[the_ad_group id=”107″]

ኢየሱስ እና የመከራ ሕይወት

በእግዚአብሔር ሕልውና የማያምኑ ሰዎች “እግዚአብሔር የለም” ለማለት በየዘመናቱ ከሚያነሧቸው ጥያቄዎች አንዱ በምድር ላይ የመከራ መኖር ነው፡፡ ʻእግዚአብሔር ቢኖር ይህ ሁሉ ጥፋት በሰዎች ላይ ለምን ይደርሳል?ʼ ይላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሰዎችም ጥያቄውን ደጋግመው ያነሡታል፡፡ ሰዎች መከራን በተለያየ መልኩ ሲጋፈጡ በእግዚአብሔር ሕልውና፣ በእግዚአብሔር መልካምነት ወይም በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ላይ ጥያቄ ይፈጠርባቸዋል፡፡ የመከራ ሕይወትና የእግዚአብሔር ሕልውና የተጋመዱ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ “እግዚአብሔር ከሌለ ይህ ሁሉ መልካም ነገር እንዴት ይኖራል? እግዚአብሔር ካለስ እንዴት ይህ ሁሉ ክፋት ይኖራል?” ሲል የጠየቀው፡፡[1]

ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍም እንዲህ ያሉ ተቃውሞዎችንና ክርክሮችን በታማኝነት ዘግቦ ስላቈየልን ቅዱሳን አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ሲሟገቱና ጥያቄ ሲያነሡ እናያለን፡፡ ለምሳሌ፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ለምን ደረሰብን?” የሚለው የጌዴዮን ጥያቄ ነው (መሳ. 6፥13)፤ ዕንባቆም ደግሞ “ሰዎችንም … አለቃ እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ?” ሲል እግዚአብሔርን ይሞግታል (ዕን. 1÷14)፡፡ ኤርምያስ በተራው “እንዳንቀላፋ ሰው፣ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኀያል ለምን ትሆናለህ?” በማለት እግዚአብሔርን ይጠይቃል (ኤር. 14፥9)፡፡ በተለይ መዝሙረ ዳዊትን ማጥናት ለዚህ በቂ ማስረጃ ይሰጣል፤ ምክንያቱም የመዝሙራቱ ይዘት ስድሳ በመቶው ሰቆቃና እንጉርጉሮን የያዘ ነውና፡፡[2] ስለዚህ መዝሙረኛውም፣ “አቤቱ፣ ንቃ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፣ ለዘወትርም አትጣለን” ሲል ለምኗል (መዝ. 44፥22)፤ “በጩኸት ደከምሁ፤ ጕሮሮዬም ሰለለ፤ አምላኬን ስጠብቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ (መዝ. 69፥3) በማለት ሲናገር፣ ጌታ ኢየሱስም “አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ?”በማለት የተናገረው ከዚሁ የመዝሙር መጽሐፍ ወስዶ ነው (ማቴ. 27፥46፤ መዝ. 22፥1)፡፡

በተለይ መከራ ሲነሣ ኢዮብን አለማንሣት አይቻልም፡፡ ሆኖም ኢዮብም ሆነ ከላይ የጠቀስናቸው ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ባለቤት የሆኑት ሰዎች ግን የእግዚአብሔርን ሕልውና አልካዱም፤ በእግዚአብሔር ማመናቸውም ግን ተቃውሞአቸውንና ሙግታቸውን ከማቅረብ አልከለከላቸውም፡፡ እምነት ለጥያቄና ለተቃውሞ ቦታ አለውና!

እውን እግዚአብሔር እያለ ለምን ይህ ሁሉ ግፍና ሰቆቃ ይደርሳል? በእርግጥ በዚህ የመከራ ጥያቄ ላይ ብዙ ተነግሯል፣ ብዙ ተጽፏል፤ ብዙ ተሰብኳል፤ ነገር ግን ጥያቄው “ዐሥሬ ተጠይቆ፣ ዐሥሬ መልስ አግኝቶ ዳግመኛ ዐሥሬ የሚጠየቅ”[3] ዐይነት በመሆኑ ዛሬም ልናነሣው ግድ ይሆናል፤ ወይም አንድ ቁርጥ ያለ መልስ አይኖረው ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ ምን ምላሽ እንደሚኖረው ማወቅ የምንችለው የእግዚአብሔር ነቢያት ምን እንደ ተናገሩ በመመልከት ቢሆንም፣ ከሁሉ በላይ ግን እግዚአብሔርን ያሳየንን ጌታ ኢየሱስን በመመልከት ነው፤ የእግዚአብሔርን መልክ በኢየሱስ ዐይተነዋልና፡፡ ታዲያ ጌታ ኢየሱስ ምን አደረገ? ለመከራ ምን ምላሽ ነበረው?

