[the_ad_group id=”107″]

ፍቅር ማለምለሚያ

በፍቅር የተጋመዱ ጥንዶች ትሥሥራቸውን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ማንሣታቸው አይቀርም። አንዳንዱ ጥያቄ የሚሰነዘረው ለአፍቃሪው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ መልስ ከተፈቃሪው ይሻል። ከሚነሡት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው “የፍቅር ጥያቄ” ነው። ራሳችንን፣ “በርግጥ አፈቅራታለሁ?”፣ “እሷስ ከልቧ ታፈቅረኛለች?” እንላለን። መነሾው ቢለያይም፣ በደስታ መኻል ስንቅር የሚል ጥያቄ እንደ መሆኑ ያስጠላል፤ ያስፈራልም። ሲ. ኤስ. ሊዊስም፣ “ፍቅር በሕይወታችን ካለ ጽኑና ቀጣይ ደስታ ከዐሥሩ የዘጠኙን እጅ ድርሻ ይወስዳል” እንደ ማለቱ ጥያቄው አይናቅም።

ፍቅርን መግለጥ መቻል ስጋት ይቀንሳል፤ መሰጠትን ያሳያል፤ እርካታን ያሳድጋል፤ መቃቃርን ይመክታል፤ ጤናማም ያደርጋል።� ስጋት የወለደው ጥያቄ ደግሞ ልባችን ተንሰራፍቶ ከመቀመጥ ይልቅ ማስረጃ ለማሰባሰብ እየኳተነ መሆኑን ያሳብቃል። በፍቅር መረጃ ያልጠገበ ልብ ደግሞ አደገኛ ነው፤ መቃቃር ይወልዳል። መጽሐፍ ቅዱሳችንም ‘የፍቅር ሙያ በልብ ነው’ በማለት የፍቅር ዝምታን አያደንቅም። እንደውም ካልተገለጠ የሚሰጠው ፋይዳ እምብዛም መሆኑን “የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል” (ምሳ. 27፥5) ይለናል። 

ፍቅርን የመግለጫ መንገዶች 

ሁላችንም ፍቅርን የምንገልጸበት መንገድ አንድ አይደለም። ፍቅር በተግባቦት የሚለዋወጡት ስለሆነ የጋራ ቋንቋ ይፈልጋል።አሊያማ፣ ተግባሩ ሁሉ ግራ ያጋባል፤ ቅራኔ ያስከትላል። የተለያየ መረዳት ፍቅርን የመስጠትንና የመቀበልን ሂደት ያኮላሸዋል። ፍቅር በሚል የምንጠብቀው ሌላ ሆኖ እስካለ፣ ያቀረብነው ምንም ቢከብር ለ‘ተቀበል’ ተባዩ ጠብ አይልም። የተፈቃሪን የፍቅር ግንዛቤ ሳናውቅ ያሳየነው ትጋት ምንዳም የወቀሳ መዐት ይሆናል። አንዳንዴ የአልተፈቀርኩም መነሾም የፍቅር መረዳታችን መለያየት እንጂ ፍቅር መነፈጋችን አይደለም። ከዚህ በታችም የፍቅር መግለጫ ለየቅል መሆኑን በማሳየት፣ ግንዛቤያችን እንድናሰፋ እጋብዛለሁኝ።� በሂደቱ ጉርሻዎችን መጠቆሜ “ያለ አላዋቂ ሳሚ…” ከሚል ወቀሳ አንዳንዶችን አድን ይሆን በሚል ነው።

አዎንታዊ የፍቅር ቃላት

ፍቅርን ስናስብ መጀመሪያ የሚመጡልን አዎንታዊ ቃላት ናቸው። በአዎንታዊና በተከሸኑ ቃላት ፍቅርን መግለጥ ግን በብቸኝነት ለኪነ ጥበብ ሰዎች፣ በተለይም ለዘፋኞች የታጠረ አስመስሎታል። በአፍቃሪያን መካከል የሚነገር ቃል ምንም ቢጎላደፍ፣ ቅርርብ እና ትሥሥር የወለዱት እንደ መሆኑ ዓለማ አቀፋዊ ሽልማት ካገኘ የፍቅር እንጉርጉሮ የበለጠ ይከብራል። ተፈቃሪ ደግሞ ከማንም በበለጠ ጣፋጭ የፍቅር ቃላትን መስማት የሚፈልገው ከአፍቃሪ መሆኑን ማስተዋል ይኖርብናል። 

