[the_ad_group id=”107″]

ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች

(The 70 Resolutions of Jonathan Edwards)

የአገረ አሜሪካን የዐሥራ ስምተኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ የመንፈሳዊ መነቃቃት ጀማሪና ቀንደኛ መሪ የሆነው ጆናታን ኤድዋርድስ በአፍላ የወጣትነት ዕድሜው ለቀሪ ሕይወቱ መመሪያ እንዲሆኑ ሰባ (70) ቁርጠኛ ውሳኔዎችን በማድረግ ለራሱ ቃል ገብቷል። ጆናታን እነዚህን ውሳኔዎች መጻፍ የጀመረው በ18ኛው የዕድሜ ዘመኑ እንደ ሆነ ይታመናል።

የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች እንዲህ በማለት ይጀምራል፦

“ከእግዚአብሔር ዕርዳታ ውጭ አንዳች እንኳን ላደርግ እንደማልችል በማወቅ፣ እንደ ፈቃዱ እስከ ሆኑ ድረስ፣ እነዚህን ቁርጠኛ ውሳኔዎች ለመጠበቅ እንድችል እግዚአብሔር በጸጋው እንዲረዳኝ ራሴን ዝቅ አድርጌ ስለ ክርስቶስ እለምነዋለሁ። እነዚህን ቁርጠኛ ውሳኔዎች በሳምንት አንድ ቀን ማንበብህን አትርሳ።

