[the_ad_group id=”107″]

የእግዜር ቅኔ

በጎችን ለመጠበቅ ውጪ ያደሩ ምስኪን እረኞች፣ የእንግዶች ማረፊያ ስፍራ አለመኖር እና የከብቶች በረት፣ የእግዚአብሔር መላእክት እና ሰብዓ ሰገል። እነዚህ በሁለቱ ወንጌላት ላይ ተሰባጥረው የተቀመጡ ትርክቶች፣ ይህ ወቅት በደረሰ ቁጥር ለረጅም ዓመታት የምሰማቸው እና የማነባቸው ቢሆኑም፣ ዘወትር የማይሰለቹኝ ምሥጢራትን የተሸከሙ ትዕይንቶች የተከታተሉባቸው ገቢራት ሆነው ይታዩኛል። ዓለማት ሁሉ የተፈጠሩበት “ቃል” እነሆ ሥጋ ሆነ! ግን፣ ግን ከተመልካች ሁሉ እረኞችን ለምን መረጠ? ከማረፊያ ስፍራ ሁሉ ለምን በከብቶች በረት ይህን ዓለም ተቀላቀለ?


እጅግ ዝቅ ብሎ …

በግሪኮ ሮም የአገዛዝ ሥርዐት በባርነት ቀንበር ሥር የነበረችው የይሁዳ ምድር በጀብድ ታሪክ በተሞሉት የነገሥታት መዋዕል እና የተስፋ ቃላት ባየሉባቸው የዳዊት መዝሙራት፣ የእግዚአብሔር ታምራት በሰፈረበት ቶራህ፣ ይልቁንም በሚያጽናኑ የነቢያት ቃላት ልባቸው በሚቃጠል ዜጎች የተሞላች ነበረች።

እጅግ ኀያል በሆነ ክንድ ከግብፅ ምድር ነጻ ስላወጣቸው አምላክ እየተማሩ ያደጉ ቢሆኑም፣ በእውነታው ግን የሮምን መራር አገዛዝ ተቀብለው እየኖሩ ነበሩ። ይህ እውነታ በውስጣቸው የፈጠረው ምሬት ተስፋን ወልዷል፤ ‘መሲሁ በሚመጣ ጊዜ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል’ የሚል!

እናም ማንም አይሁዳዊ መሲሁን በንጉሥ እልፍኝ እንጂ፣ በበረት ሊያይ አይወድም፤ ክርስቶስን በሊቀ ካህናቱ አልያም በልዑላን ሊታጀብ እንጂ በእረኞች እንዲከበብ አይመርጥም። ከረጅም ጊዜ አንሥቶ ስለ አካሉ ሳይሆን ስለ ጥላው ሲጨነቁ የኖሩ ካህናት ሳይቀሩ፣ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከኀጢአት ባርነት ነጻ ለማውጣት ስለመወለዱ ሳይሆን፣ ድፍን እስራኤልን ከጨቋኞች ነጻ ስለማውጣቱ ሲያስተምሩ ነው የኖሩት። ጥበቃቸው ልክ ይመስለኛል፤ በብሉይ  ስለ መሲሁ ነጻ አውጪነት ተተንብይዋል። ባለ ኪዳኖቹ ሕዝቦች ደግሞ ከዚህ በላይ ነጻነትን የሚሹበት ወቅት የለም።

እርሱ ግን እጅግ ዝቅ ብሎ፣ ራሱንም አዋርዶ ወደዚች ምድር መጣ። በተጠበቀበት ቦታ ሳይሆን፣ ባልታሰበበት አቅጣጫ፣ ይከብቡታል ተብለው በሚታሰቡ ታዳሚዎች ፊት ሳይሆን፣ በእረኞች መኻል የውልደቱ ብርሀን ታየ። አምላክ ሰው ሆነ! ፈጣሪ የፈጠረውን ሥጋ ሆነ። እኛን ከኀጢያት ባርነት ነጻ ሊያወጣ እርሱ በባሪያ አምሳል ተገኘ፤ ራሱን አዋረደ፤ ባዶ አደረገ።

