[the_ad_group id=”107″]

እንባዬን ተዉልኝ፤ ግና “አልዝምም”

ማቴቴስ ትሰኝ የነበረችውን መጽሔትና መላውን ብርዕ ጨባጮቿን ጥረት እያሰላሰልሁ፣ ደግሞም ሕንጸት ይሏትን ዐዲስ መጽሔት መከሠት እያሰብሁ በነበረበት አንዲት ምሽት እንዲህ፣ እንዲህ ሲሰማኝና እንዲህ፣ እንዲህ በሐሳብ ስዛቍን (ስለፋ) አመሸሁ። መጽሔቶቹም የሕይወትን ትዝታና ተስፋ በግርድፉ የማነጽርባቸው ጊዜያዊ ትእምርቶች መስለው ታዩኝ። ሐሳቤ ታዲያ ወደ ኋላና ወደ ፊት መንጠሩ አልቀረም፤ ማቴቴስ ከኋላ ሕንጸት ከፊት ለፊት። ማቴቴስ አሁን በኅትመት ላይ አይደለችምና “የት ገባች” የማለትን ነገር ብትጠይቁኝ፣ መልሱን በይፋ ለመስጠት ዕውቀቱም ሥልጣኑም የለኝም። በመገኘቷ ዘመን ልሳኗን ይዋስ እንደ ነበረ ጸሐፊ ብቻ፣ ባለመገኘቷ የሚሰማኝን አንዳች ግላዊ ስሜትና ተዛምዶኣዊ ትምህርት (lesson) መተንፈሴ አይቀሬ ኾኖብኝ ነው። ስለ ሕንጸት ደግሞ በተስፋ ደስ ቢለኝ የሞነጨርኩት ታክሎበት የቀረበ ነው። እነሆ በረከት…

ከሁሉ አስቀድሜ ማቴቴስን የጀመሯትን፣ የመሯትንና የጻፉባትን ሁሉ ማመስገን አለብኝ። ለልፋታቸው፣ ለጥረታቸው፣ ላበረከቱት ሐሳቦችና እይታዎቻቸው ባርኔጣዬን በአክብሮት አነሣለሁ፤ በምናቤስ ይህን ሳላደርግ እቀራለሁ ብላችሁ ነው? የበላበትን ወጪት ሰባሪ መኾን አልፈልግምና ነው። በ22 ቅጾቿ ስንት ቁም ነገር ተነሣ፣ ስንትስ ሐሳብ ተወሳ? ብዙ፣ ብዙ በጣም ብዙ ነው። በተለይ ከዐዲስና ማራኪ ንድፏ ጋር ታትሞ የነበረው የመጨረሻው ቅጿ ያስተናገደው ርእሰ ጕዳይ የሚያነቃም፣ የሚደንቅም፣ የሚያንቅም፣ የሚነቀንቅም… እንደ ነበር አይረሳንም።

ርግጥ ነው፤ ከመጽሔቷ ኀዘን ጋር ስንቆዝምና ከተስፋዎቿ ጋር ስንደሰት ዓመታትን ዐልፈናል። የአምላካችን የጸጋው ክብር ይመስገን ዘንድ በደካማዎቹ ሰዎች የሠራውን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ይህን ሳውጠነጥን የዛሬው አለመኖሯ በኅሊናዬ ጓዳ ብቅ አለብኝና አንባቢዎቿ ያረበበባቸው ቍዘማ ደግሞ ታሰበኝ። እርሱን ተከትሎም የገጣሚ አበባው መላኩ ስንኝ ውልብ አለብኝ። ምንጩ ሳይነጥፍ፣ ውርሳችን ሳይጐድፍ የዘራነው ሳይመክን አልቀጥል የሚልበት ማኅበረ ሰባዊ መብከንከን ውስጡን ያጋየው ሰው ሁሉ በሚያስታውሳት “አለም ማያ” ግጥም ውስጥ ትገኛለች። እርሷም፦

“… ርግማንኾኖብን፣ ባበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም ” የምትል ናት።

ግን ደግሞ፣ “ይሁና” እላለሁ። ወዲያውም እንዲህ ያስመለክተኛል፦ ዮሐንስ አድማሱ እስኪ ተጠየቁ በሚለው መድበሉ “ተወርዋሪ ኮከብ” የተሰኘች ወርቃማ ግጥም አለችው። “የሚዳሰስ ጨለማ አካል ነሥቶ” ምድርን በከደነበት ወቅት እንደ ብራቅ ደምቆ የበራ ለመሰለው ሰው (ዮፍታሔ ንጉሤ ነው) እንዲህ ብሎለታል።