  1. በሕይወቴ ዘመን ሁሉ የጊዜ ቀመር ሳያግደኝ፣ ዛሬ ቢሆን ኊልቆ መሳፍርት ዘመናት ድረስ፣ ማንኛውም ነገር የማደርገው ይበልጥ ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለራሴ ጥቅም፣ እርባና እና ደስታ እንዲሆን ቆርጫለሁ። ግዴታዬ ነው ብዬ የማስበውን ማንኛውም ነገር ለማድረግ፣ እንዲሁም ለጠቅላላው የሰው ልጅ የሚበልጥ መልካምነትና ጥቅምን የሚሰጥ ነገር ለማድረግ ቆርጫለሁ። የትኛውም ዐይነት ችግር ቢያጋጥመኝ፣ የችግሮቹ ቍጥር ምንም ያህል ቢበዙ ወይም እጅግ ብርቱ ቢሆኑ፣ እነዚህን ማድረጌ ቁርጥ ውሳኔ እንዲሆን ቆርጫለሁ።
  2. ከላይ የተጠቀሱትን ለማስፋፋት ሁሌም አዳዲስ መንገዶችና ልምምዶችን ለመፈለግ እንድጥር ቆርጫለሁ።
  3. የእነዚህን ቁርጠኛ ውሳኔዎች በከፊል ለመፈጸም ችላ ብል ወይም ደንዝዤ ከማድረግ ብቆጠብ፣ ወደ አደቤ በተመለስኩበት ቅጽበት ስለማስታውሰው ጥፋቴ ሁሉ ንስሓ እንድገባ ቆርጫለሁ።
  4. እግዚአብሔርን የሚያስከብር እንጂ፣ በሥጋዬም ሆነ በነፍሴ ሌላ ያነሰ ወይም የበዛ ነገር በጭራሽ እንደማላደርግ፣ እነዚህን ነገሮች በማስወገዴ እንዳላዝን እና እንዳልበሳጭ ቆርጫለሁ።
  5. አንድ ሰከንድም ቢሆን እንደማላባክን፣ ሆኖም ግን ጊዜዬ ሁሉ ጥቅም ላይ ለማዋል በምችለው ሁሉ እንዳደርግ ቆርጫለሁ።
  6. ስኖር፣ በሙሉ ኀይለ ብርታቴ እንድኖር ቆርጫለሁ።
  7. የሕይወቴ መጨረሻ ሰዓት ላይ ሆኜ ቢሆን እንኳን፣ ለማድረግ የምፈራውን ማንኛውንም ነገር በጭራሽ እንዳላደርግ ቆርጫለሁ።
  8. በሁሉም አቅጣጫ፣ በንግግርም ሆነ በተግባር እኔ ከደረስኩበት ርኵሰት የደረሰ ማንም እንደሌለ ራሴን እየቈጠርኩ እንደንምቀሳቀስ፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ኀጢአትን እንደፈጸምኩ ወይም እንደ ሌላው ዐይነት ድካምና ውድቀት እንዳለብኝ ራሴን እንደምጥር፣ ከዚህ በተጨማሪም የሌላው ውድቀት የራሴን ዕፍረት እንጂ፣ ሌላ አንዳች እንደማያሳይ፣ እንዲሁም የራሴ ኀጢአትና መከራ ወደ እግዚአብሔር በንስሓ እንድቀርብ የሚያስታውሰኝ እንዲሆን ቆርጫለሁ።
  9. ስለ ራሴ ሞት፣ እንዲሁም ሞትን ስለሚያመጡ የታወቁ ሁኔታዎች ሁሌም እንዳስብ ቆርጫለሁ።
  10. ሕመም ሲሰማኝ፣ የመሥዋዕታቱን እና የገሃነምን ስቃይ እንዳስብ ቆርጫለሁ።
  11. መመለስ የሚገባቸው ሥነ መለኮታዊ ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ ሲመጡ፣ አጋጣሚዎች ዕንቅፋት ካልሆኑብኝ በቀር፣ ጥያቄውን ለመፍታት የምችለውን ማንኛውንም ነገር ወዲያውኑ እንዳደርግ ቆርጫለሁ።
  12. በጉራ ተኩራርቼ ወይም እንደ እነዚህ ዐይነት ተመሳሳይ ነገሮች በማግኘቴ በከንቱ እንድኮፈስ የሚያደርገኝ ነገር እንደተሰማኝ ሲታወቀኝ፣ ወዲያውኑ አሽቀንጥሬ እንድወረውረው ቆርጫለሁ።
  13. የልግስና እና የቸርነት ወይም የበጎነት ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ለማግኘት እንድጥር ቆርጫለሁ።
