[the_ad_group id=”107″]

የኢየሱስ ትንሣኤ

የኢየሱስን ትንሣኤ ስናስብ፣ ወንጌሉንና ትሩፋቱ የሆነውን የሕይወትን ሽታ እናስባለን። በርግጥ ኢየሱስ በዮሐንስ 11 ከቍጥር 25-26 “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል” እንዳለ፣ በርሱ ሕይወት አለ። በዚህች ዐጭር ጽሑፍ ሁለት የትንሣኤውን ትሩፋቶች አወሳለሁ። ይህም በርሱ በማመን እንድንድን፣ ያመንነውም በዚሁ ተስፋ እንድንበረታና እንድንጸና ነው።

በከበረ ሰውነት እንነሣለን

በመጀመሪያ ሞት በትንሣኤው ድል ይነሳል። ስለ ትንሣኤ ከማውራታችን በፊት ግን ‘ሞት ምንድን ነው?’ ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። በብሉይ ኪዳን በአጠቃላይ ሞት በአሉታዊነቱ ነው ተጠቅሶ የምናገኘው። ይህን ከሥር ዘፍጥረት 3 እንዲሁም ዘፍጥረት 5 ላይ መመልከት እንችላለን። ደግሞም ያዕቆብ ከዮሴፍ ወደ ግብፅ ከሄደ በኋላ፣ “በኀዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ” ይላል (ዘፍጥረት 37፥35 አመት)። በዚህም የኀዘን ምልክት ሆኖ ቀርቧል። ይህንኑ ቃል ቢንያምም ወደ እስራኤል ባይመለስ ያዕቆብ የሚገጥመውን ኀዘን ለማስረዳት ተጠቅሞበታል። ይህም መልካም ያልሆነ ቦታ እንደ ሆነ እናያለን።

ኢዮብም ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ አልገለጸም፤ ይልቅ ሞትን መበስበስ እና ትቢያ እንደ መሆን ነው የቈጠረው። “ተስፋ የማደርገው ቤት መቃብር ብቻ ከሆነ፣ መኝታዬንም በጨለማ ካነጠፍሁ፣ መበስበስን፣ ‘አንተ አባቴ ነህ፤’ ትልንም፣ ‘አንቺ እናቴ’ ወይም ‘እኅቴ ነሽ’ ካልሁ፣ ታዲያ፣ የእኔ ተስፋ ወዴት ነው? ተስፋዬን የሚያይልኝስ ማን ነው? ወደ ሞት ደጅ ይወርዳልን? ዐብረንስ ወደ ትቢያ እንሄዳለንን?” (ኢዮብ 17፥13-16)።

መዝሙረኛውም ይህን የሞትን ጥልቀት እንዲህ ብሎ ይገልጸዋል፦ “ድንቅ ሥራህን ለሙታን ታሳያለህን? የሙታንስ መናፍስት ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? ምሕረትህ በመቃብር ውስጥ፣ ታማኝነትህስ እንጦርጦስ ይነገራልን?” መዝሙር 88፥10-11 (አመት)።  መዝሙረኛው ለሚጠይቀው ጥያቄ የሚጠበቀው መልስ፣ ‘አይኖርም’ የሚል ነው።

ስለዚህ በአጠቃላይ ሞት የሕይወት መቀጠልን አያሳይም። ሌስተር ገረብ እንዳለው፣ “በአብዛኛው የአይሁድ ጽሑፎች ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት የሚሉት የላቸውም። ሕይወት፣ ‘ሕይወት’ በሚባለው መልክ በሞት ያበቃል፤ ከሕይወት ቅርፊት ከመቃብር በኋላ ወይም በሺኦል ቢቀጥልም።”[1] ለዚህም ነው ወንጌሉ የምስራች የሆነው። መልካሙ ዜና ኢየሱስ ከሞተ ተነሣ፤ ስለዚህ እኛም ከሞት እንነሣለን፤ እንድናለን የሚል ነው።

ትንሣኤ’ ስንል አካላዊ ወይስ መንፈሳዊ?