ተወርወሪ ኮከብ፣ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ፣

ተወርዋሪ ኮከብ፣ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ። ” 

ብርሃን ሳይለግስ ከሚንጠራወዝ አንዳች የጠፈር አካል ይልቅ ለአፍታ ደምቆ እያበራ የሚሰወረው ተወርዋሪ ኮከብ ይበልጣል። ወቸ ጕድ! ምንም ሳይፈይዱ ከዐመት፣ ዐመት ዘልለው ዘመናትን ከማስቈጠርስ፣ አንድ የሚረባ ነገር ከውኖ በዐጭሩ መሹለክ መባረክ ነው እኮ! በማለት አስባለሁ፤ ያው ሐሳብ ነው እንግዲህ፤ ማሰብ አይከለከልም መሰል። ሐሳብ ሰንሰለትም አይደል? እንዲህ ይሉትን ታሪክ ያመጣና ደግሞ ውስጤ ይጥደዋል። በአንዲት መጽሔት (ምስክርትኾን እንጃ?) ላይ ያገኘሁት ነው።

በኾነ ሀገር ለጕብኝት የሄደ አንድ የሕክምና ዶክተር በአስጐብኝው እየተመራ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበረ ሰባዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎችን ይጐበኛል። በጕብኝቱ ማገባደጃ ላይ አንድ መካነ መቃብር ሊመለከት ይሄዳል። በእያንዳንዱ መቃብር ላይ በተተከሉ የሕይወት፣ የማንነትና የአስተዋጽዖ መግለጫ ሰሌዳዎች ላይ ያለው ጽሑፍ ቀልቡን ይስበዋል። ከየሟቹ ዐጭር መግለጫ ውስጥ አንድ ሐሳብ ግልጽ አልኾነለትም። እየተዘዋወረ ቢያነብም ቅሉ፣ ትርጕሙ አልከሠትልህ ይለዋል።

አንዱ፣ “ዶ/ር ማንትስ በተወለደ በ6 ዓመቱ ዐረፈ” ይላል። ሌላው በበኩሉ፣ “ሳይንቲስት እገሌ በተወለደ በአራት ዓመት ዕድሜው የመጨረሻ እስትንፋሱን ሰጠ” በማለት ያስነብባል። ወደ ሌላው አቅንቶ ሲመለከትም ተመሳሳይ አባባል ተደቅኗል፤ “ዝነኛው አርቲስት በሁለት ዓመቱ ተቀጠፈ” ይላል። ወደ ተቀሩትም ቢያማትር የተለየ ነገር አላገኘም። በነገሩ ግራ የተጋባው ጐብኚ ራቅ ብሎ ወደ ቆመው አስጐብኚ ጥያቄውን ይሠነዝራል።

“ወዳጄ፣ የመቃብር ላይ ጽሑፎቹ ትኵረቴን ስበውታል፤ ግራም አጋብተውኛል፤” ይላል ዶክተሩ።

“ለምን?” ሲል ይጠይቃል፤ አስጐብኚው…

“እንዴ! ምሁሮቻችሁ፣ መሪዎቸችሁ፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎቻችሁ፣ የንግድና ምጣኔ ሀብት ጎምቱ ሰዎቻችሁ ሳይወለዱ ዐድገው፣ ሳያድጉ ተምረው፣ ሳይኖሩ ነው የሚሞቱት?” በማለት በጥያቄ ይመልሳል። በዚህ ጊዜ አስጐብኚው (ነገሩ ዘወትር በሥራው ላይ የሚገጥመው ጕዳይ ነውና) እንዲህ ሲል ያብራራለታል።

“በሀገራችን በሐውልቶች ላይ የሚሰፍረው ዕድሜ መጠን ግለ ሰቡ ለሀገሩ ዕውቀቱንና ሙያውን የለገሰበት ዘመን ነው። ስለዚህ ‘ዶ/ሩ በአራት ዓመቱ ሞተ’ ማለት አራት ዓመት ሀገሩን በተጠቀሰው ሞያው አገልግሏል ማለት ነው” ይለዋል። በኹኔታው የተደነቀው ጐብኚ ሐኪም  አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ያቀርባል፣ “እኔ አሁን በቅርቡ ነው የሕክምና ሳይንስ አጥንቼ የተመረቅሁት። ታዲያ፣ የናንተ ሰው ነኝ ብለህ አስብ። አይበለውና ዛሬ ብሞት፣ መቃብሬ ላይ ምን ብላችሁ ልትጽፉ ነው?”

