[the_ad_group id=”107″]

የፍትሕ ጩኸት እና የዝምታ ኀጢአት

“ቤተ ክርስቲያን በአገር ፖለቲካ አያገባትም የሚለው የራስ ግንዛቤ፣ የአምላክ ሥጋ (ትስብእት) መሆንና ከኀጢአት በስተቀር የሰውን ሁለንተናዊ ሕይወት ከመጋራቱ እውነት እንዲሁም ከእግዚአብሔር መልካምነትና የፍጥረት ገዢነት ጋር ይጋጫል” ~ ጉዲና ቱምሳ

በመንግሥትና ቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው መስተጋብር ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን “አያገባትም፣ ገለልተኛ መሆን አለባት” ከሚለው ጀምሮ፣ ማንነቷና መልእክቷ ፖለቲካዊ ካባ እንዲለብስ ያደረጉ አመለካከቶች ይሰማሉ። እነዚህ ጠርዝ ላይ የቈሙ አመለካከቶች በብዙ መልኩ ስሑት እንደ ሆኑ እናውቃለን። በእኔ ትዝብታዊ ዕይታ ግን፣ በዶር ዐቢይ የተጀመረው የገዢው ፓርቲ የራስ-ትችትና የሕዝብ ይቅርታ የወለደው የ “መደመር” ፖለቲካ፣ እንደ ሰደድ እሳት ከመዛባቱ በፊት፣ በፍትሕ ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመረጠችው በአብዛኛው ዝምታን ነበር። አገራችን ላይ ያረበበው የክፍፍል ጽልመት ቤተ ክርስቲያንም ድባቴ ውስጥ ዘፍቋት ከርሟል።

የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የወረሰው የአገራችን የዘመናት ችግር ሦስትዮሽ ጎን አለው። አስከፊ ድኽነት፣ የፍትሕ ጥያቄ በመጨረሻም የመንግሥትን ዐቅም የተጠቀመ የተደራጀ አገራዊ ዘረፋ ነው። የሰብአዊ መብትና የሕግ የበላይነት ጥሰት፣ ለብዙ ትውልድ የሚተላለፍ የገንዘብ ዕዳ እንዲሁም አገራችንን በሰው መፈናቀል ከፍተኛ ከሆኑ አገራት ጎራ ያሰቀመጣት ለዓመታት የተዘራው ጽንፈኛ ብሔርተኝነት የጉስቁልናችን ዋና መገለጫዎች ሆነዋል። በዳዩም በፍትሕ መንበር ላይም የተሰየመውም አንድ አካል ሆኖ የከርመባት አገር እንደመሆኗ መጠን፣ ጥርጥርና ያለመተማመን ከማንነት ጥያቄ ጋር ተሰናስለው ዕንቅፋት ሆነውብናል።

በእነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስትያን ዝምታን መርጣለች፤ ቢያንስ መርጣ ከርማለች። የዚህም ምክንያቱ ፈርጀ ብዙ ነው። በታሪክ፣ “ዜግነታችን በሰማይ ነው”፤ ወይም “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል” በሚሉና በሌሎችም ከዐውዳቸው ውጭና ከቅዱሳት መጻሕፍት አጠቃላይ ምክር ተቦጭቀው የወጡ የራስ ግንዛቤ፣ ክፉ አገዛዞች ለወለዷቸው የፍሕ ጩኸቶች ቤተ ክርስቲያን ድፍን ጆሮ እንድትሰጥ አድርጓታል። ይህ የተዛነፈ አስተምህሮ ወለድ የራስ ግንዛቤ አንዳለ ሆኖ፣ ሁለት የከፉ ምክንያቶችን ማንሣት ግን የግድ ነው። አንደኛው የሞራል ልዕልና ማጣት ነው። ይኸውም መሠረቱ አገር ታማ በከረመችበት የመከፋፈል፣ የአመራርና የሥነ ምግባር ቀውስ ቤተ ክርስቲያንም መታመሷ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ በስደት ዘመንዋ (በተለይም በአስከፊው የደርግ ማርክሳዊ የክህደት አገዛዝ) ጥላ የሆነላትን የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ቸል በማለት፣ “በአምልኮ ነጻነት ስም” የመንግሥት ወሮታ እስረኛ መሆኗ የፈጠረው ዕውነትን የመጋፈጥ ዐቅመ ቢስነት ነው።

በዚህ አንጻር፣ ደርግን ፊት ለፊት በመቃወማቸው ሰማዕት ሆነው ያለፉት እንደነ ጉዲና ቱምሳ (ቢያንስ በመንግሥትና ቤተ ክርስቲያን መካከል በላው ግንኙነት) ያሉ በመከራዋ ወቅት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የመሩ አባቶቻችን ጫማቸው ሰፍቶናል! መንግሥት ዜጎቹ ላይ የአመጽ በትሩ ሲያሳርፍ፣ የፍርድ ሚዛን ሲያዛነፍ፣ የአስተዳደር በደል ሲያደርስ፣ የሕዝብን ነጻ የሆነ ፖለቲካዊ ምርጫ ብያኔ ሲክድ፣ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ያሰማውን የፍትሕ ጩኸት፣ “የሕግ ጥሰት” በሚል ፖለቲካዊ ምላሽ በኀይል ሲገዛና ንጹሕ ደም ሲያፈስ፣ ቤተ ክርስቲያን ዝም በማለት በድላለች። ይህም፣ “እርሱ [መንግሥት] ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና” (ሮሜ 13፥4) ከሚለው አምላካዊ ዐደራ ጋር ቀጥታ የሚጋጭ አካሄድ ነበር። ቤተ ክርስቲያን የግራም ሆነ የቀኝ፤ የመንግሥትም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ ልሳን አይደለችም። ወገንተኝነቷ ምንጊዜም ከአምላካዊ ፍትሕና ጽድቅ ጋር ብቻ ነው። ከፍተኛውና የላቀው ሞራላዊ ልዕልና አምላካዊ እንጂ ምድራዊ አይደለምና! የትኛውም መንግሥት፣ የዜጎቹ መልካም እረኛ በመሆን ፈንታ፣ የሰውን ከቡርነትና እኩልነት የሚረግጥ፣ አድሎአዊነትን፣ ኢፍትሐዊነትንና ግፈኝነትን የሚፈጽም ከሆነ፣ እግዚአብሔር ካሰመረለት የመልካም አገዛዝ ክልል ውጭ ወጥቶ በፍርዱ ክልል ውስጥ መግባቱ የግድ ነው።