በዘመናችን ካሉ ጥያቄዎች ውስጥ ‘አካላዊ ትንሣኤ አለ ወይ?’ የሚል ነው። አንዳንዶች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልስ፣ አካላዊ ትንሣኤ የለም፤ መንፈሳዊ ነው የሚል ነው። ከእነዚህ መካከል የቆሮንቶስ አማኞችም ወደዚህ ያጋደለ አቋም እንደ ነበራቸው ከ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 መረዳት እንችላለን። “ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ?” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥12 አመት)። ይህን ጥያቄ ጳውሎስ የጠየቀው፣ እንዲህ ዐይነት አለማመን በመካከላቸው ስለ ነበር ነው። ይህም በግሪካውያኑ መካከል በነበረው አስተሳሰብ፣ ነፍስ ቍሳዊ አካል ሳትሆን ኢምውታዊ ነች ከሚለው ጋር ተያያዥ ነው።

ጳውሎስ ግን የቆሮንቶሳውያኑን አለማመን ሙታን ካልተነሡ፣ ኢየሱስም አልተነሣም ማለት ነው ሲል ይሞግታል (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥13፡ 15፡ 16)። ከእነዚህ ክፍሎች በፊት ጳውሎስ በአጠቃላይ ሙግቱን የሚጀምረው በኢየሱስ ትንሣኤ ነው። እነዚህም ቍጥሮች ላይ ከቀረቡት ሙግቶች በተጨማሪ፣ በጽሑፉ አቀማመጥ የኢየሱስን ትንሣኤ በማስቀደም (ከቍጥር 1-11) እኛም የምንነሣው ኢየሱስ ስለ ተነሣ እንደ ሆነ ጳውሎስ ያበስራል።

ይህም የሚሆነው ኢየሱስ ሞትን ድል ስለ ነሳ ነው። እርሱ ሞትን ድል እንደነሳ፣ እኛም ሞትን ድል እንነሳለን፤ እርሱ ሞትን አሸንፎታልና። “ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥22 አመት)። በአዳም የነገሠው ክፉው ሞት በኢየሱስ እንደ ተሻረ ቍጥር 22 ያሳያል። አዳም ኀጢአት ከሠራ በኋላ እግዚአብሔር፣ “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ሲለው ትሞታለህ ማለቱ ነው። ይህንም በአጽንኦት የምንመለከተው በዘፍጥረት 5 ላይ “ሞተ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ስንመለከት ነው። ይህም በመጽሐፉ ላይ ባለው አወቃቀር፣ ማለትም ዘፍጥረት 3 ተከትሎ በመሆኑ፣ ደግሞም ከአዳም ታሪክ ስለሚጀምር በአዳም ላይ የደረሰው ሞት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ እንደደረሰ እናያለን። በምዕራፍ 5 ላይ ያለው ሞት አካላዊ ሞት እንደ ሆነ እሙን ነው።

ስለዚህ፣ ኢየሱስ በአካል ስለ ተነሣ እኛም በአካል እንነሣለን። በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቍጥር 1 ላይ የቆሮንቶስ ሰዎች የኢየሱስን በአካል መነሣት እንደተቀበሉ እናያለን። ኢየሱስ ሞቶ ተነሥቷል። ትንሣኤው በአካል ስለ ሆነ፣ ‘በአካል ታየ’ የሚለው በተደጋጋሚ በዚሁ ደብዳቤ ምዕራፍ 15 ከቍጥር 1-8 ተጽፎ የሚገኝ ነው። ይህም ሞት ድል መነሣቱን አመልካች ነው። ኢየሱስ ከሞት በአካል ስለ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ እንነሣለን የሚለውንም ሙግት አንድ ላይ ያቀርባል። ኢየሱስ ከሙታን በመነሣት በኵር ሆኗልና እኛም በእርሱ አምሳያ በአካል እንደምነሣ ጠቋሚ ነው።

እንግዲህ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሣው በቍጥር 40 ላይ ‘ሰማያዊ አካል’፣ በቍጥር 44 ደግሞ ‘መንፈሳዊ አካል’ የሚለው ነው። ሆኖም  ይህንም ቢሆን ጳውሎስ በቍጥር 42-43  አብራርቶታል። “ የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል”፤ ደግሞም በቍጥር 54 “የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ ‘ሞት በድል ተዋጠ’ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።” ይላል። ይህም መንፈሳዊና አካላዊ የሚለው፣ አካል የሌለውን ትንሣኤ ሳይሆን፣ የማይበሰብስ፣ የከበረ፣ በኀይል የተሞላ፣ ድካም የሌለበት፣ የማይሞት ነው፤ በሌላ አነጋገር የሰው ድካም የሌለበት ‘ሰውነት’ እንደ ሆነ ያሳያል።

