[the_ad_group id=”107″]

“ከሥጋ ተለይተን መኖር፣ በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል”

ቴዎድሮስ ሲሳይ

ዳግም የተወለደው፣ የጌታ ፍቅር በልቡ በእውነት የፈሰሰለት፣ የመንፈስ ቅዱስን መገኘት እና የአምላክን ኅብረት የቀመሰ፣ እርሱ ሰው ዘላቂ ደስታ በሥጋዊነት ውስጥ የለውም። ለጊዜው ከጌታ ትምህርት ቢለይ፣ ከቃሉ ትእዛዝ ቢያፈነግጥ፣ ስቶም በክፉዎች ምክር ቢሄድ ወይም በኀጢአተኞች መንገድ ቢቈም፣ በፌዘኞችም ወንበር ቢቀመጥ፣ ወዘተ. ለጊዜው ነው እንጂ፣ በዚያ ለመቆየት ምቾት የለውም። በሥጋ ክፉ ምኞት እና መሻት መኖር፣ በዚያም ተረጋግቶ መቀመጥ አይችልም፤ በዚያ ምድር መከተም አይሆንለትም። ሥፍራው ከዚያ አይደለምና ቤተኝነት አይሰማውም፤ ይከብደዋል፤ ያቃስታል፤ ይቃትታልም።

በእውነት “የሕይወት ውሃ ወንዝ” የሆነውን ኢየሱስ ጠጥቶ የሚያውቅ ሰው፣ ከጌታ ተለይቶ በሥጋ ምድረበዳ ማደር ዘግይቶ አይመቸውም፣ ቆይቶ ይጎረብጠዋል። ከጌታ ተለይቶ በሄደበት መንገድ፣ በዚያ ሲጀምር ደስታን ወይም ተድላን ያገኘ የመሰለው ቢሆን እንኳን ከእንግዲህ ደስ አይለውም፤ ከአሁን በኋላ አይደላውም። ቀድሞ የጣፈጠው ነገር አሁን ይጎመዝዘዋል፤ አሁን ያሳፍረዋል። በዚያ የሚበላው ሽንኩርት በከንፈሩ ሬት ይሆንበታል፤ የሚያላምጠው ከጕሮሮው አልወርድ ይለዋል፤ የዋጠው ውስጡን ይረብሸዋል፤ አይረጋለትም። ምን ያህል ይዘገይ ይሆናል እንጂ፣ የተስፋይቱን አገር ዐስቦ ሳያለቅስ አይቀርም። እንደ ቆሬ ልጆችም፣ “ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” ብሎ ይጠይቃል (መዝ. 42፥2)።

ከጌታ ኅብረት ለጊዜው የተለዩትን እያሰብን፣ “ታድያ የጠፉት የመመለሻቸው ጊዜ መች ነው?” ብለን ለምንጠይቅ መልሱ፣ አንዱ እንደ ጴጥሮስ የዶሮውን ጩኸት ሦስት ጊዜ እንደ ሰማ ወዲያው ያለቅሳል፤ ሌላኛው እንደ ዮናስ፣ “በሲዖልም ሆድ ውስጥ” ሆኖ ለመጮኽ፣ የዋጠውም ዓሣ እንዲተፋው ሦስት ቀን ይፈጅበታል፤ ደግሞም ሌላው እንደ እስራኤል የምሬቱ ልቅሶ ከሰማይ ሊሰማ፣ ከፈርዖንም ግዞት ለማምለጥ “የጌታ ኀይል” ይሆንለት ዘንድ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ያልፍበታል። ዋናው ነገር፣ “የጠፋው ልጅ” ምን ያህል ይዘገይ እንደ ሆነ አናውቅም እንጂ፣ ማልቀሱና መጮኹ ግን አይቀርም። ርዳታን ከማግኘቱ በፊት ግን፣ መጮኽ እና ማልቀስ ግድ ይለዋል። ጊዜውን እና ሰዓቱን አናውቅምና፣ እኛ በቤት የቀረን ቤተኞች ስለጠፋው ልጅ ማሰብ ከሆነልን “አቤቱ፤ እባክህ አሁን አድን” የሚለውን ጸሎት እናቅርብ (መዝ. 118፥25)።

