
ሐሰተኞቹ የት ነው ያሉት?
መጋቢ በድሉ ይርጋ (ዶ/ር)፣ ‘የሐሰተኛ ነቢያት እና መምህራን አድራሻ የት ነው?’ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ ምላሹንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልገው ያቀርባሉ፤ የሐሰተኞቹ መገኛ ምካቴውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም ያመለክታሉ።
[the_ad_group id=”107″]
የስሜትና የሐሳብ ቁርኝት የፍቅር አካላት ሆነው ይነሣሉ። ያልተነጣጠለ አብሮነታቸውም አንደኛው ከሌለ የሌላው ሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጋል። ለነገሩ፣ ፍቅርን ከተያያዥ ስሜትና ሐሳብ አፋቶ ትርጉም ባለው መልኩ ማሰብስ ማን ይችላል? ተፈቃሪን በምናብ አጣምሮ ራስን ማብገንን ሆነ የመጨረሻዋ ተጠባቂ ሰከንድ አምልጣን ዘላለምን የተቀላቀለች ይመስል በቁንጥንጥ “ውዳችንን” መጠበቃችን በምንስ ይብራራል? በእርግጥም ከፍቅር ጋር ተያይዞ የምናሳየው መሰጠት፣ ሐዘኔታ፣ ቅናት፣ መረበሽ ከስሜትና ከሐሳብ ትሥሥር ጋር ይዛመዳሉ። የስሜቶቻችን እና የሐሳቦቻችን ቁርኝት ከሌሎች ተደምሮ ባዕድነትን ገፎ ተፈቃሪያችን በአንድት የሚገምድ ምስጢር ነው (ዘፍ. 2፥23-24)። የቁርኝታችንም ዐይነት ውስጣዊ ቅኝት በመሆን ትውስታን፣ አመለካከትን እና የድርጊት ጥበቃን ይገራል።1 በዚህች መጣጥፍ የቁርኝትን ትርጉም፣ ዐይነቶቹ እንዲሁም አደጋቸው ይወሳል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፣ በልጅነት ከቤተ ሰብ ጋር የነበረን ትሥሥርና እና የኋላ ገጠመኞቻችን በድምር በአእምሮ መዛግብት በደማቁ ተጽፈው ስለሌሎችም ሆነ ስለ እኛ የምናስበውን ይወስናሉ። እነዚህ ውስጣዊ ቅኝቶችም የትርጉም ስሌት በመሆን ስሜታችንን የምናስተናግድበትን መንገድ፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን፣ ስለራሳችን ያለንን ትውስታ እንዲሁም አሰላስሎና ግንዛቤያችን ላይ ሥነ ልቦናዊ ተጽእኖን ያሳድራሉ። የሥነ ልቦና ባለሙያዎቹ በከፍተኛ ደረጃ የተያያዙ ትሥሥሮችን ለመግለጽ ሁለት ጉዳዮችን እንደ ዋና ምሰሶ በመጠቀም አራት ቦታ ከፍለዋቸዋል። አንደኛው፣ ስለራሳችን ያለንን ምልከታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ተፈቃሪን አስመልክቶ ያለን ግምገማ ነው።2 ስለራስ ያለን ምልከታ አዎንታዊ በሆነ ቁጥር ለራስ ያለን ግምት ጤናማና ውስጣዊ ውጥረቱ አናሳ ይሆናል። እንዲሁም ሌሎች ያለ ምልከታም በጎ በሆነ ቁጥር በተፈቃሪ ላይ ያለን መተማመንና ድጋፍ ይጠነክራል። ስለሌሎች ያለን ግምገማ አዎንታዊ የሚያሰኘው ተጓዳኛችን ʻስንፈልገው ይገኛልʼ እንዲሁም ʻፍላጎታችንን ትኩረት በመስጠት ያሟላልʼ ብለን ስንተማመን ሲሆን፣ አሉታዊ የሚሆነው ሌሎች አይቀበሉንም ወይም ይተውናል የሚለው ውጥረት ውስጣችን የሚሰማ ጩኸት ሲሆን ነው።