በአደባባይ ፍቅር፣ ያውም “የገበያው ፍቅር” እንዲህ እየተነገረለት ባለበት ዘመን ፍቅርን በቃላት አለመግለጽ ጨዋነት አይደለም፤ ያስወቅሳል። ታዲያ አፍቃሪያን ውዱ ልብ እንጂ ዋጋው በሚንር ወረቀት የማይታተሙት ቃላት በስስት እየቆጠቡ እንካችሁ የሚሉት ለምን ይሆን? በተለይ ክርስቲያኑ ፍቅርን ከተነፈሰ ለአምላክ ካለው ፍቅር የሚገምስ ሳይመስለው አይቀርም፤ ቁጥብ ነው። አንዳንዶች እንደውም ከአምላክ ጋር የፍቅር ኪዳን ሲገቡ፣ “ሌላ ሰው ታፈቅርና ዋ!” የተባሉ ሁሉ ይመስላል። ለአምላክ ያለን ፍቅር ዕድገት የጤናማነት መለኪያ አካታች አፍቃሪነታችን መሆኑንም አንዘንጋ።

ጠቢቡ ሰሎሞን ሚስትን አስመልክቶ፣ “እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቆ” ማለቱም ለትምህርታችን ነው (ምሳ. 5፥18-19)። ማሕልየ መሓልይንም ስናነብ፣ አካላዊ ውበቷን ሲያደንቅ፣ ከሌሎች ጋር በማነጻጸርም ከእርሷ የተሻለ የሚስበው እንደሌለ መናገሩንም እናስተውል (ማሕ. 1፥15-16)። አሁን እስኪ ሀገሩ ሁሉ የሚያወራለትን ዐይን የማይታየን ይመስል ዝም ማለታችን ምን ይሉታል?

አብዛኛዎቻችን “የኔ ቆንጆ በጣም ነው የምወድሽ”፣ “ታኮሪኛላሽ” ማለት ይተናነቀናል። ተሳክቶልን ከተናገርንም ከልብ ሳይሆን በሽምደዳ የተጠኑ የሚመስሉ ቃላትን እናዘንባለን። ዐይኖቻችን የፍቅራችንን ስስት፣ ድምፃችንም በአድናቆት መዋጣችንን አያሳይም። “ትውደኛለህ?” ተብለን ከተጠየቅንም፣ “ስንቴ ልንገርሽ?” ማለት ይዳዳናል። ጥያቄው መዘግየታችንን እንደማመልከቱ፣ “በቃህ ምሬሃለሁ!” መባል በተገባን ነበር! 

ፍቅርን የምንገልጽበት መንገድ ፈጠራን ያካተተ ቢሆን ይጠቅማል። የተፈቃሪያችንን ዐይን ከኋላ ሆኖ በመያዝ ወደ ጆሮ ተጠግቶ በለሆሳስ መናገርን የሚከለክል ሕግ አልሰማሁም፤ ከሩቅ ሆኖ መጣቀስን ሆነ በከናፍርታችን “እምጷ…” ማለትም ክልከላ አልወጣለትም። ከናፍርታችንን ያለ ድምፅ በማንቀሳቀስ “እወድሻለሁ” ማለት መፍነክነክን ይጨምራል።

አንድ ዐይነት ቃል ለሕይወት ዘመናችን ያከራዩን ይመስል፣ “እወድሃለሁ” ብቻ ላይ ከመፈናጠጥ ብንጠበብስ? “ለ’ኔ እኮ አንቺ …”፣ “ለ’ኔ ከምንም ትበልጪብኛለሽ”፣ “አንቺን ማግኘቴ በሕይወቴ ብዙ ደስታን ፈጥሮልኛል” እንዲሁም ውስጣዊ ውበትንም ማድነቅ ይቻላል። እነዚህ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ ቃላቱን መጠቀም ከመንፈሳዊነት መጉደል አይደለም። (ምሳ. 31፥30፤ 1ጴጥ. 3፥3-5)። 

ከእንቅልፍ ስትነቃ ዐይኗ የሚያርፍበትን ቦታ አጥንተን፣ “እወድሃሻለሁ” የሚል የፍቅር ጽሑፍ ብንተው፣ በሞባይል ወይም በኢ-ሜይል ጣፋጭ የፍቅር ቃላትን ብንከትብ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበልናት ስጦታ መሆኗን የሚያመለክት ድምፅን ቀድተን ቤታችን ብንተው የሚፈጠረውን ደስታ ቃላት አይገልጸውም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የምናደርገውን ነገር በሙሉ በእውነተኝነት ማድረግ እንደሚያስፈልገን መረሳት የለበትም። ‘እኔ እያለሁ ተፈቃሪዬ አዎንታዊ የፍቅር ቃላትን በየትኛውም ቀን አትራብም’ በሚል ለራሳችን ቃል ልንገባ ያስፈልገናል።

