[the_ad_group id=”107″]

የተዘነጋው አሁን

የተቃራኒ አቅጣጫ ጉተታ

ሁላችንም መለወጥ የምንፈልግባቸው የሕይወት አቅጣጫዎች አሉን። እነዚህ የለውጥ ትልሞቻችን መና እንዲቀሩ አንፈልግምና ለለውጡ ስኬት የሚፈለግብንን ለማድረግ እንጥራለን። የምንፈልገው ለውጥ ከምንም ቀደሞ ልባችንን አሁን (Now) ላይ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። ቀልብን አሰባስቦ ሊሠራበት በሚችለው በአሁን ላይ ማተኮር የሚያስፈልገው ያለ ምክንያት አይደለም፤ ለውጥ በሙሉ ኀይል ባለን ጊዜ ላይ ተጠቅመን የምንዘምትበት እንጂ በግማሽ ልብ እንደ ነገሩ ነካክተን የምናመጣው ጉዳይ ስላልሆነ ነው። “ጠቢብ ሲጓዝ እየተጓዘ ነው፤ ሲቀመጥ ተቀምጧል፤ ሌላ እየሆነው ያለ ምንም ነገር የለም።” የሚለውን አባባል ባለን አሁን ውስጥ የምንከውነውን እያንዳንዱን ነገር በአስተውሎት እና በትኩረት ልናደርገው እንደሚገባ ያሳስበናል። ጥቂት የማንባል ሰዎች ችግራችን እግራችን ሲጓዝ ልባችን መቀመጡ ነው፤ ልባችን ሲቀመጥ ደግሞ እግራችን ይጓዛል። ራሳችንን በተቃራኒ አቅጣጫ እየጎተትን፣ የነበርንበት ቦታ የሁሌው አድራሻችን ሆኗል። አካላችን፣ ልባችን እና አእምሮአችን በተናጠል መሮጡ እስካላበቃ፣ ባለንበት መርገጣችን ይቀጥላል።

የዝንጀሮ አእምሮ

የእኛም ልብ ሆነ የምንኖርበት ዓለም ግርግር እንደ ሆነ እናውቃለን። እያንዳንዱ ሰከንድ በርካታ ሐሳቦችን በማቀበል እያከናወንን ካለነው ነገር ሕሳባችንን ለመስረቅ ይታገለናል። ካልነቃን ደግሞ አእምሮአችን እንደ አሸን እየፈሉ ከሚወርሩት ሐሳቦችና ክስተቶች ጋር አብሮ ይሾራል። ዙረት ደግሞ ሥራ አይደለም። የምንከውነው ነገር ላይ ትኩረታችንን አሰባስበን መዝለቅ አለመቻላችን አያስገርምም፤ ጥናቶች የሚያሳዩት ሰዎች በሐሳባችን ማሳ ውስጥ እንደተለቀቁ ዝንጀሮዎች ባተሌዎች መሆናችንን ነው። ከምንከውናቸው 100 ነገሮች ውስጥ 47ቱን የምናደርገው፣ አእምሯችን ሌላ ነገር እያሰላሰለ መሆኑን የጠቆመ ጥናት አለ። ምጣኔው ያስደነግጣል። የሰው ልጅ አእምሮ ያየው ሁሉ እንደሚያምረው ዝንጀሮ ከሐሳብ ሐሳብ መዝለሉ “የዝንጀሮ አእምሮ” እንዲሰኝ አድርጎታል።1 በዚህች መጣጥፍ ዛሬ የምንከውነውን ነገር ሙሉ ኀይላችን አሁን ላይ ማድረግ የሚያስችሉንን መርሖች መመልከት ግባችን ነው።

