[the_ad_group id=”107″]

መሪነት እና ጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ

“ከታሪክ የምንማረው ነገር ከታሪክ አለመማራችን ነው።” ይህን አባባል የተናገሩት ከዓለማችን ቢሊየነሮች መካከል ከፊተኞቹ ተርታ የሚገኙቱ አሜሪካዊው ዋረን ባፌት ናቸው። እኚህ ባለጠጋ ሰው በዚህ አባባላቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልክእት እኛ ሰዎች ታሪክን ወደኋላ ተመልክተን አንዳንዶቹን ባለ ታሪኮች ለውድቀት የዳረጋቸውን ያንኑ ስሕተት መድገማችንን ወይም የተሳካላቸውን ባለ ታሪኮች ብርታት ያለመማራችንን የተደጋገመ ዝንባሌ በመመልከት ትዝብታቸውን ለማንጸባረቅ ነው። የዋረን ባፌትን አባባል መነሻ የማድረጌ ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ቆም ብለን ብንፈትሽ ለዘመናችን የመሪነት አስተሳሰብና ልምምድ የሚያስተላልፈው ቁም ነገር እንዳለ ለማሳየት ነው።

ሮበርት ባንክስ እና በርኒስ ኤም. ሌድቤተር

“Reviewing leadership: A Chris an reflection of current approaches” በሚል ርእስ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ በዘመናዊው የአመራር ዕሳቤ ላይ ሥነ መለኮታዊ ፍተሻቸውን አቅርበዋል። ይህንን በማድረግም ረጅሙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለዘመናዊው የአመራር ዕሳቤና ልምምድ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አመላክተዋል። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የታዩትን የአመራር ገጽታዎች ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ልምምድ በመነሣት ዳሰሳቸውን ጽፈዋል። በዚህም መሠረት የአምስት አብያተ ክርስቲያናትን የአመራር ልምምድ የቃኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ መሪነት በጴንጤቆስጤውያን ዘንድ ያለውን መልክ ያብራሩበት ንዑስ ሐሳብ ይገኛል። ይኽኛው የሕንጸት መጽሔት ዕትም ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጋራ ተያይዞ የቀረበ ልዩ ዕትም ከመሆኑ አኳያ የ“ሠናዩ መሪ” ዐምድም አመራርን ከጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ ጋራ አያይዞታል።

ብዙዎቹ የታሪክ ምሑራን እንደሚስማሙበት ከሆነ ጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ እ.አ.አ. በ1906 በዊልያም ጄ. ሴይሙር ይመራ በነበረውና ሎስ አንጀለስ በሚገኘው የአዙሳ መንገድ አገልግሎት እንደ ተጀመረ ይነገርለታል። ይሁን እንጂ ከዚህ ዓመት ቀደም ብለው በአሜሪካ እና በዌልስ የታዩት ጴንጤቆስጤያዊ ምልክቶች ለእንቅስቃሴው መጠንሰስ ምክንያቶች እንደ ነበሩ ይታመናል። ከእነዚህ ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው እ.አ.አ. በ1901 በቻርለስ ፎክስ ፓርሃም የተጀመረውና በቶፔካ ከተማ በካንሳስ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የቤቴል መጽሐፍ ቅዱስ ት/ ቤት ነው። ጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ በዓለም ዙሪያ እጅግ እያደገ የሚገኝ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ አለን አንደርሰንና ጓደኞቻቸው እ.አ.አ. በ2010 በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ቁጥራቸው ከ500 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባላት እንደሚገኙበት ይጠቁማሉ። ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ እ.አ.አ. በ2002 በስታንሊ ኤም. በርጊስ ዋና አርታኢነት “The new international dictionary of Pentecostal and Charismatic movements” በሚል ርእስ የተጻፈው መጽሐፍ እንደዘገበው ከሆነ ከአራት ሚሊዮን በላይ ጴንጤቆስጤያውያን በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም አኀዞች ሁሉንም የጴንጤቆስጤያውያንን ክፍሎች (ማለትም ጥንታዊው ጴንጤቆስጤያዊነትን፣ ካሪዝማቲክ እንቅስቃሴን እና ኒዮ-ጴንጤቆስጤያዊነትንi) የሚያጠቃልል ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ብዛታቸው ከፍ እንደሚል ይታመናል።

የጴንጤቆስጤያዊ መሪነት ዕሳቤዎች

ወደ ርእሰ ጉዳያችን ስንመለስ ጴንጤቆስጤያዊነት እንደ እንቅስቃሴ መታየት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የመሪነት አስተሳሰብ የሚታወቅባቸው መገለጫ ባሕርያት ነበሩት። ሁሉንም መዘርዘርና ማብራራት ባይቻልም ከመሪነት ጋር ተያይዘው የሚቀርቡትን ዋና ዋናዎቹ አስተሳሰቦች በዚህ መጣጥፍ ውስጥ እንመለከታለን።

1. እግዚአብሔር መሪ ነው

በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የመሪነት ጽንሰ ሐሳብ የሚጀምረው እግዚአብሔር መሪ እንደ ሆነ በማመን ነው። ባንክስ እና ሌድቤተር ጴንጤቆስጤያዊውን መሪነት የሚገልጹት ጴንጤቆስጤያዊነት እግዚአብሔርን ዋና መሪ እንደ ሆነ አጽንዖት መስጠቱንና መሪዎችንም የሚያስነሣው እርሱው እግዚአብሔር እንደ ሆነ ማመኑን ነው። ዶ/ር ታን-ቾው የአዙሳ መንገድን አገልግሎት ገጽታ አስመልክተው ሲጽፉ መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው መሪ እንደ ነበረ ጠቅሰዋል። በርግጥም እ.አ.አ. ከ1906- 1908 ድረስ በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ ሳምንቱን ሙሉ የሚካሄዱ መርሓ ግብሮች እንደ ነበሩ፣ በየቀኑም ሦስት ሦስት መርሓ ግብሮች ይካሄዱ እንደ ነበርና የመርሓ ግብሮቹ ገጽታም “አሳትፌነት፣ ናፋቂነት (ጉጉነት)፣ ግብታዊነት፣ ደስተኛነት፣ እና ጫጫታ” (ገጽ 43) የሰፈነበት እንደ ነበር ዶ/ር ታን ቾው ጠቁመዋል። በመሆኑም ለመንፈስ ቅዱስ ሙሉ ነጻነት ለመስጠት ሲባል ምንም ዐይነት የመርሓ ግብር ቅደም ተከተል አልነበረም። መንፈስ ቅዱስም በመካከላቸው እንደ አምላክነቱ እና እንደ መሪነቱ መጠን የወደደውን ያደርግ ነበር።

2. መሪነት ጥሪ ነው

ባንክስ እና በርኒስ በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን መሪነት ሲያብራሩ እግዚአብሔርን የስጦታዎችና የኀይል ምንጭ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር የስጦታዎች ሁሉ ምንጭ እንደ ሆነ ሁሉ እንዲሁ የመሪነትም ምንጭ ነው። ይህ መረዳት በጴንጤቆስጤያውያን መሪዎች ውስጥ ስለ ነበረ አመራርን የችሎታቸው ወይም የእውቀታቸው ጉዳይ አድርገው አይወስዱትም ነበር። እንደውም ጴንጤቆስጤያዊው መሪነት ጥሪ ነው፤ ጥሪው ደግሞ አዎንታዊ ምላሽን ይፈልጋል። በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩቱ መሪዎች እየጾሙ ያመልኩ በነበረበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ጳውሎስን ለአገልግሎት እንደጠራቸው (ሐዋ. 13፥1-2) እንዲሁ አሁንም በዘመናችን መንፈስ ቅዱስ መሪዎችን እንደሚጠራ ጴንጤቆስጤያውያን ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ሲነሣ ስሙ የሚጠቀሰው ፓርሃም የአገልግሎት ጥሪ እንደ ደረሰውና ወደ ሕክምና መስክ በመሄድ ሐሳቡን ሊለውጥ ሲል እንደገና እግዚአብሔር ወደ አገልግሎቱ እንደመለሰው ጃኮብሰን “Thinking in the Spirit: Theologies of the early Pentecostal Movement” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ አትቷል። ከዚህ የተነሣ መሪነት ለእግዚአብሔር ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ራስን ለእርሱ ሐሳብ መገልገያ እንዲሆን ማቅረብ ነው። ባንክስ እና በርኒስ በሚሉት መሠረት ጴንጤቆስጤያዊው መሪነት “ራስን ለመንፈስ ቅዱስ ኀይል እቃ አድርጎ መስጠት ነው” (ገጽ 46)።

3. እያንዳንዱ አማኝ መሪ መሆን ይችላል

መሪነት የጥቂቶች ልዕቀት አይደለም። ሁሉም አማኞች ካህናት እንደ መሆናቸው መጠን እንዲሁ ሁሉም አማኞች መሪ መሆን ይችላሉ። ባንክስ እና ሌድቤተር ይህንን ሐሳብ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ላይ በመመርኮዝ ያብራራሉ። በበዓለ ኀምሣ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሁሉ ላይ እንደ ወረደ መጠን፣ እንዲሁ መሪነት ለአማኞች ሁሉ ሊሰጥ የሚችል ስጦታ ነው። በመሆኑም ባንክስ እና ሌድቤተር “በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እያንዳንዱ አባል መሪ ሊሆን ይችላል” (ገጽ 47) በማለት ጽፈዋል። በተጨማሪም እነዚሁ ጸሓፊያን፣ እያንዳንዱ ጴንጤቆስጤያዊ አማኝ መሪ ሊሆን የመቻሉን ጉዳይ ሲያብራሩ፣ “ማንም እንዲሁም ሁሉም ሊጠራ ስለሚችል መሪነት የጥቂት ምርጦች አገልግሎት ብቻ አይደለም። መሪነት ለሁሉም ክፍት ነው” (ገጽ 47)።

4. መሪነት በብዝኀነት

በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው የመሪነት ታሪክ አግላይ አልነበረም። በጊዜው የነበረው በዘር እና በጾታ ላይ የተመሠረተው የአመራር አስተሳሰብ በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቦታ አልነበረውም። ይልቁን ሁሉንም ያቀፈና ብዝኀነትንም መገለጫው ያደረገ ነበረ።እ.አ.አ. በ1906 የተቀጣጠለው የአዙሳው መንገድ ጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ዋና መሪ የነበረው ጥቁር አሜሪካዊው ዊልያም ጄ. ሴይሙር መሆኑ በጊዜው ከነበረው የዘር መድልዎ ጋራ ሲነጻጸር አነጋጋሪ ሊባል የሚችል መሆኑን መገመት አያዳግትም። ከእርሱም ጋር ነጮችና የላቲን ዝርያዎች ያላቸው አንድ ላይ ማገልገላቸውና ማምለካቸው በክርስቶስ የነበራቸውን አንድነት የሚያሳይ፣ በመካከላቸው ያለው የአመራር አስተሳሰብም አካታች እንጂ አግላይ አለመሆኑን ያሳያል።

ዶ/ር ታን ቾው የተባሉ ጸሐፊ በሲንጋፖር ውስጥ ከተነሣው ጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ጋር በማያያዝ ጴንጤቆስጤያዊ ሥነ መለኮትን ሲጽፉ፣ የአዙሳው መንገድ አገልግሎትን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡ – “የአዙሳው አገልግሎት ሦስት ጥቁር አሜሪካውያን እና ዘጠኝ ነጭ አሜሪካውያንን ያቀፈ ዐሥራ ሁለት ሽማግሌዎች ሲኖሩት፣ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ወንዶች ሰባቱ ደግሞ ሴቶች ነበሩ” (ገጽ 45)። ይህ ታሪክ በጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው የአመራር ልምምድ እያንዳንዱ አማኝ መሪ የመሆኑ እውነታ በጊዜው ተንሰራፍቶ የነበረውን የዘረኝነትንና የጾታን ከልካይ ወሰን አልፎ እስከሚሄድ ድረስ እውን እንደ ነበረ መረዳት ይቻላል። “የጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ጅማሬ” ተብሎ ከሚታሰብበት እ.አ.አ. ከ1900 እስከ 1925 ያለውን የአሜሪካንን የጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ በሚተርከው መጽሐፋቸው ውስጥ ዳግላስ ጃኮብሰን የሴቶችን በመሪነት መሳተፍ አስመልክቶ ሚዛናዊ ማድረግ ያለብንን ጉዳይ ይጠቁሙናል። ይህም ምንም እንኳን የዘመኑ ጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ሴቶችን ከአመራር አገልግሎት ባይከለክልም አስተምህሮን ከመቅረጽ አኳያ ግን ተሳትፏቸው እጅግ ውስን መሆኑን ነው። ይህ አካሄድ ወደ ኋላ ላይ ሴቶችን ከአመራር አገልግሎት፣ ብሎም ከሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያራቀ መሆኑን ብንገነዘብም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሴቶች ያለ ምንም ገደብ በአገልግሎትም ሆነ በአመራር ደረጃ መሳተፋቸው እየመጣ ያለውን የአስተሳሰብ ለውጥ ያመለክታል።

ይሁን እንጂ የዘመኑን አስተሳሰብ ተሻግሮ የነበረው በጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረው መሪነት ወደ ኋላ ላይ የዘር ክፍፍሉ ጥላውን አጥልቶበት ነበር። ጃኮብሰን በመጽሐፋቸው ውስጥ እንዳብራሩት በሎስ አንጀለስ ውስጥ የተለያዩ ጴንጤቆስጤያዊ አብያተ ክርስቲያናት ሲጀመሩ የአዙሳው አገልግሎት ጥቁር አሜሪካዊያን ብቻ የሚገኙበት እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር በእንደዚህ ዐይነቶቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጥቁሮቹ ዋናውን መሪነት መያዝ እንዳለባቸው ይነገር የነበረ መሆኑ የቀደመውን ጤናማ አስተሳሰብ የመልቀቅ ሁኔታ እንደታየበት ጠቅሰዋል::

5. መሪነት ተከታይነት ነው

ጥሩ መሪ ጥሩ ተከታይ ነው፤ ማለትም ጥሩ የሆነ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነው። ባንክስ እና ሌድቤተር እንደሚሉት ከሆነ “የአንድ መሪ ታላቅነት የሚለካው ያ መሪ የእግዚአብሔር ተከታይ በሆነው መጠን ልክ ነው” (ገጽ 46) በማለት ጴንጤቆስጤያዊ መሪነትን ይገልጻሉ።

እያንዳንዱ አማኝ መሪ የመሆኑ ጉዳይ ሁሉም አገልጋይነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ነበር። በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው የመሪነት ሐሳብ መሪነትን በመሪነት ሐሳቡ ከመያዝና ወደ አመራር ሥፍራ ከመምጣት ይልቅ፣ እያንዳንዱ ሰው ሌሎችን ለማገልገል ካለው ፍላጎት የሚመነጭ ክስተት ሆኖ ይታይ ነበር። ዶ/ር ታን ቾው በጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን አመራር ከዘመናችን የሎሌያዊ አመራር ጽንሰ ሐሳብ ጋራ ያያይዙታል። በእርሳቸው አባባል በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን የአመራር ጽንሰ ሐሳብ ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ማገልገል እንደሆነና ተገልጋዮችን ማጎልበት ላይ እንደሚያተኩር ይገልጻሉ። ይህም መሪዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ትኩረታቸውን ከሚወስደው ራስ ተኮር ከሆነው የስኬት ቀመር የተለየና ከፍ ያለ መሆኑንም ጭምር የሚያመለክት ነው።

የጴንጤቆስጤያዊ መሪነት ሕጸጾች

ጴንጤቆስጤያዊ መሪነት ስሕተት አልባ ነበረን? በፍጹም! ሰው ባለበት እንዴት ስሕተት ይጠፋል?! ስለዚህም በጴንጤቆስጤያውያኑ መካከል የነበረው የአመራር ልምምድ የራሱ የሆኑ ሕጸጾች ነበሩት። ጴንጤቆስጤያዊው አገልግሎት በባሕርዩ ደምቆ የመታየት ነገር ስላለበት አገልጋዮቹም ደምቀው ቢታዩ አያስገርምም። ቢሆንም ይህ በራሱ የሚፈጥረው ችግር አለ፤ ታዋቂነትን እና ዝነኛነትን። ከዚህ ጋራ ተያይዘው የሚመጡት አጃቢና ገንዘብ የማካበት ፍላጎቶች ጴንጤቆስጤያዊውን መሪ ለችግር ይዳርጉታል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ራስን ከሌሎች የተሻለ አድርጎ የመቁጠር አባዜም ሊጠናወት ይችላል።

ሌላኛውና በጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች መካከል ጎልተው ከታዩ ደካማ ጎኖች አንዱ የትምህርት ስስነት ነበር። ጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች ሥነ መለኮትን እንደ ፍሬ የለሽ ፍልስፍና ይወስዱት ስለ ነበር ልምምዶቻቸውን በሥነ መለኮታዊ ትንታኔ ለማቅረብ ፍላጎቱ እምብዛም አይታይባቸውም ነበር። ፍላጎቱ ሲያድርባቸውም እንኳን ጉዳዮቹን በአዝልቆት ለመመርመርና ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚደረጉ ጥረቶች ደካማዎች ነበሩ። ይህም በጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች መካከል አለመቀባበልን ፈጥሮ ነበረ። ለምሳሌ፣ በመጀመሪያዎቹ ጴንጤቆስጤያውያን ሥነ መለኮት ላይ የጻፉት ዳግላስ ጃኮብሰን ለጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ መነሣት ምክንያት የነበረው ፓርሃም ሌሎች መሪዎችን እንደማይቀበል ዘግበው ነበር። ይህ ዐይነቱ አቋም የፓርሃም ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩት የጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ መሪዎችም የሚጋሩት ጭምር ነበር። ጃኮብሰን ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፡ – “ሁሉም የጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ መሪዎች ማለት ይቻላል ስለሌላው የጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ መሪ የሚናገሩት አሉታዊ ነገር ነበር” (ገጽ 316)።

ጥቂት ምክር ለዘመናችን ጴንጤቆስጤያውያን መሪዎች

በጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው የመሪነት አስተሳሰብ ለዘመናችን ጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች ትልቅ መልእክትን ያስተላልፋል። የእግዚአብሔርን መሪነት ከሁሉም በላይ አጽንዖት በመስጠት በሕይወታቸውና በአገልግሎታቸው እግዚአብሔርን ሊያከብሩ ይገባል። እነዚህ መሪዎች የአመራር አገልግሎታቸውን ከእግዚአብሔር እንዳገኙትም ማመን ይኖርባቸዋል። እነርሱን ለአመራር አገልግሎት የጠራው እግዚአብሔር ደግሞ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ የአመራር ጸጋን አስቀምጧል። በመሆኑም ጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች ዘርንም ሆነ ጾታን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን መሠረት በማድረግ ሊከሰት ከሚችል ከማንኛውም ዐይነት የአግላይነት ዝንባሌ በመራቅ ብዝኀነትን መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ለዚህ ደግሞ መልካም የጌታ ኢየሱስ ተከታይ መሆንን ይጠይቃል።

በሌላ በኩል የዘመናችን ጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች ቀደምት ጴንጤቆስጤያዊያኑ ከነበረባቸው እንከን ሊማሩም ይገባል። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ባለ ጠግነታቸውን ሳይለቁ የትምህርት ድኽነትን ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በላይ በእነዚያ ጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች ዘንድ የነበረውን አለመቀባበልን አርቀው መያያዝን መምረጥ ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ዘመን ያለን ጴንጤቆስጤያዊ መሪዎች ከታሪክ እንማር ይሆንን?


ዋቢ ጽሑፎች

  1. Anderson, A., Bergunder, M., Droogers, A., & Van der Laan, C. (Eds.) (2010). Studying global Pentecostalism: Theories and methods. Los Angeles, CA: University of California Press.
  2. Banks, R. & Ledbe er, B. M. (2004). Reviewing leadership: A Chris an evaluation of current approaches. Grand Rapids, MI: Baker.
  3. Jacobsen, Douglas (2003). Thinking in the Spirit: Theologies of the early Pentecostal Movement. Bloomington, IN: Indiana University Press.
  4. Jacobsen, Douglas (Ed.) (2006). A reader in Pentecostal theology: Voices from the first generation. Bloomington, IN: Indiana University Press.
  5. Robeck, C. M. (2002). Azusa Street revival. In Stanley M. Burgess, The new international dictionary of Pentecostal and Charisma c movements. (Revised and Expanded Ed.). Grand Rapids, MI: Zondervan.
  6. Tan-Chow, May Ling. (2007) Pentecostal theology for the twenty-first century: Engaging with multi-faith Singapore. Hampshire: Ashgate Publishing Limited.
    i ጥንታዊው ጴንጤቆስጤያዊነት በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ከዳግም ልደት በኋላ የሚከሰት ሁለተኛ ባርኮት (Second Blessing) እንደሆነና በልሳን መጸለይ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ዋና ምልክት እንደሆነ የሚያስተምር የጴንጤቆስጤያዊነት ክፍል ነው። ካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ ደግሞ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በተለያዩ ስጦታዎች (በልሳን መናገርን ጨምሮ) የሚያገለግሉ እንደሆኑና ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ አማኞች የግድ በልሳን ላይናገሩ እንደሚችሉ የሚያስተምር የጴንጤቆስጤ ክፍል ነው።

Lidetu Alemu (Dr.)

ዶ/ር ልደቱ ዓለሙ በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት (EGST)፣ የሊደርሺፕና የማኔጅመንት ፕሮግራም ኀላፊ እንዲሁም የሥነ አመራር መምህር ናቸው። ዶ/ር ልደቱ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ (Doctor of Veterinary Medicine)፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ከ“EGST” በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት (Biblical Studies) የማስተርስ ኦፍ ዲቪኒቲ (MDiv)፣ በመጨረሻም በአሜሪካን አገር፣ ፔንሲልቬንያ ግዛት ከሚገኘው “ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ” በድርጅታዊ አመራር (Organizational Leadership) የፒ.ኤች.ዲ. (Ph.D.) ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ለፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ ማሟያ ጥናት ያደረጉት፣ “The search for good leadership behaviors: A study of the relationship between second-order global leadership dimensions and ethical ideologies” በሚል ርእስ ሲሆን፣ በአራት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ማለትም፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እና በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ውስጥ መካከለኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች (mid-level managers) ላይ የተጠና ጥናት ነው። ዶ/ር ልደቱ ከማስተማሩ ሥራ ጎን ለጎን የምርምር ሥራ፣ የስብከትና፣ የአመራር ሥልጠናዎችን የሚያካሄዱ ሲሆን፣ “Emotional Intelligence” እና “Organizational Culture” በተባሉ ርእሶችም ልዩ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። ዶ/ር ልደቱ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው።

Share this article:

መስቀሉ፦ ሲሞን ቬይ

የክርስቶስ ስቃይ ያለ ጥርጥር ልዕለ ተፍጥሯዊ ፍትሕ ነው። ያሉትን የርኅራኄ ርዳታ ሁሉ ፍጹም የከለከል ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንኳ እንዳይራራለት ያደረገ ፍትሕ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

ፍትሕ ወይስ ምሕረት

ጸሐፊ፣ ተመራማሪ እና አስተማሪ የሆነው ምኒልክ አስፋው ከሚኖርበት አሜሪካ ሆኖ ስለ ፍትሕ እና ምሕርት/ይቅርታ ባዘጋጀው ጽሑፉ የዚህ ዕትም ዋና ርእሰ ጉዳይ ጸሐፊ ሆኖ ቀርቧል። ጽሑፉ በዋናነት ከፍትሕ እና ከምሕረት የትኛው የበለጠ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመጠቆም የተሰናዳ ነው። ምኒልክ ለዚህ መነሻ የሚያደርገውም እውቁን የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሟቹ ኔልሰን ማንዴላን ነው። እንደ እርሱ እምነት ከሆነ የማንዴላ የዕርቅ መንገድ በቅራኔ ለተሞላ ኅብረተ ሰብ ዐይነተኛ ምሳሌ ነው። ትልቅነት የሚለካውም ይቅር በሚሉና ምሕረት በሚያደርጉ ሰዎች የሕይወት ፈለግ መሆኑንም ይሞግታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ቃለ መጠይቅ ከአገኘሁ ይደግ ጋር

አገኘሁ ይደግ በኢትዮጵያ የወንጌላውያን አማኞች የዝማሬ አገልግሎት ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚነሡ ዘማሪያን መካከል የሚጠቀስ ነው። ዘመን ዘለቅ በሆኑት ዝማሬዎቹም ብዙዎች ተጽናንተዋል፣ ታንጸዋልም። የሕይወትን አስቸጋሪ ፈተናዎች በመቋቋም እግዚአብሔርን በጽናት ማገልገሉ ለአርኣያነት የሚያበቃው እንደ ሆነ የሚያውቁት ይናገራሉ። የዚህን ዘማሪ 25ኛ የአገልግሎትና 20ኛ የትዳር ዘመን በዓል ምክንያት በማድረግ ሕንጸት የቆይታ ዐምድ እንግዳ አድርጎታል። ጳውሎስ ፈቃዱ ከዘማሪ አገኘሁ ይደግ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.