በአዳም የወደቀው ፍጥረት ይዋጃል

በትንሣኤ የእኛ ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን፣ ፍጥረትም ከባርነት ይዋጃል። የቅዱሳን ትንሣኤም ከፍጥረት መዋጀት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ከሮሜ 8 መረዳት እንችላለን። በአንድ ዐውድ ውስጥ ይህ መቀመጡ ለዚህ አስረጅ ነው። ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል።” (ሮሜ 8፥19 አመት) ካለ በኋላ ስለ ፍጥረት መዋጀት መናገሩን ልብ ይሏል።

አንዳንድ ሰዎች የአፍላጦንን ፍልስፍናዊ ዕሳቤ በአኗኗር ዘይቤያቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሥነ መለኮታቸው ውስጥም ያንፀባርቃሉ። ስለዚህም የሰው ልጆች መፍትሔ መሆን አይችሉም። በዓለም የሚፈጸምን የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳይሆን ከዓለም ነጥቆ የሚወስድን መንግሥት ይሰብካሉ። ይህም ኀይል የሌለውን አምላክ ያስታውሰኛል። ነገር ግን፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና ከዘፍጥረት 1 የጀመረው ታሪክ በራእይ 21 እና 22 ይፈጸማል። እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ ጥሎ የሄደ ወይም በታሪክ ውስጥ ራሱን ያልገለጠ አምላክ ሳይሆን፣ ታሪክንም የሚጠቀልል አምላክ ነው። በራእይ 21፥1-3 እንዲሁም በቍጥር 22 አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር፣ አዲሲቱም ኢየሩሳሌም ስትወርድ፣ እግዚአብሔርም በምድር  እንደሚሆን ይናገራል እንባችን ታብሶ፣ ኀዘናችን ልቅሷችንና ስቃያችን እንደሚሻር፣ ክፋት እንደሚወገድ ይገልጻል። የዚህም ምክንያቱ የኢየሱስ ሞት፣ ትንሣኤና ዳግም ምፅአት ነው።

2ኛ ቆሮንቶስ 5 እንደሚያሳየው፣ ከሞት በኋላ የምንሄድበት ቦታ ሊኖር ይችላል። ይህም ሆኖ ያለ ቅድመ ዕሳቤ በዘመናችን ካሰብናቸው፣ ከሞት በኋላ ከዓለም ውጭ ያለ መኖሪያ በአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም። ቶም ራይት የተባለ የሥነ መለኮት አስተማሪ እንደሚለው፣ ከሞት በኋላ ሕይወት ይጠብቀናል።

መጀመሪያ የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ይሞላል፤ መንግሥቱ ትመጣለች። ቤተ መቅደሱን መንግሥቱን፣ ንግሥናውን ጠቅልሎ የያዘው ንጉሥ ስላለን ይህ ይሆናል። እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ሰው መሆን፣ ሞት እና ትንሣኤ መንግሥቱ መጥታለች፤ ደግሞም ፍጻሜዋን ታገኛለች። ነገር ግን፣ ይህች መንግሥቱ ከቤተ መቅደሱ የተለየች አይደለችም። እንዴት ይህ እንደ ሆነ ላብራራ።

አንዳንድ ምሁራን አዳምና ሄዋን የነበሩበትን ገነት እንደ ቤተ መቅደሱ ይቈጥራሉ። በርግጥ ይህ አሳማኝ ዐሳብ ነው። ቤተ መቅደሱ እግዚአብሔር የሚያድርበት እንደ መሆኑ፣ እግዚአብሔርም ከአዳምና ከሄዋን ጋር እንደ መኖሩ ምድርን ቤተ መቅደሱ ብሎ መጥራቱ ትክክል ነው። እስራኤላውያንም ቤተ መቅደሱን ሲሠሩ የእግዚአብሔር ማደሪያ እንዲሆን ነበር፤ ቤተ መቅደሱ ግን ፈረሰ።