ቁጭት እና ቅዠት

ተሳክቶልን አንድ ሐሳብ ያወጣን ያወረድን ዕለት እንኳ አሁን ላይ አተኩረናል ማለት አይደለም። የምናስበው ሐሳብ ተግባራችንን እና ትኩረታችንን ከአሁን የሚያፋታበት ጊዜ አለ። ነገሩን ከሥረ መሠረቱ ብለን የጀመርነው የኋልዮሽ የሐሳብ ጉዞ እንድንሠራበት የተሰጠንን አሁንን አስረስቶ በሌላ የሐሳብ ሰረገላ ወደ ትላንት ያነጉደናል። ‘ያለፈ ትላንትን ምን ሊረባን?’ ብለን የጨከን ዕለትም የሚጠብቀን ሌላ ፈተና አለ፤ ቀልባችን በነገ እልም አስተኔ (fantasy) እና ዕቅድ (planning) ተሳፍሮ ወዳልደረሰበት ነገ ይነጉዳል። ከለውጥ ጋር ተያይዞ፣ ትላንትን ሆነ ነገን ማሰባችን በራሱ ክፋት የለውም፤ እንደውም ያስፈልጋል። የነገርን መጨረሻ እንደ ልባም አስቀድሞ አስልቶ መንቀሳቀስም ይጠቅማል። በዛሬው ጉዞው ከትላንት ትምህርት መቅሰም እና ነገን ተልሞ መነሣት፣ በለውጥ መንገድ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለመቋቋም ትከሻን ያሰፋልና እሰየው ሊባል ይገባል። ችግሩ የሐሳባችን ትኩረቱ ያለፍነው ትላንት እና የነገ ዕቅድ ብቻ ሲሆን ነው። አሁንን ዘንግቶ በተወሰደ ትላንት እና ባልተሰጠ ነገ ላይ መንጠልጠል ሕይወታችንን የኋላ ኋላ የቁጭት እና የቅዠት ማድረጉ አይቀርም።

ሰው ግን አሁን ውስጥ እየኖረ አሁንን ሊዘነጋ ይችላልን? መጠርጠሩሳ! ስንቴ ቀልበ ቢስ ሆነን እናውቃለን? እንደ ጅብራ ከተጋረጠ ነገር ጋር ስንጋጭ ሌሎች አይተው አልሳቁብንም? የሚያንባርቅ ጥሩንባ ሳንሰማ ቀርተን ከአደጋ ለጥቂት ተርፈን አናውቅም? ሐሳባችን ውጦን፣ ልንጠጣ ያዘዝነው ሻይ፣ ስኳር በሻይ እስኪመስል ሞጅረነው አናውቅም? ይኽ ሁሉ የሆነው፣ የስሜት ሕዋሳት ጥለውን ሸሽተው አይደለም፤ ሐሳባችን በትላንት፣ በአሁን እና በነገ መካከል ስለ ተቅበዘበዘ እንጂ! የሐሳብ ትኩርት ከአሁን ወደ ትላንት ወይም ወደ ነገ ብቻ ሲዞር፣ አሁን በርግጥም ተዘንግቷል። እንግዲህ አሁን የሚዘነጋ ከሆነ፣ አሁን ላይ ማተኮርን እንዴት እናዳብር የሚለው ጥያቄ ይነሣል። አሁን ላይ ማተኮር የዛሬን ሥጦታነት ተገንዝቦ፣ ለውጤታማነት ተዋስቦ (interaction) ማድረግ ነው። ስናስተውል ከባቢያችን ሆነ ውስጣችን የሚከሰተው ነገር እንግዳ መሆኑ ያበቃል። በውጤቱም፣ ነገሮችን በአዲስ መልክ መመልከት የምንችልበትን አቅም እንጎናጸፋለን፤ ገዳቢ እና አፍራሽ ሐሳቦቻችን ላይ ቀድመን በመንቃት ልናስቆማቸው እንችላለን። አሁንን የሚያስተውል ቅኝት እንዲኖረን ከተፈለገ ሦስት ነገሮችን ማዳበር ይጠቅመናል። እነዚህም ዐላማ መር አሳቢነት (intention) ዐይነ ልቦና (attention) እና ገንቢ አተያየት (attitude) ናቸው።2