አስጐብኝውም አተኵሮ እየተመለከተው፣ “ ‘ዶክተሩ እንደ ተወለደ ሞተ’ ብለን ነዋ!” አለው። ጐብኚውም መንገዱን ቀጠለ…

ይህ ታሪክ እውነት ሊኾን ይችላል፤ ላይኾንም ይችላል። የሚያስተምረን ቁም ነገር ግን የትየለሌ ነው። “እንደ ተወለደ የሞተ” ስንትና ስንት አዛውንት እኮ አለ። የሰው ልጅ በተሰጠው ዘመኑ የድርሻውን ይወጣበታል፤ ወይም በከንቱ ሲጫወትበት ኑሮ ያገባድደዋል። ብዙዎች፣ እንዲያውም፣ የዘመናቸው ባለቤትም አዛዥም የኾኑ ያህል ይሰማቸዋል። አንዳንዶቻችን ስለ ዘመናችን ያለን አስተሳሰብና አጠቃቀማችን ሲጤን፣ አንድም ተዝቆ የማያልቅ ብጤ የሚያስመስለው ሲኾን፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ በዋል ፈሰስ የምንቀልድበት ዐይነት ነው። በዘመናቸው ማጠር መርዘም ጕዳይ በጣም ተጨንቀው የሚኖሩም አሉ። በሌላ በኩል፣ ዕድሜውን ለማርዘም ሰው “የማይፈነቅለው ድንጋይ” የለም። ይህን፣ ይህን ሳውጠነጥን “የማቴቴስ  ስንብቷን (ወይ ጊዜያዊ መቋረጧን) ያፋጠነው የመጨረሻ ሥራዋ ከዋጋ በላይ እኮ ነው” የሚል ነገር ታሰበኝ። የመሰለኝን ነው እንግዲህ፤ “ሕልም እንደ ፈቺው ነው” ብላችሁ ልታልፉት ትችላላችሁ።

ባለፉት ዓመታት፣ “ለምን ሞቅ፣ ሞቅ ያለውን አትጽፉም?” የሚል ጠያቂ ገጥሞኝ ያውቃል። “ጽሑፋችሁ ሞጋችነት ይበዛዋል” ያለኝንም ሰው አስታውሳለሁ። ከስምና ዝናቸው፣ እንዲሁም ከጥቅማቸው በላይ ርቀው “ማየት የተሳናቸው” ጥቂት ልግመኞችም ደግሞ አሉ። “ስለኔ መልካም አይናገርምና የመከራ እንጀራ አብሉት” ባይ ጨካኞችም ነበሩን። “የትም ፍጩትና ቂጣውን አጕርሱን” የሚሰኘው መቋመጥ የከበሩ እሴቶችን ባፍጢሙ በደፋበት ዓለም፣ “ዋጋ መክፈልን” ሳይፈሩ ለእውነትና ጽድቅ መቆም በሰውም ዘንድ ባይኾን በጌታ ዘንድ ያስከብራል። ስለዚህ የሕንጸት ጸሐፊዎችን በርቱ ማለት አለብኝ። እናም “የትም አትፍጩት”!

አሰስ-ገሰሱን እያጋበሱና በየሐሳብ ጮሮቃው እየተምቦጫረቁ ለምእተ ዓመታት ከመኖር አንድ “አንጀት-አርስ” ጕዳይ ከውኖ ማለፍ በስንት ጣዕሙ! እኔ በበኩሌ ለገዛ ነፍሴ ተግሣጽን ተቀብዬበታለሁ፤ የማይረቡ ረጅም ዓመታትን ከመቍጠር “ለእግዚአብሔር ክብርና ለክርስቶስ አካል በረከት አንዳች ነገር ፈጽሞ ዕለቱን ፍግም ቢባልስ!” እያልኩ አስቤኣለሁ። ርባና ቢስ ዘመን፣ ቢንዘላዘል እንጂ፣ ምኑ ያጓጓል? ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ “የሰው ዕድሜ መርዘምና ማጠር እንደ ቢላ መርዘምና ማጠር ነው፤ ቁም ነገሩ ግን ከርዝመቱ ወይም ከዕጥረቱ ሳይኾን ከስለቱ ነው” እንዳሉት ነው። “ስለታም” ዘመን ያብዛልንማ!