የምድር ኑሮ ብርቱ ሰልፍ ነው፡፡ ሰዎች ዕድሜአቸው ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በላይ ይደርስ በነበረበት በዚያ “የድንጋይ ዳቦ ዘመን” እንኳ ሰዎች ከዚህች “እግዚአብሔር ከረገማት ምድር” ማረፍን እጅግ ይናፍቁ ነበር (ዘፍ. 5፥29)፡፡ ሞትና ሥቃይ፣ ኀዘንና ልቅሶ የበዛባት ይህች ምድር መቼም የዕረፍት ስፍራ ሆና አታውቅም፡፡ ጌታ ኢየሱስም ሲወለድ ይኸው ነበር የገጠመው፡፡ በእርሱ መወለድ ብዙ ሕፃናት ሞቱ፤ የእርሱንም ነፍስ ለማትረፍ ቤተ ሰቦቹ በስደት አገር ለቅቀው መሄድ ነበረባቸው (ስደቱን የፈጸሙት ዛሬ በየዜና ማሰራጫው እንደምንከታተለው በእግር እና በጀልባ ይሆን?) (ማቴ. 2፥13-18)፡፡

ጌታችን አገልግሎቱን ሲጀምር ሰይጣን በቀላሉ ስኬትን የማግኘት ግብዣ አቅርቦለት ነበር፤ እርሱ ግን ግብዣውን ወዲያ ብሎ የመከራን መንገድ መርጧል (ማቴ. 4፥1-11)፡፡ በየቀኑ የሚገጥሙት ሰዎችም ግፍ፣ በሽታ፣ ኀዘን እና ሞት የደቆሳቸው ነበሩ፡፡ የኢዮብ “ወዳጆች” ኢዮብን ከማጽናናት ይልቅ ስለ መከራ አመጣጥ ለማስተንተን እንደ ሞከሩት ሁሉ፣ የጌታ ደቀ መዛሙርትም አንዳንድ ሰዎች ላይ ስለሚደርሰው መከራ መንሥኤ ማወቅ ይፈልጉ ነበር (ዮሐ. 9፥2)፤ እርሱ ግን አቋሙ ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ የመከራውን መንሥኤ ሲጠየቅ ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ በሽታ የደቆሰውን ሰው መፈወስና ማጽናናትን ይመርጣል፡፡

አንድ ጊዜ አንደ የታወቀ አገልጋይ መኪና ሲያሽከረክር በደረሰበት አደጋ ሲሞት፣ አብረውት የነበሩ የቤተ ሰቡ አባላት ላይም ከባድ አደጋ ደረሰ፡፡ በጊዜው ስለ አሟሟቱ ብዙ መላምቶች በአማኞች ይሰነዘሩ ጀመር፡፡ ለአንዳንዶቹ፣ አገልጋዩ በተሰጠው ጸጋ መታበይ ስለ ጀመረ ነው አደጋ የደረሰበት፤ ለሌሎች ደግሞ ጥፋቱ የተገልጋዩ ሕዝብ ነበር፤ ዐይናቸውን በአገልጋዩ ላይ ስላደረጉ እግዚአብሔር ለክብሩ ቀንቶ ወሰደው፡፡ አደጋው የደረሰው ከእርሱ ጋር አብረው በነበሩት የቤተ ሰቡ አባላትም ላይ ነበር፡፡ ታዲያ “ኀጢአቱ” የእርሱ ብቻ ነበር ወይስ አብረውት የነበሩ ቤተ ሰቦቹም ጭምር? ወይስ፣ “ለኀጥአን የወረደ ለጻድቃን ይተርፋል”?

