[the_ad_group id=”107″]

ሕዝብ ከሥልጣን ይውረድ!

ታክሲ ውስጥ ነን። እኔ፣ ምናሴና የምናሴ ባለቤት፣ ዶይ። ታክሲዋ ተጠቅጥቃና ተነቅንቃ ከመሙላቷ የተነሣ፣ እንደ ሰው አፍኗት ብታስነጥስ እንደ እኔ ቀለል ያልን ሰዎች በአፍንጫ እንደሚወጣ የእንጥሻ ፍንጣሪ፣ በር ሳይከፈት እንወጣ ነበር። ወደ መዳረሻችን፣ ̋ተሻግሮ ወራጅ አለ” አንዱ ከኋላ። በረዶና ነጎድጓድ አዘል የስድብ መዓት ስታዘንብ የመጣችው ሴት ደግሞ፣ ̋ሳይሻገር ወራጅ አለ ̋ አለችና ደጋግማ ጮሄች። ሾፌሩ በኀይል መናግሯ ̋ደብሮት ̋ ነው መሰለኝ፣

̋ሴትዮ፤ ጤነኛ አይደለሽም እንዴ? ̋ አላት።
̋ ‘ሴትዮ’ ይለኛል እንዴ? ሳጥናኤል ጤናህን ይንሳህና! አሁን

አቁምልኝ! ̋ አለችው በቁጣ።
̋ደንቡ አይፈቅድም፤ ቢፈቅድም አላቆምም ̋ በሹፈት መለሰላት።

̋ ‘ደንብ’ ይላል እንዴ? ዲያብሎስ በድሚማት አናትህን ይድመጠውና!” እየተሳደደቡ ተሻገርን።

ተሻግረን ሁሉም ተሳፋሪ ሲወርድ፣ መልስ ለመቀበል ተሳዳቢዋ እመቤት እጇን ስትዘርጋ፣ ሾፌሩ ለረዳቱ ̋የእሷን ብቻ ተቀበል ̋ ብሎ ወደ ባዶው የተሳፋሪ መቀመጫ እየተመለከተ፣ ̋ከእሷ ጋር የገባችሁ ለዛሬ ሒሳቡ በእኔ ይሁንና እባካችሁ በሰላም ውረዱ ̋ ብሎ ሲያሸሙር ብትሰማም የገባት አልመሰልኝም።

“ከኢየሱስ ጋር የመደመር ዓመት” ተብሎ በተሰየመ ፖለቲካዊ ወመንፈሳዊ ይዘት ወዳለው “ጉባዔ”፣ ዶይ ካልሄድኩ ስላለችን ነው አመጣጣችን። ከወሰደችው መልስ ጋር ስድቧን ወደ ቦርሳዋ የከተተችው ይመስል በትኅትና “ወደ ፕሮግራሙ ናችሁ?” በማለቷ ከዶይ ጋር አብረው ወደ ውሰጥ እንዲገቡ አደረግን። እኔና ምናሴ ዶይን ከሆቴሉ ጉባዔ አድርሰናት፣ እሷ ከኢየሱስ ጋረ ተደምራ እስክትወጣ እኛ እንደምንጠጣው ማኪያቶ ዝብርቅርቅ ያለውን ነጭና ጥቁር ወሬያችንን ልንሰለቅጥ ከካፌው ዙፋን ተሰየምን።

ምናሴ እንደዚህ ወዳሉ ጉባዔዎች የመሄድ ፍርሀት ያደረበት፣ ባለፈው አንዱ “ነቢይ” ጋ በዶይ ንዝነዛ ሄዶ በነበረ ጊዜ ነው። ዶይ ከፊት ተቀምጣ “አድናቂሽ ነኝ፤ ፈሪሚልኝ” ማለት እስኪቀራቸው ድረስ በሚጠጓት ካሜራ ማኖች ትጋት ትደሰታለች። በአፍንጫዋ ሥር ያለውን ጸጉር ሳይቀር ዙም አድረገው ይቀርጿታል። ዶይም የምትሄደው ይህን ፍለጋ በመሆኑ ከአምልኮውና ከስብከቱ ይልቅ ትኩረቷን ይስበዋል።