ዐላማ መር አሳቢነት

አሁን ላይ ትኩረት እንዲኖረን ከተፈለገ፣ ለውጣችን ሊፈጽም የሚፈልገውን ዐላማ ማወቅ እና በዛው ዐላማ አሁናችንን መቃኘት ያስፈልጋል። ዐላማ መር አሳቢ ስንሆን፣ ከከበቡን ነገሮች መካከል ለየትኛው ትኩረት መሰጠት እንዳለብን አስቀድመን ስለ ወሰንን፣ ለጠራን ሁሉ ‘አቤት’ አንልም። እነዚህ ትኩረታችንን የምንቃኝባቸው ዐላማዎች፣ ማስታወሻ ደብተሮቻችን ላይ በትልቁ ተጽፈው የሚቀሩ ሳይሆኑ፣ በአእምሯችን ውስጥ አስታዋሽ ሆነው ሊታታሙ ያስፈልጋል። ሕይወታችን በዐላማ መር አሳቢነት ሲመራ እያንዳንዱ ሐሳብ፣ ስሜት እና ተግባር ይመዘናልና እያንዳንዱ ሰከንድ የሚያቀብለንን ሐሳብን ‘የሸምጥጥ’ ፊሽካ አድርገን መቁጠራችን ያበቃል። ዐላማ መርነት፣ ሐሳባችንን የምንፈትሽበት ሚዛን እንደ መስጠቱ ከባተሌነት ያድነናል፤ ሁሉን ነገር ከፍላጎታችን፣ ከዐላማችን እና ከራእያችን ጋር እያጠለልነው ስለምንሄድ ከውዥንብርም ይጠብቀናል። የምንፈጽመው ነገር ውጤቱ እዚያው በዚያው የማይታይ ሲሆን፣ ያለ ዐላማ ረጅም መንገድ መሄድ ይከብዳል። የለውጡን ዐላማ በትክክል ካወቅን ግን የምንሠራውን ነገር ያለውን ዋጋ በማስታወስ ጉልበታችንን ያበረታል፤ የአጭር ጊዜ ርካታን በማጣጣም ከረጅሙ ጉዟችን እንዳንዘናጋም ይረዳናል። ዐላማ መር አሳቢነት የልባችንን ሐሳባ ፍንትው አድርጎ ይገልጣል። ጥልቅ የሆኑ ጥበቃዎቻችን እና ፍላጎቶቻችንን መደበቂያ አይኖራቸውም። እኛው ለእኛ እንግዳ መሆናችን ያበቃል። ከእኛነታችን ውስጥ ለመጋፈጥ የምንፈራው ማንነት እንዳለመኖሩ መጠን ከራስ ጋር ድብብቆሽም ሆነ፣ ሽሽት ምንም አይረባንም። ሐሳቦቻችን ስንጋፈጥ፣ ከምንፈልገው ማንነት በተቃርኖ የቆሙትን ያለ ርኅራኄ እንጥላቸዋለን፤ ለዐላማችን ስኬት የሚያስፈልጉትንም እናነሣቸዋለን፤ ሕይወታችን አቅጣጫ ይይዛል።

ዐይነ ልቦና

ዐይነ ልቦና ሲኖረን እናስተውላለን፤ ያለንበት እያንዳንዷ ደቂቃ ያለ አስተውሎት እንድታልፍ አንፈልግም። ‘ምን ሰማሁ? ምን አየሁ? ምን ሸተተኝ? ምን ተመለከትኩ? ምን አሰብኩ? ስሜቴ ምን ነበር?’ ስንል እንጠይቃለን። አንዳንዴ እኮ በዛው ሰዓት የሚሰማንን ነገር ከመገንዘብ ይልቅ የነገሩን ምንጭ፣ ፋይዳ እና ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በመተንተን (elaborative awareness) አሁንን እንዘነጋለን። ዐይነት ልቦና ያላቸው ሰዎች በአንጻሩ አሁን ላይ ማተኮራቸውን የሚያሳዩ ተግባራዊ መገለጫዎች አሏቸው።

የመጀመሪያው፤ በአንድ ነገር ላይ ሐሳባቸውን አሰባስበው በንቃት መቆየት (sustained attention) ይችላሉ። እንዲህ ዐይነቱ ምልከታ ለጥልቅ ግንዛቤ ቅድመ ሁኔታ ነው። ቀልብን በአንድ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ማቆየት ግን ቀላል አይደለም። በተለይ ደግሞ ውጫዊ ማትጊያ በሌለበት፣ ለረጅም ጊዜ አእምሮን በንቃት ማቆየት ይከብዳል። የምንመለከተው ነገሩ አስደሳች ሲሆን እና ከእኛ የሚጠብቀው ነገር ከአቅማችን ሲያንስ ትኩረት ማድረግ አይቸግርም። በአንጻሩ የምንፈልገው ለውጥ የሚፈልገው ርምጃ ስሜትን የማይኮረኩር ሲሆን፣ በተደጋጋሚ መከወን ሲኖርበት እና ተግባራችን ከእኛ የሚጠብቀው ነገር ሲበዛ በትኩረት መቆየት ይከብዳል። እነኚህን ተግዳሮቶች ማለፍ የሚችል ሰብእና ከገነባን፣ ትኩረታችን አሁን ላይ መሆን አይቸግረውም።

