ስንት ማንዴሎች ቀርተው ይሆን?
ስንትስ ማንዴሎች ይነሡ ይሆን?
ጸሐፊ፣ ተመራማሪ እና አስተማሪ የሆነው ምኒልክ አስፋው ከሚኖርበት አሜሪካ ሆኖ ስለ ፍትሕ እና ምሕርት/ይቅርታ ባዘጋጀው ጽሑፉ የዚህ ዕትም ዋና ርእሰ ጉዳይ ጸሐፊ ሆኖ ቀርቧል። ጽሑፉ በዋናነት ከፍትሕ እና ከምሕረት የትኛው የበለጠ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመጠቆም የተሰናዳ ነው። ምኒልክ ለዚህ መነሻ የሚያደርገውም እውቁን የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሟቹ ኔልሰን ማንዴላን ነው። እንደ እርሱ እምነት ከሆነ የማንዴላ የዕርቅ መንገድ በቅራኔ ለተሞላ ኅብረተ ሰብ ዐይነተኛ ምሳሌ ነው። ትልቅነት የሚለካውም ይቅር በሚሉና ምሕረት በሚያደርጉ ሰዎች የሕይወት ፈለግ መሆኑንም ይሞግታል።
ከሁለት ዓመት በፊት መምህሬ “ልትጽፍ ያሰብከው በማንኛው ዘመንተኛ መሪ ላይ ነው?” ሲለኝ መልሴ ፈጣን ነበር፤ “ልጽፍ ያሰብኩት በኔልሰን ማንዴላ ላይ ነው” አልኩት። የአፍሪካ ልጅ ስለሆንሁ ወይም ለማንዴላ ትልቅ አክብሮት ስላለኝ ሊሆን ይችላል እንዲያ ፈጣን መልስ የሰጠሁት፤ ወይም “Long Walk to Freedom: The Autobiography of Nelson Mandela” የተሰኘውን መጽሐፍ ከዓመታት በፊት በአንድ ወዳጄ አሳሳቢነት የተወሰነውን ክፍል ስላነበብሁም ሊሆን ይችላል። ብቻ የማንዴላን ሕይወት፣ አመራርና በልዩ ልዩ መከራ ውስጥ የተፈተነውን ተመክሮ ለዘመንተኛው ትውልድ ካለው ፋይዳ አንጻር ለማጤን ማሰቤ መምህሬን አስደሰተው፤ እርሱም በአንድ ወገን በአባቱ የአፍሪካ ልጅ ኖሮ “በእኚህ ድንቅ ሰው ላይ የምትጽፈውን ለማንበብ በጉጉት እጠብቃለሁ” ብሎኝ ሄደ።
ዓለማችን ብዙ ዐይነት ሰዎች አስተናግዳለች። ከስመ ጥሩዎቹ ከግሪክ ፈላስፎች ጀምሮ እስከ ነጻነት ዐርበኞቹ የአፍሪካና የላቲንና አሜሪካ ልጆች ድረስ በርካታ ታላላቅ ሰዎች ተነሥተው አልፈዋል። ለሰው ልጆች ሰላም፣ ነጻነትና እኩልነት የታገሉ እንደ ነበሩ ሁሉ ባንጻሩም በሰዎች ሰብእና ተሳልቀው ያለፉ ብዙዎች ናቸው። ለዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለፍትሕና ለአገር አንድነት ብዙ ዋጋ የከፈሉ እንደ ነበሩ ሁሉ፣ ባንጻሩም ዓለምን አቀውጠው ምድርን አሰልችተው ያለፉ ብዙዎች ናቸው። አንዳንዶች ለዓለም አበሳና ፈተና ሲሆኑ ሌሎች ለዓለም ችግር መልካም መፍትሔ ሰጥተው አልፈዋል። ከእነዚያ ለዓለም መልካም መፍትሔ ከሰጡ ሰዎች መካከል አንዱ ኔልሰን ማንዴላ ናቸው።
ለመምህሬ ማስረከብ በነበረብኝ ጽሑፍ ልፋለመው የሚገባኝ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ነበር። ይኸውም ኔልሰን ማንዴላ ከምንም በላይ የሚታወቁት በየትኛው ተግባራቸው ነው?[i] በፍትሕና በነጻነት ዐርበኝነታቸው ወይስ በእርቅና በሰላም አባትነታቸው? ማንዴላን አስመልክቶ የሚጽፉ ሰዎች በሙሉ ከዚህ ወሳኝ ጥያቄ ጋር መፋለማቸው አይቀርም። አንዳንዶች የመጀመሪያውን ደግፈው ሲጽፉ ሌሎች ሁለተኛውን ደግፈው ጽፈዋል። የማንዴላ ስም ከሁለቱም ጋር ተያይዞ መጠራት አለበት የሚሉም ወገኖች አልጠፉም። እኔ ግን ሁለተኛውን አስተያየት እደግፋለሁ – ምንም እንኳ የመጀመሪያውም የማንዴላ ትግል አካል ቢሆንም። ማንዴላን ከምንም በላይ ስመ ጥር የሚያደርጋቸው የእርቅና የሰላም አባት መሆናቸው ነው፤ እኔ ኔልሰን ማንዴላን የምመለከታቸው እንደ ላቲን አሜሪካውያኑ እንደ ጉስታቮ ጉቲዬሬዝ፣ ኦስካር ሮሜሮና ሌኦናርዶ ባፍ ወይም እንደ ሰሜን አሜሪካኑ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው፤ እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል ለፍትሕና ለነጻነት በሌላ በኩል ደግሞ ለሰላምና ለእቅር ይፋለሙ ነበር። ሆኖም ከሁሉ በላይ ነገራቸውን ያስተሳሰሩት ከጭቁኖችና ፍትሕ ከተነፈጉ ድኾች ጋር ነበር። የድኾች መጨቆን፣ መረገጥና ከምድራዊ ትሩፋት ሁሉ መወገድ ከምንም በላይ ያስጨንቃቸው፣ ያበሳጫቸውና ያስቆጣቸው ነበር። ሰው ማለት እንግዲህ ለሰዎች ነጻነትና እኩልነት የሚፋለም ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ዕርቀ ሰላምም የሚታገል ነው። ስለ ነጻነት የሚታገል ሰው ስለ ሰላምም መታገል አለበት። ስለ ፍትሕ የሚፋለም ሰው ስለ እርቅም መፋለም አለበት። እንዲያውም የመጀመሪያው ማለትም ነጻነትና ፍትሕ በሁለተኛው ማለትም በሰላምና በእርቅ ሲገራ ነው የሕይወት ስምረት የሚኖረው። ለዚህ አባባል ምክንያቶቼንና ሙግቶቼን ከኔልሰን ማንዴላና ከሚሮስላቭ ቮልፍ ጋር እያናጸርሁና እያመሳከርሁ ለማቅረብ እሞክራለሁ፤ የጽሑፌ ዐቢይ ዓላማ ክርስቲያኖች የፍትሕና የእኩልነት ጒዳይ ሊያሳስባቸው እንደሚገባ ማስገንዘብ ቢሆንም እኩይ ሥርዐተ ማኅበሮችን መፋለምም ክርስቲያኖች የተጠሩበት ዓላማ እንደ ሆነ ማስገንዘብ ነው።