ምናሴ ገና ከመቀመጡ ስፒከሩ ልቡ ላይ የተተከለ ይመስል “ዱው ዱውታው” አዙሪት እንደ ያዘው ሰው አሸከርክሮ ሊጥለው ሲል ተቀመጠ። እሱ በተቀመጠበት ቅጽበት፣ “አንዳንድ መናፍስት አንዳንዶችን አደካክሟቸው አስቀምጧቸዋል። እስኪ የተቀመጡትን ወደዚህ አውጡልኝ!” የሚል ልዩ ትዕዛዝ “ነቢዩ” ሲያወጣ፣ ከየት መጡ ሳይባል የነቢዩ ጠባቂዎች አንጠልጥለው አነሡት። “ምን እያደረጋችሁ ነው?” በሚል ለማስለቀቅ ሲፈራገጥ፣ ምእመኑ እሱን በማስጣል ፈንታ እጆቹንና እግሮቹን በመያዝና በመገሰጽ ተባብረው “ከነቢዩ” እግር ሥር ጣሉት። “አጋንንት የለብኝም” ብሎ ለማስረዳት ከወደቀበት ሲነሣ፣ በሙስና ተከስሶ እንደ ተያዘ ባለ ሥልጣን ከከበበው የካሜራ መብራት፣ ከካሜራ ባለ ሙያዎች ግርግርና ጠፍረው ከያዙት ጣይ ቦዲ ጋርዶች እጅ እንደማያመልጥ ሲገባው፣ “አጋንንት የለብኝም” ብሎ ለማስረዳት ያሰበውን ሐሳብ በመተው የሚሆነውን መጠበቅ ጀመረ።

“ውጣ” የሚለው “የነቢዩ” አሰገምጋሚ ድምፅ የምር አስደነገጠው። በማስደንገጥ የጀመረው “ነቢይ”፣ አንዴ በግፍተራ፣ አንዴ በንረታ ሲያምታታው ቢያንስ “ሦስቴ ጩኽ” መባሉ ስለማይቀር ምናሴ ሳይታዘዝ መረቀለትና አምስት ጊዜ ጮኾ ተገላገለ። የእሱ የሕግ ያለህ ጩኸት የነቢዩ አገልግሎት ስኬት መለኪያ ተደርጎ ቴሌቪዥን ላይ “የነጻ መውጣት” ፕሮግራማቸው አድማቂ ሆኖ ቀረበ። ምናሴ በድንጋጤ እንጥሉ እስኪታይ ድረስ የጮኸው ምስል፣ በቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላ ምናሴ የሠፈሩ ቡና መጠጫ፣ የወሬ ርእስ ሆነ። “ድሮም ሾካካ ነገር ነው፤ አጋንትማ እንዳለበት ያስታውቃል” ከሚሉ እናቶች ጀምሮ፣ “እንዲህ ዐይነት ጸዳ ያለ ድምፅ እያለህ ነው ስታወራ የምታንኮሻኩሽው?! ቆይ አጋንንቱ ሰፍሮ የነበረው ድምፅህ ላይ ነበር?” እስከሚለው የጓደኞቹ ፉገራ ድረስ ምናሴ የተቋቋመው ሽሙጥ ነበር።

የዶይ አፍቃሪ ካሜራ ባሕርይ ለሞትም ዳርጎን ነበር። ለሰኔ 16ቱ ሰልፍ አጥቢያ “በዚህ ታሪካዊ ቀን ምስሌ ተቀረጾ ካልተቀመጠ የዚህ ትውልድ አባል መሆኔ ተረስቶ መቅረቱ ነው” ብላ ምሽት ዐሥር ሰዓት ነበር ከሰላም ሕልማችን ቀስቅሳን የቦምብ ምሳ ልታደርገን የነበረው። ሰው ለማምለጥ ሲተረማመስ ዶይ ግን ካሜራ የያዘ ጋዜጠኛ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ትል ነበር። “ኸረ ዶይ ከዚህ እንሂድ” ብንላት፣ ብዙ ሴቶች ወንዶችን ያለ ፍላጎቶቻቸው ገድል በሚከትቱባት ቀሽም በሆነችው፣ “ወንድ አይደላችሁም እንዴ?” በምትል አሸማቃቂ ጥያቄ መሰል ሐረግ ከትርምሱ መኻል እንድንቆይ አደረገችን። የእኔስ ይሁን፤ የባሏን ወንድነት መጠራጠሯ ብቻ ከቦንቡ መኻል በንዴት ያስወጣን ነበር።

ዶይ በስተመጨረሻ ጋዜጠኛ ፈልጋ ቃሏን ሰጠች። ማታ ቤቷ ገብታ ከቢቢሲ እስከ ኢቢሲ፣ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ሳይቀር ራሷን ፍለጋ ስታጣ ምናሴን ቀስቅሳ፣ “ስማ ምናሴ፤ የጋዜጣ ሪፖርተሮች ካሜራ ይይዛሉ እንዴ?” ስትለው፣ በእንቅልፍ ልቡ

“ለምን አይዙም፤ አንባቢዎቻቸውን ምን ሊያሳዩ ነው?”