  14. አንዳችን ነገር ስንኳ በበቀል በጭራሽ እንዳላደርግ ቆርጫለሁ።
  15. ምክንያት የለሽ ወይም መሠረተ ቢስ (irrational) በሆኑ ሰዎች ወይም ነገሮች፣ ነቁጣ በምታክል ቁጣ በጭራሽ እንዳልሰቃይ ቆርጫለሁ።
  16. “ለእውነተኛ ለሚታይና ለሚዳሰስ አንዳች ጥሩ ነገር” (some real good) ጠቃሚ ካልሆነ በስተቀር፣ በትንሹም ሆነ በትልቁ ክብርን የሚያዋርድ ክፉ ነገር ስለ ማንኛውም ሰው ወይም ነገር እንዳልናገር ቆርጫለሁ።
  17. ስሞት “ምነው እንዲህ በኖርኩ ኖሮ!” ብዬ እንደምመኘው ሁሌም እንድኖር ቆርጫለሁ።
  18. ስለ ወንጌሉና ስለ ወዲያኛው (የሚመጣው) ዓለም በጣም ግልጽ ግንዛቤ በሚኖሩኝ ጊዜያት፣ ሁሌም ከፍ ባለና በተሻለ የእግዚአብሔር ፍርሀት ነው ብዬ እንደማስበው እንድኖር ቆርጫለሁ።
  19. የመጨረሻው መለከት ሊነፋ ከአንድ ሰዓት በላይ እንዳልቀረ ባውቅ እንኳን፣ ለማድረግ የምፈራውን ማንኛውንም ነገር በጭራሽ እንዳላደርግ ቆርጫለሁ።
  20. ሁሌም በመብልና በመጠጥ በቁርጠኛነት ራሴን እንድመጥን ቆርጫለሁ።
  21. በሌላ ላይ ካየሁት ነገር በመነሣት ማንንም እንዳልጠላ፣ ወይም ሌላውን አዋርጄ በመጥፎነት በጭራሽ እንዳላስብ ቆርጫለሁ።
  22. በቂ ደስታን በሚመጣው ዓለም ለማግኘት በተቻለኝ መጠን እንደምጥር፣ ይህን ለማድረግ ሙሉ ኀይሌን፣ ጉልበቴን፣ ብርታቴን፣ ጭካኔዬን፤ በግድም ቢሆን እንኳን፣ በምችለው ሁሉ ወይም ሊደረግ ይቻላል ተብሎ በሚታሰብ ማንኛውም መንገድ እንድታገል ቆርጫለሁ።
  23. ለእግዚአብሔር ክብር ስል ሊደረግ የማይችል የሚመስልን ነገር ሆን ብዬ ዘወትር እንደማደርግ፣ የነገሩን ቀዳሚ ዐላማ፣ ንድፍና መጨረሻ ዱካውን እንደምመረምር፣ ነገሩ ለእግዚአብሔር ክብር የማይመጥን መሆኑን ሳውቅም፣ 4ኛውን ቁርጥ ውሳኔ የጣሰ እንደ ሆነ አድርጌ እንዳስቀምጠው ቆርጫለሁ።
  24. ግልጽ በሆነ ሁኔታ ክፉ ነገር ሳደርግ ራሴን ባገኝ፣ ይህን እንዳደርግ ያደረገኝን ዋና ነገር ወደ ኋላ ዱካውን እንደምመረምር፣ ሳገኘውም ነገሩን ድጋሚ እንደማላደርገውና ባለኝ ኀይል ሁሉ ለመታገልና ለመጸለይ እንድጥር ቆርጫለሁ።
  25. የእግዚአብሔርን ፍቅር በደቂቅ እንድጠራጠር የሚያደርገኝን አንዳች ነገር በራሴ ላይ ሳገኝ፣ ራሴን በጥንቃቄና በተከታታይ እንደምመረምር፣ ኀይሌን ሁሉ ይህን በመቃወም ላይ እንዳላውል ቆርጫለሁ።
  26. የሕይወት ዋስትናዬን የሚያደክሙ የሚመስሉ ነገሮችን አሽቀንጥሬ እንድጥል ቆርጫለሁ።
  27. አንዳች ነገርን ከማድረግ መቆጠቤ ለእግዚአብሔር ክብር ካልሆነ በስተቀር፣ ሆን ብዬ እንዳልቆጠብ፣ የመቆጠቤንም ምክንያት ዘወትር እንድመረምር ቆርጫለሁ።
  28. ቅዱሳት መጻሕፍትን ካለፋታና ያለማቋረጥ፣ ዘወትርም እንዳጠና፤ ይህንም ራሴን በቃሉ ዕውቀት ማደግ እንዳለብኝ ሲሰማኝና በግልጽ ለራሴ ሲታወቀኝ ለማድረግ ቆርጫለሁ።
