[the_ad_group id=”107″]

ድንቅ እና ታምራት ለምን?

እግዚአብሔር አምላካችን ታምራትን የሚያደርግ አምላክ ነው። ኢዮብ፣ እግዚአብሔር “የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥ የማይቈጠረውንም ታምራት ያደርጋል። የሥርዓት አምላክ ነው” ሲል ተናግሯል (ኢዮብ 9፥10)። የዚህ ጽሑፍ ዐላማ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታምራት ለመዘርዘር አይደለም። ነገር ግን፣ ታምራቱን በመመርኮዝ እግዚአብሔር አምላክና የእርሱ አገልጋዮች ድንቅና ታምራት ያደረጉበትን ምክንያት በዐጭሩ ለመመርመር ነው። በሌላ አባባል፣ እግዚአብሔር አምላክ ራሱ በቀጥታ ወይም በመልእክተኛው በኵል ታምራት የሚያደርገው፣ ለሰው ልጆች በተለይም ለራሱ ሕዝብ ሊያሳይና ሊያስተላልፍ የሚፈልገው መልእክት ስላለው ነው። በዚህም ውስጥ ዘላለማዊ ዕቅዱን በዘመናት፣ ደግሞም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ፣ የእርሱን መልካም ዐሳብና ፈቃድ እንዲፈጸም ያደርጋል።

ጽሑፉ በብሉይ እና በአዲሱ ኪዳን ውስጥ የተፈጸሙትን ዋና ዋና ታምራትን በዐጭር በዐጭሩ ለመመርመር ይሞክራል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተደረጉት ታምራት በሦስት ዘመናት ሊመደቡ የሚችሉ ናቸው፦ አንደኛው ዘመን፣ ከሙሴ ዘመን በፊት የነበረ ነው። ሁለተኛው በሙሴ ዘመን የተደረገው ነው፤ ይህም፦ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ሲያወጣ፣ በምድረ በዳ ሲመራቸው፣ እንዲሁም ተስፋይቱን ምድር ሲያወርስ (በኢያሱ ዘመን) የተመዘገቡ ናቸው። ሦስተኛው፣ በነቢያቱ ዘመን የተፈጸመ ሲሆን፣ ነቢዩ ኤልያስ፣ ኤልሳዕና ዳንኤል ዘመን የተጸሙ ታምራት ናቸው።

የአዲስ ኪዳን ታምራትን እንዲሁ በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው፣ ከጌታችን መወለድ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ያለው ሲሆን፣ በተለይ በጌታችን የተደረጉት ታምራት ተጠቃሽ ናቸው። ሁለተኛው፣ ከጌታ ዕርገት በኋላ በሐዋርያቱ ዘመን የፈጸሙት ናቸው። ሦስተኛው፣ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከናወኑት ናቸው።

በዚህኛው ጽሑፌ፣ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከተከናወኑት ታምራት መካከል ቀዳሚ ሁለቱን እንመለታለን።

  1.  ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ ሙሴ

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ራሱን የገለጠው ፈጣሪ አምላክ፣ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” በሚለው ቃል (ዘፍጥረት 1፥1)፣ እጅግ በጣም አስደናቂ ታምራትን ማድረግን ጀምሯል (በተለምዶ መላእክት የተፈጠሩት ከዘፍጥረት 1፥1  በፊት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ከዚህ በፊት ታምራት እንደነበረም ያመለክታል)። ከዚያም፣ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረተ ዓለምን እና በውስጧም የሚኖሩትን፣ ሰማይን (ሰማያትን)፣ እንዲሁም ብርሃናትንም ጭምር ፈጥሮ፣ ለሁሉ ፍጥረታትም ሥርዐትን አበጅቶ፣ በስድስት ቀናት ውስጥ ሥራውን ጨረሰ። በእነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ግን፣ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” በማለት (ቊ. 26)፣ የፍጥረቱ ቁንጮ አደረገው። የሰው ልጅ የፍጥረት ገዥ ሆኖ ከመሾሙ ባሻገርም፣ የፈጣሪው መንፈስ በውስጡ በመቀመጡ ምክንያት ከእግዚአብሔር ባሕርያት ውስጥ ተካፋይ ሆነ። ይህም ብቻ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር የተለየ ግንኙነት ያለው፣ ከፍጥረታት በሙሉ ብቸኛው ፍጡርም ነው።