የዕድሜ ባለሪከርዱ ማቱሳላ ወደ አንድ አምኣት (ሺህ ዓመት) የሚጠጋ ዘመን ፉት ብሎ ምን አመጣ? ምንም። ሰውዬው 969 ዓመታት ኖሮ ነበር። ነገር ግን፣ ታሪኩ በሰፈረበት ዘፍጥረት 5 ላይ ይኸው ሰው ረብ ያለው ሥራና ታሪክ አልተጠቀሰለትም። በአንጻሩ ግን የማቱሳላ አባት የኾነው ሔኖክ፣ እዚያ ከተዘረዘሩት መካከል በጣም ዐጭሩን ዕድሜ የኖረ ነው፤ 365 ዓመት ብቻ። ነገር ግን “ተወለደ፣ ኖረ፣ ወለደና ሞተ” የተሰኘውን የምዕራፉን አዝማች ቀይሮታል። “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ እግዚአብሔር ወሰደው” (ዘፍ. 5፥22-24) ተባለለት። ኖኅ ደግሞ የማቱሳላ የልጅ ልጁ ነው። “ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ …  አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” (ዘፍ. 6፥9)። እርሱም ከመለኮታዊ ቍጣ ለመትረፍ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ነበር። የሚገርመው፣ ኖኅ 600 ዓመት እስቲኾነው ድረስ ማቱሳላ በምድር ላይ ነበር። በተጨማሪም፣ ኖኅ ለ120 ዓመታት ጽድቅና ንስሐን ሲሰብክ የዕድሜ ባለጠጋው ሰውዬ እዚሁ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ማቱሳላ የሞተው በማየ አይኅ (የውሃ ጥፋት) ዘመን መኾኑ ነው። በዚያ ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ውስጥ በሌላ ማንኛውም ነገር የሞተ ካልኾነ በቀር፣ ሰውዬው የሞተው በውሃ ጥፋት  ነው ማለት ነው። ከዚህ የከፋ “የተቀጨ ሰው” ወዴት ይገኛል?

የማቱሳላን መርገምት ተሣቅቄበት ሳላበቃ ሐዋርያው ስለ ንጉሥ ዳዊት የተናገረው ደግሞ ብልጭ ይልልኛል። “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ” (ሐዋ. 13፥36) የሚለው። ሊያሳስበን የተገባው ምን ያህል ዘመን ኖርን የሚለው ሳይኾን የተሰጠንን ዘመን እንዴትና ለማን ኖርነው የሚለው መኾን አለበት። መቼም ዕድሜ እንደ መጽሐፍ ገጾች ነው። እያንዳንዱ ገጽ የየቀናችን ስኬትና ውድቀት፣ ደስታና ልቅሶ፣ መራራና ጣፋጭ… ተቀልሞበታል። ግን የመጽሐፉ ገጾች ተገልጠው ማለቃቸው አይቀርም፤ አንድ ቀን “ተፈጸመ” ይባልለታል። ማንም የማይሠራባት ሌሊት ከመምጣቷ በፊት ቀን ሳለ የላከንን ጌታ ሥራ ብናደርግ ግን ይበጀናል (ዮሐ. 9፥4)። ጸጸት የሌለበት ሕይወት ማለት እሱ ነው።

ይህን ይህን መሰል ሐሳብ እያመሰኳሁ ባለሁበት፣ በሰንሰለቱ ላይ ሌላ የሐሳብ ቀለበት ይመጣበታል። ይኸውም የማቴቴስ  ከኅትመት መናጠብ የጸሐፊዎቹን ዘላቂ አርምሞ ያወጀ ያህል የፈጠረውን ስሜት ይመለከታል። አክዓብ፣ “ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ። ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ” (1ነገ. 22፥8) ያለውን የሚመስል ስሜት እዚህም አልጠፋም። አርምሞውን ተመልክቶ “ኧረ! እሰይ ስለቴ ሠመረ”ን የሚያዜም ነበረ አሉ። “ዝምታው ራሱ መልእክት ቢኖረውስ?” ማለት ማን ገደለ? ዝምታ ሁሉ መሸነፍ ነውን? ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፦

ዝም ብዬ ቢያየኝ፣ ዝም ያልሁ መስሎታል፣

ሲታሰብ ነው እንጂ፣ ዝም ማለት የታል?” እንዳለው ቢኾንስ?