በመጀመሪያ የማንዴላን ሕይወት ባጭሩ እንቃኝ። ኔልሰን ማንዴላ ሐምሌ 18 ቀን፣ 1918 ዓ.ም. ከኬፕታውን በስተ ምሥራቅ 80 ማይል ርቃ በምትገኘው ምቬዞ በምትባል ስፍራ ተወለዱ። እንደ ብዙ ልጆች ሁሉ የማንዴላም ሕይወት በአካባቢያቸው ባህል፣ ልማድና ወግ የተገራ ነበር። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ትምህርት ቤት ተላኩ፤ ጥቂት ቆይቶም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአንድ የሜተዲስት ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ተከታተሉ። የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር በትውልዱ እንግሊዛዊ ሲሆን፣ በዘሩና በቆዳው ቀለም በጣም የሚኩራራ ነጭ ነበር። ማንዴላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደ ጨረሱ ወደ ጆሃንስበርግ በመሄድ ከዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀበሉ። ማንዴላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘረኛነት እርኩስ መንፈስ ጋር መፋለም የጀመሩትም ወደ ጆሃንስበር ከመጡ በኋላ ነበር። እርግጥ በወቅቱ የማንዴላን ሕይወት አቅጣጫ የሚተልም ምንም ነገር አልነበረም። ማንዴላ ሁሉንም ነገር በሙከራ መማር ነበረባቸው። ወደ አይቀሬው ትግል እንዴት እንደ ገቡ “Long Walk to Freedom” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ሲገልጹ “ወደዚህ ፍልሚያ የተቀላቀልሁት ልዩ መገለጥ አግኝቼ ወይም ልዩ አስተርእዮ ተቀብዬ አይደለም፤ ወደዚህ ፍልሚያ የተቀላቀልሁት በወገኖቼ ላይ የሚደርሰው ግፍ አስቆጥቶኝ ነው፤ እናም በውስጤ የተንቀለቀለው ቊጣ ወገኖቼን ጠፍሮ ከያዛቸው ባርነት ለመታደግ አነሣሣኝ፤ ሥርዐቱንም ለመፋለም ገፋፋኝ” ይላሉ።
ማንዴላ የANC (African National Congress) አባል በመሆን የትግሉን ፍልሚያ ቀጠሉ።[ii] ጥቂት ቆይቶም ማንዴላና ሌሎች በሥርዐቱ ግፍ የበገኑ የነጻነት ዐርበኞች በANC ጥላ ሥር የሚንቀሳቀስ የወጣቶች ሊግ አቋቁመው ትግሉን ይበልጥ አጦዙት። ሆኖም የአፓርታይድ ሥርዐት እንዲህ ዐይነቱን ዐመፅ ሊታገሥ አልቻለም። ቀንደኛ የሚባሉ የንቅናቄውን አባላት ወህኒ መወርወርና መግደል የዕለት ተዕለት ተግበሩ አደረገ። ይህ አፈናና ግድያ ብርቱ ክንዱን በእነ ማንዴላም ላይ ሰነዘረ። ማንዴላ በ1962 ዓ.ም. በአገር ክህደት ክሥ ተወንጅለው ዕድሜ ይፍታ ተፈረደባቸው። ሥርዐቱም እነ ማንዴላን ወህኒ በመወርወርና በመከርቸም የነጻነት ዐመፁን ለጊዜውም ቢሆን የደቆሰና የቀለበሰ መሰለ። ሆኖም በሌሎች አገሮች እንደታየው ሁሉ በደቡብ አፍሪካም የተረጋገጠው ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ሰዎችን በማሰርና ከትግሉ ሜዳ በማግለል ማዳፈን አይቻልም። ማንዴላ በታሰሩ ማግሥት ትግሉ ይበልጥ ተፋፋመ።
ምንም እንኳ ማንዴላ አካላቸው ቢታሰርም መንፈሳቸውና ኅሊናቸው ግን አልታሰረም ነበር። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በሮቢን ደሴት የታሰሩት ማንዴላ በአንድ በኩል የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ሲያውጠነጥኑ በሌላ በኩል ደግሞ በነጻነቱ ማግሥት ሊፈጠር የሚችለውን ብጥብጥ (አንዳንድ ሠነዶች እንደሚጠቁሙት የእርስ በእርስ ፍጅት) እንዴት መግታት እንደሚቻል ያብሰለስሉ ነበር። ማንዴላ ወህኒ ከመወርወራቸውና ከብረት አጥር በስተጀርባ ከመከርቸማቸው በፊት አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። “የነጮችን ጭቆና እፋለማለሁ፤ የጥቁሮችንም ጭቆና እፋለማለሁ፤ ጸንቼ የምቆመው ሰዎች ሁሉ በእኩልነት ለሚተዳደሩበት ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ነው፤ ለዚህ ፋይዳ ነው ካስፈለገም ሕይወቴን የምሰጠው”። ማንዴላ ታስረው ሳለም ከዚህ ጽኑ አቋም ከቶ ንቅንቅ አላሉም። ይልቁንም ይህ አቋም መሥራት አለመሥራቱን በዚያች ጠባብ ወህኒ ቤት ውስጥ ይፈትኑ ነበር። የሮቢን ደሴት ለማንዴላ ቤተ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል። ለደቡብ አፍሪካ የሚበጃት የትኛው መንገድ ነው – የብቀላው ወይስ የይቅርታው መንገድ? ጥላቻን በጥላቻ፣ ዘረኛነትንም በዘረኛነት መመለስ ወይስ ይቅር መባባል? እንግዲህ ማንዴላ ወደፊት ለሚጠብቃቸው ብርቱ ጥሪ መዘጋጀት የጀመሩት በሮቢን ደሴት ነው ማለት ይቻላል።
ከብዙ ውትወታና ጩኸት በኋላ ማንዴላ ከእስር ሲፈቱ የ71 ዓመት አዛውንት ነበሩ። የሕይወታቸውን አንድ አራተኛ ወህኒ ቤት አሳልፈው ሲወጡ በቀልን ሳይሆን እርቅን የትግላቸው መርሕ/ፋይዳ አድርገው ወጡ። መላው ዓለምም “እኚህን ሰው ለዚህ ያበቃቸው ምስጢር ምንድን ነው?” በማለት መጠየቅና መደነቅ ነበረበት። ከቶ ማንዴላን ምን ለወጣቸው? ብዙዎች የጠበቁትን ብቀላ ሳይሆን የዚያን ተቃራኒ መንገድ እንዲመርጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ሰይፍን ሳይሆን ይቅርታን እንዴት ሊያነሡ ቻሉ? እና እንግዲህ በብዙ የለውጥ ሐዋርያት ሕይወት እንደ ተመሰከረው ምርጥ ሰብእና የሚፈጠረው ከአሳዛኝ መከራ (tragedy) ሳይሆን አይቀርም በማለት መደምደም ሊኖርብን ነው። ደግሞም ከአሳዛኝ መከራ ተምሮ ለሌላ የመከራ ዑደት ምክንያት አለመሆን ትልቅ አስተዋይነት ነው። በቀለኛነትም ሆነ ደም መላሽነትና ብድር ከፋይነት ሌላ የብቀላ ዑደት ከመፍጠር በቀር ምንም አይፈይዱም። እንዲያውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ክፉ ነቀርሳ ይሆናሉ።
ማንዴላ በቀልና ደም መላሽነት ደቡብ አፍሪካን ድምጥማጧን እንደሚያጠፋት በትክክል ተገንዝበዋል። ከበቀሉ ጎዳና ይልቅ የእርቁና የይቅርታው ጎዳና ይሻላል በማለት ባይሞግቱ ኖሮ አሁን የምናውቃት ደቡብ አፍሪካ ባልተገኘችም ነበር። እርግጥ ነው አፓርታይድ በደቡብ አፍሪካውያን በተለይም በነጮችና በጥቁሮች መካከል ብርቱ ጥላቻ እንዲሰፍን አድርጓል። የደቡብ አፍሪካን ጥቁሮች ከልክ በላይ አዋርዷል፤ ሰብእናቸውን አራክሷል። በአጭሩ በዘረኛነት ላይ የተመሠረተ ሥርዐተ ማኅበር እንዲንሰራፋ አድርጓል። ሰዎች የቆዳቸው ቀለም ጥቁር በመሆኑ ብቻ ተንቀዋል፤ እንደ ምናምንቴ ተቈጥረዋል። ጥቁሮች በገዛ አገራቸው ቁም ስቅላቸውን አይተዋል። ጭቆናው አንሶ አፈናውና ጭፍጨፋው መድረሻ አሳጥቷቸዋል። እናም ለደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ነጭ ማለት “ነፍሰ በላ ጨካኝ አውሬ ነው። ነጮች የሰይጣን ቁራጮች ናቸው፤ ነጮች ጣረ ሞት ናቸው። እናም ጥቁሮችን ቁም ስቅል እንዳሳዩ እነርሱም ቁም ስቅላቸውን ማየት አለባቸው፤ የክፉ ብድራታቸውን መቀበል አለባቸው፤ ለእነርሱ የሚገባውም ሞት ብቻ ነው” የሚል በቀለኛነት በመላው ደቡብ አፍሪካ አስተጋባ።
ኔልሰን ማንዴላ ሰው አንደ መሆናቸው መጠን ይህ ሌሎችን የወረሰው የበቀለኛነት መንፈስ እርሳቸውንም መውረስ ነበረበት፤ ነገር ግን በማንዴላ ሕይወት የተመለከትነው ይህን አይደለም። ማንዴላ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ እስር ቤት መከራ ቢቀበሉም መከራው ግን አንድ ወሳኝ ነገር አስተምሯቸዋል፤ ይኸውም በቀል ለማንም የማይጠቅም መሆኑን። ይልቁንም በቀል አገር ያጠፋል፤ ሕዝብ ይደመስሳል፤ ትውልድ ይጨርሳል። የሚሻለው ብቀላ ሳይሆን ይቅር መባባል ነው። ከዚህ ውጭ ተስፋም ሆነ መልካም መጻኢ ዕድል የለም። በእውነተኛው የማንዴላ አስተሳሰብ የተከረከመውና አዲስ መልክ የተላበሰው እስር ቤት ነው የሚሉ ወገኖች ትክክል ብለዋል። ማንዴላ በዚያች የሮቢን ደሴት እስር ቤት ውስጥ ጧትና ማታ የሚያሰላስሉት አገራቸው ደቡብ አፍሪካ ከእርስ በእርስ ፍጅት ልትድን የምትችለው የትኛውን መንገድ ብትከተል ነው? የሚለውን ነበር። ጥቁሩ በነጩ እንደ ተበላ ነጩም በጥቁሩ መበላት አለበት? ጥቁሩ በነጩ እንደ ተተለተለ ነጩም በጥቁሩ መተልተል አለበት? ጥቁሩ በነጩ እንደ ተጨፈጨፈ ነጩም በጥቁሩ መጨፍጨፍ አለበት? ጥቁሩ በነጩ እንደ ተወገደ ነጩም በጥቁሩ መወገድ አለበት? ከቶ ደቡብ አፍሪካን የሚታደጋት የትኛው አማራጭ ነው? በቀለኛነት ወይስ ይቅር ባይነት?
