“እኔው ነኝ!”
የእርስ በእርስ ግንኙነቶቻችን እጅግ ታምመዋል። ሕመሙ አገራችን፣ ተቋሞቻችን፣ ማኅበሮቻችን እና ራሳችንን ያካትታል። ግንኙነቶቻችን ለምን ታመሙ? ለዚህ የግንኙነቱ አካላት ሁሉ ኀላፊነት እንዳለብን አያጠያይቅም። ሁላችንም ኀላፊነት አለብን ማለት ግን፣ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ያለበት አካል የለም ማለት አይደለም። መራሩ እውነት ለሚያነክስቱ ግንኙነታችን ዋንኛው ተጠያቂ ሌሎች ሳይሆኑ እኛው ራሳችን መሆናችን ነው። ‘ችግሩ እኔው ነኝ’ እስክንልም የምንጠብቀው ፈውሳችን በሁሉም መስክ መዘግየቱ ይቀጥላል። ሌሎች በተሳተፉበት ጕዳዮች አጥፊው ‘እኔው ነኝ’ ማለት ግን፣ ለኵራተኛው ሰብእናችን ይቸግረዋል፤ የእኛን ተጠያቂነት እስክናምን እና ተገቢውን ማስተካከያ እስክናደርግ ድረስ መፍትሔው ይርቀናል።
በልበ ሰፊነት ካየነው፣ ዋንኛው አጥፊ እኛ እንጂ ሌሎች አይደሉም ማለት ሊከብደን ባልተገባ ነበር፤ ዋንኛው አጥፊ እኛው መሆናችንን መገንዘብ የለውጥን ባሕርይ ጠንቅቀን ለምናውቅ የእፎይታ ምንጭ በሆነን ነበር። አጥፊው እኛ መሆናችን በምንስ ስሌት ዕድል ሊሰኝ ይችላል? ማጥፋት ዕድል የሆነው ማጥፋት የሚፈለግ እና የምንናፍቀው ነገር ስለ ሆነ አይደለም፤ ሰውነታችን እስከፈቀደ ድረስ ላለማጥፋት እና መሰናከያ ላለመሆን ሁል ጊዜ መጣር አለብን። አጥፊው እኛው መሆናችን ከችግር ይልቅ ዕድል የሆነበት ምክንያት ችግሩን ከተረዳን ለመለወጥ ሌላውን መጠበቅ ስለማያስፈልገን ነው።
በአጥፊነት የሚገኝ ዕድል እንዲገባን ነገሩን እኛው ሾፌር ወይም ሌሎች ከሚሾፍሩት መኪና ጋር ማስተያየት እንችላለን። መሪውን የጨበጥነው እኛ ከሆንን ሌሎችን ማስረዳት ሳያስፈልገን መንገዳችንን ማስተካከል እንችላለን። እኛ ተሳፋሪዎች በሆንበት መኪና የሾፌሩን ስሕተት ብናውቅ እንኳን፣ ማሳመን እስካልቻልን ድረስ መንገዳችን አይስተካከልም። አጥፊነት ዕድል የሚሆነው ከለውጥ ባሕርይ ጋር ተያይዞ ነው። መራሩ ሀቅ ሰዎች መለወጥ የምንችለው ራሳችንን እንጂ ሌሎችን አይደለም፤ ለሌሎች መለወጥ ምክንያት የምንሆነው ሌሎች እስከፈለጉ ብቻ ነው፤ ፍላጎቱ በሌለበት እኛ የምንዘውረው ለውጥ መቼም ሌሎች ጋር አይኖርም።
አጥፊዎቹ እና ዘዋሪዎቹ እኛው በሆንበት ጕዳይ ግን ራሳችንን ማስተካከል ስንጀምር የተበላሹት ግንኙነቶቻችን በፍጥነት መስተካከል ይጀምራሉ። ለተበላሹት ግንኙነቶቻን አጥፊዎች ሌሎች ከሆኑ ግን ጥፋታቸውን የሚያምን ልብ እስኪገዙ መጠበቅ ይኖርብናል። ይህም ጊዜ ይወስዳል፤ የምንፈልገውንም ለውጥ ያዘገያል። ነገሩ ተቃርኖ ቢመስልም የጠፋን ነገር ለማስተካከል አጥፊዎቹ እኛ መሆናችን ለውጣችንን ያቀልለዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነቶቻችንን ከበርካታ ምክንያቶች የተነሣ ሊበላሹ ይችላሉ፤ የሁሉም ማእከል ግን ከተግባቦት ክኂሎታችን ጋር ይቆራኛል። ይህም ትኵረቴን በተግባባት ላይ፣ ከተግባቦት ላይም ከተግባቦት ውስጥ ብቅጡ መስማት አለመቻላችን ላይ እንዳነጣጥር አድርጎኛል። ራሳችንን፣ የቅርቦቻችንን፣ ባልንጀሮቻችንን እና አምላክን በቅጡ መስማት አለመቻላችን ለግንኙነታችን መታመም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ጥሩ አድማጭነት ብቻውን ለሁሉም ነገር መፍትሔ ባይሆንም፣ አብዛኞቹ ችግሮቻችን ከጅምሩ እንዳይፈጠሩ ለማድረግ እና ከተፈጠሩ በኋላም በቶሎ ለመቋጨት የሚጫወተውን ሚና መገንዘብ ግን አይቸግረንም።
የሁላችን ችግር!
