[the_ad_group id=”107″]

መሪነት

ወሳኙ ጉዳይ

ʻመሪዎች ለሁሉም ዐይነት ተቋማዊ ችግር ፍቱን መድኃኒቶች ናቸውን?ʼ በርግጥ በአመራር ላይ ጥናት ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን መሪዎችን እንዲህ ባለ መልክ አያቀርቧቸውም። እጅግ የተደነቁቱ የአመራር ዘይቤዎችም ሳይቀሩ (ለምሳሌ፡- ሎሌያዊ አመራር – “Servant Leadership” እና ተሃድሷዊ አመራር – “Transformational Leadership”) ላለንበት ተቋማዊም ሆነ አገራዊ ችግር ብቸኛ መፍትሔ እንዳይደሉ እነዚሁ ምሁራን ይስማማሉ። ይህን አቋማቸውን “Leadership is not a panacea to all our problems” በማለት ነው የሚገልጡት – መሪነት ለችግሮቻችን ሁሉ ፍቱን መድኃኒት አይደለም እንደማለት ነው። ይህ ሲባል ግን የመሪዎች ሚና እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ታሪክ በመሪዎች እጅ ውስጥ ነው። የአገርም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በመሪዎች እጅ ውስጥ ነው። የአገር እና የልዩ ልዩ ተቋማት የቤተ ክርስቲያንም ጭምር ውድቀታቸውም ሆነ መነሣታቸው በመሪዎች እጅ ውስጥ ነው። በመልካም መሪዎች አመራር በቤተ ክርስቲያን በረከት ይሆናል፤ በአንጻሩ በመልካም መሪዎች ዕጦት ቤተ ክርስቲያን ስብራት ውስጥ ትገባለች። በረከቱም ሆነ ስብራቱ ደግሞ ለአገር ይተርፋል። በአገር ደረጃም እንዲሁ ነው። አንዲት አገር መልካም መሪዎች ቢኖሯት አገሪቱን በሰላምና በእድገት ጎዳና ይመሯታል። ምንም እንኳን ለዚህ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ መሪዎችን ምክንያት ማድረግ ባይቻልም፣ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ግን መሪዎች ናቸው። በሌላ አባባል ተከታዮች ወይም ውጪያዊ መንስዔዎች በውድቀትም ሆነ በመነሣት ሂደት ውስጥ ድርሻ የላቸውም ማለት አይደለም። ለማለት የተፈለገው ጉዳይ፣ ተከታዮች እና ውጪያዊ ኀይላት ምንም ያህል ድርሻ ቢኖራቸውም እንኳን መሪዎች ከሚከተሉት የአመራር ዘይቤ፣ በአጠቃላይም መሪዎች ከተላበሱት ባሕርይ የተነሣ የተበላሸውን የማስተካከል፣ የተጣመመውን የማቅናት፣ የወደቀውን የማንሣት፣ የፈረሰውን የመጠገን፣ የተበተነውን የመሰብሰብ፣ የታመመውን የማከም፣ እንደውም የሞተውን የማስነሣት ማንነት ውስጣቸው አለ። ይህን ስል “መሪዎች መለኮት ናቸው” እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፤ በድርጅታዊ አመራር ውስጥ ተቋማዊ ነፍስ በመዝራት ሊጫወቱ የሚችሉትን ሚና ለማሳየት አስቤ እንጂ።