አካላዊ ንክኪ

አንዳንድ ተፈቃሪያን ደግሞ ለቃላት እምብዛም ስፍራ የላቸውም። የፍቅር ቋንቋቸው፣ ከቃላት ይልቅ አካላዊ ንክኪ ይሆናል።እነኚህ ተፈቃሪያን፣ ሌሊቱን አምጠን ከወለድነውን የፍቅር ስንኝ ይልቅ ተጠግተን እንድናቅፋቸው ይመርጣሉ። በአካላዊ ንክኪ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችም ሌላውን ሰው መንካት በባሕርይ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖን እንደሚያሳርፍ፣ ዕይታን በሚፈለገው አቅጣጫ ለመቅረጽ ሚና እንዳለው፣ ከቃላት ባሻገር የሚደረጉ ተግባቦቶችን እንደሚያቀል፣ ጥልቅ ትሥሥርን እንደሚፈጥር ያመላክታሉ።� ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋው ወራት ለምጽ ያለበትን፣ ታማሚውን እንዲሁም ቅድስና የጎደላቸው የተባሉትን ፍቅሩን ለማሳየት በእጆቹ ዳስሷቸዋል (ማቴ. 8፥3፣ 15፤ 9፥29፤ 17፥7፤ 20፥34)። 

እነኚህ ተፈቃሪያን ልባቸው የሚረሰርሰው ስንጠጋጋቸው ነው። መታቀፍ፣ መሳም፣ እጃቸውን ማፍተልተል፣ ትከሻቸውንም ማሳጅ መደረግ ይፈልጋሉ። ምርጫቸው ይህ ሲሆን ተጠግተን ልናቅፋቸው፣ ትከሻቸውን ጨበጥ ጨበጥ ልናደርግ፣ እጃቸውን ልናፍተለትል እንዲሁም ልንላፋቸውም ጭምር እንችላለን (ዘፍ. 26፥8)።

ልብ ብሎ ለተመለከተ፣ ተፈቃሪያችን የፍቅር መግለጫዋ አካላዊ ንክኪ እንደ ሆነ ለማወቅ የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉን። ወንበር ስንለይ ወንበሯን ካስጠጋች፣ እጆቿ ወገባችንን የሙጥኝ ካለ፣ ስንላቀቅ እጃችንን ከፈለገች፣ እግሯን በእግሮቻችን ማቆላለፍ ከወደደች፣ ስንገናኝ ጉንጫችንን/ከናፍርታችንን ከመረጠች፣ ጥምጥም ማለት የምትወድ ከሆነ፣ አካላዊ ንክኪ የፍቅር መግለጫ ምርጫዋ የመሆን ዕድሉ ይሰፋል።

እንዲህ ዐይነት ተፈቃሪ፣ እጃችን ውስጥ የሻጠችውን ክንዷን ቀስ ብለን የምናስለቅቀው ከሆነ፣ በተደገፈችን ቁጥር፣ “ራስሽን ችለሽ አትቀመጪም?” ካልናት፣ መፈቀሯን ብትጠይቅ አይፈረድባትም። ይህ ሲባል ፍቅር ሲገለጥ ተቀባይነት ባለው ቦታ መደረጉን የማረጋገጥ ኀላፊነትም እንዳለብን አንዘንጋ። ሌሎች ባሉበት የሚደረግ የፍቅር ገለጣ፣ ተፈቃሪ የዕፍረት ስሜት እንዲሰማው አለማድረጉን ማረጋገጥ ያስመሰግነናል። የዚህ መልእክት ፍቅር ማኅበራዊ ጨዋነት ያስፈልገዋል ለማለት ነው እንጂ በአደባባይ ስፍራ አይኑረው የሚል ሙግት አይደለም።

የበጎነት አገልግሎት 

አንዳንድ አፍቃሪያን ደግሞ ፍቅርን የሚገልጡበት መንገድ ለሌላው ሰው በጎነት በማሳየት በማገልገል ይሆናል (1ጴጥ. 3፥6)።ስለዚህም እንዳገለገሉ ወይም እንደተገለገሉ ሲሰማቸው ፍቅርን እንደ ሰጡ ወይም እንደተቀበሉ ይቆጥራሉ። ለእነዚህ ተፈቃሪያን፣ የመፈቀራቸውም ሆነ የማፍቀራቸው ማረጋገጫቸው የሚቀበሉት በጎነትና ርኅራኄ እንደመሆኑ በሌላ ዐይነት የፍቅር ገለጣ ልባቸው ላይሸነፍ ይችላል። 

