[the_ad_group id=”107″]

ትጥቅ አስፈቺው ኢየሱስ!

ሰሞነኛው ወሬ ደግሞ ትጥቅን ስለ መፍታት እና ስላለመፍታት ነው። ከትግል መልስ በሰላም ለመፎካከር ወደ አገር ከተመለሱት ፓርቲዎች መካከል የአንደኛው ፓርቲ ሊቀ መንበር፣ በቅርቡ በሚድያ ፓርቲያቸው ትጥቁን እንደማይፈታና ጉዳዩ “sensitive” እንደ ሆነ ተናግረዋል። የኢፌዴሪ መንግሥትም ለዚህ አጸፋዊ ምላሹን ከማስጠንቀቂያ ጋር መስጠቱን የዜና አውታሮች አሰምተውናል። ሆኖም አሁንም ከፓርቲው የሚወጡ ዜናዎች ትጥቅ እንደማይፈታ የሚገልጹ ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚኖሩ ታጣቂዎችም ትጥቆቻቸውን እንዳልፈቱ ይነገራል። 


በርግጥም ትጥቅ መፍታት “sensitive” ጉዳይ ነው። ትጥቅ ፈቺ ካለ ትጥቅ አስፈቺ የመኖሩ ሁኔታም እንደተባለው በቀላሉ የሚዋጥ ጉዳይ አይደለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን “sensitive” ጉዳይ እስከ መጨረሻው ዕልባት በመስጠት ደቀ መዛሙርቱን ትጥቅ አስፈትቷቸዋል። እርሱ ትጥቅ አስፈቺ ሆኖ ተከታዮቹ ትጥቃቸውን ፈትተው እንዲከተሉት ግድ ብሏቸዋል። ክርስቲያን ትጥቁን የፈታ የክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር ነው።


ስሙም … የሰላም ልዑል ይባላል” ኢሳ 9፥6 (አ.መ.ት)


ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንቢት ከተሰጡት ስያሜዎች አንዱ “የሰላም አለቃ (ልዑል)” የሚለው ይገኝበታል። ይህም ሊመጣ ያለው መሲህ የሰላም ባለቤት፣ የሰላም አለቃ፣ የሰላም ፈጣሪ እና ራሱ ሰላም እንደ ሆነ ለይሁዳ ሕዝብ በነቢዩ ኢሳያስ በኩል የተሰጠ ትልቅ ተስፋ ነበር።

ታዲያ የሮም ግዛት (Roman Empire) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ27 ዓመተ ዓለም በአውግስጦስ ቄሳር አማካይነት ሲመሠረት “ፓክስ ሮማና” ወይም “ሰላም በሮም ግዛት” የሚል የ“ሰላም” ስብከትን ይዞ ነበር። በ“ፓክስ ሮማና” ዘመን የሰላም ልዑል የሆነው የተጠበቀው መሲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ። እርሱ ከ“ፓክስ ሮማና” የሚበልጥ ሰላምን ሰበከ።

የአውግስጦስ ቄሳርን የ“ሰላም” ስብከት እና የክርስቶስን የሰላም ልዕልና የሚለየው ታዲያ፣ አውግስጦስ ቄሳር በጦር እና በጠመንጃ የመጣ ሰላምን ሲሰብክ፣ ክርስቶስ ደግሞ ተከታዮቹን ትጥቅ አስፈትቶ፣ ዕርቅን ሰብኮ፣ መሥዋዕት ሆኖ ሰላምን የሰበከ የሰላም አራማጅ፣ የሰላም አብዮተኛ ነበር።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በርግጥም በምድር በኖረበት ጊዜ ሁሉ የሰበከው እና ያስተማረው፣ ደግሞም ደቀ መዛሙርቱን ያዘዘው ሰላማዊ ስለመሆንና ትጥቅን ስለ መፍታት ነበር። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በወንጌላቱ የሰፈሩት ንግግሮቹም ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው፡-

ዐይን ስለ ዐይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ… ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ አዙርለት” ማቴ 5፥38-39

ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ” ማቴ 5፥44

በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዙ በሰይፍ ይጠፋሉ።” ማቴ 26፥52

ሰላምን የሚያወርዱ ብጹዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።” ማቴ 5፥9


ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ትጥቅ አስፈትቷቸዋል!