ተማማኞች ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን በበጎ ዐይን ይመለከታሉ። ባላቸው ትሥሥር መታመን የተሞሉ፣ ጓደኛ መሆን የሚችሉ እንዲሁም ደግሞ አዎንታዊ ስሜት የሚያንጸባርቁ ናቸው። ጾታዊ ፍቅር እንዳለ ያምናሉ፣ ፍቅር ሳይቀዘቅዝ ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል ያስባሉ እንዲሁም ደግሞ ስለ ፍቅር የሚወድቁለት የተገባ ሰው በምድር ላይ እንደተፈጠረም ይቆጥራሉ። ከዚህ እምነታቸው የተነሣም ፍቅርን ለመቀበልም ሆነ ለመስጠት ውስጣዊ ዝግጅት አላቸው። በስሜት ወደ ሌላው መጠጋት እንዲሁም ደግሞ በልዕልና በራሳቸውም መቆም ይችላሉ። በልጅነታቸውም ከቤተ ሰቦቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸው ናቸው። ወላጆቻቸው ፍላጎቶቻቸውን በማጤን ተገቢውን ምላሽ የሰጡ፣ በአብሮነት የተገኙ፣ ከልጆቻቸው ጋር የሚናበቡ፣ በሚያደርጉት ነገር ወጥ እንጂ ተቃራኒ መልእክቶችን የማያስተላልፉ ናቸው። አፍቃሪ ሲሆኑም ተደላድሎ በትሥሥር ለመደገፍ አይረበሹም፤ ፍቅር ውጥረት አይጨምርባቸውም፤ ራስን መስጠትም የማይወጡት ዳገት አይደለም። ቅርርብን በስጋት አይገፉም፤ እንደውም ስሜት የተሞላ ፍቅር ያማልላቸዋል። ʻእተዋለሁʼ (“ተ” ጠብቆ ይነበብ) በሚል ስጋት ስለማይሸበሩ ፍቅር ለመቀበልም ሆነ ለመስጠት አይሰጉም። ስለዚህም ውስጣዊ ውጥረቱ አናሳ የሆነና ሽሽትን ቀዳሚ ምርጫቸው የማያደርጉ አፍቃሪያንን ይሆናሉ።
ስሜታቸውንም ያጋራሉ፤ ትሥሥራቸውም ጠንካራ፣ ረጅም ርቀት የሚጓዝ፣ እርካታን የተሞላ፣ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ንግግርን በኩርፊያ የማያቆም ይሆናል። የፍቅር ሕይወት በተቃና ሜዳ ላይ የሚሮጡት ሶምሶማ ሩጫ አይደለምና መንገዳቸው ሁሌ አይቀናም። ፍቅር በሚል ያሰቡት ጎዳና ባልተሳካ ጊዜ ግን በንጽጽሮሽ በቀላሉ ማገገም ይችላሉ። ያልተሳኩ የፍቅር ትሥሥሮቻቸውን አስመልክቶ ሲናገሩም ራሳቸውንም ሆነ ሌላውን አንሥተው ከመጠን ባለፈ መልኩ አያብጠለጥሉም፤ መጠጥንም ሆነ አደንዛዥ ዕጾችን ለመጽናኛነት አይፈልጉም። የእነዚህ ሰዎች ለጭንቀትና ከጤንነት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የመጋለጥ ዕድላቸው አናሳነት ከውጥረት መዳናቸው፣ ለዕጽ ያላቸው ተጋላጭነት መቀነስ፣ ለሥነ አምሮዋዊ ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው አነስተኛ እምብዛም ላያስገርም ይችላል፤ ከሞላ ጎደል አካሄዳቸው አዎንታዊ ስለሆነ። ሌሎቹ የቁርኝት ዐይነቶችም ራሳቸውን ወደዚህኛው የቁርኝት ዐይነት ለማሳደግ ሊተጉ ያስፈልጋቸዋል።