ለምሳሌ ያህል ፍቅርን በማገልገል የሚረዳ ባል አምሽታ እንደ ተኛች ያወቀ ቀን ቀድሞ ከእንቅልፍ በመንቃት ቁርስ ቢያዘጋጅ፣ ልጆችን ልብስ አለባብሶ ትምህርት ቤት የማድረስ ኀላፊነትን ቢወጣ አፍቃሪ የመሆኑ ማስረጃ ይሆናል። ምሽት ታክሲ ሲሳፈሩ፣ አመቺውን ወንበር ቀድሞ በመቆናጠጥ እንድትሸጎጥ ከመፈለግ ይልቅ ለእርሷ ቅድሚያ ቢሰጥ፤ ሸመታ ሲወጡ የተገዙትን ነገሮች ለመያዝ ቢፈቅድ ፍቅሩን ያመለክታል። እንዲህ ዐይነት አፍቃሪ በዚህ መልክ ያሳየውን ፍቅር ልብ ካላልነው የስብራት ምክንያት ልንሆን እንደምንችል ማወቅም ያስፈልጋል።

ከቢሮ ስትመለስ ውሎዋን መጠየቅ፣ ስሜቷን መካፈል፣ ግድ ስለሆነባት ወደ ቤት ይዛ የመጣችው ሥራ ካለ ከመጨቃጨቅ ይልቅ በፍጥነት መጨረስ እንድትችል ማገዝ ድካሟን ያለመልመዋል። ቤት ውስጥ የተበላሹ ነገሮች ካሉ ለመጠገን ወይም ለማስጠገን መሞከርም ፍቅርን ይበልጡኑ ያደረጃል። ምናልባትም ነገር ሲቆሽሸ እና ሲዘበራረቅ የማትወድ መሆኗን በመገንዘብ፣ ነገሮችን ማጸዳዳት፣ ልጆች ዝብርቅርቅ ያደረጓቸውን ዕቃዎች ጊዜ ወስዶጓ በፈርጅ በፈርጁ ማደራጀትም የሚፈጥረው አዎንታዊ ትሥሥርም የሚናቅ አይደለም። 

ስጦታ

አንዳንድ ተፈቃሪያን ደግሞ ፍቅርን የሚገልጡበት መንገድ ስጦታን በመቀባበል ይሆናል (ምሳ. 18፥16)። እኚህ አፍቃሪያን ማፍቀራቸውን የሚያሳብቅባቸው ለሚወዱት ሰው ስጦታ ለመስጠት መጠበባቸው ነው። ስጦታን በሚሰጡበት ጊዜም፣ የመነሻ ምክንያት ይፈልጋሉ። ስለዚህም ለቀናት ያላቸው ዋጋ ከፍተኛ ነው። የተያየንበት፣ የተዋወቅንበትን፣ የተጠያየቅንበትን የተጋባንበትን ወይም የቤተ ሰቡን አባል ልደቶች ሁሉ ታሳቢ ያደርጋሉ። በእነዚህ ቀናት፣ ሌላኛውን ለማስደነቅ ያስባሉ፤ ስጦታም ያቀርባሉ። ተፈቃሪ ፍቅርን በስጦታ የሚገልጥ ከሆነ፣ ስጦታ ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርብናል። የተሰጠንን ስጦታን በተለይም ስጦታው የፈለቀበትን ልብ ቸል ልንለው አያስፈልግም።

ስጦታ ስናበረክት ቁም ነገሩ ምን ያህል ውድ ነው በሚለው አይመሠረትም። አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ስጦታ ለጥፋት መካሻ ብቻ ልናደርገው አይገባም። የስጦታችን መልእክት መሆን ያለበት እንዳሰብናትና ፍላጎቷን ለማጥናት ጊዜ እንደሰጠን ነው። በሱፐር ማርኬት ፊት ለፊት ስናልፍ የምትወደውን ቸኮሌት ማንሳት ጣእሟን ማወቃችን ከማመልከቱ ባሻገር፣ በቀን ውሏችን ውስጥ እንዳሰብናት ይመሰክራል። በተፈቃሪ ልብ ውስጥ ከመኖር የበለጠ ምንስ ስጦታ አለ?