“እኔኮ ከካሜራ ጋር መቆሙን ብቻ ነበር ያየሁት፤ ቆይ ብቻ ይንጋ” ብላ ዛተችና ሲነጋ፣ ደም በመለገስ ሰበብ እየዞረችና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን እየመረጠች፣ “እነዚህ ባንዳ ፋሺስቶች፣ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ! ዐደራችሁን የሕዝብን ድምፅ አሰሙ። ድምፃችን እስካልተሰማ ድረስና እነዚህ አረመኔዎች እስካልተያዙ ድረስ እንቀልፍ አይወስደኝም” ብላ ተበድራ ያመጣችው ይመስል፣ እንባዋ አንዴ ብቻ ዱብ ብላ ተቋረጠች።

ይህ ሁሉ ሲሆን ምናሴና እኔ በቴሌቪዥን አየተከታተልናት ነበር።

“በርግጠኘነት የምነግረህ ‘ድምፃችንን ካላሰማችሁ እንቅልፍ አይወስደንም’ ካለችው ውጪ አንድም እውነት የለም።”

አለ ወደ እኔ ዞሮ።

“አባባ ሲሉ ከመስማቷ ውጪ ባንዳም ሆነ ፋሽስት ምን ማለት እንደ ሆነ አታውቅም። እንግዲህ እየው፤ ‘አንዳንድ የፈለገ ንዋይ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየት እንደሰጡት’ የሚባለው የእነ ዶይ ዐይነቱን ሰብስበው እኮ ነው።”

“ስማ እንደ ሰዎቹ የቀን ጅብ ምናምን ማለት አቅቶኝ አይደለም፤ ለየት ላድረገው ብዬ ነው። ደግሞም 27 ዓመት ሙሉ ጾሙን እንደ ከረመ ጅብ በጠራራ ፀሓይ አምስቴ የሚጮኽ ቀንደኛ የቀን ጅብ ባል ይዤ እየገነባሁት ያለውን ዝናዬን አላጠለሽም ብዬ ነው፤ ከገባህ።” ያለችው ዶይ በሰርፐራይዝ በተሞሉ በእነዚህ ወራት እንደየሁኔታው፣ አንዴ “መደመር፣ ፍቅር፣ ሰላምና ይቅርታ ብቻ ነው የሚያዋጣን! ለውጡ አይቀለበስም!” ስትል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ “በለውጡ አደናቃፊ ኀይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰድ አለበት” ትላለች። እንደ አንዳንድ የፈለገ ንዋይ ነዋሪ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሐሳብ እየሰጠች ኤክስፐርት ለመሆን ምንም አልቀራትም ነበር።

“ጌታን የማውቀው ስወለድ ጀምሮ ነው” እንዳላለች፣ ዛሬ ደግሞ ከኢየሱስ ጋር በመደመር ሰበብ የካሜራ ሱሷን ልትሰስን መጣች። እንደ አንዳንድ የፈለገ ንዋይ ነዋሪ ሁሉ፣ ዶይም ምን ማድረግ እንዳለባትና ለምን እንደምታደርገው ምክንያት የላትም። ሰላማዊ ሰልፍ ሰው ወጥቶ በሰላም ከገባ፣ “የዛሬው ሰልፍስ ነፈሰበት፤ ምነው? ወንዱ ቀሚስ ለበሰሳ! አንግቦ የወጣው ጥያቄ እንዲሰማለት የእነ እንትና ዘመዶች ውጡልኝ ባይል፣ የርዳታ ስንዴ ያለበትን መጋዝን ባያጋይ፣ ሆቴል ባያወድም፣ መኪና ባያነድድ፣ ጐማ ባያቃጥል ቢያንስ ሰሞኑን ዶላር ያከማቸ አንድ ባንክ ይጣ?!” ትላለች በቁጭት።