የሰው ልጅ የእግዚአብሔር በረከትና ጥቅምን ተካፋይ ብቻ ሳይሆን፣ በአምላኩ ዘንድ ተጠያቂ የሆነ ፍጡርም ነው። በአጠቃላይ ሲታይ፣ ሰው ላከናወነው መልካም ተግባር በፈጣሪው የሚመሰገን፣ ላጠፋው ጥፋት ደግሞ በአምላኩ የሚቀጣ ነው። በዚህም ምክንያት፣ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በስውር ጣልቃ እየገባ በረከቱን እና ፍርዱን ያደርጋል። የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያዎቹ ዐምስት ምዕራፎች፣ ሰዎች እንዳሻቸው በኀጢአት እንደተመላለሱ እናያለን። አራተኛው ምዕራፍ ላይ ቃየን ወንድሙ አቤልን ገደለ። እዚያው ምዕራፍ ውስጥ የቃየን ስድስተኛ ትውልድ የሆነው ላሜሕ ብላቴናውን ወግቶ መግደሉን በኩራት ይናገራል (ቊ. 23-24)። ቀጣይ በሆነው ምዕራፍ ስድስት ውስጥ ደግሞ፣ የእግዚአብሔር ልጆች የሰው ልጆችን በማግባት ኀጢአትን እያበዙ መጡ።

“የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ” ያየው እግዚአብሔር፣ “የፈጠርኩትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ አለ” (ዘፍጥረት 6፥5፡ 7)። ስለዚህም “የጥፋት ውኃ” ታምራትን በምድር ላይ አመጣ። ምን ሆነ? “በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ዕለት፣ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፤ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ” (ዘፍጥረት 7፥11-12)። ከዚህ ምን እንረዳለን? እግዚአብሔር አምላክ የጥፋት ውኃ ታምርን ያደረገው፣ የሰው ልጆች ኀጢአት ላይ ለመፍረድና ለመቅጣት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድን ነገር እናስታውስ። ይህም፣ ከኦሪት ዘፍጥረት ወደ ዮሐንስ ራእይ መጨረሻዎች ምዕራፍ ስንመጣ፣ ከኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ ፍርድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ፣ በተለምዶ “የነጩ ዙፋን ፍርድ” በተባለው የታሪክ መቋጫ፣ ታምራዊ የመጨረሻ ፍርድ ክስተት እንዳለ እንድናስተውል ነው (ራእይ 20፥11-15)።

ከኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ያደረጋቸው ድንቅና ታምራት በአብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ተጽፈው እናገኛለን። ይህም ሆኖ ግን፣ ብዙና ተከታታይ ታምራትና ድንቆች የተደረጉት በአራት ቦታዎች ወይም ዘመናት ውስጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፉልን፣ በዘመነ ሙሴ እና በነቢዩ ኤልያስ እንዲሁም እርሱን በተካው ነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን የተደረጉት ናቸው። ሁለቱ ዘመን ደግሞ አዲስ ኪዳን ውስጥ ሲሆኑ፣ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ድንቅ ተኣምር እስከ ሐዋርያት ዘመን ድረስ ያሉት ድንቅና ታምራት ናቸው። እግዚአብሔር እነዚህ ድንቆችና ታምራት ያደረገበትን ምክንያት፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው በዐጭሩ ቀጥለን ለማየት እንሞክር።

  •  ዘመነ ሙሴ

() እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ለማውጣት የተደረጉት ድንቆችና ታምራት

ከጥፋት ውኃ በኋላ የምናገኛቸው ድንቆችና ታምራት፣ እግዚአብሔር በሙሴና በአሮን በኵል በግብፅ ምድር ላይ ያደረጋቸው ናቸው (ዘፀአት ምዕራፍ 7-14)። እነዚህ ድንቆችና ታምራት ዐሥር ናቸው። ሆኖም፣ በፈርዖን ዙፋን ፊት የአሮን በትር ወደ እባብነት የተለወጠችበትን ተኣምር (ዘፀአት 7፥10) እና ሙሴ ባሕሩን ለሁለት የከፈለውን ድንቅ ተኣምር (14፥21) ከጨመርናቸው፣ ድንቆችና ታምራቱ ዐሥራ ሁለት ይሆናሉ። በጊዜ ቀመር ስናሰላው፣ ከኖህ ዘመን ከወደ አንድ ሺሕ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው (የጥፋት ውኃ ከዛሬ 4500 ዓመታት በፊት እንደ ነበረና፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር የወጡት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1446 እንደ ሆነ ይታመናል[1])። እንዲህም ሆኖ ታምራቱ ዐሥርም ይሁኑ ዐሥራ ሁለት፣ ድንቆችና ታምራቱ የተደረጉበት ምክንያት ነበራቸው።

ከኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ያደረጋቸው ድንቅና ታምራት በአብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ተጽፈው እናገኛለን። ይህም ሆኖ ግን፣ ብዙና ተከታታይ ታምራትና ድንቆች የተደረጉት በአራት ቦታዎች ወይም ዘመናት ውስጥ ነው።

ከምክንያቶቹ ውስጥ የመጀመሪያው፣ ለፈርዓንና ለግብፅ ሹማምንት የእግዚአብሔር አምላክን ብርቱ ክንድና ታላቅ ኀይሉን በማሳየት፣ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የጫኑትን ቀንበር በማንሣት፣ ከባርነት ነጻ እንዲያወጧቸው ለማስገደድ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ ግብፃውያን የእግዚአብሔርን ማንነት እንዲያውቁ ነው። “ግብፃውያንም፥ እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው ባወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆነሁ ያውቃሉ” (ዘፀአት 7፥5)። የታምራትና የድንቆቹ ታላቅነትና አስፈሪነቱን በማየትም፣ በተፈጥሮና በምድር ላይ ያሻውን የሚያደርግ ሉዓላዊ አምላክ መሆኑን እንዲያውቁ ነው። ሦስተኛው ምክንያት በግብፅ አማልክት ላይ ለመፍረድ ነው። “እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” (ዘፀአት 12፥12)።

የሥነ መለኮት ሊቃውንት በግብፅ ምድር የተደረጉት እያንዳንዱ ተኣምር በግብፅ የተለያዩ አማልክት ላይ የተደረጉ ፍርዶች ናቸው ይላሉ። ለምሳሌ ያህል፦ አዲሱ መደበኛ ትርጕም ማብራሪያ ጥቂት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። (ወደ ደም የተቀየረው የአባይ ወንዝ “ሓጲ” በሚል ይመለክ ነበር። እንቊራሪት [ጓጒንቸር] “ሐቄት” የተባለች እንስት የምትመለክበት ሲሆን፣ ሴቶች ልጆች በሚወልዱበት ጊዜ ትረዳቸዋለች ብለው ያምናሉ። ግብፃውያን በርካታ እንስሳትን ያመልኩ ነበር። በወይፈን የሚመሰለው “አጲስ”፣ በላም የምትመሰለው “ሐቶር” እና በበግ የሚመሰለው “አኑም”። … የድቅድቅ ጨለማው ተኣምር፣ በግብፃውያን ዘንድ ታላቅ አምላክ ተደርጎ የሚቈጠረው የፀሓይ አምላክ “ሬን”ን ክፉኛ የሚያዋርድ ነው።”)[2]

አራተኛው ምክንያት የኪዳን ሕዝብ ከሆነኑት የእስራኤል ሕዝቦች ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም ከብዙ ዓመታት የግብፅ ባርነት ቀንበር ነጻ እንዲወጡ ነው። የአባቶቻቸው አምላክ የሆነውን እግዚአብሔር የማዳን እጁን እና የትድግና ኀይሉን እንዲያውቁ ሆኖ፣ ከዚህም በተያያዘ ድንቅና ታምራቱን ለቀጣይ ትውልድ እንዲነግሩም ነው። “እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በግብፃውያን ያደረግሁትን ነገር ያደረግሁባቸውንም ተኣምራቴን በልጅህ፣ በልጅ ልጅህም ጆሮች ትነግር ዘንድ፥ ይህችንም ተኣምራቴን በመካከላቸው አደረግ ዘንድ የእርሱን የባሪያዎቹንም ልብ አደንድኜአለሁና ወደ ፈርዖን ግባ አለው” (ዘፀአት 10፥1-2)።

በመጨረሻም፣ የእግዚአብሔር ኀያል ስም በመላው ዓለምና በሰው ልጆች ሁሉ ዘንድ እንዲታወቅም ነው። እግዚአብሔር፣ “አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ ነገር ግን ኀይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ” (ዘፀአት 9፥15-16፤ አጽንኦት የተጨመረ) ብሎ ለፈርዖን የተናገረውን ያስታውሷል።