አሳዛኙ ነገር ግን በአደጋው ወቅት አብሮ ያልነበረው ልጁ የነበረበት ሁኔታ ነው፡፡ በአደጋው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን የቤተ ሰቡን አባላት በማስታመም እና ከአባቱ ድንገተኛ ሞት ለመጽናናት በሚጥርበት ወቅት እነዚህ በክርስቲያኖች አንደበት ይነገሩ የነበሩ መላምቶች መጽናናትን ከባድ አድርገውበታል፡፡ የመኪና አደጋ በማንም ሰው ሊደርስ የሚችል ሆኖ ሳለ፣ ይህ ልጅም በዚህ አደጋ ከእግዚአብሔር ጋር የመሟገቱ አይቀሬነት እየታወቀ የየሰዉ ግዴለሽ አስተያየት ኀዘኑን የሚያብስ እንጂ የሚያጽናና አልነበረም፤ በተለይ የቅዱሳንን እገዛ በሚፈልግበት በዚያ ጊዜ! ከብዙ ጊዜ በኋላም ከዚህ ወጣት ጋር ጥቂት ጊዜ ሳሳልፍ በወቅቱ ወገኖች በሚሰነዝሩት መላምት ዛሬም ድረስ ምን ያህል እንደ ተጎዳ ለመረዳት አልከበደኝም፡፡

አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ሁሉ መንሥኤውን (ሰበቡን) ፈልገን አንችለውም፡፡ ሰዎች ላይ አደጋ የሚደርሰው ከሌሎች የበለጡ ኀጢአተኞች ስለሆኑ አይደለም፡፡ ጌታ ኢየሱስ የጅምላ አደጋና ሥቃይ መድረሱን ለነገሩት ሰዎች ይህንኑ ነው የመለሰላቸው (ሉቃ 13፥1-5)፡፡ መከራ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ እርምጃ በሚራመዱ ሰዎችም ላይ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ በመከራ የሚያልፉ ሰዎችን ማጽናናት ቀዳሚ ሥራችን መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ ሰዎች እግዚአብሔር ለምን ጣልቃ ገብቶ እንዳላዳናቸው በጥያቄ ተወጥረው በሚሠቃዩበት ጊዜ በቁስላቸው ላይ ጨው እንዳንነሰንስ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ መከራ ሰው አይመርጥም፤ ማንንም አይምርም፤ እግዚአብሔርም ጣልቃ ላይገባ ይችላል፡፡ በብሉይ ኪዳን የምናየው የኀዘን እንጉርጉሮ ብዛት እግዚአብሔር ሁልጊዜም በቀጥታ ጣልቃ እንደሚገባ እርግጠኛ እንዳንሆን ያደርገናል፡፡[4] ጣልቃ ገብቶ የሚታደግበት ጊዜ አለ፤ የማይገባበትም ጊዜ ሞልቶአል፡፡ ምክንያቱን የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሙሴ እንዳለው ምስጢሩ ለአምላካችን ነው (ዘዳ. 29፥29)፡፡

ሆኖም ጌታ ኢየሱስ ሲመጣ መከራ በሰው ልጆች ላይ የሚደርስበትን ምስጢር አልነገረንም፤ መከራንም አላስቀረም፡፡ ለምን? ይልቁኑ በመከራ የሚያልፉ ሰዎችን አብሮአቸው በመሆን፣ በማጽናናትና በመፈወስ የእግዚአብሔርን አብሮ ኋኚነትና ሰው ወዳድነት አጸናልን፡፡ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡ በሞት ጥላ መካከል ስንሄድ እርሱ አብሮን አለ (መዝ. 23፥4)፤ በእሳት ውስጥ ስንጣል አብሮ አለ (ዳን. 3፥19-27)፡፡ እግዚአብሔር ከምናልፍበት መከራ ሁሌ አያስጥለን ይሆናል፤ ሁሌም ግን አብሮን አለ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱን የሚሰውር አምላክ ነውና (ኢሳ. 45፥15) አብሮን መሆኑ አይታወቀን ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከመከረኞች ጋር አብረን ስንሆን፣ በሚያልፉበት ነገር ውስጥ አልታያቸው ያለውን እግዚአብሔርን ማሳየት እንችላለን፡፡