ይህንን እውነታ የቤተ ክርስቲያን የተሃድሶ አባት ከሆነው ማርቲን ሉተር አገልግሎት መገንዘብ እንችላለን። ስለዚህም የመሪዎች ጉዳይ ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ መሪዎች የሚከተሉት የአመራር ዘይቤ ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ መሪዎች የተላበሱት ባሕርይም እንዲሁ ወሳኝ ጉዳይ ነው። በአጭሩ መሪዎች መልካም ሲሆኑና መልካም አመራርን ሲከተሉ ቤተ ክርስቲያን መልካም ትሆናለች፤ በተቃራኒው መሪዎች ከመልካምነት ጎዳና ሲወጡ እንዲሁ ቤተ ክርስቲያንንም ከመልካም ጎዳና እንድትወጣ በማድረግ መልኳ እንዲጎድፍ ያደርጋሉ። መሪዎች በመልካምነት ሲነሡ ቤተ ክርስቲያንም በመልካምነቷ ትነሣለች፤ መሪዎች ከከፍታቸው ሲወድቁም ቤተ ክርስቲያንም አብራቸው ትወድቃለች። መሪዎች ተግባራቸውም ሆነ ሕይወታቸው ሚዛን ሲደፋ ቤተ ክርስቲያን ትከብራለች፤ ከሚዛኑ ሲጎድሉ ግን ቤተ ክርስቲያን ከክብር ትጎድላለች።

መሪዎች በመልካምነት ሲነሡ ቤተ ክርስቲያንም በመልካምነቷ ትነሣለች፤ መሪዎች ከከፍታቸው ሲወድቁም ቤተ ክርስቲያንም አብራቸው ትወድቃለች። መሪዎች ተግባራቸውም ሆነ ሕይወታቸው ሚዛን ሲደፋ ቤተ ክርስቲያን ትከብራለች፤ ከሚዛኑ ሲጎድሉ ግን ቤተ ክርስቲያን ከክብር ትጎድላለች።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፡- “በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ” (መሳ. 5፥2)። በዚህ ክፍል መሠረት ለእግዚአብሔር የሚሆን ምሥጋና ሊመጣ የሚችለው የሁለቱ ወገኖች (የመሪዎች እና የሕዝቡ) አዎንታዊ ተሳትፎ ነው። “ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው” በሰጡ ሰዎች መካከል እንደሚገባ የሚመሩ መሪዎች ሲገኙ ለእግዚአብሔር የሚሆነው ምሥጋና ይበዛል። አሁን ያለንበት ሁኔታ “ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን” (መሳ. 17፥6) እንደሚያደርግበት እንደ እስራኤሉ የመሳፍንት ዘመን ከመምሰሉ የተነሣ የሕዝቡን የመሰጠት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ልናስገባ እንችል ይሆናል። ከዚህ የተነሣም አንድ ሰው ʻምናልባት ሕዝቡ ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ባይሰጡ ምን ይፈጠራል?ʼ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ለዚህ መልሱ ʻየመሪው ሥራ ይከብዳል እንጂ፣ ደግሞም ጊዜ ይወስዳል እንጂ ሕዝቡ ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው በመስጠት ለእግዚአብሔር የሚሆን ምሥጋና ማምጣታቸው አይቀርምʼ የሚል ይሆናል። እንዴት ሊሆን ይችላል? ይህ ሊሆን የሚችለው መሪው ከሚከተለው የአመራር ዘዬ እና ከተላሰበሰው የመሪነት ባሕርይ የተነሣ የሕዝብን ልብ ለእግዚአብሔር ሥራ ማሸነፍ እና መማረክ ይችላልና ነው። የሕዝብ፣ የተከታይ ትብብር የመሪን ሥራ ቀሊል ያደርገዋል። የሕዝብ፣ የተከታይ ትብብር ባይኖር፣ ነገር ግን የመሪዎች ሁኔታ ጤናማ ከሆነ ጊዜ ይወስዳል እንጂ፣ ዋጋ ያስከፍላል እንጂ የእግዚአብሔር ምሥጋና አይቀርም። ካልሆነማ የመሪ መሪነቱ ከምኑ ላይ ነው? ስለዚህም ቁልፉ በመሪዎች እጅ ውስጥ ነው፤ ታሪክም እንዲሁ በመሪዎች እጅ ውስጥ ነው። የመሪዎች ጉዳይ ወሳኝ ጉዳይ ነው!