አለመስማት እንደ ችግር ሲነሣ ሁላችንም እንደ ልጅ እንሆናለን። እንደ ልጅነት ዘመናችን የሚቀናን ጣት ጥቆማው እንጂ ኀላፊነት መውሰዱ አይደለም። ሌሎች ሁሉ የመስማት ችግር ያለባቸው፣ እኛ ደግሞ ከሁሉ ይልቅ በማድመጥ የተካንን እንደ ሆንን ይሰማናል፤ ላለመስማታችንም የምንደረድራቸው ምክንያቶች ዐጥረውን አያውቁም። ለነገሩ ሰዎች ለራሳችን ሲሆን ውዳሴውን፣ ለሌሎች ሲሆን ደግሞ ወቀሳውን ማሸከም ተክነናልና ልጥፋቶቻችን ሰበብ መፈለጋችን አያስገርምም።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ከመቶ ሰዎች ውስጥ ዘጠና ስድስቱ ራሳቸውን ጥሩ ሰሚዎች አድርገው ይቈጥራሉ።[1] ይህን ያህል ቍጥር ያለን ሰዎች በርግጥም ጥሩ ሰሚዎች ብንሆን፣ አብዛኞቻችን ስለ ምን የሰሚ ያለህ በሚል እንንከራተታለን? የሚሰማንን እና የሚረዳንን ሰው ያገኘን ዕለትስ ልባችን ለምንስ ያርፋል? ሰሚ ፍለጋ እግራችን እስኪቀጥን መኳተናችን እና የተሰማን ቀን መደሰታችን የሚሰሙ ሰዎች አኀዝ እጅግ ትንሽ መሆኑን ያመላክታል። ሀቁ ሁላችንም መጠኑ ይለያይ እንጂ የመስማት ችግር አለብን፤ አልሰሙንም የምንላቸውም በአብዛኛው በመስማት ከእኛ ይሻላሉ እንጂ አያንሱም፤ የአለመስማት ችግራችንን ማረቅም የመስማት ችግር እንዳለብን ከማመን ይጀምራል።
የቱን ያህል እንደሚያጽናናን እንጃ እንጂ፣ መስማት በመቸገር ብቻችንን አይደለንም። መስማት መቸገር ለውድቀታችን መነሾ እና ከውድቀት ጀምሮ ከሰውነታችን ጋር የተጣባ እና እስከ አሁን ድረስ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለን ያለ ክፉ አባዜ ነው። ይህን የተገነዘበው ሐዋርያው፣ “ለመስማት እንድንፈጥን ለመናገር ግን እንድንዘገይ” ይመክረናል (ያዕቆብ 1፥19)። ግሣጼው ያስፈለገን እኛ ለመናገር የፈጠንን እና ለመስማት የዘገየን ስለሆንን አይመስላችሁምን? ፈጽመን እንዳንሰማ ወይም ከፍለን ብቻ እንዳንሰማ ከሚያደርጉን ልማዶች መካከል የተወሰኑትን እንንቀስ።
ክፉ ልማዶች