ዝምታማ የለም። የሕንጸት መወለድስ ይህን አይናገርምን? ስንት የሚነገር ባለበት አርምሞ ዕርም ነው። ማርቲን ሉተር ኪንግ “ስለ አስፈላጊው ነገር መናገር ባቆምን ዕለት፣ ሕይወታችን ማለቅ ጀምሯል” ሲል ትርጕም አልባ ዝምታን ይጸየፋል። ይህም ሲባል ታዲያ፣ በኾነ ባልኾነው እየተነሣን መቀባጠር አለብን ለማለት አይደለም። የመለፍለፍ ዐመል የተጠናወተው ሰው የተገኘውንና አፉ ላይ የመጣውን ሁሉ እየዘረገፈ መኖሩ የተለመደ ነው። እንዲህ ዐይነቱ ሰው በዙሪያው ያለውን አቧራ ዘግኖ በዐላፊ አግዳሚው ላይ እየበተነ እንደሚዛብር ዕብድ የባልንጀራውን ስም ሲያጠፋም ሊውል ይችላል። የሰው አፍ ከጕርሻ፣ ምላስም ከመቅመስ በተጨማሪ ያላቸውን ተግባርና ጕልበት አሟጦ የሚጠቀም ለፍላፊ በየቦታው ሞልቷል።

መናገር መልካም ቢኾንም ማዳመጥ የሚበልጥበት ብዙ ምክንያት መኖሩ ሲነገር የኖረና ከሕይወትም የተማርነው ነው። ያገሬ ሰው “ባፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ” የሚለው በከንቱ አይደለም። ጥበብ በጐደለው መንገድ ምላስን መጐልጐል የሚያሳጭደው አሳር መኖሩን ለማመልከት የተነገረ ነው። ስለኾነም አበው “ዝም አይነቅዝም፤” እንዲሁም፣ “ዝምታ ወርቅ ነው” አሉ፤ ዝምብን ከአፋችን ሲገላግሉ። ስለዚህም፣ “ዝም ባለ አፍ፣ ዝምብ አይገባበትም፤” እያለ የዝምታን ውበት እያበረታታ የሚተክዝ ባህልና ማኅበረ ሰብ ሳናጠናክር አልቀረንም፤ መልካም። የሚያሳዝነው ግን መናገር በተገባበት ጕዳይ ላይ ሳይቀር ወደየዛጎላችን ሰርገን የምናሳየው አስፈሪ ጸጥታ ነው። ዳዊት ጸጋዬ አርነት የወጡ ሐሳቦች በተሰኘችው መድበሉ ውስጥ አጕል ዝምታን በምጸት ሲሸነቍጥ፣

ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም፣

ንብም ስለሚያልፈው ማር እይኖርበትም  ይላል።

ርግጥ መጽሐፉም ዝምታን ያበረታታል (ምሳ. 10፥19፤ 13፥3፤ 15፥2፤ 17፥27፤ 18፥21፤ ያዕ. 3፥26፤ 3፥1-2)። ግን ጊዜ አለው በሚለው መርሕ የሚገዛ ነው። “ለመናገርም ጊዜ አለው” (መክ. 3፥7)። ነቢዩ ኤርምያስ መናገር በሚገባው ጊዜ ዝም ማለትን ሞክሮት ነበር። “የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፤ መሸከምም አልቻልሁም” (ኤር. 20፥9) ይላል። መናገር በሚገባ ጊዜ የማርመምን ሕመም እንዴት ማራቅ እንደሚገባ መናገር ሳይኖርብን አይቀርም። ያገሬ ሰው “ዝምታ ለበግም አልበጃት፤ ዐሥራ ሁለት ኾና አንድ ነብር ፈጃት” ማለቱ መች በዋዛ ነው?

የኔም ተስፋ ሕንጸት ጨዋነት ያልራቃት “ተናጋሪ” ትኾናለች የሚል ነው። የተኵላ መዓት ዙሪያችንን ከብቦን ምን ዝምታ ይኖራል? “ያባትህ ቤት ሲወረር፣ ዐብረህ ውረር” ዐይነት ልግመትና ዳተኛነት እንደ መርግ ካልተጫነን በቀር ስለ እውነት መሟገትማ አይቀሬ ነው።

ጆን ፓይፐር Contending for Our All በተባለው መጽሐፉ ላይ እንደ ጠቀሰው፣ ስለ ቅዱስ አውግስጢኖስ ከሚነገሩ ታሪኮች መካከል በአንደኛው ላይ እንዲህ ይተረካል። ትራኬው የሚያጠነጥነው የቅዱስ አውግስጢኖስ ዐመታት ያሰቈጠረ የወንጌል አገልግሎቱ መደምደሚያ አካባቢ በተደረገ ጕዳይ ላይ ነው። አውግስጢኖስ ጤናማውን የቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮና ሐዋርያዊ ትውፊት በመጠበቅ ከመትጋት ባለፈ፣ ከልዩ ልዩ መናፍቃን ጋር በመታገል የቅዱስ ወንጌል እውነት እንዳይበረዝ ሲጮኸ ኖረ። እውነተኛው ትምህርት ሳይበረዝ እንዲሰበክ የበኵላቸውን አስተዋጽዖ ሲያበረክቱ ከነበሩት ቀደምት አበው ጋር ሰማይም ታሪክም የማይረሳውን ተግባር አከናውኗል። ነገር ግን፣ በ318 ዓ.ም. በሰሜን አፍሪቃዋ ሒጶ በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይዞ የቈየውን ሊቀ ጳጳሳዊ ኀላፊነቱን ለተተኪው የሚያስተላልፍበት ቀን ደረሰ።