በእርግጥም ታሪክ በመሪዎች እጅ ውስጥ መሆኑን፣ በእርግጥም መሪዎች ለአንድ ሕዝብ ለመነሣቱም ሆነ ለውድቀቱ ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ከብሉይ ኪዳኑ የእስራኤል ታሪክ እንማራለን። የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ (ኋላም ደቡባዊና ሰሜናዊ መንግሥት ሆኖ በሰሎሞን ልጅ በንጉሥ ሮብዓም ዘመን ለሁለት ከተከፈለ በኋላ) የኖረው ኑሮ የነገሥታቱን ኑሮ ነበር። የነገሥታቱ ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር ሲሰምር የሕዝቡም ሕይወት አብሮ ይሰምር ነበር፤ እንዲሁም ነገሥታቱ ከእግዚአብሔር መንገድ ርቀው ጣዖት በማምለክ ሕይወታቸው ሲረክስ ሕዝቡም በሚያሳዝን ሁኔታ አብሯቸው ይረክስ ነበር። በእነዚያ ዘመናት ለሕዝቡ የመቀደስም ሆነ የመርከስ ምክንያቶቹ መሪዎቹ፣ ማለትም ነገሥታቱ ነበሩ። ለዚህ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም አባትና ልጅ የሆኑትን ሁለቱን የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጥቀስ በቂ ይሆናል። እነዚህም ንጉሥ ሕዝቅያስና ልጁ ንጉሥ ምናሴ ናቸው።

ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ ከታሪኩ እንደምንመለከተው መልካም አመራርን የሚከተል መሪ ነበር። በአባቱ በንጉሥ አካዝ ዘመን ከሆነው እግዚአብሔርን ከሚያሳዝን ነገር ከመራቅ አልፎ በአባቱ ዘመን የተሠሩትን ክፉ ነገሮች ከምድሪቱ ለማስወገድ ቆርጦ የተነሣ ሰው ነበር። የሁለተኛ ነገሥት ጸሐፊ ስለ እርሱ መልካም የአመራር ዘመን ሲጽፍ “ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም” (2ነገ. 18፥5) ብሏል። ጸሐፊው እንዲህ ባለ መንገድ ለመጻፉ ምክንያቱ ምን እንደ ሆነ ማጥናት የንጉሥ ሕዝቅያስንና የተቀሩትን የይሁዳ ነገሥታትን ሕይወት ማወዳደር የሚያስፈልገን ሲሆን፣ ይህን ማድረግ ደግሞ ከዚህ መጣጥፍ መነሻ ሐሳብ ስለሚያወጣን መተዉ የግድ ይሆናል። በመሆኑም የሕዝቅያስን መልካም የአመራርን ሕይወት ብቻ ወደማየቱ እንዘልቃለን።

ንጉሥ ሕዝቅያስ እንደ ነገሠ፣ ማለትም በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ተዘግተው የነበሩትን “የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች” መክፈትና ማደስ ነበር (2ዜና 29፥3)። ካህናቱ ሌዋውያን አገልግሎታቸውን ትተው ነበረና ወደ አገልግሎታቸው እንዲመለሱና ከያሉበት እንዲመጡ በማድረግ “ልጆቼ ሆይ፥ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ” እያለ በማበረታታት አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ አደረገ (2ዜና 29፥4-11)። በዚህ በተሃድሶ ሐሳብ የተጀመረው የሕዝቅያስ የአመራር ዘመን የቀጠለው በእግዚአብሔር ቤት እና በምድሪቱ የነበረውን ጸያፍ ነገር በማስወገድ ነበር (2ዜና 29፥15-19)። በሁለተኛ ነገሥት እንደተገለጸው ሕዝቅያስ “በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፥ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ ስሙንም ነሑሽታን ብሎ ጠራው” (2ነገ. 18፥4)። የይሁዳን አለቆችንና ሕዝቡን በማስተባበርም ተቋርጦ የነበረውን አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደገና እንዲጀመር አስደረገ (2ዜና 29፥20-36)።