ሁለተኛው፤ ዐይነ ልቦና ያላቸው ሰዎች በምልከታቸው መራጭ ናቸው። የሚገጥሟቸውን መረጃዎች ሁሉ ከማግበስበስ ይልቅ፣ ከጉዳዮቻቸው ጋር ተያያዥነት ያለውን ጉዳይ ነጥለው ማተኮር (selective attention) ይችላሉ። እንዲህ ዐይነቱ ክኅሎት የሚያስፈልግበት ምክንያት፣ ትኩረታችንን የሚፈልገው ነገር ከሌሎች ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ ከመምጣቱ የተነሣ ነው። ዐይነ ልቦና ሲኖረን፣ በፊታችን ካለው መካከል ለአሁን የሚያስፈልገን የትኛው ነው የሚለውን መወሰን እንችላለን። ለዚህ ደግሞ የሚረዳን ትልቁን የሕይወታችንን ስዕል መገንዘብ ያስፈልጋል። ትልቁ ስዕል ከገባን፣ የትኞቹ የቱ ጋር ይገጥማሉ የሚለውን ማወቅ አንቸገርም። ትኩረታችን የሚጠቅመንን እየነጠለ መመልከት ካልቻለ፣ አእምሯችን በብዙ ነገሮች እንደመከበቡ መጨናነቁ አይቀርም።

ሦተኛው፤ ትኩረት መስጠት ሌላውን ሁሉ መዘንጋት ስላልሆነ ትኩረታቸውን በሚገባ ከአንድ በላይ ለሆኑ ጉዳዮች የማከፋፈል (divided attention) አቅም አላቸው። ትኩረትን ማከፋፈል የመቻል ክኅሎት የሚያስፈልገው፣ አንዳንድ ጊዜ ከአንድ በላይ በሆኑ ጉዳዮች መሳተፍ ስለሚያስፈልገን ነው። አራተኛው፤ ሲያስፈልግ ሐሳባቸውን ወደሚፈልጉት ደረጃ በፈቃዳቸው መቀያየር የሚችሉበት ትኩረት (alternate attention) አላቸው። ትኩረትን ማከፋፈል፣ ትኩረትን ከመቀያየር የሚለየው ትኩረትን መቀያየር የሚፈልገው፣ ነገሮች ተራ በተራ እንጂ በአንዴ መከወን አለመፈለጉ ነው። ምሳሌ ከፈለግን፣ መምህራችንን እያደመጥን ማስታወሻ መውሰድ ቢኖርብን፣ የሚያስፈልገን ክኅሎት ትኩረታችንን በምንጽፈው እና በምንሰማው መካከል መከፋፈል የሚፈልግ ነው። በአንጻሩ፣ መኪና እየነዳን የመኪና የጎን እና የኋላ መስታወቶችን መመልከት ቢያስፈልገን፣ ሁለቱንም በአንዴ መከወን የለብንም። ከአንዱ ወደ ሌላው መስታወት እንዘላለን እንጂ በአንዴ ሁለቱንም ልንመለከታቸው አንችልም። እንዳስፈላጊነቱ መከፋፈሉ ሆነ መቀየር መቻሉ ጠቃሚ ክኅሎቶች ናቸው።

አተያየት

ዐይነ ልቦና በራሱ የሚፈለግ ነገር ቢሆንም፣ የመጨረሻ ግብ ግን አይደለም። የትኩረታችን ጥራቱ ምን ዐይነት ነው የሚለው የሚወስነው የአተያየታችን ዐይነት ነው። ይኽ ከሆነ ደግሞ የዐይነ ልቦናችንን አተያይ መፈተሽ ይገባል። ‘አተያየታችንን መመርመር ለምን ያስፈልጋል?’ መልሱ ግልጽ ነው። በአብዛኛው ነገርን በተመለከትንበት ቅጽበት መፍረድ አብዛኛዎቻችን ስለሚቀናን ጭምር ነው። በርግጥ ችግሩ መፍረዳችን ሳይሆን፣ ለፍረጃ መቻኮላችን ነው። ያያነውን ሁሉ ወዲያውኑ መፍረድ እንዳለብን ከተሰማን፣ ለቀደምት ሚዛኖቻችን ባሪያዎች የመሆናችን እና ለሌላ ዐይነት አተያየት ውስጣችን ዝግ መሆኑን ያሳያል። የተዘጋ አእምሮ ደግሞ የሚማር ልብ አይደለምና አሁንን በጉጉት አይመለከትም። ይኽ ደግሞ በርግጥም ችግር ነው። በተለይ አተየታችን በሙሉ አሉታዊ ከሆነ፣ የፍርዳችን ግቡ ራሳችንን ሆነ ሌሎችን ማሳፈር እና መኮነን ሆኗልና ለአዎንታዊ ጉልብትና ሚናው አናሳ ነው። ይኽ ሲባል የእውነት ጣእም አይኑረን፣ የመለየትንም መንፈስ እንጣ ማለት ሳይሆን፣ ነገሮችን በትክክል እስክንገነዘባቸው ፍርድን ማዘግየት የሚችል አተያየት እንገንባ የሚል የበጎ ኅሊና ልመና ነው።