በ6ኛው ዓ.ም. “የገሊላው ይሁዳ” የሚባል ግለ ሰብ የሮማውያንን ቀረጥ በመቃወም በሮም ላይ ዐመፅ አስነሥቶ፣ በዚህም ብዙ ተከታዮችን አስታጥቆ ነበር። ይህንን ግለ ሰብ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ፈሪሳዊው ሊቅ፣ ገማልያል ሲጠቅሰው እናነብባለን (የሐሥ 5፥37)። “የገሊላው ይሁዳ” ታሪክ የከሸፈ መሲህነት ታሪክ በመባል ይታወቃል።


ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ ናዝሬት በምትባል ከተማ ሲወለድ፣ ከገሊላ “የከሸፈው መሲህ” ታሪክ ገና አልበረደም ነበር። ለዚህም ይመስላል ናትናኤል “መሲሁን [ክርስቶስን] አገኘነው” ሲሉት፣ “ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?” (ዮሐ 1፥45-46) ሲል የጠየቀው። ከገሊላ አውራጃ በርግጥ የከሸፈው “የገሊላው ይሁዳ” መሲህነት ሌላ ሰው ይነሣል ብለው እንዳያስቡ ተስፋ አስቆርጧቸው ነበር።


ጌታ ኢየሱስ ይህ ክሽፈት ከተወራበት አውራጃ ተወለደ። የኢየሱስ መንገድ ግን የክሽፈት መንገድ አልነበረም፤ መሲህነቱም እንዲሁ። ሐዋርያቱ ኋላ እንደሰበኩትም ኢየሱስ በርግጥ እርሱ ክርሰቶስ/መሲህ ነበር (የሐሥ 5፥42)! ይህ መሲህ ጦር ስላነሣና ተከታዮቹን ስላስታጠቀ ሳይሆን፣ ሰላምን ስለ ሰበከ እና “ሰይፍህን መልስ” (ማቴ 26፥52) ብሎ የደቀ መዛመርቱን ትጥቅ ስላስፈታ መሲህ ሆኖ፣ አሸንፎ በክብር ታየ!

 የኢየሱስ መንገድ ግን የክሽፈት መንገድ አልነበረም፤


የሰላሙ ልዑል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ብሔርተኝነት (Jewish Nationalism) ተነሣሽነት ለብዙ ዘመን ከገዢዎቻቸው ጋር ጦር ሲማዘዙ ከነበሩ እና ጥላቻ ሲሰበካቸው ከኖሩ ማኅበረ ሰብ 12 ሐዋርያትን መረጠ። ከእርሱ ቀደም እንደነበሩት፣ እንደ የገሊላው ይሁዳ እና ቴዎዳስ (የሐሥ 5፥36-37) ሳይሆን፣ ተከታዮቹን ሳያስታጥቅ “ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ አዙርለት” (ማቴ 5፥38-39) እያለ ዓለምን በፍቅር እንዴት መማረክ እንደሚችሉ አስተማረ።

 

ኢየሱስ ለምን ተከታዩቹን ትጥቅ አስፈታቸው?

‘ፍትሕ በሌለበት እና ክፋት በሞላበት ዓለም፣ ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለምን ትጥቅ እንዲፈቱ እና ሰላማዊ እንዲሆኑ አስገደዳቸው?’ ብለን መጠየቃችን ትክክል ነው። በዚህ ዘመን ላለንም ክርስቲያኖች ጌታችን ከዚህ የተለየ ትዕዛዝ የለውም። “ትጥቃችሁን ፍቱ! እኔን ምሰሉ!” እንደሚለን አምናለሁ። ግን ለምን? ለምንድነው እንዲህ በቃሉ አማካይነት ሰላማውያን እንድንሆንና ከጦር መሣሪያ ራሳችንን እንድናርቅ የሚያስገድደን?

