[the_ad_group id=”107″]

አዙሪቱ ይገታ፤ ተልእኮው ይፈጸም!

ከዓመታት በፊት የሚስዮናውያንን ሥልጠና ለመካፈል ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ አቅንቼ ነበር። በዚያ በቅርብ ከማውቀው ሚስዮናዊ ጋር የተልእኮውን ጉዳይ አንሥተን የተላከበትን ሕዝብ በወንጌል በመድረስ ሂደት ስለሚገጥሙት ችግሮች እና ዕክሎች ተወያየን። በውይይታችን መኻል “የሚስዮናውያን ዕጥረት አለ አይደል?” ስል ጠየቅሁት። በዕልህ እና በቁጭት የተሞላ መልስ ጠብቄ ነበር። በጠበቅሁት የስሜት ግለት ግን አልመለሰልኝም፤ “ከምንጊዜም በላይ ብዙ ሚስዮናውያን ይህንን ሕዝብ ለመድረስ የተሰማሩብት ጊዜ ላይ እንገኛለን” አለኝ። ደነገጥሁ። ቀጠሎም “በርግጥ ለተልእኮ ሥራው ሁሌም ቢሆን ሠራተኞች ጥቂቶች ናቸው፤ ነገር ግን አሁንም ከገባንበት አዙሪት መውጣት አልቻልንም። ይህ ሕዝብ መደረስ አለበት!” አለኝ። ይህንን ሲናገር በሚስዮናዊው ፊት ላይ የድካም እና የተስፋ መቁረጥ የሚመስል ስሜት ይነበብበታል።

የገባንበት “አዙሪት”

የሚስዮናዊው ንግግር ያልጠበኩት ከመሆኑም በላይ “የገባንበት አዙሪት”ን ለማወቅ ደግሞ ሌላ ጉጉት ያዘኝ። ‘ምንድነው ሚስዮናውያኑ ገባንበት የሚሉት አዙሪት?’ የሚለው ጥያቄ አእምሮዬን ወጥሮኝ ዐደረ። ይሄ የተልእኮ አዙሪት ዶ/ር መረራ ጉዲና ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ደጋግመው ሲናገሩ እንደሚጠቅሱት “ቡዳ”፣ ክርስቲያናዊ ተልእኮ አቅጣጫን ያለ ዕድገት ያስቀረ መሆን አለበት ብዬም አሰብሁ።

ስለዚህም ይህንን የተልእኮ “አዙሪት” ምንነት ለመረዳት ሰፋ ያለ ጥናት ለማድረግ ከሚስዮናውያን፣ ከተልእኮ አስተማባሪዎች (“አስተማባሪ” የሚለው ቃል አስተማሪ፣ አስተባባሪ እና አሰማሪ የሚሉት ቃላት ጥምረት ሲሆን “Mobilizer” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ይሆናል በማለት የፈበረኩት አቶ ንጉሤ ቡልቻ ናቸው ይባላል) እንዲሁም በጊዜው ካገኘኋቸው ከአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር ስወያይ ከረምሁ። የገባንበትን የተልእኮ አዙሪት ለማስረዳት ሁሉም ተመሳሳይ ሐረግ ይጠቀማሉ፤ “ዐውድንና አውዳዊነትን አለመከተል”።

ይህ ሐረግ በደፈናው አይገባም። ዐውድን አለመከተል ምን ማለት ነው? የወንጌል ተልእኮንና ዐውዳዊነትን ምን አገናኛቸው? የሚሉ ጥያቄዎች መነሣታቸው አይቀርም። እነዚህን ጥያቄዎች በዐጭሩ ለማስቀረት ያህል “ዐውድ” ሲባል በሚስዮናውያኑ አጠቃቀም የአንድ ማኅበረ ሰብ የአኗኗር ዘይቤ እንደ ማለት ነው።

በኢትዮጵያ ገነት ቤተ ክርስቲያን የ10/40 አገልግሎት መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተክሉ ወልዴ “ዐውዳዊነት”ን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፦ “ዐውዳዊነት ወደየትም ሥፍራ ሄደን በሕዝቡ መኻል፣ ከሕዝቡ ጋር የምንኖርበት ተመሳሳይ የኑሮ ዘይቤ ነው። ዐውዳዊነት የሕዝቡን ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በተገቢው መንገድ በመረዳት ማክበር ነው። ዐውዳዊነት የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ከግምት ያስገባ ሥራ ነው። ዐውዳዊነት የራሳችን ማንነትና እምነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ የወንጌልን እውነት መረዳት በሚችሉበት በራሳቸው ማንነትና ሃይማኖት በኩል ማቅረብ ነው። ዐውዳዊነት የያዝነውን መልእክት በሕዝቡ ባህል ጠቅልለን (ሥጋ አልብሰን) ማቅረብ ነው። ዐውዳዊነት ‘መልእክቱን እንዴት ባቀርብ ደስ ይለኛል ወይም ይመቸኛል’ ሳይሆን፣ ‘መልእክቱን እንዴት ባቀርበው ይደመጣል’ ብሎ ያስባል።”