የጠፋው ልጅ፣ አስቀድሞ የቀመሰው የጌታ ፍቅር ትዝታው ሲያገረሽበት፣ የተስፋው ናፍቆት ሲበረታበት፣ ያኔ ራሱን ካገኘበት ከባዕድ (ከሥጋዊነት) ምድር ሆኖ፣ “ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር፣ በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል” የሚለውን ተመሳሳይ የናፍቆት ድምፅ ያሰማል (2ኛ ቆሮ. 5፥8)። ከሙታን ሠፈር የተከለውን ድንኳኑን አፈራርሶ፣ ካስማውን ነቅሎ፣ ወደ ብርሃን መንገድ፣ ወደ ተስፋይቱ አገር፣ ወደ ሕያዋን ማኅበር፣ ወደ ጌታም ገበታ ለመድረስ የሚቸኩልበት ቀን ይመጣል። ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ነጻነት ይፈልሳል። ከሞት ወደ ሕይወት ይሮጣል። እንደ ወፍ በርሮ ያመልጣል።

ነፍሴ እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች፣

በረረች አመለጠች ነፍሴ፣ በአዳኟ በአየሱሴ

የተሰኘውን የነጻነት እና የደስታ መዝሙር[1] ይዘምራል። የማምለጥ ነገር የገባቸው ደግሞ፣ ዐብረውት ይዘምራሉ።


[1] ይህ መዝሙር በዘማሪ ሳሙኤል ተስፋ ሚካኤል የተዘመረ ነው። ዝማሬውን በሚከተለው የዩቲዩብ መስፈንጠሪያ ማድመጥ ይችላሉ፦ https://music.youtube.com/watch?v=ykHhZPn-Nls&si=hFY5jzrHrER0iLkY

Tewodros Sissay

ቴዎድሮስ ሲሳይ፣ ነዋሪነቱን በምድረ አሜሪካ፣ ቴክሳስ ዳላስ ውስጥ ያደረገ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው።

Share this article:

የወንጌላውያኑ መንታ መንገድ

የኢትዮጵያ ወንጌላዊው ክርስትና በአገሪቱ ከመቶ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈው ይህ ሃይማኖታዊ ማኅበረ ሰብ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ የራሱን አሻራ እየተወ የመጣ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይልቁኑም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እንደ ከዚህ ቀደሙ የተናቀ ማኅበረ ሰብ ሆኖ ላለመቀጠል በሚያደርገው ትግል እየተፈጠረ ያለው ለውጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት የተከሰተው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ለውጥ በአገሪቱ ሃይማኖታዊ መስጋብር ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በዚህ ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚም ተጎጂም መኖሩ አይቀርም፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ ይህ ለውጥ ለወንጌላውያኑ ማኅበረ ሰብ የድል ብሥራት ይዞ እንደመጣ ሊታሰብ ይችላል፡፡ በርግጥ ይህ አስተሳሰብ እውነት የሚሆንባቸው ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላል፤ በአንጻሩም ያልተጠበቀ ውጤት አስከትሎ እንደ ሆነ ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

መሪነትም እንደ ውበት

ለመሆኑ፣ የየቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች አንድን የአመራር ዘይቤ በሚመሯት ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንዲውል ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳሰቡት የአመራር ዘይቤውን ውጤታማነት ማየት ቢቸግራቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ተጨማሪ ያንብቡ

የማይናወጥ ሐሴት

“እግዚአብሔር አምላክህከጓደኞችህ ይልቅበደስታ ዘይት ቀባህ፥”ዕብራውያን 1፥9 “መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ …ወደ ጌታህ ደስታ ግባ:”ማቴዎስ 25፥21 የማይናወጥ ሐሴትየኢየሱስ ክርስቶስ ደስታትርጕም በአማረ ታቦር ከከፋ አደጋ ያዳኖት

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.