አንዳንዶቻችን የምንችለው በሙሉ ልብ ማድመጥ ሳይሆን፣ ሰሚ መምሰልን ብቻ ነው። በዐብሮነት ያለው አካላችን እንጂ ልባችን በዐሳብ ነጉዷል፤ አካልን አስገኝቶ በዐሳብ መባዘን የብዙዎቻችን ችግር ነው። ጥሩ ሰሚዎች ስንሆን ግን የምናስገኘው አካላችንን ብቻ ሳይሆን፣ ሁለንተናችንን ይሆናል። ዛሬ ላይ ተሳክቶልን ሰማን ያልን ዕለትም ሁሉን ከማድመጥ ይልቅ የምንፈልገውን መርጦ መስማት ይቀልለናል። ያልገቡንን ነገሮች ጠይቆ ከመረዳት ይልቅ፣ የእኛውኑ ግምት በሌሎች ሰዎች ንግግር ውስጥ ስንሰገስግ እንገኛልን። ማድመጥ ሌላውን መረዳት እንጂ ራስን መልሶ ማድመጥ አይደለም። ጥሩ አድማጭነት ሁሉን እንድናደምጥ እና ባልገቡን ነገሮች ላይ በችኰላ ድምዳሜ ላይ ከመድረስ ይልቅ ማብራሪያ እንድንጠይቅ ያደርገናል።
አዲስ ንግግር ሰው እየተናገረ ቀድሞ የሰማነው ነገር ጨምድዶ የሚይዘን ጥቂት አይደለንም። አንዴ የሰማነው ሰው ሁሌም አቋሙ እና አመለካከቱ ተመሳሳይ ይመስለናል። ዐሳባችንን ስንቀያይር ራሳችንን የምናገኝ ሰዎች ሌሎች ከዐሳባቸው ፍንክች አይሉም ብለን ማመናችን በርግጥም ያስገርማል። ሰዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ ስንዘነጋ በአንድ ጕዳይ ሰዎችን ከአንዴ በላይ አናደምጥም፤ ከሰማንም የማወቅ ጕጕት አይታይብንም። ጥሩ አድማጭ ስንሆን ግን አንድ ፊልምን ደጋግመው ያለመሰልቸት የሚመለከቱ ልጆችን እንመስላለን። በእያንዳንዱ ድግግሞሽ ውስጥ ከዚህ በፊት ልብ ያላልነውን ነገር የምናስተውልበት ዕድል ይኖረናል።
አንዳንዶቻችን ደግሞ የምንሰማው የተናጋሪውን ስሜት አጥልለን ነው። የሌላውን ዐሳብ አንሥቶ ስሜትን ገሸሸ ማድረግ እንደ በደል እንደሚቈጠር፣ ሰዎች ቃላቸውን ብቻ ሳይሆን ስሜታቸውንም ጭምር መደመጥ እንደሚፈልጉ እንዘነጋለን። ስሜትን ማድመጥ አለመቻልም በአካል መቀራረቡ እያለ የሥነ ልቦናዊ ርቀትን እንድንፈጥር አድርጎናል። ጥሩ አድማጭ ሲወጣን ከቃል ባሻገር ያሉ የስሜት እና የድርጊት መገለጫዎች ጭምር ልባችንን ይገዙታል። ስሜቶችን እና ድርጊቶችን አለማድመጥ የከረሙ ቅያሜዎችን ድንገቴ ውሳኔ አድርገን እንድንመለከታቸው ያደርጉናል።
የአንዳንዶቻችን አሰማም እያደመጥን መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ የለውም፤ የፈዛዜ የሚባለው ዐይነት ነው፤ ንቃት ይጎድለዋል። ስናደምጥ በየመኻሉ ያልገቡንን ጥያቄዎችን አንጠይቅም፤ በአካላችን ጭምር የሚገለጥ ንቁ ተሳትፎ የለንም። የሰማነውን ነገር ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እና መረዳታችንን ለማሳየት በእኛው ቃል የሰማነውን ነገር መልሶ መግለጽ እንደሚያስፈልግ የምንዘነጋም አለን። እነዚህ ሁሉ ቅያሜን የሚፈጥሩ እና መተማመንን የሚያጠፉ ክፉ ልማዶች ናቸው።