ነገር ግን፣ ልብ ልንለው የሚገባን፣ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን።” (ዮሐንስ 1፥14 አመት) ሲል፣ በገነት የነበረው ቤተ መቅደስ፣ በእስራኤላውያን መካከል የነበረው ቤተ መቅደስ አምላክ በሆነው በኢየሱስ በመካከላችን ማደሩ ነው። “ዐደረ” የሚለው ቃል፣ የክብርን ማደር ወይንም ካቦድ አመላካች ነው። ይህም የቤተ መቅደስ ቋንቋ ነው። ደግሞም ኢየሱስ ራሱን ቤተ መቅደሱ እንደ ሆነ ገልጧል (ዮሐንስ ወንጌል 2፥18-21)።

ስለዚህ ቤተ መቅደሱ በኢየሱስ በመካከላችን በምድር እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን። የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት በተለያየ ቦታ ኢየሱስ ሲናገር (ማቴዎስ 12፤ ሉቃስ 17) ይህንኑ ያሳያል። መንግሥቱም የመጣችው በንጉሡም፣ በሊቀ ካህኑም በኢየሱስ ስለ ሆነ በሁለቱም ልዩነትን ማድረግ አይገባም።

መንግሥቱም ፍጻሜ የሚያገኘው፣ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል።” (ራእይ 21፥3 አመት) የሚለው ቃል ሲፈጸም ነው። ደግሞም በራእይ 21፥22 በከተማይቱ ቤተ መቅደስ እንደማይኖር ይናገራል። ይህም የሚሆነው የእግዚአብሔር መገኘት በሙላት ስለሚሆን ነው።

ከዚህ መላው ምድር የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደምትሆን፣ ይህም ቤተ መቅደሱ በመካከላችን እንደሆነው ከላይ እንዳሳየሁት ሁሉ፣ መንግሥቱም በመካከላችን በሙላት እንደሚሆን አመላካች ነው። ደግሞም በመንግሥቱና በቤተ መቅደሱ መካከል ልዩነት የለም። ራእይ 21፥22ም ቤተ መቅደሱ በሙላት በምድር እንደሚሆን ያሳያል። መንግሥቱንም እንጠባበቃለን የሚለውም የዚህ መገለጫ ነው።

የኢየሱስም መምጣት ከመንፈሱ መምጣት ጋር የተያያዘ ነው። በራእይ 22፥1 እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ መስተዋት የጠራውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤” ታዲያ ይህ የሕይወት ውሃ ምን ማለት ነው? በዮሐንስ 4፥10 እና በዮሐንስ 7፥37 ላይ ይህ የሕይወት ውሃ ተጠቅሷል። ኢየሱስ በዮሐንስ 7፥37 እንደተጠቀሰው እንዲህ አለ፣ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤” (ዮሐንስ 7፥37 አመት)። ይህን ከማለቱ በፊት እርሱ ክርስቶስ መሆኑን እና ስለ ሥራው (ሞቱና ትንሣኤው) በቍጥር 25-36 አስተምሯቸዋል። የሕይወት ውሃ ሊል የፈለገው ምን እንደ ሆነ በቍጥር 38 ላይ ተገልጿል፤ በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናግሯል፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልተሰጠም ነበርና። ስለዚህ፣ በራእይ 22፥1 ላይ ያለው ስለ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት ነው ብለን መደምደም እንችላለን።

ይህም ኤደንን በሚያመላክት መንገድ ምድርን የሚያረሰርስ እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን፤ ምክንያቱም፣ “ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ” (ራእይ 22፥2 አመት)። ይህ ቃል ከዘፍጥረት 2፥10 ጋር ተመሳሳይነት አለው። “የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከኤድን ይፈስስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር” (ዘፍጥረት 2፥10 አመት)። ስለዚህም ኤደንን የሚያረሰርስ እንደ ሆነ መገንዘብ እንችላለን። ከዚህም በኤደን የሆነው የፍጥረት መውደቅ (ዘፍጥረት 3) በሮሜ 8፥18-25፣ ራእይ 21፥1፡ 4 እንደተጻፈው እንደሚዋጅ ማየት እንችላለን። ይህንም በደንብ ገልጾ የሚያሳየው ሮሜ 8፥18-22 ነው።