ሁለተኛው የቁርኝት ዐይነት ድብልቅልቅ በሚል ሊገለጽ ይችላል። ለዚህ ባሕርይ መነሾው በልጅነት የተቀበሉት ፍቅር እና እንክብካቤ ወጥ መርሕን የማይከተልና ለልጆች ፍላጎት ተገቢውን ምላሽ በቅጡ ካለማግኘት የመጣ መሆኑ ይነገራል። ከጨቅላነታቸው ላልተቀበሉት ፍቅርና እንክብካቤ ራሳቸውን እንደ ጥፋተኛ አድርገው መቁጠር ይጀምራሉ። አፍቃሪ በሚሆኑበት ጊዜም ከተፈቃሪያቸው የሚሹት ቅርርብና ድጋፍ ከፍተኛ ነው። አፍቃሪያቸው ጋር መዋሓድንና መጣበቅን የሚፈልጉ በአንጻሩ ደግሞ አፍቃሪያቸው የሚተዋቸው መስሎዋቸው የሚጨነቁ ናቸው። ለቀረበላቸው የፍቅር ጥያቄ ምንም ዐይነት ምርጫ ሳያደርጉ/ሳያመዛዝኑ በፍጥነት እጅ የሚሰጡበት አጋጣሚም ከፍተኛ ነው።
እነዚህ አፍቃሪያን ስለራሳቸው ያላቸው ሚዛን ዝቅተኛ ነው። የሚያፈቅሩትን ሰው ግን ያንቆለጳጵሱታል። ያለትሥሥር መኖር ይቸገራሉ እንዲሁም ደግሞ ስሜታቸው እጅጉን ይለዋወጣል። የሆነ ጊዜ ስሜታቸው ውጥር ይላል፤ ደግሞም ፍረሃት ይወራቸዋል፤ ብቸኝነትም ይሰማቸዋል። ከሚዋዥቀው ስሜታቸው የተነሣ ሌሎች ሊሸሹዋቸው ይችላሉ:፡የሚፈልጉት ነገር ላይ እጅግ ከማተኮራቸው የተነሣ ሌላኛው ሰው የተለየ ስሜትና ፍላጎት ሊኖረው እንደሚችልም ይዘነጋሉ።
ʻልተው እችላለውʼ የሚለው የፍርሃታቸው መነሾ ተፈቃሪያቸው ድካማቸውን በሂደት ይገነዘባል ከሚል ስጋት ነው። ከተፈቃሪም የሚጠብቁት ትሥሥር ከፍተኛ እንደመሆኑና ከጥበቃቸው የተነሣም የሚቀበሉት እንደማነሱ መጠን ተቃርኖውን ለማስታረቅ ይዘይዳሉ። ዘዴያቸውም ደግሞ አፍቃሪዎቻቸውን መክሰስ ይሆናል። ውስጣቸው እየተካሄደ ያለውንና ራሳቸው የፈጠሩትን ስጋት በመዘንጋትም አፍቃሪያቸውን ሊተማመኑበት የማይችል፣ የሚዋዥቅ እንዲሁም ለመሰጠት ያልተዘጋጀ በሚል ይከሱታል፤ ደግሞም ይጨቃጨቃሉ።
ያላቸውን ቅርርብ ለማጠንከር ስለሚፈልጉም፣ አፍቃሪያቸው በግሉ የሚተነፍሰው አየር ሁሉ የተነፈገ እስኪመስለው ድረስ ይጠጉታል። ይህ ጥረት አፍቃሪን ከመማረክ ይልቅ እስር ቤት የገባ ዐይነት ስሜትን በመፍጠር የነበረውን ክፍተት ይበልጥ እንዲሰፋ መንገድ ያመቻቻል። ከመጠን ባለፈ መልኩ እንካችሁ የሚሉት ምቾት፣ ድጋፍና እንክብካቤ ተፈቃሪን ይረብሻል። የቀረቡዋቸውም በሂደት ከእንክብካቤ ብዛት ይሸሹዋቸዋል። ከሚገባው በላይ መስጠታቸውም መነሾው ከሌላው ጋር ለመተሣሠር ካላቸው ፍላጎት የተነሣ እንጂ በእውነትም ለተፈቃሪያቸው ፍላጎት ከማሰባቸው አይደለም።