መሰማት አንናፍቅ
የሐዋርያው ያዕቆብ ለመስማት ፍጠኑ ያለን በከንቱ አይደለም። መስማት ግንኙነቶቻችን ጤናማ እንዲሆኑ ከምናደርግበት ምክንያቶች መካከል ዋንኛው ነው። የመስማትን አስፈላጊነት የተረዱ ሰዎች በታሪካችን ውስጥ አልጠፉም፤ የእነዚህ ሰዎች ዐይነተኛ መለያ ለራስ ከሚገባው በላይ ትኵረት አለመስጠት ነው። ጥቅሙን ከተረዱት የቤተ ክርስቲያን የበረሓ አባቶች መካከከል መናኙ አባ ፓይመንን እናንሣ። እኚህን አባት “በምኖርበት አከባቢ እንዴት ልኑር?” ሲል አንድ ሰው ይጠይቃቸዋል። ይህ ጥያቄ የቀረበው ለእኛ ቢሆን መልሳችን ምን ይሆን? ‘ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ተናገር፤ የማትጠቀምበት ዕድል አይኑር’ እንለው ይሆን? የመናኙ መልስ ግን አስገራሚ ነበር። እንዲህ ሲሉም መከሩት፣ “በግዞት እንዳለ ሰው ራስህን ተመልከት፤ መሰማትን አትሻ፤ ያኔም ሰላም ይኖርሀል።”[2]
የመነናኙ አባት መልስ ከሰውነታችን ቅኝት ጋር የሚገጥም አይደለም። ማናችንስ በተወለድንበትና የእኔ ነው በምንለው አከባቢ እንደ ግዞተኛ መኖር እንፈቅዳለን? ሰዎች ሁሉ ስለ እኛ ቢያወሩ እና ቢተርኩ ደስ አይለንምን? አድማጮች በሆንበት ቦታስ ተናጋሪው እኛ መሆን ነበረብን በሚል የምንብሰለሰልስ አይደለንምን? ሰዎች በባሕርያችን ሁል ጊዜ ካድማጭነት ይልቅ ወደ ተናጋሪነት እናደላለን፤ እኛ ሰው ሁሉ ሊሰማው የሚገባ ሌሎች ደግሞ የሚደመጥ አንዳች ነገር እንደሌላቸው እናስባለን። ምኞታችንም የተሻለ ተደማጭነት የምናገኝበት መድረክ ፍለጋስ አይደለምን? የተደማጭነት ፍለጋ ጕዞ ጥላን እንደ መከተል መሆኑ ይጠፋናል፤ ጥላ በቀረብነው ቍጥር ይርቀናልና ነፍሳችንን ሰላም ያሳጣታል። የምንናገርበትን መድረክ መፈለግ የልባችን ጥማት ሆኖ እስካለ ድረስ በርግጥም ማድመጥ ቅኝታችን የመሆኑ ዕድል አናሳ ነው። ሌላው ሲናገር የመናገር ተራውን በጕጕት የሚጠብቅ ሰው በትክክልስ እንዴት ከልቡ ያደምጣል?
ለምን ከበደን?