  29. እግዚአብሔር መልስ አይሰጥም ብዬ ተስፋ የማላደርገውን ጸሎት፣ ጸሎት ነው ብዬ እንደማላሳልፈው፣ የጸሎት ልመና አድርጌ እንዳልቈጥረው፤ እግዚአብሔር አይቀበለውም ብዬ ተስፋ የማላደርገውን ንስሓንም፣ ንስሓ አድርጌ እንዳልቈጥረው ቆርጫለሁ።
  30. በእያንዳንዱ ሳምንት በእምነት ከፍ ያለን ነገር ለማምጣት የተቻለኝን ያህል እንድጥር፣ ካለፈው ሳምንት ከፍ ባለ ጸጋም እንድኖር ቆርጫለሁ።
  31. ልኂቅ ከሆነው የክርስትና ክብር ጋር ፍጹም የተስማማ፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ፍቅር ጠቃሚ፣ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ትሕትና ጋር የተስማማ፣ የራሴን ጉድለትና ውድቀት በማሰብ፣ እንዲሁም ከወርቃማው ሕግ ጋር የተስማማ ካልሆነ በስተቀር ስለ ማንኛውም ሰው በጭራሽ በተቃውሞ ምንም እንደማልናገር ቆርጫለሁ፤
  32. ለአደራነቴ (my trust) በጣም በጥብቅ ወይም በትጋትና በጽናት ታማኝ እንደምሆን፣ ምሳሌ 20፥6 ላይ “የታመነውን ሰው ግን ማን ያገኘዋል?” የሚለው በከፊል እንኳን እንዳይፈጸምብኝ ቆርጫለሁ።
  33. በሌላ አንጻር የሚያመጣው ጉዳቱ የሚከብድ እስካልሆነ ድረስ፣ በተቻለኝ መጠን ሰላምን ለማምጣት፣ ለመጠበቅ፣ ለመመሥረትና ለማቆየት ሁሌም እንድሠራ ቆርጫለሁ። (Dec. 26, 1722)
  34. የጠራና ግልጽ እውነትን እንጂ፣ ተራ ወሬ ወይም ታሪክን እንዳልናገር ቆርጫለሁ።
  35. ግዴታዬን መወጣቴን ራሴን በምጠይቅበት ጊዜ ሁሉ፣ ሰላሜና መንፈሴ ተረብሾ እንደሆን እንድመረምር፣ ስጋቴ እስከሚወገድም ከድርጊቴ እንቆጠብ ቆርጫለሁ። (Dec. 18, 1722)
  36. አንዳች የሚጠቅም ጥሩ ነገር ካላየሁበት በስተቀር፣ ክፋ ነገር ስለ ማንኛውም ሰው ወይም ነገር በጭራሽ እንደማልናገር ቆርጫለሁ። (Dec. 19, 1722)
  37. ሁሌም ወደ መኝታ ስሄድ፣ ችላ ስላልኩት፣ ስለፈጸምኩት ኀጢአት፣ ራሴን ስለካድኩበት ወይም ራሴን ስላታለልኩት ነገሮች ራሴን እንድጠይቅ፣ ይህንም በየሳምንቱ፣ በየወሩ እና በየዓመቱ መጨረሻ እንዳደርግ ቆርጫለሁ። (Dec. 22 & 26, 1722)
  38. የሞኝኘትና እርባና ቢስ [ቃል] ወይም ቀልድ የበዛበትን አንዳች ነገር በጌታ ቀን ጭራሽ እንዳልናገር ቆርጫለሁ። (Dec. 23, 1722 ሰንበት ምሽት)
  39. የመግደፍን ሕጋዊነት ከመጠየቅ ውጭ፣ ሕጋዊ ቢሆንም ባይሆንም፣ ሕጋዊነቱን የምጠራጠረውን፣ በኋላም እንዲህ ይሆናል ብዬ የምጠራጠረውን አንዳችንም ነገር በጭራሽ እንዳላደርግ ቆርጫለሁ።
  40. ወደ መኝታ ከመሄዴ በፊት፣ ምግብና መጠጥን ጨምሮ፣ በቀኑ ውሎዬ በተቻለኝ ሁሉ ከፍ ባለ ጥንቃቄ ተመላልሼ እንደ ሆነ በእያንዳንዱ ምሽት ራሴን እንድጠይቅ ቆርጫለሁ። (Jan. 7, 1723)
  41. ማንኛውንም ነገር ከዚህ በተሻለ ማድረግ እችል እንደ ሆነ በእያንዳንዱ ቀን፣ ሳምንት፣ ወር እና የዓመት መጨረሻ ራሴን እንድመረምር ቆርጫለሁ። (Jan. 11, 1723)