በተለይ በምድራችን እዚህም እዚያም እየተረጨ ያለው “የብልጽግና ወንጌል” የተሰኘው አስተምህሮ አማኝነት መከራ እንዳይደርስብን ዋስትና እንደሚሆነን ማስተማሩ ይህ ዐይነቱን አለመግባባት በመፍጠር ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ስለዚህ ሰዎች በሽታ ወይም ችግር ሲደርስባቸው እምነት እንደጎደላቸው ማሰብ ለብዙዎች ቀላል ነው፡፡ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ከማጽናናት እና በችግራቸው አብሮ ከመቸገር ይልቅ እምነትን በተግባር ያለ መለማመድ ምሳሌ ሲደረጉ ይታያል፡፡ ስለዚህ እነርሱም የአማኞች አብሮነት እጅግ በሚያስፈልጋቸው በችግራቸው ጊዜ ከአማኞች ለመሸሽ ይገደዳሉ፡፡ በችግር ጊዜ ደራሽና አጽናኝ መሆን የሚጠበቅባቸው አማኞች ችግርን አባባሽ ሆነው ያርፉታል፡፡ ለመሆኑ የኢዮብ “ወዳጆችስ” ከዚህ የተለየ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር ደጋግሞ “ጻድቅና ከክፋት የራቀ” በማለት የተናገረለትን ሰው እምነት እንዳጣና ኀጢአት እንደሚለማመድ ስለዚህም መከራው እንደ ደረሰበት መናገር ምን ይባላል? እግዚአብሔር መጨረሻ የገሠጸው ግን እነርሱን ነበር፡፡ ኢዮብን ለማጽናናት ቢመጡም ተጨማሪ ሥቃይ ፈጥረውበት ሄዱ፡፡

አማኞች በሰው የሚደርስ ችግር እንደማይደርስብን ዋስትና አልተሰጠንም፡፡ እንዲያውም መከራ ሲደርስ ሰዎች ከተደጋገፉ ችግሩ ይቀልላቸዋልና እንደ አማኝ ይህን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ጌታ ኢየሱስ በየትኛውም የመከራ ጕዳይ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ ፈውስና መጽናናትን ፍለጋ ወደ እርሱ የመጡ ሰዎችን “መጀመሪያውኑ ይህ የደረሰባችሁ እምነት ስለ ጎደላችሁ፣ አዎንታዊ ቃል ስላላወጃችሁ፣ ቅርጫት ውስጥ ገንዘብ ስላልወረወራችሁ፣ የተሰበከውን ቃል የራሳችሁ ስላላደረጋችሁ፣ የተደበቀ ኀጢአት ስላለባችሁ ነው” የሚል ትንታኔ አልሰጠም፡፡ መከራ የሰዎች የአርባ ቀን ዕድል በመሆኑ ዐይናቸውን ጨፍነው እንዲቀበሉትም አላግባባም፡፡[5]ጌታ ኢየሱስ ሲያደርግ የኖረው አንድ ነገር ነው፤ ወደ እርሱ የመጡትን ሕመምተኞች ሁሉ ፈወሳቸው፤ ያዘኑትንም አጽናናቸው፡፡ ወደ እርሱ ያልመጡትንም ወደ እነርሱ እየሄደ ተመሳሳይ ነገር አደረገ፡፡ ፍቅርን በተግባር አስተማረ፡፡ ለነገሩማ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምናገኘው እያንዳንዱ ስለ መከራ የሚያወራ ምንባብ ከመንሥኤው ይልቅ ለመከራው የሚኖረን ምላሽ ላይ የሚያተኲር ነው፡፡”[6] እኛስ ማንን መምሰል እንፈልጋለን?

በቅርቡ በኒውዚላንድ (አውስትራሊያ) ባለች “ክራይስት ቸርች” የተባለች ከተማ ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት ደርሶ ነበር፡፡ ሰዎች ሞተዋል፤ የቤተ ክርስቲያንን ሕንጻ ጨምሮ ንብረት ወድሟል፡፡ ዜናውን በቀረበባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ “በክርስቶስ ስም በተሰየመች ከተማ እንኳ ይህ ይደርሳል? ይህች ከተማ ከአደጋው ብትተርፍ ኖሮ ለወንጌል ምስክርነት መልካም አይሆንም ነበር?” ብዬ ዐስቤአለሁ፡፡ በእርግጥ የተለያየ አደጋ ተራፊዎች በየአጋጣሚው የሚያቀርቡልን ምስክርነት ከአደጋው በተአምር ስለ መዳናቸው በመሆኑ ሁሌም ተመሳሳይ ተአምር እንዲከሰት እንድንጠብቅ አድርገውናል፡፡ በየአደጋው የሚሞቱትስ ሰዎች እምነት ስለ ጎደላቸው ነው ወይስ ይበልጥ ኀጢአተኛ ስለ ሆኑ ነው ያልተረፉት?