ወንጌል የአንድን ማኅበረ ሰብ ዐውድ በመጠቀም ለማኅበረ ሰቡ አባላት መድረስ አለበት። በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሕዝቦች የራሳቸው የሆነ ባህል አላቸው። ባህል ደግሞ በራሱ ክፉ አይደለም። በወንጌል የምንደርሰው ሕዝብ የራሱ ባህልና ወግ እንዳለው ሁሉ፣ ይህንን ሕዝብ ለማገልገል የሚላከው አገልጋይም እንዲሁ የራሱ የሆነ ባህልና ዐውድ ይኖረዋል።

ሰዎችን ሁሉ አንድ የሚያደርግ እውነት አለ፤ ይህም እውነት በሁለት የተለያዩ ባህሎች የሚኖሩ ሰዎች እንዲቀራረቡ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ባህል በጥቅሉ ኀጢአት አይደለም፤ ማንነት የሚገለጥበት ነው፤ በቀላሉም ልናስወግደውም የምንችለው አይደለም። ለዚህም ነው ነጮቹ “A text without its context is a pretext” (ዐውድን ያላገናዘበ ትርጉም ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ያደርሳል) የሚሉት። አንድን ማኅበረ ሰብ በወንጌል ለመድረስ የዚያን ማኅበረ ሰብ ዐውድ መገንዘብ ያስፈልጋል።

እንግዲህ አዙሪቱ ዐውዳዊነትን አለማወቅ እና አለመከተል፣ ማለትም ሚስዮናውያን እና አብያተ ክርስቲያናት በወንጌል የሚደርሷቸውን ሕዝቦች ባህል እና አኗኗር አለማወቅ እና አለመረዳት፣ እንዲሁም ባህሉን እንደ ወንጌል ዐውድ በመጠቀም ለመድረስ ጥረት አለማድረግ መሆኑ ነው። ሚስዮናዊው ወዳጄም ይህንን ክፍተት በራሱም፣ በሌሎች ሚስዮናውያን ላይም እንደተመለከተ አልደበቀኝም። እኔም በግሌ እንዳስተዋልሁትና እንዳጠናሁት ዐውድን ጠብቆ የወንጌልን መልእክት በማቅረብ ደረጃ ክፍተት አለብን።

የአዙሪቱ ጡዘት

በቅርቡ ወደ ጅግጅጋ ለተመሳሳይ ጉዳይ አቅንቼ የተመለከትሁትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። የሶማሌ ክልል ሕዝብ 99.7 በመቶ የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን፣ ከክልሉ ነዋሪዎች 0.3 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ክርስቲያን አልያም የሌላ እምነት ተከታዮች ናቸው።

እንደ ጅግጅጋ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብረ ዩሐንስ ከሆነ፣ በጅግጀጋ ብቻ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥር ዐሥር አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ። ጅግጅጋን አስቀድማ የረገጠችው የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በ SIM ሚስዮናውያን (በ1950ዎቹ) አማካይነት ስትሆን፣ ከእርሷ በመቀጠል የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ትከተላለች (በ1960ዎቹ)። ስለዚህ ወንጌል ወደ ሶማሌ ምድር ከረገጠ ከ60 ዓመት በላይ አስቆጥሯል። አሁን እንጠይቅ፤ በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል የሶማሌ ሕዝብ ወንጌሉን አምኖ ድኗል? ይህንን ጥያቄ መመለስ በስፍራው ለሚያገለግሉ ብዙዎች ልብን የሚሰብር እና ድካም ውስጥ የሚከትት ነው።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በዐሥሩ አብያተ ክርስቲያናት ሥር ካሉት አባላት የሶማሌ ብሔረ ሰብ ተወላጅ ሆነው ከእስልምና ወደ ክርስትና የመጡት ሰዎች ሦስት ወይም አራት ቢሆኑ ነው። ከእነርሱ ውጭ 99 በመቶ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናቱን የሞሉት ከመኻል፣ ከደቡብ እና ከሰሜን ኢትዮጵያ ለሥራ ጅግጅጋ መጥተው የቀሩ ክርስቲያኖች ናቸው። እንደ አቶ ተክሉ አገላለጽ፣ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት “ሶማሌ ላይ ያሉ የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት” ናቸው። ሶማሌ ክልል ውስጥ ይገኙ እንጂ የሶማሌ ግን አይደሉም። ሶማሌዎች አይገቡባቸውም፤ በሶማሊኛ አይዘመርም፤ በሶማሊኛ አይሰበክም። ይህ ደግሞ የአዙሪቱ ጡዘት ነው።