በደንብ ካሰብነው ማድመጥ ከመናገር ይልቅ መቅለል ነበረበት። የዚህ ዐይነተኛ ምክንያት ማድመጥ እንደ መናገር አንደበተ ርቱእ መሆንን እና በርካታ ዕውቀትን ማከማቸት ስለማይፈልግ ነው። በሙሉ ልብ ራስን ማስገኘት ብቻውን ለማድመጥ ይበቃል። ለዚህም ነው ጠቢቡ ሞኞች እንኳን በዝምታቸው ጠቢብ ተደርገው ይወሰዳሉ የሚለን (ምሳሌ 17፥28)። ማድመጥ እንደ ጠቢብ ሞኞችን እንኳ የሚያስቈጥር ሆኖ ሳለ ስለ ምን ከበደ? መናገር ከባዱ ነገር ሆኖ ሳለስ ስለ ምን ቀለለ? ከመናገር በመቆጠብ ከብዙ ኀጢያት መዳን (ምሳሌ 10፥19) እና አክብሮት ማትረፍ እየተቻለ (ምሳሌ 11፥12) ስለ ምን በፊታችን ቀለለ? ብዙዎቻችን ማመን ይቸግረናል እንጂ፣ ከማንም በበለጠ እጅጉን መስማት የምንወድደው ድምፅ የራሳችንን ነው።
ስለ ራሳችን ስናወራ ጥሩ ስሜት ይሰማናል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኔውሮሳይንስ መስክ የተደረጉ ጥናቶች ስለ ራስ መናገር ልክ ምግብ፣ ገንዘብ እና ወሲብ የሚሰጡትን ዐይነት ደስታ ለሰዎች እንደሚያጎናጽፉ አመላክተዋል። ነገሩ ስለ ራሳችን ስናወራ የሚሰማን ስሜት የምንወድደውን ምግን ስንበላ፣ ገንዘብ ስናገኝ እና ወሲብ ስንፈጽም ከሚሰማን ጥሩ ስሜት ጋር ይመሳሰላል። ስለ ራሳችን ማውራት ጥቅማችንን እንደሚያስቀርብን እያወቅን እንኳን ስለ ራሳችን ከማውራት የምንቆጠበውም ጥቂቶች ነን። በቤተ ሙከራ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች ይህን ያመለክታሉ። ስለ ራሳችን ለማውራት በሚል ብቻ ከምናገኘው ገቢ 25 ከመቶ ያህሉን እስከማጣት ድረስ እንደምንጨክን ያሳያሉ።[3] እውነታው ሰዎች ማውራት እና መሰማት እጅግ እንወድዳለን፤ መስማት ደግሞ የአብዛኞቻችን ፈተና ነው።
ከላይ የጠቀስናቸው ጥናቶችም አንድምታቸው ምንድን ነው? የማድመጥ ችግራችን ፈተናው ራሳችንን ማድመጥ ከሚሰጠን ደስታ ጋር መጣባቱን ያመለክታል። የቅርብ ደስታ ከሚሰጡ ነገሮች ማሸነፍ የቱን ያህል ከባድ መሆኑን ደግሞ በሕይወታችን እናውቀዋለን። ማድረግ እንደሌለብን የምናውቃቸው የምናደርጋቸው ነገሮች ብዙ አይደሉምን? የአብዛኞቻችን ችግርስ የቅርብ ደስታን ለዘለቄታዊ ደስታ መሠዋት አለመቻል አይደለምን? ከሥጋ ይልቅ አትክልት አብዝቶ መብላት ጠቃሚ መሆኑ በባለሙያዎቸ ተደጋግሞ ቢነገርም፣ ሥጋውን ስናላምጥ የሚሰጠንን ደስታ ዐልፈን መሄድ ግን ይቸግረናል። መጠጥ፣ ማጨስ እና መቃም የሚያመጣውን ችግር ብዙዎች እያወቁ ከሚሰጡት የቅርብ ደስታ ራሳቸውን መግታት ይቸገራሉ።
ማድመጥን የምንሸሽበት ሌላኛው ምክንያት አድማጭነት የደካማነት ስሜት እንዲሰማን ስለሚያደርግ ነው። የራሳችን አስተያየት ባለን ጕዳዮች ላይ፣ ሌሎች ሲናገሩ እና እኛ ስናደምጥ ዐሳባችንን ይፈተሻል፤ የምናደምጣቸው ዐሳባችንን እና አመለካከታችንን ያጸኑልናል ወይም ይሞግቱናል። ሌሎቹን መስማት አለብን የሚለው እምነት ማናችንም ምሉዕ አለመሆናችንን እንድናምን ያደርገናል። ማናችንም በምንም ጕዳይ መሉዕ አለመሆናችን እውነት ሆኖ ሳለ፣ ለምን ይህንኑ እውነት ማመን እና መኖር አልፈለግንም? ነገሩ ማናችንም ራሳችንን አንዳች ነገር እንደጎደለው መመልከት