በዚያም ቀን፣ ትሑቱ ተተኪው፣ ኢራቅሊዎስ፣ ከተቀመጠበት ተነሥቶ እንዲህ ተናገረ፦ “እነሆ፣ እንደ አሸን የፈሉት ዋዝንቢቶች (ፌንጣ አስተኔዎች) እየተጯጯኹ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ታላቁ ዝዪ ግን ሊያረምም ነው” አለ። ልብ የሚነካ አነጋገር ነበር። ኢራቅሊዎስ ሥጋቱ የነበረው፣ እነዚያ ነፍስን የሚያንገደግዱ የኑፋቄ ማዕበሎች ከየአቅጣጫው በነፈሱ ቊጥር ያለማወላወል በጽናት ይመክት የነበረው ታላቅ ድምፅ “ጸጥ ሊል ይኾን?” በማለት ነበር።

እንደ አውግስጢኖስ ያሉ በርካታ ታላላቅ ድምፆች በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመን ሁሉ ሲናገሩ ኖረዋል፤ እኛም በአግባቡ እናዳምጣቸዋለን። የእግዚአብሔር ባላደራዎች ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠውን እምነት ለመጠበቅ ሲጋደሉ (ይሁዳ 3) ኖረው ዐልፈዋል። እነዚህ የእምነት ዐርበኞች ታሪክና ተረት ብቻ አይደሉም። ሞተውም እንኳን ገና ይናገራሉ (ዕብ. 11፥4)።

የእኛስ ዘመን ተስፋ ይኖረዋልን? አዎ! አንዳንድ ዝዪዎች በኛም ዘመን እየዘመሩ ነው፤ ግና ብዙ አይደሉም። ዝማሬያቸውም ገና ዘመናትን ተሻግሮ ይዘልቅ እንደኾነ ጊዜ ይነግረናል። በርግጥ ታሪክ በመቶዎች ለሚቈጠሩ ዝዪዎች ያን ፍርዱን ቀደም ብሎ ሰጥቷል። እነርሱ ቢሞቱም እንኳ፣ ሥራቸው የዘመን ሚዛንን ተሻግሮ ቆሟል። ስለዚህ የእነርሱን ዜማ እኛ እናደምጠው ዘንድ ዛሬም ከዋጋው ጋር አለ። ዜማቸውን ግን የት ነው የምናገኘውና የምናደምጠው? በበርካታ ድል በታጀበው ተጋድሎአቸው እናደምጣቸዋለን። የገናናው ጌታችን ዳግመ ምጽአት እሰከዚያ የሚቈይ ከኾነና የታሪክ ሀዲድ ካልታጠፈ፣ ቀጣዩ ትውልድስ እኛን ያዳምጠን ይኾን? ሞጋች ጥያቄ ነው። ይህ እውን ይኾን ዘንድ ግን ስለ እውነት እንኑር፣ እንጩኽ፣ እንመካከር።

ዘመናችን መጽሐፍ ቅዱስን ተተግነው ለሚገነፍሉና ነፍስን በሚያጥወለውል ሕፀፆች ለተሞሉት ትምህርቶች ሰፊ ሜዳ ያዋሰ መስሏል። ስለኾነም እጅግ ብዙ እንቶ ፈንቶዎች በእምነት ትምህርት ተመስለው በየቤተ ክርስቲያኑ ሲንቧቹ ተስተውለዋል። ታዲያ በዚህ መካከል እንደ ሻማ ቀልጠው እንደ ከዋክብት የሚንተገተጉ ፋናዎች ያስፈልጉናል። በጫጫታ ድምፅ በተሞላው አድማስ መካከል ጐልተው የሚደመጡ ዝዪዎች “በዲዮጋን ፋኖስ” ይፈለጋሉ። ሕዝበ እግዚአብሔር በቃለ እግዚአብሔርና በጤናማ ትምህርት ታንጾ በደቀ መዝሙርነት እንዲያድግ መምህራን እንዲበዙልን እንሻለን። የእውነተኛ መጋቢያንን መነሣት እንመኛለን። እውነቱን ከስሕተት ለይተው የሚያመላክቱ፣ የእግዚአብሔር መንጋ ከኑፋቄ አሽክላ የሚጠብቁ እረኞች ወዴት ናቸው? በየዘመኑ የሚነሡ የስሕተት ትምህርቶች ዐይነትና ብዛት ተቈጥሮ የሚዘለቅ ባይኾንም፣ ስለ እውነት ግድ የሚላቸው ትሩፋን እንዲነሣሱ እንጮኻለን። እንደ ጋን ውስጥ መብራት ያልተዳፈነ ወጋገን የሚያሳዩ “ተወርዋሪ ከዋክብት” ናፍቀውናል።