“የሶማሌን ሕዝብ ዐውድ ልንቀበል ስላልፈቀድን ሶማሌዎች ወደ እኛ አይመጡም” አለችኝ ስለዚህ ጉዳይ ያናገርኋት በድሬዳዋ የምታገለግል ሚስዮናዊት። ጥያቄዬን ቀጠልኩ፤ “በጅግጅጋ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥር ከሚያገለግሉ ወደ 50 ከሚጠጉ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች መካከል ስንቶቹ የሶማሊኛን ቋንቋ አቀላጥፈው በመናገር ለሶማሌዎች ወንጌልን ማድረስ ይችላሉ?” መልሱ “ሁለት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ብቻ!” የሚል ነበር።

እነዚህ አኀዞች በርግጥ በአከባቢው ያሉ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችንም የሚያስጨንቁ እንደ ሆኑ ተረድቻለሁ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስብሰባ እና ውይይት እንደተደረገም አውቃለሁ። ከሁሉም በላይ የጅግጅጋ አብያተ ክርስቲያናትን ለምሳሌ አነሣሁ እንጂ፣ እውነታው ግን ተዘዋውሬ እንዳየሁት ይህ በአብዛኛው በወንጌል ያልተደረሱ አከባቢዎችን ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የምንደርሰውን ማኅበረ ሰብ ባህል በማወቅ በዐውዳቸው ልንደርሳቸው ስላልቆረጥን የተላክንበት ማኅበረ ሰብ ዘንድ ውጤታማ የወንጌል ሥራ እየሠራን አይደለም።

አዙሪቱ በከተሞች   

ሚስዮናዊነት የከበረ ጥሪ ነው። ስለ ዐውዳዊነት ስናነሣ የሚስዮናውያንን ስሕተት ለማጉላት ሆኖ መታሰብ የለበትም። በእግዚአብሔር ጥሪ ወደ መከሩ ከተሰማሩት ሚስዮናውያን በላይ የዐውዳዊነት ጉዳይ የእያንዳንዱ የከተሜዎች አማኝ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ስሙ “ቦሌ ሚካኤል” በሚባለው አከባቢ እጅግ በጣም ብዙ ሶማሌያውያን (የክልል አምስት ሶማሌ ተወላጆች “ሶማሌዎች” ሲባሉ፣ ከውጭ በስደት መጥተው እዚህ የሚኖሩት ደግሞ “ሶማሌያውያን” ይባላሉ) ይኖራሉ። አሁን አሁን ደግሞ ብዙ ሶርያውያን በአከባቢው ይታያሉ። የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ዐውዳዊነትን የሚፈታተነው እውነት ታዲያ እነዚህ ሶማሌዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ብዙ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መገኘታቸው ነው። እነዚህን ማኅበረ ሰቦች በወንጌል ለመድረስ የግድ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ማወቅ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር መወዳጀት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ግን አሁንም ብዙ ሥራ ይቀረናል። በአከባቢው የሚገኝ አንድ የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን በቅርብ ትልቅ ሕንጻ እንደገነቡ አውቃለሁ። ይህ ሕንጻ ከአዙሪታችን የሚያወጣን አንድ መፍትሔ ይዞ ቢመጣ መልካም ነው፤ ካልሆነ ግን አልጠቀመንም።

አዲስ አበባ የብዙ ብሔር ብሔረ ሰቦች መኖሪያ መሆኗ፣ በፊት ሚስዮናውያን ሲላክባቸው የነበሩ ሕዝቦች አሁን ወደ አዲስ አበባ መጥተው ጎረቤታችን እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት በወንጌል ያልተደረሱት የውጭ ሶማሌያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ሱዳናውያን እንዲሁም ቻይኖችን ተጎራብተዋል። ይህ እንግዲህ የአዙሪቱ ጥሪ ነው። ዐውዳዊነት እዚህ ጋር ነው የሚፈተሸው። ባህላቸውን አክብረንና ቋንቋቸውን ተምረን፣ ተወዳጅተናቸው ወንጌልን እንነግራቸው ይሆን? ወይስ እኛ “አዲስ አበቤ” ሆነን እንቀር ይሆን?