ስጦታ ስንሰጥ የምርጫችን መሠረት ምርጫዋ ቢሆን ይሻላል። አበባ ለምትወድ ተፈቃሪ ውድ ልብስ ከመግዛት፣ ከበር አበባ ቀንጥሶ መስጠት የተሻለ መፍነክነክ ይፈጥራል። ስጦታችንንም ነገ የሚደርቅ አበባ ወይም ሆድ የማይሞላ ቸኮሌት ከሚል ማጀቢያ ጋር ማቅረብም አያስፈልግም። ብዙ ወንዶች ከሚስቱት ነገሮች መካከል አንዱ ስጦታቸው የቤትን ጎዶሎ እንጂ የሷን ፍላጎት አለማሰቡ ነው። ስጦታችን እሷነቷን፣ ልዩነቷን እና ትሥሥራችንን ዋጋ እንደምንሰጠው ቢያመለክት ይመረጣል።

የአብሮነት ጊዜ

አንዳንድ ተፈቃሪያን በአብሮነት ነገሮችን መከወን ደስ ያሰኛቸዋል። በአብሮነታቸውም የቀን ውሎን መተረክ እንዲሁም የሌላኛውን መስማት ይሻሉ። መስማት የተባለውን መድገም መቻል አይደለም፤ ልብንና አካልን አቀናጅቶ ባልተከፋፈለ የልብ ጉጉነት የተናጋሪን ጉዳይና ስሜት ቀዳሚ ማድረግ እንጂ! እንደ አማራጭ መንገዶች ፊልም በጋራ መመልከት፣ ቲያትር ቤት መግባት፣ ቤት ማጽዳት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ ማኅበራዊ ክንውኖች ላይ መሳተፍ ይቻላል። 

ተፈቃሪያችን የፍቅር መረዳቷ የአብሮነት ጊዜያት ሲሆኑ፣ እንደምንም ተጣበን በጋራ ነገሮችን ለመከወን ራሳችንን ማስገኘት ይኖርብናል። በተለይ በተለያየ ሥራ መስክ ተጠምደን የምንውል ከሆነ፣ አሰልሰው የሚመጡ የዕረፍት ቀናትን እና በዓላትን አስቀድመን ለአብሮነት ማቀድ ይኖርብናል። ከሥራ መልስ በቀስታ የእግር ጉዞ ልናደርግ፣ አንዳንድ ቀን ወጣ እያሉ መመገብም ይቻላል።


መደምደሚያ 

ፍቅር የሚገልጥበት መንገድ ለየቅል ነው።የተፈቃሪን የፍቅርን አገላለጥ መገንዘብም እንዲሰማልን የፈለግነው ፍቅራችን ጆሮ እንዲያገኝ ይረዳዋል። የተነጋገርናቸው አማራጭ የፍቅር መግለጫ መንገዶች ግን የማይመጋገቡና ንጥል አይደሉም። ምርጫቸው ይለያይ እንጂ፣ ተፈቃሪዎች የፍቅር ቃላትን ሹክ ብንላቸው፣ አካላዊ ንክኪን ብንጠቀም ፣ በበጎነት ብናገለግላቸው፣ አብሮነታችን ቢጨምር፣ ስጦታን ብናበረክት ደስ ይሰኛሉ። ፍቅራችን መግለጥ እንድንችል ፍቅሩ እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን!

ማጣቀሻ

  1. Marie-Joelle Estrada, “Communication in Intimate Relationships: The Romantic Construal Model,” in The psychology of love, ed. Michele Antoinette Paludi (California: Praeger, 2012).107-132
  2. Gary D Chapman, The heart of the ve love (Chicago : North eld Publishing, 2007)
  3. Elliot Greene & Barbara Goodrich-Dunn, The psychology of the body, (Philadelphia: Lippincott Williams & Wilkins, 2012)

Share this article:

ነውር የሌለው አምልኮ

በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን ከሚያዚያ 2–3፣2006 ዓ.ም.“ጉባኤ ስለ ወላጅ አጥ ልጆች በኢትዮጵያ፡- ሀገራዊ ጥሪ ለሀገራዊ መፍትሔ” በሚል መሪ ቃል ጉባኤ ተካሄዶ ነበር። ጉባኤውን ያዘጋጁት “ቤታኒ ክርስቲያን ሰርቪስስ”፣ “ሜክ ዩር ማርክ”፣ “ቅድሚያ ፋውንዴሽን”፣ “የልጆች ዕድገት ሥልጠናና ምርምር ማዕከል” እንዲሁም “አባት ለሌላቸው ብሩኅ ተስፋ” ሲሆኑ፣ ድርጅቶቹም በልጆች አገልግሎት ዙሪያ የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው። በዝግጅቱ ላይ 470 የሚደርሱ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ ቤተ ሰቦች እና ለልጆች ልዩ ሸክም ያላቸው ወገኖች እንደታደሙ ከአዘጋጆቹ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.