[the_ad_group id=”107″]

የገንዘብ ጣጣ

አሜሪካ፤ ኅዳር 8፣ 1985 (እ.አ.አ)

ለስምንት ዓመታት የወጣቶች መጋቢ በመሆን ሲያገለግል የቆየው የ42 ዓመቱ መጋቢ ኑዛዜ አስደንጋጭ ነበር። መጋቢው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በጉባኤ ፊት ቆሞ “በእግዚአብሔር፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼ፣ በቤተ ሰቦቼና የክርስቶስ አካል በሆነችው ኮሎራዶ በምትገኘው የኢውዛ ባይብል ቤተ ክርስቲያን ፊት ኀጢአትን አድርጌአለሁ” በማለት ተናገረ። ላለፉት ስድስት ዓመታት ከቤተ ክርሰቲያኒቱ የመባ መሰብሰቢያ ዕቃ ውስጥና እርሱ ከሚመራው አገልግሎት ከወጣቶች ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 42,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን በመውሰድ ለራሱ ጥቅም ያውል እንደነበርና ይህንን ወንጀሉን ከትዳር አጋሩም ሰውሮ ያደርግ እንደ ነበር በመግለጽ እራሱን በቤተ ክርሰቲያኒቱ መሪዎች አና በአገሪቱ ሕግ ተጠያቂ ለማድርግ እንደ ወሰነ ተናገረ። በዚህም ምክንያት በማጭበርበርና በስርቆት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ። 

አገር ቤት

ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ምንጯ ከምዕመኖቿ የሚሰጥ ዐሥራት፣ መባና ስጦታ ናቸው፤ ምእመኑም ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው እንደሚሰጥ አያስብም። ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም ለመቀጠል ገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው። ‘ይህን ገንዘብ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እየተጠቀመችበት ነው? ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ነው? ወይንስ የግለ ሰቦች ኪሰ ማደለቢያ ሆኗል? ተቀባይነት ያለው የፋይናንስ ሕግ በምን ያህሉ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ በሥራ ላይ ይውላል?’ እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ለማንሣት ተገቢው ጊዜ አሁን ነው።

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ገንዘብን በተመለከተ “አደገኛ” ሊባሉ የሚችሉ አካሄዶች እየታዩ እንደ ሆነ ይነገራል። በተለያዩ ምክንያቶች ከምዕመናን የሚሰበሰብን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል፣ ተመሳሳይ ደረሰኝ በማሳተም ገንዘብ መሰብሰብ፣ ለተጋባዥ አገልጋዮች የሚከፈለውን የትራንሰፖርት አበል/ስጦታ ቀንሶ መስጠት ወይም ጭራሹኑ አለማድረስ፣ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም አገልግሎት ውስጥ እጅግ የተጋነነ የክፍያ ልዩነት መኖር፣ አገልግሎት ሲጠሩ ʻስንት ትከፍሉናላቹህ?ʼ ብሎ መደራደር፣ የደለበ ዐሥራት ለሚከፍሉ ባለጸጎች በጉባኤ የተለየ ስፍራ መስጠት፣ “እስታቴር ያለውን ዓሣ ማጥመድ” በሚል ብኂል ሀብታሞችን ማሳደድ፣ ወዘተ…. ይህ ሁሉ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚነሡ ነቀፋዎች ናቸው።

ተቋማዊ መዋቅር 

አገልጋዮች ገንዘብን ባለመውደድ መንጋውን ሊጎበኙና ሊያገልግሉ እንደሚገባ የቅዱስ ቃሉ ምክርና ትእዛዝ ነው። በበርካታ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጠር ግጭት ሽፋኑ ሌላ ቢሆንም እውነተኛው ምክንያት ግን በገንዘብና በጥቅም መነሾነት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። በሜክሲኮ አማኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በመጋቢነት የሚያገለግሉት ኤርምያስ ይርጉ “ለአገልጋዮች ትልቁ ነገር ከገንዘብ ፍቅር መራቅ ነው” በማለት “በገንዘብ ያልታመነ አገልጋይ በሌላ ነገር መታመን እንደሚቸግረው” ይናገራሉ። አክለውም “የገንዘብ ፍቅር ከሃይማኖት አስቶ እራስን በስቃይ እስከመውጋት የሚያደርስ እንደ ሆነ” መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ ያደርጋሉ። 

የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው “በሕገ መንግሥት በተደነገገው የሃይማኖት ነጻነት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን የሚያውቃት በሕጋዊ ፈቃድ የምትንቀሳቀስ ተቋም አድርጎ ነው። ስለዚህ ዓመታዊ የሥራና የፋይናንስ ሪፖርት የሚጠበቅ እንደ መሆኑ የገባውና የወጣው ገንዘብ በአግባቡ በሕጋዊ ሠነዶች ተደግፈው ሊቀርቡ ይገባል” ሲሉ የገንዘብ ብክነትና ጉድለት ሲከሰት ገንዘብ ያጎደለው ግለ ሰብ በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ሕጎች ሊጠየቅ እንደሚችል ያስረዳሉ።

ለገንዘብ ብክነትም ሆነ ለሌሎች አስተዳደራዊ እክሎች መነሾ ከሚባሉት መካከል በቂ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት ያለመኖር እንደ ሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። በተለይም፣ የክርስትናን እምነት በንቅናቄ (movement) ደረጃ በማስቀጠልና የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊነት በማደራጀት መካከል ያለው ክፍተት ለዚህ ጉልሕ አስተዋጽኦ ሳያበረክት አልቀረም። ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም በዕቅድ የምትመራ፣ ተቀባይነት ያለው የፋይናንስ ሥርዐት ያላት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራርን የዘረጋችና ምሳሌያዊ ንፅሕናን የተጎናጸፈች ልትሆን ያስፈልጋታል።

አንዳንድ አገልጋዮች “ዐሥራት የአገልጋይ ቀለብ እንጂ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ወጪዎች ሥራ ማስፈጸሚያ አይደለም” ሲሉ ይደመጣሉ። እንዲህ ዐይነቱ አመለካከት ከሞላ ጎደል የሚመነጨው ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ ሕጋዊ ተቋም ያለመመልከት ችግር ነው። በሌላ አባባል “ምድራዊው” አሠራር “ለመንፈሳዊው ይገዛል” የሚል ሃይማኖታዊ ድምፀት ከተጫነው አመለካከት የሚመነጭ ነው። ይህን የመሰለው አመለካከት ሁልጊዜም ከገንዘብ ብክነት ጋር ብቻ ይገናኛል ማለት አይደለም፤ እንደውም ከዛ ባለፈ አስተምህሯዊ አቋሞችና መንፈሳዊ ልምምዶች ላይ ተጠየቅ እንዳይኖርባቸው ሰፊ ክልከላን ያደርጋል።

ተቋማዊ መዋቅርን በተመለከተ ወንጌላዊ ደሉ ጸጋዬ ለሕንጽት ሲናገሩ፣ “አንዳንድ መጋቢዎች የሚያዋቅሩት አመራር (ጠቅላላ ጉባኤና ቦርድ) የግል ትውውቅ ያላቸውና ስሕተት ሲፈጠር ለመጠየቅ አቅም የሌላቸውን ሰዎች በመሆኑ መጋቢው እንደፈለገው እንዲሆን በር ይከፍታል” ይላሉ። የሚያገለግሉት ሕዝብ በከፋ ድኽነት በሚማቅቅበት ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የዋና መጋቢው ደመወዝ ፍጹም የተጋነነ ሲሆን ታይቷል። በርግጥም የተጠናከረ ተቋማዊ አደረጃጀት/ አሠራር በሌለበት ሁኔታ እንዲህ ዐይነቱ ችግር ቢከሰት ሊያስገርም አይችልም።

ተቋማዊ የአደረጃጀት ዕጦት የሚያስከትለው ችግር የገንዘብ ብክነት ብቻ አይደለም፤ የ“ጉልበት ብክነትም” የሳንቲሙ ሌላኛው ገጽታ ነው። “የጉልበት ብዝበዛ” በሚያሰኝ መልኩ ቁጥራቸው የበዙ አገልጋዮች ለበርካታ ዓመታት በአላስፈላጊ ጉስቁልና እና ድኽነት እንዲማቅቁ ሆነዋል። የዚህ ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያን የበጀት አቅሟ አናሳ ስለሆነ ነው የሚለው መልስ ሙሉውን ገጽ አያሳይም፤ ʻየአገልጋይ ዋጋው በሰማይ ነውʼ የሚል ጫፍ ረገጥ አመለካከት ማጠንጠኛው ስለሆነም ጭምር ነው። “ታሽቶሎጂ” ይሉት ፈሊጥ የዚህ አስተሳሰብ ማነፀሪያው ነው። በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት የገንዘብ ሀብት ያላቸው ቤተ ክርስቲያናት “የጉልበት ብዝበዛውን” ከሚያካሄዱት መካከል መሆናቸው በርግጥም የበጀት ዕጦት ላለመሆኑ ማሳያ ነው። ቤተ ክርስቲያንን እንደ ተቋም ማየት ሲቻል፣ የተቋሙን ሠራተኛ (የአገልጋዩን) ጥቅምና መብት ማስከበር እንደ ዳገት የከበደ አይሆንም። ምን ያህሉ ቤተ ክርስቲያናት የአገሪቱን የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ያገናዘበ የሰው ኀይል አስተዳደር ይከተሉ ይሆን?

የፖስታዋ ነገር

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አገልጋይ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በፖስታ የተሰጠው ገንዘብ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለትራንስፖርት ብላ ከምትሰጠው እጅጉን አንሶ እንዳገኘው ለሕንጸት ተናግሯል። አገልጋዩ እንደሚለው ከሆነ ነገሩ በስሐተት የተፈጠረ እንዳልነበር ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ለማወቅ ችሏል።

ከፖስታ ገንዘብ ከመቀነስ በከፋ ጭራሹኑ ባዶ ፖስታ የተሰጣቸው አገልጋዮችም እንዳሉ ይወራል። በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ጂማ ዲልቦ እንደሚሉት፣ “እንዲህ ዐይነት ሰው በወንጀል ሕግ መሠረት በማታለል ወይም እምነት በማጉደል ሊጠየቅ እንደሚችል” ይጠቁማሉ። የተጠቀሰውን ዐይነት ችግር ለመከላከል በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ከጉባኤ በኋላ መሪዎች ያገለገለውን ሰው ቢሮ ድረስ ጠርተው ከጸልዩና ከባረኩ በኋላ የትራንስፖርት ገንዘቡ በግልጽ ተሰጥቶት በተዘጋጀው ሠነድ ላይ እንዲፈርም ይደረጋል። ለመጋቢ ኤርምያስ ይርጉ ግን ይህ አሠራር ብዙ ምቾት አይሰጣቸውም፤ “ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ብትሆንም የእምነት ስፍራ እንደ መሆኗ መጠን ሁሉም ነገር በሕግ ይመራ ማለት አስቸጋሪ” ሊሆን እንደሚችል ያሰምሩበታል። “አንዳንድ በዕድሜና በልምድ ትልቅ የሆኑ ሰዎችን ቢሮ ጠርቶ እዚህ ላይ ፈርሙና ገንዘብ ውሰዱ” ማለት ከአክብሮት አንጻር እንደሚከብድም ያስረዳሉ። አክለውም “ገንዘብ የሚያጎድሉ አገልጋዮች ካሉ ሌብነታቸው እንደ ይሁዳ እስኪገልጣቸው መተው እንጂ በስንቱ ተቆጣጥሮ ይዘለቃል?” በማለትም ይጠይቃሉ።

የአገልጋይ ደምወዙ ስንት ነው?

አገልገዮች እንደ ማንኛውም ሰው ፍላጎት ያላቸው እንጂ ልዩ ፍጥረት ተደርገው መታየት አይገባቸውም። ለበርካታ ዓመታት የአገልጋዮች ቤት የሰቆቃና የመከራ ሲሆን፣ ልጀቻቸውም ደኻ አደጎች የሆኑባቸው ናቸው። በአንጻሩ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አገልጋዮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለጠጎች ሲሆኑ እየታየ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን መክፈትም እጅግ አትራፊና በአቋራጭ መክበሪያ መንገድ እንደ ሆነ መታሰብ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ታዲያ ሚዛኑ የቱ ጋ ነው?