አስቀድመን እንዳልነው፣ ከፍርሃትም ይሁን ከማናቸውም ነገር የመነጫና ተገቢነት የሌለው ዝምታ “ይራቀን” ብለናል። ቈይማ! የፈሪው ሰውዬ ታሪክ ትዝ አለኝ። አንድ ፈሪ ሰውዬና ጓደኛው ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ ውለው ካሰቡበት ባለመድረሳቸው በአንድ መስክ (ሜዳ) ላይ ለማደር ግድ ይኾንባቸዋል። አውሬ እንዳይተናኰላቸው የነበራቸው ሥጋት ግን ገና እንቅልፍ እንዳሸለባቸው እውን ኾነ። አድፍጦ የመጣ አንድ ጅብ በውድቅቱ ሌሊት ሥራውን ጀምሮ ነበር። ጅቡ የኾነ ነገር በጥርሱ ሲያደቅቅ ሰምቶ ከእንቅልፉ የነቃው የፈሪው ሰው ባልንጀራ ፈሪውን ሰውዬ በሹክሹክታ ይጠራና “ምንድነው ባክህ የምሰማው?” ይለዋል። ፈሪውም እየተንቀጠቀጠ፣ “ዝም በል በናትህ፣ ቀኝ እግሬን ነው የሚቈረጥመው” አለው። “እየተቈረጠሙ” ዝምታን መናፈቅ ምን ይባላል?

ዙሪያ ገባው የበግ ለምድ በለበሰ ተኵላ ተሞልቶ እያየን ዝምታችን የጤንነት ነው? የእምነት ቈራጥነት እግዚአብሔር እንዲያድለን እንለምን እንጅ። ትናንት ከሩቅ የምንሰማው ከንቱ ልማድና ልምምድ ከደጃፋችን ሲንሰራፋ እጃችንን ባፍ ላይ ብንጭን ይበቃል? ሰሞኑን ማኅበራዊ ሚዲያውን አጨናንቆ የከረመውና ተከታዮቹን (ለምንም ዓላማ ቢሆን) ሳር እንዲግጡ ያዘዘው መጋቢ ተብዬ የሠራው ግፍ ነገ በእኛው መካከል ላለመፈጸሙ ዋስትና የለም። ዳሩን ካልጠበቁት ማህሉ ዳር መኾኑን ደጋግመን አይተናል፤ ዝም አንልም። ቅዱስ አትናቴዎስ አፋሽ አጎንባሹ ጊዜ ለሰጠው ሐሰተኛ ሲያረግድ “ዞር በል” ብሎ እንደኖረ እናውቃለን። “ዓለም እውነትን ተጻሮ የቆመ እንደኾን፣ አትናቴዎስ ዓለምን ተጻሮ ይቆማል” ሲል ዐወጀ፤ እንዲሁም ተመላለሰ። “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራልና፣” ከዐመታት በኋላ፣ “Attanasious Contra Mundom — አትናቴዎስ የዓለሙ ተቀናቃኝ ” እየተባለ ለመጠራት በቃ።

ይህ ሲባል ፍቅር በጐደለው እውነት መጨካከን አለብን ማለት አይደለም። ተሠገዎኣዊ ፈያጅነታችን (Incarnational Relevance) እንዳይዘነጋ መጣር አለብን። ተግባራዊ የደቀ መዝሙርነት ሕይወትን፣ የቅዱሳን ኅብረትንና ፍቅርን ችላ በማለት ለአደባባይ ጩኸት ብቻ ያጋደለ ትኵረት መስጠትም አይገባንም። እውነትን በአደባባይ አስጩኸን ስናበቃ፣ ያችኑ እውነት በፍቅር የሚያንሾካሹክ ልከኛ ሕይወት ከሌለን ቀልጠን አቅልጠናል ማለት ነው። ስለ እውነት መሞት አለብን እንጂ ስለ እውነት ልንገድል አልተጠራንም። ስለ እውነት መዘመር ያለብንን ያህል ስለ እውነት ማልቀስ ይኖርብናል። ስለ እውነት መከራከር የሚያስፈልገውን ያህል ስለ እውነት ዝም ማለትን መልመድ ይገባል። አስተምህሮኣዊ ርቱዕነት (doctrinal orthodoxy) እንደሚያሳስበን ሁሉ ነቢያዊ ተጋፋጭነትን (prophetic confrontation) መዘንጋት የለብንም።

