[the_ad_group id=”107″]

“አሁን ብትመለስ ጌታ ወደ ቤትህ”

“ስንቶች ለስምህ ቆመው ዘምረዋል
ስንቶች በስምህ ስብከትን ሰብከዋል
አሁን ብትመለስ ጌታ ወደ ቤትህ
ከሕይወት ጎድለዋል ጠፍተዋል ልጆችህ”

ዛሬ ማለዳ ከመኝታዬ ከተነሣሁበት ደቂቃ ጀምሮ በአእምሮዬ እያቃጨለ ያለው ይህ የመዝሙር ስንኝ የሰንበት ተማሪ በነበርሁባቸው በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ሲዘመር እሰማው የነበረ ነው፡፡ እንደማስታውሰው ይህ መዝሙር በተዘመረ ቁጥር በየሰዉ ዓይን ውስጥ እንባ ይቋጠር ነበር፡፡ የቀድሞው ፍቅር፣ ትሕትና፣ የዋህነት… አሁን ጠፍቶ ቤትህ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኗል፤ እባክህ በምሕረትህ የቀደመውን ዘመን መልስልን የሚል ተማጽኖ ያዘለ መዝሙር ነው፤ በመቃተት የሚዘመር!

ድንገት ጌታ ወደ ቤቱ ቢመለስስ? የሚለው ጥያቄ የምር የሚያስበረግግ እየሆነብኝ ነው፡፡ በምድር ላይ የጽድቅ ተጽእኖ እንድታመጣ፣ የእውነት ዐምድና መሠረት እንድትሆን፣ በአጠቃላይም እርሱ በምድር ያለ ያህል እንድትወክለው “እንደራሴው” አድርጎ የተከላት ቤተ ክርስቲያኑ እንዲህ መቅኖ አጥታ፣ ወርቁ ብቻ ሳይሆን ሚዛኑም ጠፍቶባት ሲያያት ምን ያህል ታሳዝነው?!

በሙሴ መሪነት ከግብፅ ምድር የወጣው ሕዝብ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ብርቱ ክንድ ዐይቶ ግሩም ዝማሬ አቅርቧል፡፡ አንድ ቀን ግን ሙሴ ይህንኑ ሕዝብ በምድረ በዳ ላይ ትቶ ለዐርባ ቀንና እና ሌሊት ያህል ወደ ተራራ ወጣ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለቀጣዩ ዘመን መርሕ የሚሆነውን ሕግ ከእግዚአብሔር ሊቀበል ነበር፡፡ ሲመለስ ግን የነበረው እንዳልነበረ ሆኖ ጠበቀው፡፡ ለመገናኛው ድንኳን ማሳመሪያ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር ታልሞ ከግብፃውያን ላይ የተበዘበዘው ወርቅ የጥጃ ምስል ተሠርቶበት፣ ለተሠራውም ምስል “ከግብፅ ያወጣን አምላክ” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶት ቅልጥ ያለ ፌሽታ እየተደረገ ደረሰ፡፡ ቁጣውን መቆጣጠር ተሳነው፤ በእጁ ያያዛቸውን የድንጋይ ጽላቶች እስኪሰብር ድረስ! (ዘጸ. 32)

ʻአሁን ጌታ ወደ ቤቱ ቢመለስስ?ʼ ብላችሁ ዐስባችሁ ታውቃላችሁ? እንዲህ ዐስባችሁ ካወቃችሁ ውስጣችሁ ሰላም እንደማይሰማው እገምታለሁ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ ይህንን ዐይነት ጥያቄ አንሥተን ራሳችንን እንድንመረምር የሚጋብዙ ክፍሎች አሉ፤ ለምሳሌ ጌታችን ራሱ በሉቃስ ወንጌል 18፥8 ላይ ኮርኳሪ ጥያቄ አንሥቷል፡- “ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” በሌላም ስፍራ በድንገተኛው የጌታ መመለስ ተዝረክርከው የሚገኙ የቤቱ ሹመኞች እንደሚኖሩ ተጠቁሟል፤ ማቴ. 24፥45-51፡፡ አሁን ጌታ ድንገት ቢመጣስ?