  42. በጥምቀቴ ቀን እንዲሁም ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ስቀላቀል ራሴን ለእግዚአብሔር መስጠቴን በሞገስ የገባሁትን ቃል ዘወትር እንደማድስ ቆርጫለሁ። ይህንም January, 1722-23 በሃያኛው ቀን ድጋሚ በሞገስ አድርጌያለሁ።
  43. ከአሁን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ፣ በሙላትና በሁሉም የእግዚአብሔር እንጂ፣ በማንኛውም ሁኔታ ራሴን የእኔው አድርጌ እንዳልወስድ ቆርጫለሁ። ይህም ከቅዳሜ January 12, 1723 ከታየው ጋር የተስማማ ነው።
  44. የእምነት ውጤትን የሚያመጣ እንጂ፣ አንዳችም ነገር በማንኛውም ተግባሬ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብኝ ቆርጫለሁ። እንዲሁም፣ የትኛውም ተግባሬ ከእምነት ውጤቱ ጋር የተስማማ እንጂ፣ እጅግ በጥቂቱም የተለየ እንዳይሆን ቆርጫለሁ። (Jan.12, 1723)
  45. ለእምነት ጠቃሚ ካልሆነ በስተቀር፣ የትኛውንም ተድላ ይሁን መከራ፣ ደስታ ይሁን ኀዘን፣ ማንኛውንም ዐይነት ስሜት፣ የትኛውንም የስሜት መጠን፣ ከእነዚህም ጋር የተያያዘ ማንኛውም ሁኔታ እንዳላስተናግድ ቆርጫለሁ። (Jan. 12 & 13, 1723)
  46. አስቸግሬ እናቴንና አባቴን ቅንጣት በምታክል አንዳች ነገር ለማሳዘን በጭራሽ እንደማልፈቅድ ቆርጫለሁ። ንግግሬን በመለዋወጥ ወይም በመቀባጠር ይሁን በማደርገው ነገር በጭራሽ ቅር እደማላሰኛቸው፣ ይህንንም በማንኛውም የቤተሰብ አባል ላይ/ዘንድ እንደማላደርግ ቆርጫለሁ።
  47. መልካም፣ በሁሉ ዘንድ ጣፋጭና ቅን፣ ጸጥተኛ፣ ሰላማዊ፣ በቃኝ ባይ፣ ቀላል፣ የሚያዝን፣ ደግ፣ ዝቅ ያለ፣ የዋህ፣ ትሑት፣ ዕሺ ባይ፣ ታዛዥ፣ ትጉህና ታታሪ፣ ቸር፣ ትክክለኛ፣ ታጋሽ፣ ልከኛ፣ ይቅር ባይ፣ ቀና ባሕርይ የሌለበትን ነገር ሁሉ እምቢ ለማለት እጅግ በጣም እንድጥር፤ ወደ እነዚህ ጠባዮች የሚመራኝን ነገር ሁሉ እንዳደርግ፤ ይህንም እንዳደረግሁ በየሳምንቱ ራሴን በጥብቅ እንድመረምር ቆርጫለሁ። (May 5, 1723. ሰንበት ጠዋት)
  48. በእኔ ውስጥ በእውነት ስለ ክርስቶስ መሻት እንዳለኝና እንደሌለኝ ለማወቅ፣ የነፍሴን ሁኔታ በእጅግ መልካምነትና ጥራት፣ እንዲሁም በጥብቅ ሁሌም እንድመረምር፤ በዚህም በምሞትበት ጊዜ ስለዚህ ንስሓ የሚያስገባ አንዳች ችላ ባይነት እንዳይገኝብኝ ቆርጫለሁ። (May 26, 1723)
  49. በሚቻለኝ መቼም ቢሆን ቸልተኛ እንደማልሆን ቆርጫለሁ።
  50. የሚመጣው ዓለም ወይም መንግሥተ ሰማያት ከመግባቴ በፊት ከፍ ባለ ሁኔታ እና በአርቆ አሳቢነት እየኖርኩ እንደ ሆነ በመመርመር እንደምመላለስ ቆርጫለሁ። (July 5, 1723)
  51. እንዲህ ባደርግ በመጨረሻ ይፈረድብኛል በሚል እሳቤ በሁሉም አንጻር እንደምንቀሳቀስ ቆርጫለሁ። (July 8, 1723)
  52. አረጋውያን ሰዎች ሕይወታቸውን ድጋሚ የመኖር ዕድል ቢያገኙ፣ “እንዲህ እኖር ነበር!” ሲሉ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ። አረጋዊ እንደምሆን በማሰብ፣ መኖር የነበረብኝ እንዲህ መሆን ነበረበት ብዬ እንደማስበው ዛሬን እንድኖር ቆርጫለሁ። (July 8, 1723)
