በጥፋት መሠረት ታንጸው በደምሳሳ እይታ የተነሳሡ፣ ጥቂት ያለ አግባብ የታጠቁ የውድመት መልእከተኞች የማይታሰብ ሰቆቃና ዕልቂት በትውልድ ላይ እንደ ዝናብ ያዘንባሉ፣ ከተሞችንና የልማት ተቋማትን ያጋያሉ። እነዚህ በዕውር ድንብር የተቃኙ የመከራ ሰለባ፣ እሳት ለመቆስቆስ የተሰማሩ አጥፊዎች፣ የክፍለ ዘመናትና የብዙ ትውልዶች አሻራ ያረፈባቸውን ዘመን ጠገብ የሥልጣኔና የዕድገት ውጤቶች ከመቅጽበት ወደ ብዙ ዓመታት ጨለማ የኋልዮሽ ይመልሳሉ። አውዳሚ ለመሆን ክኅሎት አይጠይቅም።
የማምለኪያ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የመሳሰሉ ለግንባታ ዓመታትን ያስቆጠሩ የብዙኀን መገልገያ ተቋማትን ዶግ ዐመድ ለማልበስ ጊዜና ሥልጠና አያስፈልገውም። የሚጠይቀው በክፋትና በበቀል ስሜት የተለከፈ አፍላነት ነው። ያለ ዕውቀት የተለቀቀ አፍላነት እሳት ነው። በጥንቃቄ ያልተገራ ስሜታዊ ግልቢያ ያገኘውን ታሪካዊ ዳርቻ የሚሰለቅጥ፣ የአሁኑን የሚደመስስ፣ መጪውን የሚያጨልም ነው። ከምክንያታዊነት የተፋታ፣ በጭፍን የሚነዳ የስሜት ግነፈላ፣ ሃዲዱን ስቶ እየከነፈ ያገኘውን ሁሉ ያለ ምሕረት እያጠፋና እየጨፈላለቀ፣ በመጨረሻም ራሱ በፈጠረው እሳት ተቀጣጥሎና ጋይቶ እንደሚወድም ባቡር ነው። በስሕተት ተግባር ላይ ተሰማርተው ልማትን እንደማይጠብቁ ሁሉ፣ በሠናይ ዐላማ ሥር ተጠልለው የጥፋትን ሰይፍ አይመዝዙም።
በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎችና ምክንያቶች ግጭቶች እየተፈጠሩ የንብረት ውድመትና የማይተካውን ክቡር የሰው ሕይወትም እያሳጡን ይገኛሉ። በቅርቡ በኦሮሚያ አንዳንድ አከባቢዎች በተከሰተው አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት ያላዘነ፣ በውስጡ ያልተብከነከነ፣ ያልተረበሸ፣ ‘ለምን?’ ብሎም ያልጠየቀ ቅን ዜጋ ይኖራል ማለት ይከብዳል። እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች የማይሽሩ ጠባሳዎችን በትውልዱ አእምሮ እየከተቡ፣ ማኅበራዊ አለመረጋጋትን እያስከተሉ፣ ተከባብሮ የመኖርንም እሴቶች እየደመሰሱ ነው። በተጨማሪም ሁላችንም በየቤታችን የማኅበራዊውም ሆነ የኢኮኖሚያዊ ጦሶቹም ተጠቂ ሆነናል። ለዓመታት የሚድኽው የአገራችን ኢኮኖሚም ቢሆን፣ ለዳዴ ሲጣጣር በእነዚህ ክስተቶች ቁልቁል በተደጋጋሚ እየተደፈቀ ነው።
ሰዎች ከምክንያታዊነት በተፋታ መንገድ የሚወስኑት ውሳኔ እንዲሁም በስሜትና ግልፍተኝነት የሚፈጽሙት ተግባር መቼም ቢሆን የማይቀለብሱትን ውድመትና የእድሜ ልክ ጸጸትን ያወርሳቸዋል። ነገር ግን እነዚህን ድርጊቶች የወለዱ እኩይ እሳቤዎች አሁን ተዘርተው አሁን የበቀሉ ዘሮች ናቸው? ለብዙ ዘመናት ተዋድዶ፣ ተዋልዶ፣ ተከባብሮና ተሳስቦ በኖረ ሕዝብ መኻል ይህ አስከፊ ተግባር በዚህ መጠንና ቅጽበት እንዴት ተፈጸመ? ብሎ ለጠየቀና ለመልሱ ግራ ለተጋባ እንዲሁም ስሜት ከምክንያታዊነት ፍጹም ሲፋታ ምን ሊሆን ይችላል? መሰል ጥፋቶችንስ በርግጥ ያስከትላል? መውጪያ መንገዱና መፍትሔውስ?
እነዚህን መሰል ብርቱ ጥያቄዎች ለሚጠይቅ ባለአእምሮ፣ የወንጌል ብርሃን በበራላቸው የሥነ አእምሮ፣ ሥነ ልቦናና፣ ሥነ መለኮት ምሁሩ በሆኑት ሳሙኤል ወልዴ (ዶ/ር) ተጽፎ ለንባብ የቀረበው፣ “ከመደነጋገር መነጋገር” የሚለው ግሩም፣ ወቅታዊና ሳይንሳዊ መጽሐፍ መልስ ይሰጣል። ትውልድን እየበሉ፣ አገርን እያወደሙ፣ እናቶችን እያስለቀሱ፣ የአገር መሪዎችን፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ምሁራንን ግራ እያጋቡ ላሉ አገር አቀፍ ተግዳሮቷች መፍትሔው “ከመደነጋገር መነጋገር፣ ከመነካከስ መወቃቀስ” መሆኑን በማሳየት አንባቢያን ለመነጋገር ክኅሎት እንዲነሳሡ፣ በብርቱና በጥበብ ደራሲው ይቀሰቅሳሉ።
“ከመደነጋገር መነጋገር” የሚለውን የመጽሐፉን ርእስ ተመልክቶ እንደ እኔ የመነጋገርን አስፈላጊነት የማይረዳ ሰው በአገራችን አለን? ‘ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ በመነጋገር የተፈታና የሚፈታ አገራዊ ችግር ይኖር ይሆን?’ ብሎ በዙሪያው በሚያየውና በሚሰማው ሁሉ ግራ በመጋባትና በመቆዘም ጥያቄ ለሚጠይቅ አንባቢ፣ ጸሐፊው በመጽሐፋቸው፣ ‘አዎ! አለ’ ይላሉ። በመነጋገር ክኅሎት በተሞላና “በእውነት ላይ ተመሥርቶ በፍቅር በተሟሸ” የልብ ለልብ ምክክር የማይፈቱ ቤተ ሰባዊ፣ ማኅበረ ሰባዊ፣ ኅብረተ ሰባዊና አገራዊ ችግሮችና የማንሻገራቸው እንቅፋቶች የሉም በማለት፣ ዐብሮና ተከባብሮ የመኖር ተስፋችንን እንደገና ይቀሰቅሳሉ። አስገራሚ ታሪካዊ እውነቶችንም በምሳሌነት በማንሣት አልረፈደብንም ይላሉ።
አሁን አሁን በእኛ የእርስ በእርስ እልቂት የሚገረሙትና፣ ምናልባትም ከመጋረጃ ጀርባ የሚሳለቁብን የበለጸጉት ምእራባውያን አገሮች ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት በስሜታዊነትና በግብታዊነት ተነሳሥተው የሌላ አገር ድንበር ጥሶ በገባ ውሻ ሰበብ እንኳን ሳይቀር፣ አንዱ አገር በሌላው ላይ የጦርነት ክተት አውጀዋል፤ ጦር ሰብቀውና አዝምተው ተፋጅተዋል፤ ተላልቀዋል በማለት የታሪክን መዛግብት ገልጸው ያሳዩናል። የተጠቀሰውንና ሌሎችንም አስቂኝና አስገራሚ ምእራፍ ዐልፈው ምእራባውያኖቹ ለአሁኑ የሰከነ ፖለቲካቸውና ለደረሱበት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ብልጽግና ዋና ሃዲዱ ተቀራርቦ የልብ ለልብ መነጋገራቸው ብቻ ነው በማለትም ዐሳባቸውን ያስረግጣሉ።
ለግል ጥቅማቸው ያሰፈሰፉ በመኻል ያሉ ‘ጆከሮችን’፣ ‘አንቂዎች ነን’ ባዮችንና የግጭት አትራፊዎችን ከመካከል በማስወገድ “በእውነት ላይ ተመሥርቶ በፍቅር በተሟሸ” ውጤታማ ንግግር የጋራ ዐላማን ማስጠበቅ፣ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ ጥርጣሬና ሀሜትም በማጥፋት ወደ ጋራ ግብ መጎዝ እንደሚቻል በግልጽ ያመላክታሉ። ለዚህም እንዲረዳ ሳይንሳዊ ትንታኔና አጋዠ መርሆችን ለአንባቢው በዝርዝር ያስቀመጡበትም መንገድ ልዩ ነው። “ዝምታ ወርቅ ነው”፣ “ሙያ በልብ ነው” እያለ የነበረውን ትውልድም ሆነ “አሁን ጊዜዬ” ነው ብሎ ዘመኑ ባስገኘለት የመናገሪያ መንገድ ሁሉ በየአደባባዩ ለሚዘላብደው ትውልድ ከውጤታም የንግግር ክኅሎት መጉደላቸውን በማስረጃ ያሳያሉ። አንዳንዴም በእውቀት በመገሰጽ ሁሉንም ዜጋ ወደ ትክክለኛው ሀዲድ ለመመለስ ይታገላሉ። ሁላችንም እንደምንረዳው ዛሬ የነገው ስኬት መሠረት የሚታነጽበት አጋጣሚ ነው። አንዱና ዋነኛው የአገራዊ ብልፅግና መሠረት ደግሞ ደራሲው እንዳሠመሩበት “ጭንብልን አውልቆ” ልብ ለልብ ተቀራርቦ የመነጋገርና ችግርን በንግግር የመፍታት ክኅሎት ነው።
በርግጥ መነጋገር ለችግሮቻችን መፍትሔን የሚያመጣ ከሆነ በአገራችን የሚከሰቱት ግጭቶች ለምን እልቂትን ያዘንባሉ? ስላልተነጋገርን ነው? ወይስ መናገራችንን እንደ መነጋገር እየቆጠርን ሰንብተን ነው?
ቤተ ሰብና የኅብረተ ሰብ አካላት በተወለዱበት አገርና በሚኖርበት መንደር ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጸጋና የተለያዩ አቅራቦቶች እየተቋደሱ ሲኖሩ ሁልጊዜ በመከባበርና በመተሳሰብ ነው የሚኖሩት ብለን ብንል ራሳችንን መዋሸት ነው። በሚሰማንም አድማጭ ዘንድ ትዝብት ላይ እንወድቃለን። ግጭት የአቅርቦት እጥረት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ዕለት በዕለት ሲፈጠር የምናስተውለው ጉዳይ ነው። “ከመደነጋገር መነጋገር” በቤተ ሰብ፣ በማኅበረ ሰብና በብሔረ ሰቦች መካከል በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶችና በሚያስከትሏቸው ውድመቶች ግራ ለተጋቡ አንባብያን የተስፋን ጭላንጭል በሚያሳይ መንገድ የግጭትን መንስኤና መፍቻ መንገዶችን በግሩም ሁኔታም ተተንትኖበታል። ለችግሮቻችንም እንደ ዐይነተኛ የመድኃኒት “ማዘዣ ቀላጤ” (prescription) በግሩም ሁኔታ ለመለወጥ ለተዘጋጀ አእምሮ ሁሉ ታዟዋል።
“ግጭቶች የአስተሳሰባችንን አድማስ እንድናሰፋ የሚጠቅመን መነፅርና ወደ ማደግና ወደ መሻሻል የሚያስተናብሩ አጋጣሚዎችና ጎሕ ቀዳጆች ናቸው”፤ “ግጭት አብሮ የመኖር ጠላት ሳይሆን ነዋሪዎች አብረው ለመኖር የሚከፍሉትን የዋጋ መጠን የሚለኩበት ሚዛን ነው” በማለት ዶ/ር ሳሙኤል በእያንዳንዱን ግለ ሰብ ትከሻ ላይ የኀላፊነቱ ድረሻ ሲያሳርፉ፣ ለመሪዎችም “በቤተ ሰብና በማኅበረ ሰብ፣ በብሔረ ሰብና በኅብረተ ሰብ መካከል ግጭት ሲፈጠር ለመሪዎች የሚደወል የተግባር ጥሪ ነው”፤ “ችግርና አለመግባባት ለእድገት በር ከፋች አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን፣ እውነተኛ መሪዎች ራሳቸውን የሚገልጡበት ነባራዊ መድረክ ነው” በማለት በየደረጃው በአገራችን የመሪነት ኀላፊነት ላይ ያሉ ሁሉ ራሳቸውን እንዲፈትሹና ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ያስገነዝባሉ።
“የመሪዎች ኀላፊነት” በተሰኘው ሌላኛው ምእራፍ ላይ ደግሞ፣ በጎ መሪዎች በታሪክ ውስጥ የሚኖራቸውን ድርሻ አበክረው የሚያውቁና በኅብረተ ሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያበቃ ብቃት፣ ተግባራዊና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል በሚል በብርቱ ይሞግታሉ። መሪዎች ማሟላት ይኖርባቸዋል ካሏቸው ዝርዝሮች ውጭ የሆነ መሪን መሾም በተለማማጅ ፓይለት ለመብረር አየር ላይ መውጣትና በሚፈጸመውም ስሕተት በደስታ ፈርሞ ለመሞት መዘጋጀት ነው ይሉናል። መሪ ልሁን ብሎ በመሪነት መንበር ለመቀመጥ ለሚማልለውም “ፖለቲከኛ”፣ ‘በምንና ምን መንገዶች መሪ ለመሆን ተዘጋጅተሃል?’ ብሎ ተመሪውም ሕዝብ አጥብቆ የሚጠይቅበትን ዝርዝር መስፈርቶችን ተንትነዋል።
“ከመደነጋገር መነጋገር” የሥነ ጽሑፍ ውበትን ተላብሶ፣ በስምንት ምእራፎች ተሰድሮ በርእሰ ጉዳዩ ላይ የጠለቁ ሳይንሳዊ ትንተናዎች፣ ወቅታዊ ኩነቶች፣ ሚዛናዊ ሥነ መለኮታዊ መረዳቶች እንዲሁም ታሪካዊ ክስተቶች ተዋሕደው የቀረቡበት መጽሐፍ ነው። በእያንዳንዱ ምእራፍ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም አንቀጽ በሚባል ደረጃ የሚያመራምሩ፣ የሚያነቁና ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ ዐሳቦች ተሰድረዋል። እኔ ግን በዚህች ዐጠር ያለች ጽሑፍ ሁሉንም ምእራፎች በመነካካት እይታዬን በማካፈል ፋንታ፣ ግጭቶቹ ላይ መቆየቴ ግን ከሰሞኑ ልቤን ካከበደው ክስተት ጋር ንባቤ ስለገጠመብኝና በመጽሐፉ ውስጥ ለወቅታዊው ችግሮቻችን ብዙ መድኃኒትና ተስፋ የሚሆኑን እውነቶች ሰለተመለከትኩኝ ነው።
ከመደነጋገር መነጋገር መሳጭ፣ ገላጭ፣ ሞጋች፣ አስተማሪና አነቃቂ በሆነ መንገድ የቀረበ እጅግ በጣም የተመሰጥኩበትና ብዙ የተማርኩበት መጽሐፍ ነው። በእኔ መመዘኛ በዚህ ደረጃና ርእስ ተዘጋጅቶ ያነበብሁት በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ የለም ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ይህን አስረግጬ ያለ ምንም ማመንታት ይህን ለምታነብቡ የምገልጸው መጽሐፉን ስታነቡቡት በአስተያየቴ እንደምትስማሙ በማመንና ከዚህ በጥራትና በጥንቃቄ ተሰናድቶ ከቀረበልን ማዕድ እንዳትጎድሉ በመሻትም ጭምር ነው።
ሳሙኤል ወልዴን (ዶ/ር) በዚህ አጋጣሚ ስለዚህ በብዙ እውቀት ሰድረውና በጥንቃቄ አሰናድተው ስላቀረቡልን መጽሐፍ ከልብ የሆነ ምስጋናዬን ላቀርብላቸው እወድዳለሁ። በሌሎችም ሳይንሳዊ፣ አስተዳደራዊ፣ አገራዊ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ መሰል ሚዛናዊና በሳል ሥራዎቻቸውን ለማንበብ መጎጎቴን አልሸሽግም። ሳይዘገዩ ጀባ እንደሚሉንም ተስፋ አደርጋለው። መጽሐፉን የምታነብቡ አንባቢያንም ከምንባባችሁ መልስ ተመሳሳይ ጥያቄ እንደ እኔው ታቀርቡ ይሆናል ብዬ እገምታለው። አስተያየታችሁንም በዚሁ መድረክ ለመስማትና አገራዊ ፋይዳ ባላቸው በመጽሐፉ ውስጥ በተነሡ ጭብጦች ዙሪያ ለመወያየት እንድንችል የዚህ ድረ ገጽ አጋፋሪዎች ሁኔታዎችን ቢያመቻቹልን መልካም ይሆናል እላለው። ጥያቄዬንም ለድረ ገጹ አጋፋሪና አጋሮቻቸው በትኅትና አቀርባለው።
በቸር እንሰንብት!
Add comment