[the_ad_group id=”107″]

ኢየሱስ ጥያቄ፤ ኢየሱስ መልስ

ሕንጸት ከልደት (ገና) በዓል በፊት ቀጣዩ ቅጿ እንደማይደርስ በማሰብ ዛሬውኑ “እንኳን አደረሳችሁ” ማለቴ የወግ ነው። ከመልካም ምኞት መግለጫዬ በላይ ግን የክብረ በዓሉን ምክንያት በዚህ መልኩ ብናየው በማለት ይህችን ከትቤአለሁ። ጥያቄና መልስ።

ሰው ኾነን በመፈጠራችን እናስባለንና ዘወትር በጥያቄዎችና መልሶች መካከል የምንመላለስ ፍጥረት ነን። ከእንስሳት ከለዩን ጠባያት መካከል አንደኛው ይኸው ነው፤ እናስባለን። ስለምናስብም እንጠይቃለን። የዘመናዊ ፍልስፍና አባት የሚሉት ሬኔ ዴካርት “ኑባሬዬ በማሰቤ የተገናዘበ ነው”[1] ይላል። ማሰብ እስካለ ድረስ መጠየቅ ይኖራል። ጥያቄው ደግሞ ልዩ ልዩ ነው። ርግጥ ሁሉም ጥያቄ እኩል ፋይዳ የለውም። መላቅጡ የጠፋበት ጥያቄ አለ። የሕይወትና የሞት ያህል የገዘፈ ዐሠሣም ይኖራል። አንዳንዱ ብንሸሸው የማናመልጠው ዐይነት ጥያቄ ነው፤ ዘመንን ሙሉ ሲከተል የሚኖር።

ከዚህ መሰል ጥያቄዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ስለ ኢየሱስ ይመለከታል፤ እርሱን ከማወቅ የሚመነጭ ጥያቄ። አንተ ራስህን ማን ታደርጋለህ?” (ዮሐ. 8፥53) ይሉት ዐይነት። እርሱም እኔ ማን እንደ ኾንሁ ትላላችሁ?” (ማቴ. 16፥15) በማለት ጠይቋል። በታሪክ ውስጥ የርሱን ያህል ያጠያየቀ፣ ያመራመረ፣ ያጨቃጨቀና ያነጋገረ ማንም የለም፤ ወደ ፊትም አይኖርም።

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ስመ ጥር መጋቤ ሐዲስ የኾነው ቶም ራይት (N.T. Right) “የመጀመሪያው ምእት ዓመት ታሪክ ላይ የሚያተኵር የታሪክ ተመራማሪ … ኢየሱስን ከሚመለከት ጥያቄ ማፈግፈግ አይቻለውም” ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ልክ ነው፤ የማያመልጡት ጥያቄ ነው።

የኢየሱስ የማንነቱ ማረጋገጫ ራሱ ነው። መጽሐፍ አልጻፈም፤ የሚመራው ጦር ኀይል አልነበረውም፤ የፖለቲካ ሥልጣን አልጨበጠም፤ ወይም የሀብት ማማ አልተቈናጠጠም። በመዋዕለ ሥጋዌው፣ ከኖረበት መንደር በአንድ መቶ ኪሎ ሜትር የርቀት ወሰን ውስጥ ነበር የተመላለሰው። ነገር ግን፣ አቻ ያልነበረው ሕይወቱ፣ ልብ ሰርስሮ የሚገባው ትምህርቱና እጅ በአፍ የሚያስጭኑ ሥራዎቹ የብዙ ሰዎችን ትኵረት ስበው እንዲከተሉት ወይም እንዲቃወሙት ያስገድዱ ነበር። በጊዜው የነበረው ዓለም፣ ተቋማትና ሥርዓትም በሕይወቱና ትምህርቱ መደናገጣቸው አልቀረም። እርሱ ማን ነው?