መደመር ለዶይ ጠዋት ቸርች ሄዳ ስትመለስ “የቀን ጅብ” ብላ መሳደብ ነው፤ ሰልፍ ባለበት ሁሉ ቦንብ አለ ብሎ መጠርጠር፣ ሲፈዝ የተገኘ ምስኪን ወጣት ካገኘች ዘቅዝቃ መስቀል፤ ከተወገዘች ‘ይህን ያደረጉ አይወክሉኝም’ ማለት ነው ለእሷ መደመር።

ያዘዝነው ማኪያቶ ሳይመጣ ምናሴ ሚስቱን ማማት ጀመረ። “ሚስትህን ማማት ማለት ስለ ራስህ እንደ ማውራት ማለት ነው” ብሎ የሚያምነው ምናሴ፣ ዶይን ሲያማ፣ ማለቴ ስለ ራሱ ሲያወራ ምንም አያስቀርም። “ምን ላድረጋት በእናትህ?! ፖለቲካው እሳት በሆነበት ዘመን፣ የፍርድ ቤት ዳኞች በብዕር ፈንታ፣ ሚስማር ያለው መዶሻ በሚይዙበት ወቅት የፍትሕ ያለህ ብዬ ብጽፍ፣ ‘እፈታሃለሁ፤ አርፈህ ቁጭ በል’ ብላኝ አዲስ የአማርኛ ፊልም በወጣ ቁጥር ታንከራትተኝ ጀመር። እኔ ደግሞ ጥሎብኝ አዳዲስ የአማርኛ ፊልሞችንና የትምህርት ፖሊሲውን አልወዳቸውም። ሁለቱም የተቀረጹት በአንድ ካሜራ ይመስል፣ መጀመሪያቸውም መጨረሻቸውም አያምርም። ይህ አልበቃ ብሏት “በነቢያቱ ቤት እየወሰደችኝ ቶንሲሌ እስኪያብጥ ታስጮኼኛለች።”

እውነቱን ነው። ባለፈው ጊዜ፣ “ከዚህ በኋላ ነቢያት ቤት አልሄድም፤ ምክንየቱም ትንቢታቸው የማይፈጸም ግምት ነው” ሲላት፣

“የትኛው ትንቢት ነው ያልተፈጸመው?” አለችው በልበ ሙሉነት፤ “በዚህ ዓመት ነቢያት ፓርላማ ይገባሉ ያለው?”

“እና ከጠቅላይ ሚስትሩ በላይ ምን ዐይነት ነቢይ ትፈልጋለሀ? ፓርላማ ያሉ ሁሉም የለውጡ አካላት፣ ነቢያት ናቸው”

“አፈ ጉባዔአቸውም?”

“እሳቸው እንዲያውም ዋና ነቢይት ናቸው፤ ካልፈግህ ግን አለመሄድ ትችላለህ። እነሱን ግን አትንካብኝ፤ የሕዝብ ብሶት የወለዳቸው የቁርጥ ቀን ጀግኖቻችን ናቸው” በማለቷ ከዙረት አርፏል።

ምናሴ ሕዝብ ሲባል አይወድም፤ “ሕዝብ ማለት ዶይንና መሰሎቿን የሚወክል ከሆነ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት መሆን የለበትም” ባይ ነው። “ ‘ሕዘብ ማለት መግደል መሸነፍ ነው’ ለማለት ወጥቶ የሚገድል፣ ‘መደመር ነው የሚያዋጣን’ ለማለት ተሰልፎ፣ ‘የእኔ ዘመድ ሳትሆን እዚህ ምን ትሠራለህ?’ እያለ ሰይፍ የሚመዝዝ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከቀን እንቅልፍህ ቀስቅሶህ በካራቴ በሚመታህ ነቢይ ፊት የሚጥልህ ነው።”

Asnake Endrias

የመጽሐፍ ቅኝት:- “መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ”

ይህ ጽሑፍ፣ “መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ” በተሰኘው የምኒልክ አስፋው መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ የሚያድረግ ነው። ዳሰሳውን የሚያቀርበው ነቢዩ ዓለሙ (ዶ/ር) ሲሆን፣ ምኒልክ በሥነ አፈታት ምንነትና ፋይዳ ላይ ፈር ቀዳጅ የሆነ ሥራ ማበርከቱን ያወሳል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.