ለማጠቃለል ልሞክር። ብዙ የተለፋለት ነገር ሲከስም ማስቈጨቱ አይቀርም ይኾናል። የትሩፋን ናፍቆት በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፣ “ሕልም ሲከስም ቍጭት እንደ እግር እሳት ያንገበግባል፤ እየዋለ እያደር ጸጸት ወደ ልቡና ይዘልቃል። ሕልምም ኾነ ቅዠት በሌላቸው ሰዎች ዘንድ የማይገኝ ውስጣዊ ነዲድ ኅሊናን ይሞሸልቃል።” የሚጣሉህ ይኖራሉ፤ ፈቀቅ ትላለህ። መጽናትም አለብህ። የአንድ ሰው ዋነኛ መለኪያው በምቾትና መደላደል ውስጥ በርትቶ ማለፉ አይደለም፤  በችግርና ውጥረት ውስጥ ጸንቶ መቆም በመቻሉ ነው።

ይስሐቅ መጀመሪያ ያወጣው የውሃ ምንጭ “ኤሴቅ (ክርክር)” ሲያስነሣበት ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ድጋሚ  ቈፈረ። ሁለተኛው ምንጩም “ስጥና (ጠላትነት)” የሞላበት ኾነ። ግና ተስፋ አልቈረጠም። በትዕግሥት “ርኆቦት (ሰፊዎች)” እስቲወጣ ድረስ በትጋት ለፍቶ የለምን (ዘፍ. 26፥15-22)? መንገዱ ይኸው ነው። በተለመደው አባባል ማሰብም ይቻላል። “ሰይጣን የትናንትና ውድቀታችንን ሲያስታውሰን፣ እኛ ደግሞ የእርሱን መጪ ጊዜ እናስታውሰዋለን።”

የተለየ ዓላማ የለንም። ቢኾንልን ከሐዋርያው ጋር የምንለው ይህን ነው፦ “እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው” (ቆላ. 1፥28)። መልካሙን ማድረግ ለራስም ይጠቅማል። ንጹሕና የተከበረ ነገር መሥራት ትዝታችንን ከመቈሸሽ ይጠብቀዋል። የርስ በርስ መደጋገፋችን ያበረታታናል። ብቻችንን የቀረን ሲመስለን፣ ሌሎች አጋሮች እንዳሉን ባወቅን ጊዜ ተስፋችን ይለመልማልና። ጕዳዩ ከበደ ሚካኤል “በቅኔ አዝመራ” ውሰጥ እንዳቀለሙት ነው፤

በሥራ በዕውቀት ግሎ ለመነሣት፣

ቈስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደ እሳት። ”

Solomon Abebe G. Medihin

ከታሪክ አልማር ብለን ይሆን?

“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በወንጌላውያን አማኞች መካከል ያለውን ታሪካዊ የአግላይነት ውጥረት ይበልጡን የሚያከርሩ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሚዛንና ብስለት ያጡ አስተምህሮቶች እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጐደላቸው ሥነ ምግባራዊ ቀውሶች መታየት ከጀመሩ ሰንብተዋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በእነዚሁ ሁለት ታላላቅ ቤተ እምነቶች ውስጥ ያለው የእርስ በእርስ መከፋፈል፣ ጐሣዊና ፖለቲካዊ ጽንፈኝነትን የተላበሰ በመሆኑ፣ የአገሪቱን ፈርጀ ብዙ መከራ የበለጠ አክብዶታል።” ግርማ በቀለ (ዶ/ር)

ተጨማሪ ያንብቡ

ያላለቀው ጉዞ!

ተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) “ያላለቀው ጉዞ!” ሲል በሰየመው ጽሑፉ፣ በልማትና ዕድገት መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት በማስቃኘት፣ አገራችን ኢትዮጵያ “ሄድ መጣ” እያለ የሚያማልላትን ተስፋ በሙሉ እጇ ትጨብጠው ዘንድ ልታደርጋቸው የሚገቡ ያላቸውን አንዳንድ ነጥቦች እንደሚከተለው ያስነብባል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.