ምን አለፋችሁ፣ ኢየሱስ የሰው ልብ ወይ ከዚህ ወይ ከዚያ የተንጠለጠለበት ጥያቄ ኾኗል። ገና በጠዋቱ ተቃዋሚዎቹ እርሱን ከበውት ‘እስከ መቼ ልባችንንአንጠልጥለህ ታቆየናለህ?’” (ዮሐ. 10፥24 ዐመትለመኾኑ አንተ ማን ነህ?” (ዮሐ. 8፥25 ዐመትእነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ” (ማር. 11፥28፡ 29) በማለት ሲፏድዱ ቈይተዋል። ልደቱ ቤተ መንግሥት አናውጧል፤ ቤተ ክህነት በጥብጧል፤ እረኞችን በደስታ አስደንግጧል፤ ሰማይና ምድርን በአንድነት አስዘምሯል (ማቴ. 2፤ ሉቃ. 2)። መች ይኸ ብቻ፤ በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም፦ ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን፦ አይደለም፥ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር (ዮሐ. 7፥12)። ገሚሱ በደግነቱ ሲያምን ገሚሱ እንደ “አሳች” ፈረጀው።

ይህ መናወዝ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት እንደ ቀጠለ ነው። በተወሰኑ ሰዎች ታላቅ የምግባር መምህር ተደርጎ ተወድሷል፤ ለሌሎች ደግሞ ንጹሑ ነቢያቸው ኾኗል። “መናፍቅ” ነበር ብለው ራሳቸውን ያሳመኑ ነበሩ፤ አሉም። ነገር ግን እርሱ እንደ ተናገረው እንዲሁ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሲሑ ነው ብለው ያመኑበት ሞልተዋል። ማንም ይሁን ማን፣ ስለ ኢየሱስ አንድ ነገር ሳይል እንዳያልፍ ሰማይ ወስኗል፤ ኢየሱስ “ጥያቄ” ነው።

ከታላላቅ የእምነት ተቋማት ጀምሮ እስከ ትንንሽ ቡድኖች ድረስ በተለያየ መንገድ ስሙ ተጠርቶአል። ሃይማኖተኞች፣ ጦረኞች፣ ጠቢባን፣ ዐዋቆች፣ ጸሓፍት፣ ድኾች፣ ሀብታሞች ወዘተ. እርሱን በሚመለከት ዐቋም ይዘዋል። የሃይማኖት ምሁራን፣ ፈላስፎች፣ አሰላሳዮች፣ አርቲስቶች፣ ጠቢባን፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና ፖለቲከኞች፣ የቻሉትን ያህል፣ በትምህርቱና በሕይወቱ ተመስጠዋል። ፍተሻው ዛሬም መቋጫ አላገኘም። ከአይሁድ ጀምሮ እስከ ለየላቸው አረማውያን ድረስ በእርሱ ጕዳይ ተሟግተዋል፣ ጽፈውለታል፣ ጽፈውበታልም።

ቮልቴር የዚህን ሰው ትምህርት “በብዕሬ ጠራርጌ በማጥፋት ተረት አደርገዋለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስንም ወደ ሙዚየም አስገባለሁ” ብሎ ዝቶበታል። ማን ተረት ኾኖ እንደ ቀረ ታሪክ ምስክርነቱን ሰጥቶአል። ናፖሊዎን በፈንታው ሲናገር፣ “እስክንድር (ታላቁ)፣ ቄሳር፣ ቻርማኝና እኔ ታላላቅ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛተ መንግሥታት መሥርተናል፤ የገናናነታችን መሠረቱ ግን ጕልበት ብቻ ነበር። ኢየሱስ ግን መንግሥቱን የመሠረተው ጦር ሳይመዝ ዓለምን በፍቅሩ አሸንፎ ነው፤ በዚች ቅጽበት እንኳ ስለ ስሙ የሚሞቱለት ሚሊዮኖች ናቸው” ሲል ተደሟል። አንዳንዶች ኢየሱስን አምላክ ለማለት ባይደፍሩም በታላቅ የምግባር መምህርነቱ ወይም በነቢይነቱ ለመደነቅ ነፍስ አልቀረላቸውም። ግን ይህን ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ዋነኛው ጥያቄ ገና አልተመለሰም።

ይህ “ጥያቄ” ከላይ ብርሃን ካልጐበኘው በቀር ማንም አይመልሰውም። “ወንድሞቹ” ተብለው የሚታወቁ ሰዎች እንኳ እስከ ትንሣኤው ድረስ አላወቁትም ነበር። በትምህርቱና በዓላማው ላይ ሲያላግጡ ለከት አልነበራቸውም (ዮሐ. 7፥3-4)። ወደ ገዛ አገሩ መጥቶ በትምህርቱ ጥበብ፣ በተአምራቱ ምጥቀት ያስገረማቸው የሰፈሩ ሰዎች ያወቁት መስሏቸው ሲዘባበቱ ተሰምተዋል፤ ʻአብጠርጥረን እናውቀው የለም ወይ?ʼ (ማቴ. 13፥55-56) በማለት ተመጻደቁ፤ “የመንደራቸውን ልጅ” በቀላሉ የለዩት መስሏቸው ፈዘዙ። ኾኖም በትክክል ሳያውቁት ቀርተዋል። ለእነርሱ ጸራቢው የማርያም ልጅ (ማር. 6፥3) ብቻ ነበር የመሰላቸው። ለአንዳንዶች እግዚአብሔርን የሚገልጥ የመንግሥቱ ሰባኪ እንደ ነበረ ሲገለጥላቸው፤ ሌሎች ደግሞ መለኮትን የተሳደበ መናፍቅ አድርገው ቈጠሩት (ማቴ. 9፥3)፤ እንደመሰላቸው (ሉቃ. 3፥23) የገመቱ የነበሩትን ያህል፣ መርምረን “ወንጀለኛነቱን” አረጋግጠናል በማለት የፈረዱበት ከነቍስላቸው ወደ መቃብራቸው ወርደዋል።

ስለ እርሱ የተባለውን ምስጢር “በልቧ የምትጠባበቅ” ቅድስት ድንግል እንደ ነበረች ሁሉ (ሉቃ. 2፥19።51)፣ የተናቀና የተጠላ ለሚያዩትም ደም ግባት የሌለው ተራ መንገደኛ የመሰላቸውም አልታጡም። ኢየሱስ ጥያቄ ነው። በዚህ ሰው ስም ከአጋንንት እስራት የተፈቱ፣ ከኀጢአት አርነት የወጡ፣ የተለወጡና መንግሥቱን የተቀበሉ በልባቸው አንግሠውታል። በስሙ የስደትን ጽዋ ተጐንጭተዋል፤ በእርሱ ሰበብ ቤተ ሰብ ተከፍሏል፤ ትዳር ተሟግቷል፤ መንግሥታት ተናውጠዋል፤ ዓለም ተከፋፍሏል።

እንዳልነው፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በኢየሱስ ጕዳይ ሲነጋገር፣ ሲነታረክ ሲታመስና በሐሳብ ሲላጋ ኖሯል። ይህን ለማሳየት ከዚያው ዘመን የበለጠ ማስረጃ የለም። የማንነቱ ጥያቄ ናላቸውን ያዞረው ሰዎች ሊገድሉት በያዙት ጊዜ እንኳ ከጥያቄው አላመለጡም ነበር። “በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆችጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና፦ ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅምአትመልሱልኝም ” (ሉቃ. 22፥66-68)። በቅንዓትና በክፋት ተነሣሥተው የሚጠይቁ ነበሩና አልመለሰላቸውም። ዓለሙ ሁሉ የተከተለው ስለ መሰላቸው በቀብጸ ተስፋ አረገረጉ (ዮሐ. 12፥19)። ሕይወቱና ትምህርቱ ስለ በጠበጣቸው መታገሥ ያልቻሉና እርሱን ያሰሩት እኒያ ወገኖች ከነጥያቄያቸው ታስረው ቀሩ። እርሱ ራሱ በመገለጥ ብርሃን በልባችን ካልበራ ጭለማ በሕይወታችን ጥልቅ ላይ እንዳረበበ ይቀጥላል (2ቆሮ. 2፥6፤ 4፥4)።

ኢየሩሳሌም በልደቱ ታውካ (ማቴ. 2፥3) በንጉሣዊ አገባቡ “ይህ ማነው?” ስትል ተናውጣለች (ዮሐ. 21፥10)። “ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ማን ነኝትላለህ” (ዮሐ. 1፥22)? “በምን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ?” (ሉቃ. 20፥2) ባይ አሰማርታለች። “ጻፎችና ፈሪሳውያን በአፉ የተናገረውን ሊነጥቁ ሲያደቡ፥ እጅግይቃወሙና ስለ ብዙ ነገር እንዲናገር ያነሣሡ ጀመር” (ሉቃ. 11፥54)። መውጫ መግቢያውን በጆሮ ጠቢ ሸማቂ ሞልታ ስታሳድደውም ነበር (ሉቃ. 20፥20)። የመለኮት ጕብኝት በደጇ እንደ ቆመ አላወቀችምና፣ ሊሰበስባት የመጣውን አዳኟን ወርውራ ጣለችው። ኢየሱስ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ” (ቍ. 17)!

ያቺ በርኅራኄ ያለቀሰላት ከተማ (ሉቃ. 19፥41) ከጥያቄዋ ፋታ ለማግኘት (ጥያቄውን ለማስወገድ) ኢየሱስን ማስወገድ አማራጭ ኾኖ አገኘችው። መስቀል ላይ አኑራው እንኳ አላረፈችም ነበር። የዐላፊ አግዳሚውን ዐንገት እያስነቀነቀች፣ የካህናት አለቆችና ጻፎችን አሰማርታ እያስዘበተች፣ ተቸንክረው እንኳ መላሳቸው የማይገራ ሌቦች በግራ ቀኙ ሰቅላ እያስነቀፈች ልታንጓጥጠው ጣረች (ማቴ. 27፥ 39-44)። “በምድር ልብ ውስጥ” ልታዳፍነው ወደ መቃብር አወረደችው። መቃብሩን አትማ፣ ዘበኞች ቀጥራ ዋሻውን አስጠበቀች። ግን ጸጥ ረጭ ልታደርገው የገደለችው መሲሕ ከሁለት ሌሊት በኋላ ዓለምን “የሚበጠብጥ”ጥያቄ ኾኖ መጣ (የሐዋ. 5፥28)፤ ከሙታን ተነሣ።

በሐሰት ከስሰውና አስመስክረው “ይወገድልን” ብለው የሰቀሉት ሰዎች ደስታቸው ከሦስት ቀን በላይ አልዘለቀም። ሌላ ጭንቅ። ተገላገልነው ያሉት “ጥያቄ” እጅግ ተባብሶ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ማለዳ ደጃቸውን አንኳኳ፤ የገደላችሁትና የቀበራችሁት “በመቃብር የለም” የሚል መርዶ ከፊት ለፊታቸው ተገትሮ ነበር (ማቴ. 28፥1-11)። እነሆ፣ ይህ ጥያቄ ላለፉት ሁለት አምአት ከእያንዳንዱ ነፍስ ፊት እንደ ተደቀነ አለ። ትንሣኤው ጠላቶቹን ከቀዳሚ “ስሕተቶች” ሁሉ የበለጠ አስደነብሯል (ማቴ. 12-15)። በጊዜው የነበረ ዐቋምና ተቋም ሁሉ የኢየሱስን ዜና ትንሣኤ አፍኖ ለማስቀረት አለኝ የሚለውን ሁሉ ከፈለ (ማቴ. 28፥12)፤ ገንዘቡንም የፈጠራ ታሪኩንም ለዚሁ ዓላማ መደበ።

ግን ዓለም ኢየሱስን ለምን ነበር የጠላው? ዓለም የጠላው ሥራው ክፉ መኾኑን ስለ መሰከረበት አይደለምን (ዮሐ. 7፥7)? እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም(ዮሐ8፥23) ብሎ ነበር። ሥራው ክፉ የኾነ ሰው ጨለማን እንጂ ብርሃንን አይቀርብም (ዮሐ. 3፥20-21)።

እርሱ የማንንም ሕይወት አልጐዳም፤ በዘረፋና ምርኮ አልተሳተፈም፤ ሥዒረ መንግሥት አላካሄደም፤ ለድኾች ወዳጅ፣ ማኅበራዊ ስብራት ወደ ጠርዝ ለገፋቸው ምንዱባን ጓደኛቸው ነበር። ሁሉን የያዘና የሰውን ሕይወት ርቃን በጸጋ የሚሸፍን የሕይወት ራስ ሰው ፍለጋ በመጣ ጊዜ ግን ዓለም ለእርሱ ቦታ አልነበራትም። ሕይወታችንን በሚመስል ምጸት ዓለም ለኢየሱስ ያቀረበችለት ቦታ በረትና ግርግም ብቻ ነው (ሉቃ. 2፥7፡ 12፡ 16)፤ የተውሶ ግርግም። ለማስተማር ታንኳ ተውሶ ነበር (ሉቃ. 5፥3)፤ የፋሲካውን ራት ለመጨረሻ ጊዜ በተውሶ ቤት አበላ (ሉቃ. 22፥7-12)። በመጨረሻም የሰው ልጅ ለመሲሑ ያዘጋጀው “ከፍታ” የመስቀል እንጨት ኾነ፤ በዘረጋው የፍቅር እጁ ላይም ችንካር አኖረበት። ንፉጉ ዓለም፣ ክፉውም የሰው ልብ የእግዚአብሔርን መሲሕ በጭካኔ ሰቀለ። ሊቤዠው የወረደለትና የተዋረደለትን መሲሕ በክፋት ገደለ፤ ቀበረም። የተቀበረውም በተውሶ መቃብር ነበረ (ማቴ. 27፥60)።

የኔና የናንተ ዓለም ወንበዴውን መርጦ ጻድቁን የጣለ ዓለም ነው፤ በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው (ማቴ. 27፥16)። ምርጫ በተሰጣቸው ጊዜ በኢየሱስ ፈንታ በርባንን ፍታልን (ሉቃ. 23፥18) በማለት ገዢውን ለመኑ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ (ዮሐ. 18፥40)። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን የሰው ልጅ የሕይወት ጕድፍ በትዝብት ሲያወሳ እናንተ ግን ቅዱሱን፣ ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ። የሕይወትንምራስ ገደላችሁት” (የሐዋ. 3፥14) ይላል። ነፍሰ ገዳዩን (ሕይወት አጥፊውን) በሕይወት ራስ የለወጠው ዓለም ኢየሱስ ተወግዶ ሽፍታ እንዲሰጠው በአደባባይ ተሰልፎ ለመነ። ለምን? ታዳጊያቸውን እያዩት እንዳያዩት ከዐይናቸው ተሰውሮ ነበርና (ሉቃ. 19፥42)።

ይህን ውሳኔ ለማሳለፍ በፍርድ ችሎት የተቀመጠው ጲላጦስም ከአንድ ወሳኝ ጥያቄ ጋር ተፋጠጠ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው?”(ማቴ. 27፥22) ሲል በጣር ጮኸ። ማንም ሊያመልጠው የማይችለውን ጥያቄ ተጋፈጠ። ይህ ነገር በየሃይማኖቱና ፍልስፍናው ጥጋ ጥግ እየተውተረተሩ የማያመልጡት ጥያቄ ነው። የክርስትናን ስም በማጕደፍ መጽሐፉን በማቃጠል፣ ተከታዮቹን በማሳደድና በማሠቃየት የፈጠራ ታሪክ በማዘጋጀት ልናድበሰብሰው ብንፈልግም የማናመልጠው ጥያቄ ነው። ዲያብሎስና የዚህ ዓለም አሠራር በቻሉት ሁሉ ሞክረው ይህን ጥያቄ ሊያጠፉት አልቻሉም። “ይህን ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” ጥያቄውን እኔም እመልሳለሁ፤ አንተም ትመልሳለህ፤ አንቺም ትመልሻለሽ፤ እርስዎም ይመልሳሉ። ምላሻችን ግን ምን ይኾናል?

ሰዎች ኢየሱስ እንደ ጥያቄ ግራ ሲያጋባቸው ኖሯል። ብዙ መደናበር ታይቷል። ዓለም በጥበቧ ልታውቀው ስላልተቻላት ግን ምላሹን እግዚአብሔር ሰጥቶናል። እግዚአብሔር ለዓለሙ የሰጠው ጥያቄም ኾነ መልስ ራሱ ጌታ ኢየሱስን ነው። ኢየሱስ፦ የእግዚአብሔር ጥያቄ፤ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መልስ። አዎ፣ እግዚአብሔር ለገለጠለት የታዘዘና ምስክሩን የተቀበለ ዐወቀ። ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ኾነ አተመ” (ዮሐ. 3፥33)። እኛም እንደ እረኞቹ በትሕትና እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የኾነውን ነገር እንይ” (ሉቃ. 2፥15)። በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ለማዳን (1ቆሮ. 1፥21) በወደደው እግዚአብሔር መገለጥ ለሚያምን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው (ቍ. 24)።

መላእክቱ ሊያዩት የሚጓጕለትን (1ጴጥ. 1፥12)፣ ነቢያት ከሩቅ ሊያዩትና ሊሰሙት የናፈቁትን (ሉቃ. 10፥24) እንዲያዩትና እንዲሰሙት ታሪክ ዕድል የሰጣቸው ሰዎች ግን ገፉት፤ ገፈተሩት፤ ከሰፈራቸው አስወጡት፤ ከተማቸውን እንዲለቅላቸው ለመኑት (ማር. 5፥17)። አትበጥብጠን አሉት። ገደል ሊከቱት ፈለጉ (ሉቃ. 4፥29)፣ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ (ዮሐ. 8፥59፤ 10፥31)። ክስ መሠረቱ፣ ሰበብ ፈለጉበት፣ በቃል የሚያጠምድ ጆሮ ጠቢ እያደባ እንዲከተለው አሰማሩበት። የሐሰት ምስክር ቀጠሩበት (ማቴ. 27፥59-61)። ገደሉትም። ትንሣኤውን ለማስተባበል ጉቦ ለመክፈል ገንዘብ መደቡ። ምን ያልሞከሩት ነገር አለ? እኛ ከየትኛው ወገን ነን? የመውደቃችን ወይም የመነሣታችን ዕጣ ከእርሱ ጋር ተቋጥሯል።

አንድ ጠያቂ (ዐቋሙ ምንም ዐይነት ቢኾን) ስለ ኢየሱስ በሚሰነዝራቸው ጥያቄዎች ከውስጥ የመነጩ ፍላጎቶችን የሚዳስሱ ናቸው። አንድ ሰው ታሪክ ጸሐፊ ቢኾን ፈላስፋ የነገረ መለኮት አጥኚ ወይም ባህለ ማኅበራዊ ሐያሲ ወይም በቀላል አነጋገር ማንኛውም የሰውን ልጅ ከደስታና ኀዘኑ ሳይነጥል ማጥናት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ቢኾን ስለ ኢየሱስ መጠየቅ ያለባቸውን ጥያቄዎች ነው የሚያነሣው። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ የምንለው ነገር ሁሉ በንጽረተ ዓለማችን ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ የትየለሌ ነው። በዝርው አማርኛ መንዝሬ በጆን ኒውተን የግጥም ቃላት ለመናገር፣ “ስለ ክርስቶስ የምታስበው የትኛውም ነገር እምነትህንና ነገረ ሥራህን (የሕይወት ንድፍህን) የሚመዝን ፈተና ነው። ስለ እርሱ በትክክለኛነት ካላወቅህና ካላሰብህ በሌላ በምንም ነገር ትክክል ልትኾን አትችልም።”

ይህ ሁሉ ለምን ይኾናል? ሹመቱ ነው፤ ተልእኮው ነው። ከመጀመሪያም የታሪክን አቅጣጫ ነድፏል። የሰውን ዕጣ ፈንታ ከፍሏል። የዚህም ኾነ የሚመጣው ዓለም መውጫ መግቢያ ያለ እርሱ ሊነደፍ አልቻለም። እግዚአብሔር የላከው ኢየሱስ ስለዚሁ ተሹሟል። ሰዎች ለመውደቃቸው ወይም ለመነሣታቸው ዕጣቸው በርሱ ይወሰናል። እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል” (ሉቃ. 2፥34-35)። የመውደቅና የመነሣት ዓለት።