“ፍትሕ የጎደለውን ሕግ ለሚያወጡ፣ ጭቈና የሞላበትን ሥርዐት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! የድኾችን መብት ለሚገፉ፣ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!” (ኢሳ 10፥1-2)

የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የሰላምና የሀቀኝነት ስብከት፣ የተገላቢጦሽ ሆኖ፣ ከቤተ መንግሥት ወደ ቤተ ክህነት ሆኗል! ከታች ወደ ላይ! ይህ ዐይናችንን፣ በኀፍረት እድንሰብርና ለንስሓ ካላነሣሣን ምን ተስፋ አለ? ጌታ፣ “ዐይንሽን በዕፍረት አልሰብር ብለሻል” እንደ አላት ይሁዳ ሳንሆን አልቀረንም! (ኤር 3:3)። አገርን በተመለከተ፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወድቆ በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ሰው ያለበትን ስቃይ በውል ዕያወቁ፣ ገለልተኝነትን እንደመረጡት ካህኑና ሌዋዊ ሆነናል። ለሕዝባችን የፍትሕና የሰላም ጩኸት ያሳየነውን ዘገምተኝነት፣ ተግባር የለሽ ስብከታችንን “ሰላምም ሳይኖር፣ ‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ።” (ኤር. 6፥14) እንደተበለላቸው ካህናት ስብከት አድርጎታል።

አገራዊ ንስሓ ያስፈልገናል – ከልብ የሆነ! እግዚአብሔርን ሕዛብችንንም ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባናል! ይህ ንስሓ፣ የወቅቱ “የመደመር” አጀንዳ ካመጣው ተጽእኖ የተነሣ፣ ካለው አገራዊ እንቅሰቃሴ ጋር አብሮ ለመሄድ የሚደረግ አፋዊ፣ (ለይስሙላና ለራስ መዋቅራዊ መደላደል ሳይሆን)፣ ልብንና ኩላሊትና በሚመረምር ሁሉ ቻይና ዐዋቂ በሆነ ልዑል እግዚአብሔር ፊት የሚደረግ ንስሓ ሊሆን ይገባል። እርሱ ሁሉን ያያል፤ ሁሉንም ያውቃል። አገራችን ልትከተል በወሰነችው ብሔራዊ የዕርቅ ጎዳና፣ ቤተ ክርቲያን በንስሓ የእግዚአብሔርንና የሕዝብን ሞገስ በማግኘት የሰላም ድልድይና የዕርቅ መንበር ልትሆን ይገባታል።

አቤቱ ይቅር በለን፤ በማስታረቅ ሂደት ውስጥ፣ እውነትና ምሕረት፣ ፍትሕና ጽድቅ ይገናኙ! አሜን!

የኅብረቱ ውሳኔ በአዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ ሲታይ

በቅርቡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት “አጋር አባል” ሲል የተቀበላቸውን ቤተ እምነቶችና መሪዎቻቸውን መነሻ አድርጎ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል። ጉዳዩ እስከ አሁንም የተቋጨ አይመስልም። ይህንን ተከትሎ ኅብረቱ የወሰደው ውሳኔ ከሞላ ጎደል አዲስ ኪዳናዊ አመራርን የሚከተል ሆኖ አግኝቼዋለሁ የሚሉት የሥነ አመራር መምህር የሆኑት ልደቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ

እውነተኛ አገልጋይ ማነው?

የምንኖረው እጅግ በዘመነ ትውልድ ውስጥ ነው። በዘመኑ ውስጥ በዓይናችን የምናያቸውና በልቡናችን የምናስተውላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በተለይም በብዙ አቅጣጫ ውሸተኞች ሆነው ሳሉ ነገር ግን እውነተኛውን መስለው የሚገለጡ ነገሮችን እናስተውላለን።

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢየሱስ እና የመከራ ሕይወት

በእግዚአብሔር ሕልውና የማያምኑ ሰዎች “እግዚአብሔር የለም” ለማለት በየዘመናቱ ከሚያነሧቸው ጥያቄዎች አንዱ በምድር ላይ የመከራ መኖር ነው፡፡ ʻእግዚአብሔር ቢኖር ይህ ሁሉ ጥፋት በሰዎች ላይ ለምን ይደርሳል?ʼ ይላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሰዎችም ጥያቄውን ደጋግመው ያነሡታል፡፡ ሰዎች መከራን በተለያየ መልኩ ሲጋፈጡ በእግዚአብሔር ሕልውና፣ በእግዚአብሔር መልካምነት ወይም በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ላይ ጥያቄ ይፈጠርባቸዋል፡፡ የመከራ ሕይወትና የእግዚአብሔር ሕልውና የተጋመዱ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ “እግዚአብሔር ከሌለ ይህ ሁሉ መልካም ነገር እንዴት ይኖራል? እግዚአብሔር ካለስ እንዴት ይህ ሁሉ ክፋት ይኖራል?” ሲል የጠየቀው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.