ከእነዚህ ሌላ ሌሎች ቀጣይ ምክንያቶችን መጨመር ይቻላል። ነገር ግን፣ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ላይ ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ እጅግ አስደንጋጭና አስፈሪ ድንቅና ታምራትን ያደረገው በምክንያት እንደ ሆነ ለማሳየት ያህል የተጠቀሱት በቂ ናቸው። በድንቅና በታምራቱ የግብፅ ሰዎች ሲፈረድባቸው፣ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከድንጋጤና ከመቅሠፍቶቹ ተጠብቀውና ተከልለው ቀዳሚ ተጠቃሚዎች እንደ ነበሩ ግልጽ ነው። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር እየወጡ እያለም ባሕር ለሁለት ተከፍሎላቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲሻገሩ ተደርገዋል (ዘፀአት 14)። ከዚህ እጅግ አስገራሚና በጣም አስደናቂ ተኣምር ቢያንስ ሦስት ትምህርትን ማውጣት እንችላለን።

የመጀመሪያው፣ እስራኤላውያንን ያሳድዱ የነበሩት የግብፅ ሠራዊት ሁሉ ባሕሩ ውስጥ እንዲሰጥሙ በማድረግ እንደተፈረደባቸው ያሳያል። ከዚህም ጋር በተያያዘ፣ የባሕሩ ውኃ ወደ ቀድሞው ሁኔታ በመመለሱ ምክንያት፣ ግብፃውያን እንደገና ሊያሳድዷቸው አልቻሉም። በዚህም የግብፃውያን የባርያ ጌትነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደተዘጋ ያሳያል። ሁለተኛው፣ እስራኤላውያን እዚህ እስከ ደረሱበት ድረስ ካዩዋቸው ድንቅና ታምራት በተጨማሪ፣ የአምላካቸው እግዚአብሔርን ታላቅና አስፈሪ ክንድ በባሕሩ ለሁለት መከፈልና በደረቅ ምድር መሻገርን በዐይናቸው እንዲያዩ ነው። በዚህም፣ በእርሱ ላይ እንዲታመኑና እንዲፈሩት፣ የሚገባውንም ክብር እንዲሰጡት፣ ለቀጣይ ትውልድ እንዲነግሩም ጭምር ነው። ሦስተኛው፣ የግብፃውያን ጌትነት እንደተዘጋው ሁሉ፣ የእስራኤላውያንም ባርያነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደ ተዘጋ ራሳቸው እስራኤላውያን እንዲያውቁትም ነው። ወደ ፊት እንደሚያደርጉት ልባቸው ወደ ግብፅ ምድር ቢመኝም፣ የባሕሩ ተከፍሎ መዘጋት ወደ ኋላ መመለስ እንደማቻል ያሳያል።

() በምድረ በዳ የተደረጉት ታምራት

የሚያሳዝነው ግን፣ እነዚህን ድንቆችና ታምራት በፊታቸውና በዐይናቸው ሲደረግ ያዩት የኪዳን ሕዝቦች፣ ወደ የተስፋይቱ ምድር ለመግባት ለአርባ ዓመታት በምድረ በዳ መንከራተታቸው ነው። ይህም ሆኖ፣ በምድረ በዳ ሕይወታቸው ውስጥም ከነማጕረምረምና ካለማመናቸው ጋር ብዙ የጌታ አምላክን ታምራት ዐይተዋል።

የባሕሩ ውኃ ወደ ቀድሞው ሁኔታ በመመለሱ ምክንያት፣ ግብፃውያን እንደገና ሊያሳድዷቸው አልቻሉም። በዚህም የግብፃውያን የባርያ ጌትነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደተዘጋ ያሳያል።

ውኃ ጠማን ብለው ሲጮኹ፣ የተመረዘ ውኃ እንዲጣፍጥ በማድረግ (ዘፀአት 15፥23-26)፣ እንዲሁም ከአለት ውኃ እዲፈልቅላቸው ሆኗል (ዘፀአት 17፥6፤ ዘኊልቅ 20፥2-11)። በራብ ልንሞት ነው ብለው ሲያጐራጕሩ፣ “ከሰማይ እንጀራ” ዘንቦላቸዋል (ዘፀአት 16)።