እንደ አዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ወዘተ. ያሉ ከተሞቻችን በዐውዳዊነት ፈተናዎች ውስጥ ናቸው። የሐዋሳ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋሳ እንደ ቀደሙት ዘመን የ“ክርስቲያን ከተማ” ሆና እንደማትዘልቅ ይገነዘቡታል። የአዳማ አማኞች በወንጌል ያልተደረሱት ከረዩንና ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌዎችን ችላ ማለት እንደማይቻል ያውቁታል። ነዋሪዎች ከገጠር ወደ ከተማ የሚያደርጉት ፍልሰት እጅግ እየጨመረ ከመምጣቱ የተነሣ ከተሞች በወንጌል ባልተደረሱ ሕዝቦች እየተሞሉ ናቸው። ይህ ደግሞ የተልእኮው አዙሪት ወደ ከተሞችም እየመጣ እንደ ሆነ ጠቋሚ ነው።

አዙሪቱን መግታት  

በኢትዮጵያ ያልተደረሱ ሕዝቦች ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ሳሙኤል ክብረዓብ በቅርቡ፣ “peoplegroupsethiopia.net” የሚባል ድረ ገጽ ይፋ አድርገዋል። ድረ ገጹም በአገራችን በወንጌል ያተደረሱ ሕዝቦችን እንዲሁም በውስጣቸው የሚገኙ የአማኞች ብዛትን በዝርዝር ያስቀምጣል። ከመረጃው ማየት እንደሚቻለውም ወንጌል ያልገባባቸው እጅግ ብዙ ማኅበረ ሰቦች እንዳሉ ነው። ‘እግዚአብሔር ለእነዚህ ሕዝቦች ያለው ዕቅድ ምንድነው?’ ብለን የጠየቅን እንደ ሆነ የምናገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልስ፣ “ሁሉ እንዲድኑ እና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” የሚል ነው (1ኛ ጢሞ 2፥4) ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቢሆን በሰጠው እና በተለምዶ “ታላቁ ትእዛዝ” ብለን በምንጠራው ምንባብ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ…” (ማቴ 28፥19) ነው ያለው። የግሪኩን ትርጉም በቀጥታ ከተጠቀምን፣ “ሕዝቦች (ne hulu)” የሚለውን የአማርኛ ቃል፣ “ብሔር ብሔረ ሰቦችን ሁሉ” (Panta ta Ethne) በሚለው መተካት ይቻላል። ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ብሔር ብሔረ ሰቦች ሁሉ እንዲሄዱ ነበር ያዘዘው። ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን የሚለው ይህንኑ ነው፤ “ወደ ብሔር ብሔረ ሰቦች ሁሉ ሂዱ”።

ወደ ብሔረ ሰቦች በመሄድ ወንጌል ለመስበክ ስንነሣ ታዲያ ከላይ ካየነው የተልእኮ አዙሪት የሚገላግለን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን መገንዘብ አለብን። የዐውዳዊነት የመጨረሻው ትልቁ ምሳሌ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታ ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ሰው ከሴት መወለዱ የተላከለትን ሕዝብ ለመግባባት ጠቅሞታል። መልኣክ ሆኖ ቢወለድ ኖሮ ግንኙነቱ የሰው አይሆንም ነበር። የሕዝቡን ቋንቋ ይናገር ስለ ነበር መናገር የፈለገውን ይናገር፣ ማስተማር የፈለገውን ያስተምር ነበር። የሕዝቡን ባህል አክብሮ ኖሯል፤ ስለዚህም ከሰዎች ጋር በቀላሉ ይግባባ ነበር። ይህም ሰዎች ሊረዷቸው የሚችሏቸውን ምሳሌዎች በመናገር ከሕዝቡ ጋር በቀላሉ እንዲግባባ አድርጎት ነበር።

እንግዲህ የእምነታችን ጀማሪ እና ፍጹም አድረጊ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልክት ሩጫችንን በመሮጥ አዙሪቱን እንግታ። ብዙዎች በራሳቸው ባህል ብቻ ታጥረው ባሉበት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብር እና ለሰዎች መዳን ብለን ጌታችን ሰማይን እንዳቋረጠ እኛ ደግሞ ባህል አቋርጠን ያልተደረሱትን ጎረቤቶቻችንን በከተሞች እና በገጠሮች እንድረሳቸው።

Share this article:

የክርስቶስ ወንጌል እና ሳምራውያን

“እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሓደ፣ በዐዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፣ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስ ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልንም በመስቀል ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ. 2፥14-18)።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.