  53. ራሴን በላቀና ከፍ ባለ ደስተኛ የአእምሮ ስሜት ውስጥ ሳገኘው፣ ጥሩ የሆነውን ሁሉ እደማሻሽል፣ ነፍሴን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንድጥልና በእርሱም ላይ እንዳውላት፣ በእርሱ እንድታመንና በዐደራው ሥር እንድሆን፣ መላ ራሴን ለእርሱ ስእለት አድርጌ እንድሰጥ ቆርጫለሁ። ይህም በመድኅኔ እንድታመን ተረድቼ ለደኅንነቴ ዋስትና እንዲኖረኝ ነው። (July 8, 1723)
  54. ስለ ማንኛውም ሰው በጫወታ መኻል ሲነገር፣ ምስጋና የሚገባው መሆኑ በውስጤ ከተሰማኝ፣ ልከተለው እንድጥር ቆርጫለሁ። (July 8, 1723)
  55. የመንግሥተ ሰማያት ደስታን እንዲሁም የገሃነም ስቃይን አስቀድሜ እንዳየሁ በመቍጠር፣ ማድረግ ይገባኛል ብዬ ከማስበው እጅግ በላቀ ሁኔታ እንድኖር ቆርጫለሁ። (July 8, 1723)
  56. ምንም ያህል ስኬታማ ወይም ያልተሳካልኝ ብሆን፣ በጭራሽ ለብልሹነቴ ራሴን አሳልፌ እንዳልሰጥ ወይም ትግሌን በጥቂቱ እንኳን ጋብ እንዳላደርግ ቆርጫለሁ።
  57. ክፉ ቀናትና የሚጠሉኝ ሲያውኩኝ ወይም ሲያስፈሩኝ፣ በቅድሚያ የራሴን ድርሻ ተወጥቼ እንደ ሆነ እንድመረምር፣ እንደማደርገውም ርግጠኛ እንድሆን፤ ይህም እንደ እግዚአብሔር መግቦት (Providence) እስከምችለው ድረስ በግሌ መወጣት ስለሚገባኝ የራሴ ድርሻና ኀጢአት እንጂ፣ ስለ ሌላ በአንዳች እንዳልጨነቅ ቆርጫለሁ። (June 9 & July 13, 1723)
  58. በውይይት ወቅት ከጥላቻ፣ ከማስጨነቅና ከቁጣ ራሴን መቆጠብ ብቻ ሳይሆን፣ የፍቅር፣ የደስታ እና የበጎነትን መንፈስ እንደማሳይ ወይም እንደምፈጥር ቆርጫለሁ። (May 27 & July 13, 1723)
  59. ለጥላቻና ለቁጣ መነሣሣቴን ሳውቅ፣ መልካምን ለማሰብና ለማድረግ በጣም እንድታገል፤ አዎን፣ አንዳንዴ የማይጠቅመኝ ሌላ ጊዜ አስተዋይነት የጎደለኝ ቢመስል እንኳን መልካም ሰብእናን እንዳሳይ ቆርጫለሁ። (May 12, July 2, & July 13)
  60. ስሜቴ በጥቂቱም ቢሆን መሥመር መሳት ሲጀምር፣ ጥቂት ቅሬታ በውስጤ ሲሰማኝ፣ ወይም ወለም ዘለምታን ሳስተውል፤ ነገሩን በጥብቅ ለመመርመር ራሴን ላስገደድ ቆርጫለሁ። (July 4 & 13, 1723)
  61. አእምሮዬ ሃይማኖት ላይ በሙላትና በመጣበቅ እንዳያተኵርና እንዲያመቻምች በሚያደርግ ድምፅ እንዳልወሰድ፣ ማንኛውም ዐይነት ምክንያቶች ቢኖሩኝ ማዳመጥ የሚገባኝን ማድመጥ ወይም የማይገባኝን ላለማድመጥ፣ ወዘተ. ማድረጉ ይበልጥ ጠቃሚ እንደ ሆነ ቆርጫለሁ። (May 21 & July 13, 1723)
  62. ግዴታዬን እንጂ ምንም ነገር ላለማድረግ፣ ከዚህ በተያያዘም በኤፌ. 6፥6-8 መሠረት፣ ለጌታ እንጂ ለሰው እንደማላደርገው በማወቅ፣ “እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና” እንደሚለው፣ በፈቃዴ እና በደስታ እንደማደርገው ቆርጫለሁ። (June 25 & July 13, 1723)