ማንዴላ ተራው የጥቁሩ ከሆነ አገር ሊደመሰስ ትውልድም ሊጠፋ እንደሚችል በሚገባ ተረድተዋል። ይህም ውሎ አድሮ ሌላ አካይስታዊ ዑደት እንደሚፈጥር አስተውለዋል። እንደ ማንዴላ ሁሉ ተራው የጥቁሩ መሆን የለበትም በማለት በብርቱ ከተሟገቱ ወገኖች መካከል አንዱ ሊቀ ጳጳስ ዴስሞን ቱቱ ናቸው። እንዲያውም ማንዴላ ከእስር ተፈትተው የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዘዳንት ሲሆኑ “የእርቅና የሰላም ተቋሙን” በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተደረጉት ቱቱ ነበሩ።[iii] እንደ ማንዴላ ሁሉ ቱቱም “ያለ ይቅርታ ተስፋ የለንም” የሚል ብርቱ አቋም ነበራቸው። እርግጥ እንደ ሰው ሲታሰብ ተራው የጥቁሩ መሆን ነበረበት። ይሁንና በቀል እማንዴላ ቀመርና ሒሳብ ውስጥ ስፍራ አልነበረውም። የደቡብ አፍሪካ መጻኢ ዕድል ፈንታ የተመሠረተው በዕርቀ ሰላሙ መንገድ ላይ ብቻ ነበር። ምንም እንኳ ብዙዎች በማንዴላና በቱቱ አቋም ደስ ባይሰኙም (የብዙዎች አቋም “ደም መመለስ፣ ብድርም መከፈል አለበት” የሚል ስለ ነበር) ማንዴላና ቱቱ ግን ብቀላ ምርጡ መንገድ እንዳልሆነ አስተውለዋል። ፍጹም ነጻነት በብቀላ አይገኝም ነው የማንዴላና የቱቱ ሙግት። እንግዲህ ማንዴላ ለበቀል ዕድል ፈንታ ባለመስጠት ሕዝቦች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ ምርጥ ጎዳና ለዘመንተኛው ትውልድ አመላከቱ ማለት ይቻላል። እንደ ማንዴላ እምነት ጥላቻ ጥላቻን ይወልዳል፤ ጥፋተኛን መቅጣትና ፍዳውን መስጠት ይቻል ይሆናል፤ ይህ ግን ምርጡ መንገድ አይደለም። ምርጡ መንገድ ይቅርታ ነው። እውነተኛ ሰላም ከበቀል ጋር አንዳች ዝምድና የለውም። እንዲያውም ሰላም የእርቅ እንጂ የበቀል ልጅ አይደለችም።
ኢማኑኤል ካታንጎሌ እና ክሪስ ራይስ Reconciling All Things: A Christian Vision for Justice, Peace and Healing በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “ማንዴላ በእስር ቤት ሳሉ አዲስ ማንነት ተላብሰው ነበር” ይላሉ። ይህም አዲስ ማንነት የማይታየውን ተስፋ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ማንነት ነበር። ምንም እንኳ ማንዴላ በእስር ላይ ቢሆኑም፣ በቅርቡም ከእስር ተፈትቼ ነጻ እወጣለሁ የሚል ተስፋ ባይኖራቸውም የሚኖሩት ግን እንደ ነጻ ሰው ነበር፤ “ማንዴላ እርሳቸውና ለእስር የዳረጓቸው ነጮች በአንድነት በአዲሲቷ ደቡብ አፍሪካ ሲኖሩ ይታያቸው ነበር”።[iv] ይህ እጅግ አስገራሚ እይታ ነው። ማንዴላ በጨለማ ውስጥ ብርሃናዊ ሕይወት ይኖሩ ነበር ማለት ነው። አስተሳሰባቸው የተቀረጸው ባልጨበጡትና ከቶ ባላዩት ነገር ነበር። ይህም ምናልባት የዕብራውያን ጸሐፊ ስለ እምነት ዐርበኞች ከተናገረው ነገር ጋር ሳይዛመድ አይቀርም። እነዚያ የእምነት ዐርበኞች ያን ሁሉ መከራ ሲቀበሉ “ስለማይታየው ነገር ተረድተው ነበር”። ደግሞም “የሚሻልን አገር” ተስፋ አድርገው ነበር (ዕብ. 11)። ማንዴላም በመከራ ውስጥ ሆነው የተሻለ አገር ያልሙ ነበር። የማንዴላ ግለ ታሪክ እንደሚመሰክረው ማንዴላ ስለ ክርስቲያናዊው ተስፋ ጥልቅ መረዳት ነበራቸው። ራሳቸውንም የሚመለከቱት ከውድቀቱ እንደሚማር እንደ ትጉ ክርስቲያን ነበር። ለማንዴላ ክርስቶስ ሊከተሉት የሚገባ ፍጹም ምሳሌ ነው። በክርስቶስ ዘንድ ዐመፅ (በቀል) ከሌለ በተከታዮቹም ዘንድ ዐመፅ (በቀል) ሊኖር አይገባም ነው ሙግታቸው። እናም በሰይፍ ትግል ከምንፈልገው ፍጹም ግብ መድረስ አይቻልም። በዚህ ረገድ ማንዴላ እንደ መሃተመ ጋንዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ ፍጹም “ሰላመኛ” ነበሩ ማለት ነው። በማንዴላ አስተያየት “ከይቅርታ ፖለቲካ” ውጭ ወይም በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀው “ከደቡብ አፍሪካው ተኣምር” ውጭ በደቡብ አፍሪካ እውነተኛው ብርሃን ሊታይ አይቻልም።[v] በሌላ አባባል ያለ ይቅርታና እርቅ (forgiveness and reconciliation) በዳይና ተበዳይ ዝንታለም ትምምን በሌለበት አድማስ እንዲኖሩ ያደርጋል፤ ማለትም በዳይና ተበዳይ በበቀል ዑደት ውስጥ እንዲዳክሩ ያደርጋል። በቀል መጨረሻና መቋጫ ከሌለው፣ ዑደቱ ዝንታለም ይቀጥላል። ተረኛው በዳይ ወይም ተረኛው ተበዳይ ማን እንደ ሆነ ማንም የሚያውቅ የለም። ማን ያውቃል በሌሎች ስፍራዎች እንደታየው ሥልጣን የጨበጡ ተበዳዮች እነርሱ ራሳቸው በዳይ ሆነው ተገኝተዋል። ʻኧረ የሰማይና የምድር ጌታ እንዲህ ከሰውነት ተራ ሲያወጡን ዝም አትበል!ʼ በማለት ወደ ላይ የጮኹና የቃተቱ እነርሱ ራሳቸው ሌሎችን አበሳና ፍዳ አሳይተዋል። ታዲያ የሚሻለው ምንድን ነው? ግፍንና በደልን ቈጥሮ መበቀል? ብድሩን መክፈል? ደም መመለስ? ፍዳውን መስጠት? ወይስ ለማንዴላ የበራውን የዕርቀ ሰላም ብርሃን መከተል?
እዚህ ላይ ነገሩን ይበልጥ ለመመርመርና ለጥያቄዎቹም መልስ ለመስጠት ይረዳን ዘንድ ወደ ሚሮስላቭ ቮልፍ ትንተና ማቅናት ይኖርብናል። እንደ ማንዴላ ሁሉ ቮልፍም በእኩይ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ አልፏል። የክሮሻ ተወላጅ እንደ መሆኑ እነዚያ ጨካኝ ሰርቦች በአገሩ ዜጎች ላይ የሚያደርሱትን በደል በገዛ ዐይኑ ተመልክቷል። እርሱም ራሱ ቢሆን ከሰርቦች እጅ በተኣምር ነው ያመለጠው። ቮልፍ ሁኔታውን ሲተርክ “ሰዎችን ያንገላቱ ነበር፤ ሴቶችን ይደፍሩ ነበር፤ አብያተ ክርስቲያናትን ያቃጥሉ ነበር፤ ከተሞችን ያወድሙ ነበር” ካለ በኋላ ታዲያ “እንደዚህ ዐይነት ሰዎችን የምቀበለው እንዴት ነው? እንደዚህ ዐይነት ሰዎችንስ ለመቀበል ኀይል የምናገኘው ከየት ነው?” በማለት ይጠይቃል። ቮልፍ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ አንዱ እግዚአብሔር ከተለመው መንገድ ውጭ ሌላ የተሻለ ምርጥ መንገድ የለም ይላል። እግዚአብሔር ዐመፀኛ ሰዎችን የተቀበለበት መንገድ እኛም እንደ ጠላት የምንመለከታቸውን ሰዎች እጃችንን ዘርግተን ለመቀበል ምሳሌአችን መሆን አለበት። በቮልፍ እምነት ይህ እግዚአብሔር ሰዎችን የተቀበለበት መንገድ “ጠፍቶ በተገኘው ልጅ” ምሳሌ በሚገባ ተገልጧል (ሉቃ. 15፥11-32)። ደግሞም Exclusion and Embrace: A Theological Exploration of Identity, Otherness, and Reconciliation በተሰኘው መጽሐፉ እንዳብራራው አባት የወሰደው እርምጃ ፍትሐዊ ቢሆን ኖሮ የጠፋው ልጅ ለመመለስና ከቤተ ሰቡ ጋር ዳግመኛ ለመቀላቀል ዕድል ባላገኘም ነበር። አባት ለዚያ አባካኝ ልጁ ተገቢውን ቅጣት አልሰጠም፤ ይልቁንም ይቅር ብሎ ተቀበለው። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ባሕርይ በትክክል የሚያንጸባርቀው ፍትሕ ሳይሆን ይቅርታ ነው። እንዲህ ሲባል ግን እግዚአብሔር ለፍትሕ ግድ የለውም ማለት አይደለም። ነገር ግን ፍትሕ በላቀው እሴት ወይም ፋይዳ መገራት አለበት፤ ማለት ፍትሕ በይቅርታና በፍቅር መገራት አለበት። የእግዚአብሔር ፍትሕና ይቅርታ (ቅን ፍርድና ፍቅር) እርስ በእርስ የተሳሰሩ ቢሆኑም የሚቀናቀኑ አይደሉም። አንዱ የሚልቀውን ተግባር ለመፈጸም ለሌላው ስፍራ ይለቃል።
እርግጥ ቮልፍ በይቅርታና በፍትሕ መካከል ሲራመድ በመካከላቸው ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጓል። ይቅርታ ፍትሕን አይደመስስም፤ ይሁንና ይቅርታ የፍትሕን ብይን (ጥያቄ) መሥዋዕት በመሆን ይመልሳል። እናም ቮልፍ ይህን እውነታ የሚያዛምደው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከፈጸመው ምሳሌያዊ ተግባር ጋር ነው። ይቅርታ ምን ያህል ብርቱ ዋጋ እንደሚያስከፍል በትክክል የሚያሳየን መስቀሉ ነው። ይቅር የሚሉ ሁሉ በእርግጥ ይጎዳሉ። ባንጻሩም ይቅር የሚሉ ሁሉ በፍትሕ ይታረዳሉ። በመሆኑም ፍትሕ እንዲሰፍን የሚጋደሉ ሁሉ ይቅርታም እንዲበዛ ካልተጋደሉ ራሱ ፍትሕ የምንለው ነገር ትርጉም ያጣል። ለዚህ ሁሉ መሠረቱ ግን ሥቁሉ ክርስቶስ ነው። ሚሮስላቭ ቮልፍ እንደሚለው “በቀል በቀልን ይወልዳል”፤ በሌላ አነጋገር የበቀል ዑደት ሊደመሰስ የሚችለው በቀል የሚፈልገውን እንዲያገኝ በመፍቀድና ለበቀል እጅ በመስጠት ሳይሆን በቀል የሚፈልገው እንዳይፈጽም በመከልከል ነው። አንድ በቀል ባለበት ሌሎች ዐሥር በቀሎች ይወለዳሉ። በቀል መቀለብ የለበትም፤ አልያ ሰብቶ ድራሻችንን ያጠፋዋል፤ ይልቁንም በቀል በራብ መጠግረር ነው ያለበት፤ የበቀል ዑደት እየበዛና እየሰፋ ከሄደ መጨረሻው እርስ በእርስ መጠፋፋት ነው። ለማንዴላ የበራው እንግዲህ ይህ ብርሃን ነበር። ቮልፍ ስለ በቀልና መዘዙ ሲያወሳ ስለ ፍትሕም አውስቷል። እንደ ቮልፍ አባባል ለፍትሕ መቆም ተገቢ ነው፤ ማለት አጥፊዎች መቀጣት አለባቸው፤ በዳይ መካስ አለበት፤ ተበዳይም መካስ አለበት፤[vi] ይሁንና ለፍትሕ የምንጋደለውን ያህል ለይቅርታም መጋደል አለብን። በቮልፍ አስተያየት ፍትሕ በይቅርታ ካልተገራ ፍጹም ፈውስ አያመጣም። እንዲያውም የበቀል ዑደት ፍጹም ሙሉ በሙሉ የሚደመሰሰው በፍትሕ ሳይሆን በይቅርታ ነው። ይቅር ስንል ያን ጊዜ ሙሉ ፈውስ እናገኛለን። ይቅር ስንል የበቀልን ዑደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንሰባብራለን። እዚህ ላይ የቮልፍ ውትወታ “አጥፊዎች ሁልጊዜ መቀጣት አለባቸው ወይ?” ከሚለው ጥያቄ ጋር እንድንፋለም ነው። አጥፊዎች ሁልጊዜ ቢቀጡ ድምር ውጤቱ ምን ይሆናል? በቅርቡ በእኔ ሕይወት የደረሰ አንድ አብነት ልጥቀስ።
ከጧቱ 1:30AM (ከሌሊቱ 7:30) ላይ ከሥራ ወደ ቤቴ ስመለስ እሰፈሬ መዳረሻ ላይ ያለ አንድ የትራፊክ መብራት አስቆመኝ። ልክ እንደ እኔ ሌሎችም መኪኖች ቆሙ። እዚያው በቆምንበት ሁለት ደቂቃ አለፈ፤ አራት ደቂቃ አለፈ፤ አንዳንድ መኪኖች የትራፊክ መብራቱ ተበላሽቷል በሚል ቀይ መብራት እንደ በራ ጥሰው ሄዱ። ስድስት ደቂቃ አለፈ፤ ስምንት ደቂቃ አለፈ። አንደኛው መኪና ቀይ መብራት እንደ በራ ጥሼ ከምሄድ በሚል ወደ ኋላ እየነዳ ሄዶ በሚቀጥለው መታጠፊያ ሸመጠጠ። ይህን ያደረገው እዚያ ትራፊክ መብራት ላይ ቀይ መብራት እንደበራ ጥሰው የሚሄዱ ሰዎችን የሚቀርጽ “የቀይ መብራት ጣሾች” ካሜራ ስላለ ነው። እኔም ልክ ወደኋላ እየነዳ እንደሄደው ሰውዬ ወደኋላ እየነዳሁ በመሄድ በሚቀጥለው መንገድ ጉዞ ጀመርሁ። ጥቂት እንደ ነዳሁ (ምናልባት 20 እርምጃ) ባለ ሁለት ትራፊክ መተላለፊያ መንገድ ላይ እየተጓዝሁ መሆኔን ሳውቅ ወዲያው ወደ ትክክለኛው ጎዳና ገባሁ። ለካስ ይህን ሁሉ ቆማ (አድፍጣ ብል ይቀላል) የምትከታተል አንዲት ፖሊስ ከኋላችን ነበረች። ፖሊሷ እየጋለበች መጥታ እኔን አስቆመችኝና “የምትነዳው ለአንተ ባልተፈቀደ መንገድ ላይ መሆኑን ታውቃለህ?” አለችን። አዎ አውቄአለሁ፤ ስሕተቴንም ተረድቼ ያው እንደምታዪኝ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ገባሁ አልኳት። “ወደ ጥግ ቁምና መንጃ ፈቃድህን ስጠኝ” አለችን። ወደ ጥግ ቆሜ መንጃ ፈቃዴን ሰጠኋት። ከ20 ደቂቃ በኋላ ተመለሰችና “እዚህ ቲኬት ላይ ፈርም” አለችኝ። የሆነውን ሁሉ ላስረዳት ሞከርሁ። “ስሚ ወደኋላ እየነዳሁ የመጣሁት ያስቆመኝ የትራፊክ መብራት ስለማይሠራና እዚያ ትራፊክ መብራት ላይ መኪኖችን የሚቀርጽ የቀይ መብራት ካሜራ ስላለ ነው። በዚህ ላይ ሥራ ውዬ ደክሞኝ ወደ ቤት ለመድረስ ቸኩያለሁ። ትራፊክ መብራቱ ላይ ወደ 10 ደቂቃ ያህል በመቆሜ ተበሳጭቻለሁ። ጥፋቴንም እንደተገነዘብሁ ወዲያው አርሜአለሁ። ሆነ ብዬ ያጠፋሁ ሰው አይደለሁም። እንደምታዪው አንድም ቀን የትራፊክ ወንጀል ፈጽሜ አላውቅም፤ በዚህ ላይ ሰው ይሳሳታል፤ ሁላችንም እንሳሳታለን፤ ቁም ነገሩ ጥፋትን ተገንዝቦ ከማረሙ ላይ ነው” አልኳት። የፖሊሷ አሳብ ያለው እኔን ከመቅጣቱ ላይ እንጂ የእኔን ሁኔታ ከመረዳቱ ላይ አልነበረም። እንዲያውም የእኔ ሁኔታ ለእርሷ ምኗም አልነበረም። እኔን በመቅጣቷም ደስ የተሰኘች ይመስላል።
ወዲያው ወደ ኅሊናዬ የመጣው የፍትሕና የይቅርታ ጒዳይ ነበር። ፍትሕ ለይቅርታ ስፍራ ከሌለው ሕግና ፍትሕ አስፈጻሚዎችን ከሰውነት ተራ ያወጣል እንዴ? የሚል ጥያቄም ተፈጠረብኝ። ፖሊሷን ምን ደንታ ቢስ አደረጋት? አመዛዛኝ ኅሊናዋን ምን ሰለበው? ማለት ምን “አቃወሳት/አቀወሳት?” የምለውን እንዳትሰማ ጆሮዋን ምን ደፈነው?[vii] እርግጥ አንዳንዶች እንደሚሉት ፖሊሶች ምንም ሥራ የላቸውም፤ ሥራቸው አውቆም ሆነ ሳያውቅ የተገኘን ጥፋተኛ መቅጣት ብቻ ነው። ደመወዝ የሚከፈላቸውም ሆነ ከተሞች ለአንዳንድ ወጪያቸው ገቢ የሚያገኙት በከፊል ከቅጣት ከሚገኝ ገንዘብ ነው። ፖሊሷ የተበላሸውን የትራፊክ መብራት ሄዳ ማየት ትችል ነበር፤ ወደኋላ እየነዳሁ የመጣሁትና እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባሁት ወንጀል ለመሥራት ፈልጌ እንዳልሆነ ከሁኔታዬ በሚገባ ተረድታለች። ስሕተቴንም ተገንዝቤ ጥፋተኛነቴን ተቀብያለሁ። ምሕረት እንዲደረግልኝም ለምኛለሁ – የቊራ ጩኸት ሆነ እንጂ!። በዚያ ውድቅት ሌሊት የሚቀጣ ሰው ስለጣለላት “አምላኳን” ለማመስገን ምክንያት ሆኜላት ይሆን?! እናም “ፍትሕ በይቅርታና በምሕረት ካልተገራ ተመልሶ ብርቱ መጨቆኛ ይሆናል” የሚለው አባባል የገባኝ ይሄኔ ነው። በፖሊሷ እጅ ሥልጣንና ፍትሕ ነበር። ሥልጣኑና ፍትሑ ግን ምስኪን ጥፋተኛን ለመቅጣት በዚህም ፍዳውን ለማሳየት ብቻ ዋለ (ከ122 ዳለር ቅጣት በተጨማሪ ገና የፍርድ ቤት ቀጠሮ ይጠብቀኛል፤ መንጃ ፈቃዴን ለመንጠቅ ይሁን ወይም ሌላ ቊርጡ ባይታወቅም)። ሥልጣንና ፍትሕ በእርግጥ በእኔ ሕይወት መጨቈኛ፣ ፍዳ አበሳ ማሳያ ሆነው አየሁ። በፖሊሷና በሥርዐቱ እምነት ፍትሕ ባለማወቅ ላጠፋ ሰው እንኳ ምሕረት አያደርግም። የፍትሕ ሥራ ሰዎችን ሁሉ ልክ ልካቸውን ማስገባት ነው፤ በጥሩ አገላለጽ “ጥፋተኛን መበቀል” ነው። ፖሊሷ (ወይም ሥርዕቱ) አሰፍነዋለሁ የሚሉት ፍትሕ ግን በይቅርታና በምሕረት ቢገራ ኖሮ በመካከላችን ሰላም በተፈጠረ ነበር። አሁን በእኔና በፖሊሷ (እንዲሁም በሥርዐቱ) መካከል ትምምንም ሆነ ቅብብል የለም። አስተሳሰቤን የሚገራ ሌላ የላቀ እሴት ስላለኝ እንጂ እርሷንም ሆነ ሥርዐቱን በጠላትነት ጎራ ከመፈረጅ ምንም የሚያግደኝ ነገር አይኖርም።[viii] የዚህ ሁሉ ድምር ውጤቱ ታዲያ መጎዳዳት ነው። እንግዲህ ፍትሕ በብቻው ሰላም አያሰፍንም ማለት ነው። ፍጹም ሰላም የፍትሕና የይቅርታ ድምር ውጤት ነው። ይሁንና በይቅርታ የተገራ ፍትሕ ነው ትርጒም ላለውና ለሰላማዊ ሕይወት የሚበጀው።
እና እንግዲህ ከቶ ማን ነው “ምርጡ መንገድ ሌላ ምንም ሳይሆን የሰላሙና የእርቁ መንገድ ነው” በማለት ተግቶ የሚሰብክልን? ማን ነው “በቀል በቀልን ይወልዳል፤ የሚሻለው መወጋገድ ሳይሆን መቀባበል ነው” በማለት የሚያውጅልን? እኔ የምመኘው በነገራቸው ሁሉ ልክ እንደ ማንዴላ ዐይነት ሰዎች እንዲነሡ አይደለም። ቁመታቸው፣ መልካቸውና ነገረ ሥራቸው ሁሉ ልክ ማንዴላን የሚመስሉ ሰዎች እንዲወለዱ አይደለም። ወይም ደግሞ ልክ እንደ ማንዴላ የሚያስቡ ሰዎች እንዲፈጠሩ አይደለም። በነገረ ሥራቸው ሁሉ ልክ ማንዴላን የሚመስሉ ሰዎች አያስፈልጉንም። እኔ የምመኘው የማንዴላን እሴትና ፋይዳ፣ እምነትና ጽናት ወኔና ቅን አሳቢነት የሚያስተጋቡ ሰዎች እንዲነሡ ነው። በቀልን ሳይሆን እርቅን፣ ሰይፍን ሳይሆን ምሕረትን የሚያነሡ ሰዎች እንዲወለዱ ነው። የሰው ልጆች ታሪክ የበቀልና የሰይፍ ታሪክ ነው። ይህ ደግሞ ከቶ አልጠቀመንም፤ ይልቁንም ይበልጥ አበጣበጠን፤ ይበልጥ አከፋፋን፤ ይበልጥ አራራቀን። ጭቆና፣ ብዝበዛና ብቀላ ምርጥ እሴቶች አይደሉም። ምርጡ እሴት ይቅርታና ምሕረት ነው። እንግዲህ ትልቅነት የሚለካው በላቀው እሴት ከሆነ ትልቆቹ ይቅር የሚሉና ምሕረት የሚያደርጉ ናቸው። እኔን አሁን በጣም የሚያስጨንቀኝ እንደ ማንዴላ ዐይነት ሰዎች በሌሉበት ዓለም “የሰዎች ሰውነትና እኩልነት” የሚረጋገጠው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። ለራሳቸው ሳይሆን ለሌሎች የሚኖሩ ሰዎች እየጠፉ በመጡበት ዓለም እንዴት መኖር ይቻላል? ሰዎች በሰላምና በፍቅር ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስላቸውን መሠረት ድምጥማጡን እያጠፋን እንዴት ነው ወደፊት መራመድ የሚቻለው? ልጆቻችንና ቀጣዩ ትውልድስ ተስፋ የሚኖራቸው እንዴት ነው? እናም ሄጄ ሄጄ “ከዚህ በኋላ ዓለማችን እንደ ማንዴላ ዐይነት ሰዎች ታገኝ ይሆን ወይ?” ከሚል ብርቱ ጥያቄ ጋር እላተማለሁ። እንደምን ያለህ ጨለምተኛው/ጸለምተኛው ነህ እጃል፤ ምነው ደግ ደጉ ቢታይህ ካልተባልሁ ከማንዴላ በኋላ ለሕዝብና ለአገር የሚቆረቆሩ ሰዎች ላይነሡ ይችሉ ይሆናል የሚል ብርቱ ጥርጣሬ አለኝ – ምንም እንኳ እንደዚህ ዐይነት ሰዎች ከቶ አይነሡም የሚል ግትር አቋም ባይኖረኝም።
እንደሚመስለው ከሆነ ግን ከመሃተመ ጋንዲ፣ ከኦስካር ሮሜሮ፣ ከእማሆይ ተሬዛ፣ ከማርቲን ሉተር ኪንግ በኋላ የእነርሱን ሰላመኛነት፣ ቁርጠኛነትና ለትውልድ አሳቢነት የተከተሉ ሰዎች አልተነሡም። ታዲያ አንተም እኮ ከጨለምተኞች በምንም አትለይም እንዳልባል ግን ለእኛም የእኛን ተግዳሮት የሚፋለሙ ምርጥ ልጆች ይሰጡናል ብል ሳይሻል አይቀርም። እነዚያኞቹ የራሳቸውን ዘመን ጭራቅ እንደተፋለሙ ሁሉ ለእኛም የእኛን ዘመን ጭራቅ የሚፋለሙ ጀግኖች ይሰጡናል። አንድ ወዳጄ ፈታኝና ተስፋ በሚያስቈርጥ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፍ ይህን ዳገት የወጣሁት “በራሱ በተስፋ መቊረጥ ላይ ተስፋ ስለ ቈረጥሁ ነው” ይላል። አባባሉ ግሩም መልእክት አለው። እግዚአብሔር አለ፤ የሰዎችንም አካሄድ ይመዝናል፤ ዐይንን የፈጠረው እርሱ ያያል የምንል ከሆነ ጨለማው የቱንም ያህል ቢበረታ በእርሱ ተስፋ አይቈረጥም። አንድዬ ጠበኛነትን ሳይሆን ሰላመኛነትን የሚያስተጋቡ የእርቅ፣ የሰላምና የይቅርታ ብርሃን የበራላቸውን “ብሩሃውያንን” ይስጠን! እኔ እንደ ክርስቲያን ጨለምተኛ ልሆን አልችልም። አንድዬንም የምማጸነው የመስቀሉና የዕርቀ ሰላሙ መንገድ የገባቸው ሰዎች እንዲሰጠን ነው። በአንድ በኩል ለጽድቅ፣ ለፍትሕና ለእውነት የሚቆሙ በሌላ በኩል ደግሞ ለሰው ልጆች ሰላምና ደኅንነት የሚቆረቆሩ ሰዎች ያብዛልን። አልያ ዓለማችን ትቃወሳለች፤ ትታመሳለች፤ ትቃወጣለች። አቤቱ እይ! አቤቱ ለምስኪኖች ድረስ! አቤቱ ዕቡያንን ዝም አትበል! አቤቱ ስማ፤ መልስም!!
[i] ይህን ጽሑፍ ሳስረክብ ማንዴላ 94 ዓመታቸውን ለማክበር በዝግጅ ላይ ነበሩ። አሁን ግን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበት ሙት ዓመት ተከብሯል፤ የአገሬ ቀሳውስት እንደሚሉት “አንድዬ በዕቅፉ ይቀበላቸው”።
[ii] ANC የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ንቅናቄ ነው፤ የተመሠረተውም ሰው በላውን የአፓርታይድ ሥርዐት ገርስሶ ለመጣልና የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ነው። ብዙ ሰዎች ለንቅናቄው ዓላማ ሲሉ ታስረዋል፤ ብዙዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ወደ 21, 000 የሚጠጉ ሰዎች በሥርዐቱ ተገድለዋል። ይህ አኀዝ በየጊዜው የታሰሩትንና የታፈኑትን አይጨምርም።
[iii] ተቋሙ “የፍትሕና የሰላም ተቋም” አለመባሉ በእጅጉ ያስደንቃል። እኔ እንደሚመስለኝ ይህ ትልቅ መረዳት ነው። ፍትሕ በሚልቀው መርሕ ካልተገራ አገር ያጠፋል። እንዲህ ሲባል ግን ፍትሕ አያስፈልግም ማለት ሳይሆን ፍትሕ በሚልቀው መርሕ መገራት አለበት ማለት ነው።
[iv] Emmanuel Katongole and Chris Rice, Reconciling All Things: A Christian Vision for Justice, Peace and Healing (Downers Grove: IVP Books, 2008), 97.
[v] ይህም “the South- African miracle” እየተባለ የሚጠራው ነው።
[vi] ሁለተኛው “መካስ” ጠብቆ ካልተነበበ ለማለት የፈለግሁት ትርጉም አይሰጥም። ባጭሩ በዳይ ካሽ ተበዳይም ተካሽ መሆን አለበት ለማለት ነው።
[vii] ምናልባት “ፖሊሷን” ከማለት ይልቅ “ሥርዐቱን” ማለት ይሻል ይሆናል። ሥርዐቱን ምን ደንታ ቢስ አደረገው? አመዛዛኝነት ከሥርዐቱ ለምን ጠፋ? ሥርዐቱን ምን አቃወሰው/አቀወሰው? ምን ድንጋይ አደረገው?
[viii] ፖሊሷ በጻፈችው ቅጣት መሠረት የፍርድ ቤት ቀነ ቀጠሮው ደርሶ ወደ ፍርድ ቤት ሄድሁ። አዳራሹን እንደ እኔ የቅጣት ብይን ተጥሎባቸው የመጡ ሰዎች ሞልተውታል። ሁለት አስተናባሪዎች፣ አንድ ፖሊስና አንድ ዳኛ ወደ መድረኩ ወጡ። በመጀመሪያ ዳኛው ስለ ፍርዱ ሥርዐትና ከእኛ ምን እንደሚጠበቅ ማስፈራሪያ አዘል አጭር መግለጫ ሰጡ፤ ከዚያም ፖሊሷ በእጅጉ ያስገረመኝን መግለጫ ሰጠች፤ “ያለ ምንም ድርድር ጥፋተኛነቱን የተቀበለ ሰውና የተጣለበትን ቅጣት ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ ሰው የተጣለበትን ቅጣት ከፍሎ ይሄዳል፤ በመንጃ ፈቃዱ ላይም ምንም ነጥብ አይያዝበትም በነጻ ይሄዳል፤ ነገር ግን ዳኛው ፊት ቀርቤ ነገሬን/ጉዳዬን አስረዳለሁ የሚል ሰው ካለ ዳኛው ፊት ይቀርባል፤ ሆኖም ዳኛው ምክንያቱን ካልተቀበሉ የተጣለበትን ቅጣት ይከፍላል፤ ደግሞም በመንጃ ፈቃዱ ላይ ነጥብ ይያዝበታል” (በመንጃ ፈቃድ ላይ የሚያዙ ነጥቦች አምስት ከደረሱ መንጃ ፈቃድ ያሰናጥቃሉ)። ሰዉ ሁሉ “ጎመን በጤና” ብሎ የመጀመሪያን አማራጭ ተቀበለ። እኔ መቼም ይህን ፍትሕ ነው ብዬ ለመቀበል ያስቸግረኛል። ይህ በእውነተኛው በዝባዥና ጨቋኝ ኢሰብአዊና አካይስታዊ ሥርዐት ነው። ሰዎች ፍትሐዊ ያልሆነውን ነገር በግድ እንዲመርጡ የሚያስገድድ ሥርዐት ነው። ሰዎች ጒዳያቸውን እንዳያስረዱ ዕድል የሚነፍግ ሥርዐት ነው። አሁን አማራጩ አንድና አንድ ብቻ ነው – ለሥርዐቱ ጸጥ ለጥ ብሎ መገዛት፤ ሥርዐቱ ፍትሐዊም ሆነ አልሆነ ሥርዐቱን አለመጠርጠር። እርግጥ ዮርገን ሞልትማን እንደሚለው በሰዎች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት በመፈጸም ሰዎችን የሥርዐቱ ባርያ የሚያደርጉ ከሁሉ በፊት እነርሱ ራሳቸው የሌላ ነገር ባርያ ናቸው (Jurgen Moltmann, Religion, Revolution and the Future)። ሞልትማን ያ ነገር ምን እንደ ሆነ መገመቱን ለአንባቢው ትቷል፤ ከዐውዱ እንደምንረዳው ያ ነገር ሰይጣንና አጋንንታዊ መንፈስ ነው። ሰዎች የሰይጣን ባርያ ካልሆኑ በስተቀር ሌላውን ሰው አይጨቁኑም፣ አያስጨንቁም፤ አይበዘብዙም፤ በሰዎች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት አይፈጽሙም፤ ሰዎችን መግቢያ መውጫ አያሳጡም።
Add comment