ካለመፈለጋችን ጋር ይያያዛል። በመምሰል ደረጃ እንኳን ቢሆን እንደ አዋቂ አቋም በያዝናቸው ጕዳዮች ላይ መቈጠር እንፈልጋለን። ስለዚህም የሚሞግቱትን ነገሮች ስናደምጥ የእኛን አተያይ ለማዳበር ከመጠቀም ይልቅ የምንሰማውን ነገር ቸል ወደ ማለት እናዘንብላለን። ይህም ተናጋሪዎቹ ልባችን ውስጥ ቦታ የሚያገኙት ከእኛ ዐሳብ ጋር ዕይታቸው የቱን ያህል ገጥሟል በሚለው ሚዛን እንዲሆን ያደርገዋል። ከእኛ ዐሳብ ጋር የማይገጥም ዐሳብ በተሰነዘረ ቍጥር፣ መከላከያ ዐሳብ ወደ ማደራጀቱ እናጋድላለን።
የተሻለው መንገድ
መስማት የሁላችንም ችግር ከሆን ምን እናድርግ? ከሁሉ በፊት የመስማት ችግር እንዳለብን እንመን፤ ያለመስማት የሚያስከፍለንን ዋጋም እንረዳ። የመስማት አስፈላጊነትን በየዕለቱ የሚያስታውሱ ምልክቶች በሕይወታችን ውስጥ ይኑሩን፤ መስማትን የሚያወድሱ አባባሎችን እናሰላስል፤ መስማት የምንችልበትን ጸጋ እንጠይቅ፤ በእርስ በእርስ ግንኙነቶቻችን ውስጥ ሌሎችን እየተረዳናችው መሆኑን ለመጠየቅ እንድፈር። ባለመስማት የሚጠቅመንን እና የሚያሳድገንን ነገር በተከላከልን ቍጥር ግን፣ ይበልጡኑ እንደምንጉድል እንጂ አንዳች እንደማናተርፍ ራሳችንን እናስረዳ፣ እንሞግት።
በመስማት ራሳችንን ከማደርጀት ይልቅ ወደ መከላከሉ እና ወደ ማጥቃቱ የምናደላበት ምክንያት ማድመጥ እኛ የማናውቀው፣ ነገር ግን ማወቅ የነበረብንን ነገር ሌላኛው ሰው ሊሰጠን ይችላል የሚል ሰፊ እና ቅን ልብ ስለሚፈልግ ነው። ይህን ልብ አብዛኞቻችን በተፈጥሮ ስላልታደልነው በልምምድ ልናመጣው እንጣር። ማድመጥ መደጋገፍን ማመን እንጂ፣ ትንሽነት ሆኖ አይሰማን። አድማጮችነት ለአደባባይ ሕይወት ባይሆንም እጅግ ተፈላጊ ሰው የሚያደርግ መሆኑን ግን እናስተውል። ከመስማት ይልቅ ለመናገር ያለንን ውስጣዊ ጕጕትም ገደብ እናስይዘው። ያኔም በማድመጥ ውስጥ የምንገኛው ልዩነት ከሚያፈርሰን ነገር ይልቅ የሚሞላን እንደ ሆነ ስለምናውቅ የተለየ አተያይ ሆን ብለን የምንፈልገው ነገራችን ይሆናል። ባደመጥን ቍጥር ልባችን ሁሉን በአክብሮት ማስተናገድ የሚችል እንግዳ ተቀባይ ቤት ይሆናል። ከመጋፋት ይልቅ መደጋገፍ እና መተባበርን ምርጫችን ይሆናል። የሚያደምጥ ልብ ጋር ሁሉም ቤተኝነት ስለሚፈልግ፣ መተማምን ይገነባል፤ መተማመን ካለ ደግሞ ጥሉ አያሰጋንም፤ ግንኙነቶችም ይፈወሳሉ። ግንኙነቶቻችን አሁንም ድረስ ‘የጆሮ ያለህ’ እያሉ እየተጣሩ ነው። ጆሮ አለን?
[1] Lynn H.Turner and Richard West. An introduction to communication (Cambridge University Press, 2018), 109.
[2] John Wortley, The anonymous sayings of the desert fathers: A select edition and complete English translation (Cambridge University Press, 2013), n.p.
[3] John Wortley, The anonymous sayings of the desert fathers: A select edition and complete English translation (Cambridge University Press, 2013), n.p.
Add comment