ከእነዚህ በተረፈ ደግሞ፣ ምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር ሙሉ ጥበቃና ከለላ ውስጥ ነበሩ። ከምድረ በዳው ቊርና ሀሩር እንዲሁም ከአስፈሪ አውሬዎችና አደጋዎች ተጠብቀዋል። ቅያሪ ልብስና ጫማ አልነበራቸው፦ “አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራኋችሁ፤ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አላረጀም” በማለት እግዚአብሔር [በሙሴ] ምስክርነቱን ይሰጣል (ዘዳግም 29፥5)። ይህን ጥቅስ ፌስቡክ ላይ አስቀምጬው፣ አንዲት እኅት “በዕድሜያቸው ሲያድጉ [ልብሱ] አላጠራቸው፤ ጫማውም አልጠበባቸው” የሚል አስተያየትን አስቀምጣለች። እውነቷን ነው። ከግብፅ ሲወጡ የተወለደ ሕፃን ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በደጅ ሲሆኑ፣ አርባ ዓመቱ ይሆናል። ሕፃን እያለ የለበሰው ልብስ ከእርሱ አካል ጋር ዐብሮ ማደግ ይኖርበታል። የተጫሙት ጫማ በእግራቸው ላይ ያለማርጀቱ ተኣምር ብቻ ሳይሆን፣ በየጊዜው ከእግራቸው መጠን ጋር መለወጡም እጅግ የሚደንቅ ነው። ይህን ከእኛ አምላክ ከሆነው ጌታ እግዚአብሔር ውጪ ሊያደርግ የሚችል ማንም፣ ምንም ኀይል የለም! ሰውነታቸውን ይታጠቡም እንደ ነበር የተነገረ ነገር የለም። ስለዚህም፣ ከብዙ በሽታና ተላላፊ ወረርሺኞችም ተጠብቀው ነበር ማለት ነው።

ከእነዚህም በተጨማሪ፣ በመንገዳቸው አሕዛብ እንዳያጠቋቸው በእግዚአብሔር ፍርሀት ተጠብቀዋል። ልምድ ሳይኖራቸው በአምላካቸው ታምራዊ ዕርዳታ፣ አማሌቅን በጦርነት አሸንፈዋል (ዘፀአት 17፥8-16)። በዐላማ ላይ የተሰቀለውን የነሐስ እባብ በማየት ከሞት ተጠብቀዋል (ዘኊልቅ 12፥4-9)። የሞዓብ ንጉሥ የነበረው ባላቅ እስራኤልን እንዲረግምለት የተጠራው ሐሰተኛ ነቢይ በለዓም፣ በጌታ ትእዛዝ እንዳይረግማቸው ተከልክሎ እንዲመርቃቸው ተደርጓል (ዘኁልቅ 23-24)።

የተጫሙት ጫማ በእግራቸው ላይ ያለማርጀቱ ተኣምር ብቻ ሳይሆን፣ በየጊዜው ከእግራቸው መጠን ጋር መለወጡም እጅግ የሚደንቅ ነው።

() ተስፋይቱን ምድር ለመውረስ (በኢያሱ ዘመን)

ከሙሴ የመሪነት በትሩን የተረከበው ኢያሱም በዘመኑ ብዙ ታምራትን ዐይቷል። ከየዮርዳኖስ ወንዝ ከመቈም እስከ ተስፋይቱ ምድርን ኀይለኛና ታላላቅ አሕዛብን አሸንፎ በብዙ ድል መውረስ ድረስ! የኢያሪኮ ግንብ ማንም ሳይነካው በእስራኤላውያን መታዘዝ በጩኸታቸው ብቻ ማፍረሳቸውን እናስታውስ። እንዲሁም ኢያሱ፣ “በገባዖን ሸለቆ ፀሓይ ትቁም! በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ” በማለት ያዘዘውን ያስታውሷል። ምን ሆነ? ተፈጥሮ ታዘዘች፣ “ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሓይ ቈመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሓይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም” (ኢያሱ 10፥13)።

‘ፀሓይ አንድ ቦታ እንደ ቈመች፣ ምድርም በዙሪያዋ እንደምትዞር ይታወቃል። ታዲያ፣ ፀሓይ እንዴት ልትቈም ቻለች?’ የሚል የጥርጣሬ ጥያቄን ብዙዎች ያነሣሉ። ለዚህ ዐጭሩ መልስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ተራ ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ እንጂ፣ በሳይንሳዊ መግለጫ አይደለም። ጠዋት ላይ “ፀሓይ ወጣች” እንጂ፣ “መሬት ዞረች” አንልም። ምሽት ላይ “ፀሓይ ገባች” እንደምንለው ሁሉ፣ ኢያሱም ፀሓይን ቍሚ ብሎ አዘዛት።

ለምሳሌ ያህል፣ የኢያሱ መጽሐፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ፣ “ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በፀሓይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ፤ ትወርሷትማላችሁ” (ቊ. 15፤ አጽንኦት የተጨመረ) የሚል ቃልን እናገኛለን። “ፀሓይ ትቍም” የሚለው፣ በሌላ አባባል “ለመግባት ትዘግይ” ማለትም ነው። በኢያሱ ዕይታ የቈመችው ዐይኑን ከፍ አድርጎ የሚያያት ፀሓይ እንጂ፣ በላይዋ ላይ የቈመባት ግዙፏ ምድር አይደለችም። ምክንያቱም ፀሓይ የምትወጣውና የምትገባው ምድር በዙሪያዋ በመዞሯ ሳቢያ ነውና! ስለዚህ፣ ፀሓይ ቈመች የሚለው፣ ምድር መዞር መቈሟን የሚያሳይ ነው። አንዳንድ ምሁራን ምድር ሙሉ በሙሉ እንድትቈም ሳይሆን፣ ፍጥነቷ ተቀንሶ ሊሆን ይችላል ይላሉ። አያይዘውም፣ እግዚአብሔር የፀሓይን ብርሃን በሆነ “ኮስማዊ መስታዎት” (cosmic “mirror”) እንዲያልፍ አድርጎት ሊሆንም ይችላል ይላሉ[3]

በዚህ ሁሉ ውስጥ፣ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን በኵል ሊሠራና ሊፈጽም የፈለገው ጊዜያዊ፣ ዘላቂና ዘላለማዊ ዐሳብና ዕቅድ ነበረው። ለአባቶቻቸው ቃል ኪዳን በገባው መሠረት የተስፋይቱን ምድር እንዲወርሱ አድርጓቸዋል። በተለያዩ ሰዎች ሕይወትና ሁኔታዎች፣ እንዲሁም ምሳሌና ምልክቶች ውስጥም መሢሕን እንደሚልክ እየደጋገመ ተናግሯል፤ አሳይቷል። ከዚሁ ሕዝብም አንድያ ልጁ ሰው ሆኖ ከድንግል በታምር እንዲወለድ አድርጓል። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የኪዳን ሕዝብ ለሆኑት ሕዝብና ለዓለም ሁሉ መዳኛ መንገድ መሆኑን አሳይቷል። በመጨረሻም፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በታምራዊው ትንሣኤው ሞትን ድል አድርጎ ክርስቶስ ጌታና አዳኝ መሆኑን አስመስክሯል!

መደምደሚያ

ከብሉይ ኪዳን ድንቆችና ታምራት ምን ግንዛቤ መውሰድ እንችላለን? ድንቅና ታምራትን ለማድረግ ቦታን፣ ጊዜን እና ሰውን የሚመርጥና የሚወስን እግዚአብሔር ራሱ መሆኑ እናስተውላለን። ታምራት አድራጊውን ሰውም መራጩ እግዚአብሔር ራሱ ነው። እነዚህን ግንዛቤዎች ይበልጥ ለማጠናከር እስቲ ጥቂት ቃላትን እንጨምር።

የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ ልጆች የሆኑት እስራኤላውያን በግብፅ በባእድ ምድር ለአራት መቶ ዓመታት በባርነት እንደሚገዙ እግዚአብሔር ለአብርሃም አስቀድሞ ነግሮት ነበር። “[እግዚብሔር] አብራምንም አለው፦ ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በርግጥ ዕወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል” (ዘፍ. 15፥13)። ይህም ሆኖ፣ ከባርነት ራሱ እግዚአብሔር እንደሚያወጣቸውም ቀድሞ አስታውቆታል። “ደግሞም በባርነት በሚገዟቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ” (ቊ. 14)። ይህ እንዲህ እንዳለ ግን፣ “ባእድ ምድር” ግብፅ እንዲሆን፣ “አራት መቶ ዓመታት” የተባለውን ዘመን ማብቂያ ወቅትን፣ እንዲሁም ባርነቱ እንዲያልቅ የተደረገላቸውን ትውልድ የመረጠና የወሰነው እግዚአብሔር ራሱ ነው። አገሩ ግብፅ ሳይሆን ሌላ ምድር ለምን አልሆነም? በግብፅ ላይ የተፈጸመው ፍርድስ ለምን ከአንድ ትውልድ በፊት (ወይም ከአንድ ትውልድ በኋላ) አልሆነም?

ነቢዩ ኤርሚያስ ግን፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክልና በታማኝነቱ በመናገሩ ሲሰቃይና ማላገጫ ሲሆን የታምራት እጁን አልዘረጋም። ኤርሚያስ ውኃ ጉድጓድ ውስጥ ሲጣል ጎትቶ ያወጣው ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነበር። በዳንኤልና በጓደኞቹ መከራና ስቃይ ጣልቃ ገብቶ የታደጋቸው አምላክ፣ የነቢዩ ኤርሚያስን ጩኸትና ሰቆቃ እንዳልሰማ ሆኖ ምነው መልስ ሳይሰጥ ቀረ?

ሕዝቡን ከግብፅ መርቶ ለማውጣት ሙሴና አሮን ለምን ተመርጠው ወደ ፈርዖን ተላኩ? በቀጣይ ጽሑፍ የምንመለከተው ወደ ነገሥታትና ነቢያቱ ስንሻገርም፣ ድንቅና ታምራት የተደረጉባቸውን ቦታ፣ ጊዜና ሰውን የሚወስንና የሚመርጠው እግዚአብሔር ነበር። ሳሙኤል በእስራኤል ምድር ታላቅ ነቢይ ነበር። “እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ” (1 ሳሙኤል 3፥20)።

ይህም ሆኖ ግን፣ ሳሙኤል እንደ ነቢዩ ኤልያስና ኤልሳዕ ድንቅና ታምራት ማድረጉ አልተጻፈልንም። በቦታ፣ በጊዜና በሁኔታ የማይወሰነው አምላክ፣ የዳንኤል ጓደኞችን በባቢሎን ምድርና በናቡከደናፆር ፊት ከእሳት ታድጓቸዋል። ነቢዩ ዳንኤልንም በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ ጠብቆት በሕይወት እንዲወጣ አድርጓል (ዳንኤል 3 እና 6)። ነቢዩ ኤርሚያስ ግን፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክልና በታማኝነቱ በመናገሩ ሲሰቃይና ማላገጫ ሲሆን የታምራት እጁን አልዘረጋም። ኤርሚያስ ውኃ ጉድጓድ ውስጥ ሲጣል ጎትቶ ያወጣው ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነበር። በዳንኤልና በጓደኞቹ መከራና ስቃይ ጣልቃ ገብቶ የታደጋቸው አምላክ፣ የነቢዩ ኤርሚያስን ጩኸትና ሰቆቃ እንዳልሰማ ሆኖ ምነው መልስ ሳይሰጥ ቀረ?

አምላካችን ድንቆችና ታምራትን የሚደርግበት የራሱ ምክንያት አለው። ይህንም ለማድረግ ቦታን፣ ጊዜን እና ሰውን እንዲሁም ሊጠቀምበት የፈለገውን አገልጋይና ሁኔታን የሚመርጥና የሚወስነው እርሱ ራሱ ነው። ለመሆኑ ይህ ነገር ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በኋላ ባለው የአዲስ ኪዳን ዘመን ተለውጦ ይሆን? እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣይ ክፍል መልስን እንሻለን።


[1] HENRY H. HALLEY, “HALLEY’S BIBLE HANDBOOK” (Zondervan), 2000, 2007.

[2] መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (ኢንተርናሽናል መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር)፤ ገጽ 94-98።

[3] Norman L. Geisler and Thomas Howe, “The Book of Bible Difficulties” (Baker Books, 1992), p.141.

Share this article:

የኅብረቱ ውሳኔ በአዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ ሲታይ

በቅርቡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት “አጋር አባል” ሲል የተቀበላቸውን ቤተ እምነቶችና መሪዎቻቸውን መነሻ አድርጎ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል። ጉዳዩ እስከ አሁንም የተቋጨ አይመስልም። ይህንን ተከትሎ ኅብረቱ የወሰደው ውሳኔ ከሞላ ጎደል አዲስ ኪዳናዊ አመራርን የሚከተል ሆኖ አግኝቼዋለሁ የሚሉት የሥነ አመራር መምህር የሆኑት ልደቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.