ስለዚህ በኢየሱስ ትንሣኤ እና ዳግም ምፅአት ፍጥረት ይዋጃል እንጂ አይጠፋም። መንግሥቱና ቤተ መቅደሱ በኀይል በኢየሱስ መጥታለች! ንጉሡም ሊቀ ካህኑም በሰማይና በምድር ሥልጣን ተሰጥቶኛል ያለው ኢየሱስ ነው። ታላቁ ተስፋችንም ይህ ንጉሥ ወደ ምድር መምጣቱ፣ መንግሥቱም በሙላት መሆኗ የክፋት መንገድና የፍጥረት መዋጀት ነው እንጂ፣ የእኛ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አይደለም። ኢየሱስ እንደተባለው ከማሪያም ተወለደ፣ ሞተ፣ ተነሣ። ይህም በብሉይ ኪዳን ነቢያት እንደተባለው ሆነ። ስለዚህም እንዳለው ተመልሶ እንደሚመጣ ርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ታዲያ እንዴት እንኑር?

  1. ለጌታ በትጋት እንኑር

በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ከቍጥር 29 ጀምሮ ጳውሎስ መከራን መቀበል ገሸሽ የማይለው የትንሣኤ ተስፋ ስላለው እንደ ሆነ ይነግራቸዋል። አሰቃቂ መከራንም ተቀብሎ ቆሮንቶሳውያኑም በትጋት እንዲኖሩ እንዲህ ሲል ያሳስባቸዋል፣ “ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥58 አመት)። ይህ ማሳሰቢያ ለእኛም ጭምር ነው። በኢየሱስ ትንሣኤ ስላለን በትጋት መኖር ይሁንልን።

  • የፍጥረት እንደ ራሴዎች በመሆን እንኑር

ብርሃንና ጨው በመሆን በፍትሕና በሰላም እንኑር። ፍጥረትን እንደ እግዚአብሔር አምሳል እንንከባከብ። ፍጥረት እንደሚጠፋ ሳይሆን እንደሚዋጅ፣ እንደ መልካም ነገር እንንከባከብ። እንደ መልካም ካህናት በሕይወታችን ሁሉ እግዚአብሔርን እናክብር። “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ።” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥9 አመት) ተብለናልና!


[1]  Grabbe, An Introduction to First Century Judaism, 78; compare Bauckham, “Life, Death, and the Afterlife”, 80.

Share this article:

የዘመነ ዜማ ለዘመናት ንጉሥ – ዜማ ለክርስቶስ

ከ1960ዎቹ የሙሉ ወንጌል ሀ መዘምራን እስከ ዜማ ለክርስቶስ ህብረት፣ በአንድ እጅ ጣት ከሚቆጠሩ ዝማሬዎች እስከ አለንበት ዘመን የዝማሬ ጎርፍ፣ ከለሆሳስ የጓዳ ዝማሬ እስከ አደባባይ ሆታ፣ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ዘማሪያን እስከ ወጣት ዘማሪያን . . . ይህ የኢትዮጵያ ቤ/ክ የዝማሬ ታሪክ ነው፡፡ መዝሙር ተቀዛቅዟል የለም አድጓል የሚለውን ሙግት የሻረ አዲስ የዝማሬ መንፈስ፣ ሁሉንም የሚያስማማ አቀራረብ፣ የተዋጣለትና የተሟላ ዝማሬ እነሆ ከወጣት ዘማሪያን ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ተብርክቷል፤ ከዜማ ለክርስቶስ፡፡ ወጣትነታቸውን፣ ጉብዝናቸውንና ችሎታቸውን ሁሉ ለጌታ የሰው ወጣቶች የሰጠኸንን አንሆ ብለው ለዘመናት ንጉስ ከልብ የሆነ ሕያው ዝማሬ ተቀኝተዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ትጥቅ አስፈቺው ኢየሱስ!

ናኦል በፈቃዱ፣ የሰሞኑ መነጋገሪያ ከሆነው ትጥቅ የመፍታትና አለመፍታት ፖለቲካዊ ውዝግብ ባሻገር፣ ሌላ ትጥቅ አስፈቺ እንዳለ ያስታውሰናል። ክርስቲያኖችም የትጥቅ ትግል እንዴት ሊያዩት እንደሚገባም ሐሳብ ያቀብላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

A fine Facebook embed example, this is

Proactively deploy backward-compatible catalysts for change rather than maintainable channels. Seamlessly create cost effective infrastructures via frictionless process improvements. Phosfluorescently target effective convergence vis-a-vis mission-critical

ተጨማሪ ያንብቡ

2 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.