ሌላውን ማመን ይቸገራሉ፤ ስለዚህም በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል የሚጥሩና ቀናተኞች መሆናቸው አይቀርም። ውጤቱም ከተፈቃሪ ጋር በመደጋገም ግጭት እየፈጠሩ ይቆራረጣሉ፤ ደግሞም መልሰው ያድሱታል። ግጭት የፈጠሩ ጉዳዮች ለውይይት በሚቀርቡበት ጊዜም ስሜታዊ ይሆናሉ፤ ይናደዳሉ። የሚያረካ ትሥሥር መሠረቱ ደግሞ አንዱ የሌላው ነጻነት ሲደግፍና ለተለያዩ አስተሳሰቦች/አመለካከቶች እውቅና ሲሰጥ ነው። አፍቃሪያን ስለመጠጋጋት ያላቸው ዕይታ የሌላውን ሰው ልዕልና እስኪያጠፋ ድርስ ሊሆን እንደማይገባ ሊረዱ ያስፈልጋል። ስለቅርርብ ያላቸው መረዳትም ከእውነታው አንጻር ተሞርዶ ሊቃኝም ግድ ነው። ከእንዲህ ዐይነት ሰዎች ጋር የተጣመሩ ፍቅረኞች፣ ሰዎቹ ስለራስ ያላቸውን አመለካከት አዎንታዊ እንዲያደርጉ አብረዋቸው ሊሠሩና ድካማቸውን ሊገነዘቡ የግድ ይሆናል።
ከፍቅረኛቸው ጋር ነገር አልሆንም ብሎ ሲለያዩም ጉዳታቸው ከፍተኛ ነው። ነገረ ጉዳዩ ከተቋጨ በኋላ፣ እረፍትና ደስታ እምብዛም አይሰማቸውም። ገዝፎ የሚታየው ስሜታቸው ሓዘን፣ ፍረሃትና ንዴት ይሆናል። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በሚገርም ሁኔታ ላልተሳካው ነገር ራሳቸውን በአጥፊነት ይፈርጃሉ። ምን አጥፍቼ ነው የተለያየነው ሲሉ ይብሰለሰላሉ፤ ራሳቸውን ይሞግታሉ። በየጨዋታቸው መኻልም የቀደመ ፍቅራቸውን ለማዳን ምን እንዳጎደሉ አጥብቀው ይጠይቃሉ።
አንዳንዶች ራሳቸውን አስመልክቶ ያላቸው ዕይታ በጎ ሲሆን ለሌሎች ግን ስፍራ አይሰጡም። ስለራሳቸው ያላቸውን አዎንታዊ ዕይታ የሚጠብቁት ራሳቸውን ከቅርብ ግንኙነቶች በማሸሽ ነው። በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ እውነተኛ ፍቅር የመጻሕፍት ገጾች ውስጥ እንጂ ገሓዱ ዓለም ላይ እንደሌለ አስረግጠው ይናገራሉ። ለእነርሱ እውነተኛ ፍቅር ካለም አፍላነቱ እስኪያልፍ እንጂ የሚከስም መሆኑን ይተነብያሉ። ይህን መሰሉን ባሕርይ የሚያንጸባርቁ ሰዎች፣ ቤተ ሰቦቻቸው ለፍላጎታቸው ተገቢውን ምላሽ የማይሰጡ የነበሩ፣ ፍቅርና እንክብካቤን ያልተቀበሉ ናቸው።
መለያ ባሕርያቸው ስሜት አልባ መሆናቸው ነው፤ በተለይም አሉታዊ ስሜትን ይደብቃሉ። መቆጣትና መንገብገብን ፈጽሞውኑ ሊገልጹ አይፈልጉም። ከሚገባው በላይ በራሳቸው የሚደገፉ፣ ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩ፣ የቅርርብ ትሥሥርን አስፈላጊነት የሚያጣጥሉ እንዲሁም ደግሞ ሌሎች ሰዎች ባይቀበሉዋቸውም እምብዛም ግድ የሌላቸው ናቸው። ለሌላው ያላቸው አመለካከት አነስተኛ ከመሆኑ የተነሣ ለግጭት እምብዛም አይነሣሡም፤ በማኅበራዊ ጉዳዮችም ነገርን ተጭነው እንደ አቋም አይዙም። በአብሮነት ዘመንም ነገር ባይቀጥል በእነርሱ ሕይወት ምንም ነገር እንደማይለወጥ ስለሚናገሩ ተፈቃሪ ቤተኝነት አይሰማውም።
መሰጠታቸው አነስተኛ ሲሆን ሌላን ብዙም አያምኑም፤ ከትሥሥር የሚያገኙት እርካታም እንደዚሁ አናሳ ነው። ከማንም ጋር ያላቸው ትሥሥ እጅጉን ተጠጋግቶ እንዲቀራረብና ትሥሥር የሚፈጥረውን ሕመም እንዲሰማቸው ፈጽሞውን አይፈልጉም። አሉታዊ አመለካከቶችን ራሳቸው አስቀድሞ ለመከላከል በሚል ይገነባሉ። ለእነርሱ ተፈቃሪያን ልብን ሰጥተው ሊደገፉባቸው የማይገባ፣ ሲፈለጉ የማይገኙ ብሎም ደግሞ ከራሳቸው ባሻገር ለሌላው ሰው ደንታ ቢስ ተደርገው ይሳላሉ። አንድምታው የሚኖራቸው የግንኙነት ዐይነት ርቀትን የተሞላ፣ ውስጣዊና ልባዊ መሰጠቱ አናሳ ይሆናል።