የአሦር ንጉሥ ሰሜን እስራኤልን ያፈለሰው በሕዝቅያስ ስድስተኛ የንግሥና ዓመት ላይ ሲሆን (2ነገ. 18፥10)፣ ተመሳሳይ ሥራውን ከስምንት ዓመት በኋላ በይሁዳ ላይ ሊፈጽም ሲነሣ (2ነገ. 18፥13) ንጉሡ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ላይ ከነበረው መታመን እና መደገፍ የተነሣ እግዚአብሔር መልኣኩን ልኮ በታላቅ ማዳን እንዳዳናቸው በሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ታሪኩ ተመዝገቧል (2ነገ. 18-19፤ 2ዜና 32፤ ኢሳ 36-37)።

እነዚህ ክስተቶች ንጉሥ ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር ጋር የሠመረ ሕይወት እንደነበረው የሚያሳዩ ሲሆኑ፣ ይህ መልካም ሕይወቱና እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገው የአመራር ዘይቤው የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዮቹ ካህናትም ጭምር ልባቸውንና ሐሳባቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲመልሱ ምክንያት ሆኗል።

በተቃራኒው የልጁ የንጉሥ ምናሴ ሕይወት ግን እንደ አባቱ እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ አልነበረም። ምንም እንኳን ከነገሥታቱ ሁሉ ለብዙ ዓመታት የነገሠው ምናሴ ቢሆንም (ለ55 ዓመታት – 2ነገ. 21፥1) እጅግ ክፉ ነገርን በእግዚአብሔር ፊት ካደረጉ ነገሥታት ዋንኛው ነበረ። ኀጢአቱ የተነጻጸረውም እግዚአብሔር ከከነዓን ካወጣቸው አሕዛብ ሕይወት ጋር ነበር፤ “እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ”(2ዜና 33፥2)። ካደረጋቸው ክፉ ነገሮች መካከል “አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፥ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበኣል መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸው” (2ነገ. 21፥3፤ 2ዜና 33፥3)፤ “እግዚአብሔርም፦ ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ” (2ነገ. 21፥4፤ 2ዜና 33፥4)፤ “ልጁንም በእሳት አሳለፈ፥ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ” (2ነገ. 21፥6፤ 2ዜና 33፥6)፤ “ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ” (2ነገ. 21፥16)።

በእነዚህ ክፉ ድርጊቶቹ እስራኤልን በጠማማ መንገድ እንዲሄዱ አደረጋቸው፤ “እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው” (2ነገ. 21፥9፤ 2ዜና 33፥9)። በመሆኑም እግዚአብሔር በሰሜን እስራኤል የደረሰው ነገር ሁሉ በይሁዳም እንደሚደገም ተናገረ፡-

እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት እጅ እንዲህ ሲል ተናገረ። የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ርኵሰት አድርጎአልና፥ ከፊቱም የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሥራ ሠርቶአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና፣ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ ሰውም ወጭቱን እንዲወለውል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ። የርስቴንም ቅሬታ እጥላለሁ፥ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ። (2ነገ. 21፥10-14)

የንጉሥ ምናሴ ሕይወት ሌላ የሚያስተምረን ቁም ነገር አለ። እንዲህ ምሳሌ እስከማይገኝለት ድረስ ከእግዚአብሔር መንገድ ለወጣውና ይሁዳን ላሳተው ለንጉሥ ምናሴ እግዚአብሔር ሌላ እድል እንደሰጠው የሁለተኛ ዜና ጸሐፊ ከጻፈው ታሪክ እንማራለን። ይህም የእግዚአብሔርን የርኅራኄ ልክ፣ የምሕረቱንም ብዛት ጉልሕ በሆነ መልኩ እንማርበታለን። በጣም ደስ የሚለው ነገር ደግሞ ንጉሥ ምናሴ በተሠጠው እድል መጠቀሙ ነው።

እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው ግን አልሰሙትም። ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ፤ ወደ እርሱም ጸለየ እርሱም ተለመነው፤ ጸሎቱንም ሰማው፤ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ አወቀ። . . . እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፤ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው። የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፤ የደኅንነትና የምስጋናም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ። ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር። (2ዜና 33፥10-17)