‘ፍትሕ በሌለበት እና ክፋት በሞላበት ዓለም፣ ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለምን ትጥቅ እንዲፈቱ እና ሰላማዊ እንዲሆኑ አስገደዳቸው?’


1. ኢየሱስ ራሱ ሰላም ስለ ሆነ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ሰላማችን” (ኤፌ 2፥14) ደግሞም “የሰላም ልዑል” (ኢሳ 9፥6) ይለዋል። ‘መጽሐፍ ቅዱሰን አምኛለሁ፤ ክርስቶስን ተቀብያለሁ’ የሚል ክርስቲያን ክርስቶስ ሰላም እንደ ሆነ እንዲያምን ይገደዳል። ክርስቶስ ሰላም ከሆነ ክርስቶስን መስበክ ሰላምን መስበክ ማለት ነው። እውነተኛ ሰላም ደግሞ ከትጥቅ ጋር አይሰበክም። እውነተኛ ሰላም ከፍቅር እና መሥዋዕትነት ጋር የሚሰበክ ነው። ስለሆነም ኢየሱስ ሰላም መሆኑ እኛም የሰላም ሰባኪዎች መሆናችን ትጥቃችንን ፈተን እንድንከተለው ያስገድደናል።


2. ኢየሱስ ራሱ ሰላማዊ ስለ ሆነ፡- ጌታችን ኢየሱስ “ሰላም” ብቻ ሳይሆን ሰላማዊም ነበር፤ እንቅስቃሴውም ሆነ አስተምህሮው ፍጹም ሰላማዊ ነበር። ጌታችን ኢየሱስ እንቅሰቃሴው አንድም ጊዜ የሕዝብን ሰላም በጠመንጃ ሲያውክ አንመለከተውም፤ በንግግሩም ለጦርነት የሚያነሣሣ ንግግርን ሲያደርግ አናየውም። ስብከቱም ኑሮውም የሚናገረው ኢየሱስ ሰላማዊ እንደ ሆነ ብቻ ነው። ስብከቱ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ”፣ ተግባሩም ለተፉበት እና ለሰቀሉት “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እያለ እንጂ፣ ሰይፍን እያማዘዘ አልነበረም። ክርሰቲያን ዛሬ ሰላማዊ መሆን አለበት፤ ደግሞም ትጥቁን መፍታት አለበት ምክንያቱም ክርስቶስ ሰላማዊ ስለ ነበረ።


3. በቀል የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፡- ሰላማዊነት ከመሥዋዕትነት ጋር እንደሚመጣ የታወቀ ነው። የክርስቶስ ሰላማዊ አካሄድ መሰቀልን ነው ያተረፈለት። የቅዱሳን ሐዋርያቱ ሰላማዊ አካሄድ ሰማዕትነት ነው ያስገኘላቸው። ለጊዜው በርግጥ የተሸነፉ ይመስላል፣ ነገር ግን ክርስቶስም ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል፤ ደግሞም የወጉት እያዩ ዳግም ይመለሳል። ደቀ መዛሙርቱም በሰማዕትነት ደማቸው እኛን አስገኝቷል፤ ፍሬያቸው በዝቷል። በመጨረሻው ቀን እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ይበቀልላቸዋል (ራዕ 15፥4-6)።