ይህች ምድር የኖኅ አባት እንዳለው የተረገመች ምድር ናት (ዘፍ. 5፥29)፤ በኀጢአት ምክንያት እርግማን ደርሶባታል፡፡ ስለዚህ ብዙ ኀዘን፣ ብዙ እንባ፣ ብዙ ሥቃይ፣ ብዙ ጥያቄ አለባት፡፡ የምንወዳቸው ሰዎች ድንገት ይታመማሉ፤ አደጋ ይደርስባቸዋል፤ ይሞታሉ፤ የተፈጥሮ አደጋም በየቦታው ይደርሳል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረው ፍጥረት በመቃተትና በምጥ ተይዟል (ሮሜ 8፥22)፤ እኛም የፍጥረቱ አካል ነንና በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የምንኖረው፡፡ ይህች ምድር የኀዘን ስፍራ ናት፡፡ እዚህ በምንም ሁኔታ ውስጥ ከኀዘን ነጻ መሆን አይቻልም፡፡ ይልቁኑ ኀዘን የሌለባትን “አዲሲቷን ምድር” እየናፈቅን መኖሩ ነው የሚያዋጣን፡፡ ሞት አንድ ቀን ይሸነፋል፤ “የታባቱ ሞትም ይሙት”[7] ሲሉ መፎከር ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ ሞት የሚሸነፍበት ቀን መኖሩን ቅዱሱ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ ስለዚህ እርሱን ማወጅ ይበጃል፡፡

ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ እንዳደረገው ችግርና አደጋ ሲደርስ ለችግሩ ተጋላጮች መጸለይ ተገቢ ክርስቲያናዊ ኀላፊነት ነው፡፡ ከዚያ በላይ ግን ጌታም እንዳደረገው ፈጥነን መድረስና ማገዝ፣ ማጽናናት ይጠበቅብናል፡፡ ክርስቲያን በምንም ዐይነት አደጋ ውስጥ ለሚያልፉና በየትኛውም ቦታ በሚገኙ የአደጋ ሰለባዎች ፈጥኖ ደራሽ መሆን አለበት፡፡ ክርስቲያን ወደ ልቅሶና ኀዘን ቤት ለመድረስ መፍጠን አለበት፡፡ ክርስቲያን ከሚያለቅሱ ጋር ማልቀስ አለበት፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ነው፤ ጌታችን ሰዎችን ሲዳስስ እንጂ የችግሩን መግፍኤ ሲያብራራ አላየንምና!

በእርግጥ ወደ እግዚአብሔር መጮኽም እንችላለን፤ እግዚአብሔር በሕዝቡ ጒዳይ ግድየለሽ አይደለምና፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር በሕዝቡ ጭንቀት ይጨነቃል (ኢሳ. 63፥9)፤ መከራችን ያሳዝነዋል (ዮሐ. 11፥33-35)፡፡ መከራ ከሚቀበሉ እና ከሚሠቃዩ ጋር እግዚአብሔር አብሮ መኖሩንና አብሮ መከራ መቀበሉን አለመቀበልና እግዚአብሔርን የዳር (የሩቅ) ተመልካች ማድረግ ስድብ ነው፡፡[8]