በልጅነቴ እመለከተው የነበረ አንድ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም ላይ የማልረሳው ትዕይንት አለ፡፡ በጕርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ሁለት ልጆች የነበሯቸው እናትና አባት (የፊልሙ ዋነኛ ገጸ ባሕርያት እነዚህ አራት የቤተ ሰብ አባላት ነበሩ) ልጆቻቸውን ትተው ለሥራ ጉዳይ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ፡፡ በመካከል ግን የልጆቻቸውንና የቤታቸውን ደኅንነት ለመጠየቅ ብለው ወደ ቤታቸው ስልክ ይደውላሉ፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ ጎረምሶቹ ልጆቻቸው የወላጆቻቸውን መውጣት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ጓደኞቻቸውን በመጥራት ቅልጥ ያለ ፓርቲ አዘጋጅተው እየጨፈሩ ነበር፡፡ ድንገት የቤቱ ስልክ ሲጮህ ልጁ ያነሣውና “ሄሎ” ይላል፡፡ በወዲያኛው ጫፍ የነበረው አባት በስልኩ ውስጥ ያልጠበቀው የጫጫታ ድምፅ ስለሰማ ደንግጦ የተሳሳተ ቁጥር እንዳልደወለ ለማረጋገጥ “የሚስተር እገሌ ቤት ነው?” ብሎ የራሱን ስም ይጠራል፡፡ ጎረምሳውም ፈጠን ብሎ “ተሳስተሃል ዳዲ” ብሎ ይዘጋዋል፡፡ ወዲያው ግን ይደነግጣል፤ ለካንስ “ተሳስተሃል” ይበል እንጂ ደዋዩን “አባቴ” ብሎ ነበር የጠራው፡፡ ሥነ ምግባር ቢጠፋም የአፍ ልማድ አልጠፋማ!

ይህን ሳስብ የእኛ ነገር ይመጣብኛል፡፡ ቤቱን በራሳችን የስሜት ሙቀት “ቀውጠነው” ባለቤቱን “የእኔ ቤት ነው ወይስ ሌላ?” ብሎ እንዲያስብ ካደረግነው በኋላ መልሰን ግን “አባታችን” እንለዋለን፡፡ ይህስ ከአፍ ልማድ ሌላ ምን ይባላል? ለዚህ ዐይነቱ አፍ ላይ ብቻ ለቀረ ፍቅር የአምላክ ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡- “አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ?” (ሚል. 1፥6)፤ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” (ማቴ. 7፥21)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረውን ፍራቻ የገለጠው በዚህ መልክ ነበር፤ “ስመጣ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል” (2ቆሮ. 12፥20)፡፡ ይህ ፍርሃቱ መነሻ ነበረው፤ በቀደመው ምዕራፍ ላይ እንደተናገረው በሐሰተኛ አስተማሪዎች ምክንያት አእምሮአቸው ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና እንዳይለወጥ ተጨባጭ ስጋት አለበትና፡፡ ድንግሊቱን የክርስቶስ እጮኛ (ቤተ ክርስቲያንን) በማማለል ክብረ ንጽሕናዋን ሊደፍሩ ያሰፈሰፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በምድራዊ ስኬት፣ በአእምሮአዊ ደስታ፣ በአካላዊ ጤንነት ተስፋዎች በማታለል ሙሽራው ሲመጣ ልታገኘው የምትችለውን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ሐሴት ረስታ ለጊዜያዊ ነገሮች እንድትሸነፍ እያደረጓት ይገኛሉ፡፡ አሁን ጌታ በድንገት ቢመለስስ?