  63. በየትኛውም ወቅት ከእኔ በቀር ዓለም ላይ አንድ ሰው እንጂ ሌላ ሰው እንደሌለ ዐይነት በማሰብ፤ በሁሉም ፈርጅ የተፈተነ ሙሉ ክርስቲያን መሆን የሚገባው፣ ክርስቲያናዊነት በእውነተኝነት ሁሌም ደምቆ የሚንጸባረቅበት፤ እንዲሁም በማንኛውም አቅጣጫ ወይም ቦታም ሆነ ከየትኛውም ባሕርይ አንጻር ሲታይ፣ ምርጥና ተወዳጅ ሆኖ የሚታይ፣ ይህን እንደማደርግ፤ ይህን ሰው ለመሆን፣ እንዲሁም በጊዜዬ እንዲህ የምኖ እንደምሆን በአለኝ ኀይል ሁሉ እንደምታገል ወይም እንድደክም ቆርጫለሁ። (Jan. 14 & July 13, 1723)
  64. ሐዋርያው፣ “በማይነገር መቃተት” ብሎ የተናገረውን (ሮሜ 8፥26)፣ እንዲሁም መዝሙረኛው መዝሙር 110፥20 ላይ፣ “ነፍሴ ሁልጊዜ እጅግ ናፈቀች” ብሎ ያስቀመጠውን በማገኝ ጊዜ፣ እጅግ ከፍ ባለ ኀይል እንደማደረጃቸው፣ ይህን ፍላጎቴን በጋለ ስሜትና ልባዊ በሆነ ብርታት እንደማደርግ፣ ይህንም ደጋግሜ ለማድረግ እንዳልደክም ቆርጫለሁ። (July 23 & August 10, 1723)
  65. በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ነፍሴን ለእርሱ ገልጬ እንደማሳይ፣ ኀጢአቶቼን ሁሉ፣ ፈተናዎቼን፣ ትግሎቼን፣ ኀዘኖቼን፣ ፍርሀቶቼን፣ ተስፋዎቼን፣ ፍላጎቶቼን እንዲሁም ሁሉን ነገርና ሁኔታዎችን ይህን ነገር እንደማደርግ፤ እንዲሁም መንገዴን ለእግዚአብሔር እንዳሳውቅ ቆርጫለሁ። ይህም ዶ/ር ማንቶን መዝሙር 119ን ካስተማሩት እንደ 27ኛው ስብከታቸው ነው[1](July 26 & August 10, 1723) [Thomas Manton, One Hundred and Ninety Sermons on the Hundred and Ninteeth Psalm (London, 1861).]
  66. የለጋስነት ባሕርይ እንዲኖረኝ፣ በታማኝነት ማድረግ አይገባኝ ከሆነ በስተቀር፣ በሁሉም ስብስብ ወይም ጕባኤ ለመሥራትና ለመናገር ሁሌም እንድጥር ቆርጫለሁ።
  67. ከመከራና ከጭንቀት በኋላ፣ ከዚያ ምን እደተማርኩ ራሴን እንድጠይቅ፣ ከዚህም ምን መልካም ነገር እንዳገኘሁ፣ እንዲሁም፣ ከእነርሱ ምን ጥቅምና ውስጣዊ ዕይታን አሁን እንዳለኝ ራሴን እንድጠይቅ ቆርጫለሁ።
  68. በእኔው በራሴ ውስጥ የማየውን ደካማነት ወይም ኀጢአት ለእኔው ለራሴ በእውነተኛነት ንስሓ እንደምገባ፣ ጕዳዩ እምነትን በተመለከተ ከሆነ ደግሞ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ንስሓ እንደምገባና የሚያስፈልገኝን ዕርዳታ እርሱን እንድለምንም ቆርጫለሁ። (July 23 & August 10, 1723)
  69. ሌሎች ሲያደርጉት ሳይ፣ ምነው እኔ ባደረኩት የምላቸውን ነገሮች ሁሌም ለማድረግ ቆርጫለሁ። (Aug. 11,1723)
  70. በምናገረው ሁሉ አንዳች ቸርነት ወይም ፍቅር (benevolence) እንዲኖርበት ቆርጫለሁ።” (Aug. 17, 1723)

