄዎች ቤተ መንግሥት ነው።45 ራሱ ባርት ኸርማን በአንድ በኩል ከለዘብተኞቹ ምሁራን ጋር እየወገነ በሌላ በኩል እንዲህ ይላል፤ ክርስትና ተጽዕኖ ያላሳደረበት የትምህርት ዘርፍ አለ ለማለት ያስቸግራል። ሥነ ጥበብ ቢሆን ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ ቢሆን ፍልስፍና፣ ሥነ ምግባር ቢሆን ሕግ፣ ሁሉም የክርስትና ብርቱ አሻራ አርፎባቸዋል፤ እዚህ ላይ ሥነ ምጣኔንም መጥቀስ ይቻላል። ክርስቲያናዊው አስተምህሮ መላውን አውሮፓ፣ ትንሹ እስያንና ሰሜን አፍሪካን ባያጥለቀልቅ ኖሮ በእነዚህ የትምህርት ዘርፎች ስመ ጥር የሚባሉ ምሁራን ባልተፈጠሩም ነበር።46
በመጨረሻ እንዲህ በማለት ነገሬን ልጨርስ፤ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ አማካይነት ወደ ዓለሙ መጥቷል። ምሕረቱን ገልጧል፤ ፍቅሩን አሳይቷል፤ እጁን ዘርግቷል። ተፍጻሜታዊው መሲሕ ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። አሁን ምንም ነገር ሊያስፈራን አይገባም። እግዚአብሔር አዛዥነቱን ለማንም አልሰጠም፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን አዛዥነት ማንም መውሰድ አይችልም። በሽታም ሆነ ሞት እግዚአብሔርን ከዙፋኑ አይነቅሉትም። ይልቁንም በሽታና ሞት በትንሣኤው ጌታ መፍትሄ አግኝተዋል። ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቷል። መቃብሩ ባዶ ነው፤ ሞት አይዘውም፤ ሞት ከንቱ አያደርገውም። እግዚአብሔር ጥንትም ሆነ አሁን ከሃሌ ኲሉ ነው፤ ማለት ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። አማሬ ኲሉ ነው፤ ማለት ሁሉን አዋቂ ጌታ ነው። አኀዜ ኲሉና መላዔ ኲሉ ነው፤ ማለት በሁሉ ስፍራ የሚገኝ ልዑል ነው። ስለዚህ ምንም ነገር ሊያስፈራን አይገባም። በኮቪድ 19 ምክንያት አገር ሊሸበር፣ ዓለምም ሊታወክ ይችላል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ በምንም ሁኔታ ውስጥ ኀይላቸውን ያድሳሉ ። ከእግዚአብሔር ጋር የሆኑ ከሁኔታዎች በላይይሰፋሉ ፤ ይንሳፈፋሉ ። ፍርሃት አያቀልጣቸውም፤ ይልቁንም በሚያስፈራው ሁኔታ ውስጥ ከጌቶች ጌታ ጋር ሆነው ይጓዛሉ። እንግዲህ ወሳኙ እኛያለንበት ሁኔታ ሳይሆን የጌታ ከእኛ ጋር መሆነ ነው። ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቷል፤ ሞትንም ድል አድርጓል። እርሱ ከእኛ ጋር ከሆነ ታዲያ ማን ሊቃወመን ይችላል?
1. ለዚህ ለዛሬ በሽታ ነጩን የባሕር ዛፍ ቅጠሉን እየቀቀላችሁ ማታ ስትተኙ በላቦቱ ታጠኑ። ደግሞ የባሕሩን ዛፍ ቅጠል እርጥቡን በብዙ አድርጋችሁ በቤታችሁም ውስጥ በየደጃችሁ እያነደዳችሁ አጭሱበት።
2. አይነ ምድራችሁን ሳትቆፍሩ አትቀመጡ። አይነ ምድር ተቀምጣችሁ ስትነሡ ባይነ ምድራችሁ ላይ የባሕር ዛፍ ቅጠል ጣሉበት። ያልጣላችሁበት እንደሆነ ከአይነ ምድራችሁ ላይ እንደ ገና በሽታ ይነሣል።
3. ባትታመሙም ብትታመሙም ውሃ እያፈላችሁ በውስጡ ጨው እየጨመራችሁ ጠዋትና ማታ አፋችሁን ተጉመጥመጡ።
4. ውሻ ድመት በቅሎና ፈረስ ሌላም ይህን የመሰለ ሁሉ በሞተባችሁ ጊዜ ሽታው በሽታ ያመጣልና ቅበሩት።
5. ሰው የሞተባችሁ እንደሆነ መቃብሩን በጣም አዝልቃችሁ ሳትቆፍሩ አትቅበሩ። በጣም ሳትቆፍሩ የቀበራችሁ እንደሆነ አውሬና ውሻ እያወጣ ይበላዋል። ሽታውም ከዛሬው የበለጠ በሽታ ያመጣብናል።
6. በቤቱ ሰው የታመመበት ሰው ወደ ማዘጋጃ ቤት ድረስ እየመጣ አለዋጋ መድኃኒቱን ይውሰድ። በማናቸውም ምክንያት የሚያድን እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን የሚያድን እግዚአብሔር ነው ብሎ መድኃኒት አላደግም ማለት እግ ዚአብሔርን መፈታተን ይሆናልና መድኃኒት አናደርግም አትበሉ። መድኃኒትንም የፈጠረልን እግዚአብሔር ነው።
7. ደግሞ ከመቃ ብር ላይ በሽታ እን ዳይነሣ ብሎ መንግሥታችን በቸርነቱ ብዙ ኖራ በየቤተ ክርስቲያኑ አስመጥቶልናልና በመቃብሩ ውስጥ ሬሳውን አስገብታችሁ በላዩ ጥቂት አፈር ጨምራችሁ ባፈሩ ላይ ኖራውን አልብሱና ከዚያ በኋላ አፈር መልሱበት። ኖራው የሬሳውን በሽታ ያጠፋውና በሽታ እንዳይነሣ ይሆናል።
ኅዳር 20 ቀን፥ 1911 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ።
የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዲሬክተር ኅሩይ ወ. ሥ.
Share this article:
ይቅርታ መጠየቅ ምን ማለት ነው? ሰዎች ይቅርታ ለመጠየቅ ለምን ይቸገራሉ? የተሠራው በደል በተበዳዩ ላይ ካሳድረው ጉዳት አንጻር፣ የበዳዩ ይቅርታ ጥየቃ የሚያጎናጸፈው ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ ምንድን ነው?
Observers take wait-and-see approach to televangelist “correcting” his prosperity gospel theology.
ይህ ያለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብና የባህል ሽግግር/ለውጥ እጅግ በጣም ፈጣን የሚባል ነው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአንድ አካባቢ ያሉ አስተሳሰቦች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሃይማኖታዊ ተዋስኦዎች፣ ወዘተ. ወደ ሌላው አካባቢ ለመድረስ ዓመታትን፣ ምናልባትም ዘመናትን የሚያስቆጥሩበት ረጅሙ ጊዜ አሁን አጥሯል፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም፣ የብዙኀን መገናኛ ሚና ግን ጉልሕ ሥፍራ የሚይዝ እንደ ሆነ ከብዙዎች የተሰወረ አይደለም፡፡
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment