[the_ad_group id=”107″]

መሪነትም እንደ ውበት

ለመሆኑ፣ የየቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች አንድን የአመራር ዘይቤ በሚመሯት ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንዲውል ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳሰቡት የአመራር ዘይቤውን ውጤታማነት ማየት ቢቸግራቸው ምን ማድረግ ይችላሉ? ወይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትጀመር ዐውዱን ባልጠበቀ መልኩ ተግባራዊ የተደረገ የአመራር ዘይቤ ቢኖር ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል? አንዴ ለምደውታልና የአመራር ዘይቤያቸውን ሳይለውጡ፣ በለመዱት ግን ውጤታማ ባልሆኑበት የአመራር ዘይቤ ጸንተው ይቀጥሉበትን? አንዴ የቤተ ክርስቲያናቸው አሠራር አካል ሆኗልና ከነችግሩ ይኑሩን? በአጠቃላይስ ለቅዱሳን የመታነጽ፣ ለቤተ ክርስቲያንም የዕድገት ምክንያት ሊሆን የታሰበው አመራር ለቅዱሳን የስብራት፣ ለቤተ ክርስቲያንም የውድቀት ምክንያት ሲሆን ዝም ብለው ይመልከቱን? ለእንደዚህ ዐይነቶቹ ሞጋች ጥያቄዎች ይረዳን ዘንድ መሪነትን ከውበት ጋር በማነጻጸር እንመልከተው።

ውበት ድንበር አለው፤ ውበት ክልል አለው። ውበት ድንበር ከሌለው፣ ውበት ክልል ከሌለው ለመዋብ ብለው ከንፈራቸውን ሰንጥቀው ገል የሚያንጠለጥሉትን ኢትዮጵያውያኑን የሙርሲ ጎሣዎችንና ተቀራራቢውን ነገር በጆሯቸው የሚያደርጉትን ኬንያውያኑን የማሳይ ጎሣዎችን ውበት የሚዳኘው ማነው? ያው ውበቱ የሚገኝበት ባህልና አካባቢ ካልሆነ በቀር የዚህን መሰሉን ውበት ውብነት አጽዳቂው ማነው? ደግሞስ የውበት ውብነቱ ከምኑ ላይ ነው? ከተለምዷዊው ዝርዝር ብንነሣ እንኳን ለአፍንጫ ከሰልካካነት ውጪ፣ ለዐይን ከዛጎልማነት ውጪ፣ ለጸጉር ከዞማነት ውጪ፣ ለተረከዝ ከሎሚነት ውጪ . . . ስንቱ ያስበዋል? ስንቱስ ይስማማበታል? የውበት ውብነቱ እንዲህ ወይም እንዲያ ከሆነ የአንደኛውን ወገን የውበት ዝርዝር ሌላኛው እንዴት ይቀበለዋል? አንደኛው የተቀበለውን የውበትን መስፈርትንስ ስንቱ ያጸድቀዋል? በመሆኑም ውበት ክልል አለው። እንደውም ውበት መልክኣ ምድራዊ ድንበርና ክልል ብቻ ሳይሆን የዘመንም ክልል አለው። እዚህችው የኢትዮጵያ መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ እንኳን የጸጉር ርዝማኔ በግሩም ውበትነቱ ተቆጥሮ “ይጠቀለላል እንደ ዘንዶ” እንዳልተባለለት ሁሉ ለውበት ተብሎ፣ ለማማር ተብሎ የስንት እኅቶቻችን ጸጉር የምላጭ ሲሳይ ሆነ?! ይህ እንግዲህ ልዩ ልዩ ዐይነት የሆነውን የጸጉር አሠራሩን፣ አለባበሱን፣ አጋጊያጡን ሳይጨምር ነው። እናም ሁሉም በየፈርጁ፣ በየክልሉ “ውበት” ተባለ፤ ባለ ውበቱም “ውብ” ተባለ። “ውበት እንደ ተመልካቹ ነው” እንዲሉ።

ታድያ ውበት እንደ ተመልካቹ ቢሆንም እንኳን ይኸው አንጻራዊ የሆነው ውበት በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈሪያ ወጥቶለትና መመዘኛ ተበጅቶለት እጅግ ብዙ እንስቶች የሚወዳደሩበት መስክ ሆኗል። በርግጥ ውድድሩ የቁንጅና ውድድር እንደ መሆኑ መጠን ውበት ላይ ቢያተኩርም፣ ሌሎች መለኪያዎችም አሉት (ተሰጥዖን እንደ ምሳሌነት ይጠቅሷል።) በየውድድሩ ፍጻሜም በመስፈርቱ መሠረት ከሁሉ አብላጫ ነጥብ ያስመዘገቡ እንስቶች እንዲሸለሙ ይደረጋል። አሸናፊዎቹ እንስቶችም የየአገሩን የቆንጆነት አክሊል ይደፋሉ። እነዚህ የአሸናፊነትን ማዕረግ የተቀዳጁት እንስቶችም የኢትዮጵያ ቆንጆ (Miss Ethiopia)”፣ “የፊሊፒንስ ቆንጆ (Miss Philippines)”፣ “የቻይና ቆንጆ (Miss China)”፣ “የዓለም ቆንጆ (Miss Universe)” እየተባሉ ይሞገሳሉ። ውበት እንደ ተመልካቹ ቢሆንም እንኳን በተደረሰበት ስምምነት መሠረት ተመዝኖ “የተሻለው ውበት” እውቅና ይሰጠዋል። የአሸናፊነት ማዕረጉን ማግኘት የሚሹቱ ሌሎች እንስቶችም ራሳቸውን ወደ መመዘኛው ለማድረስ ይተጋሉ። ግን ውበትን ይታደሉታል እንጂ ይካኑታል እንዴ?

መሪነትም እንደ ውበት ነው። ውበት እንደ ተመልካቹ እንደ ሆነ ሁሉ እንዲሁ መሪነትም እንደየተመልካቹ ነው። የውበት ውብነቱ እንደየባህሉ እንደሚለያይ እንዲሁ መሪነትም ከባህል ባህል ይለያያል። በአንደኛው አካባቢ የተሞገሰው የመሪነት ዘይቤ በሌላኛው ሰፈር ጭራሹኑ ላይታወቅ ይችላል። ይህ ዕሳቤ ይልቁኑ የጦዘው በሥነ አመራር ዙሪያ ከተሰማሩት ምሁራን ከግማሽ በላይ የሆኑቱ ከሰሜን አሜሪካ መሆናቸው ነው። እናም የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት አንድ ጥያቄ አጫረ፡- “እዚህ አሜሪካ በውጤታማነቱ የተመሰከረለት የአመራር ባሕርይ በሌላውም ዓለም እንዲሁ ሊሆን ይችላልን?” የሚል። የተጫረው ጥያቄ ጥያቄ ሆኖም አልቀረ፤ ለቀጣይ ምርምሮች በር ከፈተ እንጂ!

የውበት ውብነቱ እንደየባህሉ እንደሚለያይ እንዲሁ መሪነትም ከባህል ባህል ይለያያል።

“ውበት እንደ ተመልካቹ ነው” የሚለው ብኂል የእንግሊዝኛ አቻ አለው፡- “Beauty is in the eye of the beholder” የሚል። እናም ይህን የእንግሊዝኛውን ብኂል ርእስ በማድረግ የጥናት ጽሑፋቸውን እ.አ.አ. በ2006 ያሳተሙት የሥነ አመራር ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ አመራር እንደየባህሉ ይለያያል።1 ለነገሩ የጥናት ጽሑፋቸው ዋና መሠረት የነበረው በ60 የተለያዩ አገሮች ላይ በተደረገው ጥናት ላይ በመመርኮዝ የተጻፈውና እ.አ.አ. በ2004 የታተመው ዳጎስ ያለ ባለ 800 ገጽ መጽሐፍ ነው። ጥናቱ ያካተተው 60 አገሮችን ሲሆን፣ እያንዳንዱ አገር እንደ አንድ ማኅበረ ሰብ ሲወሰድ፣ ሁለት አገሮች ግን ካላቸው ባሕርይ የተነሣ ሁለት ሁለት ማኅበረ ሰቦች ተወስደውላቸው በድምሩ 62 ማኅበረ ሰቦች መጠናታቸውን ልብ ይሏል።

ይህ በመስኩ “የመጀመሪያ” የተባለለት መጽሐፍ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱትን 62 ማኅበረ ሰቦች ተመሳሳይ የሚያደርጓቸውን የባህል ገጽታዎች በመውሰድ ማኅበረ ሰቦቹን በዐሥር የከፈለ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ የማኅበረ ሰብ ቡድን ውስጥ ደግሞ “ተመራጭ” የሆኑትን የአመራር ባሕርያት በመዘርዘር ይተነትናል። በተለይ ደግሞ በሁሉም ማኅበረ ሰብ ውስጥ በውጤታማነታቸው ተመራጭ የሆኑ የአመራር ባሕርያት ተለይተው መታወቃቸው በሥነ አመራር መስክ አዲስ መረዳትን የፈነጠቀ ነበር። ይህም መረዳት ምንም እንኳን ውበት እንደ ተመልካቹ ቢለያይም፣ ሁሉም በሚስማማበት መልኩ ውበትን መመዘን እንደተቻለ እንዲሁ መሪነትም ከባህል ባህል የመለያየቱን ያህል በሁሉም ባህል ውስጥ በተመራጭነታቸው የጋራ የሆኑ የአመራር ባሕርያትን ነቅሶ ማውጣት መቻሉ (“ቻ” ይጠብቃል) ነው። ማለትም ለውጤታማነት ይረዳሉ ተብለው ከተለዩቱ የአመራር ባሕርያት ውስጥ አንዳንዶቹ በሁሉም ዘንድ እውቅናን (Universal endorsement) ማግኘታቸው በሥነ አመራር መስክ ትልቅ እመርታ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህንን አስተዋጽዖውንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የጥናት ቡድኑ ከተለያዩ የአሜሪካ ተቋማት ሽልማት ተበርክቶለታል።

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እንደሚነሣ ይታሰባል፡ – “ለመሆኑ እነዚህ በሁሉም ማኅበረ ሰብ ውስጥ በውጤታማነታቸው ተመራጭ የሆኑቱ የአመራር ባሕርያት ስንት ናቸው? ደግሞስ ምን ምን በመባል ይታወቃሉ?” የሚል። በአጠቃላይ መጽሐፉ ስድስት የአመራር ባሕርያትን በመዘርዘር የተነተነ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በሁሉም ማኅበረ ሰብ ውስጥ በውጤታማነታቸው ተመራጭ የሆኑ የአመራር ባሕርያት ናቸው። እነዚህ ተመራጭ የአመራር ባሕርያት ካሪዝማዊአመራር(Charisma c/Value-based)፣ የቡድን አመራር (Team Oriented)፣ አሳትፌ አመራር (Par cipa ve) እና የርኅራኄ አመራር (Humane Oriented) ተብለው ተሰይመዋል። ቀሪዎቹ ሁለት የአመራር ባሕርያት፣ ማለትም ራስ አድን አመራር (Self-Protec ve) እና ራስ ገዝ አመራር (Autonomous) ተመራጭነታቸው ከባህል ባህል ይለያያል። ይህ ማለት ፊተኞቹ የአመራር ባሕርያት በሁሉም ማኅበረ ሰብ በውጤታማነታቸው ተመራጭ ወይም ተፈላጊ የአመራር ባሕርያት ሲሆኑ፣ ኋለኞቹ ግን ተመራጭነታቸው ወይም ተፈላጊነታቸው ከማኅበረ ሰብ ማኅበረ ሰብ የሚለያይ ነው። በዚህ በዛሬው መጣጥፍ ከቦታ ውስንነት የተነሣ እነዚህን በዝርዝር ለመዳሰስ የማይቻል ሲሆን፣ ወደፊት ግን እንደ አስፈላጊነታቸው የሚቃኙ ይሆናል። ቢሆንም ከእነዚህ ተፈላጊ የአመራር ባሕርያት ዝርዝር አንድ መረዳት የሚያስፈልገን ነገር አለ። ይህም የአመራር ዘይቤ ከባህል ባህል “ይለያያል”፣ “ውበት እንደ ተመልቹ እንደ ሆነ ሁሉ አመራርም እንዲሁ ነው” ቢባልም፣ በሁሉም ባህል የጸደቁና ተቀባይነትን ያገኙ (Universally endorsed) የአመራር ባሕርያት እንዳሉ ሊሠመርበት ይገባል። ተመራጭነታቸውም በአንድ ተቋም ውስጥ ሊያስገኙ ከሚችሉት ውጤታማነት የተነሣ ነው። በሌላ አባባል መሪዎች የባህል ድንበር ሳይገድባቸው እነዚህን የአመራር ባሕርያት እንደ አስፈላጊነታቸው መጠን ቢለማመዷቸው በረከትን፣ ዕድገትን፣ የበለጠ ውጤታማነትን ወደሚመሯቸው ቤተ ክርስቲያናት ወይም ልዩ ልዩ ተቋማት ማምጣት ይችላሉ።

ከዚህ በመነሣት እኛም ክርስቲያኖች ከባህሉ ውጪ አንሆንምና በባህላችን፣ አልፎ ተርፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆኑቱ የአመራር ባሕርያት አስፈላጊ ሆነው ስናገኛቸው ልንጠቀምባቸው እንደምንችል መጽሐፉ ጠቋሚ ነው። በተለይም፣ ከላይ በዚህ መጣጥፍ ጅማሬ ላይ በተሰደሩትና በሌሎች ሞጋች ጥያቄዎች ስንከበብ ቆም ብለን ዙሪያ ገባችንን ማየትና ያሉንን የአመራር አማራጮች ማሰብ ብልኅነት ነው። ‘ይህ የአመራር ዘይቤ በቤተ ክርስቲያናችን የቆየ አሠራር ነው፤ ይህ ዐይነቱ አመራር በቤተ ክርስቲያናችን የተለመደ ነው’ እያሉ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ትውልድን መጉዳት እጅግ የከበደ የመሪዎች በደል ነው። መሪዎች የአዎንታዊ ለውጥ ምክንያት ሊሆኑ ሲገባቸው የለውጡ ሐሳብ ከጎፈነናቸው ቤተ ክርስቲያንን ለትልቅ ውድቀት እያንደረደሯት ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ረገድ ሙሴ ትልቅ ምሳሌ ይሆነናል።

ሙሴ ካሪዝማዊ መሪ ነው። ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ መሠረት ካሪዝማዊ መሪዎች ተከታዮቻቸውን ለታሰበው ዓላማ የመቀስቀስ፣ የማነሣሣት እንዲሁም ሊደረስበት የታሰበውን ስኬት የማሳየት ችሎታ ያላቸው ናቸው። እነዚህ መሪዎች ባለ ራእዮች ደግሞም ያዩትን ለመጨበጥ በእውነተኛነትና በቆራጥነት የሚተጉ ናቸው። እንዲሁ ሙሴም ለእስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ቤት የመውጣታቸውን የምሥራች በማሰማት ልባቸውን የቀሰቀሰ (ዘፀ. 4፥29-31)፣ ልባቸው ሲደነግጥ ያደፋፈረ (ዘፀ. 14፥13-14፤ 12፥26-28)፣ ፈርዖን ልቡን አደንድኖ “እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም አልለቅም” (ዘፀ. 5፥2) ሲል በቆራጥነት ሕዝቡን እንዲለቅ በመናገር በፊቱ ተኣምራትን ያደረገ (ዘፀ. 7-12)፣ ደግሞም እስራኤላውያን እግዚአብሔርን የሚከተሉበትንና ሕይወታቸውንም የሚመሩበትን ሕግ ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ያስተላለፈ (ዘፀ. 19-20) ካሪዝማዊ መሪ ነው።

ሙሴ ከካሪዝማዊ መሪነቱ በተጨማሪ አሳትፌ (Participative) መሪም ነበር። ሙሴ የአሳትፌ መሪነትን በተለየ መንገድ መለማመድ የጀመረው በአማቱ በዮቶር አማካይነት በሕዝቡ ላይ በየደረጃው የሺህ አለቆችን፣ የመቶ አለቆችን፣ የኀምሣ አለቆችን እና የዐሥር አለቆችን እንዲሾም በመከረውና ተግባራዊ ባደረገ ጊዜ ነበር (ዘፀ. 18)። እዚህ ላይ የአመራር ሥራውን ሁሉ ጠቅልሎ ይዞ ለነበረው ለሙሴ ዮቶር ምክሩን ሲጀምር፣ “የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም” (ዘፀ. 18፥17) ማለቱን ልብ ይሏል! ሙሴ ከእግዚአብሔር በቀጥታ የመሪነትን ጥሪ የተቀበለና ካሪዝማዊ አመራሩ በግልጽ የታየ መሪ ቢሆንም እንኳን፣ አሁን ከደረሰበት ደረጃ አንጻር ግን “መልካም” አመራርን እየተገበረ አልነበረምና ወደ አመራር ሕይወቱ አሳትፌ አመራርን ሲያስገባ እንመለከታለን። ይህ በዚህ ዘመን ላሉ መሪዎች ትልቅ ምሳሌነት አለው። ሙሴ በብዙ ዐሥርት ዓመታት የአመራር ልምዱ ሳይመካ ወይም በአጉል መንፈሳዊነት ‘ይህ ከእግዚአብሔር የመጣልኝ የመሪነት መለኮታዊ ጥሪ ነው፤ ደግሞም ባለ ራእዩ እኔ ነኝ’ በማለት ራሱን ሳይደልል ከዚህ በፊት የመሪነት

ልምድ ይኑረው አይኑረው በውል የማይታወቀውን፣ ግን ምክሩ ትክክል የነበረውን አማቱ ዮቶርን መስማቱ ለዘመኑ መሪዎች ትልቅ ትምህርት ነው። ሠናይ መሪዎች በየጊዜው ውጤታማ የሆነውን የአመራርን ዘይቤ በመላበስ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ይተጋሉ። ሠናይ መሪዎች እንደሚገባ አላሠራ ያላቸውን ዕድሜ ጠገብ የአመራር ዘይቤ ለመቀየር ትሑታን ናቸው።

ስለዚህም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ቆጥሮ በሰጣችሁ በአመራር አገልግሎታችሁ የበለጠ ፍሬያማ እንድትሆኑለት ይፈልጋል። በመሆኑም፣ እባካችሁ አሁን እየተከተላችሁትና እየተለማመዳችሁት ያለው የአመራር ዘይቤ አላስኬድ ቢላችሁ ቆም ብላችሁ ዐስቡ። ይህ አስተዋይነት ነው፤ መንፈሳዊነትም ነው። ለተተኪው የመሪ ትውልድ ልታስተላልፉለት ከምትችሉት እጅግ በርካታ ቁም ነገሮች መካከል ‘ተሳስቼ ነበር!’ የሚለውንም ጭምር እንደ ሆነ ልብ በሉ። በዚህ አድራጎታችሁ የቤተ ክርስቲያንን የወደፊት ገጽታ ትወስናላችሁ። በቡድን እያገለገላችሁ ነውን? መልካም አድርጋችኋል። ደግሞም ለምታገለግሏቸው ሰዎች በማሰብ፣ በመራራት (“Humane Oriented” በመሆን) አገልግሉ። በቡድን ማገልገላችሁ ብቻውን በቂ አይደለምና። በቡድን እየመሩ ቤተ ክርስቲያንን ቀውስ ውስጥ መክተት አለና! ካሪዝማቲክ መሪዎች ናችሁን? እርሱም መልካም ነው። ይሁንና ሁልጊዜ ሁሉንም ነገር እናንተ ማድረግ አይጠበቅባችሁምና ሌሎችንም ጸጋቸውን እያያችሁ አሰማሯቸው፤ በአመራርም ውስጥ አሳትፏቸው። ያኔ ሠናይ መሪ በመሆናችሁ ከእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ብድራትን ትቀበላላችሁ፤ ለሚመጣውም ትውልድ መልካም ታሪክን ታወርሳላችሁ። ውበት እንደሆነው ሁሉ እንዲሁ መሪነትም እንደየተመልካቹ ይለያያል። እናንተ “ውብ” ያላችሁት ውበት የውበትን ሚዛን ካልደፋ ከውበት ጎራ ልቆ እንደማይወጣ እንዲሁ “ግሩም” ያላችሁትም መሪነት ተመዝኖ አይከብድ ይሆናል። እናም የአመራር ዘይቤያችሁ ሠናይ ይሆን ዘንድ ራስን መፈተሹ የክብር መንገድ ይሆንላችኋል። ሠናይ የአመራር ዘመንን እመኝላችኋለሁ! 


የግርጌ ማስታወሻ

  1. Javidan, M., Dorfman, P. W., De Luque, M. S., & House, R. J. (2006). In the eye of the beholder: Cross cultural lessons in leadership from Project GLOBE. Academy of Management Perspec ve, 20(1): 67–91. Retrieved from: www.jstor.org
  2. House, R. J., Hanges, P. J., Javidan, M., Dorfman, P. W., & Gupta, V. (Eds.). (2004). Culture, leadership, and organiza ons: The GLOBE study of 62 socie es. Thousand Oaks, CA: Sage.

Share this article:

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.