ዛሬም ከልቡ ለተከተለው ኢየሱስ ትጥቅ አስፈቺ ነው።


4. የኢየሱስ መንገድ አሸናፊ ስለ ሆነ፡- አርስታይደስ የተባለ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ክርስቲያን በዚያ ዘመን ስለ ነበሩት ክርስቲያኖች ሲናገር፣ “ክርስቲያኖች ራሳቸው ላይ እንዲደረግባቸው የማይፈልጉትን ነገር ሌሎች ሰዎች ላይ አያደርጉም ነበር። ጨቋኞቻቸውን ያጽናናሉ፤ ደግሞም ጓደኞቻቸው ያደግርጓቸዋል። ለጠላቶቻቸውም መልካምን ያደርጋሉ። ለጨቋኞቻቸው ከሚያሳዩአቸው ፍቅር የተነሣ ጨቋኞቻቸው ክርስቲያን ለመሆን ይገደዳሉ።” (The Apology of Aristides 15) ክርስትና በመጨረሻም ያለ ጠመንጃ ሮምን አሸንፏል። የኢየሱስ መንገድ ለጊዜው አይምሰል እንጂ፣ ማሸነፉ አይቀርም። ትጥቅ ፈትቶ ሰላማዊ አካሄድ መሄድ ለጊዜው ዋጋ ያስከፍል እንጂ፣ በመጨረሻ ግን ድልን መቀዳጀቱ አይቀርም።


ፈረንሳዊው የጦር መሪ ናፖሊዩን ቦናባርቴ በአንድ ወቅት ስለ ክርስቶስ ሲናገር፣ “ታላቁ እስክንድሮስ፣ ቄሳር፣ ቻርላማኝ እና እኔ ትላልቅ መንግሥታትን መሥርተናል። የእኛ ክኅሎት ግን በምን ላይ ነበር የተመሠረተው? በኀይል ላይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መንግሥቱን በፍቅር ላይ መሠረተ፤ በዚህ ሰዓት ሚልዮኖች ስለ ስሙ ይሞቱለታል!” ኢየሱስ ሚልዮኖችን ያሸነፈው በፍቅሩ ነው።


በጦር ኀይላቸው ብዙዎችን ያሰለፉት እነ አውግስጦስ ቄሳር፣ ናፖሊዩን፣ ታላቁ እስክንድሮስ፣ ቻርላማኝ ወዘተ. ዛሬ የሉም፤ አልፈዋል። ትጥቅ አስፈትቶ ሰላምን የሰበከው ኢየሱስ ግን ዛሬም ሰላም ነው፤ ዛሬም መንግሥቱ የጸና ደግሞም የሰላም ነው። ዛሬም ልጆቹ ሰላማውያን የሰላምም ሰባኪያን ናቸው። ዛሬም ከልቡ ለተከተለው ኢየሱስ ትጠቅ አስፈቺ ነው። አዎን፤ ለክርስቲያኖች የትጥቅ ጉዳይ “sensitive” ጉዳይ አይደለም። ትጥቅ አስፈቺው ኢየሱስ ሲሆን፣ ትጥቅ ፈቺዎቹ ደግሞ ወድደው የተከተሉት ክርስቲያኖች ናቸው።

Share this article:

ከመደመር ማግስት የግድ ሊታወቁ የሚገባቸው ሁኔታዎች

ከተራዛሚ ግጭቶችና ቍርቍሶች ለመውጣት ብዙ አገሮች ድኅረ ግጭት የሰላም ግንባታ ትግሎችን አካሂደዋል፤ እያካሄዱም ይገኛሉ። ማኅበረ ሰብ ፊትና ጀርባ ሆኖ ከቆየባቸው የተራዘሙ ግጭቶች ወጥቶ፣ አንዲትን በራእይ የተጣጣመች አገር መልሶ መገንባት “መደመር” ከሚለው ቃል ጋር ሳይጋጭ፣ ነገር ግን ከዚያ በዘለለ መልኩ በርካታ የሰላም ግንባታ ሒደት ያለበት ውስብስብና ተከታታይ ተግባራትን ይጠይቃል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ዛሬ ያልተመቸን ሕዝቦች

ኢትዮጵያውያን በቀድሞው ዘመን ናፋቂነት የዛሬውን ዕድል እያባከንን እንደ ሆነ፣ ተካልኝ ነጋ (ፒ.ኤች.ዲ) በዚህ መጣጥፉ ይሞግታል። በተለይም በትላንት ናፍቆት ውስጥ ስለ “ጀግኖቻችን” ያለን ምልከታ፣ የዛሬውን አብሮ ነዋሪ ወንድማችንን እንዳይጎዳውም ያሳስበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.