ከእነዚህ ጋር የተጣመሩ አፍቃሪያንም ራሳቸውን ያሸሹ እንዲሁም ራሳቸውን ግልጽ ለማድረግ ያልወደዱ አድርገው ይወስዱዋቸዋል። በእርግጥም በቅርርብ ስሜታቸውና ልምምዶቻቸው ግልጽ ሆኖ ለሌላው ሰው ለማሳየት እንደመዘግየታቸው እንዲህ ዐይነቱ ስሜት መፈጠሩ አይደንቅም። ለአፍቃሪያቸውም የሚያሳዩት እንክብካቤና ድጋፍም ከዚህ በፊት ከተገለጹት የቁርኝት ዐይነቶች አንጻር እጅጉን አናሳ ነው። እኚህ አፍቃሪያን አመለካከቶቻቸውን ለማጽናት ከድርጊቶች ሁሉ ውስጥ ሰበብ መፈለጋቸው አይቀርምና ብዙ ትእግሥትን ይፈልጋሉ። በተጓዳኛቸው ላይ መተማመን ለመፍጠርም በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎችን በፍቅር ሕይወት ውስጥ ይጠብቃሉ/ይሻሉ።
ፊሪ አፍቃሪያን ስለራሳቸው ሆነ ስለሌሎች ያላቸው አመለካከት በጥቅሉ አሉታዊ ሲሆን ቅርበትን ይሸሻሉ። ራሳቸውን እርባና እንደሌላቸው፣ ሌሎችም ትተው ለመሄድ እያኮበከቡ እንዳሉ ያስባሉ። የማንንም በጎነት አያምኑም። የሌሎች በጎነትም አንዳች የተደበቀ ዓላማ እንዳነገበ አድርገው ያስባሉ። ሰዎች ያለ ምክንያት እያሸመቁባቸው እንደሆነና ጊዜው ሲመጣ እንደሚያሳድዳቸው ይሰማቸዋል። ያለ በቂ ምክንያት ይቀናሉ። በልጅነታቸው በአብዛኛው ግድ የለሽና በአጎሳቃይ ድባብ ውስጥ ያለፉ ናቸው።
ፍቅር ሲነሣ ምልከታቸው ጨለምተኛ በመሆኑ ከፍቅርና ቅርርብ ካላቸው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ይሸሻሉ፤ ስሜት የተሞላባቸውን መጋፈጦችን አይወዱም፤ ማኅበራዊ ካልሆኑና ሥራ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ጊዜያቸውን ማጥፋት ይመርጣሉ። አፍቃሪያቸው ራሱን አስመልክቶ ግልጥልጥ በማድረግ ሲነግራቸው ጥሩ ስሜት አይሰማቸውም። ውስጣቸው ያለውን ስሜት አውጥተው መናገር ይፈራሉ። የፍረሃታቸው መነሻ ʻግንኙነቴ እንክትክቱን ይወጣልʼ በሚል ስጋት ነው። የእነርሱንም ሆነ በሰዎች ውስጥ ያለውን ድካም ለመቆጣጠር የሚዘይዱት መንገድ ራሳቸውን ሳይሰጡ የሚደረግ አካላዊ የፍቅር ልውውጥን ይደሰቱበታል። በፍቅር ሕይወታቸው በአብዛኛው ስኬታማ አይደሉም።
በሚገርም ሁኔታ ደግሞ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ የሌሎች ሰዎችን ይሁንታ ይሻሉ። ይሁንታንም ከመጠን ባለፈ ከመፈለጋቸው የተነሣም ገና ለገና ʻባላገኘውስʼ በሚል ቅርርብን ይሸሻሉ። ለእነርሱ ግንኙነት የሚጀምረውም ሆነ የሚፈርሰው ሐሳባቸው ውስጥ እንጂ በተግባራዊ እርምጃ አይደለም። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ያሏቸውን ትሥሥሮች በማቋረጥ ይታወቃሉ። ባሉዋቸው ትሥሥሮች ውስጥም በትክክል መንቀሳቀስ ይከብዳቸዋል፤ መተማመን የተሞሉ አይደሉም። ፍቅረኛቸውንም አስመልክቶ መተማመን የሌላቸው፣ ስለሌላው የማይጠነቀቁና ሲፈለጉ የማይገኙ እንደሆኑ ይቆጥራሉ፤ በንዴትም ይታወቃሉ። ድብርት ያጠቃቸዋል፣ ውጥረትን በመደጋገም ያስተናግዳሉ፣ ድንገት ይቀየሩና በቁጣ ያንባርቃሉ፤ የእንቅልፍ ችግርም ይታይባቸዋል። ከምናብ ዓለማቸው ወደ ገሐዱ ዓለም ብቅ እንዲሉ በርካታ መበረታቻዎችን እና ድጋፎችን ይፈልጋሉ።
የልጅነት አስተዳደጋችን እና ያለፍንበት የሕይወት ዱካ ተጽእኖ የፍቅር ቁርኝታችን ላይ አሻራ እንደሚጥል በመገንዘብ በራሳችን ላይ ልንነቃ ያስፈልገናል። በአፍቃሪያን መካከል ያለው የስሜትና የሐሳብ ቁርኝት በጽኑዕና በተደላደለ መሠረት ላይ እንዲቆም ደግሞ በተግባቦት ክኅሎት መደረጅት፣ የዕለት ተʻለት ግንኙነቶች ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ መጣር እንዲሁም ደግሞ ግጭቶችን የመፍታት ችሎታን ማዳበር የግድ ይላል። እነዚህን ለመተግበር ግን የችግሩን ምንጭ ማወቅ ግድ ይላልናና ራሳችንን እንመርምር ብሎም ለማስተካከል እንጣር፤ ተፈቃሪችንንም እንረዳ። የፍቅር ገመዳችን አንድነት እንዲጠነክር በስሜትና በሐሳብ እንጎዳኝ፡፡ ፍቅር ለመጎዳት ያለንን ዕድል ከማስፋት ባሻገር መልካምነታችንንም እንደሚያበዛ አንዘንጋ። ይህን ማድረግ እንድንችልም እግዚአብሔር ጸጋውን ይስጠን!
Share this article:
መጋቢ በድሉ ይርጋ (ዶ/ር)፣ ‘የሐሰተኛ ነቢያት እና መምህራን አድራሻ የት ነው?’ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ ምላሹንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልገው ያቀርባሉ፤ የሐሰተኞቹ መገኛ ምካቴውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም ያመለክታሉ።
የትንሣኤን በዓል በምናከብርበት በዚህ ሰሞን፣ ስለ ጌታችን ትንሣኤ ምንነትና ፋይዳ ባትሴባ ሰይፉ የሚከተለውን አስነብባለች።
“ጥበቡ፡- የምድረ በዳው እረኛ” በሚል ለንባብ የበቃው መጽሐፍ በብዙ ቅጂዎች ተባዝቶ መነበብ ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። ባለፉት ዐሥራ አንድ ወራትም በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በመጽሐፉ ይዘትና ቅርጽ ላይ የተለያዩ ውይይቶች ተካሄደዋል። በዋናነት በአንድ ቤተ ሰብ ሕይወት ላይ የሚያጠነጥነው ይህ መጽሐፍ የብዙዎችን ስሜት መግዛት እንደቻለም ይነገራል። ሰላማዊት አድማሱ ከጸሐፊዋ ወ/ሮ ሊሻን አጎናፍር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment