[the_ad_group id=”107″]

"ዘጠኙ ቅዱሳን" የተሰኘው ይህ የገናዬ ዕሸቱ ጽሑፍ፣ በወንጌልና ተልእኮ እንቅስቃሴ ላይ አተኩራ ከምታስነብባቸው ሥራዎቿ መካከል ሦስተኛው ነው።

ከክርስትና ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ ጋር ተያይዞ ባላቸው ግልህ ተጽዕኖ፣ “ዘጠኙ ቅዱሳን” (ዘጠኙ መነኰሳት) በሚል ስያሜያቸው የሚታወቁት መነኰሳት ግንባር ቀደም ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህን ካህናት ከነበራቸው ፀረ ኬልቄዶን ሥነ መለኮታዊ አቋም የተነሣ፣ ከሮማውያን የሚደርስባቸውን መከራ እና ስደት በመሸሽ በ480 ዓ.ም. (A.D.) ከባይዛንታይን ኢምፓየርና ከተለያዩ አገራት፣ ማለትም ከሶሪያ፣ ከቁስጥንጥንያ፣ ከአንጾኪያ እና ሮም ተሰድደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው። የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሡ አልዓሚዳ እና ሕዝቡ መልካም አቀባበል አድርገውላቸው እንደ ነበር ይነገራል። እነዚህም፦ አባ አሌፍ፣ አባ ጽሕማ፣ አባ አረጋዊ (ዘሚካኤል)፣ አባ አፍጲ፣ አባ ገሪማ (ይስሐቅ)፣ አባ ጴንጠልዮን፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ይምዓታ፣ አባ ጉባ ሲባሉ፣ በአክሱም እና በቀሩት የትግራይ አውራጃዎች ወንጌልን እየሰበኩ በብዙ ስፍራዎች ተንቀሳቅሰዋል።

ዘጠኙ ቅዱሳን አክሱም ከደረሱ በኋላ ግዕዝ ያጠኑ ሲሆን፣ ቀጥለውም መጽሐፍ ቅዱስን እና በአታንሲያስ የተጻፈ መጻሕፍትን ከግሪክ ወይም ሰፕቱዋጀንት እና ከአረማይክ ወደ ግዕዝ በመተርጐም ሕዝቡ በቋንቋው እንዲገለገል አድርገዋል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ እስከተተረጐመበት እስከ 17ተኛው ክፍለ ዘመን በግዕዝ እየተነበበ ቈይቷል። በሳባ ፊደላት ላይ ማናበቢያዎችን በመጨመርና የግሪክ ቍጥሮችን በማከል የግዕዝ ቋንቋ ንድፍ (orthography) ላይ ትልቅ መሻሻል አምጥተዋል።

የዘጠኙ ቅዱሳን የወንጌል ትምህርት ይዘት እና ሰዎችንም ወደ እምነት ለማምጣት የተጠቀሙት መንገድ በርግጠኝነት ባይታወቅም፣ ከአክሱም እና አዱሊስ በማለፍ፣ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሔድ ክርስትናን ከመስበክ ባለፈ ተባሕትዎ እና የመነኰሳት ሥርዐትን አስተዋውቀዋል። እያንዳንዳቸውም ራቅ ባሉ እና ለኑሮ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ገዳማት በማቋቋም ክርስትና በሰፊው እንዲስፋፋ አስተዋጽዖ አድረገዋል። ከእነዚህም መካከል አባ አፍጲ በየሃ፣ አባ አሌፍ በመረብ ወንዝ አካባቢ፣ አባ አረጋዊ በደብረ ዳሞ፣ አባ ሊቃኖስ እና አባ ጴንጠልዮን በአክሱም፣ አባ ገሪማ በአድዋ፣ አባ ይምዓታ በገረርታ ያቋቋሟቸውን ገዳማት መጥቀስ ይቻላል።

በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ ካደረጉት እስተዋጽዖ ባሻገር፣ የአምልኮ ሥርዓት ላይ መሻሻል አምጥተዋል። የዜማ አባት በመባል የሚታወቀው ቅዱስ ያሬድ፣ የአባ አረጋዊ ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ይነገራል። ያሬድ ኢትዮጵያን የራስዋ የዜማ ባለቤት ያደረገና መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን በመድረስ በፀናፅል፣ በከበሮ፣ በመቋሚያ፣ በሽብሸባና በጭብጨባ ዜማ የደረሰ ዕዝል፣ ግዕዝ፣ አራራይ በተባሉ የዜማ ዐይነቶች እግዚአብሔርን ያመሰገነ የዜማ አባት ነው። ዘጠኙ ቅዱሳን በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ቀደምት ዕድገት ባደረጉት አስተዋጽዖ ሲታወሱ ይኖራሉ።

ዋቢ መጻሕፍት

  • Fekadu Girma, Evangelical Faith Movement in Ethiopia; Origions and Establisment of the Ethiopian evalgelical Church, Mekane Yesus p. 1 7- 18
  • የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥት ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፤ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ በ1920ዎቹ ዓመታት ተጻፈ፤ በወይዘሮ ሠናይት ተክለማርያም። ሴንትራል ፕሪንተርስ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፤ ገጽ 21
  • ባሕሩ ዘውዴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 1983 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፤ 2000 ዓ.ም፤ ገጽ 23- 24

Genaye Eshetu

Genaye Eshetu is a Creative Communicator. She did her BA in Language and Literature and her Masters in Journalism and Communication. She aspires to combine and use various communications means, especially media, which is the global language of this generation, for creative evangelism.

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.