የኬምብሪጁ ምሁርና በእግዚአብሔር የማያምን የነበረው ሲ. ኤስ. ሉዊስ በክርስቶስ ካመነ በኋላ ከጻፋቸው መጻሕፍት በአንዱ (Mere Christianity) ውስጥ እንዲህ ይላል፤ “አንዱን ምረጥ። ይህ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፣ ነውም፤ አሊያ ወፈፌ ወይም ከዚያ የከፋ ነገር ነው። እንግዲያው ጸጥ አሰኘው፣ ከፊቱ ላይም ትፋበት፣ እንደ አንዳች ክፉ ጋኔን ቈጥረህ ግደለው። ወይም ከእግሩ ሥር ተንበርክከህ ጌታዬና አምላኬ ብለህ ጥራው። ግና ታላቅ ሰብአዊ መምህር ነበረ በሚሰኝ ግራ የተጋባ አባባል ውስጥ አትወሸቅ። እርሱ ያን እንድንል አልፈለገም።”

እውነት በክርስቶስ ኢየሱስ ተገልጧል። ያልተለወጠና የማይለወጥ እውነት የእግዚአብሔርን ዓለማ ወደሚያሳካበት ዳርቻ እየተንደረደረ ነው። ያ ዓላማ የሚሟላውና የመጨረሻ ተፍጻሜቱን የሚቀዳጀውም በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። ስለ እርሱ ሁሉን መዘርዘር አይቻልም። ትምህርቱ ልዩ ነው፤ ሕይወቱ ማራኪም አወዛጋቢም ነበር። ዛሬም እርሱ ያው ነው። የተሰቀለውና ከሞት ተለይቶ የተነሣው፣ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ የኾነው፤ ዓለሙን ያዳነውና በዓለሙም የሚፈርደው፣ የኀጢአተኞች ወዳጅና የሁሉ ጌታ፣ አሁን ያለው ደግሞም የሚመለሰው ጌታችን ኢየሱስ ዛሬም ያው፣ ዛሬም ሕያው ነው። የዓለምን ጥያቄ ሁሉ እግዚአብሔር የመለሰው በልጁ በኩል ነው። እርሱ ካልመለሰልን ሕይወታችን አልተመለሰም፤ ዘላለማችን ተስፋ የለውም፤ ነፍሳችን ተቅበዝብዛ መጥፋቷ ነው። ነገር ግን፣ “በመጽሐፍ፦ እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአል” (1ጴጥ. 2፥6)። ስሙ ለዘለዓለም ብሩክ ይሁን። አሜን።

[1] “I think, therefore I am.”

ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?

ባንቱ ገብረ ማርያም በዚህ ዐጭር ጽሑፋቸው፣ የሕይወታቸውን ዙሪያ ገባ ይቃኛሉ፤ ቃኝተውም አንድ መለያ ብቻ የሌለው ማንነት የተጎናጸፉ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንድ ጥያቄ ግን ማንሣታቸው አልቀረም፤ “ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?” የሚል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እንዴት እንድትተይቡ ተጠንቀቁ!

“በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች፣ የሰርክ ልማድ እስኪመስል ድረስ እየታዩ ያሉት አንዳንድ ምልልሶቻችን፣ ለትልቅ ቅራኔ በር የሚከፍቱና አሉታዊ ስሜቶች ያየሉባቸው ናቸው። ከዐሳብ ይልቅ ሰብእናን ማጥቃትንና የተቃወመንን ኹሉ በተመጣጣኝ የመልስ ምቶች ማደባየትን ተክነናል። ከፉውን በመልካም የመመለስና በጸድቅ በልጦ የመገኘት ክርስቲያናዊ ዕሴት ያለን እስከማይመስል ድረስ፣ ለኹሉ በሰፈሩት ቍና የመስፈር ዓለማዊ ጥበብ ተጠናውቶናል። ዐሳቡን ያልገዛንለት ሰው ሲኖር፣ ሌሎች ሰዎች ለዚያ ሰው ያላቸው ክብርና ፍቅር እስኪሸረሸር ድረስ በሚዘልቅ ጥቃት እንከፋበታለን፤ የለየት ማጠልሸት ውስጥ እንገባለን።” አሳየኸኝ ለገሰ

ተጨማሪ ያንብቡ


My Father’s Confession: Jesus and the OLF

The Oromo Liberation Front (OLF) has returned to Ethiopia saying it will continue its struggle peacefully after years of armed fighting from outside. The long-time leaders and icons of the movement have been welcomed by many on September 15, 2018 after many years of exile. Sadly, my father didn’t live long enough to see this day.

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.