የዘመን አጋሮቹ ከምድራዊ ባርነት ያላቅቃቸው ዘንድ ሲሹት፣ እርሱ ግን የሰው ልጅን ሁሉ ከኀጢአት ባርነት ይታደግ ዘንድ ወደ ምድር መጣ። እንደ ማንኛችንም ይህችን ዓለም አልቅሶ ተቀላቀለ፤ ሊያውም ምቾት በማይሰጥ ቦታ። እጣን እና ከርቤን በታጠኑ ክፍሎች ሳይሆን፣ ለአፍንጫ የሚሰነፍጥ የከብቶች ፅዳጅ በሞላበት ደብዛዛ በረት! ለምን? ለምን? ይህ ሁሌም በውስጤ የሚያቃጭል ጥያቄ ነው።

ባለቅኔው አምላክ

አምላኬን እንደ ባለ ቅኔ አየዋለሁ። ወደ ምድር በገባበት ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ ትዝብቴ ራሱን በምሳሌ ሲያስረዳን፣ በቅኔ ሲያዜምልን አደምጠዋለሁ። ጥላ እና አካል፣ ምሳሌ እና እውነታ፣ ትርክት እና ክስተት እያደረገ ሲያሻው አስቀድሞ ይመክረናል፤ ሲፈልግ ያለንበትን ያስረዳናል። እናም በእነዚህ ቀዝቃዛ እና ረጅም የገና ሌሊቶች ለምን ክርስቶስ በዚህ መልኩ እንደተቀላቀለን ሳስብ ይህ ባለ ቅኔው ጌታዬ ምናልባት ሊያስረዳኝ ያሰበውን ያገኘሁት መሰለኝ።

ከልቤ በላይ የማይመች በረት የቱ ነው? በኀጢአት ብዛትስ ከእኔ ልብ ይልቅ የከረፋ እና የቆሸሸ ደብዛዛ በረት ይኖር ይሆን? አይመስለኝም። ከእኔ በላይ የዓለም ጥበብ የማይገባው እና እጅግ የተናቀ “እረኛስ” ወዴት አለ? አዎን፤ ክርስቶስ ወደ ምድር በበረት ቢመጣም ከኀጢአት ባርነት ሊያድን የወደደው ግን እኔን ነው። ክርስቶስ ዳግም የተወለደበት መራሩ በረት የእኔ ማንነት መሆን አለበት! ባለ ቅኔው እርሱ ከሞቱ በኋላ “ዳግም” የሚወለድበትን በረት አስቀድሞ ሊነግረን ወደ ዓለም ዝቅ ብሎ መጣ። እናም ይህን የክፋት ሥር የሆነ ብርሃን የለሽ ልቤ በ“ገናው” ተወልዶበት፣ በ“ፋሲካው” ደግሞ ያጸዳው ይዟል። በዓለም ካሉ ውዳቂ ቦታዎች የመጨረሻ በሆነው ተወለደ፤ በዓለም እጅግ የተናቁትን ታዳሚዎቹ አደረገ። ታዲያ ይሄ በዓለም የተናቅን ከሆንነው ከእኛ እና በምድር ሁሉ ቆሻሻ ከሆነው ልባችን አይገናኝምን?

መልካም የልደት በዓል!

Wongel Alemayehu

Wongel is a banker residing in Addis Ababa. He is the author of a novel called "Ke'enkib sir". He attends at Gullele Meserete Kirstos Church.

Share this article:

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ክብር ነው

አማረ ታቦር፣ “Seeing and Savoring Jesus Christ” ከተሰኘው የመጋቢ ጆን ፓይፐር መጽሐፍ እየቀነጨበ የሚያቀርበውን ንባብ ሦስተኛ ክፍል እዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል። በዚህኛው የትርጉም ክፍል፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ መለኮትነት ሐተታ የተሰጠበት ሲሆን፣ ይህም መለኮታዊ ማንነት በስሞቹ መንጸባረቁን ያስቃኛል።


ተጨማሪ ያንብቡ

“ብቻህን ለመቆም ተዘጋጅ”

“እግዚአብሔር የሁላችን አምላክ መሆኑ ርግጥ ነው። ግና የሁላችን አምላክ የእኔ፣ የልቤ፣ የግሌ አምላክ እንዳይሆን ምን ይከለክለዋል? “እኛ” “እኔ”ን ያስቀራልን? “እኛ” የተሠራው ከ“እኔ” አይደለምን?” ጳውሎስ ፈቃዱ

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.