ማሳሰቢያ፦ የአንዳንዶቹ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች ጥንታዊ መሆን ወደ አማርኛ ለመተርጎም አዳጋች እንደ ሆነ ታሳቢ እንዲደረግ ተርጓሚው ያሳስባል። (እንግሊዘኛውን ከዚህ ድረ ገጽ ማግኘት ይቻላል፦ https://www.desiringgod.org/articles/the-resolutions-of-jonathan-edwards

Share this article:

እግዚአብሔርን የመፍራት በረከት

የምንኖርበትን ዓለም በትዝብት መነፅር ብንመለከት የሰው ልጅ ሕይወት ውጣ ውረድና ትግል የበዛበት በመሆኑ ፍቅርና ጥላቻን እንዲሁም በእምነትና በክህደት መካከል ያለው የነፍስ ፍትጊያ እንዴት እንደ ሆነ ለመረዳት አንቸገርም። ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ራሱን ከሌላው የተሻለ አድርጎ ለሌሎች ለማሳየት ወይም ከሌላው ሰው በልጦ ለመታየት የማይምሰው ጉድጓድና የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የተፈጥሮ ሕግን ተከትሎ ጊዜው ሲመሽና ሲነጋ የሰውም ሕይወት አንዴ ሲጨልም፣ አንዳንዴ ደግሞ ፍንትው ብሎ ፀሓይ እንደወጣችለት ቀን ሲበራ ይታያል።

ተጨማሪ ያንብቡ

5 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • Thank you very much brother Amare Tabor. Many have read it, but only you have brought it to our table.

  • 8• በሁሉም አቅጣጫ፣ በንግግርም ሆነ በተግባር እኔ ከደረስኩበት ርኵሰት የደረሰ ማንም እንደሌለ ራሴን እየቈጠርኩ እንደንምቀሳቀስ፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ኀጢአትን እንደፈጸምኩ ወይም እንደ ሌላው ዐይነት ድካምና ውድቀት እንዳለብኝ ራሴን #እንደምቆጥር፣ ከዚህ በተጨማሪም የሌላው ውድቀት የራሴን ዕፍረት እንጂ፣ ሌላ አንዳች እንደማያሳይ፣ እንዲሁም የራሴ ኀጢአትና መከራ ወደ እግዚአብሔር በንስሓ እንድቀርብ የሚያስታውሰኝ እንዲሆን ቆርጫለሁ።

  • ወንድሜ አማረ፤ እጅግ ግሩም ሥራ ሠራህ፤ የአእምሮ ወቀሳዬንም ሻርክልኝ፤ ጌታ ኢየሱስ አብዝቶ ይባርክህ፡፡ የጆናታን ኤድዋርድስ ውሳኔዎች እጅግ የምወዳቸው ናቸው፤ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ጀምሬ ያልዘለቅሁባቸው ጊዜያት በርካታ ነበሩና ይህን ሥራ ሳይ እጅግ ተደሰትሁ፡፡
    በብዙ የምወደውንና የምታነጽበትን ጽሐፍ በቋንቋዬ አገኘሁት፤ እንዴት ደስ ይላል፡፡ ይህ ብዙዎችን እንደሚያንጽ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ያክብርልኝ የተወደድህ ሆይ! ሕንጸቶችንም ከልቤ ላመሰግን እወዳለሁ፤ ወደ እናንተ ቤት ጎራ ስል የማገኘው ብዙ ነው፤ ተባረኩ፡፡

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.