አንዳንዴ ደግሞ በአእምሮዋችን ሽው የሚሉ አሉታዊ አስተሳሰቦችን ከመጋፈጥ ይልቅ በፍጥነት ልንጨቁናቸው (supress) እና በሌላ ልንተካቸው (replace) እንጣደፋለን። እንዲህ ዐይነቱም አካሄድ ገንቢ አይደለም። የስሜቶቻችንን እና የሐሳቦቻችንን ጥልቀት ሳይገነዘቡ ግብ ግብ መግጠም ራስን ለተሸናፊነት እና ለተስፋ ቆራጭነት ማጋለጥ መሆኑን እናስተውል። ይልቁኑ የማንወደደው ማንነታችንን ከመሸሽ ይልቅ እስከ ጥግ ድረስ እንጋፈጠው። ያኔም እውነተኛ ፈውስ ይሆንልናል፤ በራሳችንም ከመደናገጥ እንተርፋለን። ራሳችንን እስከ መቼ ሸሽተን እንችላለን? እንሰብስብህ ያልነው ሐሳባችን ጥሎን ሲፈረጥጥ ያገኘነው ዕለትም፣ ራሳችንን ለመክሰስ አንቸኩል። ይልቁኑ ለራሳችን በሚራራ መልኩ ወደምንፈልገው አቅጣጫ የምንመልስበት ቸርነት (charity) ይኑረን። ለራሳችን ደግነት እና ርኅራኄን ማድረግ ካልጀመርን ጊዜያችን በመብሰልሰል ይባክናል። ይኼም አሁንን የሚያባክን ሌላ ኪሳራ ይሆናል።

የዚህች መጣጥፍ መልእክት ግልጽ ነው። በእጃን ላይ ያለው አሁን እንደ መሆኑ አሁንን አንዘንጋ፤ ልክ እንደ ጠቢቡ ስንጓዝ እንጓዝ፣ ስንቀመጥ አንቀመጥ። ይኽ እንዲሆን ደግሞ በዐላማ መር አሳቢነት ራሳችንን እናሠልጥን፣ ዐይነ ልቦናችን እንክፈት፣ የአተያየታችንም ጥራቱ ይስተካከል። ቸር እንሰንብት!


[1] Ivtzan, Itai, and Tim Lomas, eds. Mindfulness in positive psychology: The science of meditation and wellbeing. Routledge, 2016፣110

[2] Schonert-Reichl, Kimberly A., and Robert W. Roeser, eds. Handbook of mindfulness in education: Integrating theory and research into practice. Springer, 2016፣ 84-85.

Share this article:

መስቀሉ

“መስቀል የሰውን ስቃይ እግዚአብሔር አምላክ የተካፈለበት፣ የኢዮብ ጥያቄ “አንተ የሥጋ ዐይን አለህን?” የሚለው ፍንትው ያለ ምላሽ ያገኘበት፤ ስቃይ ለእግዚአብሔር ባዕድ እንዳልሆነ የተመሠከረበት፣. . . ነው።” በሰሎሞን ከበደ

ተጨማሪ ያንብቡ

አስታራቂ መሪዎች ይፈለጋሉ!

በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኀን የምንሰማው የጦርነት እና የግጭት ወሬ የምንኖርባትን ዓለም በሰቆቃ የተሞላች አድርጓታል፡፡ ጥላቻውና በቀለኝነቱም ከቀን ወደ ቀን እያየለ የሚመጣ እንጂ የሚበርድ አይመስልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.