“የአገልጋይ ክፍያ ምን ያህል መሆን አለበት የሚለው አከራካሪ ጉዳይ መሆን የለበትም፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ አቅሟና እንደ ሁኔታው ልትከፍል ይገባል” የሚሉት ወ/ዊ ደሉ ጸጋዬ ናቸው። እንደ መንግሥት መዋቅር ይህንን ያህል መሆን አለበት ማለት እንደሚከብድ የሚያስረዱት ወ/ዊ ደሉ፣ የአገልጋዮች ደሞዝ እንደ አካባቢው ሁኔታ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ገቢ እንዲሁም እንደ አገልጋዩ ኀላፊነትና የአገልግሎት ዘመን ቆይታ ሊሆን እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

“በመጽሐፍ ቅዱስ ʻእጥፍ ክብር ይገባቸዋልʼ የተባለላቸው ሌሎች ሳይሆኑ አገልጋዮች ናቸው” የሚሉት ደግሞ መጋቢ ኤርምያስ ይርጉ ናቸው። “አገልጋዮችን ቤተ ክርስቲያን ከምታከብርባቸው መንገዶች አንዱ ለኑሯቸው የሚገባውን በማድረግ፣ የሚባቸውንም በመክፈል ነው” ይላሉ መጋቢው። “በርግጥ እነርሱ ስለ ነፍሳችን ይተጋሉና ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ልትተጋ ይገባል።” 

ወንጌላዊ ደሉም “አገልጋዮች ተቸግረው የሰው እጅ እስኪያዩና ለልመና ወይም ለማጭበርበር እስኪጋለጡ መድረስ የለባቸውም” ባይ ናቸው። ወንጌላዊው ይህንን ችግር ለመቅረፍም “ቤተር ላይፍ ሚኒስትሪ” የተሰኘ መንፈሳዊ ተቋም መሥርተው ለችግር የተጋለጡ አገልጋዮችንና ቤተ ሰባቸውን በገንዘብ እየደገፉ እንደ ሆነ ነው ለሕንጸት የገለጹት። 

“አገልገዮች ከሚያገለግሉት ሕዝብ የራቀ ሕይወት ሊኖራቸው አይገባም። ሐዋርያት ያላቸውንና ሕዝቡ ያመጣውን ለእያንዳንዱ እንደሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉ ነበር” የሚሉት መጋቢ ኤርምያስ ናቸው። እንደ መጋቢው ከሆነ አንድ አገልጋይ “ቃሉን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱንም፣ ገንዘቡንም ማካፈል” እንደሚገባው አጽንዖት ይሰጣሉል። አያይዘውም፣ “አገልጋዮች ለተጠሩለት ወንጌል በመጠን እየኖሩ ሊያገለግሉ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ʻበመጠን ኑሩ፣ ንቁም፤ ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ዙሪያችሁን ይዞራልʼ ነው” ሲሉ ምክር አዘል መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ። 

በአደባባይ ወጥቶ ʻየተሰጠኝን እምነት በማጉደል እግዚአብሔርን፣ ቤተ ሰቤንና ምእመናንን በድያለሁʼ የሚል “ጀግና” እስኪገኝ ድረስ፣ ዝርፊያው እንዲቆም ጉስቁልናውም እንዲቀር ወደ ላይም ወደ ጎንም መጮኹ ሳይበጅ አይቀርም።

” ‘መንፈስ ቅዱስ ካልተናገረ እኔ የምነግራችሁ አንዳች የለም’ ብሎ ጉባኤውን ማሰናበት ጤናማነት ነው”

መጋቢ መስፍን ሙሉጌታ በኮልፌ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በመጋቢነት ያገለግላሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ዘወትር ዓርብ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታዘጋጀው “የፈውስና ነጻ የማውጣት” መርሓ ግብር ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህ ዘመን በፈውስ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ያገልግላሉ ከሚባሉት አገልጋዮች መካከል የመጋቢ መስፍን ስም ቀድሞ ይነሣል። ሕንጸት ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ስጦታዎቹ እና አጠቃቀሙ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው ስለሚነሡ ጉዳዮች ከመጋቢ መስፍን ሙሉጌታ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.