በእርግጥም ታሪክ በመሪዎች እጅ ውስጥ ነው፤ በእርግጥም መሪዎች ወሳኞች ናቸው። ከላይ ከሁለቱ አባትና ልጅ መሪዎች ሕይወት እንደተመለከትነው መሪዎች በጎ ወይም ክፉ በሆነ መንገድ የሕዝባቸውን ሕይወት ይቃኛሉ። የእነርሱ ሕይወት በጎ ከሆነ የሕዝባቸውም ሕይወት በጎ ይሆናል። በተቃራኒው ደግሞ የእነርሱ ሕይወት ክፉ ከሆነ የሕዝባቸውም ሕይወት በክፋት የተሞላ ይሆናል።

በማንኛውም ዐይነት ተቋም ውስጥ በመሪነት ሥፍራ ያለን ወገኖች ራሳችንና የአመራር አገልግሎታችንን በዚህ የታሪክ መስታወትነት መፈተሽ ተገቢ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። እንደ ፈሪሳዊያኑ ራስ ጸደቅ ካልሆንን በቀር አሁን በየቤተ ክርስቲያኑ ላለው መልካም ላልሆነው ነገር፣ ከመካከላችንም አልፎ አደባባይ ለወጣው ነውር መሪዎች ትልቁን ሚና እንደተጫወትን እናስብ ይሆን? እያሰብን ካልሆነ ቆም ብሎ ማሰቡ ጠቃሚ ይሆናል። እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን!

Share this article:

“የክርስቲያን ሚዲያዎች ሲታዩና ተግባራቸው ሲገመገምም አብዛኛዎቹ አንባቢውንም ሆነ ተመልካቹን የማይመጥኑ…ሆነው እናገኛቸዋለን” – ቃለ መጠይቅ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር

ሚክያስ በላይ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡን በሚመለከት ስለ ኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም፣ አብያተ ክርስቲያናት ከኅብረተ ሰቡ ጋር ስላላቸው መስተጋብር እንዲሁም በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያንን አመራር ጋር ሊያያዙ በሚችሉ ጭብጦች ዙሪያ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢየሱስ ጥያቄ፤ ኢየሱስ መልስ

ሕንጸት ከልደት (ገና) በዓል በፊት ቀጣዩ ቅጿ እንደማይደርስ በማሰብ ዛሬውኑ “እንኳን አደረሳችሁ” ማለቴ የወግ ነው። ከመልካም ምኞት መግለጫዬ በላይ ግን የክብረ በዓሉን ምክንያት በዚህ መልኩ ብናየው በማለት ይህችን ከትቤአለሁ። ጥያቄና መልስ።

ተጨማሪ ያንብቡ

የገንዘብ ጣጣ

ለስምንት ዓመታት የወጣቶች መጋቢ በመሆን ሲያገለግል የቆየው የ42 ዓመቱ መጋቢ ኑዛዜ አስደንጋጭ ነበር። መጋቢው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በጉባኤ ፊት ቆሞ “በእግዚአብሔር፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼ፣ በቤተ ሰቦቼና የክርስቶስ አካል በሆነችው ኮሎራዶ በምትገኘው የኢውዛ ባይብል ቤተ ክርስቲያን ፊት ኀጢአትን አድርጌአለሁ” በማለት ተናገረ። ላለፉት ስድስት ዓመታት ከቤተ ክርሰቲያኒቱ የመባ መሰብሰቢያ ዕቃ ውስጥና እርሱ ከሚመራው አገልግሎት ከወጣቶች ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 42,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን በመውሰድ ለራሱ ጥቅም ያውል እንደነበርና ይህንን ወንጀሉን ከትዳር አጋሩም ሰውሮ ያደርግ እንደ ነበር በመግለጽ እራሱን በቤተ ክርሰቲያኒቱ መሪዎች አና በአገሪቱ ሕግ ተጠያቂ ለማድርግ እንደ ወሰነ ተናገረ። በዚህም ምክንያት በማጭበርበርና በስርቆት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.