እግዚአብሔር ግን የታሪክን መጋረጃ እስኪገልጥ ወይም ታሪክ እስከሚጠቀለልበትና ዘመኑ እስከሚዘጋበት ድረስ ሁኔታዎች አይለወጡ ይሆናል፡፡ ያኔ ግን በግልጥ ሁሉን እናያለን፡፡ እስከዚያው ድረስ በምድር ሁሌም ችግር ይኖራል! ሆኖም በሰዎች ላይ በሚደርሱ አደጋዎችና ችግሮች ላይ ተቃውሞአችንን መግለጽ እንችላለን፡፡ ግፍን መቃወም እንችላለን፤ ነቢያቱ ተቃውሞአቸውን እንደ ገለጡ፣ እኛም መቃወም እንችላለን፤ ክርስትና ግፍን ዐይተን እንዳላየ እንድናልፍ ምንም ዐይነት ፈቃድ አይሰጠንም፡፡ ለምሳሌ፣ የተፈጥሮ ሙቀት መጨመርና የአየር ብክለት ብዙ ጥፋቶችን እያደረሰ ነው፤ ሚዛናዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖሩና የኑሮ ውድነቱ ብዙ ድኾችንና ራብተኞችን እየፈጠረ ነው፤ የፍትሕ መታጣት የብዙ ስብራትና ኀዘን እርሾ ነው፤ ይህን መቃወም ክርስቲያናዊ ኀላፊነት ነው፡፡ እንዲያውም ይህን ማድረግ ያለባቸው አማንያን ናቸው፤ ምክንያቱም ሚሮስላቭ ዎልቭ እንዳለው “የዚህን ምድር ክፋት መቃወም የሚቻለው በመልካም አምላክ መኖር ካመኑ ብቻ ነው፤ አሊያ ተቃውሞው ትርጒም አይኖረውም፡፡”[9] 


[1]Lee Strobel, The Case for Faith: A Journalist Investigates the Toughest Objections to Christianity (Grand Rapids, Mi.: 2000)33.

[2] Lynn Anderson, Quoted in Lee Strobel, The Case for Faith: A Journalist Investigates the Toughest Objections to Christianity(Grand Rapids, Mi.: 2000)232.

[3]ሰለሞን ዴሬሳ፤ ልጅነት (አዲስ አበባ፤ 1962) ገጽ 7፡፡

[4] Philip Yancey, The Questions that Never Goes Away (London: Hodder, 2013) 69.

[5]ዝኒ ከማሁ፣ 47.

[6]ዝኒ ከማሁ፣ 36.

[7]ጸጋዬገ/መድህን፤እሳትወይአበባ (አዲስአበባ፣ 1966 ዓ.ም) ገጽ 123፡፡

[8]Jürgen Moltmann, The Crucified God: The Cross of Christ as the Foundation and Criticism of Christian Theology, trans. by R. A. Wilson and John Bowden (New York: Harper & Row, 1974), 274.

[9] Miroslav Wolf, Free of Charge: Giving and Forgiving in a Culture Stripped of Grace (Grand Rapids: Zondervan, 2005) 229 quoted in Yancey, Questions,105.

Share this article:

” ‘መንፈስ ቅዱስ ካልተናገረ እኔ የምነግራችሁ አንዳች የለም’ ብሎ ጉባኤውን ማሰናበት ጤናማነት ነው”

መጋቢ መስፍን ሙሉጌታ በኮልፌ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በመጋቢነት ያገለግላሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ዘወትር ዓርብ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታዘጋጀው “የፈውስና ነጻ የማውጣት” መርሓ ግብር ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህ ዘመን በፈውስ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ያገልግላሉ ከሚባሉት አገልጋዮች መካከል የመጋቢ መስፍን ስም ቀድሞ ይነሣል። ሕንጸት ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ስጦታዎቹ እና አጠቃቀሙ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው ስለሚነሡ ጉዳዮች ከመጋቢ መስፍን ሙሉጌታ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ውግዘቱና የተሰጠው ምላሽ

“እኔ ያልገባኝ በእነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ተጠቅሞ አያውቅም እያላችሁ ነው? እኔ ብዙ ሲሠራባቸው ስላየሁ አከብራቸዋለሁ፡፡ ምናልባት ትምህርት ሲያስተምሩ በሚመርጡት የአነጋገር ሥነ ሥርዐት፣ አንዳንዴም የእኔነት መንፈስ ሲታይባቸው እኔም በግሌ አይመቸኝም፡፡ ይህም ማለት ግን እግዚአብሔር በእነሱ የሚሠራውን ሥራ ያሳንሰዋል ማለት አይደለም፡፡ እርሱ መርጦ የሚጠቀምባቸውን እኛ ልናወግዝ ማን ነን? …”

ተጨማሪ ያንብቡ

መልካም ጅምሩ እንዳይደናቀፍ

የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.