የእስራኤል መንግሥት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት ሰሜነኞቹ የተናገሩት ቃል ሁሌ ይገርመኛል፡፡ አርቆ ዐሳቢው ዳዊት በእግዚአብሔር ፍርሃት፣ በብዙ ተጋድሎና በትሑት አገዛዝ አንድ አድርጎ ያስተዳደረው ግዛት ሊበታተን መሆኑን አይተው “ዳዊት ሆይ፣ አሁን ቤትህን ተመልከት” ነበር ያሉት (1ነገ. 12፥16)፡፡ ግን እውነትም ዳዊት በሮብዓም ዘመን ለሁለት ተከፍላ የተዳከመችውን አገሩን ቢያያት ምን ይሰማው ነበር ይሆን? በሌላስ በኩል እነ ጳውሎስ በስውር ሾልከው ለገቡት አሳቾች ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቀው ሳይገዙ ያስተላለፉልን ንጽሕ ወንጌል (ገላ. 2፥5) እንዲህ ተሸቃቅጦ ቢያዩት ምን ይሰማቸው ይሆን? እነርሱስ ሩጫቸውን ጨርሰው አንዴ ላይመለሱ ሄደዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ተመልሶ ይመጣል፡፡ ደግሞስ አሁን ቢሆንስ?

ጌታ በዐውደ ስብከቱ ከሰጣቸው ምሳሌዎች አብላጫዎቹ በዳግመኛ ምጽዓቱ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ ከምሳሌዎቹ እንደምንረዳውም ዳግም ምጽዓቱ የሚሆነው ብዙዎች እንቅልፍ ሲከብድባቸው፣ ዐመፅ በቤቱ መድረክ ላይ እንኳ ሲነግሥ፣ በርካታ ተከታዮቹ በመክሊቶቻቸው በማትረፍ ፈንታ ደብቀው ቀብረውት፣ ወዘተ. ነው፡፡ ስለዚህ “ይመጣልኛል” ሳይሆን “ይመጣብኛል” የሚል ይበዛል ማለት ነው፡፡ በርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “መገለጡን የሚወዱ” የተዘጋጁ ብቻ ናቸው፤ መልካሙን ገድል ተጋድለው (ለወንጌል አሸናፊነት እንጂ ለሥጋቸው ምቾት ያልሆነውን ፍልሚያ)፣ ሩጫውን ጨርሰው (የጥሎ ማለፉን ሳይሆን የወንጌል ዱላ ቅብብሉን)፣ ሃይማኖትን ጠብቀው (ለቅዱሳን አንዴ የተሰጠውን እንጂ እንደ ጥብቆአቸው በልካቸው ያላሰፉትን) የኖሩ (2ጢሞ. 4፥7-8)፡፡

መግቢያዬን በመዝሙር ስንኝ እንዳደረግሁ መደምደሚያዬንም በዚያው ላድርገውና ከተወዳጁ ዘማሪ ታምራት ኃይሌ መዝሙር ጥቂት ስንኞች፡-

“ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው

እነዚያ ባሮች ብፁዓን ናቸው፤

አስቀምጦ ያገለግላቸዋል በማዕዱ

እኔንም አርገኝ ከእነርሱ እንʼዳንዱ”

Leul Hailu

ፍርሀት እና ምሕረት

“ምሕረቱ ያለው፣ ፍርሀቱ ላለባቸው ነው። በእግዚአብሔር የማያምኑ፣ ፍርሀቱን የማያውቁ ወይም የናቁ፣ እነርሱ ምሕረቱን አያውቁም፤ አይቀበሉምም።” ቴዎድሮስ ሲሳይ

ተጨማሪ ያንብቡ

ምስክርነቶቻችን ቢፈተሹሳ?

“ሀገሩን ሁሉ በትምህርቱ የሚያስደምም ሰው ራስ ሆቴል አከባቢ ተነስቷል!” የሚል የወዳጆቼ ጉትጎቷ ቀን ከሌት ቢከታተለኝ፣ በአንድ በኩል በርካቶችን ያስደመመውን ትምህርት ለመቋደስ ብሎም ከዚሁ ከአመለጠህ የወዳጆቼ ጉትጎታ ለማምለጥ በሚል ሁለት ልብ ነበር እግሮቼን ያቀናሁት። በእርግጥም በዛች ቀን ብቻ ወዳጆቼን ምን ነካብኝ ያሰኙ አስተምሮቶችን በአይኔ በብረቱ ተመልክቼ ተመልሻለው፤ ዳግም አልተመለስኩም፤ ደግሞም አልመለስም።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.